ቃልህ እንዳይባክን

በምትኩ አዲሱ

 

መግቢያ

በጥቂት ቃል ፍሬ ያለው አሳብ መናገርና መጻፍ እንዴት ይቻላል? የቃላተኛነት መንስኤው ምንድነው? መፍትሔውስ? እነዚህን አሳቦች ቀጥለን እንመለከታለን።

ቃል ጐርፍ ቢሆን

ከሚያስፈልግ በላይ ያወራንበት ጊዜ ይታወሰናል። ብዙ አውርተን ሳንግባባ ቀርተናል። አለመግባባት ከቃል ማነስ አይደለም ማለት ነው።

በአንጻሩ፣ ቃል ሳይወጣን በዝምታ ብቻ ተግባብተናል።

ረጅም ሐተታ አንብበን “እንዲህ ሊል ፈልጐ ነው ይህን ሁሉ የዘበዘበዘው?” ብለናል። የቃላተኛነት አንድ ገጽታው በከንቱ ቃል ማባዛቱ ነው።

መግባባት በቃል ብዛትም አይገኝም ማለት ነው።

ብዙ የሚናገሩ ብዙ ይደመጣሉ ማለት አይደለም። ንግግር የሚያሳምሩ በአብዛኛው ሌላውን ማዳመጥ የተሳናቸው ናቸው። እንግዲህ በጥቂት ቃል አሳባቸውን መግለጽ የተቻላቸው እንዴት ያስቀኑ? እነዚህም ጥቂት ይናገራሉ፤ ሁሌ ይደመጣሉ።

ነገር የለም፣ መናገርም የለም

ድምፃቸውም አይሰማም።

ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ

ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ (መዝሙር 19፡ 3-4)።

ለአንዳንዶቻችን ከተናገርን በኋላ ማሰብ ይቀናናል ብንል ከእውነት የራቀ አይሆንም። በቃላት ተወርረናል። የቃል ድር አድርቶብናል። ዛሬማ ስልኩም ይኸው እንደ አገር ቤት እብድና እንደ ውጭ አገር ጋጋኖ ያጯጩኸናል።

ቴሌቪዥኑ፣ ጋዜጣው፣ አውራ መንገዱ፣ ኢንተርኔቱ፤ እነዚህ ሁሉ የቃላት አሸንዳ ናቸው። ከፈቀድንላቸው ፋታ ይነሱናል፤ ይገዙናል። በጸጥታና በዝግታ እንዳንረማመድ ያዋክቡናል። እኛም መዋከቡን የወደድነው ይመስላል።

በቤተ ክርስቲያንስ የምንሰማው ምንድነው? ቃል ጐርፍ ቢሆን ገና ድሮ በሰጠምን። ቃል ገንዘብ ቢሆን ብዙዎቻችን ፈጥነን በከሰርን፤ ልመና በጀመርን!

ቃል ያግባባናል 

ቃል ያግባባናል። አሳባችንን ይገልጽልናል፤ ከእንስሳ ይለየናል። ቃል መታያችን ነው፤ ሕይወታችን ነው። በተናገርን ቁጥር ማንነታችን ይገለጻልና። ሰው እንደ አንደበቱ ቃል ይቀል-ላል ወይም ይከብዳል።

ቃል እንገባለን፣ እናፈርሳለን። መጣሁ ብለን እንቀራለን፤ ቀረሁ ብለን እንመጣለን።

የልባችንን መግለጽ ስንችል የሚሰማን ደስታና ሲያቅት ደግሞ የሚሰማን ጣር ይታሰበን። አፍ በፈታንበት ቋንቋ እንኳ አሳባችንን መግለጽ የሚቸግረን ሰዓት አለ። ለዚህስ ሳይሆን ይቀራል ሐዘን ወይም ደስታ የወደቀበት ሰው ከመናገር ይልቅ ቃል-የለሽ ድምጽ ማሰማት የሚቀናው?!

ቃል ለያይቶናል

ድንበር የማያውቅ ድንበር የማይመክተው ዘመን ላይ ደርሰናል። ሰዎች ከቀድሞው ይልቅ በፈጠነና በረቀቀ መንገድ የመናገርና የመጻፍ ጥበብና መብት እየተቀዳጁ ነው። በዚያው ልክ ግን አለመግባባት እየተባዛ ሄዷል።

አለመግባባት በመሠረቱ ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ውጤት ነው (ዘፍጥረት 11፡ 1-9)። እግዚአብሔር በአምሳሉ ሲፈጥረን ለራሱ ነበርና፤ ከርሱ ጋር ተስማምተን እንድንኖር ነበር።

በአምሳሉ ፈጠረን ማለት አሳባችንን መግለጽና ማስረዳት እንድንችል ጸጋ አጐናጸፈን ማለት ነው። ነገር ግን ባለመታዘዝ ይኸንን መብት ጣልን። በኛና በፈጠረን አምላክ መካከል፣ በኛና በፍጥረት መካከል ቅራኔ ተፈጠረ።

ራሳችንንም እንኳ መረዳት ተሳነን፣ ሕልውናችን ተዛባ። የሌሎችን አሳብ መስማትና መቀበል አቃተን። ይህን ኃጢአት ያበላሸውን ግኑኝነት ወደ ክርስቶስ መንግሥት እስክንሰበሰብ በከፊል እንጂ ፍጹምና ሙሉ ሆኖ በዚህኛው ዓለም አንቀዳጅም።

ዛሬ እንደ ልጅ እንናገራለን፤ በመስታወት በድንግዝግዝ እናያለን። እውቀታችንም ከፊል ነው። በዚያን ቀን ግን እግዚአብሔር የሚያውቀንን ያህል ሙሉ እውቀት ይኖረናል (1ኛ ቆሮ.13፡ 11-13)። እውቀታችንና ቃላችን፣ አሳባችንና ተግባራችን አንድ ይሆናሉ። ዳግመኛም አይነጣጠሉም። ሃሌ ሉያ!

ከቤትና ከጐረቤት

መግባቢያችንን የምንወርሰው በመጀመሪያ ከቤት ከወላጆቻችን ነው። ከአካባቢው ባሕል፣ ከትምህርት ቤት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከአገር መሪዎችና እውቅ ባለሙያዎች ጨምረን እንቀስማለን።

ያለፉት ሠላሳ ዓመታት ያስተማሩን አንድ ነገር ቢኖር ያም የተንዛዛ፣ ሥነ ምግባር የጐደለው፣ ለሰሚው ቀርቶ ለተናጋሪውም የማይ-ገባ የንግግር ባሕልን ነው።

ትምህርት ቤቶች ከተለያየ ኑሮና ባሕል ውስጥ የተውጣጡትን የማቀራረብና የማግባባት ተግባርና ኃላፊነት እንዳለባቸው የታወቀ ነው። በሌላ አነጋገር፣ እያንዳንዱ ሰው ተወልዶ ባደገበት አኳኋን ቢቀጥል አንድነት ባልተገኘ፤ አገርና ብሄራዊ ስሜት ባልተገነባ።

ተማሪው ሊቀበለው የሚገባውን ከመምህሩ ብቁ አለመሆን ወይም ከመመሪያዎችና ከአቅርቦት አለመሟላት የተነሳ ሳያገኝ ቢቀር ራሱን ብቻ ሳይሆን የማኅበረ ሰቡን ዕድገት ያዳክማል፤ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ያናጋል ማለት ነው። ለመሆኑ ትምህርት ቤቶች ቀጣዩን ትውልድ በማዘጋጀት ረገድ ግዴታቸውን እየተወጡ ነው? አይመስለንም!

 

የሃይማኖት ተቋሟትም አምልኰ ሥርዓትና መንፈሳዊ መመሪያዎችን ይሰጣሉ፤ የቀደመውን ትውልድ ከኋለኛው ጋር ያስተዋውቃሉ፣ ያገናኛሉ። የሚሰጡት ትምህርት ግን የተወሳሰበና ለመረዳት የሚያዳግት፣ የአማንያኑን ኑሮና አስተሳሰብ የማይገነዘብ ከሆነ ሰሚው ያንኑ ማስተጋባት ይጀምራል። ለማኅበራዊ ግንኙነቶች መጠናከር ምክንያት ሊሆን የተገባው እንግዲህ ለመፈረካከሱ ሰበብ ሆነ ማለት ነው።

እውን አሁን ቤተ ክርስቲያን ድርሻዋን ችላ አላለችም ብሎ ለመናገር የሚደፍር በመካከላችን ይገኝ ይሆን? መፍትሔ ለመሻት ቆርጫለሁ የሚልስ?

ቃልህ ጥቂት ይሁን

“እግዚአብሔር በሰማይ፣ አንተም በምድር ነህና፣ በአፍህ አትፍጠን፣ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል፤ ስለዚህ ቃላትህ ጥቂት ትሁን … በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም” (መክብብ 5፡ 2-3፤ ምሳሌ 10፡ 19)።

ጥቂቱ ቃልህ ደግሞ ግልጽ ይሁን። ጥቂቱ ይሥራ፣ ምድር ላይ አይውደቅ። ስለ ሳሙኤል ሲናገር “ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቅም ነበር” ይላል (1ኛ ሳሙኤል 3፡ 19)። ሳሙኤል የሚናገረው ነበረው። ንግግሩ ግልጽ ነበረ። ራሱን ሳይሆን እግዚአብሔርን እዕዐሕ መስማት የለመደ ሰው ነበረ። እግዚአብሔር አብሮት ስለ ነበረ የሚናገረውም ግልጽ ነበር። ዘንድሮ ግን ግራና ቀኝ የተቆለለውን የቃል ክምር የእግዚአብሔር እሳት ካልሆነ በስተቀር የዓለም ማዘጋጃ ቤት አጽድቶ አይጨርሰውም። 

ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች ቃላተኛነት ለማረም “ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጽ የታሰበው እንዴት ይታወቃል?… ሌሎችን አስተምር ዘንድ እልፍ ቃላት … ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ” ይላቸዋል (1ኛ ቆሮ. 14፡3-19)። ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው መግባባትን በመፍጠርና በማነጽ ላይ ነው። “የሰውን አሳብ በክርስቶስ እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ማፍረስና … ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ መማረክ” ላይ ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 10፡ 5)።

ከቤተ ክርስቲያን መልስ

በቤተ ክርስቲያን ሆነ በአገር ደረጃ የቃላተኛነት ባሕል እየተስፋፋ ሄዷል። ከቤተ ክርስቲያን መልስ እስቲ ለአንድ አፍታ ስንሰማና ስንናገር የቆየነውን እናሰላስል። ምን ያህሉን እናስታውሳለን? ምን ያህሉ ምድር ላይ ወድቋል?

ቃላተኛነት ከሚከሰትባቸው መንገዶች ጥቂቱ ይህን ይመስላል፦

·        የሰሞኑን ቃላት ያስተጋባል፤ በተለመዱ ቃላት መግለጽ ሲቻል ባዕድ ቃላት ይበዛዋል

(“ዴስቲኒ” ይላል፣ ለምሳሌ)። መሰል ቃላትን መደጋገም ከጥራዝ ነጠቅነት አያልፍም፤ ለነፍስም ለሥጋም አይበጅም። ቀረና ምን ይጎዳል ብሎ ማሰብም አንዳንዴ አይከፋም!

·        ባንድ ጊዜ ብዙ ማስረዳት ይሞክራል

·        ስላላብላላው ንግግሩና አሳቡ እያደር ይቃረናል

·        እራሱ ያልተረዳውን ሊያስረዳ ይጥራል

·        የሰሚውንና የአንባቢውን አቅም አይመጥንም

·        ነገሮችን መሠወር ያዋቂነት ምልክት ይመስለዋል

·        የሚታዘበው ያለ አይመስለውም

·        ምን ሲደረግ እጠየቃለሁ? ስለሚል የመንፈሳዊነትን ሽፋን ለራሱ ያበጃል። እንኳንስ ሥጋ ለባሽ እግዚአብሔርም ይጠየቃል እኰ!(ይመልከቱ፦ ዘጸ. 3፡13፤ ዮሐ. 4፡7-26፤ 10፡ 24፤ ኢሳይያስ 1፡ 18)። የወንጌል ኃይሉና ሥልጣኑ ግልጽና ቀሊል መሆኑ ላይ እንደሆነ ማን ባስታወሰ!

·        መንፈሳዊ የሚመስሉ ነገር ግን ባዶ ቃላትን ያዥጐደጉዳል

·        የማያስፈልግ፣ ጊዜ የሚያራዝም ሐተታ ያበዛል

·        ከመልእክቱ እውነት ይልቅ በራሱ ንግግር ይማረካል፣ ይረካል

·        ሰው ሊሰማው የሚፈልገውን ይናገራል 

·        መናገር እንጂ መስማት አያውቅም፣ አይፈልግም

·        ምሳሌዎቹ፣ ዘይቤዎቹ የውሰት ናቸው፤ የሰሚውን ባሕላዊ አስተሳሰብ አያንጸባርቁም። ከዚህ ቀደም በሌላ ሥፍራ እንዳስነበብነው ለወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አንደኛው ወጥመድ የምዕራቡ ዓለም ባሕላዊ ክርስትና ከሐዲስ ትምህርት አለመ-ለ-የቱ ነው። በሌላ አነጋገር እንደ ዓለማውያኑ ወገኖቻችን ከአገሬው ይልቅ የባዕዱን ማጣቀስ ይቀናናል።

ጌታን ካወቅነው

ጌታን አውቀነው አብረነው ከኖርን ንግግራችን የጠራ መሆን ይኖርበታል። በአንጻሩ፣ ንግግራችንና ቃል አመራረጣችን የተወሳሰበና ያልጠራ ከሆነ ምዕመኑም ያንኑ ይዞ ያድጋል። ቃላት ይዥጎደጎዳሉ፤ ማስተዋል የሚገኝበትን ጤናና እውቀት ግን አያቀዳጁም።

በበኣል ቀሳውስትና በእግዚአብሔር ነቢይ በኤልያስ መካከል የነበረው ልዩነት ቀሳውስቱ ለረጅም ጊዜ አምላካቸውን እየጠሩ መዘብዘባቸው ነው። “በታላቅ ቃል ጮኹ…እያነከሱ አሸበሸቡ…በኣል ሆይ ስማን እያሉ… ትንቢት (እየተናገሩ) ከጧት እስከ ቀትር ድረስ” ዋሉ።

ኤልያስ ግን የተናገረው ጥቂትና ግልጽ የሆነ ቃል ነበረ፦

“አቤቱ፣ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፣ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፣ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፣ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። አንተ፣ አቤቱ፣ አምላክ እንደ ሆንህ፣ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፣ አቤቱ፣ ስማኝ አለ” (1ኛ ነገሥት 18፡ 26-29፣ 36-37)።

እግዚአብሔር የማይሰማ ይመስል ጩኸት አብዝተን ይሆን? እግዚአብሔርን በቃላት ብዛት ልናሳምነው እየጣርን ይሆን? ሽብሸባችን ለመታየት ይሆን? ለራሳችን ይሆን? “በመናገር ብዛት የሚሰሙ ይመስላቸዋልና” (ማቴዎስ 5፡ 7)። “ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን” (መዝሙር 94፡ 9)? በእግዚአብሔር ፊት ዝምታን ሞክረናል? ዝምታ መንፈሳዊነትን የሚያጐድል መስሎን ይሆን? ይህን ስንል ሽብሸባ ሆነ ጮኽታ በጅምላ ስሕተት ነው ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

የቃላተኛነት መንስኤዎች ብዙ ሊሆኑ ቢችሉም እነዚህ ግን ዋነኞቹ ናቸው።

·        አለመጸለይ፦ “የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ” (ኤፌሶን 6፡ 19-20)።

·        የምንለው ሳይኖረን ወይም አባባሉን ሳናውቅ ቀርተን። ከአፋችን የሚወጣው አእምሮአችንን የመገብነው ነው። ምንም ካልመገብነው፣ ወይም ጤናና ሕይወት የማይገኝበትን ከመገብነው ወዛችንና ቁመናችንም ያንኑ ማንጸባረቅ ይጀምራል።

“በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው … ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ” (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡ 14-16)።

·        አለማንበብ፣ አለማጥናት፣ የምናነበውን አለመምረጥ።

·        ከተወሰነ ክልል ውጭ ማንበብን እንደ ኃጢአት መቁጠር። አሳቡን አለማብላላት አለማገናዘብና ግልጽ ያልሆነውን ለመግለጽ መሞከር፤

·        እውነትን ማስተላለፍ ሳይሆን አድማጩን ማዝናናትና ማስገረም ቅድሚያ ስላገኘ፤

·        መናገር እንጂ መስማት ስላላወቅን፤ ሌላው ሲናገር እንደ ማድመጥ ቀጥሎ የምንለውን ማሰላሰል።

·        ሩጫና መዋከብ እንጂ በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ አለማለት። “ዕረፉ” ይለናል፤ “ዕረፉ፣ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ” (መዝሙር 46፡ 10ሀ)።

መፍትሔው ምንድነው?

እስቲ ከጌታ ሕይወት እንጀምር። ጌታ ከአብ ጋር ያላቋረጠ ግንኙነት ነበረው። በዝምታ ሆነ በጥቂቱ የሚያስገርም ነገር ይናገር ነበር። በቃሉ እንዲያጠምዱት የተላኩት እንኳ “ይህ ሰው እንደሚናገረው ዓይነት ማንም ተናግሮ አያውቅም” ከማለት ወዲያ ምንም አላገኙበትም (ዮሐንስ 7፡ 46፤ ኢሳይያስ 53፡ 7፤ ማቴዎስ 27፡ 11-14)።

ከእግዚአብሔር ቃል ደግሞ እንመልከት። የምንጋራው አንድ ዋነኛ ነገር ቢኖር የእግዚአብሔር ቃል ነው። ይኸው መጽሐፍ ራሳችንን በቃል ሆነ በጽሑፍ እንደሚገባ ለመግለጽ ያስችለናል። መታረሚያችንና መመሪያችንን ይዟልና።

ስንቶች ነን መጽሐፍ ቅዱስን የሕልውናችንና የአስተሳሰባችን መሠረት ያደረግን?

መዘንጋት የሌለበት ነገር ቢኖር ይኸ ነው፦ በተገኘበት ቋንቋና ባሕል መጽሐፍ ቅዱስ ላመኑት የዘር ሐረግና የታሪክ ማኅደር ሆኖ ይኖራል።

መጽሐፍ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ሕዝብ አፍ መፍቻው ነው፤ መጽናኛው ነው፤ ከአምላኩና ርስ በርሱ የሚተሳሰርበት ዓይነተኛ መሣርያ ነው። የማኅበረ ሰብ ጥናት ሊቅ የሆነው ሮድኒ ስታርክ እንኳ ራሱን እንደ ክርስቲያን ሳይቆጥር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና የምዕራባውያን ሥልጣኔ መሠረት ነው ሲል መስክሯል። 

በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ዛሬ ትኩረት ያልተሰጠው አገልግሎት ቢኖር ቃሉን በዝርዝር፣ በጥልቀትና በአንድ ወጥነቱ የሚያገናዝቡና የሚያስተምሩ መምህራን ቁጥር ማነስ ነው። ያሉቱ ጥቂቶች ደግሞ አቀራረባቸው ላለው ምዕመን አልተስማማም በሚል ሰበብ ወደ ጐን ተደርገዋል። ከዚህም የተነሳ መሠረት የለቀቀ ሚዛን ያጣ ቀዳሚውን ትርጉም የሳተ ተባራሪ ጥቅስ በዝቷል። ምዕመኑን በእግዚአብሔር ቤት ሥርዓት ከማነጽ ይልቅ ማባበልና ለታሰበው አስተዳደራዊ ተግባር ማስገዛት ቅድሚያ ተሰጥቶታል። ይህ ተግባር በምዕመን ገጽታ ላይ ምልክት እየተወ ነው። 

የተመረጠ ቃል፣ የታረመ አንደበት

መጽሐፈ ሩት 1፡ 1-5 ላይ ያለውን ምንባብ አብረን እንመልከት፦

“እንዲህም ሆነ፣ መሳፍንት ይፈርዱ በነበረ ጊዜ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። አንድ ሰውም ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር በሞዓብ ምድር ሊቀመጥ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ተነሥቶ ሄደ። የሰውዬውም ስም አቤሜሌክ፣ የሚስቱም ስም ኑኃሚን፣ የሁለቱም ልጆች ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበረ፤ የቤተ ልሔም ይሁዳም የኤፍራታ ሰዎች ነበሩ። ወደ ሞዓብም ምድር መጡ፤ በዚያም ተቀመጡ። የኑኃሚንም ባል አቤሜሌክ ሞተ፣ እርስዋና ሁለቱ ልጆችዋ ቀሩ። እነርሱም ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስት አገቡ፤ የአንዲቱ ስም ዖርፋ፣ የሁለተኛይቱም ስም ሩት ነበረ። በዚያም አሥር ዓመት ያህል ተቀመጡ። መሐሎንና ኬሌዎንም ሁለቱ ሞቱ፤ ሴቲቱም ከሁለቱ ልጆችዋና ከባልዋ ተለይታ ቀረች።”

በዚህች አጭር አንቀጽ ምን ምን ጉዳይ ተነግሮናል? እስቲ ጥቂቱን እንዘርዝር፦

·        የስድስት ሰዎች ሕይወት ታሪክ

·        የኖሩበት ሠፈርና አገር

·        በወቅቱ የነበረው መንግሥት

·        የኤኰኖሚውና የአየሩ ጠባይ መዛባት

·        ለቅቀው የሄዱበት አገር

·        በዚያም የደረሰባቸው ጉዳትና የተሰማቸው ስሜት፤

ስንቶቻችን ነን ይህን ያህል ስፋት ያለው ታሪክ ባጭሩ መናገር ወይም መጻፍ የምንችል? እንግዲህ አስተሳሰባችን እንዲቀና ንግግራችንም የተለቀመ እንዲሆን ከተፈለገ እንደዚህ ከመሰለ ጽሑፍ ጋር መክረም ይኖርብናል ማለት ነው።

የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መለማመድ ይኖርብናል። “መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን” ይላልና (1ኛ ቆሮንቶስ 2፡ 13)። ይኸው መንፈስ በአእምሮአችንና በስልጣኔአችን ብርታት ልንደርስበት ያልቻልነውን ሕያው ጥበብና እውቀት ያስታውቀናል። የምናውጀውን እውነት እያስደመጠ ያስገርመናል፤ ያሰግደናል።

የአንደበታችን ቃል ልክ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ይኸው መንፈስ በውስጣችን ሆኖ ቅር ይሰኛል፤ ይቆጣል። ሰላሙ ይርቀናል። መናገሪያው ነው። ይህንንም ንስሃ ያስተካክለዋል።

ካደመጥነውና ከታዘዝነው ደግሞ እያደር ራስን መግዛት ያጐናጽፈናል። ይረዳናል። ጭምትነት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እንደ ሆነ አንርሣ (2ኛ ቲቶ 2፡ 2፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡ 8፣11)። ጭምትነት ደግሞ ብዙ አለማውራት ሳይሆን በአስፈላጊው ሰዓትና ሥፍራ መናገር ነው። “የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች” (መክብብ 9፡ 17)። ያንን አልገዛ እያለ የሚያፈነግጠውን ክፍል እስኪ-ገ-ዛ ድረስ ለርሱ ማስረከብ ያሻናል ማለት ነው።

ቃላችን የተለቀመ እንዲሆን ጥሩ አጻጻፍ የሚገኝባቸውን መጻሕፍት መርጦ ማንበብ ያስፈልጋል። የታወቁ የአገራችን ደራሲያን የተዋጣላቸው መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች እንደ ሆኑ አንርሣ። ምናልባት የሚያነቡበት ምክንያት እኛ ከምናነብበት ምክንያት ይለይ ይሆናል። ቢሆንም አስተሳሰባቸውን የሚያዋቅሩት ለዛም የሚጐናጸፉት በአብዛኛው እኛ አንደ ቀላል የወሰድነውን መጽሐፍ በማንበብ ነው። በዓለም ዕውቅ የሆኑ ደራሲያን እንግሊዛዊው ሼክስፒር፣ ጀርመናዊው ገርተ፣ አሜሪካዊቷ ቶኒ ሞሪሰን፣ ሩሲያዊያኑ ቶልስቶይና ዶስቶየቭስኪ፣ ወዘተ ጡት የጣሉትና ጐልምሰው የሸበቱት እንደዚሁ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ ነው።

ለምናምን ለኛማ መኖሪያችን ሊሆን እንዴት አይገባው? አስቀድመን ግን ይህ ልማድ እንዳይጐለብት የሚጻረረንን የቴክኖሎጂ ሱስና ግርግር አደብ ማስያዝ ይኖርብናል።

በመጨረሻም፣ ሲያመች ንግግራችንን በቴፕ ቀድቶ ማዳመጥ፣ የሚቀርበን ሰው እንዲተቸን መጠየቅ።

የመድረክ አገልግሎት የምንሰጥ ፈተናችን ጥቂት አይደለም። በንግግር ብዛት ስንወሳስብ እንዳንገኝ አልፎ አልፎ ምዕመኑ ካቀረብንለት ትምህርት ውስጥ ጥቂቱን በጽሑፍ እንዲያሠፍር መጠየቅ ይኖርብን ይሆናል። ይህ ለራሳችን እርምት ብቻ ሳይሆን፣ ለሰሚው እድገት ጥንቃቄ እንድንወስድ ይረዳል። 

ላመኑ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ መኖራቸው ለዚህም ጭምር ካልሆናቸው ለምን ይበጃቸዋል? እንግዲያስ ቃላተኛ ከመሆን፣ ነፋስ የሚወስደው ገለባ ከሆነ ንግግር ለመላቀቅ ራሳችንን እናለማምድ። ራስን ማለማመድ ጥረት ይጠይቃል። ትግስት፣ ቁርጠኛነትና መስዋእትነትን ይጠይቃል።

የተሰበከልን ኢየሱስ “አዎን” በሚል ቃል እንጂ “አዎንና አይደለም በሚል አወላዋይ ቃል አልነበረም” (2ኛ ቆሮንቶስ 1፡ 19፣ 1980 ትርጉም)። “በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ” (ፊልጵስዩስ 4፡ 8)። አሳብ ድርጊትን ይወልዳል፤ ድርጊት ደግሞ ሲደጋገም አሳብን አጐልምሶ ያጸናል።

 

Copyright 2007 by Mitiku Adisu

Top Art Credit: Wossene Kosrof http://africa.si.edu/exhibits/inscribing/images/wosenePaintingLG.jpg

 

 

 

 

 

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org