እግዚአብሔር ታደገን

በተሾመ ወርቁ

በይርጋለም ከተማ የክርስቲያኖች መታሰርና መደብደብ በ1970ዎቹ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በ1967 ዓ.ም. ከቤተ ክርስቲያኒቱ ምሥረታ ጀምሮ አብሮ ያደገ ነበር። መሰብሰቢያችንን በድንጋይ ሲደበድቡ፣ ሆ ብለው እየጨፈሩ መጥተው አሰልፈው ከተማ ለከተማ ሲያዞሩንና (የቀበሌ አመራሮች ወጣቶችና የከተማ ቦዘኔዎችን በማሰባሰብ) የቤተ ክርስቲያንን ንብረት ሲዘርፉ ሲያስሩንና ሲፈቱን የኖሩ ቢሆንም በተለይ በ 1970-71 በነበሩት ዓመታት በየትምህርት ቤቱ፣ በየመንገዱና በየሰፈሩ ሁሉ ዱላና አንዳንዴም ከቤት እየተወሰዱ መታሠር የዕለት ተዕለት ዜና ነበር።  

በ 1970 ዓ.ም. በሚያዝያ ወር በከተማው ውስጥ ያሉት በሙሉ ታፍሰው በመታሰር በቀይ ሽብር አፋፋሚዎች በሰደፍና በጫማ (በርግጫ) በመደብደብ የብዙ ቅዱሳንን ደም አፍስሰዋል። በዚህን ጊዜም ነበር፣ “እየመሰከሩ ተገረፉ፣ ጌታን አስከብረው ተመለሱ” የሚለው መዝሙር የተደረሰው።

ዕለተ እሑድ ሚያዝያ 21፣ 1971 ዓ.ም. በከተማው የክርስቲያን ሠርግ ነበር። ከዚያ ወጥተን ወደ የቤታችን በመጓዝ ላይ ሳለን በቤተ ክርስቲያን በዕድሜው የመጨረሻ ትንሽ የነበረው እንዲሁም በምስክርነት አገልግሎቱ የሚታወቀውና አሁም ግን ወደ ጌታ የሄደው ወንድማችን ደባልቄ መስፍን ከአንድ ቀን በፊት ከቤቱ ተወስዶ ታስሮ ስለነበር እርሱን ለመጠየቅ በመንገድ ዳር ወዳለው ቀበሌ ጐራ አልን። ትንሽ አጫውተነው ተሰነባብተን ስንወጣ ጠመንጃ ያነገተ ዘበኛ “በሕግ አምላክ” ቢሮ ትፈለጋላችሁ ሲለን፣ የምንፈለግበትን ምክንያት ባናውቀውም ለሕጉ ለመታዘዝ ወደ ተጠራንበት አመራን። ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ በቁጥጥር ሥር አዋሉን።

ያቺ ዕለት ፍቅር የሚፈተንባት የሰባቱ ዓመት እስር የተጀመረባት ዕለት ነበረች። በማግስቱ ከትንሹ ደባልቄ ጋር እኔና ወንጌላዊ ኃይሉ በቀለ ሦስት ሆነን ወደ ፖሊስ መምሪያ ተላለፍን። ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ወደ ወኅኒ ቤት ተላክን። 

ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት መንፈስ ቅዱስ ሕዝቡን እያነቃቃ ያዘጋጅ ነበር። የሦስታችን ቀድሞ መታሰር የቀሩትን ለበለጠ ገድል እንዲዘጋጁ አድርጓቸዋል። በታሰርነውም ሆነ በውጪ ባሉት ከፍተኛ የመንፈስ ቅዱስ መጽናናትና መነቃቃት ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኔ 16 ቀን 1971 ዓ.ም. በውጪ የነበሩት ተስፋዬ ጋቢሶን ጨምሮ ወደ እስር ቤት ገቡ። ከዚህም በኋላ በቡድን ከፋፍለው በቀበሌና በፖሊስ ጣቢያ መድበው ከባድ ሥራ ማሠራት ጀመሩ።

መስከረም 29 ቀን 1972 ዓ.ም. ሦስታችንን ከወኅኒ ቤት አውጥተው ከየቀበሌውም ሰብስበው ፖሊስ ጣቢያ አከማቹን። በማግስቱ በቁጥር በየቀበሌው እየተመደብን ወደ ተዘጋጀልን የመከራ ድግስ እንድንበታተን ተደረገ። ከዚያም ቋጠሮው እየጠበቀ እውነተኛው ፍቅር የሚመዘንበት ጊዜ መጣ። የመከራ ዶፍ ዘነበ፤ በጉዳዩም የተካኑ ሰዎች ሥራቸው ማሰቃየት ብቻ ሆነ። መከራው ግን ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን አልቻለም (ሮሜ 8፡ 35-39)።

እናሳምንበታለን ብለው ያዘጋጁትን የመከራ ዓይነቶችን ሁሉ አራት ወር ሙሉ አፈራረቁብን። ስላልተቻላቸው እንደገና ሰብስበው ወደ ወኅኒ ቤት ጨመሩን። ከዋነኞቹም አንዱ በቁጭትና በዛቻ “እነዚህን ጥቂቶችን ማሳመን ያቃተን ሌሎችንማ እንዴት ልናደርግ ነው?” ብሎ ሲናገር ተደምጧል።

በሰባቱ ዓመታት ከተፈራረቁብን አንዱን ለመጥቀስ ያህል ከማንም ሰው ጋር እንዳንገናኝና ስንቅ እንዳይገባልን ተደርጓል። በታሰርንም በአምስተኛ ዓመታችን ወደ ነገሌ ቦረና እንድንወሰድ ተደረገ። በስፍራው እንደ ደረስንም ያለን ንብረት ሁሉ ወደ ግምጃ ቤት ሲገባ ከለበስናቸው ሸሚዝና ነጠላ አንሶላ በቀር ሌላውን ሁሉ አስወልቀው እንዲሁ እንድንኖር ተደረግን። በዚህን ጊዜ ነበር የቦረናው የወኅኒ ቤት አዛዥ “እስቲ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ ያድናችሁ?” ብሎ የተሳለቀብን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እግዚአብሔር መልሱን ሲሰጠን “እግዚአብሔር ሲረዳ ከሰማያት ወርዶ …” የሚለው መዝሙር የተዘመረው።

በነገሌ ቦረና ቅጣት ጌታ እየረዳን ያለ መሸነፋችን ሲታወቅ ወደ ይርጋለም ወኅኒ ቤት ይመለሱ ተባለ። በወኅኒ ውስጥ አንዳንዴ በአንድ ክፍል ውስጥ ለየብቻችን ያስሩናል። በአንድ ላይ ስንሆን ደግሞ ይጠናከራሉ ብለው በየክፍሉ ይበትኑናል። እንደገና እስረኛውን ሰበኩት በከሉት ብለው ይሰበስቡናል። እነርሱም አብረውን ተቸገሩ። በዚህ ውስጥ አእምሮን ሁሉ የሚያልፈው የእግዚአብሔር ሰላም ልባችንን ይጠብቅ ስለነበር በወኅኒ ቤት ውስጥ የነበሩ እስረኞች ከሚደርስብን ተጽዕኖ የተነሳ ማዘን ሲገባን ፈገግታ ስለማይለየንና ስለምንስቅ “የሰላም ሚኒስቴር” የሚል የቅጽል ስም አውጥተውልን ነበር። የእግዚአብሔር የጉብኝት ጊዜም ሲደርስ ከሰባት ዓመት ከአንድ ወር መከራ በኋላ እንድንፈታ ታዘዘ፣ የጌታ ስም በምድር ሁሉ ተመሰገነ።

ያሳለፍናቸው ሰባት ዓመታት የብዙ ቅዱሳንንና የብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ፍቅር ያየንባቸው ጊዜአት ነበሩ። በይርጋለም የነበረውን ችግር ሰምተው ያለመታከት ያልጸለዩ፣ ልባቸው አብሮን ያልታሰረ፣ ጌታ ችግሮቻችንን ሲፈታ አብሮ መንፈሱ ያልተፈታና ያልፈነደቀ ማንም አልነበረም።

ዛሬ አብረን ከታሰርን 13 ወንዶች መካከል 10 ያህሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን ሲወጡ እህቶቻችን ደግሞ በቤተ ክርስቲያን በትልቅ ፍቅር ጌታን እያገለገሉ ይገኛሉ። ክብር ለእግዚአብሔር ለአምላካችን እስከ ዘለዓለም ድረስ ይሁን (2ኛ ቆሮንቶስ 1፡ 8-11)።

(ብርሃን መጽሔት፣ ቁጥር 30፣ 1990፣ ገጽ 25)