ሞት ጅማሬ ነው ወይስ ፍጻሜ? [ክፍል 2]

በምትኩ አዲሱ

 

መግቢያ

በክፍል አንድ የሚከተሉትን አሳቦች ተመልክተን ነበር። 1. ሰው ሟች እንደ ሆነ፣ የሞትን ምንነት ለመረዳት እንደሚጥር 2. ስለ ሞት ያለን መረዳት ግላዊና ማኅበራዊ አኗኗራችንን እንደሚወስነው 3. ለመኖር ያለው ጥማት ሰው ለሞት እንዳልተሠራ እንደሚያስረዳ 4. ከሞት በኋላ ሕይወት አለ/የለም የሚሉ ሁለት ዋነኛ አመለካከቶች እንዳሉ 5. ከሞት በኋላ ሕይወት ካለ፣ “ከሞት በኋላ ሕይወት የለም” ሲሉ የኖሩት ኪሣራቸው የከፋ እንደሚሆን 6. በክርስቶስ ከሙታን መነሣት የሞትና የሕይወት ፍርሃት ምላሽ እንዳገኘ፤ በክርስቶስ የሚያምኑ የጸና ተስፋና የተዋበ ፍጻሜ ከዚሁ ጀምሮ እንደሚቀዳጁ።

መቃብር ለቋሚውና ለሟቹ ምድራዊ አድራሻው ነው። ይህንኑ አሳብ ቀጥሎ እንመለከታለን።

ክፍል ሁለት

መካነ መቃብር

አልፎ አልፎ መካነ መቃብር መጐብኘት ስለ ሞትና ስለ ሕይወት ጉዳይ እንድናስብ ያስገድደናል። ጥጋብ ያታልለናል። የወዳጅ ብዛት፣ የሥራ ብዛት፣ የብልጽግና ብዛት ያዘናጋናል። ሥልጣን ያስታብየናል፣ ያሰክረንና ሟች መሆናችንን እንኳ ሳይቀር ያስረሳናል። መጽሐፍ ግን እንዲህ ይለናል፦

“ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፣ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፣ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። … የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፣ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው” (መክብብ 72-4)

የምናውቃቸውን ተሸክመን ቀብረን እንመለስና፣ ሌሎች ደግሞ በተራችን ቀብረውን ይመለሳሉ። የሰው ሕይወት መቀባበር ብቻ ነው ማለት ነው? ለመኖር የሚወተውተውንና የሚጓጓውን ውስጣችንንስ መቅበር ከቶ እንዴት ይቻላል? ረሃብ መኖሩ ምግብ መኖሩን ያስረዳል። ለመኖር መጣጣር ደግሞ እዚህ እንዳልተወሰንን፣ ይልቅ ነገ እንዳለ፣ ዘላለማዊነት እንዳለ ይጠቁማል።

“እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ በመወሰን ሁሉን ነገር ውብ አድርጐ ሠርቶታል፤ ዘላለማዊነትንም በሰው ልቦና አሳድሮአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሁሉ እስከ መጨረሻ ያውቅ ዘንድ ለሰው የተሰጠው እውቀት ሙሉ አይደለም” (መክብብ 211)

ቀብር ላይ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይከናወናሉ። ጸሎት ይደረጋል፤ ፍትሃት ይደረጋል። ለአንዳንዶች ሙሉ ፍትሃት፤ ለሌሎች እንደ ነገሩ። ይህ አድልዎ ለቀሪው ቤተ ዘመድና ለራስ እንጂ ለተሻገሩት ምንም ለውጥ አያመጣም። አንዳንዶች ቅዱስ ዮሴፍ ይቀበራሉ፤ ሌሎች ጴጥሮስ ወጳውሎስ። ለብዙዎች መሬት ጫር ጫር ተደርጐ።

አንዳንዶችም በገዛ አገራቸው መቀበሪያ ያጣሉ። ብዙዎች ጦር ሜዳ ላይ ሳይገነዙ፣ በባዕድ ምድር ተበትነዋል። በዕብነ በረድና በብረት አጥር የደመቀ መቃብር አለ። እንደ ዙፋን የደረጀ አለ። ለምልክት የራስጌ ብረት ብቻ የተደረገለት አለ። የራስጌ ምልክት እንኳ ያጣ አለ። የተመዘበረ አለ። የፈረሰ አለ። ሌላውን ለመቅበር የሚረማመዱበት አረም የበላው አለ። የሰው ዕዳሪ የከበበው አለ። ሌላ ተደርቦ የሚቀበርበት አለ።

“ሰው ከንቱ” ብለህ ጻፍ

ሟቹን እጅግ የሚያገንን ዜና ዕረፍት አለ። ዜና ዕረፍቱ መሸነጋገያ፣ መካካቢያ፣ እግዚአብሔርን ማባበያና መደለያ የሚመስልበት ወቅት አለ። የአንዳንዱ ደግሞ ቀብሩም ጥድፍያ ስለሚሆን ከሰው ያነሰ ፍጥረት ያስመስለዋል።

ይህም ሆኖ በሞቱም እንኳ ሰው ሰው ነው። ልዩ ነው። ዝነኛ ቢሆን ባይሆን ታሪክ አለው፤ ክቡር ነው። አፈርን ያበጀ፣ እስትንፋሱን እፍ ያለበት ሕያው እግዚአብሔር ነውና። ሰውን ሰው ያሰኘው በአምላክ አምሳል መፈጠሩ ነው። ባጭሩ፣ ሰው ለተባለ ሁሉ ተመን አይገኝለትም። የሰው ተመኑ በፈጣሪው እጅ ሥራ ልክ ነውና። ይህ አስተሳሰብ እርስ በርስ ለመከባበሪያ ጐዳናው ነው።

ሞት ያፈረሰው በመታሰቢያው ጽናት ተመልሶ ቋሚውን ያጽናናል፣ ያሳስባል፣ ያነጋግራል። ይህን እያሰበ ሳይሆን አይቀርም ሰዓሊው ባለ ቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ መካነ መቃብር ሄዶ በድን ለማነጋገር የበቃው፦

ማነህ የተኛኸው?

እንቅልፍ የደበተህ ሥጋህን ጥለኸው።

ምን ኖረሃል አንተ

ንጉሥ ኖረሃል ወይ፣ ኖረሃል ወይ ጌታ?

ወይ ቁርንጮ ለባሽ ለማኙ ከርታታ?

ጉድ ነው! መልክህ የለም።

ማነሽ ማነህ አንተ?

ማናችሁ እናንተ?

ያሻሃል ምስክር

ሞተህ ስትቀበር

ድንጋይ ላይ ተጽፎ የሚናገርልህ

ምልክት የሚሰጥ አንተ ለመሆንህ፤

ሐውልት የሚያቆይህ

ዘመድ ያስፈልጋል ከሌላው ለይቶ

መንገደኛ እንዲያውቅህ ቆሞ ተመልክቶ።

                       

[“አፅም”(1949)]

 

                         

የታሪክ ማኅደር

መካነ መቃብር ግለሰቡ የኖረበትን ዘመንና ሁኔታ የሚያስረዳ ራሱን የቻለ የታሪክ ማኅደር ነው። በጉለሌ መካነ መቃብር የኡጋንዳ፣ የኬንያ፣ የህንድ፣ የታንዛኒያ፣ የሮዴዥያ (የዛሬዋ ዚምባብዌ)፣ የሱማሌ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የእንግሊዝ ወዘተ ወታደሮች አርፈዋል። ከአጠገቡ ደግሞ የኢጣልያ ወታደራዊ መካነ መቃብር ይገኛል። እነዚህን ምን አመጣቸው? ጠላቶቻችንና ባዕዳን ሆነው ሳለ እንዴት ያገር ልጅ ያላገኘውን መታሰቢያ ሊያገኙ ቻሉ? ይህን መጠየቅ ወደ ኋላ ሰባ አመት ይመልሰናል። የፋሺስት ኢጣሊያን ወረራ ያስታውሰናል። የአውሮጳን ቅኝ ግዛት ታሪክ ያስረዳናል። የራሳችንን በመናቃችን የታሪክ ክስ ይመሠርትብናል፤ የኅሊና ሙግት ያነሳብናል።

የኢትዮጵያ አብዮተኞች መካነ መቃብር ከሌላው ዜጋ ተከልሎ መሠራቱ የደርግን አገዛዝ ይገልጸዋል። እንግዲህ በቀብሩ ላይና ዙሪያ ከመስቀል ይልቅ የመስኰቦች ማጭድና መዶሻ፣ ከመላእክት ምስልና ከወንጌል ቃል ይልቅ የነ አያ ሌኒን ቃል ቢገኝበት ምን ይደንቃል?

የሟችን ፊት በፀሐይ መውጫ ትይዩ ማድረግ በአገራችን የተለመደ ነው። ይህም ለትንሣኤ ቀን ዝግጅት እንደሆነ ይታሰባል። መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል ይላልና፤

መቃብር የማይገኝበት የምድር ጥግ የለም። በዝዋይ-ሻላ-ላንጋኖ-ሻሸመኔ-አርሲ መንገድ ዳር ሐውልቶች ተኰልኩለዋል። እነዚህም እንደ ጥሩ ወንጌላዊ አላፊ አግዳሚውን ያሳስባሉ፣ ይወቅሳሉ።

ሙታኑን የማያከብር ሕዝብ ለቋሚው ይራራል ማለት ዘበት ነው።

ባለ መኪናዎች መካነ መቃብር አጠገብ ሲደርሱ ዝግና ጸጥ እንዲሉና በሰዓት ከአስራ አምስት ኪሎ ሜትር በላይ እንዳያሽከረክሩ ሕግ ቢወጣስ? ከመንገዱ ዳርቻ ደግሞ፣ “ፍጻሜዬ እንዴት ይሆን?” ወይም “ምን ቅርስ ይሆን ትቼ የማልፈው?” የሚሉ ቅስቶች ቢተከሉስ?

 

Text Box:  
 
 
ቂም ይዤ እንዳልሞት ብቻ
                                        ፍጻሜዬ እንዴት ይሆን?

                                                        ቂም ይዤ እንዳልሞት ብቻ

 

የሐውልት ግንባታ

አንዳንዱ ሐውልት ተነባብሮ የተገነባ ነው። ይህ ልማድ ከጣልያን ጋር አገራችን እንደገባ ይነገራል። ከሦስተኛ ደርብ ላይ የሟች ፎቶ፣ ሁለተኛው ደርብ ላይ የፔፕሲ ኮላ ምልክት፣ ወረድ ብሎ ደግሞ የተጋደመ በግ ስዕል የሚታይበት አለ። በሌላ ሥፍራ ደግሞ የክላሸን ጠመንጃና የወታደር ልብስ ምስል ይታያል።

እዚህኛው ሟች ጦሩን ወይም ምንሽሩን ይዞ ቆሟል። ሟች በጥይት ነው የተቀነጠሰው ለማሰኘት ይሆን? ጠብ አይበጅም ለማሰኘት ይሆን? ባዕዳን መጥፊያችንን አቀበሉን ለማሰኘት ይሆን? እኔን ያየ ተቀጣ ማለቱ ይሆን?

እንግዲህ እንዳንጠይቀው ዝምታ ውጦታል፤ ችላ እንዳንል ዝምታው አያሳርፈንም!

ከስድሳ ስድስቱ አብዮት ወዲህ በሲሚንቶና በደማቅ ቀለም ያሸበረቁ መካነ መቃብሮችን ማየት የተለመደ ሆኖ ነበር። ክርስቲያኑንና እስላሙን፣ አማራና ኦሮሞውን ጐን ለጐን ማድረግ ያልተለመደ አይደለም። ሟች ፈረስ ላይ ተቀምጦ ጦሩን ሰብቆ ይታያል። ወይም በሬ፣ አንበሳና ነብር ከግርጌ አምረው ይታያሉ።

የአብዮቱን ድል ካላንጸባረቀ ስለ ተባለ ይሆን ይኸ ሁሉ ኪነ ጥበብ መካነ መቃብር የወረደው? 

መካነ መቃብር ምርኰአቸውን ይዘው ከወዲያ ወዲህ ይጣራሉ፣ ይነጋገራሉ፣ ያንሾካሹካሉ።

ከወዲያ ወዲህ ተጣርተው

ሙታን ባንድ ላይ ተቃጥረው

ያጫውታሉ የሞቱትን

ቆመው የሚሄዱትን

አንደኛው፦

  • “ሩጫዬን ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” ይላል።
  • ቀበል አድርጐ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበል”።
  • ካጠገቡ፣ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ይላል።
  • ይኸኛው፣ የተወለደበትና ያረፈበትን ዘመን አንግቧል።

 

Text Box:  

          አቶ፡ ቦሩ፡ በሪሶ፡ በ18-72-ዓ.ም
       ተወልዶ፡ በ1985 ግንቦት

13-9-85-ዓ.ም
          ከዚህ ዓለም
          በሞት ተለይ
          ቶዋል፡

እኛ ሐበሾች እንደ ፈረንጆቹ በሞትና በሟች ላይ መቀለድ አይሆንልንም። ምናችን ሞኝ? “ነግ በኔ!” ነው። እዚህ አሜሪካ ግን ታሪኩ ሌላ ነው። ጆርጂያ ግዛት ውስጥ ለምሳሌ፦

  • “አሞኛል ብያችሁ ነበር እኰ” ይላል።
  • ሌላ ሥፍራ ደግሞ፦ “በስሕተት ሰቅለውኝ” ይላል።
  • “ይቅርታ፣ አልተነሳሁሎትም” ይላል ሌላኛው፣ እንደ ተጋደመ።
  • “ትንሣኤ እጠብቃለሁ” የዚህኛው ነው።
  • “ሚስቴ እዚህ አርፋለች፣ እኔም አርፌአለሁ” ይላል፣ የተቸገረ ባል።

ሞትን መሸወድ ቢቻል

ሰው ከልደቱ እስከ ግብአተ መሬቱ ድረስ ሕይወቱ በሞት የታጠረ ነው። ከዚህ ወጥመድ ለማምለጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተያዘው ዘይቤ የራስን መታሰቢያ ዘላለማዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ነው። ይህም በአብዛኛው በለጸጉ በሚባሉ አገሮችና በአጠቃላይ የዚህ ምድር ሐብት በተወዳጃቸው ሰዎች አካባቢ የሚታይ ሽር ጉድ ነው። የምድሩ ድሎት አልበቃ ብሎአቸው የሰማዩንም ይቃሙናል። በአሜሪካ ባሁኑ ወቅት ሬሣን በጥንት ግብጻውያን ጥበብ አዘጋጅቶ ማቆየት የባለ ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ ሆኗል።

በአሜሪካ ግዛት በዩታህ የሚገኝ ድርጅት በአንድ ሬሣ 63 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስከፍል ታውቋል። ይህ ሁሉ ድካም፦ “እንደ ማንም አፈር ይብላኝ? … ይህን የመሰለ ገላ ላፈር?” ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ይመስላል። ራስን ከማምለክ የመነጨ ይመስላል። እነዚሁ የራሳቸውን ኰፒ ለመፍጠር የማይመለሱ ናቸው። የኔ ቢጤው በነርሱ ዓይን አይመዝንም፤ ለምድር ሸክም ስለ ሆነ መወገዱ ዕረፍት ነው። በነዚሁ ሚዛን ለምድር ፍግነት እንኳ የማይበቃ አለ። የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዲታው ክቡር በርሉስኰኒ በዕብነ በረድና በልዩ ጥበብ የተገነባ መካነ መቃብር ከመኖሪያ ቤታቸው ምድር ቤት ውስጥ አሠርተዋል። ሳይንስ የሞተውን ማንሠራራት ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል እምነት ስላደረባቸው የርሳቸውንና የቅርብ ዘመዶቻቸውን ገላ አመቻችቶ ለማዘጋጀት አስበው እንደሆነ ይነገራል።

እነሆ፣ ሳይንስ ሰው እውነትን እንዳያስብ እንቅልፍ የሚያስወስድ ዕፅ ሆኖበታል።

እዚሁ አሜሪካ አንድ ባልና ሚስት ዙፋን በሚያህል አልጋ ላይ ጐን ለጐን ተጋድመው ይታያሉ። ሞትም እንኳ አይነጣጥለንም ለማሰኘት ይሆን? የሐዲስ ዓለማየሁን “ፍቅር እስከ መቃብር” አንብበው ይሆን?!

የአትላንታ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ሚስተር ሜይነርድ በመሐል ከተማው ትይዩ ጉብታ ላይ ተጋድመዋል። ሲነሡ የሚወዷትንና ያስተዳደሯትን ከተማቸውን ቀድመው እንዲያዩ ይሆን?

አገራችን መካነ መቃብር ለመዝናኛነት አይታሰብም። ሌሊት ደግሞ የአጋንንት፣ የጅብ፣ የሌሊት ወፍና የእብዶች ክልል እንደሆነ ይታሰባል። እዚህ አሜሪካ ግን ለመዝናኛነት ይውላል። ጽዳቱ፣ በአበቦች በኩሬዎችና በተክል መድመቁ የሙታን ከተማ እንዳይመስል አድርጎታል። አስተዳደሩ የተደራጀ ስለሆነ ሙታን ከተጋደሙበት ሆነው ቋሚውን ያኖራሉ፣ ሥራ ያስይዛሉ፣ ይጦራሉ። ቤተ ሰቦች የሚበሉትን ጭነው ውሎአቸውን የሚዝናኑበት መናፈሻ አለው። ሕጻናት የሚፈነጩበት፣ ፎቶ የሚነሱበት ክልል ነው። ቱሪስቶች የሚጐበኙት ነው።

አንዳንድ ባልና ሚስት ደግሞ ፍቻቸውን ሳይቀር ለመፈጻጸም የሚቃጠሩበት አደባባይ ነው።

ዘመናዊ ሥልጣኔና ክህደት እንዲህ ከመስፋፋቱ በፊት ከልደት እስከ ግባ-መሬት የቤተ ክርስቲያን ወይም የቤተ ሃይማኖት ሥልጣን ነበረ። የዘመኑን ሰው ከቀደመው ትውልድ የሚለየው የዘመኑ ሰው ከነፍሱ ይልቅ ለሥጋውና ለመብቱ የላቀ ትኩረት መስጠቱ ነው።

ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ይቀበር የነበር ዛሬ ከቦታ ጥበት የተነሣ ይሁን በሌላ ምክንያት ልደቱና ሞቱ እየተቃረነ ሄዷል። ይባስ ብሎ ሌሎች ማኅበራዊ ድርጅቶች የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን እየተሻሙ ይገኛሉ። ለምሳሌ፣ በደቡብ አሜሪካና በአንዳንድ የአውሮጳ የእግር ኳስ ክለቦች ለማኅበርተኛቸው ድሮ ያልነበረ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል። እነዚሁ ክለቦች ልደት ይሁን፣ ሠርግ፣ መዝናኛ ይሁን ዕድር፤ ቀብርንና አልባሳትን በተመለከተ መረዳጃና ተቀጥላ ኢንዱስትሪ አቋቁመዋል። በቤተ ክርስቲያን ፈንታ ሌላ የሃይማኖት ድርጅት በኳስ ጨዋታ ተገን ተመሠረተ ማለት ነው። የውጭውን ባሕል ያለ ጥያቄ መኰረጅ በአገራችን የተለመደ ተግባር ስለሆነ ይህ ልማድ ነገ በአንዱ ክለብ ውስጥ ቢከሰት አይድነቀን!

የሞትን አስፈሪነት መቀባበል፣ ማለዘብ፣ ማዘግየት፣ በሾኬ መጣል፣ አታልሎ ማለፍና ጐል ማስገባት ይቻል ይሆን?

አንዳንዶች ውሃና ዛፍ ካለበት እንጂ አትቅበሩኝ ይላሉ። ወይም ጉድጓድ ውስጥ መቀበሬን ሳስበው ጭንቅ ጭንቅ ይለኛል የሚሉት ጨርሶ የማይሞቱ ስለሚመስላቸው ይሆን? መንገድ ዳር ቅበሩኝ የሚሉስ ራቅ ካሉ ብቸኛነቱን አስበው ይሆን?

ሞትና ፍትሕ

ከሞት በኋላ ሕይወት ካለ፣ ያም የሰላምና የደስታ ኑሮ ከሆነ፤ ሁሉም አንድ ላይ ተጨፍልቆ ወደ ዘላለም ፍስሃ ሊገባ ነው? ማጣሪያስ እንዴት አይኖረውም? ፍርድ ከሌለስ በዚህ ምድር ላይ በመልካም ሥነ ምግባር መኖር ምን ትርጉም ይኖረዋል? ይህ አሳሳቢ ጥያቄ ነው። ይህን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ አንዳንዶች ሞት እንዳለ አለማሰቡን ይመርጣሉ።

በ 6ኛው መቶ ዓመተ ዓለም የኖረ የግሪኰች ፈላስፋ “ለሞት ፍርሃት መድኃኒቱ ከተቻለ አለመወለድ ነው፣ ከተወለዱም በአፋጣኝ ማምለጥ ነው” ሲል ችግሩን ለመፍታት ሞክሯል። የሞት ፍርሃት በመሠረቱ የሚቀጥለው ምዕራፍ የሚያመጣውን በውል ካለማወቅና በምድር የሚታየው ሥቃይ ብሶ ይደገም እንደ ሆነ ከመሥጋት የሚመነጭ ነው።

ማጠቃለያ

“ሞት አይቀርም” ሲል አንተን የማይጨምር ይመስልሃል? ሞት ቀጠሮ አይሰጥም ሲል ላንተ ብቻ የሚዘገይ፣ አንተን ብቻ የሚዘነጋ ይመስልሃል? ሞት ምን እንደሆነ አውቀሃል? ማምለጫ ይኖረው እንደሆነስ አስበህበታል ወይንስ ጊዜ ማጥፋት መስሎ ይታይሃል? በመርሣትስ ብዛት ማዘግየትና ማስቀረት ይቻላል? ሕይወትን ያህል ዋነኛ የሆነ ቁም ነገር እንዲህ እንደ ዋዛ ችላ ሊባል ይገባል? ሞት ፍጻሜስ ከሆነ ሕይወትን ለማቆየት ይህ ሁሉ ትግልና ኪሣራ ለምን አስፈለገ? ከተሻገርክስ በኋላ እንደ ተሳሳትክ ብትገነዘብ ምን ማምለጫ አዘጋጅተሃል? ይህን ጽሑፍ ማንበብህስ የኑሮህን አቅጣጫ እንዴት ሊለውጠው ይገባል?

                                                               

 

 

 

picture