ፍትሕና ምሕረት
ክፍል ሁለት
ርኅራኄ
ርኅራኄ የሌላኛውን
ሰው ሥቃይ ወይም ችግር መጋራት ማለት ነው። በእስር ወይም በጭንቅ ውስጥ እንዳለው ሰው ሆኖ ራስን ማሰብ ነው።
(ዕብራውያን 13፡3)
ርኅራኄ ከተጎዳው ጋር
በልብ በሐሳብና በስሜት ችግርን መጋራት ሲሆን ምሕረት ደግሞ በሐሳብና በስሜት ከመጋራት አልፎ የጉዳተኛውን ሁኔታ በበጎ
ለመቀየር የሚወሰድ ተግባራዊ እርምጃ ነው። ይህም ዋጋን መክፈል ወይም መሥዋዕትነትን ግድ ይላል።
ግድ የለሽነት፣ ደንታ
ቢስነት፣ ምንተዳዬ ባይነት የርኅራኄ ተቃራኒ ሲሆኑ በቀል፣ ቅጣት፣ ውግዣ ደግሞ የምሕረት ተቃራኒ ናቸው።
ምሕረት፦ ሐዘኔታ፣
በጎነት፣ ርኅራኄ ከአንዱ ወደ ሌላው፣ መብቱ ወዳልሆነው፣ እንደ ብድር ምላሽ ወደማይጠየቅበት ጉዳተኛ ወይም ለመመለስ
ወደማይበቃ ጉዳተኛ ጉዳቱን ለማስወገድ የሚዘረጋ የሚሰነዘር መልካምነት ነው።
እግዚአብሔር የርኅራኄ
አባት ነው። የእግዚአብሔር ወገኖች የርኅራኄ ሰዎች ሊሆኑ ይገባል።
ወደ ተጎሳቆሉት
መቅረብና ሁኔታዎቻቸውን ማየት መመልከት ርኅራኄን ይቀሰቅሳል፤ የምሕረት እርምጃ እንድንወስድ ያዘጋጀናል።
ጌታ ኢየሱስም ወደ
ሕዝቡ ወጥቶ ሁኔታቸውን ባየ ጊዜ እንዳዘነላቸው፣ እንደራራላቸው የምሕረትንም አገልግሎት እንደ ፈጸመ በወንጌሎች ውስጥ
እናነባለን፤
ሕዝቡም እረኛ
እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው። ማቴዎስ 9፡ 36
እግዚአብሔር
የመጽናናት አባትና የርኅራኄ ሁሉ አምላክ ነው። እግዚአብሔር ለተገፉ፣ ለድኾች ራራ ሲባል መገፋታቸውን ተጋራ፣ ችግራቸውን
አየ፣ ተሰማው፣ ገደደው ማለት ነው።
ከዚያም እግዚአብሔር
እንዲህ አለ፦ በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትን ጩኸት
ሰምቻለሁ፣ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ… ልታደጋቸውና … ላወጣቸው ወርጃለሁ። ዘጸአት 3፡ 7-8
ፍትሕንና ምሕረትን
እንዳናደባልቅ መጠንቀቅ ያስፈልገናል
ምሕረት በፍትሕ ላይ
ያይላል እንጂ ፍትሕ ምሕረት እንዳናደርግ አያስገድደንም፤ ለምሳሌ ያህል በማቴዎስ 20፡ 1-15 የተጠቀሰውን የአትክልት
ቦታ ባለቤትና ሠራተኞች ጉዳይ እንመልከት፤ በማለዳ በቀን አንድ ዲናር ሊከፍላቸው ከተስማሙ በኋላ ሠራተኞችን በወይኑ ቦታ
አሰማራቸው፤ ኋላም ከቀኑ ሦስት ሰዓት ላይ፣ ስድስት ሰዓት ላይ፣ ዘጠኝ ሰዓት ላይና አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ሥራ ፈትተው
የነበሩ የቀን ሠራተኞችን ጠርቶ አሰማራቸው።
በቀኑ መጨረሻም
በአሥራ አንደኛው ሰዓት ከተቀጠሩት ሠራተኞች ተነሥቶ ከፈለ። በአሥራ አንደኛው ሰዓት ለመጡት አንድ ዲናር ከፈላቸው፤
በማለዳ በሥራው ላይ የተሠማሩት በዚህ ሁኔታ እኛ የበለጠ ይከፈለናል የሚል ግምት ቢይዙም ለእነርሱም በመጀመሪያው ውለታ
መሠረት ለእያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተከፈላቸው።
እነርሱም “እነዚህ
በመጨረሻ የተቀበሉት አንድ ሰዓት ብቻ ሲሠሩ፣ ቀኑን ሙሉ ስንደክምና በፀሐይ ስንንቃቃ ከዋልነው ጋር እንዴት እኩል
ትከፍለናለህ?” በማለት በባለቤቱ ላይ አጉረመረሙ።
ባለቤቱም አንደኛውን
ሠራተኛ እንዲህ አለው “ወዳጄ ሆይ በደል አላደረስሁብህም፤ በአንድ ዲናር ለመሥራት ከእኔ ጋር ተስማምተህ አልነበረምን?
በል ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያህል በመጨረሻ ለመጣውም ሰው መስጠት እፈልጋለሁ። ታዲያ በራሴ ገንዘብ
የፈለግሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ ቸር በመሆኔ ምቀኝነት ያዘህን?”
ባለቤቱ አንድ አንድ
ዲናር በማለዳ ለተቀጠሩት መክፈሉ ፍትሐዊ ነው። በአሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ለተቀጠሩት ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ዲናር
መስጠቱ፣ ከአንድ ዲናር ያነሰ አለመስጠቱ ከፍትሕ አልፎ የሄደ የምሕረት አድራጎት የቸርነት ሥራ ነው።
በዚህ ምሳሌ ውስጥ
የምንገነዘበው ወይም የምንማረው ፍትሕ አይጓደል እንጂ አልፈን ተርፈን ምሕረት እንዳናደርግ ፍትሕ የማይከላከል መሆኑን
ነው።
የእግዚአብሔር ፍትሕ
ለሁሉም ነው
የእግዚአብሔር ርኅራኄ
ፍትሕ ለተጓደለባቸው፣ ለተጎሳቆሉ፣ በምድር ላይ ለተጨቆኑ ሁሉ እንጂ ለኪዳኑ ሕዝብ ብቻ አልነበረም፤ አይደለም።
አምላክ
ሆይ፣ ይህም የሆነው አንተ
የምድር
ጎስቋሎችን ለማዳን
ለፍርድ
በተነሣህ ጊዜ ነው። መዝሙር 76፡ 9
እግዚአብሔር
ለተጨቆኑ ሁሉ
ቅን
ፍርድንና ፍትሕን ይሰጣቸዋል። መዝሙር 103፡ 6
ይህም በግብፅ ምድር
ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቋቸውም የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፣ አዳኝና ታዳጊ
ይልክላቸዋል፤ እርሱም ያድናቸዋል። እግዚአብሔር ራሱን ለግብፃውያን ይገልጣል፤ እነርሱም በዚያ ቀን እግዚአብሔርን
ያውቁታል፤ በመሥዋትዕና በእህል ቁርባንም ያመልኩታል። ለእግዚአብሔር ስለት ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽሙታል።
ኢሳይያስ 19፡ 20-21
ብሉይ ኪዳን
በሃይማኖታዊው ታሪክና በሌላው ታሪክ መካከል፣ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነትና በታሪክ ውስጥ በሚያደርጉት
አስተዋፅኦ መካከል፣ እግዚአብሔር በኪዳኑ ሕዝብ መካከል በሚያደርገውና በሌሎች ሕዝቦች መካከል በሚያደርገው ሥራው ከፍትሕ
አንጻር ልዩነት አያሳይም። እግዚአብሔር የእስራኤልን ታሪክ እንደሚቆጣጠር ሁሉ፣ የአሕዛብንም ታሪክ ይቆጣጠራል።
እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ያለው የጌትነት መልክ በአሕዛብ ላይ ካለው ጌትነት መልክ የተለየ ኪዳናዊ ገጽታ ያለው ቢሆንም
እግዚአብሔር የሕዝቦች ሁሉ ጌታ፣ የነገሥታት ሁሉ ንጉሥ ነው።
እግዚአብሔር በኪዳኑ
ሕዝብ መካከል ይሠራል፤ በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ ይሠራል። ሕዝቦች ሁሉ የእግዚአብሔር ናቸው።
አምላክ
ሆይ፣ ተነሥ፣ በምድር ላይ ፍረድ
ሕዝቦች ሁሉ
ርስትህ ናቸውና። መዝሙር 82፡ 8
የሰራዊት ጌታ
እግዚአብሔርም፣ “ሕዝቤ ግብፅ፣ የእጄ ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል፣ የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል።
ኢሳይያስ 19፡ 25
የእግዚአብሔር ኪዳን
ከኖኅም ጋር ይሁን ከአብርሃም ወይም ከሌላ ግለ ሰብ ጋር፣ የሚገባው ኪዳን፣ ቃል ተጋቢው ላይ የሚያተኩር ይሁን እንጂ
ሌላውን ገፍትሮ የሚያስቀር አይደለም። እግዚአብሔር ከአንድ ሰው ጋር ኪዳን እንደሚገባ ሁሉ ከሌላውም ሰው ጋር ኪዳን
ይገባል። ከአንዱ ጋር ኪዳን ስለገባ ከሌላውም ጋር ሌላ ቃል ኪዳን እንዳይገባ የሚያግደው ነገር የለም። አንዳንድ ጊዜ
የእግዚአብሔር ኪዳን ከእኔ ጋር ወይም ከእኛ ጋር ብቻ እንደ ሆነ ቆጥረን ሌላው ከእግዚአብሔር ጋር ኪዳን እንደሌለው ወይም
ከእግዚአብሔር ለሚሆን ኪዳን እንዳልበቃ፣ እንደማይበቃ በመቁጠር ራሳችንን እንደልላለን፤ ሌላውንም ከእግዚአብሔር ጋር
ከሚኖር ግንኙነት ክበብ ውጭ ገፍትረን እንገኛለን፤ የእግዚአብሔርንም አምላክነት በሞኖፖል በስሜታችን ወይም በአሳባችን
አጓጉል ይዘን እንታያለን። የእግዚአብሔር አባትነት ለሁሉም እንደሚሆን መገንዘብ ይሳነናል።
ነቢያትም
የእግዚአብሔርን ጌትነት በእስራኤል ላይ እንዳወጁ ሁሉ በሌላውም ሕዝብ ላይ ጌታ እንደ ሆነ አውጀዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ
እግዚአብሔር “ባሪያዬ ናቡከደነፆር፣ የቀባሁት ቂሮስ” ወዘተ እያለ የአሕዛብን ነገሥታት ሲጠቅስ እንመለከታለን።
አንዱን ፍጡር በአንድ
መልክ ሠርቶ ሌላውን ፍጡር በሌላ መልክ መሥራቱ ሁሉን አንድ ዓይነት አለማድረጉ እግዚአብሔርን አድሎአዊ እንደሆነ
ሊያስቆጥር አይገባም።
የእግዚአብሔር
ፍትሐዊነት ፍጥረቱን አንድ ዓይነት እንዲያደርግ የሚያስገድድና ፍጥረቱን ልዩ ልዩ አድርጎ እንዳይሠራ ሥልጣኑን የሚገድብ
አይደለም። እግዚአብሔር የፍትሕ መነሻ የፍትሕ አምላክ ነው እንጂ ፍትሕ የእግዚአብሔር አምላክ አምላክ አይደለም። እርሱ
የፍትሕ መለኪያ ይሆናል እንጂ ለእርሱ መለኪያ አይዘረጋለትም። ለምሳሌ፦
ይቀጥላል…
ETHIOPIANCHURCH.ORG Copyright © 1993 by
Mitiku Adisu All rights reserved
በሰለሞን ከበደ

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org