ርዕሰ አንቀጽ
ሳንተዋወቅ እንቻቻል ማለት ትርፉ ድካም ነው
የሃይማኖቶች መብዛት ሰዎች የፈጠሩት ጣጣ እንጂ እግዚአብሔር የሠራው እንዳልሆነ ተደጋግሞ ይነገራል። ከዚህም የተነሣ “ሃይማኖቶች አንድ ናቸው” ለማሰኘት የተለመዱ አባባሎችን እንሰማለን፦
“አንደኛው አላህ ቢል
“ሌላኛው እግዚሐር ቢል
“ይኸኛው ዋቃ ቢል፣ ስም እንጂ የለየው ፈጣሪ እንደሆነ ያው አንድ ነው”
ወይም
“ማክረር አያስፈልግም፤ ሁሉን በልክ ማድረግ ነው … መቻቻል መፋቀር ነው የሚያስፈልግ”
ወይም
“ችግሩ ያለው ሰው ዘንድ ነው። እግዚአብሔርማ እርዱኝ እረዳችኋለሁ ነው ያለው …” ይላል።
መሠረታዊ ልዩነቶች እንዳሉም መጠቆም ሰላምን አለመፈለግና አክራሪነት እንደ ሆነ ይታሰባል፤ የአለመሠልጠንና የድንቁርና ምልክት ነው ይባላል።
ሰዎችን ላለማስቀየም ልዩነቶችን ችላ ማለትና ከጊዜው ጋር መራመድ ይመረጣል። የሚፈለገው በጭፍኑ “አንድ ነን” ማለቱ ነው። አንድነቱ የሚፈለገው ልዩ ልዩ መሆንን ለመካድ ከሆነ ግን የሚፈጥረው የውሸት አንድነትን ነው።
እንቻቻል ሲል፣ ያለመቻቻሉ መንስዔ ምን እንደ ሆነ አብሮ አይገለጽም። “አክራሪ” ወይም “በልክ” ሲል የተናጋሪው ማንነትና ምክንያቱ አይጣራም።
ሁሉም “መብቴን” ባለበት በዚህ ዘመን እነዚህን መሰል ቃላት ጐልተዋል። የምንሰማውና የምናየው ችግር ግን መሠረቱ የመብት ሳይሆን የአለመተዋወቅ ጉዳይ ነው።
ድብቅነት ተመርጧል፤ ከዚህም የተነሣ ሰው ሁለት ገጽታ ይዞ ለመጓዝ ተገድዷል። አንደኛው ገጽታ እንጀራና ተቀባይነት ላለማጣት የሚደረገው ጥረት ነው። ሌላኛው ገጽታ በጉያ ደብቆ የያዘው እውነተኛ እምነቱ ነው። በጉያስ እስከመቸ ይዞ ይዘልቃል? መቸና በምን ሁኔታ ያ ድብቅነት ይፋ እንደሚወጣ አይታወቅምና ውሎ ሲያድር አለመተማመንና ጥርጣሬን ማራባቱ አይቀርም።
የተለያዩ እምነቶችን ለማስማማት የሚሯሯጡ አንዳንዴ ከየትኛውም የእምነት ወገን ያልሆኑ ናቸው። ከደጅ ቆመው ስላልተረዱት ጉዳይ ለመናገር የማያፍሩ ናቸው። በማስማማቱ ሰበብ የራሳቸውን ዓላማ የሚያራምዱ ናቸው። ከየትኛውም ወገን አለመሆናቸውን እንደ ኒሻን እያገላበጡ ያሳያሉ። “አድልዖ አያሳዩም፣ ሚዛናዊነትን ተጐናጽፈዋል” እንዲባልላቸው ይሻሉ።
ዳኝነታቸው ግን ገና ከምጣዱ ያስታውቃል። ሁለቱንም ወገን አያጠግብም። ባለ ጉዳዩንና ተመልካቹን ግራ ያጋባል። ልኩን ከማስካድ አይመለስም። እስከነአንካቴውም፦ “ሁሉም ይቀላቀል” ማለት ይቃጣዋል።
ደጋግመው “አንድ ነን፣ አንድ ነን” ሲሉ አለመግባባት ተፈጥሮ የማያውቅ ያስመስላሉ።
አለመተዋወቅ ወደ አለመቻቻል፣ ወደ አሉባልታና ወደ ጥላቻ ያመራል። ነገር ከተበላሸ በኋላ ማቃናት ደግሞ አዳጋች ይሆናል። ቢቻልም እንኳ ብዙ ትዕግስትና ጥንቃቄ ይጠይቃል። ስንቱስ ሰው ነው ይህን ለማድረግ ጊዜና ጉልበት የሚያገኘው? አብዛኛው ሰው ነገርን ከሥሩ ከማጣራት ይልቅ እንደ ሰነፍ ተማሪ ያልተረዳውን መቅዳት ይቀናዋል።
የገዛ ራስን እምነት እንደሚገባ አለማወቅ ሌላኛው ችግር ነው። እንደሚገባ የሚያስረዱና የሚያስተምሩ መምህራንና መሪዎችን ማጣት። መምህራኑን፦ “ቃሉና ሥርዓቱ እንዲህ ይል የለ?” ብሎ ለመጠየቅ አለመብቃት። የተረዱትን እውነት ለሌላው ማስረዳት አለመቻል። “እኔ እንዳልኩት ካልሆነ ምን ተደርጎ?” የሚል ግትርነት። ችግሩ ባጭሩ አለመከባበር ነው።
ፈጣሪም እንደሚያይ መዘንጋት። ልዩ ልዩ ሆኖ አብሮ ለመኖር አለመፍቀድ። ሰውን አለመውደድ። ራስን ብቻ መውደድ፣ የራስን ጥቅም ብቻ ማሳደድ ነው። ሰውን የሚወድድና የሚያከብር ራሱንም በዚያው ውስጥ መውደድና ማክበር ይለማመዳል። ሰውን ከነእንከኑ መውደድ ይለምዳል፤ እራሱም እንከን እንዳለበት ይገነዘባል። ርኅራኄ ያሳያል።
ልጅን እንኳ ሲወዱ እስከነንፍጡ ነው።
አለመቻቻል በተጨማሪ፣ የሰውን መሠረታዊ ባሕርይ የመዘንጋት ውጤት ነው። ሥልጣኔ ያባባሰውን የሰውን ልጅ የጭካኔ ታሪክ አለማጤን ነው። ታሪክን የሚዘነጉ፣ ሁሉ ሁሌ እንግዳ እንደሆነባቸው ይኖራሉ። ትንሹን ያጋንናሉ፤ መዓት እንደ መጣ ያስመስላሉ። ተደናብረው ያደናብራሉ።
በመጨረሻም፣ አለመቻቻል የሚፈጠረው የተለመደውን ባልተለመደ አሠራር ወዲያው ለመተካት ከመፈለግ ነው። የአገሬውን ባሕልና አስተሳሰብ ማናጋቱን፣ ሌላውን ሰው ስጋት ላይ መጣሉን ካለማስተዋል ነው።
ለመቻቻል ቀርቦ መተዋወቅ ግድ ያስፈልጋል። ከርቀት ሆኖ መነጋገር ትርፉ መጯጯህ ነው። አንዴ ብቻ ሳይሆን ጊዜውና ሁኔታው በሚጠይቀው መሠረት ደግሞ ደጋግሞ መነጋገር ያሻል። አንደኛው የሌላኛውን አላማ አቋምና ጥያቄ እንዳያዛባ መጠንቀቅ፣ መታገስ ያሻል። የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን ደግሞ ማሰብ ይጠቅማል። ያንድ ቀን ስሕተት የዘላለም ፀፀት እንዳይሆን ማለት ነው።
ሳንተዋወቅ እንዴት እንቻቻል? ሳንተማመን ምን እንወያይ? ሳንወያይ እንዴት እንተዋወቅ፣ እንዴት እንተማመን? ሳንቀራረብስ እንዴት እንወያይ? እስከ መቸስ በአፈ ቀላጤና በ”ቱርጁማን” እንኑር?
ብንተዋወቅ እምነታችን በሚያስተምረን መሠረት ለመኖርና ለመማማር በጣርን። አለመቻቻልን በመቻቻል በሻርን።
እንግዲያስ አንድነት መልካም ነው፤ ልዩ ልዩ መሆንም መልካም ነው። መተዋወቅ፣ መቀባበልና መከባበር ግን ይመረጣል።

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org