የመንፈሳዊ ጤንነት ፍተሻ
በተስፋዬ ታደሰ
በሰለጠነው ዓለም ሰዎች ጤናማ መሆን ያለመሆናቸውን ለማወቅ በዓመት አንዴ ወይንም ሁለቴ የአካላቸውን ጤንነት በሐኪም ያስፈትሻሉ፤ የሚበረታታ ጥሩ ልምድ ነው። ለጊዜው ምልክትና ስሜት የሌላቸው ደዌዎች አቆጥቁጠው ቢሆን እንኳ ሥር ሳይሰዱ ከወዲሁ ለመቅጨት ይጠቅማል። ወደ አገራችን መለስ ስንል ደግሞ ጤናማ መሆን ያለመሆኑን ለማወቅ የጤንነት ፍተሻ የሚደረገው ግድ በሚል አጋጣሚ ነው። መኪና ለማሽከርከር የሚያስችል ፈቃድ ለማግኘት፣ በኰርሶች ለመሳተፍና ሥራ ለማግኘት፣ ወደ ባሕር ማዶ ለመሄድ ካልሆነ በስተቀር የጤንነት ፍተሻ በፍጹም አይታሰብም። ሌላው ቀርቶ የሕመም ስሜቶችና አካላዊ ለውጦች ችላ ስለሚባሉ በቀላሉ ሊወገድ በሚችሉ በሽታዎች ሕይወታቸውን የሚያጡ አያሌዎች ናቸው።
ምን ጊዜም ቢሆን ጤንነትን የመሰለ ሃብት የለም። ስለ ጤንነታችን እግዚአብሔርን ማመስገን፣ ጤንነትንም መጠበቅ፣ ጤንነታችንን የሚገዳደሩ ነገሮችን መቆጣጠርና ማራቅ ብልኅነት ነው። “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” ተብሎስ የለ? በእርግጥ ከጥንቃቄ የሚያልፍ ሕመም ሊከሰት ይችላል። ደግሞም በመታከም የሚዳን ወይም የማይዳን ቢሆን ሁሉን ለሚችል አምላክ ነግሮ ማረፍና ተመስገን ማለት ጤንነት ብቻ ሳይሆን በረከትም ነው።
የሥጋዊ አካላችን ጤንነት መፈተሽ እንዳለበት ሁሉ የመንፈሳዊ አካላችን ጤንነትም ፍተሻ ያስፈልገዋል። በየጊዜው ፍተሻ ካልተደረገለትና እንክብካቤ ካጣ ይታመምና ከሥጋዊ አካላችን ይልቅ ለበለጠ አደጋ ይጋለጣል። እንዲያውም ሕመሙ ሥጋዊ አካላችንን እስከ ማጥቃት ይደርሳል። ደግሞም ግለ ሰብን አቁስሎና ገድሎ የሚቆም አይደለም። ቤተ ሰብን አልፎም ማኅበረ ምዕመንን የሚጐዳ ይሆናል።
የመንፈሳዊ ጤንነት መታወክ ምክንያቶች ጥቂቶች ባይሆኑም አንዳንዶቹ በዋዛ የሚታለፉ አይደሉም። በተለይማ ፈጣኖቹና ተላላፊዎቹ በማር የተለወሰ መርዝ የሚባለውን ዓይነት መልክ የያዙ እጅግ መርዛሞች ናቸው። እንደ እነዚህ ያሉቱ ከጥንቃቄ ጉድለት ሊከሰቱ የሚችሉ ይሆናሉ፣ ወይንም ብስለት ከማጣት።
ከጥንቃቄ ጉድለት በሚባለው ምክንያት ለአጥቢያ ማኅበረ ምዕመን አገልጋዮች መቅረብ የሚገባው ጥያቄ አለ። ለስብከት፣ ለትምህርት፣ ለዝማሬና ለልዩ ልዩ ሥልጠናዎች መድረካችንን የምንፈቅድላቸው አገልጋዮችን ጤንነት ለማወቅ እንተጋለን? ወይስ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ይወቅ ብለን ኃላፊነታችንን ዘንግተን ይሆን? የውስጡን ገልጦ የሚያውቅ እግዚአብሔር መሆኑ እውነት ነው። ሆኖም ለአገልግሎት ስንጋብዝ የእውነተኛ አገልጋይነት ድርሻችንን መወጣት ግዴታችን ይሁን። ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት ማራመዳቸውንና ጤናማነታቸውን ኅብረት ካደረጉበት አጥቢያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በማጥናት ለመንጋው ጤንነት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።
ሌላው የመርዙ ቫይረስ ተሸካሚዎች ገዳይ መርዛቸውን የሚነሰንሱበት ምቹ ቦታዎችን ነቅቶ መጠበቅ ተገቢ ነው። የተለያዩ ሕብረቶችን ቤተ ክርስቲያን በበላይ መጠበቅ ብትችል መልካም ነው። በነጻነት ስም ኑፋቄና አጋንንታዊ ትምህርቶች የክርስትናን ካባ እየለበሱ የምዕመኑን ጤንነት በመርዛቸው እንዳይበክሉ ጥንቃቄ የሚደረግባቸውን አካባቢዎች ለማስታወስ ብዬ ነው (ዮሐንስ 21፡ 15-17)።
በመሠረቱ በክርስትና ስም የሚደረጉ ሆኖም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጣጣሙ ትምህርቶችን በግልጽ የምናይበት ዘመን ላይ እንዳለን ማወቅ አለብን። እንደዚህ በመሳሰሉ በሽታዎች ተለክፈው ዓይኖቻቸውን የተያዙ የበሽታቸውንም ምልክት ያስተዋልንባቸው ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን ልንገነዘበው የሚገባ ዋነኛው ነገር ቢኖር መንፈሳዊ የጤንነት ፍተሻ አድርጐ ሕመሙን መለየት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነው። ዓላማችን መሆን ያለበት ከስህተት ተመልሰው በእግዚአብሔር ቃል መስዋዕትነት ራሳቸውን አይተው ያጐደሉብንን የአካል ክፍል መሆናቸውን እንደገና ሙሉ እንዲያደርጉት ነውና አበክረን ልንጸልይላቸው ይገባል።
የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለማወክና ተልዕኰዋን በብቃት እንዳትወጣ ሰይጣን በብዙ ዓይነት መንገድ ከመሞከር ቦዝኖ አያውቅም። ጭልጥ ያለውን ስህተት እውነት እያስመሰለና መንፈሳዊነትን እየቀባባ የሰዎችን ልብ ማማለሉ አያስደንቅም። “ሥራውን አንስተውም” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከላይ የተገለጸው እንቅስቃሴ ስሜትን የሚማርክ በማይፈጸም ተስፋ የሚያነሆልል በመሆኑ አዳዲስ ነገርን ለመቅመስ፣ ለማየትና ለመዳሰስ የሚቻኰለው የኑፋቄ ትምህርት ሰለባ ወጣቱ ሆኗል። እነኚሁ ወጣቶች በትምህርቱ ላይ ምንም እንከን አላገኘንበትም፤ እንዲያውም ሕይወታችን ለመለመበት፣ የወደፊቱ ተስፋችን ብሩህ ሆነልን እያሉ ያልተረዱትን እውነት መሳይ ውሸት ቢያሞካሹትም የትምህርቱን መሠረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያለመሆኑን ያህል የሚፈጠረውን ኪሳራና የመጨረሻውን ግብ አሳዛኝ ፍጻሜ መሆኑን ከአስተምህሮታቸው ስንገነዘብ ልባችን በሐዘን ይደማል። “በሬ ሆይ፣ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ…” የሚለውን ተረት ልብ ይሏል።
እንግዲህ መንፈሳዊውን የጤንነት ፍተሻ አዘውትረን እናድርግ። ለዚህም የምንጠቀምበት መሣሪያችን ዘለዓለማዊ የሆነው የሕያው እግዚአብሔር ቃል ነው። “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፣ ራሳችሁን ፈትኑ” እንደተባለው (2ኛ ቆሮንቶስ 13፡ 5) በነገር ሁሉ ንቁ እንሁን። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትም ነጥቦች ለፍተሻው ይረዱናል ብዬ አምናለሁ።
ሀ. የዓይኖቻችን ጤንነት ይፈተሽ
አምሮቱ ለሌሎቹ የአካል ክፍሎች እንቅፋት እንዳይሆን ይጥራ። ዓይን የሃሳብ መግቢያና የሰው ጠባይና ስሜት መግለጫ ስለሆነ ማስተዋል በጐደለው ስሜታዊ እንቅስቃሴ አይማረክ (ዘኁልቁ 15፡ 39፤ ማቴዎስ 5፡ 29፤ ሉቃስ 11፡ 34-36)።
ለ. የጆሮቻችን ጤንነት ይፈተሽ
ሁሉን የሚችለውን የእግዚአብሔርን ድምጽ ከእንግዳ ድምጽ ለመለየት አንቸገር። እንደ ዳዊት “እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ” የሚል ዝግጁነት ይኑረን (መዝሙር 84፡ 8)።
ሐ. የሆዳችን ጤንነት ይፈተሽ
ጌታ ኢየሱስ “በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ፣ የሕይወት ውሃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” አለ (ዮሐንስ 7፡ 38)። ፈውስ የሚሆነው የሕይወት ውሃ ከሆዳችን እየፈለቀ መሆኑን እንፈትሽ። ቤተ ክርስቲያንን የሚያጐድፍ ነገር የምንናገር ከሆነ የውስጥ መታወክ ገጥሞን ይሆናልና በቶሎ እንታከም።
መ. ጉልበቶቻችን ይፈተሹ
ጉልበቶቻችን ለማን እየደከሙ እንደሆነ ልብ እንበል። ጉልበት ሁሉ ሊንበረከክለት ለሚገባው ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንበርከክ። በእግዚአብሔር የተመረጡ ሰዎች ጉልበታቸውን ሊያስገዙ የሚገባቸው ለእንግዳ ትምህርትና ሐሳብ ሳይሆን ለእግዚአብሔር መሆን አለበት።
“ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፣ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው። እንግዶች ጉልበቱን በሉት፤ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፤ እርሱም አላወቀም” ስለሚል (ሆሴዕ 7፡ 8) ጉልበታችንን ሳናውቀው ለማይገቡና ለሚያፈርሱ ነገሮች እንዳናስበላ ራሳችንን እንመርምር።
(ብርሃን መጽሔት፣ ቁጥር 28፣ 1989፣ ገጽ 26-27። ጽሑፋ በመጠኑ አጥሯል)
