ሕይወት ቢራቢሮ?

በምትኩ አዲሱ

ባለቅኔው ጸጋዬ “እሳት ወይ አበባ” በሚል ርዕስ ካሠፈራቸው ግጥሞች መካከል አንዱ ‘ሕይወት ቢራቢሮ’ የተሰኘው ነው። ግጥሙ እንደ ተቀሩቱ ሁሉ በውበትና በጥልቀት የታነጸ ነው። ሆኖም ከሌሎቹ ይልቅ በተለየ መንገድ የመኖርን ትርጉም ይመረምራል፣ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን መልስ በጥርጣሬ ይቃኛል። “የሕይወት መገኛዋ ከየት ነው? ግሥጋሴዋስ ወዴት ነው?” ይለናል። እርግጠኛ የሆነ መልስ እስኪመጣለት አይጠብቅም። በፍለጋው ይረካል። አሳቡ መጓዙ ላይ እንጂ መድረሱ ላይ አይደለም። ይህንን በቃል አመራረጡና በሐረግ አደራደሩ ያብራራልናል።  

የቅኔ ስልቱና ውበቱ በአንዳንድ መልኩ ከከበደ ሚካኤል ጋር ቢመሳሰልም፣ ጸጋዬ ከከበደና ከሌሎች ሁሉ የሚለይበት ሶስት ዓይነተኛ መንገዶች አሉ። ይኸውም አንደኛ፣ ሰብአዊነትን ከሠፈር እስከ አህጉር፣ ከአህጉር እስከ አህጉራት ድረስ ለማስተሳሰር፤ ከጥንት ወደ ዛሬና ከዛሬ ወደ ጥንት ለማሸጋገር ጥረት ማድረጉ ነው። በዚያው ልክ ስለ እውነት ምንነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ ነጻነት፣ ስለ (አገር) ፍቅር፣ ስለ ዘላለማዊነት፣ ስለ ሞት፣ ወዘተ ማውጋቱ ነው። ሁለተኛ፣ ከተለመዱ የግጥም ሥርዓቶች ሌላ “የጸጋዬ ቤት” የተሰኘ የራሱን አቀማመር መፍጠሩ ነው። በመጨረሻም፣ ጽሑፎቹ መጽሐፍ ቅዱስን በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ማጣቀሳቸው ነው። ይህ የመጨረሻው ነጥብ የጸጋዬን ጽሑፎች ‘መንፈሳዊነት’ ይበልጥ ጉልህ ያደርገዋል። ‘መንፈሳዊ’ በዚህ አገባቡ፣ በሚታየው አይረካም ወይም አይወሰንም ለማለት ነው። ባለፈው ላይ ተመርኩዞ የወደፊቱን ብስራት ያመጣልናል ለማለት ነው። የማይታየውን የሕይወትን ጥልቅ ምሥጢርና አጭርነት፣ የፍጥረትን ውስብስብነትና የራሱን ሕልውና ለመረዳት ይጥራል ማለታችን ነው። በዚህ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ ማጣቀሱን ባጭሩ ጠቁመን በ ‘ሕይወት ቢራቢሮ’ ገጽታ ላይ እንወያያለን። 

  1. ከመጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሁለት ክፍሎች ተጠቅሰዋል፣

·     ይኸ ይሆን አልፋ-ኦሜጋ? (መጽሐፈ ራእይ 1፡8)፣

·     ይኸ ይሆን አስቀድሞ ቃል? (የዮሐንስ ወንጌል 1፡1)

 

  1. ክርስቲያናዊና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች በተዘዋዋሪ የተገለጹባቸው ቃላት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፣

·    ጸጋ፣ ሞገስ፦ ይህም ስጦታ እንጂ በራስ የሚገኝ ስላለመሆኑ፣ የሚለበስ ስለመሆኑ

·   “ፀሐይ የኅዘን ማቅ አጥልቃ” ይላል፤

·    ብርሃንና ጭለማ ገናናነታቸውና ተፈራራቂነታቸው። ይኸው አሳብ ተደጋግሞ ተገልጿል። በርቶ፣ ተጥለቅልቆ፣ ጮራ፣ መንጸባርቅ፣ ፀሐይ፣ ፈገግታ፣ ቀን፣ ብልጭታ፣ ውጋጋን፣ ንጋት። ሲመሽ፣ ሌት። 

·    ሞትና ሕይወት፤ በጋና ክረምት፤ ደስታና ኅዘን፤ ሰማይና ምድር

·     ግማደ መስቀል

·     ጽዋ፤ ፍስሃ፤ ሢሳይ

 

  1. ቢራቢሮ ሕይወት

የቢራ ቢሮ “ልደትና ዕድሜዋ” አራት የዕድገት ሂደት ይታይበታል። ስትበርር ውል-ውል ብን-ብን ትላለች። እንደ ጢስና እንደ ላባ ገላዋ የቀለላት ነች፤ ትንሳፈፋለች። አቅጣጫዋን ማወቅ ሆነ መከታተል ያዳግታል። በበረራ ላይ እያለች መያዝ አስቸጋሪ ይሆናል። ለመያዝ ማድፈጥ፣ ብዙ ጥረትና ትግስት ይጠይቃል። ሲቀርቧት አታስፈራም። ግን ለአያያዝ አታመችም። ለዚህ ይሆን ባለቅኔው ከሕይወት ጋር ያመሳሰላት? ምግቧን ከአበባ ወደ አበባ እየዘመተች ትቀስማለች። እግረ መንገዷን አበቦቹን እያዳቀለች ሕይወትን ታራባለች። በቀለማት አሸብርቃ ከሩቅ እንደምትታየው ሳትሆን ቀርበው ሲነኳት ብን ብላ የምትረግፍ ሕልም ፍጥረት ነች። እውነትም፣ የጥንት ግሪኰች የሰው ነፍስ ስትወጣ በቢራቢሮ ተመስላ ነው የሚሉት ያለ አንዳች ምክንያት አይደለም።  

ቢራቢሮ ሥፍራ አትመርጥም። ከጉድፍ ላይ ተነሥታ በርራ ከሚያማምሩና ሽታቸው ከሚያውድ ዕፀዋት ላይ ታርፋለች። ሊይዟት የሚሹ ሁሉ “እንደ ልጅ” መሆን ይኖርባቸዋል። መገረም የገዛቸው ሊሆኑ ይገባል። በፍጥረት ውስብስብነት፣ ውበትና ውህደት የተማረኩ፣ የልጅነታቸውን የማድነቅና የመጠየቅ ጸጋ ያልጣሉ መሆን ይኖርባቸዋል።  

ቢራ ቢሮ ከአበባው ላይ፣ ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ

ከቄጠማው፣ ከለምለሙ፣ ሰምረሽ፣ አቅፈሽ መመሰሉ 

 

  1. ሕይወት ቢራቢሮ

ባለቅኔው ሕይወትን አይተማመንባትም። አላፊ መሆኗን ይገነዘባል። ቢራቢሮ ይህን እንድታመላክተው ይሻል። በኑሮ ግርግር መሐል የተዘነጋውን ጥልቅና የሰነበተ ለሰው ሁሉ መሠረታዊ የሆነ ጥያቄ ይጠይቃል፤ 

እስቲ አስተምሪኝ ቢራ ቢሮ፣ ሰው ለመባል አለኝታዬ

ቀድሞ የት ነው መነሻዬ

ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ?… 

 

  1. መነሻና መድረሻ

መነሻና መድረሻ እንዳለ ቢያስታውቅም፣ ሕይወትን ዑደት እንጂ በአንድ አቅጣጫ እንደምትሄድ አይገነዘብም። ፍጥረት ሳያቋርጥ ይቀያየራል፤ ይነሣል፣ ይሮጣል፣ ይደፋል። ቀና ብሎ ቀጥ ብሎ ወደ ፊት አይገሠግስም። መውጫ አጥቶ ይሆን? መውጫውን ማየት ተስኖት ይሆን?  

ሲነሣ ሲሮጥ ሲደፋ፣ ሲያጋድል ሲያባዛ ሚዛን…

ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ይወድማል ይባላል

ልደቱ ዕድሜና ሞቱ፣ አለማቋረጥ ይጓዛል

 

  1. ቀዳሚ ጥያቄ?

በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን የሕይወት ጅማሬና ፍጻሜ ትምህርት ሌላ ማብራርያ ያክልበታል፣ እንደገና ለምርመራ ያቀርባል፣  

ሲተረትማ ሲወጋ፣ ከየብልጭታው ውጋጋን

የሰው የአራዊት የአእዋፍ፣ ውስብስብ ነገደ ጉንዳን

ሲነሣ ሲሮጥ ሲደፋ፣ ሲያጋድል ሲያባዛ ሚዛን

በማይመጠን ታላቅ ኃይል፣ በተፈጥሮ ግዙፍ ሥልጣን

ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ይወድማል ይባላል…

ሲነገር እንደ ሰማነው… 

መልሱን አይሰጠንም። የባለቅኔ ተግባሩ ያ አይደለምና። ማሳሰቡ ላይ እንጂ። ባለቅኔ ባለ ራእይ ነው። ራእዩን እንጂ አፈጻጸሙን አያስታውቀንም። በአእምሮው ውስጥ እንደ በራለት ብርሃን መጠን ያየውን ዓለም አኳኋን ይነግረናል። የምናውቀውን እውነት የምናየውን ዓለም ከመልመድ ብዛት ድንቅኛነቱን እንዳንዘነጋ ጠርዞ በማፈራረቅ ገጽታውን በማቀያየር እንደ አዲስ ያቀርብልናል። ባለቅኔው መነጋገሪያ በሆነን በዚህ ግጥም ውስጥ ዝናብና ዝንብን፣ ፀሐይና ጐርፍን፣ አበባና እሳትን፣ ዕንባና ዶፍን፣ ጐጆና መስክን፣ በርኖስና የኅዘንን ማቅ፣ ወዘተ እያነጻጸረ፣ እያጣመረ፣ እያመሳሰለ ያነጋግረናል።  

  1. ሕይወት አላፊ ነው፤ “ሲመሽ፣ ሲሸሽ፣ ስትከንፍ፣ ሲረግፍ፣ ሲገፍ፣ አለፈ” እያለ ያስረዳል፣

  1. የሕይወት ‘ቢራቢሮነት’ የተወሰነለት የሕይወት ሂደት ቢኖረውም፣ አስተማማኝነት ግን አይታይበትም። ቢሆንም ከተቀጠረለት አያመልጥም። ይህንን እውነት ልብ በሚወጋ ስንኝ ይገልጸዋል፣

ቢራ ቢሮ ሆኖ እማይበር

ፀደይ ሆኖ የሚዘልቅ የለም …

ይሁን ያለን ዲበ-ኩሉ፣ የኑሮ ግማደ መስቀል

ለካ እንዲያው ነው መርበትበቱ፣ ሥረ-ቃሉ ላይነቀል?… 

 

  1. ግጥሙን በመገረም ዝግታ ጥያቄ ይከፍታል፣

ቢራ ቢሮ ከአበባው ላይ፣ ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ

ከቄጠማው፣ ከለምለሙ፣ ሰምረሽ፣ አቅፈሽ መመሰሉ 

መደምደሚያው ምላሽ ሳያገኝ የጥያቄውን ደጅ በመሻቱ ትይዩ እንደ ተከፈተ ይተወዋል። ሊደርስበት የሚናፍቀውን፣ ግን ከሁኔታዎች የተነሣ ያልተቻለውን እያሰበ ይወተውታል፤ ያንንም ሁናቴ በእግረ-አሳቡ ይዳስሳል…      

ምን አለበት ላንዲት ሰሞን

ቢራ ቢሮ እኔ አንቺን ብሆን? 

የሕይወት ትርጉም በመነሻና በመድረሻዋ ሳይሆን በተገኘንበት ነው ማለቱ ይሆን?…? የሰው ሕይወት እንደ ንጋትና እንደ ምሽት በድግግሞሽ የታጠረ ስለሆነ፣ ይህን እውነት ለማንጸባረቅ ይሆን ስንኞቹ የተደጋገሙት?  

  1.  የግጥሙ ‘መንፈሳዊ’ መሆን ምን ያስረዳናል?

ባለቅኔው ግጥሙን ከጻፈበት ጊዜ አንስቶ (በ 1961 ተጻፈ) እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ድረስ (1998) ሲጠይቀው ስለኖረው ጥያቄ አንድ አቋም ብቻ ነበረው ማለት ያዳግተናል። ደግሞ ከሃምሳ ዓመት ፈጠራዎቹ ውስጥ በአንዲቱ ግጥም ብቻ ብንገመግመው እንበድላለን። ስለ ግጥሙ ግን ቢያንስ ሶስት ቁም ነገሮችን መገንዘብ እንችላለን። የመጀመሪያው፣ ባለ ቅኔው የተገኘበትን ባሕል ሕዝብ መልክዓ ምድር ምን ያህል እንደሚያውቅና እንደሚያከብር ያሳያል። ሁለተኛ፣ የሕዝቡን ቋንቋና ባሕል ሳይጋፋ ሳይንቅ ወደ አንድ አቅጣጫ ለመምራት ያደረገውን ጥረት ያመለክታል። ማኅበረ ሰቡ ልክ ነው ብሎ የተቀበለውን እውነት እንደገና እንዲመረምር ይጋብዛል።    

ሲተረትማ ሲወጋ…ሲነገር እንደ ሰማነው          

ሶስተኛ፣ እውነትን ለማወቅ ያደረገውን ጥረት ያስረዳል። ሰው የዘላለሙን ጉዳይ ለመረዳት በውስጡ ምን ያህል ጥልቅ ጥማት እንዳለው ያሳያል። “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጐ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው” (መክብብ 3፡11)። ያም ጥማት በሆነ ባልሆነው እንደማይረካ ያስገነዝበናል። ሊያረካው ቢችል ያ ነገር ከርሱ ውጭ እንደሆነ፣ ፍለጋውም የሚያስከትለው ረሐብ ከቶ ብርቱ እንደሆነ በመረዳት ይወተውታል፣

         ምን አለበት ላንዲት ሰሞን

         ቢራ ቢሮ እኔ አንቺን ብሆን

         በፍስሃሽ ብጥለቀለቅ፣ ብነግሥባት ባንቺ ጽዮን?

         ጸጋ ሞገስሽን ለብሼ፣ እኔ ባንቺ ስም አልፌ

         እኔ ባየርሽ ሰፍፌ

         እኔ ባክናፍሽ ከንፌ

         ምን አለበት ቢራ ቢሮ፣ … አንቺ ቀለም ለበስ ቅጠል

         የብርሃን ጮራ ጠለል

         ተወርዋሪ ሲሣይ መሰል፣

         ምን አለበት ቢራ ቢሮ፣ ዕድልሽን እኔ ብታደል?…

 

  1.  እውነትና ሕይወት

“ሕይወት ቢራቢሮ” ቤተ ክርስቲያን የምትጠይቃቸውንና ልትጠይቃቸው ሲገባት የዘነጋቻቸውን ጥያቄዎች መልሶ ያቀርብልናል፤

· ስለ እውነት እናስተምራለን፣ ግን እውነት በተገኘበት ሁሉ የእግዚአብሔር እውነት እንደሆነ እናስተውላለን?

·    ሰው በእግዚአብሔር አምሳል እንደ ተፈጠረ እናምናለን፣ ፍትሕ ሲጐድል ሰብዓዊ መብት ሲገፋ እንቆረቆራለን?

·    ወገኖቻችን ወደ ወንጌል እውነት እንዲደርሱ እንወዳለን፣ እንላለን። የወገኖቻችንን አስተሳሰብ ባሕል አኗኗር ለመረዳት እንጥራለን? ወይስ በንቀት እናያለን?

·    ለሕይወት ጥያቄ በርግጠኝነት መልሱን በክርስቶስ በኩል አግኝተናል እንላለን፤ እርካታ ይታይብናል? ክርስቶስን ከማያውቁት ምን ይለየናል? ፍለጋውንስ ችላ ብለን ይሆን (1ኛ ጴጥሮስ 2፡21)? ፍለጋውን ከእርግጠኝነቱ ጋር ደርበን መያዝ ተለማምደናል? የክርስቶስ በሆኑቱ ዘንድ እርካታና መሻት አብረው ይገኛሉና። እርግጠኝነት ሲጠፋ መዋተት ይመጣል፣ ፍለጋ ሲጐድል ደግሞ የማይታገሥ ግትርነት ያይላል።

አምላኬ፣ አምላኬ፣ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ

ነፍሴን አንተን ተጠማች

ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች…

ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች…

ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች (መዝሙር 63) 

¤ 

            ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ

            አቤቱ፣ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች (መዝሙር 42) 

                                                         ¤   

            የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና

            የተራቆተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቷልና (መዝሙር 107)

    12. ግልጽ ቋንቋ

ባለ ቅኔው ጸጋዬ የተጠቀመባቸው ምርጥ፣ ውብና ጥራት ያላቸው ቃላት ናቸው። ከምናውቀውና ከምንረዳው ሁኔታ ተነሥቶ አብረነው እንድንጓዝ ይጋብዘናል። በአገላለጹ ማማር ይማርከናል፤ በምኞታችን በጥያቄአችንና በናፍቆታችን በኩል ስለቀረበን ልንሰማው እንፈቅዳለን፣ እንገደዳለን። የጠብቅነውንና የምንፈልገውን መልስ አይሰጠን ይሆናል። ዳሩ ግን፣ የያዝነውን እውነት እንድንመረምር ይጠይቀናል። ለሚቀርቡልን ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት ደግሞ አስቀድሞ ጥያቄውን በትክክል መረዳት ይኖርብናል።

ከምናነብባቸው ጽሑፎች አንዳንዶቹ ከአስተሳሰባችንና ከባሕላችን ጋር ያልተገናዘቡ፣ የተኰረጁና ለመረዳት የሚያዳግቱ ናቸው። የራስን ሳያውቁ የሌላውን ማስተጋባት ነውር ነው፤ ከክብር መጉደል ነው። ማስመሰል ራስን መናቅ ነው። የራስን ጥሎ በጭፍኑ የሌላውን ማስተጋባት የእግዚአብሔርን ዓላማ መሳት ነው፤ ሲብስም እግዚአብሔርን መናቅ ነው።

          ዕድልሽ የዋዛም አይደል

          ክፉ ፈተና ነው መምሰል፤…

          በርቺ እንግዲህ ቢራቢሮ፣ ክረምት ላንች ብቻ አለፈ

          መስሎ አላድር ያለውማ፣ በጐርፍ ዘቅጦ ጐረፈ          

የእግዚአብሔር ሕዝብ ሕይወቱና ቋንቋው ግልጽ መሆን ይኖርበታል። በቤተ ክርስቲያን ክልል ብቻ የተወሰን ሊሆን አይገባውም። አኗኗሩ ለሚያየው ጥያቄ የማይፈጥር፣ ለሚሰማው የማያደናግር መሆን አለበት (የሐዋ ሥራ 2)። ካልተረዱን ችግሩ ያለው እኛ ጋ ነው ማለት ነው።

13. በቅኔና በዝማሬ

ዘማሪዎች ሙዚቃው ላይ እንደሚተጉ ሁሉ የዝማሬውንም ቃል ማጥራት ይኖርባቸዋል። የባለቅኔው አንዲቷ ቃል ብትወገድ ወይም ብትለወጥ በግጥሙ ሕልውና ላይ ብዙ ለውጥ ያስከትላል። የቃላቱ አደራደርና አመራረጥ የራሱ የሆነ የሚፈልቅ ሙዚቃ ቃና አለው። ሥርዓት አለው፤ ዝግታ አለው። ማዕርግ አለው።

         ቢራቢሮ ከአበባው ላይ፣ ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ

         ከቄጠማው፣ ከለምለሙ፣ ሰምረሽ አቅፈሽ መመሰሉ

ከአንዳንድ ከምንሰማቸው መዝሙሮች ውስጥ ሐረጐች እንዳለ ቢሠረዙ እንኳ ለውጥ አያመጣም። ለወንጌል ክብር የማይመቹ ቃላትን ቤት እንዲመታ ብቻ ወይም ሰዎች የሚነጋገሩበት ቋንቋ ነው በሚል ሰበብ መጠቀም የሰሚውን እድገት ይገታል፤ አያንጽም፤ አያነጻም። ከአገር መሪ የማይጠበቅ ወይም የሚጠበቅ አነጋገር አለ። ከወንጌል አገልጋይ (ዘማሪ) የማይጠበቅ ወይም የሚጠበቅ እንደዚሁ አለ። ለዚህ ነው ወንጌል በኃይሉ ሙላት እንዲተላለፍ ከተፈለገ ከብዙ ጸሎት ጋር አእምሮንና ልብን በእግዚአብሔር ቃል መግራት የሚያስፈልገው። ለዚህም ነው መንፈሳዊ እውነትን ለመግለጽ ብዙ ጸጋ የሚያስጠይቀው (ኤፌሶን 6፡20)። ለዚህ ነው ዝማሬው የሰሚውን ልብ እንዲነካና ለውጥ እንዲያስከትል ያለፍንበትን የተረዳነውን እውነት መስበክና መዘመር የሚኖርብን። ከቃላቱና ከሙዚቃው ጋር የተዘመረበቱ መንፈስ ወደ ነፍስ ፈጥኖ ይደርሳልና።

የዘማሪዎች ድርሻና ኃላፊነት ከፍተኛ ስለሆነ መዝሙሮች ከመታተማቸው በፊት ዘማሪው ቀርቦ ቤተ ክርስቲያንን ወይም ጸጋ የተሰጣቸውን ማማከር ከስሕተት ይጠብቃል (ዕብራውያን 13፡7፤ ሮሜ 16፡7)። ይህ ማለት ሳንሱር ይደረግ ማለት አይደለም። አንዱ ሌላውን የሚጠብቅበት መንገድ ይፈጠር ማለት እንጂ። የፍቅርና የትሕትና መንገዱ ይኸ ነው። ደግሞም ከመንፈስ ቅዱስ አሳብና አሠራር ጋር ይስማማል እንጂ አይቃረንም። ለቤተ ክርስቲያን መገዛትን ይጠይቃል። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የአንድ ሰው፣ የጥቂቶች፣ የአንድ ትውልድ ወይም የባልንጀሮች ጉዳይ እንዳይደለ መገንዘብን ይጠይቃል። የቤቱ ጉዳይ የግለሰቦች፣ የሴቶች ወይንም የወጣቶች ብቻ እንዳይሆን አድርጐ ጌታ መስርቶታልና። እንግዲህ እግዚአብሔር ያገጣጠምውን ሰው አይለያይ (1ኛ ቆሮንቶስ 12)። ባጭሩ፣ የአንድ ወንድምና እህት መሰናከል የኔም የሁላችንም መሰናከል ይሆናል።

የቃላት አመራረጥ ንጹሕ አስተሳሰቦችን እንዲያነሳሱ ታስቦ ሊሆን ይገባል (ፊልጵስዩስ 4፡8፤ 2ኛ ጴጥሮስ 1፡14-15፤ 3፡1-2)። ቤት የሚመቱ፣ ሥርዓት የያዙ፣ ለማስታወስ የሚረዱ ሊሆኑ ይገባል። የተደረገለትን ብቻ ሳይሆን ያደረገለትን አምላክ ኃያልነት፣ ቸርነት፣ ቅዱስነት፣ ዘላለማዊነት ወዘተ ማግነን ይኖርበታል። የወንድም ተስፋዬ ጋቢሶን መዝሙሮች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

መንፈሳዊ ሙዚቃ ቅንብሩ የጉራጊኛ፣ ትግርኛ፣ ሬጌ?  ዳንኪራ ስልት ሊያስታውሰን አይገባም። ሙዚቃው የቃሉን አሳብ ለማስተላለፍ የሚያግዝ እንጂ የሚሻማ የሚጋፋ የሚያጨናግፍ የሚያደናገር ከቃሉ መልእክት የሚያዘናጋ መሆን የለበትም። የሚያዘናጋ ከሆነ ወይ መዝሙሩ መቅረት አለበት ወይም ያለ ሙዚቃ መሣርያ መዘመር ይኖርበታል ማለት ነው።

14. መደምደሚያ

የወንጌል አገልጋዮች የዓለምን ቋንቋ መረዳትና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቋንቋ ደግሞ ለዓለም መግለጽና ማስረዳት መቻል ይኖርባቸዋል። በአንድ ሥፍራ ለጸሎት ተሰብስበው ሳሉ፣ “እስቲ ለነፍሳት እንጸልይ” እንዳለውና፣ በመካከል የነበረ እንግዳም፣ “እነዚህ ጴንጤዎች አሁንስ አበዙት፣ ብለው ብለው ደግሞ ለትንኝና ለገብረ-ጉንዳን እንጸልይ ይበሉ?” አለ እንደተባለው ማለት ነው።

የአገራችንን ልማድ ወግና ታሪክ የሚያስረዳ ስለሆነ የዚህ ባለቅኔና ሌሎች ጻሕፍት ሥራዎች በስነ-መለኰት ትምህርት ተቋማት በተጨማሪ በመደበኛነት ሊጠኑ ይገባል። የሌሎችን ቋንቋ ማወቅ የአክብሮት መግለጫ ብቻ ሳይሆን የምሥራቹንም ወንጌል ማብሰሪያ መንገድ ስለሆነ እያንዳንዱ አፍ ከፈታበት ሌላ ሌላ ቋንቋ መማሩ አስፈላጊ ይሆናል። እስቲ ግጥሙን በአንድ ወጥነቱ እናንብብ፣

 

ãምአ2006

_____________________________

 

ሕይወት ቢራቢሮ

ቢራ ቢሮ ከአበባው ላይ፣ ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ

ከቄጠማው፣ ከለምለሙ፣ ሰምረሽ አቅፈሽ መመሰሉ

ለምንድነው ቢራቢሮ

አበባሽ ከአበባው ሠምሮ፣

በፀደይ ከዐደይ ጋር ፈክቶ

በርቶ፣ ተጥለቅልቆ ደርቶ

እንደ ጮራ ተንዠርግጐ፣ በመንጸባርቅ ተንጣሎ

ፀደይ አክሎ ፀደይ መስሎ

ውሎ፣…ኋላ ቀኑ ሲመሽ

ፀሐይ ግንባሯን ቀልሳ፣ ከጭለማ ክንፍ ስትሸሽ

ብርሃኗ በሌት ተዳፍኖ፣ ዓይኗም ፈገግታዋም ሲሰንፍ

አዝርእቱ እርጭ ብሎ፣ ጸጋውን ከመልኩ ሲገፍ

አበባው ምድሩን ሲንተራስ፣ ያፈር ጽዋ ዕረፍቱን ሲገድፍ

ቢራ ቢሮ ያንቺስ ሞገስ፣ ለምንድነው አብሮ እሚረግፍ?…

ምን አይተሻል ከቄጠማ፣ ምን አይተሻል ከለምለሙ?…

ቀን አብረሽ አብበሽ ውለሽ፣ ሲመሽ አብረሽ ማስለምለሙ?…

አስተምሪኝ ቢራ ቢሮ፣ ሰው ለመባል አለኝታዬ

ቀድሞ የት ነው መነሻዬ

ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ?…

ሲተረትማ ሲወጋ፣ ከየብልጭታው ውጋጋን

የሰው የአራዊት የአእዋፍ፣ ውስብስብ ነገደ ጉንዳን

ሲነሣ ሲሮጥ ሲደፋ፣ ሲያጋድል ሲያባዛ ሚዛን

በማይመጠን ታላቅ ኃይል፣ በተፈጥሮ ግዙፍ ሥልጣን

ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ይወድማል ይባላል

ልደቱ ዕድሜና ሞቱ፣ አለማቋረጥ ይጓዛል፣

ይኸ ይሆን አልፋ-ኦሜጋ? ይኸ ይሆን አስቀድሞ ቃል?…

ያንቺሳ ምሥጢር ምንድነው፣ ቢራ ቢሮ እንወያይ

አንቺ የዕፀዋት አዋዋይ

ከፀደይ ጋር ፀደይ መሳይ

ከአበባም አበባ መሳይ…

ምን አለበት ላንዲት ሰሞን

ቢራ ቢሮ እኔ አንቺን ብሆን

በፍስሃሽ ብጥለቀለቅ፣ ብነግሥባት ባንቺ ጽዮን?

ጸጋ ሞገስሽን ለብሼ፣ እኔ ባንቺ ስም አልፌ

እኔ ባየርሽ ሰፍፌ

እኔ ባክናፍሽ ከንፌ

ምን አለበት ቢራ ቢሮ፣….እንቺ ቀለም ለበስ ቅጠል

የብርሃን ጮራ ጠለል

ተወርዋሪ ሲሣይ መሰል፣

ምን አለበት ቢራ ቢሮ፣ ዕድልሽን እኔ ብታደል?…

ትንኞች፣ ዝንቦች ያሙሻል

ወረተኛ ነሽ ይሉሻል፣

ከአበባ አበባ መክነፍሽ

ከፀደይ በጋ መዝለቅሽ፣

ከሾህ፣ ከጉድፍ ስትስቂ

ከየስንጥሩ ስትወድቂ

ስትዳሪ፣ ወግ ስትነጥቂ

እያወቅሽ እንዳላዋቂ

የወረት ነው ብለውሻል፣ ቢራ ቢሮ ተጠንቀቂ።

የበጋው እንኳ ግድ የለም፣ የሀጋይ አሰድ እሳቱ

ቢያነድሽ፣ ቢያክነፈንፍሽ፣ ቢያጤንብሽ ትኩሳቱ

ተፈታትኖሽ ነው ፍትወቱ

አለውልሽ መዋተቱ

ከጉድፍ ጋር መጋጨቱ።

ምነው ታዲያን ቢራ ቢሮ፣ በዝንቦች ወራት በበልጉ

አበቦች ሲጠውልጉ

መስኩ ቦዘን ሲከናነብ፣ በትንኝ ጪስ ሲታፈን

አረንጓዴው ሲገረጣ፣ ያሸበረቀው ሲሸፈን

ፀሐይ የኅዘን ማቅ አጥልቃ፣ በጉም በርኖስ ስትዳፈን

እንደ ደስታዋ ጊዜ፣ መከራዋን ሳትካፈይ

ጭንቀቷን አብረሽ ሳትቀበይ

ከትንኝ ጋር ስትጋፊ፣ አልቀመጥ ብለሽ አርፈሽ

ይኸው አጉል ስም ተረፈሽ።

ቢራ ቢሮ ተናገሪ፣ ሞያው እንዲህ ነው ባንቺ ዓለም

ከፀደይ የፀደይ ቀለም፣ ከበልግ የበልግ ቀለም

ከአበባውም፣ ከጉድፉም፣ ከትንኙም መስሎ መግጠም?

ለካ እንዲህ ነው ያማርሽባት፣ የሕይወትን አገም ጠቀም

ቢራ ቢሮ ሆኖ እማይበር፣ ፀደይ ሆኖ የሚዘልቅ የለም?!

ላንቺ ይብላኝልኝ እንጂ፣ ለኔስ ክረምት ደረሰ

በሰማያት ዕንባ ምድርን፣ ሊጠርግ እያግበሰበሰ፣

አበባውን እንደጉድፍ፣ ጉድፉን ከዝንብ ጋር ሲያስስ

ሁሉን እኩል ሲያግበሰብስ

አጥርና ጐጆ ሲድስ

ሜዳውን በደለል ሲምስ

ግንዱን በዶፍ ሲገረስስ

ክረምት አያ እናት አይምሬ፣ ማመዛዘኛም የለህ ወይ?

ጉድፍ፣ ጽጌ-ረዳ፣ ዐደይ

ማንንም ከማንም አትለይ?

አየን የሁሉ እኩል ቤት ወግ

መደምሰስ፣ መገርሰስ፣ መጥረግ!

ቢራ ቢሮ እንዴት ነበር፣ ያንቺስ የክረምቱ ውሎ?

መቸም ለይቶ ፈጥሮሻል፣ ከሁሉ አድረሽ ኑሮ ብሎ

የመመሰል ሙያ ክኖ፣ የመጠጋት አቅል አድሎ…

ከረምሽ አሉ እንደ ሌት ወፍ

ተለትመሽ ከቤት ክፈፍ፣

እንደ ግንደ-በል ምስጦች፣ ከምሰሶ ተገን መግባት

በየጣራ እንደ ሸረሪት፣ በምድጃ እንደ እሳት እራት

ዕድልሽ የዋዛም አደል

ክፉ ፈተና ነው መምሰል፣…

በርቺ እንግዲህ ቢራ ቢሮ፣ ክረምት ላንች ብቻ አለፈ

መስሎ አላድር ያለውማ፣ በጐርፍ ዘቅጦ ጐረፈ

ለካ ምሥጢርሽ ይኸው ነው። በቃኝ እኔም አልሳሳት

ሲነገር እንደሰማነው፣ ከየብልጭታው ውጋጋን

የሰው፣ የአራዊት፣ የአእዋፍ፣ ውስብስብ ነገደ ጉንዳን

በማይመጠን ታላቅ ኃይል፣ በተፈጥሮ ግዙፍ ሥልጣን

ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ያልፋል ይባላል

ልደቱ ዕድሜና ሞቱ፣ አለማቋረጥ ይጓዛል

ይኸው ነው አልፋ-ኦሜጋ? ይኸው ነው አስቀድሞ ቃል?

በኅሊና መሳከሩ፣ ላይሆን የቆሽት ሕመም ማብቀል

በአለብላቢት መለብለቡ፣ ልቦናን በሣግ መቀቀል

ይሁን ያለን ዲበ-ኩሉ፣ የኑሮ ግማደ መስቀል

ለካ እንዲያው ነው መርበትበቱ፣ ሥረ-ቃሉ ላይነቀል?…

በይ ብር በይ ቢራ ቢሮ፣ ክረምት ላንቺ ብቻ አለፈ

ሌላው በጐርፍ ጐረፈ

ሞተ፣ በተኛበት ረጋ…

ፀደይ ላንቺ ብቻ ነጋ

ሽር ብለሽ መንቆጥቆጥ ነው፣ ከዚያም፣ ከዚያም፣ ከዚያም ሠምሮ

አወቅሁብሽ፣ ነቃሁብሽ፣ አንቺ ሕይወት ቢራ ቢሮ…

ቀናሁ መሰል አንች ወላዋይ?

ነይ ብር በይ እንወያይ

አንቺ የዕፀዋት አዋዋይ

ከፀደይ ጋር ፀደይ መሳይ

ከአበባም አበባ መሳይ…

ምን አለበት ላንዲት ሰሞን

ቢራ ቢሮ እኔ አንቺን ብሆን? 

እሳት ወይ አበባ፣ ገጽ 57-62፤ 1966 ዓ.ም. ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ።