የወንጌል ስርጭትና እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ (ክፍል 2)
በምትኩ አዲሱ

 

ክፍል ሁለት፦ የተያያዝነው ጉዞ

በክፍል አንድ እንዳሳሰብነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በጐ ሥራዎች እንዳልተሠሩ ለማስመሰል አይደለም። ይልቅ በወንጌል ስርጭት ሳቢያ የተከሰቱ አዝማሚያዎችን ለመጠቆምና እንደ ሁኔታው መፍትሔዎችን ለማቀድ እንዲያስችል ነው። አዝማሚያ ውሎ ሲያድር መደበኛ ይሆናል፤ ልክ እንደ ሆነ መታሰብ ይጀምራል፤ ማረሙም እንደ ነውር ይቆጠራል። የዚህ ጽሑፍ ሌላኛው ዓላማ የጥንቱን የሐዋርያትን ልማድ ለማበረታታት ነው (የሐዋርያት ሥራ 242፣ 62-4)። ይህም ቃለ እግዚአብሔርን ገልጦ ማንበብና ማሰላሰልን፣ መጸለይና በታማኝነት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መጐናጸፍና ጠቃሚ ሰው መሆንን ይጨምራል። 

1. አዝማሚያው ምን ይመስላል?

ላመኑና ላላመኑ ብዙሃን የወንጌል ዕውቀት ማሰራጫ ዓይነተኛ መንገዱ በዝማሬ ስለሆነ ይህንኑ እስቲ አንቃኝ። በምዕራቡ ዓለም እንደተለመደው፣ በአገራችንም የዓለም ድምጻዊ በተቀናበረ ሙዚቃ “የጽዮንን ዝማሬ” ቀምሮ ለገበያ ቢያቀርብ ምን እንል ይሆን? “ታሽገው የሚሸጡ” ዝማሬዎችን ለማቅረብ ቴክኒኩ ቢያስችልም አሁን የሚጠበቀው ተቃውሞ እንዳያስነሳ ምቹ ጊዜ ነው። ቀስ በቀስ “ለጌታ ክብር ነው” በሚል ሰበብ ድንበሩ እየደበዘዘና እየተደፈረ ነው። የገበያ ውድድርና ሥልጣን ማንንም ይማርካል። ገበያና ገንዘብ ከጌታ ቤት ሥራ ጋር በማይመች አኳኃን ሲጣመሩ ግን ነገር መበላሸቱ አይቀርም። የዘማሪው ልብስና ቁመና ሳይቀር ለሺያጭ እንደሚቀርብ ዕቃ ትኩረት ይሰጠዋል ማለት ነው። ለምስል መስገድ ሲባል አዝማሚያው ይኸ እንደሆነስ?

“ሌዋዊው” ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውጭ ቆሞ እያዜመ እንዳይሆን እንስጋ። የማረኩት የሚጠይቁትን ዝማሬ ሲዘምር እንዳይገኝ። በአገልግሎት ስም ጸጋውን በዝናና በገንዘብ እየቸበቸበ እንዳይሆን። ለቤተ መቅደስ ሥርዓት ይገዛል? ወይስ “በአዲስ ራእይ” አሳብቦ ሙዚቃውን ይዞ ይኮበልላል? ሙዚቃው የተመረጠ ወንበር የሚናጠቅበት መሣሪያው ነው? የጌታና ለጌታ መሆኑ ቀርቶ የግልና ለግል መሆን ጀምሮ ይሆን? እንግዲህ ከዚህ የተነሳ ነው አንዳንዱን መዝሙር ከአንድ ጊዜ በላይ መስማት የሚያቅተው። በጸሎት ሳይሆን በሙዚቃ ኪነ-ጥበብ ብቻ ስለ ተቀመመ ለጸሎት አይጋብዝም። ካላጸለየና የእግዚአብሔርን ህልውና ካላስታወቀ ዝማሬ ከመዝናኛነት አላለፈም ማለት ነው። የመንፈሳዊ መዝሙሮች መሠረታዊ ግብ የእግዚአብሔርን ህልውናና ክብር ማስታወቅና የሰሚውን አዕምሮና መንፈስ አንፆ ወደ አምላኩ ማቅናት ነው።

የሙዚቃውን ቅኝት በተመለከተ አንዳንዴ በዓለም ያሉትን ለመሳብ የተፈጠረ ዘዴ እንደሆነ ይደመጣል። እርግጥ እግዚአብሔርን መወሰን አንችልም፤ ከልብ የተሰጠውን ያን አይንቅምና፤ ያንኑ ለማዳን ይጠቀምበታልና። ዘመኑ የሚጠይቀው አሠራር አይኖርም ማለት አንችልም። ቅርሳችንን ግን ችላ ብንል የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ታሪክ ማቃለል ይሆንብናል። ያጐድልብናል። ሰዎችን የምናቀርብበት መንገድ ለሁሉም አንድ ወጥ መሆን እንደሌለበት ቢታወቅም፣ ክብር የሌለበት የሰው ብልሃት ብቻ ሆኖ እንዳይገኝ መስጋት ይኖርብናል። የሙዚቃን መንፈሳዊ ጥራት ለመለየት የረቀቀ የሙዚቃ ዕውቀት አያሻም። መንፈሳቸው ለሚለይ የሙዚቃ ስልትም እንኳ ይህን አይሰውርባቸውምና። መጽሐፍ እንደሚል፦ “መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና፣ ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈስ በኩል ገለጠው… መንፈሳዊ ሰው… ሁሉን ይመረምራል፣ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም” (1ኛ ቆሮንቶስ 210፣15)። 

በዚሁ በአሜሪካ ለምሳሌ፣ ከነባር ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የተፈናቀሉትንና ርቀው የኖሩትን ላለማስቀየም ሲባል መስቀል-አልባ አምልኰ ቤቶችን ማነጽ ተጀምሯል። መስቀል የሥቃይ፣ የመስዋእትነትና የሰው ኃጢአት ውጤት መግለጫ መሆኑን ማስታወስ የማይፈልጉ በዝተዋል። የመስቀሉ ማእከላዊነትና መልእክት በብልጽግናና በ“ራስ ማሻሻያ” ብልሃቶች፣ በግለኛነትና በመካካብ ወንጌል እየተተካ ነው። በዚሁ አስተሳሰብ መሠረት ቤተ ክርስቲያን በንግድ ተቋም ትመሰላለች። መጋቢ ደግሞ የተቋሙ ባለቤት ወይም ተቀጣሪ አስተዳዳሪ ነው። ምዕመኑ ገበያተኛ ነው። ብዛት ብልጽግና ነው። ምዕመኑ እዚህ ካልጣመው ወይም ሌላ “ራእይ” ከመጣለት ትቶ እዚያ የመሄድ መብቱ የተጠበቀ ነው። ተጠሪነቱ ለራሱ ነው። ላወጣው ወጪ ተመጣጣኝ አገልግሎት ይሻል። “ራእይ” እንደ ልብ ሆኗል። ወደ ሌላ እንዳይኰበልልበት ዘዴ መፍጠር ደግሞ የትጉዕ መሪ ኃላፊነት ነው። ምሪት የሚገኘው ከመንፈስ ቅዱስና ከቃሉ ሳይሆን ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ስሜትና ፍላጐት በመነሳት ነው። የተቋሙ ፍሬ በሰው፣ በገንዘብና በእንቅስቃሴ ዘርፍ ብዛት ይመዘናል። ቃሉ ግን የሚነግረን የመስቀሉ ነገር ለሃይማኖተኞችና ለምድር ሰዎች እንደማይመቻቸው ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 118-25፤ ፊልጵስዩስ 318-21)።

ለአንድ ሰሞን ያለ ሙዚቃ መሣርያ ቢመለክ ስንቱ ሰው ይሆን ቤተ ክርስቲያን መምጣት የሚያቆመው? ለአንድ ሰሞን ጉባዔ የመረጠውን መዝሙራት መዘመር ቢጀመር ምን ለውጥ ያስከትል ይሆን? በየአምልኰው ክፍለ ጊዜ የአንድ ሰዓት ፍጹም ፀጥታ ቢታወጅ መንፈሳዊነትን እንዳጐደለ ይቆጠር ይሆን? (ራእይ 8፡1፤ 1ኛ ነገሥት 19፡12፤ መክብብ 3፡7፤ 5፡2 ይመልከቱ) ስንቶች ይሆኑ እንደ ነቢዩ ዕንባቆም “ምንም እንኳ ካሴትና ሲዲ ባይሸጥ፣ ታዋቂነትና ጥሪም ባይመጣ፣ በማገልገል ውስጥ ጉዳት እንጂ ትርፍ ባይገኝ፣ ሙዚቃውም ባይጋጋል፣ እኔ ግን ለጌታ እዘምራለሁ” የሚሉ? (ዕንባቆም 317-19)

2. “አይ ፖድ”፣ አይ ሲዲ፣ አይ ስነ-መለኰት

በመሠረቱ ቴክኖሎጂ በራሱ ክፉም በጐም ነው ማለት አይቻልም። እንደ እሳት ጠቄሜታው ነው የሚተረጉመውና። በግል አስተሳሰብ፣ በቤተ ክርስቲያን አሠራርና በአገር አቅም ላይ ጉልህ ለውጥ እየታየ ነው። ቴክኖሎጂው ስለ ተለወጠ ብቻ ተጠቃሚውም የያዘውን መለወጥ ይኖርበታል ማለት አይደለም። ተጠቃሚው በአብዛኛው በያዘው የማይረጋውና የማይረካው “ደረጃ” ለመጠበቅ ወይም ቁሳቁስን ማጋበስ እርካታ የሚሰጥ መስሎት ይሆን?

በአገራችን ለምሳሌ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የ”ሞባይል” ስልክ “ቀጭኑን ሽቦ” እየተካው መጥቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የነበረው ስልክ ለአገሬው ተጠቃሚ እንኳ አልተዳረሰም። ሌላው የዓለም ክፍል ‘ዘመናዊ’ ወደ ሆነው ስለ ተሸጋገረ ብቻ አብረን መንከራተት አለብን ያለ ማነው? ምናልባት ጊዜ አለፈበት የተባለውን ነገር ግን ችግራችንን የሚያቃልልልንን ማስፋፋቱ አይቀልም ነበር? እንላለን። በአገር ደረጃ ቢሆን በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በምዕመኑ ኑሮ ውስጥ የተዛባ አመለካከት እንዳለ ይህ ሊያስረዳ ይችላል። ባጭሩ፣ ቴክኖሎጂ ልንጠቀምበት እንጂ ሊጠቀምብን፣ ሊያገለግለን እንጂ ልናገለግለው አልተፈጠረም። ተሳታፊ እንጂ ተመልካች ሊያደርገን አይገባም።  

ቪዲዮ ቀጂው አስር ደቂቃ ያህል ዘግይቶ ስለመጣ ይካሄድ የነበረው አምልኰ አንደገና እንዲጀመር የተደረገበትን አንድ ስብሰባ አስታውሳለሁ። በየስብሰባው የሚቀረጹትን ቪዲዮዎች ተሰብስበን ስናይ “ይኸ እከሌ አይደለም? … እከሊት ምነው እንዲህ ከሳች? ውፍረቷ ይሻላት ነበር፤ … እንትናን ደግሞ ምን መለጠው? የዚህ አገር ዉሃ መቸም…” ማለታችን አልቀረም።

“ቴክኖሎጂ እኰ ጌታም የሚወደው ነው” ይሉናል። ዝግ ብሎ ላሰበ ግን ከላይ በጠቀስናቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚጠቀሙት ቁጥር አቅሙና ዕውቀቱ ከማይፈቅድላቸው ጋር ሲነጻጸር ኢምንት መሆኑን ነው። ስለሆነም የጥቂቶች ፈቃድ በብዙሃን መላከክ የለበትም። ፍላጐቶቻችንን ክርስትና ማንሳት ክርስቲያናዊ ያደርገዋል ማለት አይደለም።

ቤተ ክርስቲያን የፆም አዋጅ ያክል፣ “ቴፕ ያለህ ቴፕህን፣ ሲዲ ያለህ ሲዲህን፣ ሌላም ስም ያለው ያለህ ያለህን፣ የሌለህ ደግሞ እንዳትቀር ለብርቱ ጉዳይ ፈልጌሃለሁ” ብትል፤ ሁለት ነገሮች የሚከሰቱ ይመስለናል። የመጀመሪያው፣ የሸቀጡ ብዛት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ፣ በምዕመን መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ነው። አንዳንዱ ለቤት ማዳመቂያ፣ ሌላው ገንዘብ ተርፎት፣ ሌላው ከማን አንሼ፣ አንዳንዱን ሻጭ አሞኝቶት፤ ሁሉም የየግሉ ምክንያት አያጣም እንላለን። ይኸው ሸቀጥ ተሰብስቦ ወደ መጣበት አገር ቢመለስ በምዕመን መንፈሳዊነት ላይ ኪሣራ ያስከትል ይሆን?!

3. መልእክቱ ምዕመኑ ራሱ ነው

መንፈሳዊነት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር በመሆን እንጂ በሚታይ በውጫዊ ተጽዕኖ አይገኝም። የቴክኖሎጂ እድገትና አጠቃቀም መልካምም አሳሳቢም ነው። አንዱን ሳናጣጥም ሌላው መልክና ቁመና ቀይሮ ከተፍ ይላል። እኛም ከአንዱ ወደ ሌላኛው ስንከንፍ እንታያለን። ከቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን፣ ከአገር አገር የምንለው፣ ጸንተን የማንገኘው በሰሞነኛውና በውጫዊ አስተሳሰብ ስለምንነዳ ይሆን? ሥር የሰደደ፣ መሰጠትን የሚጠይቅ የጠራ ነገር የሚፈለግ አልሆነም። የሚፈለገው ይልቅ ወዲያው ውጤት የሚያሳየው፣ እጅ በጅ የሆነው፣ የሚታየው፣ ብዙ ጥረት የማይጠይቀው፣ በኛው ሚዛን የተሻለ የምንለው ነው። ምሪታችንን ከማን ይሆን የምንቀበለው? እያንዳንዱ የራሱን ሕይወት መምራት እንዳለበት የታወቀ ቢሆንም የአማኒያን ግን በ “ሥጋ ምኞት በዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም በመመካት” ሊሆን አይችልም (1ኛ ዮሐንስ 215-16)። አኗኗራችን ከዓለማዊያን የሚለየው በምንድነው? በዓለም እንዳሉቱ ቁሳቁስ የምናግበሰብስ ከሆነ “የክርስቶስ መልእክት” መሆናችን ቀርቶ የሸቀጥ መልእክተኞች እንሆናለን (2ቆሮንቶስ 33)። እውነትን ትተን ምቾት ብንሻ ሳይመቸን እንኖራለን፤ እውነቱ ቀርቦልን ይሠወርብናል (ሉቃስ 1619-31፤ ማቴዎስ 25)። እውነትን አጥብቀን ብንሻ ግን የክርስቶስ ሰላምና እርካታ ይጨመርልናል። “እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤… ያላችሁ ይብቃችሁ” የሚለን ለዚሁ ነው (ኤፌሶን 515፤ ዕብራውያን 135፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 48፤ ፊልጵስዩስ 411-12)።

4. ያጠረ ክር

የንግድ ነገር ከተነሣ እኛም የምንለው አናጣም። የመዝሙራት ቅጂ ተሻሽሏል ይሉናል፤ እርግጥም ተሻሽሏል። የሚገርመው ግን ከቴፑ ይሁን ከመዝሙሩ ሁሉም እያጠረ መጥቷል። አንድ የሙሉ ወንጌል መዘምራን ቁ.2 ክር ለምሳሌ ሃያ መዝሙር ሊሞላ ምንም አልቀረውም። ክሩ አጥሮባቸው እንጂ ይጨምሩ ነበር እንላለን።

ወንጌልን ከሸቀጥና ከንግድ ጋር አቀራርቦ ማሰብ ቅሥፈትን እንደ መጋበዝ ይመስል የነበረበት ዘመን ነበረ። የዛሬውማ ከአስሩም መዝሙር በዝቶ ወይ የመጀመሪያው መዝሙር መጨረሻ ላይ በከፊል ይደገማል፤ ወይም በመሳሪያ ብቻ ደግሞ ይቀርባል። የብርሃን ልጆች ከዓለም ልጆች እኩል ሠለጠኑ እንበል? ወይስ የዓለም አሠራር በስርጭት ላይ የማይገባ ተጽዕኖ እያደረገ ነው? ይህ ሐተታ እርግጥ ሁሉን አይመለከትም። ወንጌልን ያለ ወጪ ማዳረስ ይቻላል ግን ማለታችን አይደለም።

አንዳንዶች ዘማሪዎች የሰከነ አማካሪ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የሚገሥጻቸው፤ ሁሉም ግን የሚጸልይላቸው። የቆሙበት ሥፍራና የዕድሜአቸው ክልል ለፈተና የተጋለጠ ነውና። ጠላትም የወንጌል መተላለፊያ እንደ ሆነ ስለሚያውቅ አጥብቆ ይታገለናል። ጥቂቶቹም ከጌታ ቤት ውጭ ያለውን ብዙ ስለማያውቁ ግርግሩ አደናግሯቸዋል። ሲብስም አባብሏቸዋል። ተጠሪነታቸው “አዎን፣ ሃሌ ሉያ” ለሚሏቸው ግለሰቦች ስለሆነ ሲስቱ ሃይ የሚላቸው አያገኙም። ተመልሶ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር መከለል አማራጭ የለውም። ማስተዋል ይስጥ።

ፉክክር የታወጀ ይመስል አንዱ አዲስ መዝሙር በሌላ አዲስ መዝሙር ሲለዋወጥ በጌታ ጸጋ ያካበትናቸው ውድ መዝሙራት፣ ትዝታችን በምስጋና እንዳይበረክት ለዝገትና ለመረሳት ተዳርገዋል። የሚቀጥለውስ ትውልድ የዚህኛውን ትውልድ ትዝታ ይርሳውን? የእምነት አካሄድ “ሲወርድ ሲዋረድ” የመጣና የሚቀጥል ነው። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ “የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችን ልብ ወደ አባቶች… የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ” መመለስ ነው (ሚልክያስ 46፤ ሉቃስ 117)። ቴክኖሎጂ በጐም ነገር አለው። ከላይ እንደጠቆምነው፣ ልንገለገልበት እንጂ ልናገለግለው ግን አይገባም። በሠለጠኑ አገሮች ያየነውን ሁሉ ከሻን ተጐታች እንጂ የራሳችን ኑሮ መሪዎች መሆን አንችልም።

5.     የሥልጣኔ ገደቡ

ዛሬም እንደ ጥንቱ ወንጌል የሚሠራጨው ወዳጅ ለጐረቤቱ አፍ ላፍ የምሥራቹን ሲያወራ ነው። “በዚህ ዘመን ኖር ቢሆን ጌታም በቴክኖሎጂ ይገለገል ነበር እኰ” ይባላል። የሚሲዮናዊ ጥናት ሊቅ የሆነው ማክጋቭራን ለምሳሌ የሕንድን ሕዝብ ቶሎ በወንጌል ለመድረስ በየመንደር ማዕከላት የቪዲዮ ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም ይቻላል ብሎ ነበር። ልንዘነጋው የማይገባን ነገር ቢኖር የጌታ ወንጌል ሰውን እንጂ የዘመኑን ግኝት ያማከለ እንዳልነበረ ነው። ይህም ማለት በወቅቱ የተገኘውን መሣሪያ አልተጠቀመበትም ማለት አይደለም። ዋነኛ ትኩረቱ በአምሳሉ በፈጠረው ሰው ላይ ነው ማለት እንጂ። የሰማሪያዊቱንና የጌርጌሴኖኑን ሰው ታሪክ ማገናዘብ ይጠቅማል (ዮሐንስ 4፤ ማርቆስ 51-20)። የጠራቸውን “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ያለውም ለዚሁ ነው (ማርቆስ 16፡15)። ጌታን ልንወስነው አንችልም። ቴክኖሎጂ ብዙ ጥቅም ቢኖረውም እስትንፋስ እንዳለበት ሰው አይሆንም። የደስታና የሐዘን ስሜት አይታይበትም፤ ቴሌቪዥንና ቪዲዮ ደግሞ አንድ አቅጣጫ ንግግር እንጂ ምልልስ አያውቅም። አይዳሰስም፣ ሥጋና ደም አይካፈልም (1ኛ ዮሐንስ 11-2፤ ዕብራውያን 214-15፤ ዮሐንስ 14)። ባጭሩ ቴክኖሎጂ ብዙ ጥቅም ቢኖረውም ከሚገባ በላይ ግን ሥፍራ ልንሰጠው አይገባም ማለታችን ነው።

ቴክኖሎጂ በገነነባቸው አገሮች ሰው ከራሱና ከመሰሉ እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር ለመቆራረጡ አንደኛው ምክንያት ሆኗል። ግንኙነት ያባዛ እየመሰለ ሰውን ብቸኝነት ለቅቆበታል። አብረው ይጓዛሉ፤ ሩቅ ካለ ሰው ጋር በየፊናቸው ያወራሉ። የቅርቡ ርቋል፤ የሩቁ ቀርቧል ማለት ነው። ድምጽ በዝቷል፤ ባለ አንድ ፊት ጫጫታ ነግሷል። ስንቶች ናቸው በዚህ ዘመን የጽሞና ሕይወት የሚለማመዱ? የሰው ቁጥር በዛ ካላለ ያመለኩ የማይመስላቸው ዛሬ ጥቂቶች አይደሉም! ቴክኖሎጂ ምን ያህል ቢራቀቅ ያልተሰጠን ሕይወት ደቀ መዝሙር አያደርግም!

ሮም ሥልጡን እንደ ነበረ አንዘንጋ። ግሪክም። ሥልጣኔ በኛ አልተጀመረም። በዘመኑ ሁሉም ሥልጡን ነው። ጊዜው ሲያልፍ አረጀ ያልተባለ የለም። ኃጢአትና ጽድቅ እንዲሁም የሰው መሠረታዊ ባሕሪይ ግን እስካሁን አልተሻሻለም። እርግጥ ስለምንኖርባት ዓለም ከቀደሙት ይልቅ ዕውቀት አካብተን ሊሆን ይችላል። ሆኖም ጥበብንና ማኅበራዊነትን ሳንጥል አይደለም።

መደምደሚያ

ወንጌልን በተለያየ መልኩ ለማሰራጨት ምን መሠረታዊ ዕቅዶች ሊኖሩ ይገባል? ለዚህ ጥያቄ መልሱ እንደ ሁኔታው ሊለያይ ቢችልም፣ መሠረቱ ግን እያንዳንዱን ምዕመን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ማገናኘት ነው፣ ለመንፈስ ቅዱስ አደራ መስጠት ነው። ከጥገኛ እምነት ማላቀቅ ነው፣ በጌታ ቤት ሙሉ ማኅበርተኛ ወደ መሆን ደረጃ ላይ ማምጣት ነው። የጸሎትን ሕይወት ማለማመድ ነው። መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ሥርዓት ማሳወቅ ነው። አስተሳሰብን ለሚሰርቁ ባሕላዊ አመለካከቶች ከቃሉ ምላሽ የመሻትን ልማድ ማጐናጸፍ ነው። በአዕምሮ ጭምር የበሰሉ ወደ መሆን ማድረስ ነው። በተጨማሪ ከታች የተጠቀሱት ነጥቦች መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ።

·        የመጻፍና የማንበብ ልምዳችን እንደሚገባ የዳበረ አይደለም፤ ይህን የምንለው ማንበብና መጻፍ ስለማይችሉት ወገኖቻችን አይደለም። ወይም ማንበብ ሲችሉና ሲፈልጉ የገንዘብ አቅም ያገዳቸውን አይደለም። ይልቅ ጥቂትም ቢሆኑ ለማንበብና ለመጻፍ በቅተዋል የምንላቸውን እንጂ። የማያነብቡ እንዲያነብቡ፣ የሚያነብቡ ይበልጥ እንዲያነብቡ ማድረግ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ፣ ማሕበራዊ፣ ብሔራዊ ግዴታዋና ተግባሯ ሊሆን ይገባል። ያመኑት ሁሉ በቤታቸው ሆነ በእግዚአብሔር ቤት ከቃሉ የተነጠለ ኑሮ ሊኖራቸው አይችልምና። ይህን ሁኔታ ተገን አድርጐ ማቀድ ያስፈልጋል።

·        ሰማዕት ጉዲና ቱምሣ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስን ከስድሳ ስድስቱ አብዮት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች መሠረተ ትምህርት እንድታካሄድ የሰጡት አመራር ሊኮረጅ እንጂ ሊዘነጋ አይገባም። ይህን የመሰለውን ግዳጅ ለመፈጸም መንግሥት አዋጅ እስኪያውጅ መጠበቅ አያሻም። ሰውንና የሕልውና መብቱን በሚመለከት ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ እንጂ ተከታይ መሆን የለባትም። የስነ-መለኰት ትምህርት ተቋማትን ከማደራጀቱ ጋር ተያይዞ ተራውን ምዕመንና ቤተ ክርስቲያን በምትገኝባቸው ቀበሌዎች ኗሪዎቹን እንዲጽፉና እንዲያነብቡ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። መሃይምነት ከጌታ ቤት ይወገድ! አንባቢ በበዛ ቁጥር በብዙ ቁም ነገር ውስጥ የሚሳተፉ እንዲሁ ይበዛሉና። ይህም በተራው የመጽሐፎችንና የመጽሔቶችን ሺያጭ ከፍ ያደርገዋል፣ የአሳብ ልውውጦችን ያዳብራል ማለት ነው።

·        ማንበብ የሚችሉ የማንበብ ልምድ እንዲያዳብሩ፣ ትጉህና ታማኝ በሆኑ ምዕመናን እጅ በየአካባቢው የሠፈር ቤተ መጻሕፍትና ክበቦችና ማቋቋም ጠቃሚ ነው። በተለይም ለወጣቱ ትውልድ። በወር ይሁን በተወሰኑ ቀናት እንዲነበቡ በተመረጡ ጠቃሚ ጽሑፎች ላይ የአሳብ ልውውጥ ማድረግ ይህን ባሕል ያዳብረዋል። ደጋግሞ ማድረግ ልማድ ይሆናል፤ ጥሩ ልማድ ምን ጊዜም ጥሩ ነው። በቤተ ክርስቲያን ደረጃ የንባብ ቀን እንደ ፆም ቀን በዓመቱ እቅድ ውስጥ ሥፍራ ቢሰጠው እርስ በርስ የመበረታታትንና የመማማርን ልምድ ያስገኛል።

·        የመጻፍ ልምድ እንዲዳብር፣ አጭር ኮርሶችን ማዘጋጀት፣ ዝንባሌ ያላቸውን ማሰባሰብ፣ በጀት መድቦ በአስፈላጊ ቁም ነገሮች ላይ እንዲጽፉ ብቃት ያላቸውን ግለ ሰቦችን ማሰማራት፤ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የዲሞክራሲ ሂደት እንዲፋጠንና ተደማጭነትን እንዲያገኙ ይረዳል። የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶች ይህን መሠረት በማድረግ ሊዘጋጁ ይገባል።

·        በደርግ ዘመን የነበረው ሁኔታ ሊታሰበን ይገባል። በተለይ አገር-አቀፍ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሕልውናቸው ከሚያጠራጥር የውጭ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርባቸዋል (ይመልከቱ፦ http://blogs.salon.com/0003494/2005/10/16.html)። ከሁሉ አስቀድሞ የነዚህን ድርጅቶች ማንነት ማጣራት ያስፈልጋል። በአሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ ወንጌላውያን ድርጅቶችና መሪዎቻቸው በጭፍን የመንግሥታቸውን የውጭ ፖሊሲ የሚያራምዱ ወይም የሚያስተጋቡ ሆነዋል። ሌሎች ደግሞ ከአገሬው ምዕመን የሚገኘው ገቢ ስላቆለቆለ በታዳጊ አገሮች ችግር ተገን ያልነበረ ዕቅድ እያወጡ እርዳታ በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ። 

“ጅብ እማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” እንደ ተባለው ቤተ ክርስቲያን እንተክላለን እያሉ የሚጐርፉ ሁሉ ከኋላቸው ሌላ ታሪክ ሊኖራቸው እንደሚችል የምንገነዘብ ይመስለናል። ቤተ ክርስቲያን ገንዘብና ቁሳቁሶችን ስላቀረቡላት ወይም ለግለሰቦች የገቢ ምንጭ ስለ ተገኘ ብቻ ልታስተናግዳቸው አይገባም። እንዲያውም ልትገልጣቸው ይገባል። ወይም የሰከነ አቋም ካላቸው ድርጅቶችና እውነተኛ የጌታ አገልጋዮች ምስክርነት እንዲያቀርቡ ግድ ልትላቸው ይገባል። እያንዳንዱ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባል ከማን ጋር እንደተጣመረ ማጣራት ይጠቅማል። ለመሆኑ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያ ኅብረት በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ስም፣ ድርጅታዊ ዓላማና መነኻሪያ ዝርዝር ይኖረው ይሆን? እነዚሁ ድርጅቶች ለየመጡበት አድራሻ የሚያቀርቡትን ሪፖርት ማመሳከር ቢቻል ምን ትዝብት ያተርፍ ይሆን? የሥነ ምግባር ጉድለት ሲገኝባቸው በድኅረ ገጽ ማስታወቅ ይጀመር ይሆን?

·        ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናኗ የትኛው ዝማሬ ያልተጣራ ትምህርት እንደሚያስተጋባ ማጣራትና ማስታወቅ፣ ሲያስፈልግም ማገድ ይኖርባታል። በዝማሬ የሚቀርቡትን የወንጌል መልእክቶች ይዘትና ብቃት መመዘን አስፈላጊም ተገቢም ነው።

·        የቤተ ክርስቲያን ዕድገቷ ወደ ኋላ መመልከትን ይጨምራል። ታሪኳንና ቅርሷን መዘንጋት ትልቅ አደጋ ነው። ዛሬ የሚታየው ቀድሞ ያልነበረ አይደለም። የሚመጣውም ያለፈውን የሚደግም ነው። ለመማር መዘግየትና የተማረውን መርሣት የሰው ሁሉ ባሕርይ ነውና።

·        ወጣቱን ትውልድ ለማስተናገድ ሲባል በሚታየው ላይ ብቻ ማተኰርና የቀደመውን የበረከት ዘመን ችላ ማለት ውሎ ሲያድር የወንጌልን መልእክት ማዛባቱ አይቀርም። ትውልዱንም ከቅርሱ ያጓድልበታል። የሚቀጥለውም ትውልድ የዚህኛውን ከዘነጋ የሚከተለውን ክስረት መገመት አያቅትም። ታሪኩን የሚዘነጋ በታሪክም ይዘነጋል እንዲሉ ማለት ነው!     

·        የአብያተ ክርስቲያናት አምልኰ ሥርዓትና የቃሉ ትምህርት መመሳሰል ሊያሳስበን ይገባል። የቴክኖሎጂ ዓለም አቀፋዊ ጫና በ “ልዩነት” ውስጥ ያለውን ውበት አክስሞ አንድ ወጥነትን እያጸና ነው። በቀድሞ ዘመናት ለቤተ ክርስቲያን መዘምራን የተለያዩ የሙዚቃ መሣርያዎችን መጠቀም ግዴታ ነበር። አብሮ መለማመድ፣ በአንድ ሥፍራ ቀጠሮ አክብሮ መገናኘት፣ አብሮ በጾምና መጸለይ፣ መቻቻል፣ መስማማት፣ መኰራረፍና መታረቅ ነበረባቸው። ዛሬማ ጊታሩም፣ አኰርዲዮኑም፣ ከበሮውም ተጠቃልሎ በአንድ “ኪ-ቦርድ” ቀርቧል። የቴክኖሎጂ ውጤት ከሰብአዊነትና ከኅብረት ጐዳና እንዳያፈናቅለን ምን ጥንቃቄ መውሰድ ያስፈልጋል?