ሞት ፍጻሜ ነው ጅማሬ?
በምትኩ አዲሱ

ክፍል አንድ

መግቢያ

ሞት ፍጻሜ ነው ጅማሬ? የሚለው የቆየና የሰውን ልጅ ያነጋገረ ጥያቄ ነው። ሞት ፍጻሜ ነው የሚሉ አሉ:: ጅማሬ ነው የሚሉም አሉ። የማናቸው ነው ልኩ? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ የሕይወታችንን ዓይነትና አቅጣጫ በከፊልም ቢሆን ይገልጻል፣ ይወስናል። አንደኛው “እንብላ፣ እንጠጣ፣ ነገ እንሞታለን” የሚል አስተሳሰብ ይኖረዋል። ሌላኛው “እንብላ፣ እንጠጣ፣ ነገ እንሞታለን፤ … ግን እንጠየቅበታለን“ ይላል። ከሁለቱም ወገን ያልሆነው ደግሞ “ከሞትኩ በኋላ ለሚሆነው እኔ ምን አሳሰበኝ? … ሲደርስ አስብበታለሁ” እያለ በቀጠሮ ያቆየዋል።  

እያንዳንዱ ትውልድ በበራለት መጠን የሞትን ምሥጢር ለመረዳት ያላቋረጠ ጥረት አድርጓል። የጥንት ግብጻውያን ለምሳሌ፣ ሞትን ረጅም ጉዞ ከመሄድ ጋር ያመሳስሉት ነበር። ስለዚህም ለሟች ስንቅ ይሰንቁለታል፤ ሰውነቱ እንዳይፈርስ በልዩ ቅመም ይገንዙና ጓዝ ንብረቱን አስይዘው ይሸኙታል። በዚህ አድራጐታቸውም ዘላለማዊነትን እንደሚቀዳጁ ያስባሉ። ሟች በሌላ ተመስሎ ይመለሳል የሚል እምነትም ነበራቸው። ግሪኰች ደግሞ ሰው የማይሞት ነፍስ አለው ይሉ ነበር። አይሁድ፦ ዘር በመተካቱ፣ በመልካም ስሙና ግብሩ ሰው ለዘላለም የሚተርፍ መታሰቢያን ያገኛል ይላሉ። በአንጻሩ፦ ክርስቲያኖች ሰው ከሞተ በኋላ ሞትና ዘመን የማይገዛውን አካልና ሕይወት በትንሣኤ ይቀዳጃል፤ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወቱም በፈጠረው አምላክ ፊት መልስ ይሰጥበታል ብለው ያምናሉ።

ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት፣ ከእርሱ በኋላም ፍርድ (ተመድቦባቸውዋል) … መልካም ቢሆን ክፉ እንዳደረገ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና … እንግዲያስ፣ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” (ዕብራውያን 927-28፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 510፤ ሮሜ 1412)።

ወደድንም ጠላን የሞት ጥያቄ ሰው ሁሉ በግልና በጋራ መልስ ሊሰጥበት የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው። እንግዲያስ፣ ምን መልስ ይዘሃል? እርግጠኛ መልስ ይዘሃል? ከሁሉ በፊት ጥያቄ ሊሆን የሚገባው ይኸ ነው።

ሞት

ስለ ሞት ያለን አመለካከት ኑሮአችንን ብቻ ሳይሆን ከሌሎችና ከአካባቢአችን ጋር ያለንን ግንኙነት ይወስነዋል ብለናል። ስለ ሞት ያለን መረዳት በክሕደትና በቀልድ ላይ የተመሠረተ ከሆነ ለራሳችን ሕይወት ሆነ ለሌሎች ያለን አክብሮት እንደዚሁ ያነሰ ይሆናል። ከራሱ አልፎ ለሌላው መልካም ቅርስ መተው ወንጀል የሚመስለው ሰው አለ። “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” የሚለው አባባል እንዲያው በአህያ ይላከካል እንጂ ለአንዳንዱስ የሕይወቱ መመሪያ ነው! ለእንዲህ ዓይነቱ ሰው ሞት አፋፍ ደርሶ መመለስ ካልሆነ በስተቀር ጥሩ መካሪ አይገኝለትም። ከልብ ድካም፣ ከከባድ አደጋ፣ ከወህኒ እሥራት የተረፉ ሰዎች ወይም የሞት ገመድ አንገታቸው ላይ የገባላቸው አኳኋናቸው ከቀድሞው በጣሙን የሚቀየረው ለዚህ ነው። እያንዳንዷ ትንፋሽ የግዜር ስጦታ እንጂ የሰው ችሎታ እንዳልሆነች ወደ መረዳት ይደርሳሉ። የወዳጅ ቀርቶ የመንገደኛው ሰላምታ፣ የወፉ ጫጫታ፣ የማታ ጀንበር፣ የጧት ጮራ፣ ቡና ተቆልቶ ሲወቀጥ፣ ቁራሽ እንጀራ በድቁስ ከባልንጀራ ጋር መቁረስ፣ ልጆች መስክ ላይ ባዶ እግራቸውን ሲጫወቱና ሲሳሳቁ፣ ቁጭ ብሎ ማውራቱ፣ ሲያስገመግም ሰማዩ፣ ቀድሞ እንደ ቀላል ይታዩ የነበሩ ነገሮች አሁን ልዩ ጣዕምና ትርጉም ይሰጣሉ። “እንዴት አደርክ፣ እንዴት አመሸሽ” ያምራል፣ ይናፍቃል።

የአገራችን የተማረው ክፍል ግን ከሞትና ከረጅም ዘመን ሐዘንና ስደት ጋር እየኖረም፣ እርስ በርሱ ባለው ግኑኝነት ገና ጠቃሚ ትምህርት የቀሰመ አይመስልም። ለምን ይሆን?

የሞትን ኃይል መገንዘብ የሥልጣኔ በር ከፋች እንደሆነ ይነገራል። የሞትን ኃይል ለማክሸፍና ለማዘግየት የሚደረገው ጥረት እንደዚሁ ለተለያዩ ሕክምና ግኝቶች ምክንያት ሆኗል። ይህ ግኝት እርጅናን ለማዘግየት የሚደረገውን ሙከራ ይጨምራል። ሰዎች የተወሰነላቸውን ዘመን በእርጅናና ኋላም በሞት ሳይቀሙ በፊት የተቻላቸውን ያህል ሊደሰቱበትና መታሰቢያ ሊያገኙ ይጥራሉ፣ ይፍጨረጨራሉ። የአንዳንዶች መታሰቢያ ሞትን በማራባት ይሆናል። ባጭሩ ግን፣ ሞት ፍጻሜ ነው የሚሉ ሞት ጅማሬ ነው ከሚሉት የተለየ አመለካከት ይኖራቸዋል ማለት ነው።

የዕልቂት ዘመን ደግሞ የሚያሳድረው አስተሳሰብ አለ። የአብዮተኞች ሽብር “ዛሬ ውዬ መግባቴን እንጃልኝ” እስከ ማለት አድርሶ ነበር። በአገራችን የተዛመተው የኤይድስ በሽታም እንዲሁ ስለ ሞት አጽንተን እንድናስብ አድርጓል። ከ1980 እስከ 1984 የተደረገ አንድ ጥናት በ 5 እና 14 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉት ይልቅ ከ 25 እስከ 39 ባሉቱ ላይ ሞት እንደበረታ ያስረዳል። በነዚሁ ዓመታት ውስጥ በ 35 እና 39 ዕድሜ ክልል ባሉት ውስጥ የሟች ቁጥር በአምስት እጥፍ አድጓል። የዛሬ ሠላሳና አርባ ዓመት ሞት ለአዛውንትና ለጦረኞች ብቻ እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ዛሬ ግን ወላጅ ወልዶ አሳድጐ አስታምሞ ቀባሪ ሆኗል። ለዘላለም የሚኖር የሚመስለው የነበረ ወጣት ነገሩ ተገልብጦበታል። ያገኘውን ቶሎ ቶሎ ብሎ ተደስቶ ማለፍን አማራጭ የሌለው ቁርጠኛ አሳቡ አድርጐታል። የዚህ ትውልድ ወደ ውጭ ለመጉረፍ አንዱ ምክንያት ይኸ ይሆን? በቃሉና በያዘው የማይጸናውስ ለምን ይሆን?!

ሞት አይቀርም

“ሞት አይቀርም፣ ስም አይቀበርም”፣ “ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከመሬት”፣ “ሁሉ ሟች ነው” ማለት የተለመደ አነጋገር ነው። ተናጋሪው ግን በአብዛኛው ራሱን በአባባሉ ውስጥ ጨምሮ አይመለከትም። ሟች ሁልጊዜ ወዲያ ማዶ ያለ ሌላኛው ሰው ነው። ለዚህም ነው በጦርነት መቶ ሺ ሰው አለቀ ሲባል ከወሬነት የማያልፈው፤ ክብደቱን መመዘን የሚያዳግተው። ተራ ሲደርሰን ግን ለመታዘብ ፋታም አይሰጠንም። 

“እኔም እኰ ሟች ነኝ” ብሎ ማሰብ ቢችል አለመተዛዘንና መናቆር በቀነሰ። የሕይወትን አጭርነት በመገንዘብ ውስጥ በጐ ማድረግ በጨመረ። አልለመድ ያለ እንደ ሞት ምንም የለም። ሁሌ አዲስ ነው። ሰው ለሞት እንዳልተፈጠረ፣ ዘላለማዊ እንደ ሆነ ይኸ አንዱ ማስረጃ አይደለም ወይ? በሥራ ብዛት፣ በጨዋታ ብዛት፣ በመብላትና በመጠጣት ብዛት የሞትን አሳብ ለመርሣት ይጥራል፤ ግን ዕረፍት አያገኝም። ረጋ ማለት መልካም ነው።

ለጥቂቶች ሕይወት ካለመኖር ወደ አለመኖር የሚደረግ ጉዞ ነው። እነዚህ የሚያስቡት አሁን የሚገኙበት ሁኔታ የሚያስገኘውን ጥቅም ብቻ ይሆናል። ቅድም እንዳልነው ስለ ሞትና ከሞት በኋላ ስለሚመጣው መቸጋገር ሥራ መፍታት እንደሆነ ይገምታሉ። ለብዙዎች ግን ጉዞው ከሕይወት ወደ ሕይወት ነው። እርግጥ ዝርዝሩና አተረጓጐሙ ይለያያል።

·        ለሒንዱ እምነት ተከታዮች ለምሳሌ፣ ሕይወት ከባሕር እንደ ወጣ ጠብታ ነው፤ ሞት ደግሞ ጠብታው ወደ ወጣበት ባሕር መመለሱ ነው።

·        ለቡዲስት እምነት ተከታዮች ሕይወት የሚጠፋ ሻማ ብርሃን ነው፤ ከዚህ ሕይወት ወዲያ የሚቀር ነገር አይኖርም ይላሉ።

·        በክርስቶስ ለሚያምኑ ሕይወት ከሕይወት የተገኘ ነው። ሰው ከዘላለማዊነት ለዘላለማዊነት የተሠራ ፍጡር ነው። ኢየሱስ አልዓዛር መቃብር አጠገብ ቆሞ ያነባው አልዓዛርን ስለሚወደው ብቻ ሳይሆን ሞት ያልተገባውን ሥልጣን ማግኘቱን በማሰብ ነው፤ ሰውን ከሕይወት አፈናቅሎ ማንገላታቱን በማሰብ ነው። ያንን የቀደመውን የጸጋ ክብር በሞቱና በትንሣኤው ኃይል ሊነጥቅ ቀንቶ ነው። (ዮሐንስ ወንጌል 11)። ሞት በመሠረቱ ከአምላክ ርቆ የመኖር ውጤት ወይም የኃጢአት ውጤት ነው። በክርስቶስ በኩል ዕርቅ ስለ ተደረገ፣ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የጠፋ ልጅ ወደ ወላጁ እንደሚመለስ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ ለዘላለም መኖር ይቻላል ይላሉ።  

እያንዳንዱ ኅብረተሰብ በጠቢባኑ፣ በባለ ቅኔዎቹ በኩልና እንደ ደረሰበት የባሕል ዕድገትና ለውጥ የሞትን አኳኋን ለመታዘብ ጥሯል። ግሪኰች ለምሳሌ፣ ሞት የእንቅልፍ ታናሽ ነው ይሉናል። እንግሊዛዊያኑ ድራይደንና ኪትስ (በ17ኛውና በ19ኝኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኖረው የሞቱ) ከግሪኰች ተቀብለው ሞትን “ተኝቶ አለመንቃት” ነው ብለውታል። ይህን እንኳ ያገራችንም ሰው አያጣውም። ሩሲያዊው ቶልስቶይ ደግሞ “ሕይወት እንደ አረፋ የሚሟሟ ከሆነ ይህ ሁሉ ትግልና መንገላታት ታዲያ ምን ትርጉም ይኖረዋል?” ሲል ለሰው ሁሉ የሚተርፍ ጥያቄ ጠይቋል።

የኛው ባለ ቅኔ ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ “የት አባቱ! ሞትም ይሙት!” በተሰኘው ግጥሙ (1963)፦

እባካችሁ ዘመዶቼ፣ ስሞት ሞትም አብሮኝ ይሙት

                  …

            በሙሾ ግነን አትበሉት

                  …

በዳንኪራችሁ ውገሩት

            ከአጥንቴ በታች ቅበሩት። ብሏል።

ሞት ዘመድ አይሆንም፤ ሞት መሸነፍ ያለበት ኃይል ነው ማለቱ ይሆን? ወይስ ፍጻሜ ስለሆነ ቋሚው አይድከም ማለቱ ነው?

ትንሣኤም አይቀርም

ጳውሎስ ሐዋርያው በግሪክና በአይሁድ ባሕል የሠለጠነ የሕግ ምሑር ነበረ። የሞትን ምሥጢር ለመፍታት የተደረገውን ያልተሳካ ጥረት ታዝቧል። ሞት የኃጢአት ውጤት መሆኑን ተረድቷል። ሁለት ሕግ ማለትም የሞት ሕግና የሕይወት ሕግ በሰዎችና በዓለም ውስጥ እንደሚሠራም ተረድቷል። “መልካም ነገር የማድረግ ፍላጐት ቢኖረኝም ያንን መልካም ነገር የማድረግ ችሎታ የለኝም … የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁ … የኃጢአት ሕግ እስረኛ የሚያደርገኝ ሌላ ሕግ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ መኖሩን አያለሁ … ወደ ሞት ከሚወስደኝ ከዚህ ጐስቋላ ሰውነትስ ማን ያድነኛል” (ሮሜ 77-25)? በሌላ ሥፍራ ደግሞ እንዲህ የሚል ተጽፏል፦ “ሥጋና ደም ያላቸው ሰዎች እንደ መሆናቸው መጠን፣ ኢየሱስም እንደ እነርሱ ሰው ሆነ፤ ይህን ያደረገውም በሞቱ አማካይነት በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስን ለመሻር ነው። እንዲሁም ሞትን በመፍራት ምክንያት ዕድሜ ልካቸውን በባርነት ይገዙ የነበሩትን ለመዋጀት ነው … ” (ዕብራውያን 214-15)።

የናዝሬቱ ኢየሱስ ከሙታን ተነስቶ ከተገለጠለት በኋላ፣ ጳውሎስ የሞት ሥልጣን እንደ ተሻረ ማወጅ ጀመረ። “ሞት የመጣው በአንዱ ሰው በአዳም (ባለ መታዘዙ) ምክንያት እንደሆነ፣ ከሞት መነሣትም የሚመጣው በአንዱ ሰው በክርስቶስ (መታዘዝ) ምክንያት ነው … የሞቱ ሰዎች የሚነሡት እንዴት ነው? ከሞት ሲነሡ የሚኖራቸው አካልስ ምን ዓይነት ነው? … አንተ ሞኝ! የምትዘራው እህል ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም፤ አንተ ስትዘራም ስንዴ ወይም ሌላ እህል ብቻ ትዘራለህ እንጂ በኋላ የሚበቅለውን ተክል አይደለም። እግዚአብሔር ግን ለዘሩ እንደ ፈለገ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር ልዩ ልዩ አካል ይሰጠዋል … እነሆ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ… ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ፣ በዚያን ጊዜ፦

ሞት ድል በመነሳት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፣ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፣ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን (1ኛ ቆሮንቶስ 1521-22፣ 35-38፣ 51-57)።

ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ በስተርጅና በተሰጠው የዓለም ፍጻሜ ራእይ እንዲህ ይላል፦

“ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፤ … ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ … እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፣ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኅዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” (ራእይ 2013-14፤ 213-4)።

ድንቅ ነው! ድንቅ ነው! ለዘላለም አልፈታ ብሎ ትውልድን ሲያንገላታ የቆየ ምሥጢር እነሆ በክርስቶስ ተፈትቷል! አለማወቅ ወይም አለመታዘዝ ካልሆነ በስተቀር ከንግዲህ መንገላታት አያሻም ማለት ነው። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ይላል ኢየሱስ። “የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፣ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” ይላል ከሙታን የተነሣው። (ዮሐንስ 11፡ 25-26)። “አትፍራ፣ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ” ይላል። ስለ ሞት ምንነት አስረግጦ መናገር የሚችል የሞትን ጣር ቀምሶ ከሙታን የተነሣው ብቻ ነው! ፈላስፎችን፣ ሃይማኖተኞችን፣ ተራውን ሰው ሳይቀር በፍርሃት ምሥጢር አስሮ ያስገበረውን ድል ያደረገ ብቻ ነው! ይህን ያደረገ ከኢየሱስ በስተቀረ ማንም የለም። 

ይቀጥላል …