በንዲህ የተገኘ ወዳጅነት እንዴት ውብ ነው?

በምትኩ አዲሱ
ማንም ቢሆን አረጋግጦ በያዘው እምነቱ ምክንያት ተስፋና ክብር እንጂ ውርደት ይደርስብኛል ብሎ አያስብም። ውርደትን ቀምሶ ማሳለፍ ግን ውሎ ሲያድር ብዙ ትዝታ ጥሎ ያልፋል።
እምነት ሁለት መልክ አለው። በራሱ የሚታመን አለ። በፈጣሪው የሚታመን አለ። ሁለቱም ይፈተናሉ። አንደኛው ይወድቃል፣ ሌላኛው ይጸናል።
ሰው ሲባል ራሱን ለማስወደድ፣ ያልሆነውን ሆኖ ለመታየት የማይፈጥረው ዘዴ የለም። እነዚህ ብልሃቶቹ ግን ሁሌ ያዛልቃሉ ማለት አይደለም:: አያድርስና ለምሳሌ እስር ቤት ቢታጎር ምን ማድረግ ይችላል? ምናልባት ራሱን ለመመርመር መነሻ ምክንያት ያገኝ ይሆናል።
በተወሰነ ሥፍራና በጠበበ ሁኔታ ውስጥ መገናኘት ያለውዴታም ቢሆን መቀራረብን ማስከተሉ አይቀርም። መቀራረብም መተያየትንና መጠናናትን፣ መጠናናትም እያደር መተዋወቅንና መገላለጥን ያመጣል።
እንግዲህ የድብብቆሽ ኑሮ ዋነኛ ጠር ቢኖር መገላለጥ ነው፤ ከሰው ጋር ወዳጅነት መፍጠር ነው።
ሰው ሆድና ጀርባውን ከተገላለጠ ራቁቱን ቀረ ማለት ነው። ራሱን ለነቀፌታ አመቻቸ ማለት ነው። ሌላኛው ሊያጠፋው ወይም ሊያለማው የሚችልበት አዝማሚያ ተፈጠረ ማለት ነው:: ከሰው ጋር መኖር ትልቅ አደራ ነው፤ ትልቅ አደጋ ነው። … ወይ ተማምኖ እየተጋገዙ መኖርን ያስከትላል፤ ወይም እየተማሙ መገዛገዝን።
የያዙት እምነት የሚመዘነውና የግል መሆኑ የሚረጋገጠው ደግሞ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ተፈትኖ ያለፈ እንደሆነ ብቻ ነው። የምቹ ዘመን እምነትማ እንዳልተገራ ወይፈን ለቁም ነገር አይውልም:: ከጊዜ-አመጣሹና ጊዜ-አጠፋሹ ተለይቶ አይታይም።
ነፍስ ለነፍስ መገናኘትና ቋንቋ ለቋንቋ መነጋገር የሚቻለው እያደር ነው። በቅድሚያ ግን ግርዶሹ መገፈፍ ይኖርበታል:: መከራም የሚላከው አዳፋውን ገጽታ ለማጥራትና ይኸን የማስመሰል ካብ ለመናድ ነው…
ይህን በመሰለ ሁኔታ ውስጥ የተገኘ ወዳጅ እንግዲህ እንዴት ውድ ነው? ፍቅሩስ እንዴት ድንቅ ነው? ትዝታውስ እንዴት የማያረጅ ነው?
ቢያንስ ለአንድ ሌላ ሰው የልቡን አሳብ መግለጥ ያላወቀ፣ መከራም ያልሞከረው ሰው ምንኛ ምስኪን ነው? ሁሉን እንደ ተጠራጠረ ራሱን በራሱ እንዳሠረ ይኖራል። ኑሮው የተሟላለት ቢመስልም የኑሮን ጣዕም ሳያጣጥም ይኖራል።
ሕይወቱን አላካፈለምና የበዛ ሕይወት አይቀበልም። ተዘግቶ እንደ ኖረ ደጅ ብርሃንም እንደማይገባበት ለጨለማ እንጂ ለምንም አይበጅም።
የእህል ዘር ተቋጥሮ ቢቀመጥ ተቋጥሮ ይቀራል። ተቋጥሮ ይረሣል። ሊያበዛው የሚችለውን ሕይወቱን በውስጡ አፍኖ ነክሶ ይዞታልና ብቻውን ይሞታል …
እንግዲህ የተዘጋው ደጅ ሲከፈት ጨለማው ሥፍራ ይለቃል። የተቋጠረው ተፈትቶ ሲበተን መትረፍ ይጀምራል። ይህንን ደጅ የሚከፍትና የተቆለፈውን መዳፍ የሚዘረጋ ቅድም እንዳልነው በአብዛኛው መከራ ብቻ ነው።
መከራ ባቆራኛቸው ግለ ሰቦች ዘንድ ከቀን ቀን የሚከሰተውን ለውጥ ማስተዋል ደግሞ ራሱን የቻለ ትምህርት ይሰጣል።
የመጀመሪያው ቀን ላይ ድንበር መጋራቱ፣ የራሴ የሚባል መታጣቱ ያስቆጣ ይሆናል። አለዚያም ምግቡ፣ የሰው ጠረን … ማንኮራፋቱ … የመኝታ አለመመቸት፣ ኩርፊያው፣ ሌት ደግሞ የጀርባ አጥንት ሲላቀቅ ሙቀቱና ግማቱ ዐመል ያሳጣ ይሆናል።
ውሎ ሲያድር ግን ይህም ይለመዳል። ይባስ ብሎም ይዋሃዳል። ጊዜውም እየራቀ ሲሄድ በሌላ አዲስ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በናፍቆት ይታሰባል። ይህም ዕርቃን የመውጫ መጀመሪያው ነው።
ከዚያም ይመሻል። ይነጋል። ተስፋ የተደረገበቱ ሁሉ ይዘገይና “መቸ ይሆን?” ማለት ይመጣል። መላ መምታት፣ በጭፍን በሰቀቀን መኖር መፍረክረክ ይጀምራል። ይኸኔ የሰው ዋጋ ይታወቃል። ቀልሎ መገኘትና ለቁም ነገር መብቃት ይከተላል። መደጋገፍ … ተስፋ መሰጣጣት፣ በመከራ እየቀለዱ ቀን መግፋት ይቀጥላል። ይህ ደግሞ የመደማመጥ፣ የመግባባትና የመተሳሰር ሁለተኛው ነው።
በንዲህ የተገኘ ወዳጅነት እንዴት ውብ ነው? እንዴት የማይረሣ ነው? እንዴት የሚመረጥ ነው?
ከፍተኛ 10፣ አዲስ አበባ
