የቤተ ክርስቲያን
የመሠረት መልሕቆችና መሪነት ክፍል አንድ
የእግዚአብሔር
የሰላምና የጽድቅ መንግሥት በምድር እግዚአብሔር
በዘላለማዊ ምክሩና ዓላማው የሰው ልጅ ኑሮው፣ ሕይወቱ፣ ትዳሩ ሁሉ ሰላም የሠፈነበትና ጤንነቱ የተሟላ እንዲሆን ይፈልጋል።
የሰው ልጅ ሰላምና ጤና ሊያገኝ የሚችለውም እግዚአብሔርን በማወቅ በርሱ ብቻ በመታመን በትእዛዙና በሃሳቡ ብቻ የሄደ
እንደሆነ ነው። ከዚህም የተነሣ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ መሪዎች አድርጎ በላካቸው መሳፍንት፣ ነቢያት፣ ነገሥታት፣ ካህናት
ሕዝቡን ሥርዓቱንና መንገዱን ያስተምራቸው ነበር። እግዚአብሔር ለሰው
ልጆች ያሰበው የተሟላ ሕይወትና ኑሮ ሊመጣ የሚችለው እርሱ እራሱ በምድር በሚመሠርተው መንግሥት ብቻ መሆኑን ነቢያት
ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ ባሳሰበው መሠረት ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተናግሮ ነበር፦
ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድር
ምስኪኖችም ፍትኅን ይበይናል፣ በአፉ በትር ምድርን ይመታል፣ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። ጽድቅ የወገቡ
መታጠቂያ፣ ታማኝነትም የጎኑ መቀነት ይሆናል። ኢሳይያስ 11፡ 4-5 ከዚህ ጥቅስ
የምንረዳው የይሁዳ ሕዝብ በኃጢአት የተሞላ፣ ድሃ አደጉን የሚበድል፣ ፍትኅና ቅንነት በጎደለው ኑሮው ክፋትን ማብዛቱን፤
ሰዎች በሰላም አብረው እንዲኖሩ ለማድረግ እግዚአብሔር ጣልቃ እንደሚገባና ስግብግብነትን፣ ደሃ መበደልንና ጭቆናን፣
ክፋትንና ኃጢአተኛነትን አስወግዶ ፍትኅን በመመስረት ጽድቅንና ሰላምን እንደሚያመጣ ማቀዱን ነው። ይህንኑ
እግዚአብሔር የገባውን የተስፋ ቃል እንደገና ሲያረጋግጥ ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተናግሮ ነበር፦ በዚያ
ዘመንና በዚያ ጊዜ፣ ከዳዊት ቤት የጽድቅ ቅርንጫፍ አበቅላለሁ በምድሪቱም
ፍትኅንና ጽድቅን ያደርጋል በዚያ
ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ ኢየሩሳሌም በሰላም ትኖራለች
የምትጠራበትም ስም፣ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል። ኤርምያስ 33፡ 15-16 ከላይ የተጠቀሱት
ሁለት ክፍሎች ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውና የሁለተኛ መምጣቱን የሚናገሩ ሲሆኑ፤ በመጀመሪያ መምጣቱ ሰዎችን
ከኃጢአታቸው ንስሃ እንዲገቡ የሚጠራና የሚያስተምር ሲሆን በዳግም ምፃቱ ግን በመላው ምድር የራሱን የፍትኅና የጽድቅ
መንግሥት ለመመስረት የሚሠራውን ሥራ የሚናገር ክፍል ነው። በጊዜው እነዚህ ቃላት የተነገሩት ለይሁዳ ምድር ለእስራኤላውያን
ይምሰሉ እንጂ በእስራኤላውያን አማካይነት የምድር ወገኖች በሙሉ እንደሚድኑ ቀደም ብሎ በተደጋጋሚ የተነገረ ስለሆነ ይህ
በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተፈጻሚነቱን የሚያገኝ እውነተኛና ትክክለኛ ቃል መሆኑን ሲያረጋግጥ ማየት ይቻላል። የዚህ ትንቢት
ተፈጻሚነቱ ሲቃረብ ሚክያስ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር፦
አንቺ ግን ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ፣ ከይሁዳ ነገዶች
መካከል ትንሿ ብትሆኚም አመጣጡ ከጥንት ከቀድሞ ዘመን የሆነ የእስራኤል ገዥ ከአንቺ ይወጣልኛል … በእግዚአብሔር ኃይል
በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ታላቅነት ፀንቶ ይቆማል፣ መንጋውንም ይጠብቃል፣ በዚያን ጊዜ ኃያልነቱ እስከ ምድር ዳርቻ
ስለሚደርስ ተደላድለው ይኖራሉ። እርሱም ሰላማቸው ይሆናል። ሚክያስ 5፡ 2-5 ይህ ከቤተልሔም
ይወጣል የተባለው ገዥ መሲሁ ጌታ ኢየሱስ ነው። ትንቢቱም ትክክል ነበር። ጌታ ኢየሱስ ከዳዊት ዘር በቤተልሔም ተወልዶአል።
እግዚአብሔር በመለኮታዊ ሥራው በዘላለማዊ ምክሩ በሰው ታሪክ ጣልቃ ገብቶ የዓለም ንጉሥና አዳኝ ኢየሱስ እንዲወለድ
አድርጎአል። ይህ ንጉሥ ነው የራሱን መንግሥት በምድር የሚመሠርተው። የርሱም መንግሥት የጦር፣ የምድራዊ ሥልጣንና ግዛት
ሳትሆን የንስሃ፣ የኃጢአት ስርየትና የጽድቅ መንግሥት ናት። የመንግሥቱም ምሥረታ ይፋዊ የሆነ እንቅስቃሴ በጀመረበት ጊዜ
“ንስሃ ግቡ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና” ብሎ ማስተማሩ ይህንኑ ለማረጋገጥ ነበር። ማቴዎስ 4፡ 17 የመሲህ መንግሥት
የሰላምና የጽድቅ መንግሥት ናት፤ ፍትኅ የሰፈነባት፣ ባለ ጸጋውና ድሃው እኩል የሚታዩባት፣ ምዝበራና ብዝበዛ፣ ክፋትና
ጥፋት የማይፈቀድባት፣ ሰዎች ከመጥፎ ሕይወትና ከክፋት ኑሮ ተለይተው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና አካሄድ የሚመላለሱባት
መንግሥት ናት። የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት እግዚአብሔርን ባለማወቅ በኃጢአት ከመኖር ተለይቶ በአዲስ ሕይወት በጽድቅና
በቅድስና መኖር ማለት ነው። ከኃጢአት መለየት፣ መራቅ፣ መተው ማለት ነው። በዚህም የጽድቅ መንግሥት ተካፋይ መሆን
ይቻላል። ይህን የጽድቅ
መንግሥት ሲመሠርት ጌታ ኢየሱስ ብቻውን አላደረገም፤ ነገር ግን ከርሱ የመንግሥቱን የጽድቅ ሥራ የሚረከቡና የሚያስፋፉትን
ደቀ መዛሙርት በመምረጥ አስፈላጊ የሆነውን ትምህርት በመስጠት ነበር የላካቸው። ይህንን ሃሳብ በሚከተለው ጥቅስ ውስጥ
እናገኛለን፦
ኢየሱስም ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች
አደርጋችኋለሁ። ማቴዎስ 4፡ 19 የእግዚአብሔር
መንግሥት የምትመሠረተው በትምህርት፣ በስብከትና በፈውስ መሆኑን እያሳያቸው የተመረጡት ከርሱ ጋር በቀጥታ በሥራው
እንዲሳተፉ ከርሱም በኋላ ሥራውን እንዲቀጥሉ ሥልጣን ሰጣቸው። በዚህ በሰው ማዳን
ሥራ ያሰማራቸው አሥራ ሁለት ደቀመዛሙርት ብቻ አልነበሩም። በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 9 እና 10 እንደምናነበው ሌሎችንም
ሰባ የሆኑትን መርጦ እንደ ሾማቸውና እንደ ላካቸው እናያለን። ሲናገርም፦
መከሩ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው፤
ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ቦታ እንዲልክ ለምኑት… ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች
እየፈወሳችሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች በሏቸው… እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፣ እናንተንም
የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም። በማለት የሥራውን
ስፋት፣ የሥራውን ክብደትና አስፈላጊነት በማሳየት ታላቅ አደራ ጥሎባቸው ነበር። ጌታ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠውን ይህን
ታላቅ አደራ ተቀባዮቹ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በማስተማር ሰዎችን ወደ ንስሃ በመጥራት የእግዚአብሔር የጽድቅ መንግሥት
ዜጎች እንዲሆኑ ከሚመጣውም ቁጣ እንዲያመልጡ በማሳሰብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና በትጋት በጌታ መንፈስ ቅዱስ
ረድዔት ሲሠሩ ቆይተው በቅብብሎሽ እኛ ዘንድ ደርሶአል። ሐዋሪያትም
በመሠረቱት መሠረትና ባቋቋሟቸው አብያተ ክርስቲያናት ሲካሄድ የነበረው ይህ “ታላቁ ተልእኮ” በመባል የሚታወቀው የሰውን
ማዳን፣ የእግዚአብሔር የጽድቅ መንግሥት ሥራ ዛሬም ቢሆን በአብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ መንገዶች እየተሠራ ይገኛል። ሀ.
የቤተክርስቲያን ምሥረታ ጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑ የተመሠረተችበትን ቃል ሲናገር፦ “አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚህ ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፤
የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” ብሎ ነበር። ማቴዎስ 16፡18 ጌታ ኢየሱስ ይህን
የተናገረው፣ “ለመሆኑ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ነው ይላሉ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ … ስምዖን ጰጥሮስ “አንተ ክርስቶስ
የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ በመለሰለት ጊዜ ነበር። የጴጥሮስን መልስ አንዳንድ ቤተክርስቲያናት በሌላ መንገድ
ቢተረጉሙትም አብዛኛዎቹ የሚከተለውን ትርጉም ይጋራሉ ወይም ይስማሙበታል። ይኸውም፦ ይህንንም
ለማረጋገጥ የምንችለው ሐዋሪያው ጴጥሮስ ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ ጀምሮ በሰጠው በክርስቶስ ስቅለት፣ ሞትና ትንሳኤ ላይ ብቻ
በተመሠረተ ትምህርትና ምስክርነት ነው። ይህንንም በሐዋሪያት ሥራ ምዕራፍ 2፣ 3፣ 4፣ 5 ላይ ማየትና መረዳት ይቻላል። ቤተክርስቲያንም
በጴንጤቆስጤ ቀን በበዓለ ሃምሳ ዕለት ተመሠረተች። በዚህ ቀን መንፈስ ቅዱስ በአስደናቂ ሁኔታ ወርዶ ሰዎች በተለያዩ
ቋንቋዎች መናገር ሲጀምሩ፣ ሐዋሪያው ጴጥሮስ በክርስቶስ ስቅለት፣ ሞትና ትንሳኤ ላይ ብቻ የተመሠረተውን ትምህርትና ስብከት
ካሰማ በኋላ የሰዎች ልብ እጅግ ተነካ። ጴጥሮስም፦ “ንስሃ ግቡ፣ ኃጢአታችሁ እንዲሰረይላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም
ተጠመቁ፣ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” በማለት የድነት ጥሪ አቀረበላችሁ። በዚያን ቀንም አምነው የተጠመቁ ሦስት
ሺህ እንደ ነበሩና የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያንም በዚያን ዕለት እንደ ተመሠረተች በሐዋሪያት ሥራ ምዕራፍ 2 እንደሚገባ
ተገልጿል። ሐዋሪያው ጳውሎስ
ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክት አንድ መሪ በእግዚአብሔር ቤት እንዴት መኖር እንደሚገባው ሲጽፍ፣ “ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ
ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። ብዘገይ ግን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ
እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱ የእውነት ዓምድና መሠረት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ነው።” ብሎአል። በዚህ ጥቅስ ስለ
ቤተክርስቲያን አራት መሠረታዊ ሃሳቦችን መመልከት ይቻላል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡ 14-16 ለ.
የቤተክርስቲያን ተልእኰ ምንድነው? የቤተክርስቲያን
ተልእኰ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር የመሠረታትን መንግሥት ማስፋፋትና ማዳረስ ነው። የክርስቶስን የድነት ወንጌል ወደ
ዓለም ሁሉ በመሄድ ለፍጥረት ሁሉ ማወጅ ነው። ማርቆስ 16፡ 15። የቤተክርስቲያን ቀጥተኛ ተልእኰዋ እስከ ዓለም ዳርቻ
ድረስ የክርስቶስ ምስክር መሆን ነው። የሐዋሪያት ሥራ 1፡ 8 ቤተክርስቲያን
ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣንን በመቀበል ስለዚህ ስለ ጽድቅ መንግሥት በስፋትና በጥልቀት በማስተማር ሰዎችን የክርስቶስ
ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ደቀ መዛሙርት በማድረግ ገና በኃጢአትና በጨለማ ውስጥ ያሉትን እንድታስተምር፣ እንድታጠምቅ አደራ
የተሰጣት በክርስቶስ አዳኝነትና ጌትነት የሚያምኑ የክርስቲያኖች ኅብረት ናት። ማቴዎስ 28፡ 18-20 ቤተክርስቲያን
የተጠራችውና የተለየችው ተስፋ ለቆረጡ በኃጢአት ዓለም በክፉ ሥራቸው በጨለማ ለታገቱት የእግዚአብሔርን ታላቅ የማዳን ሥራ
ለማወጅ ነው። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡ 9-10። ቀድሞ በትውልድ አሕዛብ ለተባሉ በኑሮና በሥራ ኃጢአት በመሥራት ለታወቁ
በደለኞች፣ ከኪዳኑ ተስፋ ርቀው ላሉ ኃጢአተኞች ኢየሱስን እንደ አዳኛቸው ቢቀበሉ ኃጢአታቸው እንደሚሰረይላቸው
የእግዚአብሔር የጽድቅ መንግሥት ዜጎች እንደሚሆኑ ለማስተማር የተጠራች ናት። ሐ.
ቤተክርስቲያንን ቤተክርስቲያን የሚያሰኟት ነገሮች “ቤተክርስቲያን”
እንዲሁ በጥሬ ቃሉ የክርስቲያን ቤት ማለት ነው። ይህም ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ቤት እንደ ማለት ነው። ሆኖም ይህን ቃል
ሐዲስ ኪዳን በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ ስንመለከት “ኤክሊዚያ” የሚለውን ቃል ለመተርጎም የተሰጠ ቃል ሆኖ እናገኘዋለን።
ማቴ.16፡ 18 ሐዲስ ኪዳንን
ከግሪክ ቋንቋ ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች የተረጎሙ “ቤተክርስቲያን” ብለውታል። ይህ የግሪክ ቃል ከላይ እንዳስረዳነው
“ተጠርተው የወጡ ሰዎች” የሚል ትርጉም እንዳለው የመጽሐፍ ቅዱስና የቋንቋ ሊቃውንት ይስማሙበታል። በመሆኑም እነዚህ
“የተጠሩ” ሰዎች ላንድ የተለየ ዓላማ መለየታቸውንና መላካቸውን እንገነዘባለን። ይህንንም ለማረጋገጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
በዮሐንስ ወንጌል “ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም” ብሎአልና፣ በርግጥም ቤተክርስቲያን ለተለየ ሥራ
የተጠራችና የተለየች ኅብረት ናት። ዮሐንስ 16፡ 19 እውነተኛው
የክርስቶስ የድነት ወንጌል የሚገኘው በቤተክርስቲያን ዘንድ ነው። በሐዋሪያት ሥራና
በሌሎችም የሐዋሪያው የጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ እንደምንረዳው ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች ኅብረት ስትሆን ይህን ኅብረት
የሚመሠርቱ ወገኖች ከተለያዩ ሕዝቦች ሆነው አንድ ወይም የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው። አንድ
የሚያደርጋቸውና ኅብረታቸውን ጠንካራ የሚያደርገው ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኝ በይፋ መቀበላቸውና መከተላቸው ነው።
የራሳቸውን አንድነትና ኅብረት የሚመለከቱት በዓለም መመዘኛ ሳይሆን በክርስቶስ መመዘኛ ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስ ለኤፌሶን
ቤተክርስቲያን የአንድነት መሠረታቸው በክርስቶስ ላይ ብቻ መሆኑን የጻፈው ለእኛም ብርቱ ማስገንዘቢያና ትምህርት
እንደሚሆነን አምናለሁ።
ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም
በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ። በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ
ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፣ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ። ከሁሉ
በላይ የሆነ በሁሉም የሚሠራ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አምላክ አለ። ኤፌሶን 4፡ 2-6 የቤተክርስቲያንን
ትርጉም በጣም ባጭሩ ተመልክተናል። እንዲሁም ቤተክርስቲያን ከዓለም የተለዩ ወገኖች ኅብረት እንደ ሆነችም መሠረቷና
አንድነቷ ክርስቶስ እንደሆነ አይተናል። ሆኖም ቤተክርስቲያንን ቤተክርስቲያን ሊያሰኙአት የሚችሉትን ነገሮች ደግሞ
እንመልከት። እውነተኛ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን የሚከተሉትን ነገሮች በትክክል የምትፈጽም መሆን አለባት። የጌታ የኢየሱስ
ክርስቶስ የድነት ወንጌል በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተገለጸው የማይሰበክባትና ትምህርቱም የማይሰጥባት፣ ቅዱስ ጥምቀትና
ቅዱስ ቁርባን በታዘዘው መሠረት የማይከናወንባት ቤተክርስቲያን፣ ቤተክርስቲያን ሳትሆን እንዲሁ የሰዎች ስብስብና ሌላ
ተልእኰ ያላት ትሆናለች። ስለዚህ በተለይም የተለያዩ ትምህርቶች በሚሰጡበት በዚህ ዘመን ብዙዎች ሳይላኩ እየተላኩ፣ ከቤት
ወደ ቤት፣ ከግለሰብ ወደ ግለሰብ እየሄዱ ቤተክርስቲያን ልትቆጣጠርና ልትከታተል የማትችለውን በርካታ የስሕተት ትምህርቶችን
በማስተማር የዋሁንና አዳዲስ አማኒያንን እንዳያሳስቱ ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል።
ክፍል ሁለት፦ የቤተ
ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆች
ክፍል ሦስት፦ መሪነት
ቄስ ፍራንሲስ
እስጢፋኖስ የቤተክርስቲያን መሪና የአዲስ ሕይወት አገልግሎት ዳይሬክተር ናቸው።
በፍራንሲስ እስጢፋኖስ
ይቀጥላል…

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org