Download Geez Unicode Font if unable to read Amharic text
- ፍትሕና ምሕረት
- ይድረስ ለቴዲ አፍሮ
- የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆችና መሪነት
- ርዕሰ አንቀጽ
- የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም
- የእምነት አቋም መግለጫ ምንነትና አስፈላጊነት
እውነተኛ ክርስቲያን ማን ነው? የከበረውን ከተዋረደው ብትለይ ሞት ፍጻሜ ነው ጅማሬ? ሕፃን ተወልዶልናልና ራእይ ሲደበዝዝ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው (ክፍል 2) የወንጌል ስርጭትና እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ (ክፍል 2) በክርስትና ስም … ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እንዳይዛመት፣ እንዳይጋነን። ጥሪዬን እንዴት አውቃለሁ? የወንጌል ስርጭትና እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ “ለጸሎት ምቹ ጊዜ” “ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ሁን” “የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት አሳብ” “ስጦታህን እወቅ” “አትፍራ! ዋጋህ እጅግ ታላቅ ነው” “ማን ይምራት?” “የ "ዳቪንቺ ኰድ" ፍቺና የዘመኑ መንፈስ” “የመንፈሳዊ ጤንነት ፍተሻ” “የመጨረሻው ዘመን ስሕተት…”፣ ክፍል 2 “የመጨረሻው ዘመን ስሕተት አሠራሮችና ጥንቃቄ”፣ ክፍል 1 ሰላም ላንተ ይሁን፣
ራቅህ እንጂ እንደ አገሬ ወግ አገላብጬ እስምህ ነበር። ምን ይደረግ፣ ድንበርና ዘመን አራራቀን።
ካገር ስወጣ ባልሳሳት ገና የአስርና የአስራ አንድ ዓመት ልጅ ነበርክ። ዛሬማ ፊትህ እንደ ካፊያ ፀሐይ ደምቆ አምሮብህ ፎቶህን ሲያሳዩኝ ማመን ነው ያቃተኝ።
ግራ ተከሻዬ፦ “ይመስለዋል እንጂ እሱ አይደለም” ቢለኝ፣ ቀኝ ተከሻዬ ተቀብሎ፦ “እርሱ እራሱ ነው፣ አታየውም?” አለኝ። ግራ ቀኝ፣ ግራ ቀኝ ስል ያቺ የምትወዳትን እስክስታ ልወርድ ምንም አልቀረኝም እልሃለሁ፤
ቴዲ መባልክን የሰማሁት ገና ዛሬ ነው። አፄው ቴዎድሮስ በፈረንጅኛ አፄ ቴዲ ይባል እንዳትለኝና የእንግሊዝ ሳቄን እንዳልለቀው ብቻ?
አፍሮውን እንኳ የዛሬን አያድርግና እኛም ስንባባል ነው የኖርነው። ያንተዋ ግን ጨዋ ቁርጥ የምንላት ነች። ለአፍሮ ገና ይቀራታል ማለቴ ነው።
አያ ካሣሁንን … አፍሮነቱ ተስማማህ ወይ? በልልኝ። እንዳትረሣ።
ይገርማል፣ የጊዜው መገሥገሥ። የአብዮት መዝሙር እንዳልዘመርክ ሁላ ዛሬ ደግሞ “ጃንሆይ፣ ጃንሆይ” ማለትህ። የምትጠራቸው “ግርማዊነታቸው” በዙፋናቸው ላይ ሳሉ እንኳን ልትወለድ ቀርቶ አልታሰብክም ነበር።
የገረመኝ፣ የአብዮቱን ፍሬ ልጅ ሳይቀር አንቅሮ የተፋው ምንኛ መራራ ቢሆን ነው?
እንግዲህ ወሬ አላበዛብህም። አውቃለሁ አውሮፕላን እየተሳፈርክ ስለሆነ ቸኩለሃል። ከአውሮፕላን ወርደህ ያቺ መኪናህ ውስጥ ገብተህ በርረህ ሳታመልጠኝ አየር ላይ ልቅለብህ ብዬ ነው።
ቴዲ። ኧረ ይኸ የምሰማብህ ነገር ምንድነው?
“ጃህ” ትላለህ አሉ። እንጃ ማለትህ ነው? ጐረበቴን ብጠይቀው የምን እንጃ ነው? እርስዎ ደግሞ አበዙት። ጃህ ይበሉ፤ ሁለት ቃል ነው ብሎ ጣል ጣል አረገብኝ።
እሽ፣ ጃስ ይሁን፤ ፍቺው ምን ይሆን? ብለው፦ ጃማ ጃንሆይን ነው፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ነው፤ አይለኝ መሰለህ?
እንዴት ተደርጐ፣ በምን ሂሳብ ጃህ ጃንሆይን ይሆናል? ብለው፤ በጃማይካዎች እንደርሱ ነው፤ ጃማይካ ማለት እነዚህ ጃንሆይ አምጥተው ሻሸመኔ ያሠፈሯቸው ናቸው፣ ብሎ አብራራልኝ። እግዚአብሔር ይስጠው።
ታዲያ ጃንሆይ እኝህ የምናውቃቸው ጃንሆይ አይደሉም? እንዴት ያስተሠርያሉ ትላለህ? ከመቸ ወዲህ ነው አምላክ የሆኑት? ከሞቱ በኋላ ነው ወይስ በሕይወት እያሉ? ደግሞስ ጃማይካው ቢል ተቀበልከው? በሐሺሽ ፍላት ግርማዊነታቸውን አምላክ ነው ቢል ጭሱ ጋርዶበት ይሆናል ብለህ እንዴት አልጠረጠርክም? ሀበሻ መሆንህ ቀረና ነው? ያንተው ይባስ፤ የለም የለም አብዮቱ አልለቀቀህም ማለት ነው።
ቴዲ። ይህ ሳያንስ ሌላም ወሬ ሰማሁብህ።
ደግሞ ምን ይሆን? ትላለህ አውቃለሁ። የሠራኸውን አሁን አጣኸውና ነው? ክርስቲያንና እስላም ማለት ምን ያስፈልጋል፣ ቢጋባ ምንም አይደለም ትላለህ አሉ።
ፍቅርን ሃይማኖት አያግደው ማለትህ እንደ ሆነ ገብቶኛል። እርግጥ ሊጋባ ያሰበን ምን ይመልሰዋል ብለህ ነው? ልንበላት ያሰብናትን አሞራ ዥግራ እንላት የለ? የሃይማኖት ምሥጢርና ኃይል ለገባቸው ግን አንተ እንዳቀለልከው መቸ ሆነና?
ስታስበው ድንበር አይኑር ነው የምትለው? ሁሉ እንዳፈቀደ ይሁን ነው የምትለው? ይኸ አባባልማ ለነጮቹም አልበጃቸው። ይኸውልህ፣ ወንዱ ሴት፣ ሴቱም ወንድ ቢሆን መብትና ነጻነት እንጂ ኃጢአት አይደለም፣ የፈጣሪን ሥርዓት መዳፈርና ማፍረስ አይደለም እያሉን ነው።
ያለ ክርስቶስና ያለ ወንጌሉም ክርስቲያን መሆን ይቻላል እያሉ ነው። ስንቱን ዘርዝሬ እጨርሳለሁ።
አንዳንዶችም ክርስቲያን ነን፣ ከሃዲም ነን፤ ማለት ጀምረዋል። በአንድ ጊዜ ሁሉንም መሆን እንችላለን ነው ነገሩ።
ልክና ስሕተት ብሎ ነገር የለም፤ እያንዳንዱ በመሰለው የሚያደርገው ነው ልኩ እያሉን ነው።
ያውልህ፣ እምቢ ብለናቸው ነው እንጂ፦ ሰው ራሱ አምላክ ነው እያሉን ነው። ስታስበኝ እኔ አሁን ምኔ ነው አምላክ? አንተስ ምንህ ነው አምላክ? እንደ ሞኝ ያደርጋቸዋል ልበል?! ይኸውልህ፣ የሚሉት አንዱም አልጠቀማቸውም። እንደ መበልጸጋቸው እንዳይመስልህ። እውነት በብልጽግና ብዛት መች ተገኘና! የሕይወትን ውል ስተውታል፣ እልሃለሁ።
ቴዲ። አገር ወዳድነት እንዳለብህ አውቃለሁ። ክርስቲያኑና እስላሙ በጋብቻ ይጣመር ያልከው፦ መስጊድ ይቀድስ፣ ቤተ ክርስቲያን ሰላት ያድርግ እያልክ እንዳይሆን ብቻ። አይመስለኝም።
ከመ … ለያየቱ
ከመ … ነታረኩ
መድኃኒቱ
መ … ከባበሩ
መ … ተሳሰቡና
መፋቀሩነው ማለትህ ይመስለኛል። በጐ አሳብ ነው። ግን የጀመርከው በጐ የሚመስል ሃሳብ መጨረሻው ወዴት እንደሚያመራ አስበህበታል? እንጃ የሰውን ባሕርይና የሃይማኖትን ታሪክ እንደሚገባ ያጤንኸው አልመሰለኝም።
ለመሆኑ፣ ሁሉ ይቀላቀል ድንበር ይደብዝዝ የምትለዋን ሃሳብ ከወዴት አገኘሃት? መቻቻሉን ስላጣንበት፣ ሁሉ አንድ ወጥ ይሁን ማለት ፍርደ ገምድልነት አይሆንም ወይ? ገደብና ሥርዓት እኰ እሥራት ሳይሆን ነጻነት ነው። ልዩ ልዩ መሆን ፀጋና ውበት አለው። የሕልውናም መጠበቂያ ነው። አንድ ወጥነት አያምርም፤ አንድነትንም አያስገኝም። ይልቅ እሥራት ነው። አብዮቱ ትዝ ይበልህ …
ኢትዮጵያ ምድር መወለዳችን ከፈረንጁና ከኬንያው ለይቶናል። መለያና ክብር አቀዳጅቶናል። ያም ኢትዮጵያዊነታችን ነው። የሁሉ ሰው ስም አበበና አበበች ቢሆን ምን ያምራል? ፈረንጁን ካልሆንኩ ብንል ፈረንጁንም ኢትዮጵያዊውንም ሳንሆን ዋልለን እንቀራታለን። በገደብና በየመልኩ ይሁን ማለት እሥራት አይደለም ያልኩህ ለዚህ ነው።
ቴዲ። የለም፣ የለም ይኸ የምሰማብህ ነገር አላማረኝም።
ይህንኑ ጉዳይ ለጐረቤቴ ባጫውተው፦ ገና ኖትና፣ ወዲህ ጠጋ ጠጋ ይበሉ እንጂ አይለኝ መሰለህ?
ወዴት ጠጋ ጠጋ ልበል? ብለው
ከዘመኑ ጋር ይሠለፉ እንጂ፣ ገና የስብስቴውን ነው የሚያወሩትሳ?
ዘመን አልፎ ቢያልፍብኝ፣ ቀኝና ግራዬን አጣሁት ማን አለህ? ልለው አሰብኩና ሌላ እንዳልናገር ራሴን ያዝኩት እልሃለሁ።
ቴዲ አፍሮ። ቴዲ ልበልህ እንጂ ምን ምርጫ አለኝ። ይኸ የምሰማብህ ነገር አላማረኝም።
እረፍት ነስቶኛልና አደራህን ቶሎ ቁርጡን አስታውቀኝ። ስ-ሜ እንዳልሰናበትህ ድንበር ከለለን። ምን ይደረግ?
በዓይነ ሥጋ ለመገናኘት ያብቃን።
በል ስትነዳ ቀስ በል።
/ ያንተው
ኬኔዲ በራራስCopyright
© 2006 by Ethiopianchurch.org
በሰለሞን ከበደፍትሕ በኃይል ወይም በሥልጣን አጠቃቀም ላይ ያተኩራል። ፍትሕ ትክክለኛ የኃይል ወይም የሥልጣን አጠቃቀም ነው። ኃይል ወይም ሥልጣን በአግባቡ ሥራ ላይ ሳይውል ሲቀር ፍትሕ ይዛባል፣ ይጓደላል።
የመጨረሻው ኃያልና ባለ ሥልጣን እግዚአብሔር አምላክ ነው። እርሱ ጽድቅና ፍትሕ ባሕርዩ የሆነ አምላክ እንደ ሆነ ቃሉ ይነግረናል።
ጽድቅና ፍትሕ የዙፋንህ መሠረቶች ናቸው፤ ምሕረትና ታማኝነት በፊትህ ይሄዳሉ። መዝሙር 89፡ 14
ፍትሕን የምትወድ ኃያል ንጉሥ ሆይ፣ አንተ ትክክለኛነትን መሠረትህ፣ ፍትሕንና ቅንነትንም ለያዕቆብ አደረግህ። መዝሙር 99፡ 4
እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፣ ‘እውነተኛ ፍትሕ አስፍኑ፣ እርስ በርሳችሁ ምሕረትና ርኅራኄን አድርጉ፤ መበለቲቱን ወይም ድኻ አደጉን አታስጨንቁ፤ በልባችሁም አንዳችሁ በአንዳችሁ ላይ ክፉ አታስቡ። ዘካርያስ 7፡ 9-10
ሰው ሆይ፣ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን? ሚክያስ 6፡ 8
እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነው። ፍትሕ ከእርሱ ባሕርይ የሚመነጭ ነው። በብሉይ ኪዳን ስንመለከት ጽድቅና ፍትሕ ብዙውን ጊዜ ተያይዘው በጥንድ ይቀርባሉ፤ ጽድቅ የውስጥን ሁኔታ ሲያመለክት፣ ፍትሕ ደግሞ ጽድቅን በተግባር የመግለጽ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ሆኖ ይታያል። ጽድቅና ፍትሕ ተወራራሽነት አላቸው። ሁለቱም እግዚአብሔር ከሰጠው ሞራላዊ መለኪያ ጋር በልብ በተግባርም ተጣጥሞ መገኘት ነው። ጽድቅ የልብ ወይም የውስጥ ሁኔታን ሲያመለክት፣ ፍትሕ ድርጊትን ያሳያል።
ፍትሕ በምድር ላይ የሚሰፍነው በሰዎች መካከል ኃይልና ሥልጣን በአግባቡ ማለትም የእግዚአብሔርን መመሪያ በጠበቀ መልኩ ሥራ ላይ ሲያውሉ ነው። ምን ጊዜም ኃይልና ሥልጣን በኅብረተ ሰብ መካከል በእያንዳንዱ ግለ ሰብ ላይ ተሠራጭተው ይገኛሉ። የሥርጭት መጠናቸውም ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። በሰዎች መካከል ልዩ ልዩ ኃይሎች አሉ፤ ለምሳሌ ያህል የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበረዊ፣ ግብረ ገባዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ቤተ ሰባዊ፣ የጉልበትና የአእምሮ ብሎ መጠቃቀስ ይቻላል።
የፖለቲካ ተመራጭ ፖለቲካው በሚፈቅድለት መጠን ኃይልን ሥራ ላይ ያውላል፤ ሥልጣንን ይጠቀማል። የገንዘብ ክምችት ያላቸው ሰዎች በኢኮኖሚው መስተጋብር ወይም እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፤ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖአቸው ያይላል። በሃይማኖት አካባቢ በቄሱ ወይም በመጋቢው ወይም በነቢዩ ሌሎችን አማንያንን የሚያንቀሳቅስ በመፍታትና በማሰር ወይም በመመረቅና በመርገም አንዳንዴ ሊያስገብር የሚችል ኃይል ነው፤ በማኅበረ ሰብ ውስጥ ተወዳጅነትም ኃይል ነው። በዕድሜ፣ በትምህርት፣ በሙያ ወዘተ አኳያ እንደየባህሉ ከተደማጭነት ጋር የተያያዘ ኃይልም ተሠራጭቷል።
እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነው ካልን እነዚህ ኃይሎች በትክክል ተግባር ላይ ሳይውሉ ቢቀር ይገደዋል ማለታችን ነው። ፍትሕ ተዛባ ስንል የሌሎችን ሕይወት፣ ክብር፣ ጾታዊ ፈቃድ፣ ነጻነት፣ ጉልበት፣ ሥራ፣ ገንዘብ፣ ንብረት፣ ጥቅም ለመንፈግ ወይም ለመንጠቅ ኃይል ወይም ሥልጣን በአሉታዊ መልኩ ሥራ ላይ ውሎአል ማለት ነው።
ኃያሉ ወይም ብርቱው ኃይልና ማታለልን ተጠቅሞ ደካማውን ሲገፋ ወይም ሲመዘብር ፍትሕ ተዛብቷል፤ ተጓድሏል፣ ግፍ ተፈጽሟል። ወንድ ሴትን ሲረግጥ ወይም ሴት በወንድ ላይ ስትብለጠለጥ ወይም ስታተርፍ፣ ብርቱው ደካማውን ሲቦጠቡጥ፣ ከበርቴው ደኻውን ሲበዘብዝ ግፍ ነው። የፍትሕ እንቅስቃሴ ቢኖርም ዓለማችን በአብዛኛው በግፍ የተሞላች ናት። በዓለም ዙሪያ በየጊዜውና በየቦታው ግፍ ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ የመብት ረገጣ ተንሰራፍቶ ይታያል፤ ብዙ የተገፉ ሰዎች እንባ ይፈሳል። ምድር በብዙ ሥፍራ በግፍ ጩኸት ተከድናለች፤ በአታላዮችና በሸፋጮች ተሸብራለች። ይህ ጩኸት ትናንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ነው።
ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቶአል። ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፤ ፍትሕ ድል አይነሣም፤ ፍትሕ ይጣመም ዘንድ ክፉዎች ጻድቃንን ይከባሉ። ዕንባቆም 1፡ 3-4
ነቢዩ ሚክያስም እንዲህ ይላል፣
ከዚያም እኔ እንዲህ አልኩ፣ “እናንት የያዕቆብ መሪዎች፣ እናንት የእስራኤል ቤት ገዦች ስሙ፤ ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን? መልካሙን ጠላችሁ፤ ክፉውንም ወደዳችሁ፤ የሕዝቤን ቆዳ ገፈፋችሁ፣ ዐጥንቶቻቸውንም ሰባበራችሁ፣ በመጥበሻ እንደሚጠበስ፣ በድስት እንደሚቀቀል ሥጋ ቆራረጣችኋቸው። ሚክያስ 3፡ 1-3
ሹሙ፣ ባለ ሥልጣኑ፣ ከበርቴው፣ መለዮ ለባሹ፣ ወንበዴው፣ ምሁሩ፣ ቄሱ፣ ነቢዩ በትምክሕተኝነት ይመላለሳሉ፤ ፍትሕ ያጓድላሉ። የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላል፣
የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፣ ምድሪቱን ‘አንቺ ያልነጻሽ በቁጣም ቀን ዝናብ ያላገኘሽ ምድር ነሽ’ በላት። መሳፍንቷ እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበድላሉ፤ ንብረቱንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለቶች ያደርጋሉ። ካህናቷ በሕጌ ላይ ያምፃሉ። ንዋያተ ቅድሳቴን ያረክሳሉ፤ የተቀደሰውን ከረከሰው አይለዩም፤ በጎደፈውና በንጹሑ መካከል ልዩነት እንደሌለ ያስተማራሉ፤ ሰንበታቴን ከማክበር ዘወር ብለዋል፤ በዚህም በመካከላቸው ተንቄአለሁ። በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኩላዎች ናቸው። በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ። ነቢያቷም በሐሰት ራእይና በውሸት ሟርት ይህን ሁሉ ድርጊት ያድበሰብሱላቸዋል፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ። በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ ይቀማል፤ ይዘርፋል፤ ፍትሕ በማጉደልም ድኻውንና ችግረኛውን ይጨቁናል፤ መጻተኛውንም ይበድላል። ሕዝቅኤል 22፡ 22-29
ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቁኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። ሚልክያስ 3፡ 5
እናንት ፍትሕን ወደ መራርነት የምትለውጡ፣ ጽድቅንም ወደ ምድር የምትጥሉ ወዮላችሁ! እናንተ በፍርድ አደባባይ የሚገሥጻችሁን ትጠላላችሁ፣ እውነት የሚናገረውንም ትንቃላችሁ። እናንተ ድኻውን ትረግጣላችሁ፣ እህል እንዲሰጣችሁም ታስገድዱታላችሁ፤ ስለዚህ በተጠረበ ድንጋይ ቤት ብትሠሩም፣ በውስጡ ግን አትኖሩም፤ ባማሩ የወይን ተክል ቦታዎች ወይን ብትተክሉም፣ የወይን ጠጁን ግን አትጠጡም፤ ኃጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደ ሆነ፣ በደላችሁም የቱን ያህል እንደ በዛ እኔ አውቃለሁና። ጻድቁን ትጨቁናላችሁ፣ ጉቦም ትቀበላላችሁ፣ በፍርድ አደባባይም ከድኻው ፍትሕ ትነጥቃላችሁ። ክፉውን ጥሉ፣ መልካሙንም ውደዱ፤ በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤ ምናልባትም የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።
የፍትሕን መጓደል በአምልኮአዊ ሥርዓት፣ በዝማሬ ለመሸፈን የሚደረገውን የሕዝቡን ጥረት እግዚአብሔር አይቀበለውም።
የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ አርቅ፤ የበገናህንም ዜማ እኔ አልሰማም። ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ። አሞጽ 5፡7፣ 10-12፣15፣23-24
ምሕረት
የእግዚአብሔር ቃል ስለ ጽድቅና ፍትሕ ብቻ የሚናገር አይደለም። ከዚያም አልፎ ስለ ምሕረትና ስለ ምሕረት አስፈላጊነት ይናገራል። ምሕረት እንደ ተደረገላቸው ሰዎች ምሕረት ማድረግን እንድንለማመድ ያስገነዝበናል።
መቼም ፍትሕ ለሚያስገኝልን ጠቀሜታ ምሕረት አያሻንም። ምሕረት የእኛ ጽድቅ ወይም ፍትሕ ያላደረሰንን ደረጃ የሚያደርሰን በጎነት ነው።
ለምሳሌ፦ ሕግን በመተላለፍ የ 20 ዓመት እሥራት የተፈረደበት ሰው እሥራቱ ወደ 8 ዓመት ዝቅ ቢደረግለት የ 12 ዓመት እሥራት ምሕረት ተደረገለት ማለት ነው። ይህን የ 12 ዓመት እሥራት መቀነስ ፍትሕ ሊያስገኝለት ከቶ አይችልም፤ እንዲያውም ፍትሕ የ 20 ዓመት እሥራቱ እንዲጸና ግድ የሚል ነው እንጂ።
በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ መጽደቅ፣ ከኩነኔ ማምለጥ፣ የዘላለም ሕይወት ወራሽ መሆን የፍትሕ አድራጎት ሳይሆን የእግዚአብሔር የምሕረት አድራጎት ነው። ስለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 2፡ 3 ላይ፣ “… ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል” የሚለው።
‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሐን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። ማቴዎስ 12፡ 7
ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እሻለሁና። ሆሴዕ 6፡ 6
በጽድቅ ለመኖር ፍትሕን ለማድረግ ተጠርተናል። ይህ በሰዎች መካከል ሰላምን ያሰፍናልና። ሁከት አምባጓሮ ፍርሃትና ስጋት ይገታሉ።
ይሁን እንጂ ከፍትሕ ስንጎድል ስናጓድልና ከዚያም የተነሣ በችግር፣ በጉድለት፣ በክስረት ውስጥ ወድቀን እንዳንቀር የምሕረትን መንገድ መጓዝ ያሻናል። አዲስ ኪዳንም ምሕረትን መደምደሚያ አድርጎ አቅርቦልናል።
ምሕረት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዓይነተኛ ቃል ትልቅ ሥፍራ ያለው ቃል ነው። ምሕረትን ለመረዳት ከመሞከራችን በፊት ግን ስለ ርኅራኄ ማንሳት አስፈላጊ ነው።
ይቀጥላል…
የውይይት ጥያቄዎች
1.
ፍትሕና ምሕረት ልዩነታቸው ምንድነው?2.
ፍትሕ የእግዚአብሔር ባሕርይ ነው ካልን ፍትሕ በጠፋበት ዓለም ክርስቲያኖች ድርሻቸው ምን ሊሆን ይገባል? ድርሻቸውን እንዴት ሊወጡ ይችላሉ?3.
ምሕረት በማድረጉ የሚያስታውሱት ሰው አለ? እርስዎስ ምሕረት ያደርጋሉ?4.
ጽድቅ ምንድነው? ከፍትሕ ጋር እንዴት ይዛመዳል?አቶ ሰለሞን ከበደ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሲሆኑ፣ ይህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ካቀረቡት የመክፈቻ ንግግርና ኋላም “ፍትሕና ምሕረት” በሚል ርእስ በ 1999 ዓ.ም. ካሳተሙት መጽሐፍ በከፊል የተወሰደ ነው።
የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆችና መሪነት
በፍራንሲስ እስጢፋኖስክፍል አንድ
የእግዚአብሔር የሰላምና የጽድቅ መንግሥት በምድር
እግዚአብሔር በዘላለማዊ ምክሩና ዓላማው የሰው ልጅ ኑሮው፣ ሕይወቱ፣ ትዳሩ ሁሉ ሰላም የሠፈነበትና ጤንነቱ የተሟላ እንዲሆን ይፈልጋል። የሰው ልጅ ሰላምና ጤና ሊያገኝ የሚችለውም እግዚአብሔርን በማወቅ በርሱ ብቻ በመታመን በትእዛዙና በሃሳቡ ብቻ የሄደ እንደሆነ ነው። ከዚህም የተነሣ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ መሪዎች አድርጎ በላካቸው መሳፍንት፣ ነቢያት፣ ነገሥታት፣ ካህናት ሕዝቡን ሥርዓቱንና መንገዱን ያስተምራቸው ነበር።
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያሰበው የተሟላ ሕይወትና ኑሮ ሊመጣ የሚችለው እርሱ እራሱ በምድር በሚመሠርተው መንግሥት ብቻ መሆኑን ነቢያት ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ ባሳሰበው መሠረት ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተናግሮ ነበር፦
ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድር ምስኪኖችም ፍትኅን ይበይናል፣ በአፉ በትር ምድርን ይመታል፣ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። ጽድቅ የወገቡ መታጠቂያ፣ ታማኝነትም የጎኑ መቀነት ይሆናል። ኢሳይያስ 11፡ 4-5
ከዚህ ጥቅስ የምንረዳው የይሁዳ ሕዝብ በኃጢአት የተሞላ፣ ድሃ አደጉን የሚበድል፣ ፍትኅና ቅንነት በጎደለው ኑሮው ክፋትን ማብዛቱን፤ ሰዎች በሰላም አብረው እንዲኖሩ ለማድረግ እግዚአብሔር ጣልቃ እንደሚገባና ስግብግብነትን፣ ደሃ መበደልንና ጭቆናን፣ ክፋትንና ኃጢአተኛነትን አስወግዶ ፍትኅን በመመስረት ጽድቅንና ሰላምን እንደሚያመጣ ማቀዱን ነው።
ይህንኑ እግዚአብሔር የገባውን የተስፋ ቃል እንደገና ሲያረጋግጥ ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተናግሮ ነበር፦
በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ፣ ከዳዊት ቤት የጽድቅ ቅርንጫፍ አበቅላለሁ
በምድሪቱም ፍትኅንና ጽድቅን ያደርጋል
በዚያ ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ ኢየሩሳሌም በሰላም ትኖራለች
የምትጠራበትም ስም፣ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል። ኤርምያስ 33፡ 15-16
ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ክፍሎች ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውና የሁለተኛ መምጣቱን የሚናገሩ ሲሆኑ፤ በመጀመሪያ መምጣቱ ሰዎችን ከኃጢአታቸው ንስሃ እንዲገቡ የሚጠራና የሚያስተምር ሲሆን በዳግም ምፃቱ ግን በመላው ምድር የራሱን የፍትኅና የጽድቅ መንግሥት ለመመስረት የሚሠራውን ሥራ የሚናገር ክፍል ነው። በጊዜው እነዚህ ቃላት የተነገሩት ለይሁዳ ምድር ለእስራኤላውያን ይምሰሉ እንጂ በእስራኤላውያን አማካይነት የምድር ወገኖች በሙሉ እንደሚድኑ ቀደም ብሎ በተደጋጋሚ የተነገረ ስለሆነ ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተፈጻሚነቱን የሚያገኝ እውነተኛና ትክክለኛ ቃል መሆኑን ሲያረጋግጥ ማየት ይቻላል። የዚህ ትንቢት ተፈጻሚነቱ ሲቃረብ ሚክያስ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር፦
አንቺ ግን ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ፣ ከይሁዳ ነገዶች መካከል ትንሿ ብትሆኚም አመጣጡ ከጥንት ከቀድሞ ዘመን የሆነ የእስራኤል ገዥ ከአንቺ ይወጣልኛል … በእግዚአብሔር ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ታላቅነት ፀንቶ ይቆማል፣ መንጋውንም ይጠብቃል፣ በዚያን ጊዜ ኃያልነቱ እስከ ምድር ዳርቻ ስለሚደርስ ተደላድለው ይኖራሉ። እርሱም ሰላማቸው ይሆናል። ሚክያስ 5፡ 2-5
ይህ ከቤተልሔም ይወጣል የተባለው ገዥ መሲሁ ጌታ ኢየሱስ ነው። ትንቢቱም ትክክል ነበር። ጌታ ኢየሱስ ከዳዊት ዘር በቤተልሔም ተወልዶአል። እግዚአብሔር በመለኮታዊ ሥራው በዘላለማዊ ምክሩ በሰው ታሪክ ጣልቃ ገብቶ የዓለም ንጉሥና አዳኝ ኢየሱስ እንዲወለድ አድርጎአል። ይህ ንጉሥ ነው የራሱን መንግሥት በምድር የሚመሠርተው። የርሱም መንግሥት የጦር፣ የምድራዊ ሥልጣንና ግዛት ሳትሆን የንስሃ፣ የኃጢአት ስርየትና የጽድቅ መንግሥት ናት። የመንግሥቱም ምሥረታ ይፋዊ የሆነ እንቅስቃሴ በጀመረበት ጊዜ “ንስሃ ግቡ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና” ብሎ ማስተማሩ ይህንኑ ለማረጋገጥ ነበር። ማቴዎስ 4፡ 17
የመሲህ መንግሥት የሰላምና የጽድቅ መንግሥት ናት፤ ፍትኅ የሰፈነባት፣ ባለ ጸጋውና ድሃው እኩል የሚታዩባት፣ ምዝበራና ብዝበዛ፣ ክፋትና ጥፋት የማይፈቀድባት፣ ሰዎች ከመጥፎ ሕይወትና ከክፋት ኑሮ ተለይተው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና አካሄድ የሚመላለሱባት መንግሥት ናት። የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት እግዚአብሔርን ባለማወቅ በኃጢአት ከመኖር ተለይቶ በአዲስ ሕይወት በጽድቅና በቅድስና መኖር ማለት ነው። ከኃጢአት መለየት፣ መራቅ፣ መተው ማለት ነው። በዚህም የጽድቅ መንግሥት ተካፋይ መሆን ይቻላል።
ይህን የጽድቅ መንግሥት ሲመሠርት ጌታ ኢየሱስ ብቻውን አላደረገም፤ ነገር ግን ከርሱ የመንግሥቱን የጽድቅ ሥራ የሚረከቡና የሚያስፋፉትን ደቀ መዛሙርት በመምረጥ አስፈላጊ የሆነውን ትምህርት በመስጠት ነበር የላካቸው። ይህንን ሃሳብ በሚከተለው ጥቅስ ውስጥ እናገኛለን፦
ኢየሱስም ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ። ማቴዎስ 4፡ 19
የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመሠረተው በትምህርት፣ በስብከትና በፈውስ መሆኑን እያሳያቸው የተመረጡት ከርሱ ጋር በቀጥታ በሥራው እንዲሳተፉ ከርሱም በኋላ ሥራውን እንዲቀጥሉ ሥልጣን ሰጣቸው።
በዚህ በሰው ማዳን ሥራ ያሰማራቸው አሥራ ሁለት ደቀመዛሙርት ብቻ አልነበሩም። በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 9 እና 10 እንደምናነበው ሌሎችንም ሰባ የሆኑትን መርጦ እንደ ሾማቸውና እንደ ላካቸው እናያለን። ሲናገርም፦
መከሩ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ቦታ እንዲልክ ለምኑት… ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች እየፈወሳችሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች በሏቸው… እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፣ እናንተንም የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።
በማለት የሥራውን ስፋት፣ የሥራውን ክብደትና አስፈላጊነት በማሳየት ታላቅ አደራ ጥሎባቸው ነበር። ጌታ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠውን ይህን ታላቅ አደራ ተቀባዮቹ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በማስተማር ሰዎችን ወደ ንስሃ በመጥራት የእግዚአብሔር የጽድቅ መንግሥት ዜጎች እንዲሆኑ ከሚመጣውም ቁጣ እንዲያመልጡ በማሳሰብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና በትጋት በጌታ መንፈስ ቅዱስ ረድዔት ሲሠሩ ቆይተው በቅብብሎሽ እኛ ዘንድ ደርሶአል።
ሐዋሪያትም በመሠረቱት መሠረትና ባቋቋሟቸው አብያተ ክርስቲያናት ሲካሄድ የነበረው ይህ “ታላቁ ተልእኮ” በመባል የሚታወቀው የሰውን ማዳን፣ የእግዚአብሔር የጽድቅ መንግሥት ሥራ ዛሬም ቢሆን በአብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ መንገዶች እየተሠራ ይገኛል።
ሀ. የቤተክርስቲያን ምሥረታ
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑ የተመሠረተችበትን ቃል ሲናገር፦ “አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚህ ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” ብሎ ነበር። ማቴዎስ 16፡18
ጌታ ኢየሱስ ይህን የተናገረው፣ “ለመሆኑ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ነው ይላሉ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ … ስምዖን ጰጥሮስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ በመለሰለት ጊዜ ነበር። የጴጥሮስን መልስ አንዳንድ ቤተክርስቲያናት በሌላ መንገድ ቢተረጉሙትም አብዛኛዎቹ የሚከተለውን ትርጉም ይጋራሉ ወይም ይስማሙበታል። ይኸውም፦
ቤተክርስቲያን የምትመሠረትበት ዓለት ክርስቶስ ራሱ መሆኑን፣ ይህም የኢየሱስ የድነት ሥራ እንደሆነ
ጴጥሮስ ለዚህ ለመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ሥራ መሪ እንደሚሆን
ኢየሱስም ቤተክርስቲያኑን የሚመሠርተው ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ግልጽ ባደረገው በጴጥሮስ እምነት ላይ እንደሆነ ነው። ማቴዎስ 16፡ 13-19
ይህንንም ለማረጋገጥ የምንችለው ሐዋሪያው ጴጥሮስ ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ ጀምሮ በሰጠው በክርስቶስ ስቅለት፣ ሞትና ትንሳኤ ላይ ብቻ በተመሠረተ ትምህርትና ምስክርነት ነው። ይህንንም በሐዋሪያት ሥራ ምዕራፍ 2፣ 3፣ 4፣ 5 ላይ ማየትና መረዳት ይቻላል።
ቤተክርስቲያንም በጴንጤቆስጤ ቀን በበዓለ ሃምሳ ዕለት ተመሠረተች። በዚህ ቀን መንፈስ ቅዱስ በአስደናቂ ሁኔታ ወርዶ ሰዎች በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ሲጀምሩ፣ ሐዋሪያው ጴጥሮስ በክርስቶስ ስቅለት፣ ሞትና ትንሳኤ ላይ ብቻ የተመሠረተውን ትምህርትና ስብከት ካሰማ በኋላ የሰዎች ልብ እጅግ ተነካ። ጴጥሮስም፦ “ንስሃ ግቡ፣ ኃጢአታችሁ እንዲሰረይላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፣ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” በማለት የድነት ጥሪ አቀረበላችሁ። በዚያን ቀንም አምነው የተጠመቁ ሦስት ሺህ እንደ ነበሩና የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያንም በዚያን ዕለት እንደ ተመሠረተች በሐዋሪያት ሥራ ምዕራፍ 2 እንደሚገባ ተገልጿል።
ሐዋሪያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክት አንድ መሪ በእግዚአብሔር ቤት እንዴት መኖር እንደሚገባው ሲጽፍ፣ “ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። ብዘገይ ግን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱ የእውነት ዓምድና መሠረት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ነው።” ብሎአል። በዚህ ጥቅስ ስለ ቤተክርስቲያን አራት መሠረታዊ ሃሳቦችን መመልከት ይቻላል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡ 14-16
ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት ወይም ቤተሰብ ማለት ሲሆን፣ እዚህ የተጠቀመው የግሪክ ቃል “ኦይኮስ” የሚል ነው። ይህ ደግሞ ቤተሰብ ወይም ብዙ ሰዎች የሚኖሩበት ማለት ነው። በእግዚአብሔር የሚታመኑ የሚኖሩበት ለማለት ነው።
ቤተክርስቲያን የሕያው እግዚአብሔር ጉባዔ ናት። የግሪኩ ቃል “ኤክሊዚያ” የሚል ነው። ይህን እላይ ተመልክተናል፤ “ተጠርተው የወጡ ሰዎች” ልንለው እንችላለን።
ቤተክርስቲያን የእውነት ዓምድ ናት። ምሰሶ ወይም ዓምድ ቤት ወይም ሕንጻ እንዲቆም የሚረዳ ነው። ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን እውነት የያዘችና ለሕዝብ ሁሉ የምታስተላልፍ፣ የምታስተምር፣ ወደ እውነቱም ሕዝቡን የምትመራ ጉባዔ ናት።
ቤተክርስቲያን የእውነት መሠረት ናት። ቤተክርስቲያን እውነትን በመያዝና በመደገፍ ለሁሉ እንዲታይ የምታደርግ ክርስቶስ በደሙ የዋጃትና ያነጻት አካል ናት።
ለ. የቤተክርስቲያን ተልእኰ ምንድነው?
የቤተክርስቲያን ተልእኰ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር የመሠረታትን መንግሥት ማስፋፋትና ማዳረስ ነው። የክርስቶስን የድነት ወንጌል ወደ ዓለም ሁሉ በመሄድ ለፍጥረት ሁሉ ማወጅ ነው። ማርቆስ 16፡ 15። የቤተክርስቲያን ቀጥተኛ ተልእኰዋ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ የክርስቶስ ምስክር መሆን ነው። የሐዋሪያት ሥራ 1፡ 8
ቤተክርስቲያን ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣንን በመቀበል ስለዚህ ስለ ጽድቅ መንግሥት በስፋትና በጥልቀት በማስተማር ሰዎችን የክርስቶስ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ደቀ መዛሙርት በማድረግ ገና በኃጢአትና በጨለማ ውስጥ ያሉትን እንድታስተምር፣ እንድታጠምቅ አደራ የተሰጣት በክርስቶስ አዳኝነትና ጌትነት የሚያምኑ የክርስቲያኖች ኅብረት ናት። ማቴዎስ 28፡ 18-20
ቤተክርስቲያን የተጠራችውና የተለየችው ተስፋ ለቆረጡ በኃጢአት ዓለም በክፉ ሥራቸው በጨለማ ለታገቱት የእግዚአብሔርን ታላቅ የማዳን ሥራ ለማወጅ ነው። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡ 9-10። ቀድሞ በትውልድ አሕዛብ ለተባሉ በኑሮና በሥራ ኃጢአት በመሥራት ለታወቁ በደለኞች፣ ከኪዳኑ ተስፋ ርቀው ላሉ ኃጢአተኞች ኢየሱስን እንደ አዳኛቸው ቢቀበሉ ኃጢአታቸው እንደሚሰረይላቸው የእግዚአብሔር የጽድቅ መንግሥት ዜጎች እንደሚሆኑ ለማስተማር የተጠራች ናት።
ሐ. ቤተክርስቲያንን ቤተክርስቲያን የሚያሰኟት ነገሮች
“ቤተክርስቲያን” እንዲሁ በጥሬ ቃሉ የክርስቲያን ቤት ማለት ነው። ይህም ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ቤት እንደ ማለት ነው። ሆኖም ይህን ቃል ሐዲስ ኪዳን በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ ስንመለከት “ኤክሊዚያ” የሚለውን ቃል ለመተርጎም የተሰጠ ቃል ሆኖ እናገኘዋለን። ማቴ.16፡ 18
ሐዲስ ኪዳንን ከግሪክ ቋንቋ ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች የተረጎሙ “ቤተክርስቲያን” ብለውታል። ይህ የግሪክ ቃል ከላይ እንዳስረዳነው “ተጠርተው የወጡ ሰዎች” የሚል ትርጉም እንዳለው የመጽሐፍ ቅዱስና የቋንቋ ሊቃውንት ይስማሙበታል። በመሆኑም እነዚህ “የተጠሩ” ሰዎች ላንድ የተለየ ዓላማ መለየታቸውንና መላካቸውን እንገነዘባለን። ይህንንም ለማረጋገጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል “ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም” ብሎአልና፣ በርግጥም ቤተክርስቲያን ለተለየ ሥራ የተጠራችና የተለየች ኅብረት ናት። ዮሐንስ 16፡ 19
እውነተኛው የክርስቶስ የድነት ወንጌል የሚገኘው በቤተክርስቲያን ዘንድ ነው።
በሐዋሪያት ሥራና በሌሎችም የሐዋሪያው የጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ እንደምንረዳው ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች ኅብረት ስትሆን ይህን ኅብረት የሚመሠርቱ ወገኖች ከተለያዩ ሕዝቦች ሆነው አንድ ወይም የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው።
አንድ የሚያደርጋቸውና ኅብረታቸውን ጠንካራ የሚያደርገው ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኝ በይፋ መቀበላቸውና መከተላቸው ነው። የራሳቸውን አንድነትና ኅብረት የሚመለከቱት በዓለም መመዘኛ ሳይሆን በክርስቶስ መመዘኛ ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን የአንድነት መሠረታቸው በክርስቶስ ላይ ብቻ መሆኑን የጻፈው ለእኛም ብርቱ ማስገንዘቢያና ትምህርት እንደሚሆነን አምናለሁ።
ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ። በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፣ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ። ከሁሉ በላይ የሆነ በሁሉም የሚሠራ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አምላክ አለ። ኤፌሶን 4፡ 2-6
የቤተክርስቲያንን ትርጉም በጣም ባጭሩ ተመልክተናል። እንዲሁም ቤተክርስቲያን ከዓለም የተለዩ ወገኖች ኅብረት እንደ ሆነችም መሠረቷና አንድነቷ ክርስቶስ እንደሆነ አይተናል። ሆኖም ቤተክርስቲያንን ቤተክርስቲያን ሊያሰኙአት የሚችሉትን ነገሮች ደግሞ እንመልከት። እውነተኛ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን የሚከተሉትን ነገሮች በትክክል የምትፈጽም መሆን አለባት።
በብሉይና በሐዲስ ኪዳን የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ሳይሸቃቀጥ፣ ሳይበረዝ፣ ሳይቀነስ፣ ሳይጨመር፣ ሳይለወጥ፣ በትክክልና በንጽሕና ለሰዎች የሚሰበክባት፣
ቅዱሳት ምሥጢራት ማለትም ቅዱስ ቁርባንና ቅዱስ ጥምቀት በትክክል የሚፈጸሙባት የሆነ እንደሆነ ቤተክርስቲያን መባል ትችላለች።
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የድነት ወንጌል በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተገለጸው የማይሰበክባትና ትምህርቱም የማይሰጥባት፣ ቅዱስ ጥምቀትና ቅዱስ ቁርባን በታዘዘው መሠረት የማይከናወንባት ቤተክርስቲያን፣ ቤተክርስቲያን ሳትሆን እንዲሁ የሰዎች ስብስብና ሌላ ተልእኰ ያላት ትሆናለች። ስለዚህ በተለይም የተለያዩ ትምህርቶች በሚሰጡበት በዚህ ዘመን ብዙዎች ሳይላኩ እየተላኩ፣ ከቤት ወደ ቤት፣ ከግለሰብ ወደ ግለሰብ እየሄዱ ቤተክርስቲያን ልትቆጣጠርና ልትከታተል የማትችለውን በርካታ የስሕተት ትምህርቶችን በማስተማር የዋሁንና አዳዲስ አማኒያንን እንዳያሳስቱ ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል። ይቀጥላል…
ክፍል ሁለት፦ የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆች
ክፍል ሦስት፦ መሪነት
ቄስ ፍራንሲስ እስጢፋኖስ የቤተክርስቲያን መሪና የአዲስ ሕይወት አገልግሎት ዳይሬክተር ናቸው።
የጥበብና የሰላም መጀመሪያ ዛሬም እግዚአብሔርን መፍራት ነው
ሃይማኖት የጠብና የጦርነት መንስዔ ነው አፅንቶ መባል ከጀመረ ይኸው መቶ ዓመት አለፈው።
ሃይማኖት አክራሪነትን ያጸናል፤ የዓለማትን ታሪክ
በጐና ክፉ
ብርሃንና ጨለማ
ጽድቅና ኩነኔ፣ እያለ ይመድባል።
ለድርድር ሥፍራ የለውም፤ ቅራኔን ያሰፋል፤ ወደ ጠብ ያመራል፤ ይሉናል።
ስለ ሕይወት፣ ስለ ጽድቅ፣ ስለ እውነት “እርግጠኛ መሆን ይቻላል” ስለሚል በሰላም አብሮ መኖር እንዳይቻል ጋሬጣ ሆኗል።
ለዚህ መፍትኄው ሃይማኖትን ችላ ማለት ነው፣ ይሉናል።
ሰው መረን እንዳይወጣ፣ ከአራዊት እንዲለይ ሃይማኖት ያበረከተውን ሥነ ምግባርና ገደብ እነዚሁ ይዘነጋሉ፤ ማስታወስ አይፈቅዱም።
እርግጥ በሃይማኖት ስም በደል አልተፈጸመም አንልም። ሕዝብን ለማነሳሳት ሃይማኖታዊ ሽፋን አልተበጀም አንልም።
እውን ግን ሃይማኖት ለሰላም መጥፋት ምክንያት ነው?
የታሪክ ማኅደር ሲገለጥ በተለይ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታየው አሣር መነሻው ሃይማኖታዊ ሳይሆን ብሄራዊ፣ ፖለቲካዊና ኤኰኖሚያዊ ሆኖ እናገኘዋለን።
የሶቭየት ኅብረቱ ጆዘፍ ስታሊን ብቻውን ከሃያ ሚሊዮን ያላነሰ ሰው አስፈጅቷል። በዚህ ላይ የመጀመሪያውን የዓለም ጦርነት ይጨምሩ፣
·
ሁለተኛውን ይድገሙ።·
የእስራኤልና የፍልስጤምስ?·
የኰሪያ ጦርነት ለምን ይረሣ?·
ቪየትናምስ?·
የቻይና ሽብርና የባሕል አብዮት?·
የኢትዮጵያስ የ 6/66 ግርግር?·
የኢትዮጵያና የኤርትራ ውጊያ·
ሩዋንዳ-ቡሩንዲ·
ኰንጎ፣ ወዘተየአንዳቸውም መንስዔ ሃይማኖት እንዳልሆነ እንረዳለን።
እኛ ግን የጦርነት ምክንያት ሰው የራሱን ክብር መፈላለጉና ፈሪሃ እግዚአብሔር መጥፋቱ ነው እንላለን። አያቶቻችንና አባቶቻችን ሲጠሩት የኖሩት አምላክ መረሣቱ ነው፤ ችግሩ ያለው የሰው ልብ ጋ ነው፣ እንላለን፤
ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና (ማቴዎስ ወንጌል 15፡ 19)
ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲጠፋ ወጣቱ ለአዛውንቱ ከተቀመጠበት አይነሳም። ነጋዴው በሚዛን ይበድላል። የአገር መሪው ለሕዝብ አይራራም። ልጅ ወላጁን ያዋርዳል። ወልዶ ይጥላል፣ ችላ ይላል። ጫማ አስጠርጐ ጥፊ ይከፍላል፣ ካልቾ ይመርቃል። ሰውን በቋንቋና በቁመና ያገላል ወይም ያቀርባል። በአደባባይ ለሴቶች መብት ይከራከራል፤ ቤት ገብቶ ሚስቱን ያንገላታል።
ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲጠፋ ጓዳው ከእግዚአብሔር ቤት ይበልጥበታል። ራሷን አላስደፍር ያለች ሴት ተማሪ ከትምህርት ገበታዋ ላይ ትፈናቀላለች። ይኸኛው ቃል ይገባል፣ ያፈርሳል። አማና ይበላል። ያኛው ፍቅረ-ንዋይን በረከት፣ ጮሌነቱን ጥሪ ይለዋል። መማለጃን የፍቅር ስጦታና መብት፣ የቡድን ስሜቱንና አንጀኛነቱን ደግሞ አንድነትና ኅብረት ብሎ ይሰይማቸዋል።
ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲጎድል ምሑሩ ለእውነት አልገዛ ይላል። አብሮ የኖረ ወዳጅ ይከዳል። ሸክም ያንገላታት አህያ ዱላ ይጨመርላታል። ሕግ የሚያስከብረው ይሰርቃል። ቄሱ ያታልላል። ሐኪሙ ቃለ መሃላውን ያፈርሳል። ፈላስፋው፦ አመጽም እኰ ወደ ጽድቅ ያደርሳል ይላል።
ፈጣሪ እንግዲህ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ነው። ፍጡር ደግሞ ዓለማት፣ ሰውና የሰው ሥራ ውጤቶች ናቸው። ፍጡር ፈጣሪውን ማምለክና በሥርዓቱ መተዳደር ድርሻው ነው።
ሰው ሳያመልክ መኖር አይችልም። ፈጣሪውን ካላመለከ ራሱን ያመልካል ወይም ተመልሶ ለገዛ እጁ ሥራ ይሰግዳል።
ለፈጣሪው የተለየውን የሕይወቱን ክፍል በተለያዩ ተግባራትና የኑሮ እንቅስቃሴዎች መሙላት ይሞክራል፤ ግን አይረካም። ለአምላክ ሥፍራ እስከሚለቅለት ድረስ ዕረፍትን አያይም። ይህን እውነት መፋቅ አይቻልም።
ፍጡር የፈጣሪን ሥፍራ ሲይዝ፣ ሁሉን መቆጣጠር ሲሻ፣ ያኔ ማኅበራዊ ቀውስ ይከተላል። ይኸ የዓለም ሕዝቦች ጥንትም ሆነ ዛሬ የሚያልፉበት የተመሰከረ ታሪካቸው ነው። ኃጢአት በመሠረቱ እግዚአብሔርን፦ “አታስፈልገኝም፣ እኔ በራሴ ብቁ ነኝ” ማለት ነው። ኃጢአት ከእግዚአብሔር መሸሽ ነው፤ ወደ መቅበዝበዝ ወደ ፍርሓትና ወደ ሞት ክልል ማዝገም ነው።
ወደ እግዚአብሔር መሸሽ ግን ጽድቅና ሰላም ሕይወትም ነው።
የኤኰኖሚ ስልት የሰው አዕምሮ ውጤት ነው፣ ስለዚህም ፍጡር ነው። አዕምሮ የተሰጠን ለምድራዊ ኑሮአችን እንድናውቅበት እንጂ ሰጭውን እንድንዘነጋበትና እርስ በርስ እንድንናናቅበት አይደለም። እውቀታችን የማኅበረ ሰብን ኅልውና መቆጣጠር ሲጀምር ለፈጣሪ የሚገባውን ቦታ ይዟልና አምላክ ሆነ ማለት ነው። ሰው አምልኰውን ወደ ፈጣሪው ሳይሆን ወደ ራሱ ሲያቀና በዚያው ልክ በስነ ልቡናውና በማኅበራዊ ግንኙነቱ ላይ ቀውስ መታየት ይጀምራል።
የኤኰኖሚ ሥርዓት ምን ያህል ቢሠምር በአምላክ ልክ የሰውን ሁለንተናዊ ፍላጐት ሊያረካ አይችልም። አሜሪካኖች ይመስክሩ። ጃፓኖችም ይጠሩ። ሰው ለእግዚአብሔር እንጂ እዕርሕሐሔሕሐሔ
ለእንጀራ አልተፈጠረም፤ በእንጀራ ብቻ አይኖርም። ፍላጐቱ ከእንጀራ የሰፋና የጠለቀ ነው። የሰውን ኅልውናዊ ፍላጐት የሚያውቅለትና ፈጽሞ ሊሞላለት የሚችል አሁንም ፈጣሪው ብቻ ነው።
ፍላጐትን ደግሞ እንደ ኤኰኖሚ ሥርዓት መቀየስ አይቻልም፤ ዘመን ሲለዋወጥ ስሜትም ትውልድም መለዋወጡ አይቀርምና። ማኅበራዊ ድንጋጌዎች ብቻቸውን ውስጣዊ ማንነትን ሊያረኩ አይችሉምና። ስለዚህም ሰው ሌላ ይሻል፤ ያምጻል።
የኤኰኖሚው ስልት ኅብር ወዳድ ወይም ግለኛነትን የሚያገንን ይሆናል። ኅብር ወዳዱ ግላዊነትን ስለሚጫነው ፍጥጫ ይጀመራል። ፍጥጫው ወደ ማኅበራዊ አብዮት ይቀየርና የነበረውን ይሽረዋል።
የሰው ታሪክ ጐዳናው ፏፏ የሚባልበት ጥርጊያ ሳይሆን ባልተብላሉና በተፈረካከሱ ማኅበራዊ ፍልስፍናዎች የሰረጓጐጠ ነው።
በሶቪየት ኅብረት ለሰባ ዓመት የሶሻሊዝም ሥርዓት አምላክ ሆኖ ሲያስገብር ኖረ። ሶሻሊዝም
ፍጡር ነው። የሰው አዕምሮ ውጤት ነው። ጅማሬው ተስፋና ፍትሕ እንዳለ የሚለፍፍ በመሆኑ ይማርካል፣ ያዘናጋል። ሌላ ይሆናል ብሎ አያስጠረጥርም። ፍጻሜውን ከጅምሩ ማወቅ አይቻልም ነበር ማለት ነው።
ከአምላክ ተነጥሎ ኑሮ ድንግዝግዝና ዳበሳ ነው። ሶሻሊዝም የፈጣሪን ቦታ ይዞ ኖረ። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ንብረትና ሕይወት ተሰዋለት። ከባሕር የጠለቀ ዕንባ ረገፈለት። ካፒታሊዝም የሚባል ሌላ አምላክ ደርሶ አንኰታኰተው።
ሶሻሊዝም እኛም አገር ለአስራ ሰባት ዓመት አንገላታን። በጐሣ ፖለቲካ ተተካ። የጐሣ ፖለቲካ እንደ ቀደመው ሥርዓት ፍጡር ነው። ሰዎች የቀመሙት ነው። ያለ ፈሪሃ እግዚአብሔር የቀመሩት ነው። ሰው ከፈጣሪው ላይ ዓይኑን አንስቶ ፍጡር በሆነው ላይ አደረገ። ራሱንና ጐሣውን አስበለጠ። ራሱን ከሌላው ጋር አስተያየ፤ ሌላውን ናቀ። ከዚህም የተነሳ በወዳጆች መካከል ጠብና ጉስቁልና ነገሠ።
ካፒታሊዝም ሌላ ፍጡር ነው። የሰውን ቀማኛነት ይቀሰቅሳል፣ ያንጻል። ሰው በተፈጥሮው ንፉግ ነው፣ ራስ ወዳድ ነው። ይህን ባሕርዩን ሕጋዊ ዕውቅና ያጐናጽፈውና ያንቀሳቅስዋል። ፉክክር ያይላል፤ አብሮ ተጋርቶ መኖር ይዳከማል። በዚያው መጠን የኑሮ ልዩነት እየጐላ ይሄዳል።
የሶሻሊዝም አዝማሚያው ብዙሃንን እኩል ማደህየት ነው። የካፒታሊዝም ደግሞ ጥቂቶችን ማቅበጥ ነው። ይህን ለማቃናት ማኅበረ ሰቡ መነቃነቅ ይጀምራል፤ ሲያስፈልግም ያምጻል።
ሌላም ስም ያለው ቢኖር ያው የአዕምሮ ጥበብ ፍጡር ነው። ሁሉን በአዕምሮ ብርታት መፍታት ይቻላል ይላል። ገደብ እንዳለ ይዘነጋል። ትሕትና ይጐድለዋል፤ የትዕቢት መንገድ ነው።
ብዙ ሳይቆይ መፍታት የማይችለውም እንዳለ መገንዘብ ይጀምራል። ብዙ ካበላሸ በኋላ ማለት ነው። ላለመረታት፣ እጅ ላለመስጠት ይታገላል።
እግዚአብሔርን መፍራት ክብር እንጂ ውርደት እንዳልሆነ አይገነዘብም። ሙሉነት እንጂ ጉድለት እንዳልሆነ አያስብም። የመከባበሪያ ጐዳና እንደ ሆነ አያይም። የሰዎችን በደል በእግዚአብሔር ያላክካል። የሰዎችን በደል ሲኰንን እግዚአብሔርንም አብሮ ይኰንናል። ሰው መሆኑን፣ በሌሎች ላይ ያየው ጉድለት የርሱም ዕጣ መሆኑን ይክዳል።
እምነትና እውቀት እንደማይቃረኑ፣ እንዲያውም እንደሚጠባበቁ ይዘነጋል።
በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በሳይንስ ጥበብ ለሰው የሚጠቅሙ ብዙ ግኝቶች በጊዜው ለነበሩትና ዛሬም ላለነው የተስፋ ጮራ ፈንጥቋል። ለምሳሌ፦ ፔኒሲሊን ለብዙ ስውር ቀሳፊዎች መፍትሔ አስገኝቷል። ትንሽ ነች የምንላት አስፕሪን እንኳ በመቶ ዓመት ዕድሜዋ ስንቱን ራስ ምታትና ቁርጥማት ፈንግላለች። ስንት ፍላትና ትኩሳት አብርዳለች። ባጭሩ፣ እነዚህና የመሳሰሉት ግኝቶች ለኑሮ ቅልጥፍናን አስገኝተዋል።
አንዱን ችግር መፍታት ግን ሁሉን መፍታት ይመስለውና ሰው ይታለላል። እንደ ልጅ ቸኩሎ በጥቂቱ ይፈነድቃል። ጽኑ ተስፋና እምነት ካልተጨመረበት በስተቀር ነገ እንደሚያታግለው አያስብም። የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ነው የተባለው ለዚህ ነው።
ሰው የራሱ ተስፋ ሰጭ ሊሆን አይችልም። የተገባው አይደለምና። አምላክ አይደለምና። ተስፋ ሰጭ ያለው ከሰው ውጭ ነው፤ እግዚአብሔር ብቻ ነው።
በጥበብ የገሰገሱት ለምድር ሁሉ መሪና ሚዛን አድርገው ራሳቸውን በአምላክነት ሾሙ። ወደዚህ የሥልጣኔ ደረጃ ያልደረሱትን ማስገበር መግዛት ፈለጉ። ሁሉም በተገኘበት ከበታቹ ያለውን ማንበርከክ ተግባሩ ሆነ። ራሱን ማግነን ለሰው የማያቋርጥ ምኞቱ ሆነ። ከአምላክ ሥልጣን በታች መሆኑን ዘነጋ።
ለፈጣሪ የሚገባውን ክብር ለአዕምሮው ውጤት፣ ለሥልጣኔውና ለወገኑ ክብር አዋለ። ከዚህ የተነሣ ዘላቂ የሆነ ስምምነት ሊገኝ አልቻለም። ራስን ማግነን ድሮም ቢሆን ውጤቱ ከዚህ አያልፍም። ቅድም እንዳመለከትነው መቆራቆስና ምድርን ማወክ ተጀመረ። ሰው ራሱን ስላነገሠና ሌላው ሁሉ እንዲሰግድለት ስለሻ ብዙ ቀውስ ተከተለ።
በዚህም የሰው አዕምሮ ብቻውን ሁሉን ቻይ አለመሆኑን በራሱ ላይ መሰከረ።
የሰው ብልሃት የፈጣሪን ሥርዓት አይቀይርም። የፈጣሪን ሥርዓት የሚቀይር ተአምር ብቻ ነው፤ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ተአምር የማድረግ ሥልጣን ደግሞ ለአምላክ እንጂ ለሥጋ ለባሽ አልተሰጠም።
የሰው ብርታት የአምላክን ድካም አይረታም። አምላክ ድካም አለው ከተባለ ማለት ነው። የጥበብና የሰላም መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው። የራስን ክብር መፈላለግ ዛሬም እንደ ጥንቱ የውድቀት መጀመሪያ ነው:: ራስን ማክበር እግዚአብሔርን አለመፍራት ነው፤ ሰውን መናቅ ነው። ራሳቸውን የሚያከብሩ ይዋረዳሉ፤ ለከንቱነትም አልፈው ይሰጣሉ።
የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል?
የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም። የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር። እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ …
ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን። ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤ ሕግ እስከ መጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበረና ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጊዜ ኃጢአት አይቈጠርም፤ ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ። በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤ ዳሩ ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ …
ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው። ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል …
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።
ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና። እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ። [ኢሳይያስ 53፡ 1-12፤ ሮሜ 5፡ 6-21፤ ዮሐንስ 3፡ 13-21፤ ኤፌሶን 2፡ 1-22]
የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም
በእሸቱ አባተየስሕተት ትምህርቶች ዋነኛው ምክንያት የተሳሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ነው። ማንኛውም መጽሐፍ በደራሲው መንፈስና ለማስተላለፍ በፈለገው መልእክት መሠረት መተርጎም እንዳለበት ግልጽ ነው። ይህ ካልሆነ ለደራሲው ታማኝ አለመሆንና ያላለውን አለ፣ ያላሰበውን አሰበ ወደ ማለት ያደርሳል። ይህም ወደ ስሕተት ይመራል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጻፉት መጽሐፍ ነው። 2 ጴጥሮስ 1፡ 21፤ 2 ጢሞቴዎስ 3፡ 16-17። እንዲህ ከሆነ በዚያው መንፈስ አማካይነት ካልተተረጎመ ትርጉማችን የተሳሳተ ይሆናል።
አንድ ማስታወስ የሚገባን መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተላለፈልን ሰዎችን በመጠቀም መሆኑን ነው። እንዲህ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔርንም የሰውንም እጅ (ጣት) እናያለን ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስም በሰዎች እጅና ቋንቋ የተጻፈ ፍጹም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
ከዚህ የተነሣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን በነቢያቱና በሐዋርያቱ በኩል በተጻፈ ቃሉ ገለጠልን። እነዚህ ነቢያትና ሐዋርያት በተወሰነ ዘመንና ቦታ የነበሩ፣ የግል ስጦታ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ የነበራቸው ነበሩ። እግዚአብሔር በየዘመናቱ የተነሡትን የርሱን ባሪያዎች በዚህ መልክ በመጠቀም ፈቃዱን አስታወቀ። የብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ፣ ጥቂቱም በአራማይክ፤ የአዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክ ቋንቋ የተጻፈው፣ መጻሕፍቱ በተጻፉበት ዘመን የነበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሕዝቡንም ጨምሮ እነዚያን ቋንቋዎች ይጠቀሙ ስለነበረ ነው።
ከዚህም ጋር ለተጻፉት መጻሕፍት ዘመን ቀረብ ብለው የነበሩ አባቶች የተጻፈውን ቃል በምን ዓይነት መንፈስ ተረዱት ወይም ተረጎሙት ብሎ መጠየቅ ይጠቅማል። ለምሳሌ ያክል ከጌታችንና ከሐዋርያት ዘመን አንሥቶ እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የግሪክ ቋንቋ በሜድቴራኒያን ባሕር አካባቢ በነበሩ የሮማ ግዛቶች ውስጥ የመግባቢያና የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ሆኖ ቆይቷል። በዚያን ዘመን የነበሩ ጌታን ያመኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቃሉን እንዴት ተረዱ ብሎ በመጠየቅ ከእነርሱ መማር፣ በዘመናት ሁሉ ያልተገለጠ የእግዚአብሔር እውነት ለኔ ተገለጠልኝ በማለት የሐሰት ትምህርት አስተማሪ ከመሆን ያድናል። ቃሉ “የእግዚአብሔር ቃል የተናገሩአችሁን ዋነኞቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” ይላልና። ዕብራውያን 13፡ 7። ስለዚህ ጤናማ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ለሁላችንም አስፈላጊ ነው። የስሕተት ትምህርቶች ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ነው።
የሚከተሉትን መመሪያዎች ጤናማ በሆነ መንገድ ቃሉን ለመረዳትና ለመተርጎም ከጥንት ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ የእግዚአብሔር ሰዎች ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ስለዚህ ሁላችንም በመመሪያዎቹ ብንጠቀም በማስተዋል፣ በጥበብና በትሕትና ቃሉን ለመረዳት ይጠቅመናል ብለን እናምናለን፦
1. ቃሉን ግልጽ በሆነ መሠረታዊ ትርጉሙ መረዳትና መተርጎም
ከላይ እንደገለጽነው የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ቃሉን ሲጽፉ ቋንቋቸውን ተጠቅመዋል፤ ቋንቋ ደግሞ የሰዋሰው ሕግና አገባብ አለው። ከዚህ የተነሣ አንድ ሰው የቃሉን ትርጓሜ ለማግኘት የተደበቀ ወይም የተሰወረ ነገር ከራሱ ሳይፈጥር በቀጥታ “ይህ የማነበው ቃል ምን ይላል?” ብሎ በመጠየቅ ግልጽ የሆነ ትርጓሜውን መውሰድ አለበት። የሚከተሉት ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስን በመሠረታዊ ትርጉሙ በመረዳት ውስጥ ይጠቃለላሉ።
ሀ. የቃሉን ወይም የአረፍተ ነገሩን የመጀመሪያ ትርጉም መገንዘብ፤
የቃላት ትርጉም አብዛኛውን ጊዜ ከዘመኑና ከአካባቢው ጋር የተገናኘ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል መጀመሪያ በተነገረ ወይም በተጻፈ ጊዜ ለአድማጮቹና ለአንባቢያን ምን ትርጉም ሲሰጥ ነበረ ብሎ መጠየቅ አግባብ ያለው ነው። ስለዚህ የቃሉን ትርጉም በመረዳት ለራሳችን ያለውን መልእክት ከመውሰዳችን በፊት በተቻለ መጠን የተጻፈበትን ሁኔታና የመጀመሪያ ትርጉም ማወቅ አስፈላጊ ነው።
ለ. የሥነ ጽሑፉን ዓይነት መለየት፤
መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች የተሞላ ነው። ስድ ንባብ፣ ቅኔ፣ ምሳሌዎች፣ ራእዮች፣ ታሪኮችና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘውን ቅኔ ወይም ራእይ አንድ የታሪክ ወይም የስድ ንባብ ክፍል እንደሚተረጎም መተርጎም አግባብ ያለው አይደለም። ከዚህም ሌላ ምሳሌያዊ አነጋገሮችንና ዘይቤዎችን ለየት ባለ መንገድ መተርጎም ያስፈልጋል።
ሐ. ቃሉን ወይም አረፍተ ነገሩን በቅደም ተከተሉና በአገባቡ መሠረት መተርጎም፤
አንድ ቃል ወይም ጥቅስ ከመተርጎም በፊት የሚቀድሙትንና የሚከተሉትን ጥቅሶችና አንቀጾች ማንበብና ይዞታቸውን ማወቅ ጥቅሱን ለመተርጎም አስፈላጊ ነው። አንዳንዴም በጥቅሶችና በአንቀጾች ሳንወሰን ምዕራፎችንና መጽሐፉን በሙሉ በማንበብ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። አንድ ጥቅስ የሚቆመው ብቻውን ሳይሆን በቅደም ተከተል ካሉ ጥቅሶች፣ አንቀጾችና ምዕራፎች ጋር በሐሳብ ተገናኝቶ ስለሆነ አገባቡን በቅርብም በስፋትም መመርመር ያስፈልጋል። አዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባን አሁን በመጽሐፍ ቅዱሳችን የምናየው የምዕራፍና የቁጥር ክፍፍል መጀመሪያ ሲጻፍ እንዳልነበረ ነው። ብሉይ ኪዳን በምዕራፍና በቁጥር የተከፈለው በ1445 ዓ.ም. ሲሆን አዲስ ኪዳን ደግሞ የተከፈለው በ1551 ዓ.ም. ነው። ስለዚህ ከጊዜ በኋላ በተደረገው በምዕራፍና በቁጥር ክፍፍል ሳንገደብ ሐሳቡን ለማግኘት የሚቀድመውንም የሚከተለውንም ማንበብ ያስፈልገናል።
2. መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ይተረጉማል
በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጥቅስ ወይም አንድ ክፍል ትርጉሙ ግልጽ ካልሆነ ወይም ጥያቄ የሚፈጥር ከሆነ በሌሎች ግልጽ በሆኑ፣ በማያሻሙ ጥቅሶችና ክፍሎች አንጻር መተርጎም አለበት። ይህም የሚሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ አንድ አምላክ በመሆኑና በውስጡም የሚገኘው መንፈስና ሐሳብ አንድ ስለሆነ ቃሉ አንድነት እንጂ እርስ በርስ የመቃረን መንፈስ ስሌለው ነው። በዚህ ዓይነት ቃሉን መተርጎም፣ በማስተያየት የመተርጎም መንገድ ይባላል። በዚህ መልክ ሲተረጎም የሚከተሉትን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይጠቅማል። 1 ቆሮንቶስ 2፡13።
ሀ. በመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ መሠረት መተርጎም፤
የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዓላማ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ወይም መልእክት ለሰዎች ማብሠር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዓላማ ስለ ክዋክብት፣ ስለ ከርሠ ምድር፣ ታሪክ፣ መልክዓ ምድርና የመሳሰሉትን ማስተማር ሳላልሆነ እነዚህን ለማጥናት የሚፈልግ ሌላ መጽሐፍ መፈለግ ያስፈልገዋል። ሐዋርያው የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማ ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ይጽፋል፦ “ከሕፃንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፣ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅ ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” 2ጢሞቴዎስ 3፡ 16-17።
ይህ አተረጓጎም ለመላው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱም ክፍል አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ክፍል ለምን እንደዚያ እንደ ተፃፈ ዓላማውንና ሁኔታውን ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ “እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ ነው” ብሎ የጻፈው፣ እናምናለን እያሉ በግብረገባዊና ኅብረተሰባዊ ኑሮ በግድየለሽነት ለሚኖሩት ሲሆን፣ በአንጻሩ ደግሞ በገላትያና በሮሜ ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን ለማይሠራ ኃጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል” ሲል በግብረገብ ሥራቸው ብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ ተወዳጅነትንና ጽድቅን እናገኛለን ብለው ለተመጻደቁት ሰዎች ነበር። ሁለቱም ሐዋርያት የጻፉት ተነጣጥሎ ለየብቻ ሲታይ የሚቃረን ቢመስልም የተጻፈበትን ሁኔታና የሰዎቹን ዓይነት ስናይ የሚደጋገፉ እንጂ የሚለያዩ ወይም የሚቃረኑ ሆነው አናገኝም።
ለ. ክፍሉን በተመሳሳይ ርእስ ላይ በሚናገሩ በሌሎች ክፍሎች አማካይነት መተረጎም፤
ለምሳሌ ያክል ራእይን ስንተርጉም ሌሎች የትንቢት መጻሕፍትና ክፍሎች ስላሉ ከእነርሱ ጋር እያገናዘቡ መተርጎም አስፈላጊ ነው። ስለ ጥምቀት፣ ስለ ቅዱስ ቁርባን፣ ደኅንነት፣ ንስሓ ወዘተ፣ የሚናገሩትን ክፍሎች ስለ እነዚህ አርእስት ከሚናገሩ ከሌሎች ክፍሎች ጋር እያመሳከሩ መተርጎም፤ አንዱን ጥቅስ ብቻ ወስዶ ሌሎችን ተመሳሳይ ጥቅሶች ከመርሳት ያድናል።
ሐ. የቀደመውን በኋላኛውና ሙሉ በሆነው መገለጥ አማካይነት መተርጎም፤
አዲስ ኪዳን ከብሉይ ኪዳን በኋላ እግዚአብሔር ፍጹምና ሙሉ በሆነው ልጁ ራሱን የገለጸበት ነው። “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፣ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን…” ዕብራውያን 1፡ 1-2። “ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና…” ዕብራውያን 10፡1።
ስለዚህ ብሉይ ኪዳን የሚተረጎመው እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን በገለጠው ፍጹምና ሙሉ መገለጥ መሠረት ነው። እንደዚሁም ሐዋርያት በመልእክቶቻቸው የወንጌላትና የትምህርቶቻቸው ይዘት ምን እንደሆነ አብራርተው አስተምረውናል። ስለዚህ መልእክቶቻቸው ወንጌላትን የሚያብራሩልን ናቸው።
3. መጽሐፍ ቅዱስ ሊተረጎም የሚችለው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ብቻ ነው
የእግዚአብሔር ቃል በጻፈው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ይተረጎማል። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ምክሩንና ሐሳቡን ካልተገነዘቡ “ለፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት” መስሎ ሊታየው ይቻላል።
በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ቃሉ መተርጎሙ በኛ በኩል ሊደረግ የሚገባው ዝግጅትና ጥናት ይቀራል ማለት አይደለም። በመንፈስ ቅዱስ በማሳበብ ቃሉን አንብበው ቅደም ተከተሉን፣ ባሕሉን፣ ታሪካዊ ይዞታውን ወዘተ ተመልክተው ትክክለኛ ትርጉሙን ለመረዳት ጥረትና ዝግጅት ሳያደርጉ የመጣላቸውን የሚናገሩና የሚሰብኩ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ይህ ግን ስሕተት ነው። ማንኛውም ምእመንና አገልጋይ በጸሎት መንፈስ በመሆን የቃሉን ትርጉም ለመረዳት ከፍተኛ ጥረትና ጥናት ማድረግ አለበት።
መንፈስ ቅዱስ በምእመናን ሁሉ ውስጥ የሚኖር የኅብረት ወይም የጋራ መንፈስ ነው። 1ቆሮንቶስ 12፡ 12። ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በቃሉ ለብቻዬ ያስተምረኛል እያልን በቤተ ክርስቲያን በኩል የሚሰጠውን ትምህርትና አገልግሎት መናቅ የተሳሳተ አካሄድ ነው። በቤተ ክርስቲያንም በእውነትና በትክክል ተጠርተው በማስተማር የሚደክሙትን አገልጋዮች አለመስማትም ትክክል አይደለም። መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ ስጦታዎችን እየሰጠ ምእመናንን በጋራ የሚያንጽ ስለሆነ እውነቱ ለኔ ብቻ ተገለጸልኝ ብለን ሳንኩራራ ከእርስ በርስ በተሰጠን ጸጋ መጠን ልንማማር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ለመተርጎም መቻላችን ከሌሎች መሰል ክርስቲያኖች ጋር ኅብረት እንዳይኖረን የሚያደርግ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ የአንድነት የፍቅርና የትሕትና መንፈስ ነውና።
4. ቃሉ አሁን ለኔ (ለኛ) ምን ይላል?
መንፈስ ቅዱስ ሕያው መንፈስ ስለሆነ በቃሉ አማካይነት እያንዳንዳችን አሁን ላለንበት ሁኔታ ይናገራል። ያነበብነው ቃል መጀመሪያ በተነገረበት ወይም በተጻፈበት ጊዜ ምን ትርጉም ነበረው? በአገባቡና በመላው መጽሐፍ መሠረት ምን ትርጉም አለው? ብለን ከጠየቅን በኋላ ዛሬስ ለእኔ (ለእኛ) ምን ይናገራል? ለማኅበረ ምእመናናችንስ ምን መልእክት አለው ብለን መጠየቅ ይገባናል። ማንኛውም ተቀዳሚ ዝግጅት ቃሉን ለሕይወታችን ወደምንሰማበትና ወደምናዋህድበት ደረጃ እንዲያደርሰን ያስፈልጋል። ቃሉ ዛሬ ለእኛ በሚናገርበት መልእክት መሠረት ስንሄድ እግዚአብሔርን የምንከተል፣ ከስሕተት ትምህርት የተጠበቅን በብርሃን የምንጓዝ መልእክተኞች እንሆናለን።
ዶ/ር እሸቱ አባተ በኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ ካሊፎርኒያ የሥነ መለኮት ትምህርት መምህር ሲሆኑ፣ ይህ ክፍል “ትምህርተ ሥላሴ” በሚል ርእስ በ1987 ዓ.ም. ካሳተሙት መጽሐፍ በፈቃድ የተወሰደ ነው።
እውነተኛ ክርስቲያን ማን ነው?
በገ/እግዚአብሔር ካሕሳይምንባብ:- (የሐዋርያት ሥራ 2፡37-47)
ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት:- ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው። ጴጥሮስም:- ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና:- ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው። በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ። ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር። በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።
መግቢያ
ናፖሊዮን ቦናፓርቴ የሚባል ጀግና የጦር መሪ አንድ ቀን ወደ ጦርነት ከመዝመቱ በፊት ሌላ ሰው መስሎ ወታደሮቹን እየዞረ ይጐበኝ ነበር። በፍርሃት የሚንቀጠቀጥ አንድ ወታደር ያገኝና፦ "ምን ሆነህ ነው የምትንቀጠቀጠው?” ብሎ ይጠይቀዋል። ወታደሩም ሌላ ተራ ወታደር የሚጠይቀው መስሎት፦ “የምንቀጠቀጠውማ የነገውን ጦርነት እያሰብኩ ነው” ይለዋል።
"ስምህ ማን ነው?"
"ስሜ ናፖሊዮን ነው"
ናፖሊዮን ቦናፓርቴም፦ "ወይ ስምህን ወይ ባህርይን ቀይር" አለው ይባላል።
በዚህም ዘመን፣ "ወይ ስምህን ወይ ባህርይን ቀይር" መባል የሚገባቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የክርስቲያን ባህርይ ሳይኖራቸው ክርስቲያን ነን የሚሉ ይገኛሉ። እውነተኛ ክርስቲያን ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ መልሶች እንደሚሰጡ የታወቀ ነው። በዚች አጭር ጽሑፍ ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 38-47 ሦስት የእውነተኛ ክርስቲያን ባህሪያትን እንመለከታለን።
1. እውነተኛ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ተገቢውን ምላሽ የሰጠ ሰው ነው (የሐዋ. ሥራ 2:37-41)
የጌታ ደቀ መዛሙርት በመጀመርያ ሲያደርጉ የምናየው በአንድ ልብ ሆነው ሲጸልዩ ነው (የሐዋ. ሥራ 2፡1)። ከጸለዩም በኋላ መንፈስ ቅዱስ በላያቸው ወርዶ ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው፣ ሰዎች ሊሰሙት በሚችሉት ልሳኖች /ቋንቋዎች/ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ መናገር ጀመሩ። (የሐዋ. ሥራ 2፡5-12)
በዚያን ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ ሲሰበክ ሰምተው ንስሃ ገብተው የተጠመቁና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተጨመሩ ሰዎች ሶስት ሺህ ያህሉ ነበር።
“ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ” ሲል፣ የሰሙት ምንድነው? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው።
እነዚህ ሰዎች የአይሁድ ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ። በአጭሩ የተነገራቸው፣ ኢየሱስ ጌታና መሲሕ መሆኑን ነበር። ነቢያት የተናገሩለት የዓለም መድኃኒት እርሱ እንደ ሆነና ከኃጢአት አንጽቶ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ መሆኑን ነበር። ይህንን ሲሰሙ ልባቸው ተነካ ይላል። ስለ ሰሙትም ነገር፦ "ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ?" ብለው ጠየቁ። የተነገራቸውንም ታዝዘው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ተጨመሩ።
እውነተኛ ክርስቲያን ስለ ጌታ ኢየሱስ ማንነትና ስለ እጁ ሥራ እውነተኛውን ወንጌል የሰማ፣ መንፈስ ቅዱስ ልቡን የነካውና ለመንፈስ ቅዱስ መልእክት ተገቢ ምላሽ የሰጠ ሰው ነው፡፡
ሰዎች ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሰበክ አለበት። ወንጌል ሲባል ደግሞ ሰው የሚፈልገውን እየመረጠ ሳይሆን ተገቢ ምላሽ በሚጠይቅ መንገድ ክርስቶስ ማን እንደሆነና ምን እንደሠራ መሰበክ አለበት ማለት ነው።
ሰዎች ወንጌል መስማት አለባቸው። "ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና … እምነት ደግሞ የሚመጣው ከመስማት ነው፤ መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው።" (ዕብራውያን 11፡ 2፤ ሮሜ 10፡ )። በዚህ ዘመን የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሳይሰበክ፤ የሰሚው ልብ ሳይነካ፤ የጌታ ኢየሱስ ማንነትና ሥራው በሚገባ ሳይታወቅ፤ ከኃጢአትም ንስሓ ሳይገባ፤ እውነተኛ ክርስቲያን ነኝ ማለት እየበዛ መጥቷል።
እውነተኞች የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆንና ሌሎችን እውነተኞች የጌታ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ራሳችን በቅድሚያ እውነተኞች ክርስቲያኖች ልንሆን ያስፈልጋል። የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰበክ ሰምተናል ወይ? ሰምተንስ ተገቢውን ምላሽ ሰጥተናል? ሰዎች እውነተኛ የጌታ ደቀመዛሙርት እንዲሆኑስ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየሰበክን ነው? ወይስ ሰው የሚፈልገውን እየመረጥን እንሰብካለን?
እውነተኛ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ተገቢ ምላሽ የሰጠ ሰው ነው።
2. እውነተኛ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የሚታዘዝ ሰው ነው። (የሐዋ. ሥራ 2:42-47)
በዚህ ምድብ የምናገኛቸው እውነተኞች ክርስቲያኖች ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰበክ ሰምተው ተገቢ ምላሽ የሰጡ ብቻ ሳይሆኑ፣ ምላሽ ከሰጡ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል በመማርና ቃሉን በመታዘዝ የሚተጉ ሰዎች እንደነበሩ እንገነዘባለን። ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ቃሉን ሰምቶ ምላሽ የሰጠ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የእግዚአብሔርን ቃል የሚማርና ተምሮ ደግሞ በተማረው መሠረት የሚመላለስ ሰው ነው።
በብሉይ ኪዳን ሆነ በሐዲስ የምናገኛቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ ቃሉን ለመማርና ለመታዘዝ የሚተጉ ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ፣ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር ለመታዘዝና ለማስተማር ልቡን አዘጋጅቶ ነበርና ጌታም ባርኮ ለበረከት አደረገው ይላል። (ዕዝራ 7፡10)
ሥርዓት ባለው መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል የምናጠናበት ጊዜና መንገድ አለን ወይ? ጌታ ያስተማረንንስ እንታዘዛለን ወይ? ተምሮ መታዘዝ በረከት ነው። ተምሮ አለመታዘዝ ግን መርገም ነው።
እውነተኛ ክርስቲያን ወንጌል ሰምቶ ምላሽ ከሰጠ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት እየተማረ የሚታዘዝ ሰው ነው።
3. እውነተኛ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ሆኖ ጌታን የሚያገለግል ሰው ነው። (የሐዋ. ሥራ 2:42-47)
እውነተኞች ክርስቲያኖች ለሰሙት ወንጌል ተገቢ ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት ይማሩና ይኖሩበት ነበር። በሕብረት ሆነው ደግሞ ጌታን ያገለግሉት ነበር። ከዚህ የምንረዳው ወንጌልን ሰምቶ ተገቢ ምላሽ የሰጠ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት የሚያጠናና የሚታዘዝ እውነተኛ ክርስቲያን ከሌሎች እውነተኞች ክርስቲያኖች ጋር ሆኖ ጌታን ያገለግለዋል።
እውነተኛ ክርስቲያን ከሌሎች እውነተኞች ክርስቲያኖች ጋር ቃሉን በማጥናት፤ እንጀራ በመቁረስ፤ በጸሎት፤ ያለውን በማካፈል፤ በቤትና በእግዚአብሔር ቤት በኅብረት ጌታን በምስጋና የሚያገለግል ሰው ነው።
እውነተኛ ክርስቲያን በጌታና በሰዎች ፊት ከሚኖረው ኑሮና ከሚያሳየው ድርጊታዊ ፍቅር የተነሳ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚስብ ሕይወት ያለው ሰው ነው። ሕይወታችን ሰዎችን ወደ ጌታ የሚስብ ነው ወይስ ሰዎችን ከጌታ የሚያርቅ?
እውነተኛ ክርስቲያን የጌታን ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰበክ ሰምቶ ተገቢ ምላሽ የሰጠ፤ ቃሉን ለመማርና ለመታዘዝ የሚተጋና በኑሮውና በንግግሩ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚስብ ሕይወት ያለው ሰው ነው።
መደምደሚያ
ሕይወታችን ከላይ ባየናቸው ሦስት የእውነተኛ ክርስቲያን ባህሪያት ሲመዘን ምን ይመስል ይሆን?
የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰበክ አልሰማን ከሆነ የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደሚሰበክበት ቤተ ክርስቲያን ሄደን ልንሰማ ያስፈልጋል።
ወንጌል ሰምተን ከሆነ ደግሞ ለሰማነው ወንጌል ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ንስሓ እንግባ።
ተገቢውን ምላሽ ሰጥተን ከሆነ ደግሞ ሥርዓት ባለው መንገድ ቃሉን በመማርና በመታዘዝ እንትጋ። ይህን ካደረግን ጌታን የሚያከብርና ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚስብ ሕይወት ይኖረናል፤ እውነተኞች ክርስቲያኖችም እንሆናለን።
ጌታ እውነተኞች ክርስቲያኖች የመሆን ጥማትና ጉልበት ይስጠን። አሜን።
የከበረውን ከተዋረደው ብትለይ …
በፀሐይ ዓለሙበዓለም ውስጥ የክብር ሥፍራና ደረጃ የሚሰጣቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ለምሁራን የተለየ የክብር ደረጃ እንሰጣቸው ይሆናል፤ ትምህርትም ቢሆን በዓይነቱ የከበረ ነውና። ለባለ ጸጐችም ልዩ ቦታ እንሰጣቸው ይሆናል፤ ሃብት ወይም ገንዘብ ጠቃሚ ነውና።
ሆኖም “የከበረና የተዋረደ” የሚለውን ሃሳብ ልናመሳክር የሚገባው ከሰው የውስጥ ሕይወት አንጻር ነው።
ሰው ከሌላው ፍጡር ይልቅ ልዩና ክቡር ነው። የውስጥ ሕይወቱም የተወሳሰበና ጥልቅ ነው። ሁል ጊዜ ጥያቄ አለው። እውነቱንና ልኩን እንዴት አውቃለሁ? ስሕተቱን እንዴት እለያለሁ? ይላል።
ይህን ጥያቄውን ሰው በራሱ ሃሳብ ተወስኖ በሚመስለው መንገድ ከመለሰው ይስታል። አንድ ምሪት የሚሰጥ ከሰው የተለየ ኃይል ያለው፣ የበላይ ያስፈልገዋል። ያም እግዚአብሔር ከሆነ ብቻ ነው።
ሰው ከዚህ የሕይወት ምንጭ ከሆነ ጌታ ጋር መገናኘቱና ማን መሆኑን መረዳቱ፣ ራሱንም መገንዘቡ ይበጀዋል። እግዚአብሔር ለሚፈልጉት ሁሉ ቅርብና ዕውን ነው። ለሕይወት አቅጣጫና ትርጉም መስጠት ይቻለዋል።
ውሃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ
የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም
ተራቡ፣ ተጠሙም
ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች
በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ
ከመከራቸውም አዳናቸው
ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ
የቀና መንገድን መራቸው። መዝሙር (107)፡ 4-7አዎ፣ እግዚአብሔር ለያንዳንዱ ሰው የቀና ሃሳብና ምሪት አለው። እርሱ ለሕይወት ትክክለኛውን ትርጉምና መፍትሔ ሰጭ ነው። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሕይወቱ ሲገናኝና ሲያያዝ ለምን እንደ ተፈጠረ፣ ወዴት እንደሚሄድ ይረዳል። ስለዚህ እርካታ ሊሰጠው የሚችለውን ትክክለኛ ምሪት ከአምላክ እንዲያገኝ መፈለግና መፍቀድ ይጀምራል።
ሰው ግን የእግዚአብሔርን ምሪት ባያውቅና ባያገኝ እጅግ ይጐዳል። ይስታል። መመዘኛ ስለማይኖረው እውነቱን ከስሕተት መለየት ይሳነዋል። ዕድሜውን በከንቱ ያባክናል። የእግዚአብሔር ምሪት በሌለበት ነገር ውስጥ መማሰን ትርፉ ኪሳራ ነው።
ገንዘብን እንጀራ ላይደለ
የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር
ለምን ትመዝናላችሁ? ኢሳይያስ 55፡ 2ይህን በሚመስል መንገድ እየሄደ የሚባዝነው ሰው እጅግ ብዙ ነው። ለሰው የራሱን ምርጫና ፍላጎቱን ለማድረግ መሮጡ ዋናው ሃሳቡ ነው። ነገር ግን ሊያሳርፈው የሚችለው የአምላክን ምሪት ተከትሎ ልክ የሆነውን ነገር ማድረጉ ነው። የብዙዎች ዐይን ግን ለዚህ ነገር የተከፈተ ሳይሆን የታወረ ነው። ምን ጊዜም ቢሆን ከእግዚአብሔር ሃሳብና ምሪት ውጪ የሆነ ነገር ሁሉ አናሳና ተራ ነው። ሰው ራሱን በጥልቅ የሚያውቅ ፍጥረት አይደለም። ያወቀ ግን ይመስለዋል። የሚመስል ነገር ሁሉ ልክ ነው ማለት አይደለም። የእግዚአብሔር ሃሳቡና መንገዱ ግን ትክክልና ክቡር ነው። ይህን ለመረዳት የከበረውን ከተዋረደው የሚለይ ማስተዋል ያስፈልጋል።
የሰው ሁሉ ድካሙ ወደ ፈቀደው ሃሳብ ማዘንበሉ ነው። ለጊዜው የሚጠቅም መስሎ ስለሚታየውም ነው። ከሚታየው ነገር አልፎ የማይታየውን እውነት የማወቅና የማየት አቅም የለውም። የአሁኑን እንጂ የረጅሙን ዘመን ውጤት መረዳት አይችልም።
ይህች “የእግዚአብሔር ፈቃድ” የምትባል ነገር ልዩና ምሥጢር ናት።
ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ
እግዚአብሔርን መፍራት
የሕይወት ምንጭ ነው። ምሳሌ 14፡ 27ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ያሉት ነገሮች ሁሉ ደግሞ የሞት ያህል ለሕይወት ወጥመድ ናቸው። እግዚአብሔርን ቀረብ ብሎ የለመደው ሰው የፈቃዱን ምሪት ለይቶ ያውቃል። አንዳንዴ የራሱ ፈቃድና ሃሳብ አይሎ ሲታገለው እንኳ ጥርት ያለው የአምላኩ ምሪት ወለል ይልለትና መለስ ያደርገዋል። እንደዚህ ያለው ሰው “የከበረውን ከተዋረደው” ለይቶ ያውቃል ማለት ነው።
ብትመለስ እመልስሃለሁ
በፊቴም ትቆማለህ
የከበረውን ከተዋረደው ብትለይ
እንደ አፌ ትሆናለህ። ኤርምያስ 15፡ 19ስለዚህ ለሰው ሕይወት ልኩ በእግዚአብሔር ሃሳብና ፈቃድ ውስጥ መመራቱ ብቻ ነው። የተሳተች ክቡር የአምላክ ፈቃድ ግን ከተሳተች በኋላ አትስተካከልም።
ዕቃ ያለ ግጣሙ አይስማማም፤ ልብስም የሚያምረው በየፈርጁ ሲለበስ ነው። ሰውም የሚያምርበት በቦታው ሲሆን ነው፤ ቦታው ደግሞ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ መሆን ነው።
የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል
ከመከራም ሥጋት ያርፋል። ምሳሌ 1፡ 33የእግዚአብሔር መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው። ምሳሌ 10፡ 29
የእግዚአብሔር በረከት ባለ ጠጋ ታደርጋለች
ኅዘንንም ከርስዋ ጋር አይጨምርም። ምሳሌ 10፡ 22እግዚአብሔር በሥራው ፍጹም ነው። አደራረጉም ግሩም ነው፤ በዚያም ውስጥ ፀፀት የለበትም።
ሞት ፍጻሜ ነው ጅማሬ?
በምትኩ አዲሱክፍል አንድ
መግቢያ
ሞት ፍጻሜ ነው ጅማሬ? የሚለው የቆየና የሰውን ልጅ ያነጋገረ ጥያቄ ነው። ሞት ፍጻሜ ነው የሚሉ አሉ:: ጅማሬ ነው የሚሉም አሉ። የማናቸው ነው ልኩ? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ የሕይወታችንን ዓይነትና አቅጣጫ በከፊልም ቢሆን ይገልጻል፣ ይወስናል። አንደኛው “እንብላ፣ እንጠጣ፣ ነገ እንሞታለን” የሚል አስተሳሰብ ይኖረዋል። ሌላኛው “እንብላ፣ እንጠጣ፣ ነገ እንሞታለን፤ … ግን እንጠየቅበታለን“ ይላል። ከሁለቱም ወገን ያልሆነው ደግሞ “ከሞትኩ በኋላ ለሚሆነው እኔ ምን አሳሰበኝ? … ሲደርስ አስብበታለሁ” እያለ በቀጠሮ ያቆየዋል።
እያንዳንዱ ትውልድ በበራለት መጠን የሞትን ምሥጢር ለመረዳት ያላቋረጠ ጥረት አድርጓል። የጥንት ግብጻውያን ለምሳሌ፣ ሞትን ረጅም ጉዞ ከመሄድ ጋር ያመሳስሉት ነበር። ስለዚህም ለሟች ስንቅ ይሰንቁለታል፤ ሰውነቱ እንዳይፈርስ በልዩ ቅመም ይገንዙና ጓዝ ንብረቱን አስይዘው ይሸኙታል። በዚህ አድራጐታቸውም ዘላለማዊነትን እንደሚቀዳጁ ያስባሉ። ሟች በሌላ ተመስሎ ይመለሳል የሚል እምነትም ነበራቸው። ግሪኰች ደግሞ ሰው የማይሞት ነፍስ አለው ይሉ ነበር። አይሁድ፦ ዘር በመተካቱ፣ በመልካም ስሙና ግብሩ ሰው ለዘላለም የሚተርፍ መታሰቢያን ያገኛል ይላሉ። በአንጻሩ፦ ክርስቲያኖች ሰው ከሞተ በኋላ ሞትና ዘመን የማይገዛውን አካልና ሕይወት በትንሣኤ ይቀዳጃል፤ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወቱም በፈጠረው አምላክ ፊት መልስ ይሰጥበታል ብለው ያምናሉ።
ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት፣ ከእርሱ በኋላም ፍርድ (ተመድቦባቸውዋል) … መልካም ቢሆን ክፉ እንዳደረገ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና … እንግዲያስ፣ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” (ዕብራውያን 927-28፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 510፤ ሮሜ 1412)።
ወደድንም ጠላን የሞት ጥያቄ ሰው ሁሉ በግልና በጋራ መልስ ሊሰጥበት የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው። እንግዲያስ፣ ምን መልስ ይዘሃል? እርግጠኛ መልስ ይዘሃል? ከሁሉ በፊት ጥያቄ ሊሆን የሚገባው ይኸ ነው።
ሞት
ስለ ሞት ያለን አመለካከት ኑሮአችንን ብቻ ሳይሆን ከሌሎችና ከአካባቢአችን ጋር ያለንን ግንኙነት ይወስነዋል ብለናል። ስለ ሞት ያለን መረዳት በክሕደትና በቀልድ ላይ የተመሠረተ ከሆነ ለራሳችን ሕይወት ሆነ ለሌሎች ያለን አክብሮት እንደዚሁ ያነሰ ይሆናል። ከራሱ አልፎ ለሌላው መልካም ቅርስ መተው ወንጀል የሚመስለው ሰው አለ። “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” የሚለው አባባል እንዲያው በአህያ ይላከካል እንጂ ለአንዳንዱስ የሕይወቱ መመሪያ ነው! ለእንዲህ ዓይነቱ ሰው ሞት አፋፍ ደርሶ መመለስ ካልሆነ በስተቀር ጥሩ መካሪ አይገኝለትም። ከልብ ድካም፣ ከከባድ አደጋ፣ ከወህኒ እሥራት የተረፉ ሰዎች ወይም የሞት ገመድ አንገታቸው ላይ የገባላቸው አኳኋናቸው ከቀድሞው በጣሙን የሚቀየረው ለዚህ ነው። እያንዳንዷ ትንፋሽ የግዜር ስጦታ እንጂ የሰው ችሎታ እንዳልሆነች ወደ መረዳት ይደርሳሉ። የወዳጅ ቀርቶ የመንገደኛው ሰላምታ፣ የወፉ ጫጫታ፣ የማታ ጀንበር፣ የጧት ጮራ፣ ቡና ተቆልቶ ሲወቀጥ፣ ቁራሽ እንጀራ በድቁስ ከባልንጀራ ጋር መቁረስ፣ ልጆች መስክ ላይ ባዶ እግራቸውን ሲጫወቱና ሲሳሳቁ፣ ቁጭ ብሎ ማውራቱ፣ ሲያስገመግም ሰማዩ፣ ቀድሞ እንደ ቀላል ይታዩ የነበሩ ነገሮች አሁን ልዩ ጣዕምና ትርጉም ይሰጣሉ። “እንዴት አደርክ፣ እንዴት አመሸሽ” ያምራል፣ ይናፍቃል።
የአገራችን የተማረው ክፍል ግን ከሞትና ከረጅም ዘመን ሐዘንና ስደት ጋር እየኖረም፣ እርስ በርሱ ባለው ግኑኝነት ገና ጠቃሚ ትምህርት የቀሰመ አይመስልም። ለምን ይሆን?
የሞትን ኃይል መገንዘብ የሥልጣኔ በር ከፋች እንደሆነ ይነገራል። የሞትን ኃይል ለማክሸፍና ለማዘግየት የሚደረገው ጥረት እንደዚሁ ለተለያዩ ሕክምና ግኝቶች ምክንያት ሆኗል። ይህ ግኝት እርጅናን ለማዘግየት የሚደረገውን ሙከራ ይጨምራል። ሰዎች የተወሰነላቸውን ዘመን በእርጅናና ኋላም በሞት ሳይቀሙ በፊት የተቻላቸውን ያህል ሊደሰቱበትና መታሰቢያ ሊያገኙ ይጥራሉ፣ ይፍጨረጨራሉ። የአንዳንዶች መታሰቢያ ሞትን በማራባት ይሆናል። ባጭሩ ግን፣ ሞት ፍጻሜ ነው የሚሉ ሞት ጅማሬ ነው ከሚሉት የተለየ አመለካከት ይኖራቸዋል ማለት ነው።
የዕልቂት ዘመን ደግሞ የሚያሳድረው አስተሳሰብ አለ። የአብዮተኞች ሽብር “ዛሬ ውዬ መግባቴን እንጃልኝ” እስከ ማለት አድርሶ ነበር። በአገራችን የተዛመተው የኤይድስ በሽታም እንዲሁ ስለ ሞት አጽንተን እንድናስብ አድርጓል። ከ1980 እስከ 1984 የተደረገ አንድ ጥናት በ 5 እና 14 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉት ይልቅ ከ 25 እስከ 39 ባሉቱ ላይ ሞት እንደበረታ ያስረዳል። በነዚሁ ዓመታት ውስጥ በ 35 እና 39 ዕድሜ ክልል ባሉት ውስጥ የሟች ቁጥር በአምስት እጥፍ አድጓል። የዛሬ ሠላሳና አርባ ዓመት ሞት ለአዛውንትና ለጦረኞች ብቻ እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ዛሬ ግን ወላጅ ወልዶ አሳድጐ አስታምሞ ቀባሪ ሆኗል። ለዘላለም የሚኖር የሚመስለው የነበረ ወጣት ነገሩ ተገልብጦበታል። ያገኘውን ቶሎ ቶሎ ብሎ ተደስቶ ማለፍን አማራጭ የሌለው ቁርጠኛ አሳቡ አድርጐታል። የዚህ ትውልድ ወደ ውጭ ለመጉረፍ አንዱ ምክንያት ይኸ ይሆን? በቃሉና በያዘው የማይጸናውስ ለምን ይሆን?!
ሞት አይቀርም
“ሞት አይቀርም፣ ስም አይቀበርም”፣ “ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከመሬት”፣ “ሁሉ ሟች ነው” ማለት የተለመደ አነጋገር ነው። ተናጋሪው ግን በአብዛኛው ራሱን በአባባሉ ውስጥ ጨምሮ አይመለከትም። ሟች ሁልጊዜ ወዲያ ማዶ ያለ ሌላኛው ሰው ነው። ለዚህም ነው በጦርነት መቶ ሺ ሰው አለቀ ሲባል ከወሬነት የማያልፈው፤ ክብደቱን መመዘን የሚያዳግተው። ተራ ሲደርሰን ግን ለመታዘብ ፋታም አይሰጠንም።
“እኔም እኰ ሟች ነኝ” ብሎ ማሰብ ቢችል አለመተዛዘንና መናቆር በቀነሰ። የሕይወትን አጭርነት በመገንዘብ ውስጥ በጐ ማድረግ በጨመረ። አልለመድ ያለ እንደ ሞት ምንም የለም። ሁሌ አዲስ ነው። ሰው ለሞት እንዳልተፈጠረ፣ ዘላለማዊ እንደ ሆነ ይኸ አንዱ ማስረጃ አይደለም ወይ? በሥራ ብዛት፣ በጨዋታ ብዛት፣ በመብላትና በመጠጣት ብዛት የሞትን አሳብ ለመርሣት ይጥራል፤ ግን ዕረፍት አያገኝም። ረጋ ማለት መልካም ነው።
ለጥቂቶች ሕይወት ካለመኖር ወደ አለመኖር የሚደረግ ጉዞ ነው። እነዚህ የሚያስቡት አሁን የሚገኙበት ሁኔታ የሚያስገኘውን ጥቅም ብቻ ይሆናል። ቅድም እንዳልነው ስለ ሞትና ከሞት በኋላ ስለሚመጣው መቸጋገር ሥራ መፍታት እንደሆነ ይገምታሉ። ለብዙዎች ግን ጉዞው ከሕይወት ወደ ሕይወት ነው። እርግጥ ዝርዝሩና አተረጓጐሙ ይለያያል።
· ለሒንዱ እምነት ተከታዮች ለምሳሌ፣ ሕይወት ከባሕር እንደ ወጣ ጠብታ ነው፤ ሞት ደግሞ ጠብታው ወደ ወጣበት ባሕር መመለሱ ነው።
· ለቡዲስት እምነት ተከታዮች ሕይወት የሚጠፋ ሻማ ብርሃን ነው፤ ከዚህ ሕይወት ወዲያ የሚቀር ነገር አይኖርም ይላሉ።
· በክርስቶስ ለሚያምኑ ሕይወት ከሕይወት የተገኘ ነው። ሰው ከዘላለማዊነት ለዘላለማዊነት የተሠራ ፍጡር ነው። ኢየሱስ አልዓዛር መቃብር አጠገብ ቆሞ ያነባው አልዓዛርን ስለሚወደው ብቻ ሳይሆን ሞት ያልተገባውን ሥልጣን ማግኘቱን በማሰብ ነው፤ ሰውን ከሕይወት አፈናቅሎ ማንገላታቱን በማሰብ ነው። ያንን የቀደመውን የጸጋ ክብር በሞቱና በትንሣኤው ኃይል ሊነጥቅ ቀንቶ ነው። (ዮሐንስ ወንጌል 11)። ሞት በመሠረቱ ከአምላክ ርቆ የመኖር ውጤት ወይም የኃጢአት ውጤት ነው። በክርስቶስ በኩል ዕርቅ ስለ ተደረገ፣ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የጠፋ ልጅ ወደ ወላጁ እንደሚመለስ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ ለዘላለም መኖር ይቻላል ይላሉ።
እያንዳንዱ ኅብረተሰብ በጠቢባኑ፣ በባለ ቅኔዎቹ በኩልና እንደ ደረሰበት የባሕል ዕድገትና ለውጥ የሞትን አኳኋን ለመታዘብ ጥሯል። ግሪኰች ለምሳሌ፣ ሞት የእንቅልፍ ታናሽ ነው ይሉናል። እንግሊዛዊያኑ ድራይደንና ኪትስ (በ17ኛውና በ19ኝኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኖረው የሞቱ) ከግሪኰች ተቀብለው ሞትን “ተኝቶ አለመንቃት” ነው ብለውታል። ይህን እንኳ ያገራችንም ሰው አያጣውም። ሩሲያዊው ቶልስቶይ ደግሞ “ሕይወት እንደ አረፋ የሚሟሟ ከሆነ ይህ ሁሉ ትግልና መንገላታት ታዲያ ምን ትርጉም ይኖረዋል?” ሲል ለሰው ሁሉ የሚተርፍ ጥያቄ ጠይቋል።
የኛው ባለ ቅኔ ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ “የት አባቱ! ሞትም ይሙት!” በተሰኘው ግጥሙ (1963)፦
እባካችሁ ዘመዶቼ፣ ስሞት ሞትም አብሮኝ ይሙት ...
በሙሾ ግነን አትበሉት ...
በዳንኪራችሁ ውገሩት
ከአጥንቴ በታች ቅበሩት። ብሏል።
ሞት ዘመድ አይሆንም፤ ሞት መሸነፍ ያለበት ኃይል ነው ማለቱ ይሆን? ወይስ ፍጻሜ ስለሆነ ቋሚው አይድከም ማለቱ ነው?
ትንሣኤም አይቀርም
ጳውሎስ ሐዋርያው በግሪክና በአይሁድ ባሕል የሠለጠነ የሕግ ምሑር ነበረ። የሞትን ምሥጢር ለመፍታት የተደረገውን ያልተሳካ ጥረት ታዝቧል። ሞት የኃጢአት ውጤት መሆኑን ተረድቷል። ሁለት ሕግ ማለትም የሞት ሕግና የሕይወት ሕግ በሰዎችና በዓለም ውስጥ እንደሚሠራም ተረድቷል። “መልካም ነገር የማድረግ ፍላጐት ቢኖረኝም ያንን መልካም ነገር የማድረግ ችሎታ የለኝም … የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁ … የኃጢአት ሕግ እስረኛ የሚያደርገኝ ሌላ ሕግ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ መኖሩን አያለሁ … ወደ ሞት ከሚወስደኝ ከዚህ ጐስቋላ ሰውነትስ ማን ያድነኛል” (ሮሜ 77-25)? በሌላ ሥፍራ ደግሞ እንዲህ የሚል ተጽፏል፦ “ሥጋና ደም ያላቸው ሰዎች እንደ መሆናቸው መጠን፣ ኢየሱስም እንደ እነርሱ ሰው ሆነ፤ ይህን ያደረገውም በሞቱ አማካይነት በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስን ለመሻር ነው። እንዲሁም ሞትን በመፍራት ምክንያት ዕድሜ ልካቸውን በባርነት ይገዙ የነበሩትን ለመዋጀት ነው … ” (ዕብራውያን 214-15)።
የናዝሬቱ ኢየሱስ ከሙታን ተነስቶ ከተገለጠለት በኋላ፣ ጳውሎስ የሞት ሥልጣን እንደ ተሻረ ማወጅ ጀመረ። “ሞት የመጣው በአንዱ ሰው በአዳም (ባለ መታዘዙ) ምክንያት እንደሆነ፣ ከሞት መነሣትም የሚመጣው በአንዱ ሰው በክርስቶስ (መታዘዝ) ምክንያት ነው … የሞቱ ሰዎች የሚነሡት እንዴት ነው? ከሞት ሲነሡ የሚኖራቸው አካልስ ምን ዓይነት ነው? … አንተ ሞኝ! የምትዘራው እህል ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም፤ አንተ ስትዘራም ስንዴ ወይም ሌላ እህል ብቻ ትዘራለህ እንጂ በኋላ የሚበቅለውን ተክል አይደለም። እግዚአብሔር ግን ለዘሩ እንደ ፈለገ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር ልዩ ልዩ አካል ይሰጠዋል … እነሆ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ… ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ፣ በዚያን ጊዜ፦
ሞት ድል በመነሳት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፣ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፣ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን (1ኛ ቆሮንቶስ 1521-22፣ 35-38፣ 51-57)።
ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ በስተርጅና በተሰጠው የዓለም ፍጻሜ ራእይ እንዲህ ይላል፦
“ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፤ … ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ … እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፣ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኅዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” (ራእይ 2013-14፤ 213-4)።
ድንቅ ነው! ድንቅ ነው! ለዘላለም አልፈታ ብሎ ትውልድን ሲያንገላታ የቆየ ምሥጢር እነሆ በክርስቶስ ተፈትቷል! አለማወቅ ወይም አለመታዘዝ ካልሆነ በስተቀር ከንግዲህ መንገላታት አያሻም ማለት ነው። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ይላል ኢየሱስ። “የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፣ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” ይላል ከሙታን የተነሣው። (ዮሐንስ 11፡ 25-26)። “አትፍራ፣ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ” ይላል። ስለ ሞት ምንነት አስረግጦ መናገር የሚችል የሞትን ጣር ቀምሶ ከሙታን የተነሣው ብቻ ነው! ፈላስፎችን፣ ሃይማኖተኞችን፣ ተራውን ሰው ሳይቀር በፍርሃት ምሥጢር አስሮ ያስገበረውን ድል ያደረገ ብቻ ነው! ይህን ያደረገ ከኢየሱስ በስተቀረ ማንም የለም።
ይቀጥላል …
ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል …
በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።
መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ።
እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም። እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።
የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ። የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ።
እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።
በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።
በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው።
እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ …
ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም … ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤
የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም … ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም … መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።
በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤
በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።
ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ
ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።
ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል…የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና … ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል።
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥
የሚያሳጣኝም የለም።
በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤
በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል።
ነፍሴን መለሳት፥
ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ።
በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ
አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤
በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል።
በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ
በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥
ጽዋዬም የተረፈ ነው።
ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥
በእግዚአሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።
ራእይ ሲደበዝዝ
በፀሐይ ዓለሙ
“የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋል … ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም። በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና” (ዕብራውያን 1036፣ 139)::
ባለ ብዙ ተስፋ ባለ ብዙ ራእይ የነበሩ ሰዎች ዛሬም አሉ። አጀማመራቸው ያማረና የሚቀጥል የሚመስል፣ ወቅቶችና ሁኔታዎች መፈራረቅ ሲጀምሩ እንደ ማመንታት እያሉ ግራ በመጋባት ላይ ያሉ ጥቂት አይደሉም።
ለመጠራታቸው ማስረጃ የሚሆን የሕይወታቸው ምስክርነትና ጸጋቸው ይናገራል። ግን እየቆዩ ከዋናው ዓላማቸው ሸርተት ብለው ከማይመስለውና ከማይመቸው አኗኗር ጋር ተደባልቀውና ተመሳስለው ለመኖር የሚያደርጉት ጥረት ክብደት ነስቷቸው ተራ ሰውነት ይዘው ይገኛሉ።
ትልቁ ሰው እንደ ትንሽ፣ ትንሹም ሰው እንደ ትልቅ ያልሆነውን ለመሆን ሲጥር፣ ውሸቱም እንደ ልክ ተቆጥሮ የሕይወት መመሪያ ሆኖ ሲጠናከር፣ ውስልትናም እንደ ክብር ተጐናጽፈውት ሲሠለጥን፣ ራእዩ ገደል ገብቷል እንጂ የት አለ? ባለ ራእዩስ እንደ ሁኔታው ከተቀየረ ጽኑ ምስክርነቱ የት አለ? ገና ጨቅላዎቹስ ይህን የሳተ መንገድ ተከትለውት ለወደ ፊቱ እንዴት ያሉ ሆነው ያድጉ?!
ታዲያ እውነተኞች ሲጠፉ፣ ያሉትም ከማይመስል ጋር ሲመሳሰሉ ወደ ፊት የምድሯ ሁኔታ ምን ይመስል ይሆን?
ትዳር ዝብርቅርቁ ወጥቷል። ጥንቃቄና ማስተዋል የሚያስፈልገው ይኼ ዋና ነገር እንደ ቀላል ተቆጥሮ የስብከቱም ዓይነት ለዚሁ እንደሚያመች ሆኖ ቀርቧል። አግቢም ተጋቢም፣ መራጭ ተመራጭም በዓይነታቸው አልተገናኙም። ነገሩ እንደ መደብር ዕቃ የሚሸመት ሆኗል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የሚገርመው አገልጋዮች ተሳታፊ ሆነው መሰለፋቸው ነው።
ትዳር ለመጀመር ይሁን ሌላ “የእግዚአብሔር ፈቃድና ምሪት” የሚባለው በውሸት ትንቢት ተተክቶ የሩቅ ምሥራቅ ጠቢባንን የመራቸውን ልዩ ኮከብ ያህል ታምኖበታል። ውሎ አድሮ ግን ትዳሩም ትዳር ሳይሆን ቤቱም ጣራውም ተሸንቁሮ ዝናብ እንደሚያንጠባጥብ ያህል የማያቋርጥ አሳርና መከራ እያስከተለ፦ ክርስትና ይኼ ነው እንዴ? አሰኝቷል።
አንድ ባለ ታክሲ ተሳፋሪው ሲያስቸግረው፦ “ውረድልኝ … ባይበላ፣ ባይጠጣስ” እንዳለ ሁሉ፦ ባይገባስ? “የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፣ ጌታ ተናግሮናል” ባይባልስ? ይልቅ እንዲሁ ስለ ፈለግሁ በራሴ ወስኜ ገባሁበት ቢባል አይሻልም?
ውሸት የሆነ ነገር አይበጅም፤ አያዋጣም። ኋላ ነገሩ ዕርቃኑን መቅረቱ አይቀርም። ይታወቃል። ያኔ ቀና ብሎ መሄድ የለም፤ እፍረት ብቻ ነው።
ያ ባለ ራእይስ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው? ጌታው ሹመቱን ለሌላ ለታመነ ሰው ይሰጠዋል። ምን ጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር ጥቂቶች ይሁኑ እንጂ ፈቃዱን በታማኝነት የሚያገለግሉ አያጣም።
ላስተዋለው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክርስትና መልኩ ተለውጧል። አመጽ ከመብዛቱ የተነሳ ራእይ ሁሉ ደብዝዟል። እውነት በውሸት ኃይል ተሰልስላ ልትበጠስ የደረሰች ትመስላለች። ያልተመሳሰሉ ጥቂት እውነተኞች ቢኖሩም ድምጻቸውን አጥፍተው ግራ በመጋባት ጭጭ ብለዋል! እውነቱን ጮኽ ብሎ ለማሰማት የሚጥር የለም!!
ሌሎች አመጽን ለማጠናከር ሲሯሯጡና ሲያያዙ የብርሃን ልጆች ግን በርቀት ተበታትነው ቆመዋል። ይህን ሁሉ ውዥንብር ማን ያስቁም? ማንስ ይጠራ?
አንዲት በእግዚአብሔር ኃይል ወኔ የተዘጋጀች ወንጭፍና ጠጠር ድንጋይ ጠፋችን? ማንስ ይወርውራት? እውነትን የተረዳ የሚመስለው ሁሉ ልብ አጥቷል!! ማን ይጠራ? መጪው ዘመን የሚወልደው አንድ ኃያል ጀግና ብቅ ይል ይሆን?
የወሩ ምንባብ
ምሳሌ 8፡ 32-36
አሁንም ልጆቼ ሆይ ስሙኝ
መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው
ትምህርቴን ስሙ፣ ጠቢባንም ሁኑ፣ ቸል አትበሉትም
የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው
ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ
የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ
እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና
እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጐዳል
የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወዳሉ
ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው (ክፍል 2)
በገ/እግዚአብሄር ካሕሳይካለፈው የቀጠለ…
ባለፈው ጊዜ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት 1. የጌታ ትእዛዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል 2. ራሳችን የጌታ ደቀ መዛሙርት ልንሆን ያስፈልጋል 3. ወደ አሕዛብ ሁሉ መሄድ ያስፈልጋል ብለናል። ቀሪውን ዛሬ እንመለከታለን፦
4. ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ያመኑትን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ ያስፈልጋል።
“በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 28፡ 19-20)
በአሁኑ ዘመን ስለ ጥምቀት በተለያዩ የእምነት ክፍሎች የተለያየ መረዳት ቢኖርም ጥምቀት ከጌታ ትእዛዞች አንዱ ነው። በሌላ ሥፍራም ጌታ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፣ ያላመነ ግን ይፈረድበታል” ሲል አስተምሯል። (ማርቆስ 16፡ 16)
የአዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናትም ጌታ ባዘዘው መሠረት ያመኑትን ያጠምቁ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 2፡ 41)። ዛሬም ቢሆን ያመኑት ጌታ ባዘዘው መሠረት በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ አለባቸው፣ ምክንያቱም ጥምቀት ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር የተሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ ነውና።
5. ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ጌታ ያዘዘውን ሁሉ ማስተማር ያስፈልጋል።
“ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 18፡ 19-20)
ደቀ መዛሙርት ለማፍራት መሄድ፣ መስበክ፣ ማመን፣ ማጥመቅ ብቻ በቂ አይደለም። አንድ ሰው ወንጌልን ሰምቶ ንስሓ ከገባና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምኖ ከተጠመቀ በኋላ ጌታ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቅ መማር አለበት።
በዘመናችን ወንጌል በመስበክ የተሰማሩ ብዙ ወገኖች አሉ፤ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትም ዋና ተግባራቸውን ወንጌልን መስበክ ብቻ አድርገዋል። በስብከት የሚያገለግሉ አገልጋዮች አሏቸው። በማስተማር የሚያገለግሉ አስተማሪዎች ግን የሏቸውም፤ ቢኖሯቸውም የታወቀ አይደለም። በሥርዓትና በተያያዘ መልኩ አያስተምሩም። በተገኘው ቀዳዳ ከስብከት ያልተለየ ትምህርት ብቻ መስጠት ነው የሚችሉ። ጌታ ግን ያዘዝኋችሁን በከፊል ሳይሆን ሁሉን እንዲያውቁ፣ አውቀው እንዲጠብቁ፣ እንዲታዘዙና ሥራ ላይ እንዲያውሉት አስተምሯቸው ነው ያለው።
ጌታ ያዘዘውን ሁሉ አውቆ ማስተማር ቀላል አይደለም። መጀመሪያ ራሳችን ተማሪዎች ሆነን በጌታ እግር ሥር ሆነን ጌታ ያዘዘውን መማርና በተግባር ማዋል ይጠበቅብናል።
ይህን ስንል ሁላችንም ሥራችንን ትተን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት መግባት አለብን ማለት አይደለም። ጌታ የሰጠንን ሥራችንን እየሠራንም ቢሆን ለጌታ ጊዜ መስጠት አለብን ማለት እንጂ።
ሰውን እንዲያውቅ ማስተማር በራሱ ቀላል ተግባር አይደለም። ጌታ ግን ያዘዘን እንዲያውቁ ብቻ ማስተማር ሳይሆን አውቀው እንዲታዘዙ አስተምሩ ብሎ ነው። ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም ማለት ነው። ሰው አውቆ ሲታዘዝ ነው ደቀ መዝሙር የሚሆነው። አውቆ አለመታዘዝ ከአለማወቅ የባሰ ነው። በዚህ ዘመን በአንዳንድ ሥፍራ መታዘዝ የጐደለው ዕውቀት ሲበዛ፣ በሌላ ሥፍራ ደግሞ ዕውቀት የሌለው መታዘዝ በዝቶ ይታያል። ጌታ ያዘዘው ግን ትዕዛዛቱን ሁሉ መሠረት ያደረገ መታዘዝን ነው።
የጌታ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ጌታ ያዘዘውን ሁሉ እንዲታዘዙና እንዲጠብቁ ማስተማር ያስፈልጋል።
6. ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ስንሰማራ ጌታ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር እንደ ሆነ ማወቅ ያስፈልጋል።
“እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 28፡ 20)
የጌታ እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆን ቀላል ነገር አይደለም። በእርኩሰት በተሞላች ዓለም፣ ደካማ የሆነ ሥጋ ተሸክሞ የጌታ ኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆን ከባድ ነው። የጌታ ደቀ መዝሙር ከመሆን አልፎ እውነተኛ የጌታ ደቀ መዛሙርት ማፍራት እጅግ በጣም ከባድ ነው። ታላቅ መስዋእትነት ብዙ ፍቅርና ትዕግስት የሚጠይቅ ኃላፊነት ነው። ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ መስበክ፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ ጌታ ያዘዘውን ሁሉ እንዲታዘዙና እንዲጠብቁ ማስተማር ቀላል ኃላፊነት አይደለም።
ጌታም የሰጠንን ኃላፊነት ክብደት ስላወቀና በራሳችንም ልንወጣው እንደማንችል ስለ ተገነዘበ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ በማለት ታላቅ ተስፋ ሰጥቶናል። ጌታ ሊረዳን፣ ሊመራንና ሊያስችለን ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው።
በእርሱ ታምነን፣ እርሱን ሰምተን፣ እርሱን ታዝዘን የምንወጣና የምንገባ ከሆንን ያዘዘንን ለመፈጸም ያስችለናል። የእርሱ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እንሆናለን። በእውነት የእርሱ ደቀ መዛሙርት የሆኑትን እናፈራለ። በዚህም ትርጉም ያለው ሕይወት ይታይብናል።
መደምደሚያ
ደቀ መዛሙርት ማፍራት ከጌታ የተሰጠን ትእዛዝ መሆኑንና ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከተመለከትን በኋላ ጸሎታችን ምን ሊሆን ይገባል? ጥያቄአችንስ ምን ሊሆን ይገባል? ጌታ በልባችን ያስቀመጠውን ጸሎት ከልባችን ወደ ለእርሱ እናቅርብ።
ጌታ ይህችን አጭር ጽሑፍ እንዲጠቀምበት ጸሎቴ ነው።
የውይይት ጥያቄ
1. ሰባኪና አስተማሪን ምን ይለያቸዋል?
2. ባለንበት ቤተ ክርስቲያን የማስተማር ጸጋ የተሰጣቸው አሉ? ይህንስ አገልግሎት አክብረው የሚጠቀሙ አሉ?
3. በማስተማር የሚያገለግሉ ጥቂት መሆናቸው ማስተማር የሚጠይቀውን ትዕግስትና ጥልቅ ግንዛቤ ለመቀበል ካለመፍቀድ የተነሳ ይሆን? አኗኗራችን የሩጫ በመሆኑ ይሆን? የማንበብና የማጥናት ልምድ ከማጣት ይሆን? ከምንገኝበት ሁኔታ ጋር ለማገናዘብ ካለመቻል የተነሳ ይሆን?
4. “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፣ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ሲል ምን ማለቱ ነው? (ዮሐንስ 8፡ 31-32)
የወንጌል ስርጭትና እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ (ክፍል 2)
በምትኩ አዲሱክፍል ሁለት፦ የተያያዝነው ጉዞ
በክፍል አንድ እንዳሳሰብነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በጐ ሥራዎች እንዳልተሠሩ ለማስመሰል አይደለም። ይልቅ በወንጌል ስርጭት ሳቢያ የተከሰቱ አዝማሚያዎችን ለመጠቆምና እንደ ሁኔታው መፍትሔዎችን ለማቀድ እንዲያስችል ነው። አዝማሚያ ውሎ ሲያድር መደበኛ ይሆናል፤ ልክ እንደ ሆነ መታሰብ ይጀምራል፤ ማረሙም እንደ ነውር ይቆጠራል። የዚህ ጽሑፍ ሌላኛው ዓላማ የጥንቱን የሐዋርያትን ልማድ ለማበረታታት ነው (የሐዋርያት ሥራ 242፣ 62-4)። ይህም ቃለ እግዚአብሔርን ገልጦ ማንበብና ማሰላሰልን፣ መጸለይና በታማኝነት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን መጐናጸፍና ጠቃሚ ሰው መሆንን ይጨምራል።
1. አዝማሚያው ምን ይመስላል?
ላመኑና ላላመኑ ብዙሃን የወንጌል ዕውቀት ማሰራጫ ዓይነተኛ መንገዱ በዝማሬ ስለሆነ ይህንኑ እስቲ አንቃኝ። በምዕራቡ ዓለም እንደተለመደው፣ በአገራችንም የዓለም ድምጻዊ በተቀናበረ ሙዚቃ “የጽዮንን ዝማሬ” ቀምሮ ለገበያ ቢያቀርብ ምን እንል ይሆን? “ታሽገው የሚሸጡ” ዝማሬዎችን ለማቅረብ ቴክኒኩ ቢያስችልም አሁን የሚጠበቀው ተቃውሞ እንዳያስነሳ ምቹ ጊዜ ነው። ቀስ በቀስ “ለጌታ ክብር ነው” በሚል ሰበብ ድንበሩ እየደበዘዘና እየተደፈረ ነው። የገበያ ውድድርና ሥልጣን ማንንም ይማርካል። ገበያና ገንዘብ ከጌታ ቤት ሥራ ጋር በማይመች አኳኃን ሲጣመሩ ግን ነገር መበላሸቱ አይቀርም። የዘማሪው ልብስና ቁመና ሳይቀር ለሺያጭ እንደሚቀርብ ዕቃ ትኩረት ይሰጠዋል ማለት ነው። ለምስል መስገድ ሲባል አዝማሚያው ይኸ እንደሆነስ?
“ሌዋዊው” ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውጭ ቆሞ እያዜመ እንዳይሆን እንስጋ። የማረኩት የሚጠይቁትን ዝማሬ ሲዘምር እንዳይገኝ። በአገልግሎት ስም ጸጋውን በዝናና በገንዘብ እየቸበቸበ እንዳይሆን። ለቤተ መቅደስ ሥርዓት ይገዛል? ወይስ “በአዲስ ራእይ” አሳብቦ ሙዚቃውን ይዞ ይኮበልላል? ሙዚቃው የተመረጠ ወንበር የሚናጠቅበት መሣሪያው ነው? የጌታና ለጌታ መሆኑ ቀርቶ የግልና ለግል መሆን ጀምሮ ይሆን? እንግዲህ ከዚህ የተነሳ ነው አንዳንዱን መዝሙር ከአንድ ጊዜ በላይ መስማት የሚያቅተው። በጸሎት ሳይሆን በሙዚቃ ኪነ-ጥበብ ብቻ ስለ ተቀመመ ለጸሎት አይጋብዝም። ካላጸለየና የእግዚአብሔርን ህልውና ካላስታወቀ ዝማሬ ከመዝናኛነት አላለፈም ማለት ነው። የመንፈሳዊ መዝሙሮች መሠረታዊ ግብ የእግዚአብሔርን ህልውናና ክብር ማስታወቅና የሰሚውን አዕምሮና መንፈስ አንፆ ወደ አምላኩ ማቅናት ነው።
የሙዚቃውን ቅኝት በተመለከተ አንዳንዴ በዓለም ያሉትን ለመሳብ የተፈጠረ ዘዴ እንደሆነ ይደመጣል። እርግጥ እግዚአብሔርን መወሰን አንችልም፤ ከልብ የተሰጠውን ያን አይንቅምና፤ ያንኑ ለማዳን ይጠቀምበታልና። ዘመኑ የሚጠይቀው አሠራር አይኖርም ማለት አንችልም። ቅርሳችንን ግን ችላ ብንል የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ታሪክ ማቃለል ይሆንብናል። ያጐድልብናል። ሰዎችን የምናቀርብበት መንገድ ለሁሉም አንድ ወጥ መሆን እንደሌለበት ቢታወቅም፣ ክብር የሌለበት የሰው ብልሃት ብቻ ሆኖ እንዳይገኝ መስጋት ይኖርብናል። የሙዚቃን መንፈሳዊ ጥራት ለመለየት የረቀቀ የሙዚቃ ዕውቀት አያሻም። መንፈሳቸው ለሚለይ የሙዚቃ ስልትም እንኳ ይህን አይሰውርባቸውምና። መጽሐፍ እንደሚል፦ “መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና፣ ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈስ በኩል ገለጠው… መንፈሳዊ ሰው… ሁሉን ይመረምራል፣ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም” (1ኛ ቆሮንቶስ 210፣15)።
በዚሁ በአሜሪካ ለምሳሌ፣ ከነባር ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የተፈናቀሉትንና ርቀው የኖሩትን ላለማስቀየም ሲባል መስቀል-አልባ አምልኰ ቤቶችን ማነጽ ተጀምሯል። መስቀል የሥቃይ፣ የመስዋእትነትና የሰው ኃጢአት ውጤት መግለጫ መሆኑን ማስታወስ የማይፈልጉ በዝተዋል። የመስቀሉ ማእከላዊነትና መልእክት በብልጽግናና በ“ራስ ማሻሻያ” ብልሃቶች፣ በግለኛነትና በመካካብ ወንጌል እየተተካ ነው። በዚሁ አስተሳሰብ መሠረት ቤተ ክርስቲያን በንግድ ተቋም ትመሰላለች። መጋቢ ደግሞ የተቋሙ ባለቤት ወይም ተቀጣሪ አስተዳዳሪ ነው። ምዕመኑ ገበያተኛ ነው። ብዛት ብልጽግና ነው። ምዕመኑ እዚህ ካልጣመው ወይም ሌላ “ራእይ” ከመጣለት ትቶ እዚያ የመሄድ መብቱ የተጠበቀ ነው። ተጠሪነቱ ለራሱ ነው። ላወጣው ወጪ ተመጣጣኝ አገልግሎት ይሻል። “ራእይ” እንደ ልብ ሆኗል። ወደ ሌላ እንዳይኰበልልበት ዘዴ መፍጠር ደግሞ የትጉዕ መሪ ኃላፊነት ነው። ምሪት የሚገኘው ከመንፈስ ቅዱስና ከቃሉ ሳይሆን ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ስሜትና ፍላጐት በመነሳት ነው። የተቋሙ ፍሬ በሰው፣ በገንዘብና በእንቅስቃሴ ዘርፍ ብዛት ይመዘናል። ቃሉ ግን የሚነግረን የመስቀሉ ነገር ለሃይማኖተኞችና ለምድር ሰዎች እንደማይመቻቸው ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 118-25፤ ፊልጵስዩስ 318-21)።
ለአንድ ሰሞን ያለ ሙዚቃ መሣርያ ቢመለክ ስንቱ ሰው ይሆን ቤተ ክርስቲያን መምጣት የሚያቆመው? ለአንድ ሰሞን ጉባዔ የመረጠውን መዝሙራት መዘመር ቢጀመር ምን ለውጥ ያስከትል ይሆን? በየአምልኰው ክፍለ ጊዜ የአንድ ሰዓት ፍጹም ፀጥታ ቢታወጅ መንፈሳዊነትን እንዳጐደለ ይቆጠር ይሆን? (ራእይ 8፡1፤ 1ኛ ነገሥት 19፡12፤ መክብብ 3፡7፤ 5፡2 ይመልከቱ) ስንቶች ይሆኑ እንደ ነቢዩ ዕንባቆም “ምንም እንኳ ካሴትና ሲዲ ባይሸጥ፣ ታዋቂነትና ጥሪም ባይመጣ፣ በማገልገል ውስጥ ጉዳት እንጂ ትርፍ ባይገኝ፣ ሙዚቃውም ባይጋጋል፣ እኔ ግን ለጌታ እዘምራለሁ” የሚሉ? (ዕንባቆም 317-19)
2. “አይ ፖድ”፣ አይ ሲዲ፣ አይ ስነ-መለኰት
በመሠረቱ ቴክኖሎጂ በራሱ ክፉም በጐም ነው ማለት አይቻልም። እንደ እሳት ጠቄሜታው ነው የሚተረጉመውና። በግል አስተሳሰብ፣ በቤተ ክርስቲያን አሠራርና በአገር አቅም ላይ ጉልህ ለውጥ እየታየ ነው። ቴክኖሎጂው ስለ ተለወጠ ብቻ ተጠቃሚውም የያዘውን መለወጥ ይኖርበታል ማለት አይደለም። ተጠቃሚው በአብዛኛው በያዘው የማይረጋውና የማይረካው “ደረጃ” ለመጠበቅ ወይም ቁሳቁስን ማጋበስ እርካታ የሚሰጥ መስሎት ይሆን?
በአገራችን ለምሳሌ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የ”ሞባይል” ስልክ “ቀጭኑን ሽቦ” እየተካው መጥቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የነበረው ስልክ ለአገሬው ተጠቃሚ እንኳ አልተዳረሰም። ሌላው የዓለም ክፍል ‘ዘመናዊ’ ወደ ሆነው ስለ ተሸጋገረ ብቻ አብረን መንከራተት አለብን ያለ ማነው? ምናልባት ጊዜ አለፈበት የተባለውን ነገር ግን ችግራችንን የሚያቃልልልንን ማስፋፋቱ አይቀልም ነበር? እንላለን። በአገር ደረጃ ቢሆን በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በምዕመኑ ኑሮ ውስጥ የተዛባ አመለካከት እንዳለ ይህ ሊያስረዳ ይችላል። ባጭሩ፣ ቴክኖሎጂ ልንጠቀምበት እንጂ ሊጠቀምብን፣ ሊያገለግለን እንጂ ልናገለግለው አልተፈጠረም። ተሳታፊ እንጂ ተመልካች ሊያደርገን አይገባም።
ቪዲዮ ቀጂው አስር ደቂቃ ያህል ዘግይቶ ስለመጣ ይካሄድ የነበረው አምልኰ አንደገና እንዲጀመር የተደረገበትን አንድ ስብሰባ አስታውሳለሁ። በየስብሰባው የሚቀረጹትን ቪዲዮዎች ተሰብስበን ስናይ “ይኸ እከሌ አይደለም? … እከሊት ምነው እንዲህ ከሳች? ውፍረቷ ይሻላት ነበር፤ … እንትናን ደግሞ ምን መለጠው? የዚህ አገር ዉሃ መቸም…” ማለታችን አልቀረም።
“ቴክኖሎጂ እኰ ጌታም የሚወደው ነው” ይሉናል። ዝግ ብሎ ላሰበ ግን ከላይ በጠቀስናቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚጠቀሙት ቁጥር አቅሙና ዕውቀቱ ከማይፈቅድላቸው ጋር ሲነጻጸር ኢምንት መሆኑን ነው። ስለሆነም የጥቂቶች ፈቃድ በብዙሃን መላከክ የለበትም። ፍላጐቶቻችንን ክርስትና ማንሳት ክርስቲያናዊ ያደርገዋል ማለት አይደለም።
ቤተ ክርስቲያን የፆም አዋጅ ያክል፣ “ቴፕ ያለህ ቴፕህን፣ ሲዲ ያለህ ሲዲህን፣ ሌላም ስም ያለው ያለህ ያለህን፣ የሌለህ ደግሞ እንዳትቀር ለብርቱ ጉዳይ ፈልጌሃለሁ” ብትል፤ ሁለት ነገሮች የሚከሰቱ ይመስለናል። የመጀመሪያው፣ የሸቀጡ ብዛት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ፣ በምዕመን መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ነው። አንዳንዱ ለቤት ማዳመቂያ፣ ሌላው ገንዘብ ተርፎት፣ ሌላው ከማን አንሼ፣ አንዳንዱን ሻጭ አሞኝቶት፤ ሁሉም የየግሉ ምክንያት አያጣም እንላለን። ይኸው ሸቀጥ ተሰብስቦ ወደ መጣበት አገር ቢመለስ በምዕመን መንፈሳዊነት ላይ ኪሣራ ያስከትል ይሆን?!
3. መልእክቱ ምዕመኑ ራሱ ነው
መንፈሳዊነት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር በመሆን እንጂ በሚታይ በውጫዊ ተጽዕኖ አይገኝም። የቴክኖሎጂ እድገትና አጠቃቀም መልካምም አሳሳቢም ነው። አንዱን ሳናጣጥም ሌላው መልክና ቁመና ቀይሮ ከተፍ ይላል። እኛም ከአንዱ ወደ ሌላኛው ስንከንፍ እንታያለን። ከቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን፣ ከአገር አገር የምንለው፣ ጸንተን የማንገኘው በሰሞነኛውና በውጫዊ አስተሳሰብ ስለምንነዳ ይሆን? ሥር የሰደደ፣ መሰጠትን የሚጠይቅ የጠራ ነገር የሚፈለግ አልሆነም። የሚፈለገው ይልቅ ወዲያው ውጤት የሚያሳየው፣ እጅ በጅ የሆነው፣ የሚታየው፣ ብዙ ጥረት የማይጠይቀው፣ በኛው ሚዛን የተሻለ የምንለው ነው። ምሪታችንን ከማን ይሆን የምንቀበለው? እያንዳንዱ የራሱን ሕይወት መምራት እንዳለበት የታወቀ ቢሆንም የአማኒያን ግን በ “ሥጋ ምኞት በዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም በመመካት” ሊሆን አይችልም (1ኛ ዮሐንስ 215-16)። አኗኗራችን ከዓለማዊያን የሚለየው በምንድነው? በዓለም እንዳሉቱ ቁሳቁስ የምናግበሰብስ ከሆነ “የክርስቶስ መልእክት” መሆናችን ቀርቶ የሸቀጥ መልእክተኞች እንሆናለን (2ቆሮንቶስ 33)። እውነትን ትተን ምቾት ብንሻ ሳይመቸን እንኖራለን፤ እውነቱ ቀርቦልን ይሠወርብናል (ሉቃስ 1619-31፤ ማቴዎስ 25)። እውነትን አጥብቀን ብንሻ ግን የክርስቶስ ሰላምና እርካታ ይጨመርልናል። “እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤… ያላችሁ ይብቃችሁ” የሚለን ለዚሁ ነው (ኤፌሶን 515፤ ዕብራውያን 135፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 48፤ ፊልጵስዩስ 411-12)።
4. ያጠረ ክር
የንግድ ነገር ከተነሣ እኛም የምንለው አናጣም። የመዝሙራት ቅጂ ተሻሽሏል ይሉናል፤ እርግጥም ተሻሽሏል። የሚገርመው ግን ከቴፑ ይሁን ከመዝሙሩ ሁሉም እያጠረ መጥቷል። አንድ የሙሉ ወንጌል መዘምራን ቁ.2 ክር ለምሳሌ ሃያ መዝሙር ሊሞላ ምንም አልቀረውም። ክሩ አጥሮባቸው እንጂ ይጨምሩ ነበር እንላለን።
ወንጌልን ከሸቀጥና ከንግድ ጋር አቀራርቦ ማሰብ ቅሥፈትን እንደ መጋበዝ ይመስል የነበረበት ዘመን ነበረ። የዛሬውማ ከአስሩም መዝሙር በዝቶ ወይ የመጀመሪያው መዝሙር መጨረሻ ላይ በከፊል ይደገማል፤ ወይም በመሳሪያ ብቻ ደግሞ ይቀርባል። የብርሃን ልጆች ከዓለም ልጆች እኩል ሠለጠኑ እንበል? ወይስ የዓለም አሠራር በስርጭት ላይ የማይገባ ተጽዕኖ እያደረገ ነው? ይህ ሐተታ እርግጥ ሁሉን አይመለከትም። ወንጌልን ያለ ወጪ ማዳረስ ይቻላል ግን ማለታችን አይደለም።
አንዳንዶች ዘማሪዎች የሰከነ አማካሪ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የሚገሥጻቸው፤ ሁሉም ግን የሚጸልይላቸው። የቆሙበት ሥፍራና የዕድሜአቸው ክልል ለፈተና የተጋለጠ ነውና። ጠላትም የወንጌል መተላለፊያ እንደ ሆነ ስለሚያውቅ አጥብቆ ይታገለናል። ጥቂቶቹም ከጌታ ቤት ውጭ ያለውን ብዙ ስለማያውቁ ግርግሩ አደናግሯቸዋል። ሲብስም አባብሏቸዋል። ተጠሪነታቸው “አዎን፣ ሃሌ ሉያ” ለሚሏቸው ግለሰቦች ስለሆነ ሲስቱ ሃይ የሚላቸው አያገኙም። ተመልሶ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር መከለል አማራጭ የለውም። ማስተዋል ይስጥ።
ፉክክር የታወጀ ይመስል አንዱ አዲስ መዝሙር በሌላ አዲስ መዝሙር ሲለዋወጥ በጌታ ጸጋ ያካበትናቸው ውድ መዝሙራት፣ ትዝታችን በምስጋና እንዳይበረክት ለዝገትና ለመረሳት ተዳርገዋል። የሚቀጥለውስ ትውልድ የዚህኛውን ትውልድ ትዝታ ይርሳውን? የእምነት አካሄድ “ሲወርድ ሲዋረድ” የመጣና የሚቀጥል ነው። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ “የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችን ልብ ወደ አባቶች… የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ” መመለስ ነው (ሚልክያስ 46፤ ሉቃስ 117)። ቴክኖሎጂ በጐም ነገር አለው። ከላይ እንደጠቆምነው፣ ልንገለገልበት እንጂ ልናገለግለው ግን አይገባም። በሠለጠኑ አገሮች ያየነውን ሁሉ ከሻን ተጐታች እንጂ የራሳችን ኑሮ መሪዎች መሆን አንችልም።
5. የሥልጣኔ ገደቡ
ዛሬም እንደ ጥንቱ ወንጌል የሚሠራጨው ወዳጅ ለጐረቤቱ አፍ ላፍ የምሥራቹን ሲያወራ ነው። “በዚህ ዘመን ኖር ቢሆን ጌታም በቴክኖሎጂ ይገለገል ነበር እኰ” ይባላል። የሚሲዮናዊ ጥናት ሊቅ የሆነው ማክጋቭራን ለምሳሌ የሕንድን ሕዝብ ቶሎ በወንጌል ለመድረስ በየመንደር ማዕከላት የቪዲዮ ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም ይቻላል ብሎ ነበር። ልንዘነጋው የማይገባን ነገር ቢኖር የጌታ ወንጌል ሰውን እንጂ የዘመኑን ግኝት ያማከለ እንዳልነበረ ነው። ይህም ማለት በወቅቱ የተገኘውን መሣሪያ አልተጠቀመበትም ማለት አይደለም። ዋነኛ ትኩረቱ በአምሳሉ በፈጠረው ሰው ላይ ነው ማለት እንጂ። የሰማሪያዊቱንና የጌርጌሴኖኑን ሰው ታሪክ ማገናዘብ ይጠቅማል (ዮሐንስ 4፤ ማርቆስ 51-20)። የጠራቸውን “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ያለውም ለዚሁ ነው (ማርቆስ 16፡15)። ጌታን ልንወስነው አንችልም። ቴክኖሎጂ ብዙ ጥቅም ቢኖረውም እስትንፋስ እንዳለበት ሰው አይሆንም። የደስታና የሐዘን ስሜት አይታይበትም፤ ቴሌቪዥንና ቪዲዮ ደግሞ አንድ አቅጣጫ ንግግር እንጂ ምልልስ አያውቅም። አይዳሰስም፣ ሥጋና ደም አይካፈልም (1ኛ ዮሐንስ 11-2፤ ዕብራውያን 214-15፤ ዮሐንስ 14)። ባጭሩ ቴክኖሎጂ ብዙ ጥቅም ቢኖረውም ከሚገባ በላይ ግን ሥፍራ ልንሰጠው አይገባም ማለታችን ነው።
ቴክኖሎጂ በገነነባቸው አገሮች ሰው ከራሱና ከመሰሉ እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር ለመቆራረጡ አንደኛው ምክንያት ሆኗል። ግንኙነት ያባዛ እየመሰለ ሰውን ብቸኝነት ለቅቆበታል። አብረው ይጓዛሉ፤ ሩቅ ካለ ሰው ጋር በየፊናቸው ያወራሉ። የቅርቡ ርቋል፤ የሩቁ ቀርቧል ማለት ነው። ድምጽ በዝቷል፤ ባለ አንድ ፊት ጫጫታ ነግሷል። ስንቶች ናቸው በዚህ ዘመን የጽሞና ሕይወት የሚለማመዱ? የሰው ቁጥር በዛ ካላለ ያመለኩ የማይመስላቸው ዛሬ ጥቂቶች አይደሉም! ቴክኖሎጂ ምን ያህል ቢራቀቅ ያልተሰጠን ሕይወት ደቀ መዝሙር አያደርግም!
ሮም ሥልጡን እንደ ነበረ አንዘንጋ። ግሪክም። ሥልጣኔ በኛ አልተጀመረም። በዘመኑ ሁሉም ሥልጡን ነው። ጊዜው ሲያልፍ አረጀ ያልተባለ የለም። ኃጢአትና ጽድቅ እንዲሁም የሰው መሠረታዊ ባሕሪይ ግን እስካሁን አልተሻሻለም። እርግጥ ስለምንኖርባት ዓለም ከቀደሙት ይልቅ ዕውቀት አካብተን ሊሆን ይችላል። ሆኖም ጥበብንና ማኅበራዊነትን ሳንጥል አይደለም።
መደምደሚያ
ወንጌልን በተለያየ መልኩ ለማሰራጨት ምን መሠረታዊ ዕቅዶች ሊኖሩ ይገባል? ለዚህ ጥያቄ መልሱ እንደ ሁኔታው ሊለያይ ቢችልም፣ መሠረቱ ግን እያንዳንዱን ምዕመን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ማገናኘት ነው፣ ለመንፈስ ቅዱስ አደራ መስጠት ነው። ከጥገኛ እምነት ማላቀቅ ነው፣ በጌታ ቤት ሙሉ ማኅበርተኛ ወደ መሆን ደረጃ ላይ ማምጣት ነው። የጸሎትን ሕይወት ማለማመድ ነው። መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ሥርዓት ማሳወቅ ነው። አስተሳሰብን ለሚሰርቁ ባሕላዊ አመለካከቶች ከቃሉ ምላሽ የመሻትን ልማድ ማጐናጸፍ ነው። በአዕምሮ ጭምር የበሰሉ ወደ መሆን ማድረስ ነው። በተጨማሪ ከታች የተጠቀሱት ነጥቦች መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ።
· የመጻፍና የማንበብ ልምዳችን እንደሚገባ የዳበረ አይደለም፤ ይህን የምንለው ማንበብና መጻፍ ስለማይችሉት ወገኖቻችን አይደለም። ወይም ማንበብ ሲችሉና ሲፈልጉ የገንዘብ አቅም ያገዳቸውን አይደለም። ይልቅ ጥቂትም ቢሆኑ ለማንበብና ለመጻፍ በቅተዋል የምንላቸውን እንጂ። የማያነብቡ እንዲያነብቡ፣ የሚያነብቡ ይበልጥ እንዲያነብቡ ማድረግ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ፣ ማሕበራዊ፣ ብሔራዊ ግዴታዋና ተግባሯ ሊሆን ይገባል። ያመኑት ሁሉ በቤታቸው ሆነ በእግዚአብሔር ቤት ከቃሉ የተነጠለ ኑሮ ሊኖራቸው አይችልምና። ይህን ሁኔታ ተገን አድርጐ ማቀድ ያስፈልጋል።
· ሰማዕት ጉዲና ቱምሣ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስን ከስድሳ ስድስቱ አብዮት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች መሠረተ ትምህርት እንድታካሄድ የሰጡት አመራር ሊኮረጅ እንጂ ሊዘነጋ አይገባም። ይህን የመሰለውን ግዳጅ ለመፈጸም መንግሥት አዋጅ እስኪያውጅ መጠበቅ አያሻም። ሰውንና የሕልውና መብቱን በሚመለከት ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ እንጂ ተከታይ መሆን የለባትም። የስነ-መለኰት ትምህርት ተቋማትን ከማደራጀቱ ጋር ተያይዞ ተራውን ምዕመንና ቤተ ክርስቲያን በምትገኝባቸው ቀበሌዎች ኗሪዎቹን እንዲጽፉና እንዲያነብቡ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። መሃይምነት ከጌታ ቤት ይወገድ! አንባቢ በበዛ ቁጥር በብዙ ቁም ነገር ውስጥ የሚሳተፉ እንዲሁ ይበዛሉና። ይህም በተራው የመጽሐፎችንና የመጽሔቶችን ሺያጭ ከፍ ያደርገዋል፣ የአሳብ ልውውጦችን ያዳብራል ማለት ነው።
· ማንበብ የሚችሉ የማንበብ ልምድ እንዲያዳብሩ፣ ትጉህና ታማኝ በሆኑ ምዕመናን እጅ በየአካባቢው የሠፈር ቤተ መጻሕፍትና ክበቦችና ማቋቋም ጠቃሚ ነው። በተለይም ለወጣቱ ትውልድ። በወር ይሁን በተወሰኑ ቀናት እንዲነበቡ በተመረጡ ጠቃሚ ጽሑፎች ላይ የአሳብ ልውውጥ ማድረግ ይህን ባሕል ያዳብረዋል። ደጋግሞ ማድረግ ልማድ ይሆናል፤ ጥሩ ልማድ ምን ጊዜም ጥሩ ነው። በቤተ ክርስቲያን ደረጃ የንባብ ቀን እንደ ፆም ቀን በዓመቱ እቅድ ውስጥ ሥፍራ ቢሰጠው እርስ በርስ የመበረታታትንና የመማማርን ልምድ ያስገኛል።
· የመጻፍ ልምድ እንዲዳብር፣ አጭር ኮርሶችን ማዘጋጀት፣ ዝንባሌ ያላቸውን ማሰባሰብ፣ በጀት መድቦ በአስፈላጊ ቁም ነገሮች ላይ እንዲጽፉ ብቃት ያላቸውን ግለ ሰቦችን ማሰማራት፤ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የዲሞክራሲ ሂደት እንዲፋጠንና ተደማጭነትን እንዲያገኙ ይረዳል። የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶች ይህን መሠረት በማድረግ ሊዘጋጁ ይገባል።
· በደርግ ዘመን የነበረው ሁኔታ ሊታሰበን ይገባል። በተለይ አገር-አቀፍ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሕልውናቸው ከሚያጠራጥር የውጭ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርባቸዋል (ይመልከቱ፦ http://blogs.salon.com/0003494/2005/10/16.html)። ከሁሉ አስቀድሞ የነዚህን ድርጅቶች ማንነት ማጣራት ያስፈልጋል። በአሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ ወንጌላውያን ድርጅቶችና መሪዎቻቸው በጭፍን የመንግሥታቸውን የውጭ ፖሊሲ የሚያራምዱ ወይም የሚያስተጋቡ ሆነዋል። ሌሎች ደግሞ ከአገሬው ምዕመን የሚገኘው ገቢ ስላቆለቆለ በ/