ምክንያት አጣሁኝ

የመስቀል ፍቅርህን

ጣርህን ሳስበው

ምክንያት አጣሁኝ

ወንድሜን ልጠላው

 

ፍቅር አስገድዶህ

ደፋ ቀና ያልከው

በቀራንዮ መስቀል

የተንገላታኸው

መራራውን ጽዋ

ለኔ የጠጣኸው

 

እኔ ባንተ ዳንኩኝ

አንተ ለኔ ሞተህ

ሕይወት ታወጀልኝ

ሞት በሞት ተሻረ

በትንሣኤው ጌታ

መኖር ከጀመርኩኝ

መኖሬ ካልቀረ

ድንጋይ ላነሱበት

የሾህ አክሊል ጭነው

ለተዛበቱበት

አያውቁትምና - የሚያደርጉትን

አታስብባቸው - ኃጢአታቸውን

 

ብሎ ከጸለየ

ከዚህ በላይ ፍቅር

ከቶ በማን ታየ

እኔም በመገረም

ይህንን አይቼ

ይቅር ላለማለት

ምክንያት አጥቼ

ከሱ ጋር ተስማማሁ

 

የእውነተኛ ፍቅር

ትርጉሙ ሲገባኝ

እኔም ተረታሁኝ

ወንድሜን ልጠላው ምክንያት አጣሁኝ

እህቴን ልጠላት ምክንያት አጣሁኝ

 

በይልፋሸዋ፣ ከኖርዌይ