መልካም ቀን ቶሎ ና

 

ክፉ ቀን ተወገድ፣ ተወገድ
መልካም ቀን አሁን ና
የታገልከኝ ይብቃ፣ ይብቃ
እኔም ልበል ዘና
የረፍት ጓዝህን፣ እሰይ
ጭነህ ከተፍ በላ

ህመም በዚያ ውጣ፣ ውጣ
ጤና በዚህ ግባ
አንዴ ልረፍበት፣ አንዴ
አንጀቴ አይባባ
ቀና ብዬ ልቁም፣ ልቁም
ጉልበቴ አይላላ

ክፉ ቀን ቶሎ ሂድ
መልካም ቀን ቶሎ ና
ይኸው ብዙ ዘመን
ጐድተኸኛልና
ከንግዲህስ ልጠብቅ
ከቶ አልችልምና

ዛሬ ና፣ ምነው ና
መልካም ጊዜ ሆይ ና
ክፉ ጊዜ ሆይ ሂድ
መንገዴን አታግድ

ክፉ ቀን በርረህ ሂድ
መልካም ቀን በርረህ ና
የሚዋልል ሃሳብ
ልቤ ገብቷልና

 

 
Copyright © August 2007 by Mitiku Adisu.
All rights reserved.

 

 

 

 

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org