በምትኩ አዲሱ

ዝም የማትለው እስከ መቸ ነው?

 

           

 

 

በንዲህ እንዳለ …

 

አንዲት አረንጓዴ ብረት-ለበስ መኪና እየበረረች መጥታ ከቆምኩበት ከምኒሊክ ቤተ መንግሥት መጠምዘዣ ላይ ስትደርስ ዝግ ማለት ጀመረች፤

ይኸኔ የታጎሩ ወጣቶች ድምፅና ድምድምታ፤ … ለእርድ እንደ ቀረበ እንስሣ ቃል-አልባ ተጨናንቆ ሲንፈራገጥ ሰማሁ…

“እናቴ! እናቴ!” ይሆን?

“አምላኬ! አምላኬ!” ይሆን?

ገና ከመድረሳቸው ወደ ሸለቆ እንደሚወርድ መንጋ እየተጣደፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ቁልቁለት ወረዱ፣… ርቀውም ከዐይኔ ፊት ተሰወሩ፤

ወዲያው ቀጥሎ የተኩስ እሩምታ ተሰማ …

ተኩሱ አንዴ እንደ ማሽላ ይንጣጣል … ቆይቶ ደግሞ እንደ ጋለሞታ ያሽካካል …

ምን እየተካሄደ መገመት ባያዳግትም፣ ማን በማን ላይ ምን እያካሄደ እንዳ-ለ ግን መለየት እጅግ አቅቷል፤

ከዚህስ በኋላ ወዴት ይሆን የሚዛመተው?

በንዲህ እንዳ-ለ፣ ምሽቱ ሁሉንም ዋጣቸው፤… የአጋንንት መፈንጫ ሰዓቱ ደረሰ ማለት ነው…

አሁን የሚያስፈልገው ጎሕ እስኪቀድ አጥብቆ መጸለይ ነው ብዬ ራሴን አበረታሁ። ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል?

 

እና … እባክህ አታቋርጠኝ፤ አንዴ አስጨርሰኝ …

ቅድም እንዳልኩህ … ምን ጊዜም ቢሆን፣

ሰው በሰው ነው

ሰው ለሰው ነው

ሰውና ሰው ነው…

ይኸውልህ፣ ለስንት ትውልድ የሚተርፍ መከራ በአንድ ዕለት ተጠናቀቀ… ለልማት እንዲህ ቢቸኩል የት በደረስን …

ፈቅደህ ከሰማኸኝ

ምክሬን ተቀበለኝ፣

     ሙታንህን አስባቸው

በክብር ቅበራቸው

     ለቋሚው ተጠንቀቅ

ለራስህም ፍራ

     ፊትና እጅህን

ራስህን እግርህን

አፍና ጆሮህን

ኩታህን ጭምር

አንፃ

     ለአመዳምነትህ

የወይራ ዘይት ተቀባ …

     ወደ ደጀ ሰላም ገሥግሥ …

በሩጫ ላይ እያለህ

እንደ ነቢዩ …

 

     “አንተ የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፣

     ዝም የማትለው እስከ መቸ ነው?

     ወደ ሰገባህ ግባ

     ጸጥ ብለህም ዕረፍ” … በል…

 

ቀይና ነጭ ሽብር (1969)

 

 

ETHIOPIANCHURCH.ORG

Copyright © 1993 by Mitiku Adisu

All rights reserved

  

 

 

 

 

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org