አይሞላም…
በፀሐይ ዓለሙ

የመጨረሻ የክብር ከፍታ አለ ቢባል፣ ሰው እዚያም ለመድረስ ዕድል ቢያገኝ ፍላጐቱና ልቡ አርፎ አይሞላም፤

ድንቅ የተባለ የውበት ዳርቻ ቢኖር ሰው ለዚያ ብቁ ሆኖ ቢገኝ፣ ሌላው ተወዳዳሪም መጥቶ በልጦ ቢታይ እዚያ ክልል ከተደረሰ በኃላ አይሞላም፤

ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ማስተዋል አንድ ላይ ቢከማች ግሩም የተባለ ነገር ሠርቶ ቢያሳይ ከእርሱ የበረታ ሌላ የችሎታ ኃይል ስለሚተካ የሆነው ሁሉ አይሞላም፣

ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፣ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ሥፍራ እንደገና ወደዚያ ይመለሳሉ፤ ነገር ሁሉ ያደክማል፤ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፣ ዓይን ከማየት አይጠግብም፣ ጆሮም ከመስማት አይሞላም -- መክብብ 17-8

አዎን! ማንኛውም ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ካልተያያዘ በስተቀር አይጠቅምም፤ ያደክማል። መጨረሻም የለውም። የተደረገው ሁሉ እንደገና ተመልሶ በሌላ መልኩ ሲደረግ በሕይወት ክበብ ዙሪያ ይሽከረከራል እንጂ አዲስ ነገር የለም።

የሰው ዘመኑ ጥቂት ነው፤ ሃሳቡና ዕቅዱ ፍላጐቱና ምኞቱ ግን እጅግ ብዙ ነው። ከዚያም ውስጥ ተፈጽሞ የሚያየው እጅግ ጥቂቱን ነው። ታዲያ ለሰው ምን ሊሻለው ነው? እንዲሁ ሁሉ ከንቱ መሆኑን እያሰላሰለ ይኑር?

አይደለም! ነገር ግን ሕይወት በብዙ ከምድሩ ነገር ጋር ተያይዞ ዘላለማዊው እንዳይዘነጋ ማሰብ ያሻል።

በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሣ ይሆናል፤ ለዘላለም የሚሆን የጠቢብና የሰነፍ መታሰቢያ አይገኝም፣ መክብብ 216

ባለው ነገር ላይ ለመጨመር የማይተጋ የለም፤ ሁሉም፦ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፣ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፣ ነፍሴንም፦ ዕረፊ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስ ይበልሽ እላታለሁ፣ ይላል፤ ዳሩ ግን ምንም ዕረፍት የለም።

የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጐምጀትም ብዛት ተጠበቁ…አንተ ሰነፍ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፣ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ባለጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና… ሉቃስ 1215-21፣23

ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፣ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አትሞታልና። ዮሐንስ 627

እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፣ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፤ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። ኤፌሶን 515-17

*

አቤቱ፣ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፤ የዘመኔ ቁጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ። እነሆ፣ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፣ ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም። አሁንስ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው። መዝሙር 394-7

§

picture