ፍትሕና ምሕረት
በሰለሞን ከበደ

ፍትሕ በኃይል ወይም በሥልጣን አጠቃቀም ላይ ያተኩራል። ፍትሕ ትክክለኛ የኃይል ወይም የሥልጣን አጠቃቀም ነው። ኃይል ወይም ሥልጣን በአግባቡ ሥራ ላይ ሳይውል ሲቀር ፍትሕ ይዛባል፣ ይጓደላል።

የመጨረሻው ኃያልና ባለ ሥልጣን እግዚአብሔር አምላክ ነው። እርሱ ጽድቅና ፍትሕ ባሕርዩ የሆነ አምላክ እንደ ሆነ ቃሉ ይነግረናል። 

ጽድቅና ፍትሕ የዙፋንህ መሠረቶች ናቸው፤ ምሕረትና ታማኝነት በፊትህ ይሄዳሉ። መዝሙር 89፡ 14

ፍትሕን የምትወድ ኃያል ንጉሥ ሆይ፣ አንተ ትክክለኛነትን መሠረትህ፣ ፍትሕንና ቅንነትንም ለያዕቆብ አደረግህ። መዝሙር 99፡ 4

እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፣ ‘እውነተኛ ፍትሕ አስፍኑ፣ እርስ በርሳችሁ ምሕረትና ርኅራኄን አድርጉ፤ መበለቲቱን ወይም ድኻ አደጉን አታስጨንቁ፤ በልባችሁም አንዳችሁ በአንዳችሁ ላይ ክፉ አታስቡ። ዘካርያስ 7፡ 9-10

ሰው ሆይ፣ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን? ሚክያስ 6፡ 8

እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነው። ፍትሕ ከእርሱ ባሕርይ የሚመነጭ ነው። በብሉይ ኪዳን ስንመለከት ጽድቅና ፍትሕ ብዙውን ጊዜ ተያይዘው በጥንድ ይቀርባሉ፤ ጽድቅ የውስጥን ሁኔታ ሲያመለክት፣ ፍትሕ ደግሞ ጽድቅን በተግባር የመግለጽ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ሆኖ ይታያል። ጽድቅና ፍትሕ ተወራራሽነት አላቸው። ሁለቱም እግዚአብሔር ከሰጠው ሞራላዊ መለኪያ ጋር በልብ በተግባርም ተጣጥሞ መገኘት ነው። ጽድቅ የልብ ወይም የውስጥ ሁኔታን ሲያመለክት፣ ፍትሕ ድርጊትን ያሳያል።

ፍትሕ በምድር ላይ የሚሰፍነው በሰዎች መካከል ኃይልና ሥልጣን በአግባቡ ማለትም የእግዚአብሔርን መመሪያ በጠበቀ መልኩ ሥራ ላይ ሲያውሉ ነው። ምን ጊዜም ኃይልና ሥልጣን በኅብረተ ሰብ መካከል በእያንዳንዱ ግለ ሰብ ላይ ተሠራጭተው ይገኛሉ። የሥርጭት መጠናቸውም ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። በሰዎች መካከል ልዩ ልዩ ኃይሎች አሉ፤ ለምሳሌ ያህል የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበረዊ፣ ግብረ ገባዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ቤተ ሰባዊ፣ የጉልበትና የአእምሮ ብሎ መጠቃቀስ ይቻላል።

የፖለቲካ ተመራጭ ፖለቲካው በሚፈቅድለት መጠን ኃይልን ሥራ ላይ ያውላል፤ ሥልጣንን ይጠቀማል። የገንዘብ ክምችት ያላቸው ሰዎች በኢኮኖሚው መስተጋብር ወይም እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፤ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖአቸው ያይላል። በሃይማኖት አካባቢ በቄሱ ወይም በመጋቢው ወይም በነቢዩ ሌሎችን አማንያንን የሚያንቀሳቅስ በመፍታትና በማሰር ወይም በመመረቅና በመርገም አንዳንዴ ሊያስገብር የሚችል ኃይል ነው፤ በማኅበረ ሰብ ውስጥ ተወዳጅነትም ኃይል ነው። በዕድሜ፣ በትምህርት፣ በሙያ ወዘተ አኳያ እንደየባህሉ ከተደማጭነት ጋር የተያያዘ ኃይልም ተሠራጭቷል።

እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነው ካልን እነዚህ ኃይሎች በትክክል ተግባር ላይ ሳይውሉ ቢቀር ይገደዋል ማለታችን ነው። ፍትሕ ተዛባ ስንል የሌሎችን ሕይወት፣ ክብር፣ ጾታዊ ፈቃድ፣ ነጻነት፣ ጉልበት፣ ሥራ፣ ገንዘብ፣ ንብረት፣ ጥቅም ለመንፈግ ወይም ለመንጠቅ ኃይል ወይም ሥልጣን በአሉታዊ መልኩ ሥራ ላይ ውሎአል ማለት ነው።

ኃያሉ ወይም ብርቱው ኃይልና ማታለልን ተጠቅሞ ደካማውን ሲገፋ ወይም ሲመዘብር ፍትሕ ተዛብቷል፤ ተጓድሏል፣ ግፍ ተፈጽሟል። ወንድ ሴትን ሲረግጥ ወይም ሴት በወንድ ላይ ስትብለጠለጥ ወይም ስታተርፍ፣ ብርቱው ደካማውን ሲቦጠቡጥ፣ ከበርቴው ደኻውን ሲበዘብዝ ግፍ ነው። የፍትሕ እንቅስቃሴ ቢኖርም ዓለማችን በአብዛኛው በግፍ የተሞላች ናት። በዓለም ዙሪያ በየጊዜውና በየቦታው ግፍ ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ የመብት ረገጣ ተንሰራፍቶ ይታያል፤ ብዙ የተገፉ ሰዎች እንባ ይፈሳል። ምድር በብዙ ሥፍራ በግፍ ጩኸት ተከድናለች፤ በአታላዮችና በሸፋጮች ተሸብራለች። ይህ ጩኸት ትናንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ነው።

ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቶአል። ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፤ ፍትሕ ድል አይነሣም፤ ፍትሕ ይጣመም ዘንድ ክፉዎች ጻድቃንን ይከባሉ። ዕንባቆም 1፡ 3-4

ነቢዩ ሚክያስም እንዲህ ይላል፣ 

ከዚያም እኔ እንዲህ አልኩ፣ “እናንት የያዕቆብ መሪዎች፣ እናንት የእስራኤል ቤት ገዦች ስሙ፤ ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን? መልካሙን ጠላችሁ፤ ክፉውንም ወደዳችሁ፤ የሕዝቤን ቆዳ ገፈፋችሁ፣ ዐጥንቶቻቸውንም ሰባበራችሁ፣ በመጥበሻ እንደሚጠበስ፣ በድስት እንደሚቀቀል ሥጋ ቆራረጣችኋቸው። ሚክያስ 3፡ 1-3 

ሹሙ፣ ባለ ሥልጣኑ፣ ከበርቴው፣ መለዮ ለባሹ፣ ወንበዴው፣ ምሁሩ፣ ቄሱ፣ ነቢዩ በትምክሕተኝነት ይመላለሳሉ፤ ፍትሕ ያጓድላሉ። የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላል፣

የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፣ ምድሪቱን ‘አንቺ ያልነጻሽ በቁጣም ቀን ዝናብ ያላገኘሽ ምድር ነሽ’ በላት። መሳፍንቷ እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበድላሉ፤ ንብረቱንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለቶች ያደርጋሉ። ካህናቷ በሕጌ ላይ ያምፃሉ። ንዋያተ ቅድሳቴን ያረክሳሉ፤ የተቀደሰውን ከረከሰው አይለዩም፤ በጎደፈውና በንጹሑ መካከል ልዩነት እንደሌለ ያስተማራሉ፤ ሰንበታቴን ከማክበር ዘወር ብለዋል፤ በዚህም በመካከላቸው ተንቄአለሁ። በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኩላዎች ናቸው። በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ። ነቢያቷም በሐሰት ራእይና በውሸት ሟርት ይህን ሁሉ ድርጊት ያድበሰብሱላቸዋል፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ። በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ ይቀማል፤ ይዘርፋል፤ ፍትሕ በማጉደልም ድኻውንና ችግረኛውን ይጨቁናል፤ መጻተኛውንም ይበድላል። ሕዝቅኤል 22፡ 22-29

ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቁኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። ሚልክያስ 3፡ 5

እናንት ፍትሕን ወደ መራርነት የምትለውጡ፣ ጽድቅንም ወደ ምድር የምትጥሉ ወዮላችሁ! እናንተ በፍርድ አደባባይ የሚገሥጻችሁን ትጠላላችሁ፣ እውነት የሚናገረውንም ትንቃላችሁ። እናንተ ድኻውን ትረግጣላችሁ፣ እህል እንዲሰጣችሁም ታስገድዱታላችሁ፤ ስለዚህ በተጠረበ ድንጋይ ቤት ብትሠሩም፣ በውስጡ ግን አትኖሩም፤ ባማሩ የወይን ተክል ቦታዎች ወይን ብትተክሉም፣ የወይን ጠጁን ግን አትጠጡም፤ ኃጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደ ሆነ፣ በደላችሁም የቱን ያህል እንደ በዛ እኔ አውቃለሁና። ጻድቁን ትጨቁናላችሁ፣ ጉቦም ትቀበላላችሁ፣ በፍርድ አደባባይም ከድኻው ፍትሕ ትነጥቃላችሁ። ክፉውን ጥሉ፣ መልካሙንም ውደዱ፤ በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤ ምናልባትም የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።

የፍትሕን መጓደል በአምልኮአዊ ሥርዓት፣ በዝማሬ ለመሸፈን የሚደረገውን የሕዝቡን ጥረት እግዚአብሔር አይቀበለውም።

የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ አርቅ፤ የበገናህንም ዜማ እኔ አልሰማም። ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ። አሞጽ 5፡7፣ 10-12፣15፣23-24

ምሕረት

የእግዚአብሔር ቃል ስለ ጽድቅና ፍትሕ ብቻ የሚናገር አይደለም። ከዚያም አልፎ ስለ ምሕረትና ስለ ምሕረት አስፈላጊነት ይናገራል። ምሕረት እንደ ተደረገላቸው ሰዎች ምሕረት ማድረግን እንድንለማመድ ያስገነዝበናል።

መቼም ፍትሕ ለሚያስገኝልን ጠቀሜታ ምሕረት አያሻንም። ምሕረት የእኛ ጽድቅ ወይም ፍትሕ ያላደረሰንን ደረጃ የሚያደርሰን በጎነት ነው።

ለምሳሌ፦ ሕግን በመተላለፍ የ 20 ዓመት እሥራት የተፈረደበት ሰው እሥራቱ ወደ 8 ዓመት ዝቅ ቢደረግለት የ 12 ዓመት እሥራት ምሕረት ተደረገለት ማለት ነው። ይህን የ 12 ዓመት እሥራት መቀነስ ፍትሕ ሊያስገኝለት ከቶ አይችልም፤ እንዲያውም ፍትሕ የ 20 ዓመት እሥራቱ እንዲጸና ግድ የሚል ነው እንጂ።


በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ መጽደቅ፣ ከኩነኔ ማምለጥ፣ የዘላለም ሕይወት ወራሽ መሆን የፍትሕ አድራጎት ሳይሆን የእግዚአብሔር የምሕረት አድራጎት ነው። ስለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 2፡ 3 ላይ፣ “… ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል” የሚለው።

‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሐን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። ማቴዎስ 12፡ 7 

ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እሻለሁና። ሆሴዕ 6፡ 6

በጽድቅ ለመኖር ፍትሕን ለማድረግ ተጠርተናል። ይህ በሰዎች መካከል ሰላምን ያሰፍናልና። ሁከት አምባጓሮ ፍርሃትና ስጋት ይገታሉ።

ይሁን እንጂ ከፍትሕ ስንጎድል ስናጓድልና ከዚያም የተነሣ በችግር፣ በጉድለት፣ በክስረት ውስጥ ወድቀን እንዳንቀር የምሕረትን መንገድ መጓዝ ያሻናል። አዲስ ኪዳንም ምሕረትን መደምደሚያ አድርጎ አቅርቦልናል።

ምሕረት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዓይነተኛ ቃል ትልቅ ሥፍራ ያለው ቃል ነው።

ምሕረትን ለመረዳት ከመሞከራችን በፊት ግን ስለ ርኅራኄ ማንሳት አስፈላጊ ነው።

 

ይቀጥላል…

 

የውይይት ጥያቄዎች

 

1.  ፍትሕና ምሕረት ልዩነታቸው ምንድነው?

2.  ፍትሕ የእግዚአብሔር ባሕርይ ነው ካልን ፍትሕ በጠፋበት ዓለም ክርስቲያኖች ድርሻቸው ምን ሊሆን ይገባል? ድርሻቸውን እንዴት ሊወጡ ይችላሉ?

3.  ምሕረት በማድረጉ የሚያስታውሱት ሰው አለ? እርስዎስ ምሕረት ያደርጋሉ?

4.  ጽድቅ ምንድነው? ከፍትሕ ጋር እንዴት ይዛመዳል?

 

አቶ ሰለሞን ከበደ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሲሆኑ፣ ይህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ካቀረቡት የመክፈቻ ንግግርና ኋላም “ፍትሕና ምሕረት” በሚል ርእስ በ 1999 ዓ.ም. ካሳተሙት መጽሐፍ በከፊል የተወሰደ ነው።

  

 

 

 

 

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org