የከበረውን ከተዋረደው ብትለይ …
በፀሐይ ዓለሙ

 

በዓለም ውስጥ የክብር ሥፍራና ደረጃ የሚሰጣቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ለምሁራን የተለየ የክብር ደረጃ እንሰጣቸው ይሆናል፤ ትምህርትም ቢሆን በዓይነቱ የከበረ ነውና። ለባለ ጸጐችም ልዩ ቦታ እንሰጣቸው ይሆናል፤ ሃብት ወይም ገንዘብ ጠቃሚ ነውና።

ሆኖም “የከበረና የተዋረደ” የሚለውን ሃሳብ ልናመሳክር የሚገባው ከሰው የውስጥ ሕይወት አንጻር ነው።

ሰው ከሌላው ፍጡር ይልቅ ልዩና ክቡር ነው። የውስጥ ሕይወቱም የተወሳሰበና ጥልቅ ነው። ሁል ጊዜ ጥያቄ አለው። እውነቱንና ልኩን እንዴት አውቃለሁ? ስሕተቱን እንዴት እለያለሁ? ይላል።

ይህን ጥያቄውን ሰው በራሱ ሃሳብ ተወስኖ በሚመስለው መንገድ ከመለሰው ይስታል። አንድ ምሪት የሚሰጥ ከሰው የተለየ ኃይል ያለው፣ የበላይ ያስፈልገዋል። ያም እግዚአብሔር ከሆነ ብቻ ነው።

ሰው ከዚህ የሕይወት ምንጭ ከሆነ ጌታ ጋር መገናኘቱና ማን መሆኑን መረዳቱ፣ ራሱንም መገንዘቡ ይበጀዋል። እግዚአብሔር ለሚፈልጉት ሁሉ ቅርብና ዕውን ነው። ለሕይወት አቅጣጫና ትርጉም መስጠት ይቻለዋል።

          ውሃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ
          የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም
          ተራቡ፣ ተጠሙም
          ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች
          በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ
          ከመከራቸውም አዳናቸው
          ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ
          የቀና መንገድን መራቸው። መዝሙር (107)፡ 4-7

አዎ፣ እግዚአብሔር ለያንዳንዱ ሰው የቀና ሃሳብና ምሪት አለው። እርሱ ለሕይወት ትክክለኛውን ትርጉምና መፍትሔ ሰጭ ነው። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሕይወቱ ሲገናኝና ሲያያዝ ለምን እንደ ተፈጠረ፣ ወዴት እንደሚሄድ ይረዳል። ስለዚህ እርካታ ሊሰጠው የሚችለውን ትክክለኛ ምሪት ከአምላክ እንዲያገኝ መፈለግና መፍቀድ ይጀምራል።

ሰው ግን የእግዚአብሔርን ምሪት ባያውቅና ባያገኝ እጅግ ይጐዳል። ይስታል። መመዘኛ ስለማይኖረው እውነቱን ከስሕተት መለየት ይሳነዋል። ዕድሜውን በከንቱ ያባክናል። የእግዚአብሔር ምሪት በሌለበት ነገር ውስጥ መማሰን ትርፉ ኪሳራ ነው።

          ገንዘብን እንጀራ ላይደለ
          የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር
          ለምን ትመዝናላችሁ? ኢሳይያስ 55፡ 2

ይህን በሚመስል መንገድ እየሄደ የሚባዝነው ሰው እጅግ ብዙ ነው። ለሰው የራሱን ምርጫና ፍላጎቱን ለማድረግ መሮጡ ዋናው ሃሳቡ ነው። ነገር ግን ሊያሳርፈው የሚችለው የአምላክን ምሪት ተከትሎ ልክ የሆነውን ነገር ማድረጉ ነው። የብዙዎች ዐይን ግን ለዚህ ነገር የተከፈተ ሳይሆን የታወረ ነው። ምን ጊዜም ቢሆን ከእግዚአብሔር ሃሳብና ምሪት ውጪ የሆነ ነገር ሁሉ አናሳና ተራ ነው። ሰው ራሱን በጥልቅ የሚያውቅ ፍጥረት አይደለም። ያወቀ ግን ይመስለዋል። የሚመስል ነገር ሁሉ ልክ ነው ማለት አይደለም። የእግዚአብሔር ሃሳቡና መንገዱ ግን ትክክልና ክቡር ነው። ይህን ለመረዳት የከበረውን ከተዋረደው የሚለይ ማስተዋል ያስፈልጋል።

የሰው ሁሉ ድካሙ ወደ ፈቀደው ሃሳብ ማዘንበሉ ነው። ለጊዜው የሚጠቅም መስሎ ስለሚታየውም ነው። ከሚታየው ነገር አልፎ የማይታየውን እውነት የማወቅና የማየት አቅም የለውም። የአሁኑን እንጂ የረጅሙን ዘመን ውጤት መረዳት አይችልም።

ይህች “የእግዚአብሔር ፈቃድ” የምትባል ነገር ልዩና ምሥጢር ናት።

          ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ
          እግዚአብሔርን መፍራት
          የሕይወት ምንጭ ነው። ምሳሌ 14፡ 27

ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ያሉት ነገሮች ሁሉ ደግሞ የሞት ያህል ለሕይወት ወጥመድ ናቸው። እግዚአብሔርን ቀረብ ብሎ የለመደው ሰው የፈቃዱን ምሪት ለይቶ ያውቃል። አንዳንዴ የራሱ ፈቃድና ሃሳብ አይሎ ሲታገለው እንኳ ጥርት ያለው የአምላኩ ምሪት ወለል ይልለትና መለስ ያደርገዋል። እንደዚህ ያለው ሰው “የከበረውን ከተዋረደው” ለይቶ ያውቃል ማለት ነው።

          ብትመለስ እመልስሃለሁ
          በፊቴም ትቆማለህ
          የከበረውን ከተዋረደው ብትለይ
          እንደ አፌ ትሆናለህ። ኤርምያስ 15፡ 19

ስለዚህ ለሰው ሕይወት ልኩ በእግዚአብሔር ሃሳብና ፈቃድ ውስጥ መመራቱ ብቻ ነው። የተሳተች ክቡር የአምላክ ፈቃድ ግን ከተሳተች በኋላ አትስተካከልም።

ዕቃ ያለ ግጣሙ አይስማማም፤ ልብስም የሚያምረው በየፈርጁ ሲለበስ ነው። ሰውም የሚያምርበት በቦታው ሲሆን ነው፤ ቦታው ደግሞ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ መሆን ነው። 

          የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል
          ከመከራም ሥጋት ያርፋል። ምሳሌ 1፡ 33

          የእግዚአብሔር መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው። ምሳሌ 10፡ 29 

          የእግዚአብሔር በረከት ባለ ጠጋ ታደርጋለች
          ኅዘንንም ከርስዋ ጋር አይጨምርም። ምሳሌ 10፡ 22

እግዚአብሔር በሥራው ፍጹም ነው። አደራረጉም ግሩም ነው፤ በዚያም ውስጥ ፀፀት የለበትም።