“አትፍራ… ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው”
በፀሐይ ዓለሙ
ጌታ እግዚአብሔር ለአብራም ይህን ቃል የተናገረው ከጦርነት እንደ ተመለሰ ነው። ጦርነቱ አልቆ ድል አድርጐ ከተመለሰ በኋላ አብራምን ምን የሚያስፈራ ነገር ገጠመው?
አብራም የእምነት ሰው መሆኑ ይነገርለታል፤ እምነትና ፍርሃት ደግሞ አይስማሙም። ያልተፈተነም እምነት አይሠራም። ለመሆኑ ምን ይሆን ያሳሰበው?
ለአብራም ሽልማቱና የልቡ ሙላት ከጠላት ያዳናቸው ሰዎች አድናቆትና ምሥጋና ሳይሆን የእግዚአብሔር አብሮት መሆን ለራሱ ሲረጋግጥለት ብቻ ነው።
ለአብራም ይሰማው የነበረው ፍርሃት አብሮት የቆየ ነው። ሁል ጊዜ እየተጉላላ የሚጠይቀው ጥያቄ አልተመለሰለትም፤ “… ጊዜዬ አልፏል፣ ከእንግዲህ ሊሆን አይችልም … በዚሁ ዓይነት እሞታለሁ” ይላል። ዘፍጥረት 1717
እግዚአብሔር አምላክ ግን የአብራምን ፍርሃት በሦስት መንገድ ይቆርጠዋል። የጌታ መልስ ደግሞ አያዳግምም።
አንደኛ፣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን እወቅ።
ሁለተኛ፣ የተናገርሁህን አስታውስ። ቃል ኪዳኔን አልረሳም፤ የተናገርሁትን አደርገዋለሁ። ዘፍጥረት 121-3። ስለዚህ፣
ሁሉ ነገር ባዶ ሲሆንበት ሰው ሁሉ እግዚአብሔር ወደ አለበት ሠፈር ቢመለከት ተስፋ አለው። በጌታ ዙሪያ ብዙ መልካም ነገር አለና። ከፍርሃታችን የምናመልጥበት መንገድ ይኸው ብቻ ነው። ደግሞም ልክ ነው። እምነትም የሚኖረን ይኼኔ ነው!
ሦስተኛ፣ የተናገርሁህን እንደምፈጽመው ዕወቅ። እግዚአብሔር የተናገረውን በቃል ኪዳን ያጸናዋል። መያዣ ያበጅለታል። በአብራም ዘመን ታርደው ሥጋቸው በተከፋፈለ እንስሣት መካከል ማለፍ የስምምነት ወይም የቃል ኪዳን ምልክት ነበረ። በዚህ በኛ ዘመን በጽሑፍና በምስክር ፊርማ እንደሚጸና በዚያ ዘመን በደም ይጸና ነበር። ዘፍጥረት 159-21
‡
የተበታተነውን የውል ሃሳብ ማን በራሱ ሊያይዘው ይችላል? እንዴትስ ይገጣጠም ይሆን? የቃል ኪዳናችን ዋነኛ ሰው፣ ምስክርና ኃላፊም እግዚአብሔር ነው። እርሱ የተበታተነውን መሰብሰብ አይቻለውምን? የተቆራረጠውንስ ማገጣጠም የርሱ ሥልጣን አይደለምን?
እግዚአብሔር አምላክ ይዋሽ ዘንድ ሰው አይደለም። የተናገረውን ይፈጽመው ዘንድ ለቃሉ ይተጋል። ነገር ግን የጌታን ጊዜ ማን ያውቀዋል? ቢሆንም እርሱ ሁሉን በሰዓቱ ውብ አድርጐ ይሠራዋል። ትንቢተ ኤርምያስ 112
§