ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ሁን
በብርሃኑ ደረሰ
መግቢያ
በዚህ ጽሑፍ “ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ሁን” የሚለውን አሳብ በአጭሩ ከመዳሰሳችንና አንዳንድም አሳቦች ለውይይት ከማቅረባችን በፊት በአጭሩ የአፍሪካን የወንጌል ስርጭት በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያን የክርስትና ይዘት በትንሹ ለመግለጽ እሞክራለሁ።
የወንጌል ስርጭት በአፍሪካ
የአሕዛብ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን እንዲያውቁ ነው። እግዚአብሔር አንድ ነው፣ በመካከልም ሆኖ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቀውም አንድ ነው፣ እርሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው … እኔም እምነትንና እውነትን ለማብሰር ሐዋርያና አስተማሪ ሆኜ ወደ አረማውያን የተላክሁት በዚህ ምክንያት ነው” (1 ጢሞቴዎስ 24-7)።
የእግዚአብሔር የደህንነት አዋጅ ለእያንዳንዱ ነገድ፣ ጐሣ፣ ቀለምና ሕዝብ እንዲነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲሆን፣ አፍሪካም የዚህ በረከት ተካፋይ እንድትሆን እቅዱ ነበር። ይህንኑ ለመግለጽ ከጌታ ስቅለት ጀምሮ ስሞዖን መስቀሉን በመሸከም አፍሪካን ሲወክል፣ ከእርገቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወንጌላዊ ፊሊጶስ ከተቀጣጠለ የሰማርያ የወንጌል ስርጭት ወደ ምድረ በዳ በመንፈስ ቅዱስ ተጠርቶ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባውን ወደ ወንጌል ብርሃን ሲመልስ እናያለን። ይኸው የደህንነት የምሥራች በሁለተኛውና በሶስተኛው መቶ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ወደ ሰሜን አፍሪካ ዘለቀ (ማቴዎስ 2732፤ የሐዋርያት ሥራ 826-39)።
ሁለተኛው የወንጌል ስርጭት በ 15ኛውና በ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነጋዴዎችና አዲስ አገርን በሚፈልጉ ሰዎች እንደ ተዳረሰ ይነገራል። ሦስተኛውና ዋናው የወንጌል ስርጭት በ 19ኛውና በ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሚሲዮናውያን ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የዚሁ ንቅናቄ ተሳታፊ ሆና በሁለት ታላላቅ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አልፋለች። የመንፈስ ቅዱስ እሳት በነደደበት አካባቢ በሙሉ ታላቅ ስደትና መከራ የምሥራቹን ለማዳፈን ያልተደረገ ጥረት የለም። በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ በሙሉ ቤተ ክርስቲያን ለቃሉ ታማኝ እስከሆነች ድረስ ማንም የነደደውን እሳት ሊያጠፋ አይችልም። ጌታችን ኢየሱስ በማቴዎስ 1618 እንዲህ ይላል፦ “… በዚህችም የመሠረት ድንጋይ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ ይህችንም ቤተ ክርስቲያኔን የሞት ኃይል እንኳ አያሸንፋትም።”
የወንጌል ስርጭት በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ አገራችን ባለፉት መቶ ዓመታት ብቻ በአራት ዋና ዋና ስደት ውስጥ አልፋለች ብል ስህተት አይመስለኝም። ቄስ ጉስታቭ አሬን “ኤቫንጀሊካል ፓየኒርስ” በሚል መጽሐፋቸው “… በብርቱ መስዋዕትነት ወንጌል እንደ ተጀመረ” ገልጸዋል። ሁለተኛውን ስደት ወንድዬ ዓሊ “የእኩለ ሌሊት ወገግታ” በሚለው መጽሐፉ የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ሲጽፍ፣ “ሚሲዮናውያን በጣሊያን ጦር አስገዳጅነት ከሀገር ከወጡ በኋላ” ብዙ መከራ እንደደረሰባቸው ይገልጽና “በቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ያለው መሪ አሰልጥነውና ተክተው ባይሄዱም እንኳ መንፈስ ቅዱስ ባነቃቃቸው ባነሳሳቸው የሀገሬው ተወላጆች እጅግ አስደናቂ የሚባል የወንጌል ስርጭት ተደረገ” ይላል። ሦስተኛው ስደት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የቀጠለ በባላገር ጀምሮ ወደ ከተማ የዘመተ ታላቅ እሳት ያነደደና አገሪቱን በወንጌል ያጥለቀለቀ ነው። አራተኛውና ዋናው ስደት በደርግ ዘመን ሲሆን በአገሪቱ ከነበሩት 3/4ኛ ወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናት የተዘጉበት በዋሻና በመሳሰሉት ቦታዎች የእግዚአብሔር ቃል ተደብቆ የተሠራበት ዘመን ነበር። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በዘመናት ለቃሉ የቆሙ፣ ታማኝ የሆኑ የጌታ አርበኞች ስለነበሩ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
በአጠቃላይ ወንጌል በደረሰበት ሁሉ የማይጣጣሙና በየገበያው ይጫረሱ የነበሩት ጐሣዎች ያለ መሣሪያ ሲገበያዩ ማየት የወንጌልን ኃይል ታሪክ እያወጀው ነው። ትዳር ለመያዝ ይደረግ የነበረው ዝርፊያና ግድያ በምዕመኑ ዘንድ ቆሞ ሌሎችን ወደዚህ እርቅና ሰላም እየጠራ ነው። የጠንቋይ፣ የዛርና አባ ጠቋር ኃይል ሲያንገላታቸው የነበሩት በተራቸው ራሱ ላይ ቆመው ሌላውን ወደዚህ እፎይታ ሲያመጡ ይታያሉ።
ከነጻነትና ዲሞክራሲ አንጻር ወንጌል በተሠራጨበትና ተቀባይነት ባገኘበት አካባቢ ውጤታማ የሆነውን የጌታ አዋጅ በሉቃስ ወንጌል 418 “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው። መልካም ዜናን ለድኾች እንዳበሥር ሾሞኛል፤ ለታሠሩት መፈታትን፣ ለታወሩት ማየትን እንዳውጅና የተጨቆኑትንም ነጻ እንዳወጣ ልኮኛል። እንዲሁም እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያድንበት የጸጋ ዓመት እንዳስታውቅ ልኮኛል” የሚለውን መንፈሳዊና ሥጋዊ እሥራትን የሚፈታ መሆኑን በማመን ፍትሕን በአንድም መንገድ ሆነ በሌላ ለኅብረተሰቡ ከመናገርና ንቃተ ኅሊናውን ወደዚህ ከመጐትጐት ምዕመናን ያረፉበት ዘመን የለም።
የወንጌል ኃይል በአፍሪካ ምድር እንዲህ ባለ መልክ ደምቆና አምሮም ቢቀርብ፣ ጥቁር ነጥብ እዚህና እዚያ የጣለበት ታሪክ ስላለ፣ ለ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የወንጌል ስርጭትን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ሁኔታዎችን በመቀጠል ባጭሩ ለመግለጽ እሞክራለሁ።
የወንጌል ስርጭት እንቅፋቶች
1. ጦርነትና ኤይድስ፦ ብዙ የአፍሪካ ጉዳይ ሊቃውንት ሲናገሩ ጦርነትና የኤይድስ ወረርሺኝ ከአፍሪካ ካልተገታ ምድሪቱን አጥፍቶ ሌላውንም ዓለም በስጋት ላይ ይጥላል ይላሉ። በተባበሩት መንግሥታት በተደረገው ጥናት በአፍሪካ ከ13-19 ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች በአሐዝ ሲተመን ወደ 200 ሚሊዮን ይደርሳል፤ ከነዚሁ ብዙዎች በኤይድስ በሽታ በሚቀጥሉት ዓመታት ሊያልቁ ይችላሉ ተብሎ ይፈራል። የሰው ዕድሜ ዘመኑ በአማካይ ከ 60 ዓመት ወደ 37 ዓመት እንደ ወረደ ይነገራል። በዚህ ላይ አምባገነናዊ አስተዳደር፣ የሰው መብት ረገጣ፣ ሙስና ወዘተ ተጨምሮ የሁኔታዎችን አስከፊነት ጉልህ ያደርጋል።
ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን አሳሳቢ ሁኔታዎችን ስንመለከት የወንጌልን ብርሃን በከፊል ተቀበል በሚባል ሕዝብ መካከል የጽድቅ ጫና ለምን ሥፍራ አጣ የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ ያደርጋል። አንድ የኡጋንዳ ቤተ ክርስቲያን መሪ እንዲህ ብለው ጠየቁ፦ “87 በመቶ ክርስቲያን በሚባል ሕዝቤ መሐከል የሕይወት የኑሮ የአስተዳደር ለውጥ አስተሳሰብ አለመኖሩ ክርስትናን በጥያቄ ላይ ጥሎታል” ቀጠል አድርገው፣ “85 በመቶ ክርስቲያን ተብሎ በሚጠራው የሩዋንዳ ሕዝብ ውስጥ 2 ሚሊዮኑ እንዴት ሊጨፈጨፉ ቻሉ? ማን ማንን ገደለ?” በኤይድስ የሚያልቁትስ?
ባጠቃላይ በቤተ ክርስቲያንና በሥነ መለኰት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ከደህንነት ጋር የእግዚአብሔርን መንግሥት ትምህርት ማከል ይኖርበታል። የእግዚአብሔር መንግሥት ትምህርት በቃሉ ላይ የተመሠረተ ደህንነትን በዕለታዊ ኑሮ የሚያንፀባርቅና የሚኖር ነው። መንግሥተ ሰማያትን በጥቂቱም ቢሆን ወደ ምድር የሚስብና ከቤተ ክርስቲያን ውጪ በሕብረተሰቡ መሐከል ልዩነቱን በሕይወት የሚያሳይ ለዋጭ ኃይል ነው። በጣም የሚያሳዝነው የክርስትና ፍሬ ቁልብጭ ማለቱ ለዓለም ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብም ጭምር ስለሆነ ተከታዩ ትውልድ ለእውነተኛ ክርስትና የሰጠው ትርጉም እየተለወጠ ሄዷል።
2. ስመ ክርስትና፦ የስም ክርስትና ችግር እየጐላ መጥቷል። በቅርቡ በግብጽ 13 ከተሞች ላይ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ስናካሄድ ኢየሱስን እንደ አዳኝ ከተቀበሉት መካከል አንዱ በአሌክሳንድርያ ከተማ አስተርጓሚያችን የነበረ ግለ ሰብ ነበር። ከፀሎት በኋላ ሲነግረን፦ “ከክርስቲያን ቤተሰብ ተወልጄ ቋንቋውን በማወቅ አገለግላለሁ እንጂ ስለ ግል ደህንነት ምንም አላውቅም ነበር፤ ዛሬ ብርሃን በራልኝ” ብሏል። አስተርጓሚያችን ተራ ምዕመን ሲሆን፣ በኡጋንዳ ደግሞ በአንድ የቤተ ክርስቲያን አቡን በኩል እንደዚሁ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞናል። ሌላ ብዙ ተመሳሳይ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። እነዚህ ሁኔታዎች በፀሎት እንድንተጋ፣ ቃሉንም በጊዜውም ያለ ጊዜውም በታማኝነት እንድንሰብክ እያሳሰቡን እንደሆነ እያየን ነው። የዛረው ትውልድ ይህን ሥዕል በየቤተ ክርስቲያኑ እያሳየ ሲሆን፣ ሦስተኛ ትውልድማ እንዴት ይሆን?
3. የትልቅ ጉባዔ አስተሳሰብ፦ የዛሬ 35 ዓመት ከዚያም በፊት ማኅበረ ምዕመናን በአንድ አጥቢያ ከ 300-500 ሲሆኑ፣ ትውውቁ፣ መተሳሰቡ፣ አንዱ ላንዱ መፀለዩ፣ አገልጋዮች ማፍራቱ፣ ልብ ለልብ መገናኘቱ፣ አይዞህ አይዞሽ መባባሉ፣ ድክመታችንን ብርታታችንን መገንዘቡ፣ መጐበኛኘቱ ቤተ ክርስቲያን በሕይወቴ ፈጥሮት የሄደ ትዝታ ነው።
ባለፉት 25 ዓመታት በዓለም ዙሪያ የነፈሰው ነፋስ አልፎ ተርፎ ሦስተኛውን ዓለም እያጥለቀለቀ፣ የክርስትናን የወንጌል ስርጭት የቤተ ክርስቲያንን ተከላ እየተፈታተነ ሲሆን፣ ምዕመኑ ልብ ለልብ የማይቀራረብበት፣ ቤተኛነት የማይሰማበት ኃላፊነቱን በእሑድ ብቻ የሚወስንበት፣ በአንድ ትልቅ ፋብሪካ ውስጥ ወይም ዩኒቨርሲቲ ወይም ከተማ ውስጥ ከቤቴ በላይ የሚያውቀኝ የለም የሚልበት ቦታ ላይ እያደረሰው ይሆን የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ እየመጣ ነው። ይህ ሁኔታ ግላዊነትን እያበዛ ጠያቂ ስለሌለው ተጠያቂነትን እየቀነሰና እያጠፋ የሚሄድ ይሆናል። “ግላዊነት” የሚለውን አንድ ሰው ሲገልጸው “የውስጥ ገበናን ላለመግለጽ ሲባል ከሌላው ጋር ላለመቀራረብ ራስን መቆለፊያ መንገድ ነው” ብሏል።
ትልቅ ጉባዔ ከእሑድ አንጻር እሞቀ ጉባዔ ውስጥ የመኖር ስሜት ቢፈጥርም በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12 ላይ እንደሚናገረው የአካልነት አስተሳሰብ እንደሌለው ብዙዎች እየተናገሩ ነው። ከዚህም በስተቀር አንድ ኪሎ ጨው ለአንድ ድስት እንዳልተሠራ፣ የአሜሪካንም የመብራት ኃይል በአጠቃላይ ለአንድ ከተማ ብቻ እንዳልተተከለ ቤተ ክርስቲያንም ሌሎችን አካባቢዎች ለማጣፈጥ የተቀነሰ ጨውና የሚሠራጭ ብርሃን መሆን አለባት። ወደ አንድ የመገናኛ ድንኳን መሮጫው ዘመን ስላበቃ፣ ቤቱን በየመንደሩ እየተከልን በጌታ መገኘት እንባረክ፡ ቃሉንም በታማኝነት እንዝራ፤ የእግዚአብሔር ቃል ተልዕኰውን ሳይፈጽም አይመለስምና!
4. ዓለማዊነት፦ ይህ አስተሳሰብ እግዚአብሔርን ከግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ሕብረተሰብ መንግሥትና ከትምህርት ሥነ ሥርዓትና በሀገሪቱ ካለው ማንኛውም ሁኔታ አስወጥቶ ዓለምንና ፍልስፍናውን የሚተካ ሲሆን፣ የጌታን ስም በተወሰነ አካባቢ እንደማይንቀሳቀስ ዕቃ ለማስቀመጥ የሚፈልግ ነው። አሳቡ ቁሳዊ፣ ዘላቂ ያልሆነ በጊዜያዊ ክልል ውስጥ የሚኖር፣ ምድራዊና የዘላለም ተቃራኒ የእግዚአብሔር ጠላት የጌታ ልጆች ፈታኝ ነው። የዚህም ውጤት ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌለው፣ በዓይኑ ፊት የመሰለውን የሚያደርግ ትውልድ ማፍራት ሆኗል። በምዕራቡ ዓለም ያለው የሰው አስተሳሰብ መመሪያችን የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ዋጋ ለማሳጣት ጥረት እያደረገ ነው። ስለ ኃጢአት፣ ስለ ገሃነመ እሳት፣ ስለ ፍርድና ቅድስና መስበክ እየራቀ ነው፤ የዚህ ተፅዕኖ ወደ አፍሪካም እየመጣ ነው። ይህንን አዝማሚያ እንደገና ቃሉን በታማኝነት በመስበክ እንጂ በጥበባችን ለመመለስ አንችልም። እንደገና የሐዋርያው ጳውሎስ “ቃሉን ስበክ” የሚለው ጩኸት መሰማት አለበት።
5. የሐሰት ትምህርት፦ በምድራችንም ጭምር የሐሰት ትምህርትና አስተማሪዎቹ እንደ እንጉዳይ እየበቀሉ ሲሆን ቤተ ክርስቲያንም ምዕመኖቿን ለመጠበቅ በቂ ትምህርት በመስጠት ላይ ነች ለማለት አያስደፍርም። ስለሆነም ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ባለበት ቦታ እንደ ሰንበሌጥ እየተመዘዙ ሲወሰዱ የሚገነዘብ ስሜት ብዙውን ጊዜ የለም።
ሁለተኛው አስፈሪው የሐሰት ትምህርት አስተማሪዎች ከመሐከላችን እየተነሱ ወይም በውስጣችን ሆነው የሠራዊት ጌታ ሳይናገራቸው “እንዲህ ብሏል” እያሉ በየቤቱ እንደ ጠንቋይ በቀጠሮ ለሰዎች ያልሆነ ተስፋ የሚሰጡና ቃሉንም የሚያጣምሙ ናቸው። በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ትንቢትም ሆነ ሌሎች ስጦታዎች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ሲሆኑ የማንኛውም ማህበረ ምዕመናን በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን መጠቀም ያለብን በረከቶችና የወንጌል ማሠራጫዎችና የምዕመኑ መገንቢያ ናቸው።
ሆኖም በዘመኑ የምንመለከተው ለየት ያለ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ለቃሉ ታማኝ ሆና ትክክል ያልሆነውን መንፈስ ለይታ የመገሰጽ ኃላፊነት አለባት። ባለፉት ዓመታት በጆሮዬ የሰማሁትን ለናሙና መጥቀሱ አስፈላጊ ይመስለኛል። በአንድ ትልቅ ኰንፈረንስ “ተፈውሰሃል፣ እግዚአብሔር ተናግሮኛል” ተብሎ የተነገረላት በጥቂት ወራት ስትሞት አይቻለሁ። በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አንድ እሑድ “ከሽማግሌዎች መካከል በዚህ ዓመት ውስጥ በሞት ይቀሰፋሉ” ያለች ሳይሰምርላት ቀርቶ ሰዎቹ ብዙ ዓመታት ጌታን በማገልገል ቀጥለዋል። በቅርቡ ደግሞ ካላመኑ አንዲት እናት ይደወልልኛል። ሴትዮዋ በጋብቻ የምንዛመድ ሲሆኑ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ “አቶ ብርሃኑ፣ እናንተም እንዲህ ሆናችሁ?” ይላሉ። “ምነው?” ብላቸው፣ “የሠራዊት ጌታ ከካንሰር በሽታህ ተፈውሰሃል ይላል ብላ አንዲት ሐሰተኛ ነቢይ ልጄን ነግራው በናንተ ኢየሱስ እሞኛለሁ ብሎ በሁለት ወሩ ሞተ፤ ይህ ብቻ አይደለም፣ ተፈውሰሃል ባለች በወሩ ቤትዋ እንደገና ሄዶ ሳለ የፈወሰህ ጌታ ለአገልግሎቱ መኪናህን ስጣት ብሏልና ቁልፉን ከነሊብሬው ትተህ መሄድ አለብህ አለችው።” እርሱም ይህንኑ አድርጐ በታክሲ ይመለሳል። ልጁ ሞተ። ታሪኩን ያውቁ ስለነበረ ቤተሰቡ በትርፍ ቁልፍ መኪናውን አስነስተው ተደብቀው ይወስዳሉ። ሐሰተኛዋ ነቢይ ሊብሬውን አልሰጥም፣ ወደ እኔ ስም ተዛውሯል ትላለች። “በል ብርሃኑ፣ የናንተው ጉድ ነውና እርዳኝ” አሉ። እኔም በተለያዩ ሰዎች በኩል ብሞክር አልቻልኩም። አሳሳቢ ዘመን ውስጥ እንዳለን በመገንዘብ በታማኝነት ቃሉን መስበክ አለብን።
መደምደሚያ
በአንድ ቤተ ክርስቲያን የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ እንዲህ የሚል ዐረፍተ ነገር ሰፍሮ ነበር፣ “የቤተ ክርስቲያን መቀመጫ ባዶም ቢሆን ቢሞላ እውነት አይለወጥም፤”
አንድ እሑድ ሰባኪው ኤርምያስ 2329-32 ላይ ያለውን አንብቦ “ትላንት ማታ ይህን መልእክት ሳዘጋጅ የእግዚአብሔር ቃል ልቤን ስለነካኝ በንስሃ በፊቱ ለመውደቅ ተገደድኩ፣ የእግዚአብሔር ቃል ያላለውን እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል ብያለሁ፤ የራሴንም ሕልም የእግዚአብሔር ሕልም አድርጌአለሁ። እግዚአብሔርን ሕዝቡንም በድያለሁ፣ እግዚአብሔር ይቅር ብሎኛል፣ እናንተም ይቅር በሉኝ፣ ከዚህ በኋላ እውነተኛውን ወንጌል እንድሰብክ በጸሎት እርዱኝ” አለ። በሳምንቱ መካከል በየሰው ቤት እየሄደ ይቅርታ ጠየቀ። አንዳንዶች ይህን ማድረግ አልነበረበትም ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ አይ ጥሩ አደረገ አሉ። የመጋቢው ታማኝ መሆን ግን ከዚያን ቀን ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ለውጥና በረከት አመጣ።
የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ግድም እዚህ መጥቼ ሁለት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የተነጋገሩትን አንደኛው ይነግረኝ ነበር። ብዙ ከተጫወትን በኋላ፣ “ኸረ ለመሆኑ ይህን ሕዝብ ስንደልል ስናታልል ስንት ዘመን እንቆያለን?” አለኝ። ይህ አሳሳቢ አነጋገር ኤርምያስ ከተናገረው ጋር ይሄዳል። “የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ሆናለች። ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ። ካህናትም በእነዚያ እጅ ይገዛሉ፣ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ። በፍጻሜውም ምን ታደርጋላችሁ” (ኤርምያስ 530-31)።
ሐዋሪያው ጳውሎስ ለቃሉ ያለውን ታማኝነት በመልእክቱ በማያወላውል ሁኔታ ሲገልጽ እንስማ፣ “እኛ እኰ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ንግድ ዕቃ እንደሚቸረችሩት እንደ ብዙዎች አይደለንም፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተላክን የክርስቶስ አገልጋዮች ሆነን በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት እንናገራለን … አንተ ግን በተማርከውና በተረዳኸው እውነት ጽና፣ ምክንያቱም የተማርከው ከማን እንደሆነ ታውቃለህ … በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አደራ እልሃለሁ። ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም እየመከርህ በትዕግሥትና በማስተማር ጽና። ምክንያቱም ሰዎች ንጹሑን ቃል ለመስማት የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን ለወሬ በመጐምጀት እነርሱ ራሳቸው የሚወዱትን ነገር የሚነግሯቸውን አስተማሪዎች ይሰበስባሉ፣ እውነትን መስማት ትተው ተረትን መስማት ይወዳሉ፣ አንተ ግን በሁሉ ነገር ራስህን ተቆጣጠር መከራን በመቀበል ጽና። የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ ፈጽም። የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደ መሆንህ መጠን የሚገባህን ተግባር ሁሉ አድርግ” (2ኛ ቆሮንቶስ 217፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 314፤ 41-5)።
ነቢያት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሐዋርያትና የቤተ ክርስቲያን አባቶች በታማኝነት ለቃሉ በመቆማቸው ዓለም አልወደደችም፤ እንዲያውም ገድለው ከምድረ ገጽ አስወገዷቸው።፡ ታማኝነታቸው ግን አሁን ለዓለም ይሰበካል። ለምሳሌ፣ እንግሊዛዊው ጆን ዊክልፍ በ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከነበረችበት የስሕተት ትምህርት እንድትመለስ “የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ነች፤ የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ እንጂ ሰው አይደለም… የኃጢአት ሥርየት በገንዘብ ሊሸጥ ሊለወጥ እንደማይችል እወቁ” እያለ ያስተምር ነበር። ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በእንግሊዝኛ ተረጐመ። ይህም ለ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የወንጌል ተሃድሶ ንቅናቄ መንገድ ጠራጊ ሆነ። በዘመኑ የነበረቺው ቤተ ክርስቲያን ግን በዊክልፍ ሥራ ተበሳጨች፤ ትምህርቱንም አወገዘች። በሞተ በ 44 ዓመት ሬሳው ተቆፍሮ ወጥቶ አጥንቱ ተፈጭቶ ዉሃ እንዲወስደው ተደረገ። ቼኮዝሎቫኪያዊው ጆን ሁስም እንደዚሁ የነበረውን የስሕተት ትምህርት በግልጽ በታማኝነት ከቃሉ ጋር እያመሳከረ አስተማረ፤ የቤተ ክርስቲያንም ጉባዔ ተሳስቻለሁ ብለህ ንስሃ ግባ፣ ካድ ብለው አራት ሳምንት ሰጡት። አልክድም ስላለ በእሳት አቃጠሉት።
የአገልጋዩ መንፈሳዊ ሕይወት ጤና ከእግዚአብሔር ጋር በሚያጠፋው ጊዜ መጠን ይለካል። “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ” ይላል። ለቃሉ ታማኝ ለመሆን፣ አገልጋዮች፣ በእግዚአብሔር ፊት መሆን አለባቸው ፤ የእግዚአብሔርን ድምጽ መታዘዝ አለባቸው፤ ለእግዚአብሔር ቃል ቅድሚያ መስጠት አለባቸው (ቆላስይስ 316፤ 1ኛ ሳሙኤል 927፤1ኛ ነገሥት 1222-24፤ የሐዋርያት ሥራ 1346)።
የውይይት ጥያቄዎች
1. ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ታማኝነት ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል?
2. በአፍሪካ የተደረገው የወንጌል ስርጭት መቼና እንዴት ነው?
3. የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ያለፈችባቸውን የስደት ዘመናት ግለጽ። ስደት ደርሶብህ ያውቃል? ምክንያቱስ ምንድነው?
4. ደራሲው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ያጋጠሙትን ሰዎች እንዴት ይገልጻቸዋል? አንተስ በምትገኝበት አጥቢያ እንደዚህ የመሰለ ሁኔታ አጋጥሞሃል?
5. የ”ትልቅ ጉባዔ አስተሳሰብ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ደራሲው አነስተኛ የምዕመን ቁጥር ለምን ይጠቅማል ይለናል?
6. “ዓለማዊነት”፣ “ስመ ክርስትና” እና “የሐሰት ትምህርት” የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
7. የአንድ አገልጋይ ወይም የአንድ አማኝ መንፈሳዊ ጤንነት በምን ይለካል?
(ይህ ጽሑፍ በመጠኑ አጥሯል፤ ዋናውን ቅጂ የሚሹ በ info@ethiopianchurch.org ይጠይቁ)
