ማን ይምራት?

በሰለሞን ከበደ፣  

መግቢያ 

“ማነው መሪዬ?” ይህ ቤተ ክርስቲያን ምንጊዜም ልትዘነጋው የማይገባት ዓይነተኛ ጥያቄ ነው። በዚህ ጥያቄ መሠረት መሪው ማን ነው ማለት ሰውን በአካል ሳይሆን የምትመራበትን አስተሳሰብ የሚመለከት ነው። ጥያቄው ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተዳድራት የሥርዓቷና የሥልጣኗ ምንጭ ማን ነው የሚል ይሆናል።

ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ ዓለም ወይስ ጌታ ኢየሱስና የመንግሥቱ ሥርዓት? 

ሰውን ማዕከላዊ ባደረገው በዓለም ሥነ-ልቡናዊ ትምህርት ቤተ ክርስቲያን አመለካከቷንና የትምህርቷን ንዝረት በማመሳሰል እየቃኘች ናት ወይ? ዓለም ኅብረተ ሰባዊነት ስትል ቤተ ክርስቲያን ያንኑ ትበል! ዓለም የሴቶች መብት ስላለች ቤተ ክርስቲያንም የሴቶች መብት ትበል! ቤተ ክርስቲያን የትምህርቷንና የሥልጣኗን ምንጭ ዘንግታ የዓለምን ንዝረት ታስተጋባ! የገደል ማሚቶ ትሁን! ዓለም መብት ለሰዶማውያን እያለች ስትጮኽ ቤተ ክርስቲያንም ቢቀሰሱ ምን አለበት ትበል! የዓለም ሥልጡንነት የመሪዎቿ ሥልጡን ሊሆን አይገባም። 

ዓለም በዘርና በቋንቋ በነገድ ስትከፋፈል፣ ጌታዋ ነውር እንደሌለው በግ ደሙን አፍስሶ ከነገድም ሁሉ፣ ከቋንቋም ሁሉ፣ ከወገንም ሁሉ ዋጅቶ ለአባቱ ለእግዚአብሔር የካህናት መንግሥት ለማድረግ የተቤዣት ቤተ ክርስቲያን የዓለምን ጥያቄ ጥያቄዋ አድርጋ በዘር በነገድ ተከፋፍላ መናቆር የለባትም። 

ዓለም በጊዜያዊ ተድላ ስታሽቃብጥ፣ የሙዚቃዋንም ዘይቤ እንደሚያመቻት ቃኝታ ስታቀነቅን ቤተ ክርስቲያንም በአፏ ለእግዚአብሔር፣ በልቧ ለዓለም ታዚም፣ ትሞዝቅ! ለጣዖትና ለምስል ዓለም ስትሰግድ ቤተ ክርስቲያንም ለሰው እጅ ሥራ ለሥርዓት ምስል ትስገድ? ዓለም በለቀመችበት እየቃረመች ትገኝ! 

የአሕዛብ አማልክት መመለካቸውንና ለእነርሱ መሥዋዕት መቅረቡን እንጂ አምላኪዎቹ በጽድቅና በቅድስና መመላለሳቸውን አይሹትም፣ ደንታም የላቸውም። በማንም በምንም የማይደገፍ፣ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን የሚኖር፣ የፍጥረት ሁሉ ባለቤት፣ ፍጹም ሕያው የሆነ እግዚአብሔር አምላክ፣ ከአምልኰ ረሐብ የተነሣ ጠኔ ይጥለው ይመስል፣ ንስሓ በሌለበት፣ ጽድቅና ቅድስና በጐደለው የሽንገላ አምልኰ ቤተ ክርስቲያን ራሷን ብትደልል “አመንዝራይቱ” ከመባል በምንም አታመልጥም። ንጽሕና አልባ የሆነ ዝማሬና ሙገሳ እግዚአብሔር አይቀበልም (ኢሳይያስ 1፡ 11-16፤ አሞጽ 5፡ 21-24)። 

አልፋቸውም ዖሜጋቸውም ይህች ዓለም የሆነች ምድራውያን ለገንዘብ፣ ለኃይል፣ ለሥልጣን ይሮጣሉ፤ ይሞታሉም። የቤተ ክርስቲያንም ሰዎችና አገልጋዮች እንዲሁ ገንዘብንና የገዢነት ሥልጣንን ለማግኘት ይሽቀዳደሙ! ይሻረኩ! ይሻኰቱ! ዝቅ ብሎ ለማገልገል ወገብን በመታጠቅና በመነሣት ፈንታ ለከበሬታ-ስምና ለከበሬታ ወንበር “ጥሪ አለኝ” እያሉ ይራወጡ? ወንበርን ለእኔ “ለተቀባሁት” ልቀቁልኝ አመቻቹልኝ ይሁን ራእያቸው፣ ትግላቸውና ትጋታቸው? (ይሰጡአል እንጂ ይነጥቁአል! ይታደሉታል እንጂ ይታገሉታል!) ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን” (ሉቃስ 22፡ 26)። ማገልገል እኰ፣ ከተቀመጡበት መነሣትን፣ ማበሻ ጨርቅ መታጠቅን፣ እግር ማጠቢያ ማዘጋጀትን፣ ጐንበስ ብሎ --በርከክ ብሎ የሌሎችን የቆሸሸ እግር ማጠብን፣ የረጠበውን እግር አብሶ ማድረቅንና እጣቢ መድፋትን ይጠይቃል (ዮሐንስ 13፡ 4-5)። 

የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እግዚአብሔርን መምሰል እንደ ማትረፊያ፣ ወንጌልን እንደ መነገጃ ቢያደርጉ “በነጻ ተቀበላችሁ በነጻ ስጡ” የሚለው የጌታ ትእዛዝ ወዴት ይግባ (ማቴዎስ 10፡ 8)? “ስጡ ይሰጣችኋል” የሚለው ቀርቶ በ “ስጡኝ ስጡኝ ይሰጣችኋል” ተተካ ማለት ነው። በፍቅረ ነዋይ መለከፍ፣ ለእጅ ሥራ ለገንዘብ ጣዖት መስገድ ማለት ይኸው ነው። “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” (ሮሜ 12፡ 2፣ 10)። “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፣ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ለዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” የሚለውን ቃል አንዘንጋ (1ኛ ዮሐንስ 2፡ 15)። 

መቅደስ ውስጥ ሆኖ ከአንገት በላይ ይሁን ከልብ አብዝቶ ሲጠራ፣ የቤቱ ጌታ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና በድንገት መጥቶ “እናንተ ቤቴን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት” ቢል በውኑ በፊቱ መቆም የሚችል ማነው? የብር አንጥረኛ ከዝቃጩ ብዛት የተነሣ ብር-ተብዬውን እንደሚጥል ብሩም “የተጣለ ብር” እንደሚባል እንደዚያው እንዳንሆን በንስሓ መንገድ እንጓዝ። በምሕረቱ ጸጋ፣ ልብሳችንን በበጉ ደም እንጠብ፤ ከፍቅረ-ነዋይ፣ ከፍቅረ-ሹመትና ከሥጋዊ ምኞት እንንጻ (ሚልክያስ 3፡ 1-3፤ ኤርምያስ 6፡ 30፤ ራእይ 7፡ 14፤ 22፡ 14)።   

ማጠቃለያ 

ጊዜው ደርሶ ጽዋ እስኪሞላ፣ ጌታዋ እስኪመጣና እስኪወስዳት ድረስ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ አለች። የወንጌልም ተልዕኰ ባለ አደራ ናት። እርሱ ራሱ፣ “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም”ብሎአልና። “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና” ያለው፣ ያው ጌታ ዓለምና የእርሱ ተከታዮች ያላቸውን ልዩነት ተናግሮአልና (ዮሐንስ 17)።  

ይህ ዘመን በበጉ ደም ልብሷን አጥባ ያጸዳችይቱ የክርስቶስ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ከአስመሳይቱ ዓለማዊቱና አመንዝራዊቱ ቤተ ክርስቲያን ተለይታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታወጣበትና የብርሃንና የጨለማ ልጆች የመጨረሻ ፍልሚያ ውስጥ የሚገቡበት ሰዓት ይሆን?

(ብርሃን መጽሔት፣ ቁጥር 30፣ 1990፣ ገጽ 14)