የወንጌል ስርጭትና እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ

በምትኩ አዲሱ

መግቢያ

ዝማሬና ምስሎች የቆዩ የወንጌል ማሠራጫ መሣሪያዎች ናቸው። መጻፍና ማንበብ በተስፋፋ መጠን ደግሞ ይኸው ወንጌል በስነ ጽሑፍ ጭምር እየተሠራጨ ካለንበት ዘመን ላይ ደርሷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጽሑፎች በተለያዩ ርዕሶችና ቀለማት እያሸበረቁ በማኅበራት ዓይነትና ቁጥር ለተጠቃሚው እየቀረቡ ነው። ዝማሬም በክራር ጊታርና ኪቦርድ እየታጀበ፤ በቴፕ ክር፣ ሲዲ ቪዲዮ ዲቪዲና ኢንተርኔት እየታተመ በመሸጥ ላይ ይገኛል። ዕድገት ሲባል እንግዲህ ምልክቱ ይኸ ይሆን? ይኸስ በወንጌል መልእክት ላይ ምን ለውጥ እያስከተለ ነው?

ከቀድሞው ይልቅ ዛሬ የተጠቃሚው ምርጫ ሰፋ ያለ ይመስላል። የተለያዩ ድምፆችን መስማት ውዥንብር ሊፈጥር ቢችልም፣ በዚያው ልክ የአንባቢውን ውሳኔና የመለየት ልምድ እንደሚያዳብር መገመት አያዳግትም። ይህ አዲስ ክስተት በአብያተ ክርስቲያናት አስተዳደር፣ በአዘጋጅና አታሚ ክፍል ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል። ጫናው፦ የወንጌል መልእክት ሳይሸቃቀጥ በግልጽ ለአንባቢው ቀርቧል? መጽሔቱን ወይም መጽሐፉን አዘጋጅቶ ለማቅረብ ወጪ የተደረገበቱ ምክንያት በቂ ነው? ለአንባቢው የአእምሮና የገንዘብ አቅም እንደሚስማማ ተደርጐ ወንጌላዊ ጽሑፎችን በተከታታይ ማቅረብ ተችሏል? የሚል ነው።

የአገራችን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች አቀራረብ ልዩ ልዩ ቢመስሉም ባንድነት ሲታዩ ከልዩነታቸው ይልቅ ተመሳሳይነታቸው ጐልቶ ይወጣል። እንግዲህ በሚቀጥሉት አንቀጾች ባለፉት አርባ ዓመታት በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በአማርኛ ታትመው ከወጡት መጽሔቶች፣ መጻሕፍትና መዝሙራት ውስጥ የጥቂቶቹን ይዘትና አቀራረብ መርጠን እየመረመርን እግረ መንገዳችንን ሌሎች ጉዳዮችን እንቃኛለን።

ይህ ጽሑፍ አራት ፅንሰ አሳቦችን የተመረኰዘ ሆኖ ሁለት ዐቢይ ክፍሎች ይኖሩታል፤ የመጀመሪያው አሳብ፣ የዳበረ የማንበብ ባሕል የለንም፣ የሚል ይሆናል። ለዚህም በዋነኛነት ተጠያቂ የሚሆኑት መሃይምነት፣ ያልተያያዘ የመንግሥት አመራር፣ መማርና ሥራ አጥነት መጣመራቸው፣ ጌታ በአእምሮም እንደሚመለክ አለመገንዘብ፣ ስንፍና፣ የገንዘብ እጦት፣ ለሰው አቅምና ፍላጎት የተመጠነ የጠራ ጽሑፍና የንባብ ቤቶች አለመኖር ናቸው። የሁኔታዎች አለመመቻቸት የሚለውን አሳብ እዚህ ውስጥ አንጨምርም፤ ምክንያቱም ሁኔታን ማመቻቸት የግለ ሰቡ ፋንታ ስለሚሆን። ሁለተኛው፣ የቴክኖሎጂ መራባት የነበረውን ሁኔታ አባብሶታል፣ የሚል ነው። ከሚነበበው ይልቅ በቪድዮ፣ በቴፕ፣ በሲዲና በዲቪዲ ለሚታየውና ለሚደመጠው ትኩረት ተሰጥቶታል። ለቴክኖሎጂና ለመድረክ አገልግሎት የተሰጠው ድርሻ በብብታችን ይዘነው የኖርነውን መጽሐፍ ቅዱስ ሳያስጥለን አልቀረም ብለን እንፈራለን። የግለ ሰቦችና የቤተ ክርስቲያን በጀት ብዙሃኑ ወደሚገኙበት አቅጣጫ ሳይሆን የጥቂቶችን ፍላጐት የሚከተል ሆኗል። ሦስተኛው፣ ከአገራችን ባሕልና ክርስቲያናዊ አመለካከት ጋር የማይጣጣም ተቀጥላ-ብዙ ግርግር አስተሳሰብ ሾልኰ ተዛምቷል፣ የሚል ነው። አራተኛው፣ ያለማንበብ ባሕል መዝሙራትን ዋነኛ የወንጌል ማሠራጫና የሥነ መለኰት ዕውቀት መገብያ አድርጓቸዋል። እንደዚሁ የዘማሪያን ድርሻ ከምን ጊዜውም ይልቅ ከባድና ለፈተና የተጋለጠ ሆኗል። ክብደቱና ፈተናው እነዚህን ጥያቄዎች የተከተለ ይሆናል፦ ዝማሬአቸው የብዙ ጸሎት ፍሬ ነው? ለቤተ ክርስቲያን የተገዛና በቃሉ የታነጸ ሕይወት ፍሬ ነው? ወይስ የቴክኖሎጂ የንግድና የአቋቋም? የሚል ይሆናል። በዚህ ጽሑፍ ላይ ለዚህ አገልግሎት ልዩ ትኩረት እንሰጣለን። መነሻ አሳባችን በዓመታቱ መካከል የተከናወነውን መልካም ሥራ ለመካድ አይደለም። ነገር ግን አዝማሚያቸው የማያምር ክስተቶች እንዳይቀጥሉ ለማሳሰብ ነው፤ ለማስጠንቀቅ ነው። በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ያለብንን ድርሻ በጥራት ለማከናወን ይረዳ ዘንድ ነው። አንባቢው በዚህ መንፈስ ማንበብ ይጠበቅበታል። ይህንኑ ጉዳይ በተለያዩ ርዕሶች እንደሚከተለው ከፋፍለን እንመለከታለን።

ክፍል አንድ፦ መሠረታዊ ግንዛቤዎች

1. የመጽሔቶች ገጽ አጠቃቀም

የድሮ መጽሔቶች ገጽ አጠቃቀም በክርስቲያን ስነ ጽሑፍ ምድረ በዳ ውስጥ እንደ ከረምን ጉልህ ማስረጃ ናቸው። ርዕሱ ብቻ የገጹን ሲሦ ወይንም ሩብ ያህል ሞልቶ የታየባቸው እትሞች ጥቂት አይደሉም። አንዳንዱንማ ገጽ ከጽሑፉ ጋር የማይገጥም ፎቶ ሲታገለው ይታያል። ወይንም ዝምታን እንደመረጠ ሰው ገጹ ባዶውን ተትቷል። “መጽሐፉም ዝም” ያሰኘ ይህን የመሰለ ሁኔታ ይሆን?

2. የማይመስል ምስል

ምስሎች ምዕራባዊነትን ወደ ማንጸባረቁ ያደላሉ። ታሪኩ የሚያወሳው በሰሜን አሜሪካና በአውሮጳ የተከሰተውን ለማስረዳት ከሆነ ምናልባት አይገርም ይሆናል። ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ፣ ጸሎተኛው፣ ተራሮችና ወንዞች፣ የቤተ ክርስቲያን አዳራሽ፣ ወዘተ ምዕራባዊነትን ሲያንጸባርቁ ግን ጥያቄ ይፈጥርብናል። እርግጥ፣ የፎቶ አነሳስና ዝግጅትን አለመሟላት ሊያመለክት ይችላል። ያም ቢሆን፣ ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ በባሕል ሆነ በመልክ ምዕራባዉያን አይደሉም። ወይም አንገሸግሿቸው ሊያስረዱ እንደሞከሩት ጥቁሮች ወገኖቻችን እነርሱንም አይመስሉም። አይሁዳውያን ናቸው፤ ምሥራቃውያን ናቸው፤ ሜዲተራኒያን ናቸው።

3. የስም አጠራር

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጸሐፊዎችን ስም እስከ አያት መጥቀስ ተጀምሯል። አከራካሪ ጉዳዮች ሲኖሩ ደግሞ የአስተያየት ሰጪው ስም አይገለጽም። ለምን ይሆን? የማይለቅቀን ድብቅነት ይሆን? በእግዚአብሔር ቤት ክልል ሆነን አሳባችንን መግለጽ ስለምንፈራ ይሆን? የብርሃን ልጆችን በዓለም ካሉት እንግዲህ ምን ይለያቸው? የትምህርት ደረጃንም እንደዚሁ መጥቀስ እየጨመረ መጥቷል። አብያተ ክርስቲያናት ዘመናዊውን ትምህርት በተለይም ሥነ መለኰትን በጥርጣሬ እንዳላዩ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በዚያው ልክ የእውነት ሚዛን አድርገውት ይሆን? ምድራዊ ሹመት ከጥሪ እኩል እየመዘነ ይሆን? ለመደመጥና ለመታመን የሥልጣን ምንጭ ተደርጐ ይሆን? ይህን ስንል መማሩን ለማቃለል ሳይሆን ሚዛኑን አለመጠበቅ በሁለቱም ወገን ይኖራል ለማለት ነው።

4. በምሳሌና በዕደ-ጥበብ

ምሳሌዎችንና አርአያነትን ከውጭ የመኰረጅ ዝንባሌ ይታያል። ስንቶች ናቸው የአገራችንን የሙዚቃ ባሕልና መሣሪያ ጠንቅቀው የሚያውቁ? ፈር ቀዳጁ ዘማሪ ደረጀ ከበደ በክራርና በበገና ታጅቦ የዘመረ ሰሞን ለብዙዎች ጥያቄ ፈጥሮ እንደ ነበረ ይታወሳል። እኛው በኛ እንጂ ከሌላ አንማር አንልም። መኰረጅ ግን ባጠቃላይ የአገራችን የተማረው ክፍል አባዜ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም። በአቅራቢያ ያለውን አለማወቅና መናቅ ወይም ማዛባትና መርጦ ማግነን። የውጪውን ማዳነቅ። ከውጭ ያገኘውን ከአገሬው ሁኔታ ጋር አለማዛመድ። በአካል እዚህ በአስተሳሰብ እዚያ። ወይም ከነአንካቴው በአካልም በአስተሳሰብም እዚያው። ክርስትና ከፈለቀባቸውና ከተደራጀባቸው ምድሮች ማለትም ከግሪክ፣ ከግብጽ፣ ከእስራኤል፣ ከቱርክ፣ ወዘተ ተጐራብተን እያለ የስነ-መለኰትን ትምህርት ለመቅሰም አሥር ሺህ ኪሎ ሜትር ወደ አሜሪካ መጓጓዝ ሊያስገርመን ይገባል። ያገራችንንስ ጥንታዊ እምነት ምን ያህሉን ከትውልዱ ጥያቄና ከሐዲስ ትምህርት ጋር አዛምደናል? ይህን ያነሳነው ለትዝብት ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ለማሳሰብ ጭምር ነው።

ከላይ እንደ ጠቀስነው የዘመኑ ቴክኖሎጂ የቤተ ክርስቲያንን አምልኰ ሥርዓት እየለወጠው ነው፤ ከመስማትና ከማንበብ ይልቅ በሚታየው ላይ ከሚገባው በላይ ያተኰርን ይመስላል። ይህስ እምነታችንን ምን ያህል እየሸረሽረው ይሆን (ሮሜ 1017)? እንግዲህ የመጣው ለውጥ ለበጐ ብቻ ነው ማለት ያዳግተናል። ቴክኖሎጂ የወንጌልን ስርጭት ለማፋጠን ይረዳል ይባላል። አባባሉ እውነትነት ባያጣውም፣ በጭፍኑ ከማግበስበስ በቅድሚያ እነዚህን ነጥቦች አብሮ መመልከት ያሻል፣ እንላለን።

· የቴክኖሎጂ ዕድገት ለምዕራቡ ማኅበረ ሰብ ምን ዓይነት መንፈሳዊ ዕድገት አስገኝቷል? ከአሜሪካ ወንጌል አማኞች መካከል ከ መቶ 67ቱ “ፍጹም እውነት የለም” እስከ ማለት የደረሱት ከቶ ለምን ይሆን? ወንጌል አማኝ ያልሆኑ ከመቶ 70ው እጅ እንደ አማኞቹ “እውነት እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ ነው” ማለታቸው ምን ሊያስተምረን ይገባል? ባጭሩ፣ ከስህተታቸው ልንማር እንጂ ስህተታቸውን ልንደግም ግዴታ የለብንም! · በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስጥ ምን ያህሉ የወንጌል መልእክት ለቴክኖሎጂው እንዲመች ሲባል ተድበስብሶ ቀርቷል? ወይም ትርጉሙን ለውጧል? · ምን ዓይነት መልእክት ነው የሚሠራጨው? ለማንስ ነው የሚሠራጨው? የአብዛኛው ምዕመን ኑሮ ጥቂቶች ከደረሱበት የ”ሥልጣኔ” ደረጃ የራቀ እንደሆነ እንገነዘባለን? በየቤተ ክርስቲያናቱ ለቴክኖሎጂ የሚወጣው ወጪ ጠቃሚነት እንደገና መጠናት አይኖርበትም? ቴክኖሎጂው የተፈለገው ግለ ሰቦችን ለማክበርና ለማጉላት እንደሆነስ? ስለተገኘና ስለተቻለ ብቻ መልካም ነው ማለት ነው? “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ” (1ኛ ቆሮንቶስ 1023-24)። · በቴክኖሎጂ ወንጌልን የሚያሠራጩ ተጠሪነታቸው ለማን ነው? በሚያሠራጩት መልእክት ሳቢያ ለሚፈጠረው የገንዘብ ይሁን የሞራል ወይም የስነ-ልቡና መዛባት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ይቻላል? · እርስ በርስ በአካል በመገናኘት ውስጥ የሚኖረውን ኅብረት ያጐሳቁለዋል ወይስ ያዳብረዋል (ዕብራውያን 1025)? ምዕመን የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያነብ ያበረታታል? · “ሁሉ ለማነጽ ይሁን … ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን … ሁሉ ለጌታ ክብር ይሁን” የሚለውን መስፈርት ያሟላል?

5. ትችት ወይስ ነቀፌታ?

ምንም እንኳ የትችት ባሕል በቤተ ክህነት ሊቃውንት ዘንድ የተለመደ ቢሆንም፣ በተለይ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ክልል የጽሑፎች ግምገማና ትችት ልምድ ይጐድላል። ትችት ሲባል ነቀፌታ እንጂ ክርስቲያናዊ ምግባር እንደሆነ አይታሰብም። ይህ ስህተት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የስነ-ጽሑፍ ትችት ለደራሲው እድገት፣ ለአንባቢው ጥቅምና ለስነ-ጽሑፍ ልማት አማራጭ የሌለውና ሊዳብር የሚገባ አገልግሎት ነው። በመጽሐፎች ሽፋን ጀርባ ላይ የሚሰነዘሩት አስተያየቶች በአብዛኛው መሞጋገሻና መወዳጃ ይመስላሉ። ይኸው የተመሰከረለት መጽሐፍ ሲገለጥ ግን ግድፈቶችን ብቻ ሳይሆን በተደጋገሙ ገጾች፣ ባልተብላሉ አሳቦችና ከአንድ መጽሐፍ አቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች ታጭቆ እናገኛለን። እርግጥ ጥራት ያላቸው መጽሐፍት አይጠፉም።

በመሠረቱ፣ የአንድ ጽሑፍ ግምገማ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይኖርበታል። የጽሑፉ መነሻ አላማና ዋነኛ መልእክት ባጭሩ ምንድነው? የደራሲውስ ብቃት? ጸሐፊው የተነሳበትን አላማ በሚገባ አስረድቷል? ዓይነተኛና ትክክለኛ መረጃዎችንና ምሳሌዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሟል? በዚህ ጉዳይ ላይ የማናውቀውን አዲስ መረጃ አቅርቦልናል? ሊታከል ወይም ሊታረም የሚያስፈልግ ነገር አለ? የተራ አንባቢውን የመረዳትና የባሕል አቅም እንደሚገባ ተገንዝቧል? ባጠቃላይ የጽሑፉ ጠንካራና ደካማ ጐን የቱ ላይ ነው?

የግምገማው ነጥብ ቅደም ተከተል እንደ ጽሑፉ ዓይነት ሊለወጥ ይችላል። ገምጋሚውም ራሱ በግምገማው ስለሚገመገም ጥናቱን በተመለከተ ጥንቃቄና ጥልቅ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል ማለት ነው።

6. ዘወርዋራ መንገድ

ባሕላችን ስላላደለን ይሁን ሌላ፣ በቀጥታ መነጋገርን አንመርጥም። ከቀጥተኛና ቀላል አገላለጽ ይልቅ ዘመናዊው፣ ሰሞነኛው ዘወርዋራውና ሰወርዋራው ይመረጣል። ጠጠር ማድረግ የጸሐፊውን አስተሳሰብ እንደሚያረቅቀው ይገመታል። ለምሳሌ፣ ሰላሣ አመት ከማለት “ሶስት አስርታት” ይላል። “ኤክሊሺያ” ይላል፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ማሕበርን ወይም ጉባዔን ለማመልከት። የማይወራረስ እስካልሆነ ድረስ ቃሉ ተመጣጣኝ ትርጉም እንኳ ባያገኝ በሐረግ ማስረዳት ሲቻል ማለት ነው። “ከወዲሁ” “በነቂስ” ወዘተ ሌሎች ቃላት ናቸው። “አመታትን አስቆጥሯል” (ብዙ አመታት ሆኖታል፣ ለማለት)። “አባባል” ከ “ብሂል” አይቀልም? አይቀርም ለማለት “አይቀሬ ነው” ይላል። የእንግሊዝኛውን አባባል እንዳለ ይቀዳዋል፦ “እንዳስቀመጠው” (as he put it)፤ “ለማንሳት የፈለግሁት ነጥብ” (the point I want to raise)። “ሶሻል አክሽን” ይልና በእንግሊዙ (social action) ይለዋል። “ጥላ ጉሰማ” (shadow boxing):: ወይም “ተላላፊ በሽታ” ን በቅንፍ “ኰሚዩኒካብል ዲዚዝ” ይለዋል። እንግዲህ ይህ የሚያስረዳው ጸሐፊው ሊለው ያሰበውን አብላልቶ የራሱ አላደረገውም፣ አላገናዘበውም፣ የአንባቢውን አቅም አልመጠነም፣ አሳቡና ምሳሌው የውሰት ነው ማለት ነው። አንዳንዴማ የተጻፈውን ለመረዳት ወደ እንግሊዝኛው መልሶ ከዚያ ወደ ገዛ አማርኛ መተርጐሙ ሳይቀና አይቀርም። በ1964 ዓ.ም. በታተመው ቁ.106፣ ገጽ21 ምስክረ ብርሃን መጽሔት ላይ የተመለከተውን የ አስፕሪን ማስታወቂያ እንደ ምሳሌ ልጥቀስ፤ እንዲህ ይላል፦

“…መላው ዓለም እንደሚያውቀው አስፕሪን ከስቃይ ያድናል” ይላል (በማስታወቂያው ላይ “ስቃይ” ለእንግሊዝኛው pain ፍቺ መሆኑ ነው)፤ ራስ ምታት ወይም ቁርጥማት የተሰማው ሰው እንግዲህ “ከስቃዬ እንዲያሳርፈኝ እስቲ ይህን ልዋጥ” ቢል ቤተ ዘመድ ዝም ብሎ ያየዋል ማለት ነው?

ስለ ጌታ ዳግመኛ መምጣትና ስለ “መነጠቅ” ሲያወሳ በቅንፍ እንደገና የእንግሊዞችን ቃል (rapture) ብሎ ይጨምራል። አንዳንዴም ትርጉሙን ከናንካቴው አሳስቶ rupture ይለዋል። አስፈላጊነቱ ግልጽ አይደለም። አንባቢው ቀጥ ብሎ እንዳይረማመድ ንባቡን እንዳይቀጥል ደንቃራ መሆን ነው። “መነጠቅ” የሚለው ቃል ከእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ይልቅ ለአስተሳሰባችን የቀረበ ነውና። ስለሆነም፣ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መዋስ አይኖርብንም። ይህን ማስታወስ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪ፣ የእንግሊዝኛ ቃላት በየአንቀጹ መመሳጠር ጽሑፉን የምሑራን ሹክሹታ አስመስሎታል። ይህም በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይወሰን በአገር መሪዎችም ላይ ተደጋግሞ የሚታይ ልማድ ነው።

አንድ ጽሑፍ የሚያስተላልፈው መልእክት ሊኖረው ይገባል። በአድማጩ ወይም በአንባቢው ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከታሰበ ማለት ነው። ወደ አንድ የሃሳብ አቅጣጫ ለመምራትና መተማመንን ለመፍጠር ከተፈለገ ማለት ነው። አለዚያ ጥረቱ ከንቱ ይሆናል። ሰው የሚታመነው በራሱ ድምጽ ሲናገርና ራሱን ሆኖ ሲቀርብ ነው (ዮሐንስ ምዕራፍ 9 ላይ የተፈወሰዉን ዕውር ምልልስ ይመልከቱ)። የሰው ውበቱ የሚታየው ሳያስመስል ራሱን ማቅረብ ሲፈቅድና ሲችል ነው። ነጻነቱ ኃይሉና ሥልጣኑ በዚያ ውስጥ ነው። አነጋገሩና የድምጹ አሰባበር እንደ ሌላ ሰው መምሰል ከጀመረ ወይ ይቀልዳል ይባላል፣ ወይም ጤና የለውም ያሰኛል። አይታመንም። የ 1966 አብዮት ያባዛው አንድ ነገር ቢኖር ይህን የመሰለውን ሁኔታ ነበር። ተናጋሪው የሚናገረው ነገር በአብዛኛው ባዕድ ነው። በንግግሩና በአለባበሱ ሳይቀር ራሱን አይመስልም። ሌላ ሰው ሆኖ ይቀርባል። በቤተ ክርስቲያንስ ውስጥ ከተለመደው ተፈጥሮአዊ ባሕል ውጪ “መንፈሳዊ” የሚያስመስል ድምጽ፣ ቋንቋና አኳኋን አይታይም?

ወንጌልን ለተገነዘበ ግን መልእክቱ ለመላእክት ወይም ለተለዩ ሰዎች ሳይሆን ለተራው ሰው በተራ ቋንቋ ቀርቧል። ኢየሱስ አምላክ ሆኖ ሳለ የባሪያን መልክ ለብሶ መጣ (ፊልጵስዩስ 21-10)። አዋቂውም ሕጻኑም ግሪኩም አይሁዱም ሴቱና ወንዱ ሲናገር እየገረማቸው ተረድተው ያደምጡት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ ሥልጡንና ምሁር ሰው ነበረ። ሆኖም ወንጌልን እንደሚገባ ይገልጥ ዘንድ የሌሎችን ጸሎት ሲሻ እናያለን (ኤፌሶን 620)። በቆሮንቶስ የሚገኙትን አማንያን “አንብባችሁ ማስተዋል የምትችሉትን ነገር ካልሆነ ሌላ ምንም አልጽፍላችሁም” ይላቸዋል (2 ቆሮንቶስ 113፣ 1980 ትርጉም)። ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ ዓሳ አጥማጅና የባላገር ሰው ነው። ሆኖም በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ጸጋ ሲናገር ሊቃውንትን ሳይቀር አስገረማቸው፣ ይላል (የሐዋ ሥራ 413)።

ወደ ክርስቶስ የመጣ ሰው ግልጽነትና ቀጥተኛነት ሊታይበት ይገባል። የሚለው ሊኖረው ይገባል። ሊለው የሚፈልገውን የተረዳ ሰው መሆን ይጠበቅበታል። የተረዳውን ለሰሚው አቅም መጥኖ ማቅረብ ይጠበቅበታል። እንግዲህ ከዚህ እውነት የራቀ ሁኔታ በአንዳንዱ ጽሑፍ ላይ ይታያል።

ለምሳሌ፤ ከወላጅ ቁጥጥር ውጪ ስለሆኑት ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ለማስረዳት ሜክሲኰ አገር ያለውን ካስረዳ በኋላ መደምደሚያው ላይ አንድ አፍታ የኛን አገር ይቃኛል። የሴትኛ አዳሪነትን አሳሳቢ ጉዳይ ለማስረዳት ታይላንድ አገር ደርሶ መመለስ አለበት። ስለ ጸሎት ኰሪያ፤ ስለ ስነ-መለኰት አሜሪካ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ አቋቋም ቴክሳስ ወይንም ካሊፎርኒያ፤ ስለ አሰባበክ ቲ ዲ ጄክስ እና የአሜሪካን ቴሌቪዥን አርበኞች። የሚያማምሩ ፎቶዎችስ ፈረንጅነት የማያጣቸው ኸረ እንዲያው ለምን ይሆን? የራስን ሁኔታ ላለመቀበል ከመፈለግ የተነሳ ይሆን? በሌላው ዓይን ራሱን ማየት ያበዛል። ከዚህ የተነሳ ስለሚገኝበት ሁኔታ ጥልቅ ግንዛቤ ያጣል። የውጪውን እንደ ሚዛን ከመጠቀም ይልቅ በተጨማሪ ከውስጥ ወደ ውጭ ማየት ቢጀምር ምን የአስተሳሰብ ለውጥ ያስገኝ ይሆን?

ምዕራባዊ አስተሳሰብ ከኛው የሚለይበት አንደኛው መንገድ፣ የኛ ምሥጢራዊውን በእምነት መቀበል ሲቀለው፣ የምዕራባውያኑ ግን ስም ካልሰጠው፣ ካልገለጸው ስለማያሳርፈው ነው። መጽሐፍትን ከእንግሊዝኛው ወደ አማርኛ የሚተረጉሙና የተተረጎመውን ለሚያነብቡ ይህን እውነት ማስታወስ ይጠቅማቸዋል። በአብዛኛው የነዚህና የመሳሰሉት መጽሐፍት መርሆ፦ “ይህ እንዲሆንልህ ከፈለግህ እነዚህን መመሪያዎች ተከተል፣ … ለመበልጸግ ከፈለግህ መጀመሪያ ይህን ያህል ገንዘብ ላክ… ይህን መመሪያ ተከትለው የቀናቸው፣ እነሆ! … ለነርሱ ከሠራ ላንተም ይሠራል” ይልና ፈገግታ የሚያሳዩ በአብዛኛው የሴቶችን ፎቶ ለምስክር ያቀርብልናል።

ምዕራባዊ አእምሮ ባጭሩ ከምሥጢራት ጋር መስማማት ወይም አብሮ መኖር ይሳነዋል። በምዕራቡ ክፍል ፈሪሃ እግዚአብሔርና ጽሞናዊነት አንሶ የሚታየው ከዚሁ የተነሣ ነው። ለዚህም ነው አንዳንዶች ጥንትነት ወደ አላቸው የሃይማኖት ክፍሎች መፍለስ የጀመሩት። በሥልጣኔ እርምጃ ስለገሠገሱ ብቻ የምዕራባውያን ባሕል ክርስቲያናዊ ነው ማለት አይደለም። አርአያነታቸው ያስተማምናል ማለት አይደለም። በባሕል ረገድ ከኛ እንደሚሻሉ ሊቆጠር አይገባም። የባሕሎችን ኋላ ቀርነት ቢሆን የሥልጣኔን ትብታብ የሚመዝን፣ ገርስሶ ነጻ የሚያወጣ የክርስቶስ ወንጌል ብቻ ነውና። በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ “መንፈሳዊ” መዝሙር ዘማሪዎች አርአያነታቸው በጥንቃቄ ሊመረመር ይገባል። ምክንያቱም ስልትና ቃናቸው ለዓለም ከሚያቀነቅኑት የተቀዳ ስለሆነ። በዓለም ያሉትንም ለማርካት ስለሆነ። “ኮካ ኮላ ጠጡ” ባለበት አንደበቱ፣ “ኢየሱስ ያድናል” ማለት ስለማያሳፍረው። እውነተኛ አምልኮና ዓለማዊነት ድንበሩ ስለደበዘዘ። የሙዚቃ ቅንብሮችን የሚያዘጋጁ ከንግድ ጋር የሠመረ ግንኙነት ስላላቸው። የአንዳንዶቹም መንፈሳዊነት ከነአንካቴው ስለሚያጠራጥር። በሌላ አነጋገር “ኢየሱስ፣ ኢየሱስ” ስለተባለ ብቻ ክርስቲያን ይኰናል ወይንም መንፈሳዊነትን ይጐናጸፋል ማለት አይደለም።

7. ሀ ሁ እንደገና

የአማርኛ ሆሄያት የየራሳቸውን ዝንባሌ ካሳዩ ውለው አደሩ። እውነትም ተመሳቅለናልና! “ዕግዚያብሄር” “እግዚዓብሔር” ይላል። “እየሱሥ” ወይም “እየሡስ” ይላል። ምን ለማለት እንደ ተፈለገ እስከገባ ድረስ አንተም አበዛኸው ልትሉ ትችላላችሁ። የኔ አባባል ግን እነዚህ ዝንባሌዎች ስለ ራሳችንና ስለ ሀገሪቱ የትምህርት አዝማሚያ ምንን ያመለክታሉ? ነው። መደበኛነትና ተግባቢነት ሲጓደሉ፣ እንደ ቀውስ አለመቆጠሩ ለምንድነው? ነው። አንድ ወጥነት ለመግባቢያ መሠረቱ ሆኖ ሳለ ችላ መባሉስ? ቤተ ክርስቲያንስ ምዕመኖቿን በዚህ ረገድ እንዴት ልትመክራቸው ይገባል? ኸረ እንዲያው በሥርዓት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከዚህ ሁኔታ እርምት እንዴት አይሰጥም? ነው።

8. ከሰው ስሕተት አይጠፋም

የግድፈት ብዛት በመጀመሪያ ከግድ የለሽነትና ከቅድመ ዝግጅት ማነስ ይመነጫል። ጸሐፊው ምን ለማለት እንዳሰበ ማወቅ ካስቸገረ፤ አንባቢው በራሱ ግምት ለማንበብ ይገደዳል። ያውም መንፈሰ ጠንካራው አንባቢ ካልሆነ በስተቀረ አንዳንዱ ከሚያታግለኝ ብሎ ጽሑፉን ማንበብ ይተወዋል። በዚህ ላይ አማርኛ ራሱ እንደ ዕብራዊው ዘወርዋራ ቋንቋ ነው። ሲጠብቅና ሲላላ፣ ሲነጣጠልና ሲገጣጠም ሌላ ያልታሰበ አእምሮ ይዞ ይቀርባል። “የሚያምኑ” እና “የማያምኑ” ልዩነታቸው ጭረት ታክል ቢሆንም አተረጓጐማቸው የሞትና ሕይወት ያክል ነው! አንዳንዱማ ጸሐፊ መጽሐፉ መግቢያ ወይም መደምደሚያ ላይ “አስጀምሮ ላስጨረሰኝ አምላክ ምሥጋና ይግባው” ይልና፣ “በህትመቱ ላይ ግድፈት ቢገኝበት፣ ከሰው ስሕተት ከብረት ዝገት አይጠፋምና አንባቢዬ አርሞ እንዲያነብልኝ በትሕትና እጠይቃለሁ” ብሎ ያርፈዋል። ከጽሑፉ ጋር የሚተላለፈው መልእክት ግን “ትንሽ ስሕተት ምንም አይደለም። ስሕተት መኖሩ የሚያስደንቅ አይደለም” የሚል ነው። አምላክን ማመስገኑና የሰውን ልጅ ድክመት መገንዘቡ ባልከፋ።

እንግዳ ጋብዘህ ባልታጠበ ሰሐን የሚበላ ብታቀርብለት አያስተዛዝብም? እንግዳውስ እንዴት ቢንቀኝ ነው አይልም? ሰሐኑ ያልታጠበው ውሃ ተቋርጦብን ነው … ጸሐፊው ነው … ታይፒስቱ ነው ማለት ይጠቅማል? ለአንባቢም የሚቀርብ ጽሑፍ እንዲሁ ነው። እስኪስተካከል ለምን አይቆይም? ወይም ለምን አይቀርም? ለጌታና ለአንባቢው ክብር ለወጣውም ወጪ ይህ አጸፋው ሊሆን ይገባል? ወይ ግድፈት የተገኘበትን እንደ ግድፈቱ መጠን በቅናሽ መሸጥ ይጀመር ይሆን?

9. ቅንፍ

የቅንፍ አጠቃቀም መንታ መንገድ ላይ ቆሞ መወሰን የቸገረውን ሰው ያስታውሰናል። የአንባቢውን ፍላጐት እንዳያበርድ፣ መረዳቱንም እንዳያጐሳቁል በቅንፍ ውስጥ የሚደረደሩት ቃላት በተቻለ መጠን በአንድ ቢጠቃለሉ ይጠቅማል። ይህን ማድረግ ብዙ ማሰብን ይጠይቃል። ማሰብ ደግሞ በመሠረቱ የሚመረጥ የሚመች የሚያዝናና ተግባር አይደለም። ጥልቅ አሳቢነት “የተዘጋጀ አዕምሮ” የቆረጠ ልብ ላላቸው ነው። በመጠን ለመኖር ለወሰኑ ነው። ዋጋ ለከፈሉ ነው፤ ለሚወላውሉ አይደለም። አንባቢን ማፍራት በመሠረቱ በጽሑፉ ጠቃሚነትና ጥራት ይጀምራል፤ እንላለን።

10. ማነኝ? ማን ነን?

ስለ ሐገራችን ያለንን አስተሳሰብ ስንጠቃቅስ አንዳንዴ የታሪክ መሠረት ሳንይዝ ነው። የአገር ነገር ለአንዳንዶቻችን ጭፍን ሃይማኖት ሆኖብናል። ባልተገራ ስሜት፣ በምኞትና በአሉባልታ ብቻ ሕልውናን መገንባት እንደ እንቧይ ካብ ይሆናል፤ እላለሁ። ስለ ራሳችን የተሳሳተ ግምት ከኖረን ስለ ሌሎችም እንዲሁ የተሳሳተ ግምት ይኖረናል። ከምድር ሕዝቦች ይልቅ የተለየን ወይም የተሻልን ሰዎች አይደለንም። የኬንያ ኪኩዩዎችም ስለ ራሳቸው እንዲሁ ይላሉ። ናይጄሪያዎችም። አሜሪካኖችም። ሁሉም እንዲህ ካለ፣ “ልዩ” ነን ማለት ብዙ ትርጉም አይኖረውም። “ያሉትን ይበሉ እንጂ እንደ እኛስ አይሆኑም” ማለት ይቻላል። “ደግሞስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ እኛ ስማቸው አልተጠቀሰም እኰ” እንል ይሆናል። እንግዲህ ስማችን የተጠቀሰው በኃጢአታችን ብዛት እንደሆነስ? ደግሞስ “ኢትዮጵያ” የሚለው መጠርያ ሌሎችን ይጨምር እንደሆነስ? ሰው ስለራሱ ከእውነት የራቀ አመለካከት ሲኖረው ውጤቱ ምን ጊዜም አስደሳች አይሆንም። ስለ ሰው ቀጥተኛና ልክ የሆነ ማስረጃ ሊስጥ የተቻለውና የተገባው የክርስቶስ ወንጌል ብቻ ነው። ሁሉም በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረዋል ይለናል። “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፣ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው” (የሐዋርያት ሥራ 1727)። “ሁሉም” ሲል፣ እሥራኤላዊውንና ፍልስጤማዊውን ነው፤ ሀብታሙንና ደሀውን ነው፤ ሴቱንና ወንዱን ነው፤ ሕጻኑንና አዋቂውን ነው፤ ወጣቱንና አዛውንቱን ነው፤ የተማረውንና ያልተማረውን ነው፤ ጥቁሩንና ነጩን ነው፤ “ሕዝብን፣ ነገድን፣ ወገንን፣ ቋንቋን” ነው። ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋል ከእግዚአብሔር ክብር ጐድለዋል ይለናል። ሁሉም በክርስቶስ በኩል የኃጢአት ይቅርታንና ደኅንነትን ያገኛሉ ይለናል። ከአምላኩ ጋር የታረቀ ከራሱና ከፍጥረት ሁሉ ጋር የታረቀ ነው፣ ይለናል። ማንነታችንን በዚሁ ይጠቀልለዋል! ሰውን “ልዩ” የሚያደርገው በአምላክ አምሳል መፈጠሩ ነው። “ሰው”ነት ከጐሠኛነት የሚቀድመው ለዚህ ነው። እንግዲያስ ሰውን ማክበር ፈጣሪን ማክበር ነው። ሰውን መናቅ ፈጣሪንም መናቅ ነው፤ ያም አይበጅም።

11. በሰማይና በምድር

መንፈሳዊነት ማኅበራዊውን ጉዳይ እንደማይመለከት ሲታሰብ ኖሯል። ሰው በዚች ምድር የመኖሩ ምክንያት ለመንግሥተ ሰማይ ለመዘጋጀት ነው፣ ይላል። ይህ ከፊል እውነትነት አለው። በተለይማ ፖለቲካና ሃይማኖትን መቀላቀል አደገኛ ነው፣ ይላል። ለምሳሌ በ 1968 በታተመው ቁጥር 11 የብርሃን መጽሔት ላይ “የኤምፔሪያሊዝም ሽኩቻ” በሚል ርዕስ የወጣው ጽሑፍ ያስከተለውን ጥያቄና ጉምጉምታ ማስታወስ በቂ ነው። ምድራዊውን ከመንፈሳዊው የሚነጣጥለው አስተሳሰብ፣ ባሕላችን ካመጣብን በተጨማሪ የሚሲዮናውያን ድርሻ ምን ያህሉ ይሆን? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዝባዝንኬውን ማተም፣ የእግዚአብሔርን ቤት ምሥጢር በአደባባይ መዘርገፍ፣ ግለ ሰቦችን ማግነንና መጣል እንደ ቁም ነገር ተቆጥሯል። በመሠረቱ፣ የክርስቶስ ወንጌል የዓለም ገበያን እንዲገዛ እንጂ የዓለም ገበያ የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያንና የወንጌልን ስርጭት እንዲቆጣጠር አልተፈቀደም። ኢየሱስን ጅራፍ እንዲያነሳ መጋበዝ ካልሆነ በስተቀር።

“ፖለቲካና ኰሬንቲ በሩቁ” የሚለው አነጋገር ይህንኑ የተነጣጠለ አስተሳስብ የሚያጸና ነው። ለዓለማውያን ፖለቲከኞች እንዳፈቃዳቸው እንዲፈነጩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። መልሰው ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንዲወነጅሉ። በቅድሚያ ማወቅ ያለብን አንድ ግለሰብ የአንድ ማኅበረ ሰብ አባል በመሆኑ ብቻ ፖለቲካዊ ሕልውና እንደሚኖረው ነው። ደግሞስ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ከማለትና የመንግሥተ ሰማያትን ወንጌል ከማወጅ የበረታ ምን የፖለቲካ አቋም ሊፈጠር ይችላል? ቤተ ክርስቲያን የወንጌልን እውነት እያስተማረች ምዕመናንን በሕብረተ ሰቡ ውስጥ ታሰማራቸዋለች። ሌሎችን እንደዚሁ ወደ እምነት ታመጣለች። “እከሌን ምረጡ፣ እከሊትን አትምረጡ” የሚል አቋም ላይኖራት ይችላል። ሆኖም ስለ ታማኝነት ካስተማረች በተለያየ የሕብረተ ሰቡ ክፍል የተሠማሩት ልጆቿ የ “ጨውነታቸውን” ኃላፊነት ሊወጡ በምርጫ ይወዳደራሉ። ሌባውን ተመራጭ አይመርጡም፣ ወዘተ። ሁሉም በእግዚአብሔር አምሳል እንደ ተፈጠረ ካስተማረች ምዕመናን የጐሣና የቋንቋን ልዩነት ውበት እንጂ መነጣጠል እንደሆነ አይቆጥሩም፤ “አንድ ተስፋ… አንድ አካል… አንድ መንፈስ…አንድ ጌታ… አንድ ሃይማኖት… አንዲት ጥምቀት… አንድ አምላክ” (ኤፌሶን 44-5) ይላልና። እንግዲያስ ይህንን እውነት ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜው ያመቸ ይመስላል። በአንጻሩ አለመሳተፍ የሚያስከትለውን መገመት ቀላል አይሆንም። የሁሉንም ሕይወትና ኑሮ በሚነካ ጉዳይ ላይ ጥቂቶች ብቻ እንዲወስኑበት መተው ብዙ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። ቤተ ክርስቲያን የራሷን ቤት ሥርዓት ካስያዘች ደግሞ ግፍ ሲፈጸም፣ ፍትሕ ሲጓደል አይታ ዝም አትልም። ለቀኝና ለግራ የማይል ሚዛን በእጇ ስለያዘች በንዋይ ሚዛን፣ በዝና ሚዛን፣ በወገን ሚዛን አትወሰድም። ይኸ የኋለኛው ነጥብ እንግዲህ ብዙ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ነው። የተሰዋላት ክርስቶስ በሚሰጠው ጸጋ ከዚህ ያነሰውን አይጠብቅባትም። ሆኖም ጸጋ ልዩ ልዩ ነው፤ እያንዳንዱ ጸጋውን ለይቶ ማወቅና ጌታ ባስቀመጠው ቦታ መገኘቱ ጠቃሚ ነው።

12. የወንጌል ስርጭት፣ ማኅበራዊ እርዳታና ተጠሪነት

ባለፉት 15 ዓመታት የግል አገልግሎቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በነጠላ ሳይሆን በድምሩ አስተዋጽዖአቸው የሚገመገምበት ሰዓቱ አሁን ነው። አብዛኛዎቹ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱት ከሰሜን አሜሪካ ተነስተው ነው። መልካም ሥራዎች አልተሰሩም ማለት አንችልም። በጥረታቸው አንድ ሰው ብቻ እንኳ ወደ ክርስቶስ መንግሥት መጥቶ ቢሆን ቀላል ነገር አይደለም። በተጨማሪ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ከፍቶላቸዋል፤ ማኅበራዊ ሥራም እየተሠራ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ የገንዘብ ኃይል በወንጌል ስርጭትና በወንጌል አገልጋዮች ሁኔታ ላይ ለውጥ አላመጣም ብንል የምንደልለው ራሳችንን ብቻ ነው። ልንዘነጋው የማይገባ ነገር ቢኖር በቤተ ክርስቲያን አካባቢ “የግል አገልግሎት” የሚለው አሠራር ከንግድና ከጦር ተቋማት የፈለሰ አስተሳሰብ መሆኑን ነው። ትኩረቱ በአብዛኛው አሐዛዊና ግለኛ ነው። ይኸው አገልግሎት ወይም “ራእይ” ለምን በቤተ ክርስቲያን ውስጥና በቤተ ክርስቲያን ሥር ሊካሄድ አልቻለም? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ተንጠልጥሎ መቅረት የለበትም።

የ”ግል” አገልግሎቶችን ድርሻና ኃላፊነት በሚመለከት እነዚህ ጥያቄዎች በጽኑ ሊታሰብባቸው ይገባል፤

· እንደ ሚሲዮናውያኑ የእግዚአብሔርን ሥራና ሕዝብ ላለመነጣጠል ምን ጥረትና ጥንቃቄ ተደርጓል? አገልግሎቱስ በሌሎችም መንቀሳቀስ ይችላል? ተተኪ አፍርቷል? · በምዕመንና በቤተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግኑኝነት አጠናክሯል? የ”ግል” አገልግሎቶች ምዕመኗን መገሠጽ እንዳትችል የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን አዳክሞ ይሆን? · የወንጌል አቅርቦት የሀገሬውን ባሕልና አስተሳሰብ ያከብራል ወይስ የውጪውን እንዳለ ያስተጋባል? ትኩረቱ የሰሚውን ገርነት፣ ብሶትና የኑሮ ውድቀት ይበዘብዛል ወይስ በርኅራኄ ይመለከታል? ስብዕናን ያከብራል? · አገልግሎቱ ስለሚያስከትለው ጐጂ ለውጥ ተጠያቂነትን ይቀበላል ወይስ የሌሎች ኃላፊነት እንደሆነ ይገምታል? · ድንበርተኛነትን ያገንናል? ለማንም ተጠሪ አይደለሁም፣ ‘አትድረሱብኝ፣ አልደርስባችሁም’ ይላል? · ገቢና ወጪውን ይፋ ያደርጋል? በአስተባባሪው፣ በተጠቃሚውና በአስፈጻሚው ክፍል መካከል ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል? ዓመታዊ ዕቅዱንና የሚያቀርባቸውን ሪፖርቶች ይፋ ያደርጋል? ሪፖርቱ ከተሠራው ሥራ ጋር ምን ያህል ይጣጣማል? የሥራው ታዛቢና መርማሪ ገለልተኛ አካል ነው? ባጭሩ፣ “ተጠሪነቴ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው” ማለት ለአገልጋዩ ቢሆን ለጌታ ስም መልካም አይሆንም። አገልግሎቱ የተደራጀው በተጠቃሚው ስም ስለሆነ እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ማንሳታችን ተገቢ ይሆናል፣ እርስ በርስ የምንጠባበቅበት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነውና። ይህን ቁም ነገር መዘንጋት ለብዙዎች ውድቀትና ለጌታ ስም መነቀፍ ምክንያት ሆኗል።

ይቀጥላል…