በምትኩ አዲሱ

ይቺን መጽሐፍ … ልዋሳት?

 

       እቤት ጋብዘህ እያስተናገድከው ሳለ ክፍሉንና ዕቃውን ለሐራጅ የቀረበ ይመስል መመለካከት ይጀምራል፣

      እንደ ፈራኸው የመጽሐፍት መደርደሪያው ጋ ሲደርስ ዐይኑ ተተክሎ ይቀራል…

      ለማዘናጋት፣ “እህስ … ተጫወት እንጂ የምን ዝምታ ነው? … የሚጠጣ ላምጣ?” ትለዋለህ፣

      ከንቱ ሙከራ ነው፣ እንግዳ ሆየ በአሳብ ርቆ ሄዷል፤ …

“እሺ … ኸረ እጫወታለሁ” እያለ … ድመት አድፍጦ ዐይጥ ላይ ጉብ እንደሚል እጁ የዐይኑን አቅጣጫ ተከትሎ መጽሐፍክን መዝዞ ያወጣዋል …

      እንግዲህ ለመዘጋጀት ፋታ አልሰጠ፣ … አላስታወቀ፤

      ከዚያማ የሚከተለውን አንተም ቀድሞ ጠርጥረሃል፤ … በለሠለሠ ድምጽ፣ … “ይቺን መጽሐፍ  …እ.እ.እ … ልዋ--ሳት?” ነዋ!

      ምን መልስ ልትሰጥ ነው? አትዋስ አትል፣ የማይመስል ነገር ነው፣ እንዲያውም ነውር ነው…

      በቅጽበቱ ዝምታ መካከል ግን የመጽሐፊቷ የሕይወት ታሪክ በዐይነ ኅሊናህ ፊት ውልብ ይልብሃል፤

      አንድ ቅዳሜ ዕለት፣ መርካቶ አሮጌ መጽሐፍ ተራ የሚረባ መጽሐፍ ፍለጋ ሄደህ፤ እንደ ጉምሩክ ፈታሽ ስንቱን ሰንዱቅ አስከፍተህ ስትበረብር አረፈድክ። ሁለት ቁና ብናኝ አፈር ምገህም ሳይቀናህ ቀረ፤

      አምላክ ቢመሽም ጉዳትን አይቶ ሳይክስ አይቀርምና፣ “ሁሌ አይቀና” ብለህ ተስፋ ቆርጠህ ወደ ቤትህ ልትመለስ ስታስብ፣ ይቺን አሁን እንግዳህ የጮለፋትን መጽሐፍ አገኘህ፤

      ከደስታህና ከመጓጓትህ ብዛት እቤት እስክትደርስ እንኳን አላስቻለህም፤ እንደ ሰካራም እየተወላገድክ ስታነብባት ስንቴ መንገድ ሳትክ፣ … አንድ ጊዜ ከቆመ ከኤሌክትሪክ ግንድ ጋር ተላተምክ … (ለምንድነው ያለ ቦታው የሚተክሉት?)፤

      እና ከዳር እስከ ዳር አነበብካት፣ ስለ ጣመችህ ደገምካት፣ ቁም ነገሮቿን በቢክ እስክሪብቶ አሰመርክባቸው … አሁን አሁንማ የገጾቿን ጠረን ዐይኖችህን ጨፍነህ እንኳን መለየት ጀምረህ ነበር…

      ምን ይደረግ? አታንብባት አትል፤ ሴት ልጁን እንደሚሰጥ ወላጅ አንጀትክን አጥፈህ ማየት እንጂ አሁን መላ የለውም፣

      ብቻ እንዳይቀር፣ በሠለለ ድምጽ፣ “ኦኬ፣… ስትጨርስ መመለስ አትርሣ” ትለዋለህ እንቢታህ እንዳያስነቃ ፈገግ እያልክ።

አጅሬ ምኑ ሞኝ፣ “እንዴታ! … ችግር የለም” ይልሃል፤

      ታዲያ ብዙም አትደነቅ። መጻሕፍት ካሉህ፣ ወዳጆችም ካሉህ መገናኘታቸው የማይቀር ነው፤

      መደርደሪያው እንግዲህ የጥርሰ ወላቃ ፈገግታውን እያሳየ የሚቀጥለውን እንግዳ ይጠብቃ!

      ከዚያማ ስትገናኙ በገዛ ንብረትህ “ላስታውሰው ይሆን? አላስታውሰው ይሆን? ሌላ ጊዜ ይሻል ይሆን? ሌላ ጊዜ ባላገኘውስ?” እያልክ ታመነታለህ፣ ትሠቃያለህ። የይሉኝታ ሥቃይህን ያወቀልህም የለም። እንደ ምንም ጥርስህን ነክሰህ ልትጠይቅ ያልክ ዕለት፣ እንግዳ ሆየ መቸ የዋዛ? ከምኔው አሳብክን እንዳነበበ እግዜር ይወቅለት። ብቻ ገና አፍህን ከፍተህ መናገር ሳትጀምር አቋርጦ፣ “ይኸውልህ ያቺን መጽሐፍ እኮ በጄ ይዤ ከቤት ልወጣ ስል ስልክ ተደውሎ ሳወራ እዚያው ከተቀመጥኩበት ፎቴ ላይ ረስቼ አልመጣ መሰለህ?” ይልሃል፤

      ያቺን መጽሐፍ አልክ? እስቲ ይሁና…

      እንግዲህ ባገኘኸው ቁጥር ይህንን ስታነሳበት አትኖር … ሰሚውስ ምን ይላል? ተገላቢጦሽ ኃፍረት ይዞህ ትተወዋለህ፣ …

      ከዚህ ቀደም እንደዚህ ዓይነቱን የመጽሐፍ ቀበኛ ለመከላከልና አደብ ለማስገዛት አያሌ ሙከራዎች ተደርገዋል፤

አንዱም ግን አልሠራም።

      ለምሳሌ ያክል፣ የባለቤቱ ስም ተጽፎበታል … ይህማ ቀላል አደል? አጅሪት ደልዛ የራሷን ስም ትጽፍበታለች።

ወይም እንዳያጓጓ በ “ዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ተሸፍኗል … “ምን ይዘሃል” ጥያቄ ፊት ፊትህን፣ ጆሮ ጆሮህን ይልሃል። ወይም፣  

“ይህ መጽሐፍ የርስዎ አይደለም” ይጻፍበታል … (መች አጡት?)  

“ካነበቡ በኋላ ለባለቤቱ መመለስ አይርሱ” (ይህስ አደል ችግሩ?)፤ ወይም እንደ ተማረረ አንድ ወዳጄ፣ “ዘጸአት 20፡ 15 (አትስረቅ)” ተሠምሮበታል … በአምላክ ስም መዛቱ ነው … ወይስ መቅሠፍት መጥራቱ ነው?

      ኸረ መቸ ይኸ ብቻ? ቀበኛን ለመከላከል ሲባል መኝታ ክፍል ሣጥን ውስጥ ሁሉ ሳይቀር ተቆልፎበታል፤ እንግዲህ ሊነበብ የተፈጠረ መጽሐፍ ዳኛ ሳይበይን እሥር ቤት ወረደ ማለት ነው፤

      ጥሩ መጽሐፍ ጥሩ ወዳጅ ነው፤ ያነጋግራል፣ ይመክራል፣ ታጋሽ ነው፣ ታማኝ ነው:: ይህ እውነተኛ አባባል ነው። ጥሩ ወዳጅነት ደግሞ ውሎ ሲያድር ጥሩ ዐመል ሳያስገኝ አይቀርም፤ በሌላ አነጋገር ያነበብካቸውን መጽሐፍት ብትነግረኝ ማንነትክን ከሞላ ጎደል መገምገም ይቻላል ለማለት ነው፤

      ጥሩ መጽሐፍ ደግሞ ትውልድን ያሳልፋል። ይህን እውነት የተገነዘቡ ከዘመናቸው ቁጥር በላይ በዕድሜአቸው የበለጸጉ ናቸው፤

      ብዙ የሚያነብቡ ብዙ ያነብባሉ፣ ብዙ የሚወድዱ ብዙ ይወድዳሉ። መጽሐፍትን ከመውደዱና ከማንበቡ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም፣ የግሪኮች ፈላስፋ ፕሌቶ ሲሞት ከራስጌው መጽሐፍ እንደ ተገኘ ይነገርለታል …

      ጳውሎስ ሐዋርያው በበኩሉ የእምነት ልጁ ለሆነው ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት፣ “በርኖሱንና መጽሐፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ” ይለዋል፤

      ሐዋርያው ይህንን በጻፈበት ወቅት ወዳጄ ልቤ የሚለው ዴማስ ከድቶት ነበር፤ በመከራው ሰዓት ሌሎችም እንዲሁ ጥለውት ሄደዋል። ይኸ ሳያንስ ናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ክፉ ነገር አድርጎበታል። … በዚህ ጉድ ውስጥ እያለ መጽሐፍቱን አምጣልኝ ይላል …

      ስንቶች ስለ መጽሐፍትና ስለ ብጣሽ ጽሑፍ ሲሉ ሕይወታቸው አልፏል። አንዳንዶችም ተሰድደዋል፣ ሌሎችም ታስረው ተንገላትተዋል … መጽሐፍቱም እንደዚሁ … ባንድ ትውልድ ዘንድ የተወደዱ በሌላኛው ተወግዘዋል፣ ታግደዋል፣ ለእሳትና ለመቀስ ተዳርገዋል፤

      ጥቂቶች ብቻ ዝናቸው ሳያረጅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግረዋል …

      እንደ እውነቱ ከሆነ የሚታየው ነገር ሁሉ ፈጥኖ አላፊ ነው፤ እኛም አላፊ ነን። ይዘነው የመጣነው ምንም የለም፤ ይዘነው የምንሄደው ምንም አይኖርም፤ ትተን የምናልፈው ግን አይታጣም፤

      ይልቅ ጊዜ ለመሻማት፣ “ይቺን መጽሐፍ … ልዋሳት?” ሲል፣ “አንብብና … አስተላልፋት” እንበል።

እኛም የተዋስነውና ለባለቤቱ ያልመለስነው መጽሐፍ ስለማይጠፋ ምክንያቱን ከመደርደሪያችን ውስጥ እናገኘዋለን…     

 

Óምአ2006