የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆችና መሪነት

በፍራንሲስ እስጢፋኖስ

 

ክፍል 3

 

መሪነት

የመሪነትን አጠቃላይ ትርጉምና አጠቃቀም ባጭሩ ከቃኘን በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ ስለ መንፈሣዊ መሪነት ለመረዳት እንሞክራለን። አንዳንድ ጠቃሚ ምሳሌዎችንም እናያለን።

አቶ ንጉሤ ሀብተየስና አቶ ብርሃኑ ብርቄ “የሥራ አመራርና አስተዳደር መርሆዎች፣ ተግባሮችና ዘዴዎች” በተሰኘው መጽሐፋቸው “መሪነት ሰዎችን በማግባባት፣ በፈቃደኛነት ለቡድን ዓላማ እንዲጥሩ ማድረጊያ ጥበብ ነው” ሲሉ አቶ እሸቱ እንደሻው ደግሞ “ሥራ አመራር “ በተሰኘው መጽሐፉ “… ሠራተኞች በቡድን ስሜትና በታታሪነት ለድርጅት ዓላማ መሳካት እንዲሠሩ የሚደረገው የሥራ መሪዎች ጥረት፣ መምራት ወይም አመራር መስጠት ይባላል” ብሎአል።

ሌሎች ከነዚህ ጋር የተቀራረቡ ትርጉሞች አሉ፤ ሆኖም ለዚህ ጽሑፍ አቀራረብ ለጊዜው በቂ ትርጉም ያገኘን ይመስለኛል። እላይ ካገኘናቸው ሀሳቦች “መሪነት” ከፊት ፊት እየሄዱ የሚከተሉትን ሰዎች መንገድ ማሳየት ወይም መምራት ነው ልንል እንችላለን።

መሪ ወደ አንድ ሊደረስበት ወደ ተፈለገ ግብ ተከታዮቹን የሚመራ ሰው ነው።

ወደ ግብም ለመድረስ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎችና ሂደት መሪነት ይባላል። አንድ መሪ እንዲያከናውን የተሰጠውን ድርሻ ለማከናወን የተመደበለትን የሰው ኃይል፣ ገንዘብ፣ ጊዜና መሣሪያ ሳያባክን ምርታማ በሆነ መንገድ እየተጠቀመ በትክክል መሥራት በጊዜና በጥራት መፈጸም አመቺ የሥራ ሁኔታን በመፍጠር መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።

መሪነት የመምራት ዘይቤ ሲሆን፣ ተከታዮችና ሠራተኞች ሊሠሩ ለተዘጋጁት ሥራ በዓላማ ጽናት በትጋትና በውዴታ እንዲሠሩ ማበረታታት፣ ማግባባት፣ ማሳመንና ማትጋትን ያጠቃልላል። መሪነት ተከታዮች ለሥራ እንዲነሳሱ በአንድነትም ወደ ታለመው ግብ የሚያደርስ ሥራዎችን እንዲሠሩ ማስቻልን ያካትታል።

መሪነት የሚከተሉት ዐበይት ክፍሎች አሉት፦

 

·        ዕቅድ ማውጣት

·        ማደራጀት

·        መምራት

·        መቆጣጠር

 

መሪነት አሁን የተጀመረ ሳይንስ ሳይሆን ወዲያውኑ ሰማይና ምድር ሲፈጠሩና ከዚያም በኋላ በተከታታይ ትውልዶች ሲሠራበት የኖረ ጥንታዊ የሥራ አፈጻጸም ዘይቤ ነው።

መሪነትን የሚጠቀሙ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በሰማይ የሚበርሩ አእዋፋት፣ በምድር የሚንቀሳቀሱ አውሬዎች፣ ነፍሳትና በውሃ ውስጥ የሚርመሰመሱት በሕገ ተፈጥሮ የሚጠቀሙት ነገር ነው። ለአብነትም በሰማይ የሚበርሩት ነጫጭ አሞራዎች እንደ መሪ ተከትለው ባንድ መስመር ወይም V በመሰለ ቅርጽ እንደሚበርሩ ተመልክተናል።

ንቦች ሌላ ምሳሌ ናቸው። ዝኆኖች፣ ሳላዎችና ዝንጀሮዎችም ባንድ መሪ የሚንቀሳቀሱ እንደ ሆኑ በገጠር ያደግነው የማየቱ ዕድል አጋጥሞን ይሆናል።

መሪ ተከታዮችን ያስተባብራል፣ አንድ ያደርጋቸዋል። ባንድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ሰዎች በየአቅጣጫው እንደ ተሰጣቸው ድርሻ እየሠሩ ያነሰ ውጤት እንዳያስገኙ ወይም ውጤት አልባ እንዳይሆኑ ድርጅቱ የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት ትልም ባለው የሥራ አፈጻጸም እንዲሠሩ የሚያስተባብር ሰው ነው።

1. መንፈሳዊ መሪነት

ከላይ መሪነትን በተመለከተ አጠቃላይ ትርጉሙን ለማየት ሞክረናል። ቀጥሎ የመንፈሳዊ መሪነትን ትርጉም እንመለከታለን።

መንፈሳዊ መሪነት፣ መንፈሳዊ መሪ የሚፈጽመውን ተግባር ያመለክታል።

መንፈሳዊ መሪ የሚመራቸውን ሰዎች ወደ መልካም ሥፍራና ወደ ተሟላ ሕይወት የሚመራ ሰው ነው። ከአደጋ የሚከላከል፣ የሚመግብና የሚጠብቅ ነው። ለሰዎች በጎ በጎውን የሚያስብ፣ የሚጠነቀቅና ኑሮአቸው መልካም እንዲሆን ሕይወቱን እንኳ የሚሰዋላቸው ንቁና ታታሪ ሰው ነው። (መዝሙር 23)

መንፈሳዊ መሪነት በመጀመሪያ ደረጃ አገልጋይነት ነው። ይህንን ሃሳብ ለማጠናከር ሮበርት ግሪንሊፍ “ታላቅ መሪ በመጀመሪያ ደረጃ እንደ አገልጋይ የሚታይ ነው” ሲል ተናግሮአል።

አንድ ሰው ለመሪነት ተግባር ሲፈለግ ለማገልገል መጠራቱን መረዳት አለበት። መንፈሳዊ መሪነት እራሱ አስቀድሞ እየሠራ፣ እያሳየ ምሳሌና አርኣያ የመሆን አገልግሎት ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን አንድ ባንድ ሲጠራቸው “ኑ ተከተሉኝ የሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” ባላቸው ጊዜ እርሱ ከፊት ፊታቸው እየሄደ እያስተማረ፣ መንገድ እያሳየ፣ ሰዎችን እንዴት ወደ ንስሐ እንደሚጠሩ፣ የወንጌልን የምሥራች እየሰበከ፣ የተራቡትን እየመገበ፣ የታመሙትን እየፈወሰ፣ ሙታንን እያስነሣ በተግባር አሳይቶአቸው ነበር።

ስድቡን፣ ስደቱን መከራውን፣ ስቅለቱን ሞቱን ሲቀበል የወንጌል አገልግሎት ደስታ ብቻ አለመሆኑን ለማሳየት እራሱ በሁሉም የአገልግሎት ሁኔታዎች በማለፍ መልካምና ታማኝ ምሳሌ በመሆን አሳይቶአቸዋል። (ማቴዎስ 4፡19፤ 5፡13፤ ማቴዎስ 27፡28)

መልካም መንፈሳዊ መሪ ለሚሠራው ሥራ ራእይ ሊኖረው ይገባል። መንፈሳዊ መሪ የሥራ ተነሳሽነት አለው፤ መልካም ሃሳብ ያመነጫል፤ መዋቅር ይዘረጋል፣ ዕቅድ ያወጣል፤ ሥራው የሚሠራበትን ስልት ይነድፋል፤ በተግባርም ይተረጉማል። (ነህምያ)

2.  መንፈሳዊ መሪነት የሚከተሉት መለኪያዎች ሊኖረው ይገባል


 

·        ብልኅና መካር (1ኛ ዜና 26፡14)

·        ትጉህና ብርቱ ሠራተኛ

·        ጥበብና መንፈስ የሞላበት

·        በመልካም የተመሰከረለት

·        እምነትና መንፈስ ቅዱስ ያለው (የሐዋርያት ሥራ 6፡1-6)

·        የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ኪዳኑንም የሚጠብቅ (ዘፀአት 19፡5)

·        አዋቂ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የታመነ፣ የግፍን ረብ የሚጠላ (ዘፀአት 18፡21)

·        የልብ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ ቆራጥነትና ትጋት ያለው (1ኛ ሳሙኤል 16፡6-13)

·        የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣

·        ልከኛ፣ ራሱን የሚገዛ፣ እንደሚገባ

 የሚሠራ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለማስተማር የሚበቃ (1ኛ ጢሞ3፡1-7፤ ቲቶ 2፡1-3)

·        መንፈሳዊ መሪ ትሑት፣ ልቡ በርኅራኄ የተሞላ፣ የምዕመናን አገልጋይ የሆነ ነው (ዮሐንስ 13፡1-17)

·        “የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአልና” (ማቴ 20፡28)

·        “በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፣ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን” (ማር.10፡42-45)

 

ጌታ ኢየሱስ መንፈሳዊ መሪ አገልጋይ እንጂ ተገልጋይ እንዳይደለ ሲያስተምር የሚከተለውን ብሎ ነበር፣

 

“እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፣ ትክክል ነው። እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።” (ዮሐንስ 13፡2-17)

3. የመንፈሳዊ መሪ ዋና ዋና ተግባራት

ሀ. ጥሪውን ማወቅ

ነቢዩ ኢሳይያስ፣ እግዚአብሔር የዘላለም ቅዱስ ለብርቱ ሥራ ወደ ሕዝቡ ሊልከው መፈለጉን በመረዳት እንደ ቀደሰው በእሳትም እንዳነጻው፣ እንዳዘጋጀው ከዚያም “የጌታ ድምጽ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልኛል?” ሲል መስማቱን እርሱም “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” እንዳለ እግዚአብሔርም መልእክት ሰጥቶት ወደ ኃጢአተኛና አመጸኛ ሕዝብ እንደ ላከው በራእይ ማየቱን ይናገራል። (ኢሳይያስ 6፡8-13)

ኢሳይያስ እግዚአብሔር ሲጣራ ሰማ፣ የእርሱም መልእክተኛ ለመሆን አገልግሎቱን ተቀብሎ ወጣ።

ሳሙኤል ገና ብላቴና በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር ጠርቶታል፣ ብርቱ መልእክትም ሰጥቶት ወደ ዔሊ ልኮታል። ከዚያም ለእግዚአብሔር በመታዘዙ በእስራኤል ላይ መሪ፣ ዳኛ፣ ነቢይ አድርጎ እንደ ሾመው ከ1ኛ ሳሙኤል የመጀመሪያ ምዕራፎች ላይ እናነብባለን።

እነዚህ ሁለት ታላላቅ መሪዎች የቀረበላቸውን ጥሪ በማወቅና በመቀበል የተጣለባቸውን ብርቱ አደራ በጥንቃቄ የተወጡ በመሆናቸው ለኛም መልካም ምሳሌ ናቸው።

ለ. ለተጠራለት ተግባር ትኩረት መስጠት

ሳውል በተጠራ ጊዜ እንዲህ የሚል ቃል ለሐናንያ ተሰጥቶት ነበር። “ሂድ ይህ ሰው በአሕዛብና

በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው”

(የሐዋርያት ሥራ 9፡15)። ሳውል ኋላም ጳውሎስ በመባል የሚታወቀው ታላቅ የሚስዮናዊ ጉዞዎችን በማድረግ ለተጠራለት የወንጌል አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠት ወንጌልን ሰብኮአል። ቤተ ክርስቲያንን ተክሎአል፤ አስተማሪዎችንና ሽማግሌዎችን አደራጅቶአል። ለሰዎች መዳንም በጣም ያስብ ነበር።

ሐ. የዳኑትን ደቀ መዝሙር ማድረግ

ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስንና ቲቶን ወደ ጌታ ካመጣቸው በኋላ አስተማራቸው፣ እነርሱም ደግሞ እንደዚሁ ወጥተው ወንጌልን እንዲያስተምሩ ቤተ ክርስቲያንን እንዲተክሉ፣ ሽማግሌዎችን እንዲሾሙ አዘዛቸው። (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡2-5፤ ቲቶ 1፡5-9)

መ. መሪ መተካት

መልካምና ታማኝ መሪ ሥራው እንዳይቋረጥ ወጣትና ታማኝ መሪዎችን ያዘጋጃል፤ ያስተምራል፣ ያሰማራል። ለዚህ መልካም ምሳሌ ጌታ ኢየሱስ እና ሐዋርያው ጳውሎስ ናቸው።

ሠ. መመገብና ማሳደግ

ቅንና ታማኝ መሪ ተከታዮቹን በጤናማ ትምህርት ያሳድጋቸዋል፤ ከመጥፎ ሕይወትና ኑሮ የሚጠበቁበትን ስልት አዘጋጅቶ ተግባራዊ ያደርጋል።

ረ. የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንና ቤተ እምነቶችን ራእይ እውን ማድረግ

አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖችና ቤተ እምነቶች ጤናማና ታማኝ የሆኑት መንፈሳዊ መሪዎችን ማደራጀት ማስተማርና በኃላፊነት እየመደቡ ሊያሳድጉና ሊያበረታቱ ይገባል።

ቁጥራቸው አነስተኛ ያልሆኑ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንና የቤተ እምነት መሪዎች ተተኪ መሪዎችን ለማዘጋጀት ሲያቅዱና እቅዳቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ እምብዛም አይታይም። ይህም በወንጌልና በቀለም ትምህርት ባልሠለጠኑ፣ ባልተጠሩና ባልተላኩ ሰዎች እጅ የወንጌል ሥርጭት እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል። እነዚህም ያልተማሩ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ሊመሩ የሚችሉት በመልካም ሁኔታ ነው ብሎ ለማመን ያዳግታል።

ሰ. መሪ በመሆን መልካም ምሳሌ ማሳየት

መልካም መንፈሳዊ መሪ የተከታዮቹ አገልጋይ ነው፤ እራሱ እየመራና እየሠራ የሚያሳይ፣ በሥራ ትጉ የሆነ፣ ኃላፊነትን የሚያከፋፍል፣ በዕቅድ የሚሠራ፣ ሥራን የሚቆጣጠር፣ መምከር፣ ማበረታታትና ማነሳሳት የሚችል ሰው ነው። ነህምያ ለዚህ መልካም ምሳሌ ነው።

4. ሊጠየቁ የሚገባቸው ጥያቄዎች

ተከታዮቹ ጤናማ አካላዊ፣ ስነ ልቡናዊ እድገት ያሳያሉ? በጤና፣ በማህበራዊ ኑሮና በኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከነበሩበት የተሻለ ሁኔታ ይታይባቸዋል? በተሻለና በተጠናከረ መንፈሳዊ እድገት ላይ ይገኛሉ? በመንፈሳዊ መሪው የአገልጋይነት ባህሪያት ይታዩበታል? መሪው እራሱን እያደለበ ተከታዮቹን እያቀጨጨ እያዳከመ ነው? በኑሮ ዝቅተኛ የሆኑ ኑሮአቸው ተሻሽሎአል? በሰይጣን አምልኮ የተያዙት ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸው ይቀበላሉ? ጌታን የተቀበሉ ጤናማ የሆነ የሕይወት ቃል ይመገባሉ? በምዕመናኑ መካከል ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት አለ? መሪዎች ጊዜአቸውን የሚያጠፉት በስብሰባና ውጤት አልባ በሆነ ክስ ነው? ተከታዮቹ ስለ መሪዎቻቸው ምን ይላሉ? መሪዎች የሚተኩአቸውን በዕቅድ ያዘጋጃሉ? መሪዎች ስለ ገንዘብና ስለ ሥልጣን ያላቸው አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይስማማል? መሪዎች ሌሎችን የሥራ ኃላፊዎች ሲመርጡ እንደ እግዚአብሔር ቃል በጥንቃቄ ነው?

5. የመንፈሳዊ መሪ ስህተቶች


 

·        እግዚአብሔር ጥበብና ማስተዋል እንዲሰጠው አለመጠየቅ

·        አለመጸለይ

·        ከተከታዮቹ መራቅና ምክር ለመቀበል አለመፍቀድ

·        አምባገነንነት

·        ኃላፊነቱን እንደሚገባ አለመከታተል

·        ራእይ ማጣት

·        የዕቅድ፣ የድርጅትና የስልት አሠራር አለመጠቀም

·        ኃላፊነትን አለማከፋፈል

·        በአንድ ዓላማ ዙሪያ አስተባብሮ አለማሠራት

·        የተጠራለትን ኃላፊነት ለግላዊ ፍላጎት መረማመጃና መጠቀሚያ ማድረግ

·        የእግዚአብሔርን ቃል ጥናት ችላ ማለት

·        ከገንዘብ ፍቅር፣ ከሥልጣን አምሮት፣ ከሥጋ ፍትወት አለመሸሽ


 

6. ከመንፈሳዊ መሪ የሚጠበቁ ባህሪያት

“እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በታማኝነትና በፍጹም ልብ … በፍቅር …ሰውን ሳይሆን ጌታን በሙሉ ልብ … በጸጋ ማገልገል” (2ኛ ዜና 19፡9፤ መዝሙር 2፡11፤ ገላትያ 5፡13፤ ኤፌሶን 6፡7፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡10)

 

የውይይት ጥያቄዎች

 

1. የመንፈሳዊ መሪ አመራር መንፈሳዊ ካልሆነ መሪ አመራር በምን ይለያል?

2. መንፈሳዊ ሳይሆኑ መልካም አመራር የሰጡ መሪዎች አሉ?

3. ከአንድ መልካም መሪ ሊታጡ የማይገባቸውን ሦስት ባህሪዎች ጥቀስ።

 

 

ቄስ ፍራንሲስ እስጢፋኖስ የቤተክርስቲያን መሪና የአዲስ ሕይወት አገልግሎት ዳይሬክተር ናቸው። ይህ በሦስት ክፍል ከፋፍለን ያቀረብነው ጽሑፍ ደራሲው “የጽድቅ ፀሐይ ለኢትዮጵያ” የመሪዎች ሴሚናር ላይ ከሐምሌ 19-20/1994 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መካነ ኢየሱስ ሴሚነሪ ካስተማሩት ላይ በፈቃድ የተወሰደ ነው።

 

 

 

 

 

 

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org