ርዕሰ አንቀጽ
በክርስትና ስም …
በክርስትና ስም ብዙ ግፍ ተፈጽሟል። በሳይንስም ስም። በታሪክም። በፍልስፍናም። በፍትሕና በእርዳታም ስም። ሰዎች ፍጹማን አይደሉም፤ ሲቻል ሁሉም የሚያዋጣቸውን ይሻሉ። አንዳንዴ የሚሹትን ለማግኘት የሚጠቀሙበት ዘዴ ለሁሉ ወዲያው ግልጽ አይሆንም። አንዳንዴም ብዙ ጥፋት ካስከተለ በኋላ ሥራው ይገለጣል።
በሌላ ስም ሽፋን ዓላማን ማራመድ ያልተለመደ አይደለም። ከ 17 ዓመት ተስፋ፣ ምሬትና ጉስቁልና በኋላ “ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም” ሳይንስም ሶሻሊዝምም እንዳልሆነ የገባን ይመስለናል።
ሁሉን በጅምላ ማውገዝ ግን ስሕተት ነው። ነጣጥሎ ማጣራት፣ በዝግታ ማመሳከርና መመዘን ይገባል። ተግባርና መጠርያ ሲለያይ ደግሞ ይፋ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል። በሌላ አነጋገር፣ ሳይገደድ የፈቀደውን ማመን ለማንም መብቱ ነው። እምነቱንም ሳያስገድድ ማሰማትና ማሳመን መብቱ ነው። ከመኰራረፍ መነጋገር፤ ከመራራቅ መቀራረብና መተዋወቅ ይሻላልና።
ሆን ብሎ ማንነቱን ሲሰውር ግን ጥያቄ ይፈጥራል።
በቅርቡ የ 86 ዓመቱ ኰሪያዊ አዛውንት ሬቨረንድ ሙን የድርጅቱን ማዕከል ከኬንያ ነቅሎ ወደ አገራችን ለማዛወር ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ሰምተናል (“ኢንዲያን ኦሽን” መጽሔት፣ ቁጥር 1192፣ 2006 ይመልከቱ)። ግለሰቡ በደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞች አንዳንድ የ “ሰላም” እንቅስቃሴዎችንም እያካሄደ ነው ይባላል።
ከኬንያ ለምን ለቀቀ? በዚህ ወቅት ለምን ወደ ምድራችን ዘመተ? ሰላምን ከሩቅ ማስጫን ለምን አስፈለገ? ግለሰቡ በኬንያ እንደሆነው ሁሉ የአገራችንን ምሑራንና የፖለቲካ መሪዎች አጋሩ አድርጓቸዋል። ሕዝቡ ምራቂ መሆኑ ነው። ምሑራንና መሪዎቻችን መቸ ይሆን ለአገራችን የሞራል ውድቀት ምክንያት ከመሆን የሚቆጠቡት? እስከ መቸ ነው የዛሬውን ብቻ ብለው የነገውን ችላ የሚሉት? … በሬ ሆይ፣ ገደሉን አይተህ ሣሩን?!
áá
የቤተ ክርስቲያን አመራር መዳከም፣ በሥልጣን አካባቢ የሚታየው አለመረጋጋትና የሕዝቡ ድህነት ለኰሪያዊው ምቹ ሁኔታን ሳይፈጥርለት አልቀረም። አብያተ ክርስቲያናትስ ምን ጥንቃቄ ሊወስዱ አስበዋል?
የሬቨረንድ ሙን ድርጅት “ዩኒፊኬሽን ቸርች” ይባላል። ሕጋዊ ስሙ፣ “የመንፈስ ቅዱስ ማኅበር ለዓለም አቀፍ ክርስቲያናዊ አንድነት” (The Holy Spirit Association for the Unification of World Christianity) ነው። “ዓለም አቀፍ” ሲል ዓለምን ያጥለቀለቀ ያስመስላል። እውነቱ ግን በሰሜን አሜሪካና በአውሮጳም እንኳ ከአስር ሺህ በላይ አጥባቂ ተከታዮች የሉትም። መነኻሪያው በደቡብ ኰሪያ ደቡባዊ ግዛት ሆኖ በታዳጊ አገሮች በልማትና በንግድ ስም በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ከአስር ዓመት ወዲህ ደግሞ ስልቱን ቀይሮ ለየአገሩ የአገሬውን “መሲሕ” መሾም ጀምሯል። መሲሐችን ማን ትሆን?
ይኸው ድርጅት የተለያዩ አካላት አሉት። እንዳያስነቃ “የሰላም ፌደሬሽን” “ወንድማማች” “ነጻነት” “መልካም ሥነ ምግባር” “ቤተ ሰብ” ወዘተ በሚሉ ድንቅ ሐረጐች ተሸላልመዋል። “ክፍፍል” “ቁጥጥር” “ኑፋቄ” ቢልማ ማን ይቀበለው ኖሯል?
ድርጅቱ እንደዚሁ ልዩ ልዩ ሥራዎች አሉት። ዓለም አቀፍ የሰላም ፌዴሬሽን የተሰኘው የራሱን የሰላም አምባሳደሮች ይሾማል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ “የዓለም ሰላም ፕሮፌሰሮችን” ይመለምላል፤ ለሚያካሄዱት ምርምር በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር የወጪ ድጐማና ልዩ የክብር ሽልማት ይሰጣቸዋል። ተሸላሚዎቹም ሊቅነታቸውንና ገናና ስማቸውን በማዋስ አጸፋውን ይመልሳሉ። ያጐረሳቸው እጅ የማን እንደ ሆነ ከመመርመርና ከመመስከር ይለጐማሉ፤ ይለግማሉ።
በታዋቂ ዜጐች አሳብበው ራሳቸውን የሚያስተዋውቁ፤ ባልደከሙበት ተቀባይነትና ክብርን የሚጐናጸፉ ጥቂቶች አይደሉም። እንግዲህ ሽልማትና ድጐማ መልካም ነገር ነው። ሽልማትና ድጐማ ግን ያለ ሰዓቱ፣ ያለ ቦታውና ያለ አግባቡ ሲሆን ሙስና ይባላል።
የዲሞክራሲ መብቶች ለበለጸጉ አገሮች እንደሚሠራ ሁሉ እንደ እኛ ላሉ አገሮችም እኩል ይሠራል ማለት ዘበት ነው። ስም አሳምረው ብር ጭነው ብቅ የሚሉ ሁሉ ይስተናገዱ ማለት ተገቢ ክትትል በሌለበት የሕዝቡን ደኅነነት ማጓደል ሊሆን ይችላል፤ ሥነ ልቡናውን ለሚሰልቡ ማጋለጥ ይሆናል።
የሬቨረንድ ሙን ተቀዳሚ ዓላማ ዞሮ ዞሮ እንደ ማንኛውም ድርጅት ሰዎችን በአስተሳሰብ፣ በአካልና በእምነት የራሱ ማድረግ ነው። ሌላስ ምን ተጨማሪ ዓላማ ይኖረው ይሆን?
ከላይ የጠቀስናቸው “ሰላም” “ክርስቲያን” ወዘተ የሚሉ ቃላት በጥንቃቄ ሊመረመሩ ይገባል። በዚህ በተፈረካከሰ ዓለም ሰላምና አንድነትን የሚጠላ ሕይወትን የጠላ ብቻ ነው። በአንጻሩ “ሰላም፣ ሰላም” ስለ ተባለ ሰላም ይመጣል ማለት አይደለም፤ “የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ ሰላም ሳይሆን። ሰላም ሰላም ይላሉ” (ኤርምያስ 6፡14)። ይልቅ ለግለኛ ዓላማ ሽፋን ሊሆን ይችላል። የክርስቲያን አንድነትን የሚቃወም ክርስትና ያልገባው ብቻ ነው። “አንድነት” ደግሞ የገዛ ኅልውናን መካድ አይደለም።
አሁን ጥያቄ ሊሆን የሚገባው፣ ሬቨረንድ ሙን አገራችን ድረስ ያመጣልን ክርስትና ምን ዓይነቱን ነው? የሚለው ነው።
ሌላ ሳንዘበዝብ ስለ ክርስቶስ ያለውን መረዳት እንመልከት። የክርስትና ቁልፉ ክርስቶስ ነውና። “እኔን ያየ አብን አይቶአል … መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም። በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው … እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው … በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” (ዮሐንስ 14፡ 9፤ 1፡ 18፤ ቆላስይስ 1፡ 15፤ ዮሐንስ 14፡ 6)።
እንግዲህ “ነኝ” ማለት ብቻ ክርስቲያን አያደርግም። ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ማመን ያስፈልጋልና። ቃለ እግዚአብሔር ስለርሱ የሰጠውን ምስክር ማመንና ማወቅ ይገባል። ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት በሙሉ መቀበልና እርሱ በሚሰጠው ጸጋ ፈለጉን መከተል፣ እርሱ እንደ ኖረው መኖር ያሻል (ዮሐንስ 1፡14-18፤ 14፡ 6፣9፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡5፤ ቆላስይስ 2፡9፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡ 21)።
በዚህ ዋነኛ ነጥብ ላይ ስምምነት ከጠፋ አንድነት መፍጠር ከንቱ ሙከራ ነው፤ ሽንገላ ነው። “ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል” ይላልና (ቆላስይስ 1፡ 18)።
ሬቨረንድ ሙንና ባለቤቱ በአዳምና በሔዋን ውድቀት ምክንያት የፈረሰውን የመጀመሪያውን ቤተ ሰብ ለማደስ ለሰው ሁሉ “እውነተኛ ወላጅ” ሆነን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከናል ይሉናል። ኢየሱስ ቤተ ሰብ ሳይመሠርት ስለ ተገደለ ተልዕኰውን አላጠናቀቀም ይሉናል። ሁለተኛው አዳም የሆነው ኢየሱስ ሙሉ ደኅንነትን አላስገኘም፤ ተልዕኰውን ለማጠናቀቅ ሦስተኛ አዳም እኛ ተልከናል ይሉናል። (“ኋለኛው አዳም” ለሚለው 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡ 45 ይመልከቱ)።
ኢየሱስ በመስቀል ላይ “ተፈጸመ!” ብሎ ያሰማው የድል ጩኸት እንጂ የፀፀት እንዳልሆነ አያስተውሉም፣ መካዱም አያሳፍራቸውም (ዮሐንስ ወንጌል 19፡ 30)። ኢየሱስ እንዲህ ብሏልና፦
የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውን እፈጽም ዘንድ ነው … የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና … እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ (ዮሐንስ ወንጌል 4፡ 34፤ 5፡ 30፤ 17፡ 4)
áá
አዳምና ሔዋን የወደቁት የተሰጣቸውን ትእዛዝ ባለመጠበቃቸው መሆኑ ቀርቶ በዝሙት ምክንያት ነው ይሉናል (ዘፍጥረት ምዕራፍ 3)። እንደሚሉን ከሆነ እውነተኞቹ አዳምና ሔዋን እነርሱ ናቸው። በዝሙት የመጣውን ውድቀት ለመዋጀት እነርሱ መርጠው፣ ባርከው ያጣመሩት ጋብቻ መፍትሔው ነው ይሉናል። ተጋቢዎቹን የሚመርጡ፣ የሚያጣምሩና የሚባርኩ እነርሱው ናቸው። ግለሰቦች ምርጫቸውን ጥለው ራሳቸውን አንጠልጥለው ማስረከብ ነው ድርሻቸው። አጋቢዎቹ የአምላክን ቦታ ያዙ ማለት ነው። እንግዲህ በክርስቶስ ትምህርት የማይኖር ሰው ባርኰቱ ምን ይጠቅማል? የባርኰቱስ ምንጭ ኧረ ከማን ዘንድ ይሆን? ለባርኰት ለባርኰትማ በአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ስም የሚባርክ መች አጥተን እናውቃለን?!
የመጀመሪያውን የጅምላ ጋብቻ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር (እ.ፈ.አ.) በ1982 በአሜሪካ 2 ሺህ ግለሰቦችን በአንድ ጊዜ በማጋባት ፈጽመዋል። ከአስራ አምስት በኋላ ቁጥሩ ወደ 300 ሺህ ከፍ እንዳለ ይነገራል። ሆኖም ሁሉም ተከታዮች ሳይሆኑ “ልዩ” ነገር መሞከር የሚጥማቸውንም እንደሚጨምር መረሳት የለበትም።
የጅምላ ጋብቻ ወጪ ለመጋራት ለሚያስቡ ያጓጓ ይሆናል። በአቅም መኖር ሲገባ ወጪን ፈርቶ የራስን ክብርና ነጻነት መሸጥ ግን የባሰ ችግር መፍጠር ነው።
ከ 2ቱ ሺህ ጋብቻ ውስጥ መቶው እንኳ ቢጸና ሁለተኛና ሦስተኛ ትውልድ ላይ የሚያስከትለውን የባሕልና የሞራል ለውጥ መገመት አያዳግትም። ለአገራችን እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ ያስፈልጋታል? ለውጥ ጥሩ ነው፤ የቆየ ልማድም ጥሩ ነው። ጥሩ ለውጥ ደግሞ ዘላቂ ደኅንነትና ያለፈውን በጐ ታሪክ የሚያጸና መሆን አለበት።
ካጋቧቸው የሚወለዱ ሁሉ ከአዳማዊ ኃጢአት የነጹ ይሆናሉ ይሉናል። ስለ ኃጢአት ሥርየት በመስቀል ላይ ከፈሰሰው ከክርስቶስ ደም የተነሳ ይቅር መባልና ከኃጢአት ክስና እስራት ነጻ መውጣት እንደሚቻል ተክዶ ማለት ነው። ጽድቅና ደኅንነት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ስጦታ መሆኑ ተዘንግቶ ማለት ነው (ሮሜ 3፡ 24፣ 6፡ 23፤ ኤፌሶን 2፡ 8)። የሬቨረንድ ሙን ዓይነት ልምምድ በአገራችን ባሕል ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ ቀውስ ጥንስሱ ነው። ወጣቶች ሳይጋቡ አብረው መኖር በጀመሩበት በዚህ ዘመን ለተለቀቀ ፍትወትና ለቤተሰብ መፍረስ በር ከፋች ነው።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኰሪያዊ ወላጅ ለምን እንዳስፈለገው አልተረዳንም። እዚህ ላይ ሬቨረንዱ አግብቶ መፍታቱን፣ የሰውን ቤተሰብ መገንባት ቀርቶ የራሱን ዕዳ አለመወጣቱን፣ በጦር መሣርያ ምርትና ሺያጭ ተከስሶ መመርመሩን፣ “ቤተ ክርስቲያኑን” ከመሠረተበት ከ 1954 (እ.ፈ.አ.) ጀምሮ በአብያተ ክርስቲያናት መወገዙን፣ ደጋግሞ መታሠሩንና በሕገ ወጥ ንግድ መታማቱን አናነሳም።
ሬቨረንድ ሙን የሕግ ስሙን ትርጓሜ፣ “እውነቱን የሚያብራራ” በሚል ተክቶታል። ያልተብራራ እውነት አለ ማለቱ ነው። ማንም ያልደረሰበት። ኢየሱስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ማለቱ ሳይበቃ። (ዮሐንስ ወንጌል 14፡ 6)
እንደ ሬቨረንድ ሙን ትምህርት ከሆነ የሚመጣው መሲሕ ኰሪያዊ ነው። ራሱ የሚነግሥባት የእግዚአብሔር መንግሥት ትመሰረታለች ብሎ እ.ፈ.አ. በ ‘57፣ በ ’76 እና በ ’81 የተነበየው አንዱም አልያዘም። ሐሰተኛው መሲሕ ከዚህ በምን ይለያል? (1ኛ ዮሐንስ 2፡ 18-27) ይህ ትምህርት በክርስቶስ፣ በሐዋርያቱና በነቢያቱ ትምህርት ላይ የታነጸ አይደለም (ኤፌሶን 2፡ 20)። ኢየሱስ ገልጦልኛል ከሚለውና “ዲቫይን ፕሪንሲፕል” ከተሰኘ ራሱ ካቀናበረው መጽሐፍ ላይ ይጠቅስልናል። ባጭሩ፣ ሬቨረንድ ሙን በስም እንጂ ክርስቲያን አይደለም። ሃሳዊ መሲሕ እንጂ እውነተኛ መሲሕ አይደለም።
… በመካከላችሁ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል፤ በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል (2ኛ ጴጥሮስ 2፡ 1-2)
… የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል … ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም … በክርስቶስ ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም … (1ኛ ዮሐንስ 2፡ 18፣ 22፤ 2ኛ ዮሐንስ 9)
ታዲያ ሌላ ምን ዓላማ ሊኖረው ይችላል? አንደኛ እንደየአገሩ ባሕልና ሁኔታ የሚቀየስ የንግድ ዓላማ ይኖረዋል። ይህን ለመዘርዘር አሁን መድረኩ አይፈቅድልንም። ለማንኛውም ሙን ሀብታም ድርጅት የሚያንቀሳቅስ ሀብታም ግለሰብ ነው። አገራችን ደግሞ ለአፍሪካ ማዕከልና ለመካከለኛው ምሥራቅ ድልድይ ናት። የዓባይን ውሃ ይሆን የሚፈልገው? ቀድመው በንግድ ከተደራጁት ግለሰቦችስ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖረው ይሆን? በአገራት መካከል እየተዘዋወረ ንግድ ለማስፋፋት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንና ዕውቅ መሪዎችን አጋር ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። በፓራጉዌይ ደቡብ አሜሪካ ሰሜናዊ ግዛት የአውሮጳን ትንሽ አገር የሚያህል ሰፊ ይዞታ ከነመንደርተኛው በ $22 ሚሊዮን ዶላር ገዝቷል። የመንደርተኛው ተቃውሞ ከፓራጉዌይ መንግሥት ጋር ከመስማማቱ የተነሣ ሰሚ አጥቷል። በኛም አገር ይደገም ይሆን? በዛምቢያ ደግሞ እ.ፈ.አ. በ 2001 የ 71 ዓመቱን የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አዛውንትና ሊቀ ጳጳስ ሚሊንጐን 43 ዓመት ዕድሜ ካላት ኰሪያዊት ጋር አጋብቶአል። ትዳሩ እርግጥ ሳይቆይ ፈርሷል። ግን በአማንያኑ ሥነ ልቡና ላይ ምን ያህል አለመታመንን እንደ ዘራ መገመት አያዳግትም። ለኢትዮጵያ ምን ታቅዶላት ይሆን?
ሙን በተጨማሪ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የዝነኛው የ “ዋሺንግተን ታይምስ” እና የ “ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል” “ኢንሳይት” እና “ዘ ዎርልድ ኤንድ አይ” ዜና አውታሮች ባለቤት ነው። መንግሥታትንና ባለሥልጣኖቻቸውን ማጥመጃ መረቡ እጅግ ሰፊ እንደ ሆነ እንገነዘባለን። መደመጥ የሚሹ ሁሉ ለምን እንደሚወዳጁት እንግዲህ መገመት አያቅትም።
ፖለቲካዊና ዓለም አቀፋዊ ዓላማ አለው፤ ዓለምን መቆጣጠር ተቀዳሚው ነው። የጅምላ ጋብቻ አፋጣኝ መንገዱ ነው። የየአገሩን የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የባሕል ሊቃናትን አጋር ማድረግ ጥረቱ ነው። እ.ፈ.አ. በ1972 ወደ አሜሪካ ሲገባ ጸረ-ኰሚዩኒስት አቋም ለነበራቸው ለአሜሪካ ፕሬዚደንት ኒክሰን በወቅቱ የሚያስፈልገውን ድጋፍ መስጠቱና ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል። ለፕሬዚደንቱም ፓርቲ እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀ ወዳጅ ነው። በ 2004 ለምሳሌ ለአሜሪካ ኰንግሬስ ንግግር ካደረገ በኋላ በነበረው ግብዣ ላይ ዘውድ ሲደፋና ራሱን “የሰው ልጅ አዳኝ፣ መሲሕ፣ የሚመጣው ጌታና እውነተኛ ወላጅ” ነኝ ሲል ተደምጧል። የኛንም መሪዎች ላሰበው ተግባሩ ቢያዘጋጃቸው አይድነቀን። ድርጅቱ በዋሺንግተን አካባቢ ለፈሰሰው ለአገራችን ሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ በመፍቀድ ቢያለሳልስ ወይም አንዳንዶችን ቢመለምል አይድነቀን። የዋሺንግተንን ባለ ሥልጣናት ያውቃቸዋል፣ እነርሱም ያውቁታል። ይደግፋቸዋል፣ ይደግፉታል። አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኰሪያዊ መሆናቸው ባጋጣሚ ነው?
ሬቨረንድ ሙን ሆነ ሌሎች እንደ ማንም ግለሰብ ወይም ድርጅት እውነተኛ ማንነታቸውን ገልጠው የአገራችን ሕግና ሥርዓት በሚጠይቀው መሠረት ቢመዘገቡ ምንም አልነበረም። በክርስቲያን፣ በሰላም፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ ወዘተ ሽፋን ግን አዘናግተው የሕዝቡን ባሕል፣ አስተሳሰብና እምነት ሲያዛቡ ጥያቄ ይፈጥርብናል፤ የፖለቲካ ሥራቸው ያሳስበናል። መግባባት እንዲኖር ከተፈለገ ሁሉም ወገን በጋራ ስምምነቶች መሠረት ለመተዳደር መፍቀድ ይኖርበታል። ለዚህም ስም አጠራራቸው ብቻ ሳይሆን ተግባራቸውም ግልጽ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ይኸው ሬቨረንድ እ.ፈ.አ. ከ1950ዎቹ ጀምሮ በእስያ፣ በአሜሪካና በተለይ በላቲን አሜሪካ ሲያካሄድ የቆየውን መመርመር ይጠቅማል። ያልጠረጠሩና ያላወቁ ለማይረባ ተስፋ እንዳይዳረጉ። መቸውንም ቢሆን፣ የሚያውቁት ባላንጣ ከሚጠረጥሩት ወዳጅ ሳይሻል አይቀርም።
http://peacefederation.org/index.php;
http://www.unification.org/; http://www.unification.net/
http://en.wikipedia.org/wiki/Unification_Church; http://www.religioustolerance.org/unificat.htm
http://religiousmovements.lib.virginia.edu/nrms/unification2.html; http://gadflyer.com/articles/?ArticleID=131;
http://www.unification.net/2004/20040323_1.html http://www.larouchepub.com/other/2002/2949moonification.html;
http://www.globalpolicy.org/ngos/analysis/1101moon.htm http://www.mediachannel.org/originals/moontranscript.shtml
http://www.newcovpub.com/unification/wfwp3.html; www.ffwpui.org,
http://www.freedomofmind.com/resourcecenter/groups/m/moonies/
Handbook of Denominations in the U.S. 12th Edition, pp.382-384
Encyclopedia of American Religious History. (1996),Vol.2, p.682
©Copyright, 11/2006
