እንዴት ሞልቷል ዮርዳኖስ
እንዴት ሞልቷል ዮርዳኖስ
አቤት
እንዴት ሞልቷል
ሰውን ከንስሣ አይለይም
ይወስዳል
እያፏጨ እየተመመ እያሽካካ
ይጐርፋል
እንዳልሻገር መንገዴን
ግጥም አድርጐ ዘግቷል
እንዴት ሞልቷል ዮርዳኖስ
እንዴት ሞልቷል

እንዴት ፈራሁ ዘንድሮስ
እንዴት ፈራሁ
ይህንስ መሻገር
አልችልም ብያለሁ…
ከወንዝ ወዲያ ማዶ
ተስፋዬን እያየሁ
መጠበቅ ከጀመርሁ
ጥቂት ሰንብቻለሁ
እንዴት ፈራሁ
ጌታዬ
እንዴት ፈራሁ
*
እንዴት ሞልቷል ዮርዳኖስ
እንዴት ሞልቷል?
እንደ ኤርትራ ባሕር
እፊቴ ተጋድሟል
ተራውን ጠብቆ
ሊያደክመኝ ተነሥቷል…
*
እንጃ አስፈርቶኛል
ወሬ አሸብሮኛል
ያለፈው ተረስቶኝ
ጥርጥር ገብቶኛል
ወደ ኋላ እንዳልል
ብዙ ተጉዤአለሁ
ወደ ፊቴ ደግሞ
በዚህ ተይዤአለሁ
ሥፍራ ጠቦብኛል
ዐይኔ ግን ይቃኛል
በርሬ እንዳመልጥ
ክንፍ አስፈልጐኛል
አምላክ ይረዳኛል
አምላክ ይረዳኛል
በትረ ሙሴ ትላንት
መስቀሉ ቀድሞኛል
ጌታ ሲናገረው
“ይህም ደግሞ ያልፋል” ማለት ይሻለኛል
*
እንዴት ፈርሷል ዮርዳኖስ
እሰይ
እንዴት ደርቋል…

Óምአ2006
