የ “ሐዋርያ” ዘላለም ትምህርት ሲመረመር

“ሐዋርያ” ዘላለም (ፖዝ) ጌታቸውን በኤክሰደስ ቲቪ ላይ ቤተልሔም ታፈሰ አቅርባው ነበር። ከታች የተመለከተውን ትንታኔና ትምህርት ያቀረበልን ፓስተር ዘላለም መንግሥቱ ነው። ትንታኔው በሁሉም፣ በተለይ በቤተክርስቲያን መሪዎች፣ በጥንቃቄ ሊነበብ ይገባል። ሙሉውን እትም በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይጠይቁ። ባለአራት ክፍል መጠይቁን እዚህ ጀምረው ይመልከቱ። ኢትዮፕያንቸርች አዘጋጅ፤ 4/18/16

መግቢያ። ብዙ ጊዜ በስህተት ትምህርቶች ወይም በስሕተት አስተማሪዎች ላይ ስጽፍ የምጠይቃቸው ሦስት ጥያቄዎች አሉ፤ 1. ይህ ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጻረራል? 2. ጌታ ክርስቶስን ከክብሩ ያወርደዋል? 3. የቅዱሳንን እምነት ያፈርሳል? በዚህ መጣጥፍ “ሐዋርያ ፖዝ” ስለ ኢየሱስ የተናገራቸው ስሕተቶች ወይም የስሕተት ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጻረራሉ፤ ክርስቶስን ያዋርዳሉ፤ የቅዱሳንን እምነት ያፈርሳሉ። በቃለ መጠይቁ ውስጥ ይህ ሰው ኢየሱስን፥ 1. ፖዝ አስደራጊው ኢየሱስ፤ 2. ሰይጣኑ ኢየሱስ፤ 3. ሰው ብቻ ኢየሱስ፤ 4. ታጃቢው ኢየሱስ አድርጎ አሳይቶአል። እንደ ፖዝ ያሉት ሰዎች የሚናገሩት ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ነው ወይስ እነርሱ የፈጠሩት ኢየሱስ? ብሎ መጠየቅ ተገቢና የመልሳችን መዝገብ ወደሚገኝበት ወደ ቃሉ እንድንሄድ የሚያደርገን ጥያቄ ነው። ዛሬ የምንሰማው ሐሰተኞች አስተማሪዎች የሚሰብኩን ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ሳይሆን በምናባቸው የፈጠሩት ወይም ሰይጣን ፈጥሮ ያቀበላቸው ሌላ ኢየሱስ ነው። በዚህ ሰው ትምህርቶች ውስጥ የምናገኘው ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ቆሮ. 11፥4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። ያለው ያኔም አሁንም እውነት ነው። ሌላ ኢየሱስ፥ ልዩ መንፈስ፥ ልዩ ወንጌል። ይህ ታዲያ የሚታገሡት ትምህርት መሆን የለበትም።

1/ ፖዝ አስደራጊው ኢየሱስ። ፖዝ ከሚለው ቃል ልጀምር። ሐዋርያ ዘላለም የቅጽል ስሙ ፖዝ (pause) መሆኑን ይናገራል። አንድን ነገር ለዘለቄታው ሳይሆን ለጊዜው ማቆም ማለት ነው። ልክ በሙዚቃ ወይም መዝሙር ማጫወቻ መዝሙር ሲዘመር ቆይቶ ለጊዜው አቁሞ ኋላ እንዲቀጥል እንደሚደረገው ማለት ነው። ወይም አንድ መኪና ኬላ ላይ ቆም ብሎ ተፈትሾ ጉዞውን እንዲቀጥል ሲደረግ ማለት ነው። ሐዋርያ ፖዝ ስሙ ለምን ፖዝ እንደተባለ በቃለ መጠይቁ ሲናገር፥

“እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የድህነትን፥ የኃጢአትን፥ የሞትን፥ የበሽታን አካሄድ ፖዝ አርጓል፤ አቁሟቸዋል። እነዚህ ነገሮች በሰው ሕይወት ውስጥ ፍሰታቸው ተከልክሏል። እኛ ግን እሱን ፓርት አናይም። የቆሙት በመስቀል ነው። ልክ ይኼ የቆሙትን ነገሮች ከዚህ ትውልድ ላይ ታቆምልኛለህ፤ አሁን በማስተምርሽ ትምህርት፥ በሚገባሽ እውቀት፥ ይህንን የጨለማ ፍሰት፥ ታቆምልኛለህ አለኝ ማለት ነው። . . . ፖዝ ታረግልኛለህ ሲል ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ታደርጋለህ፤ ባይ ዘ ዌይ፥ ፖዝ ማለት የቃሉ ፍቺ፥ ማቆም ማለት ነው . . . ፖዝ ማለት ፍቺውን ልንገርሽ፤ ፖዝ ማለት ጳውሎስ ማለት ነው። ሌላ ፍቺ የለውም። ጌታ ያለኝ በቀጥታ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? በዚህ ትውልድ መሐል ለኔ ጳውሎስ ነህ ነው ያለኝ። እኔ ጳውሎስ የሚለውን ቃል ትርጉሙን ወሰድኩኝና ጳውሎስ የሚለው ፊደል የግሪክ ቃል ላይ ሄጄ ሳጠናው የመጀመሪያው ላይ እመጀመሪያው ወርድ ማለት ነው፤ ሊትል ማለት ነው፤ ሩት ኦሪጂናል ኤግዞስቲቭ ኮንኮርዳንስ ሚባል አለ ግሪክና ሂብሩ ያለው፤ ሩት ወርዱ ላይ ሄጄ ስመለከተው ሩት ወርዱ ምን ይላል? ፖዝ ይላል። ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጳውሎስ የተባለው የትጋ እንደሆነ ታውቂያለሽ? ምን አርጎ ጳውሎስ እንደተባለ ታውቂያለሽ? [ሐዋ. 13፥8-11 ከተነበበ በኋላ] . . . እስከ ጊዜው ፀሐይን አታይም አለው። በሌላ አማርኛ ሰውየውን ምን አረገው? ፖዝ አረገው። ጳውሎስ ፖዝ ነው። ጳውሎስ ማለት ፖዝ ማለት ነው።"

ይህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችንም ያላሉትን እንዲል እያደረገ ሊፈታ የሚሞክረው በዚህ መንገድ መሆኑን ዝቅ ስንል እናየዋለን። ጳውሎስ Παῦλος የግሪክ ሳይሆን የሮማይስጥ ቃል ነው። ስም ሳይሆንም ቅጽል ነው፤ እንዳለውም ትርጉሙ ትንሽ፥ ታናሽ ማለት ነው። ጳውሎስ የሚለው የጳውሎስ ስም በዚያ ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቀሰ እንጂ ሳውል ጳውሎስ የተባለው ቀድሞም ነበረ። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን የሚለው ሐረግ የሚነግረን ስሙ ቀድሞውኑ ጳውሎስ መሆኑን እንጂ ሰዎች ተሰብስበው የዳቦ ስም ሲያወጡለት አይደለም። ጳውሎስ ለቅጽበት ወይም ለጊዜው ወይም ለትንሽ ጊዜ ማቆም ማለት ሳይሆን፥ እንዲያው ትንሽ ማለት ብቻ ነው። ጳውሎስ ከዚያ በፊት ሳውል እንደነበረ እናውቃለን እንጂ ለምን ጳውሎስ እንደተባለ አልተጻፈልንም። በዚህ ሰው አነባበብ እና አፈታት ውስጥ የሚታየው ጥቅሶችን በሚጠቅስበት ጊዜ የሚፈልገውን ስለሚሉ ብቻ እንጂ ዐውድ የሚባል ነገር ስለመኖሩም ግድ የሚሰኝ አይመስልም። ምንም የመጽሐፍ ቅዱስና የስነ መለኮት ትምህርት ዳራ ከሌለው ሰው ስለ ዐውድና ዳራ መጠበቅም አይቻልም። በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይም ያስተዋልኩት ይህንን ዐውድ-ዘለልነት ነው። ጥቅስን ከስፍራው ፈንቅሎ ከጥቅሱ ውስጥ ቃልን ብቻ ወስዶ መፍታት የስሕተት ትምህርቶች ዋና መታወቂያ ነው። ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውስጥ አለማለፉን በግልጥ እየተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች እየከፈተ የሚያስተምር መሆኑ እንዲህ ያሉ ብልሹና ጠማማ ፍቺዎችና አጣማሚ ፈቺዎች እየተባዙ የመምጣታቸውን መንገድ ቀያሽ መሆኑንም የሚያሳይ ነው። ጌታ ክርስቶስ ዳግም እስኪመጣ ድረስ ይህች ምድር ምን እንደምትመስል መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ግልጽ አድርጎ ይነግረናል። ከነዚህ ግልጽ ነገሮች ውስጥ ግን ኃጢአት፥ ድህነት፥ ሞት፥ በሽታና፥ የጨለማ ፍሰት “ፖዝ” እንደሚደረጉ በአንድም ስፍራ አይናገርም። “ፖዝ” እንዳደርግ ነገረኝ የሚለው ኢየሱስ ማን መሆኑ መጠየቅ ያለበት ትልቅ ጥያቄ ነው። በመስቀል ላይ የሞተልን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ እንዲህ የመሰለ ቅሌታም ሹመትና ፌዘኛ ሹም የሚሾም ንጉሥ አይደለም። ታዲያ፥ እንዲህ ያለ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ “ፖዝ” አድራጊ ሹም የሚሾም ማን ሊሆን ይችላል? መልሱ ግልጽ ነው። በኢየሱስ የሚመሰል ሰይጣን በሥራ ላይ መሆኑን የረሳንበት ቀን ትጥቃችን የተፈታበት ቀን ነው። ኢየሱስን በማንነቱ ለማወቅ ደግሞ 'ታየኝ፥ ተናገረኝ፥ ተገለጠና ይህን አለኝ፥ ላከኝ፥ ሾመኝ፥ ቀባኝ፥ ሌላም ሌላም' የሚሉንን ሰዎች ሳይሆን በቃሉ ውስጥ ራሱን የገለጠውን፥ የተጻፈውን ያንን ጌታ ነው መስማት ያለብን። ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ጋር ያለን ግንኙነት እንደ ደባል በልክና በድርበብ የሆነ ጓደኝነት ብቻ ከሆነ በተገመዱ ጥቅሶችና 'መገለጥ' በሚሉት ነገር በቀላሉ ልንታለልና ልንወሰድ እንችላለን። ያንን ኢየሱስ ካላወቅነው በሐሰተኛ ኢየሱሶች እንደ ዘበት ተጎትተን ልንወሰድ እንችላለን። “የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። 2ቆሮ. 11፥4።” ይህ “ሐዋርያ” የሚያስተዋውቀን ኢየሱስ ድህነትን፥ ኃጢአትን፥ ሞትን፥ በሽታንና ጨለማን “ፖዝ” የሚያስደርግ ብቻ ሳይሆን የሰይጣን ባሕርይ የተላበሰ ኢየሱስም ጭምር ነው።

2/ ሰይጣኑ ኢየሱስ። ኢየሱስ ሰይጣን ሆኖ ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ በግልጽ መልስ በመስጠት ፈንታ ዙሪያ ዙሪያውን ሲጎደፍር ቆየና፥ ከዚህ በፊትም ያላለውን እንዳለ ተደርጎ እንደተነገረበት አሁን መታተም ባቆመ መጽሔት እንደተጠቀሰ ካተተ በኋላ በጋዜጠኛዋ በእርግጥ ኢየሱስ እንደሰየጠነ ሲጠየቅ፥ “'ዘላለም ሰይጥኗል ኢየሱስ ትላለህ' ብለው ማቴቴስ ላይ አውጥተውኛል። በመጀመሪያ ደረጃ ያንን ቃል በቀጥታ ኢየሱስ ሰይጥኗል ሚለውን አልተጠቀምኩም። ግን፥ ቃሉ የሚናገርበት እነሱ እንዴት እንዲህ ትላለህ ሲሉ ያልኳቸው፥ 'ይሄ እኮ ማለት ከባድ ነገር አይደለም፤ አየሽ? ክርስቶስ እኔን ሲያስረዳኝ ማለት ነው፥ ስለ ሰዋዊ ማንነቱ አስረድቶኝ ከዚያ በኋላ ስልጠና ሰጠሁኝ ስለ ክርስቶስ በምድር ላይ ሰዋዊ ማንነት፥ የኖረበት ሕይወት ምናምን፥ ከዚያ በኋላ ሰዎች ጥያቄ አነሱ ምክንያቱም ማንም ያለበትን ዶክትሪን ነው ሚያምነው፤ ተጨቃጨቁ፤ ሄዱ እነሱ። 'ሰው መሆኔ ነው የገረመህ?' አለኝ። 'እርግማን ሆኜ፥ ኃጢአት ሆኜ፥ የግብጽ የበኩር ልጅ ሆኜ ሞቼላቸዋለሁ።' ሆኜ ነው ያለው። አሁንን ይሄንን ሆነ የሚለውን እንዴት ትተረጉሚዋለሽ? ኃጢአት የእግዚአብሔር መንግሥት አይደለም። የእግዚአብሔር ስብዕና አይደለም። እርግማን የእግዚአብሔር ማንነት አይደለም።”

“ፖዝ” ኢየሱስ እንዲህ አለኝ የሚለው ነገር ከተጻፈው ቃሉ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው ተደርጎ ነው የቀረበውና ማብራሪያ የተደረገው። 'ይህንን ምን ትይዋለሽ?' ብሎ ጋዜጠኛዋን ሲጠይቅ ቃሉን አንብቦ፥ 'ይህንን እንዴት ትረጂዋለሽ?' የሚል ነው የሚመስለው። የግብጽ የበኩር ልጅ ሆኜ ሞቼላቸዋለሁ ያለው ማን ነው? ለማን ነው? መቼ ነው? ይህ የመስቀሉ ሞት ነው ወይስ ሌላ? ኢየሱስ የግብጽ የበኩር ልጅ ሆኖ ከሞተ በመስቀል ላይ ከመሞቱ በፊትም ሞቶ ነበር ማለት ነው። ሰው ሳይሆን፥ ሥጋ ሳይለብስ በፊትም መለኮት ሞቶ ነበር ማለት ነው። ወይስ ይህ ሌላ ኢየሱስ ነው? ይህ በእርግጥ፥ ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ የተባለው ሌላ ኢየሱስ ነው። . . . አምላክ እርግማን ይሆናል? አምላክ ኃጢአት ይሆናል? አምላክ የኃጢአት ኔቸር አለው?

“አየሽ አሁን ችግራችን ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? ለኛ ብሎ ማንነቱን ሳይቀይር ነገር ግን ሙሉ ባሕርያችንን ወስዶ የገለጠውን ማንነት፥ 'ኖ! በውስጡ መለኮት ይዞ በሥጋው ሰው ሆኖ እንደዚህ ብሎ [እንላለን ይህ] ቤዛነቱን ፍጹም አያደርገውም። . . . [ሰየጠነ የሚለውን] ይህንን ቃል የተጠቀሙት ሌሎች ናቸው። የነ ኬንዮን፥ የሌላ ፌይዝ ላይ ያሉ ሰዎች ያሉት ነው። ግን ያሉትም ቢሆን ብዙ ስሕተት አይደለም። ለምን ብትይ ቃሉን ላሳይሽ፤ . . . የወረደበትን ጥልቀት፥ የወጣበትን ከፍታ፥ አይደለም ኤፌሶን ላይ ያለው? ይህ ከሁሉ በታች ደግሞ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ወደላይ ወጣ።

ቤተልሔም፣ ሰየጠነ ካላልክ ለምን ልታሳምነኝ ትሞክራለህ?

“እኔ ላሳምንሽ የምሞክረው እዚህ ውስጥ (አእምሮ ውስጥ) ያለውን ባሕላዊ አስተሳሰብ . . . ክርስቶስ ንጉሥ ነው ትያለሽ፤ ክርስቶስ ንጉሥ ብቻ አይደለም፤ እስከ ጥልቅ የወረደ ነው። የወረደበትን ልክ መናገርሽ ምንድነው ክፋቱ? ያልወረደበት ጥግ አለ ወይ? ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሁሉ በታች የወረደው ነው። አሸናፊነት እኮ አይደለም ያ። ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሁሉ በታች ወረደ ይላል። መውረዱ ዋጋ እያስከፈለው ነው የወረደው፤ አይደለም? የከፈለውን ዋጋ መናገር ለምን በሃይማኖት አሳብ ላይ ሆነን ለምን እንደ ክፉ አድራጊ ሰዎችን እንከሳቸዋለን?”

ትምህርቱ ተጠምዝዞ እዚያው የተሽከረከረው ቃሉን አላልኩም እያለ ትምህርቱን፥ ማለትም፥ ክርስቶስ ሰየጠነ የሚለውን ትምህርት ግን ስለሚቀበል ነው። “እነዚያ ኢየሱስ ሰየጠነ ያሉት ብዙም ስሕተት አይደለም” ማለት ብዙ እውነት ነው ማለት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ሰየጠነ ማለትን በትክክል ይቀበላል ማለት ነው። በእርግጥ ጋዜጠኛዋ እንደሞገተችው ሰየጠነ ካላለ ጉዳዩ በግልጥ እዚያ ላይ መቆም ነበረበት። ግን አይደለም፤ “አንቺ ሰለባ የሆንሽበት አንድ አስተሳሰባዊ ዓለም አለ። የዚያ አስተሳሰባዊ ዓለም ሪፍሌክሽን ነው ስሜትሽን የጎዳው። በሌላ መልክ ደግሞ ዓይንሽ ቢከፈት ክርስቶስ የወረደውን ጥግ ክብሬ ነው ብለሽ ዓይንሽ ቢከፈት ያንን ስትይው አታፍሪም? እኔ ስለ ቃል ነው ያወራሁት እንጂ ስለዚያች ነገር አይደለም። አይምሮሽ ውስጥ ግን የተገነባ ነገር አለ። ክብር ሚባለው ነገር ይሄ ነው፤ ውርደቱም እኮ ለኛ ክብራችን ነው። . . . ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ 'ሂድ አንተ ሰይጣን ከበስተኋላዬ' ያለው፤ ይቅርብሽ ብዬ ነበር ግን ልበለው፤ ጴጥሮስ እስኪሰየጥን ድረስ ሄዷል ማለት ነው? ጴጥሮስ እስኪሰጥን ሄዷል? መልሺልኝ። የጴጥሮስ የሕይወት እስታንዳርድ አዘቅት መጠኑ እስኪሰጥን ወርዷል? ኢየሱስ ጴጥሮስን መቤዥ ካለበት ወርዶ እታች ድረስ ማዳን አለበት። . . . ኢየሱስ እንደተናገረው ጴጥሮስ የሰው ልጅ ሆኖ እሰከመሰጠን ድረስ ሄዷል? ጌታ ደግሞ ሰውን ለመቤዠት ድንገት ሰው እስከወረደበት ጥግ መውረድ አለበት? ስለዚህ ጴጥሮስ ከሰጠነበት ሁኔታ ለመውጣት ክርስቶስ መሰጠን አለበት? ጴጥሮስ ሰጥኖ ከሆነ? እኔ ያንን ነው ጥልቅ አርገሽ እዪው የምለው። እኔ እስከ እርግማን አምናለሁ፤ እኔ አንቺንም ኦዲየንሱንም ቻሌንጅ የማረገው ፊደሉ ላይ ያለው የሃይማኖተኛና ከንቱ ትሕትና ቋንቋ ለምን እንጠቀማለን? እንዲህ ብለን ብንወስድስ? ጴጥሮስ እስኪሰጥን ድረስ ባሪያ ሆኗል ለሰይጣን? ጴጥሮስን ሰየጠነ እስኪያስብለው ድረስ? የሰው ልጅ የውድቀቱ ጥግ መሰይጠን እስከሚለው ድረስ ወርዷል? ከወረደ፥ ክርስቶስ ያንን ሰው ለማውጣት መሰይጠን እስከሚለው ቢወርድ ምን ችግር አለው? እኛጋ ነው ሃይማኖታዊ አይምሮ ቃሎቹን ለሚፈልገው ነገር ብቻ መጠቀም ሚፈልገው። ባላፈረበት ነገር አላፈረም። በሆነልኝ ነገር ሆኖልኛል ብዬ ስናገር አላፍርም።”

ፖዝ ደጋግሞ የተናገረው የክርስቶስ እርግማንነት ከክርስቶስ መሰይጠን ጋር ሊያቆራኘው የሞከረው ግልብ ስሕተት ነው። 'እርግማን ከሆነ እስከ መሰይጠን ቢደርስ ምን ይገርማል?' ያለበት እርግማንና መሰይጠን የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ያጤነውም አይመስልም። ክርስቶስ እርግማን የሆነበትን ሁኔታ ከእርግማን ምንነት ጋር መመልከቱ ተገቢ ነው። በመጀመሪያ የእርግማንን ምንነት መመልከት የተገባ ሲሆን የክርስቶስን እርግማንነት ደግሞ ቃሉን ከጥቅሱ ተፈናቃይ አድርጎ ሳይሆን በገላትያ 3 እንደተጻፈው ማየቱ ግድ ነው። እርግማን ወይም መርገም የሚለው ቃል የጥፋትና የቅጣት ውጤት ተቀባይ መሆንን የሚያሳይ ነው። በብሉይ ኪዳን ቋንቋ እርግማን መጥፎ ቃልን ወይም ብያኔን መናገር ወይም መቀበል ( אַָרר አራር)፤ እርም መሆን ወይም እርም መደረግ ( חֶֶרם ኼሬም) ማለትም ነው። ሌላው ቃል የክብርና ክብደት ተቃራኒ የሆነ ቅለትን ወይም ቀላልነትን የሚያሳይ קְלָלָה ቅላላህ፤ קָלַל ቃላል የሚል ቃል ነው። መቅለል፥ ውርደት፥ መውረድ፥ መዋረድ ማለት ነው። አማርኛ ሴማዊ ቋንቋ ስለሆነ ይህ ቃል አማርኛም ውስጥ ይገኛል። ጠቅላላውን ቃል ነው እያየን ያለነውና ስለ እርግማን በመጀመሪያ የምናገኘው በዘፍጥረት 3 ነው። በዘፍ. 3 አዳምና ሔዋን በመተላለፋቸው ቅጣታቸው የሆነውን ሞት/መለየት ሲቀበሉ እባብ (ሰይጣን) እና ምድር ግን የተረገሙ ሆኑ፤ ቁ. 14 እና 17። እባብ ቀድሞም የወደቀ ፍጡር ነበርና የተጨመረ ፍርድን ተቀበለ። በአዳም ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚስቱን ቃል መስማትም የተነሣ ምድር ተረገመች፤ የድካሙና የጥረቱ ምክንያት ሆነች። ከሰዎች መጀመሪያ ሲረገም የምናገኘው ወንድሙን የገደለ ቃየን ነው፤ ዘፍ. 4፥11። ከእርግማኑ ጋር የተያያዘውም የምድር በረከቷን ማገድ እና ተቅበዝባዥነቱ ናቸው። እርግማን እንግዲህ ፍርድ፥ ቅጣት፥ ብያኔ፥ የጥፋት ውጤትን መቀበል፥ ከከበረ ስፍራ መውረድና መዋረድ ነው። አዲስ ኪዳን እንደሚያስተምረን በቀደመው አባታችን በአዳም ሁላችንም ተኮንነናል፤ በክርስቶስ ግን ጸጋው አጽድቆናል፤ ሮሜ. 5፥ 15-21። ስለዚህ ከክርስቶስ ውጪ ያለ ማንም ሰው ከእርግማን በታች ነው። አዲስ ኪዳን እርግማን የሚለው ይህንን በብሉይ ኪዳንን ሕግ ሥራ ጸንቶ አለመቆምን ነው፤ ገላ. 3፥10-13። ማንም ሰው ወደ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ግን ክርስቶስ ሕግን ፈጽሞ በምትካችን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ይህንን እርግማን ስለሻረው ነጻ ሆኖአል። ወደ ክርስቶስ መረገም ወይም እርግማን መሆን እንምጣ። ቃሉ በገላ. 3፥13 ነው የተጻፈው። ፖዝ እንደሚያደርገው ጥቅሱ ከስፍራው እንዳይፈነቀል ጠቅላላውን የገላትያን መጽሐፍ አሳብ መረዳት ተገቢ ነው። የገላትያ መልእክት የተጻፈላቸው ሰዎች ገላትያ በሚባል ሰፊ አውራጃ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ናቸው። በሁለተኛው የወንጌል ጉዞው ጳውሎስ ወንጌልን ሰበከላቸውና በ3ኛው ጉዞው እያጸናና እያበረታቸው በዚያ አለፈ። ከገላትያ መልእክት እንደምንረዳው እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ አምነው ከዳኑ በኋላ ወደ ልዩ ወንጌል ፈጥነው አለፉ፤ ገላ. 1፥6። ይህ ልዩ ወንጌል በክርስቶስ ከዳኑ በኋላ ወደ መገረዝ (መገረዝ የብሉይ ኪዳን መታወቂያ ስለሆነ ሕግን ወደ መጠበቅ ማለት ነው) እንዲመለሱ ያስተማሩ ሰዎችን ትምህርት ተቀብለው ሕገኞች ሆኑ። ሕግ ወደ መጠበቅ፥ ወደ መገረዝ፥ ቀኖችና ወራትን ወደመጠበቅ፥ ወደ ባርነት ወረዱ፤ 4፥1-10። በሕግ መጽደቅ ቢቻልማ ኖሮ ክርስቶስ መምጣት፥ ሥጋ መልበስ፥ ስለ እኛ መሞት ባላስፈለገውም ነበር። ሕጉን ጠብቆ መዳን ይቻል ነበራ! ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ኢየሱስ ይህንን እውነት ነው አድምቆ እየጻፈላቸው ያለው። ጌታ ያገለገለበትን ዘመንና የሕግን ምንነት አስተውለን እንረዳ። እኛ ከሕግ በታች እንዳንሆን እርሱ ከሕግ በታች ተወለደ። እኛ ከሕግ በታች አይደለንም፤ እንዳንሆን ያደረገን ደግሞ ስለእኛ ከሕግ በታች ተወልዶ፥ ሕግን ሁሉ ፈጽሞልን፥ ከሕግ እርግማን የዋጀን ጌታ ነው። በመስቀሉም አዲሱን ኪዳን አቆመ። ነጻነት፥ ቤዛነት፥ ዋጋ ይጠይቃል። ጌታ እኛን ከሕግ ቀንበርና እርግማን ነጻ ያወጣን ነፍሱን ከፍሎ ነው። ሕግ በራሱ ምንም ክፋት የለበትም፤ ጸጋው እንዲያድነን ኪዳኑ እስኪፈጸም በእምነት ወደ እግዚአብሔር መቅረቢያው ሆኖአል። አዲሱ ኪዳን በደም ሲመረቅ ግን ቦታውን ጸጋው በእምነት እንዲያድነን ለቀቀ። በጸጋው የመዳናችን ዋጋውም ደሙ ነው። የኛ ከሕግ እርግማን አርነት መውጣት በዋጋ የተገኘ ነው። ይህ የተፈጸመው ከሕግ በታች መሆን የሌለበት እርሱ ለኛ ሲል ከሴት ተወልዶ፥ ከሕግ በታች ተወልዶ፥ በእንጨት ተሰቅሎ ከሕግ እርግማን ስለዋጀን ነው።

ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን የተጻፈውን ቃል ጠቅሶ የተናገረው እውነት ከሕግ በታች መሆን ከእርግማን በታች መሆንን ነው። ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና (ቁ. 10)። ክርስቶስ ደግሞ ከዚህ እርግማን የዋጀን ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ነው፤ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ (ቁ. 13)። ይህ ቃል 'ተብሎ ተጽፎአልና' የተባለው በዘዳ. 21፥22-23 የተጻፈው ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ፥ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥ በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው። የሚል ቃል ነው። ኃጢአተኛው በተሰቀለ ጊዜ እርግማኑን ተሸክሞ ነው በግላጭ የተሰቀለው። ሲሞትም እንደተሸከመው ሞቶአል። አይሁድ ሰዎችን በሞት ሲቀጡ ወግረው እንጂ ሰቅለው ስለማይገድሉ፥ ይህ መሰቀል የሬሳ ሰቅሎ እንደ መቀጣጫ ማሳየት ሳይሆን የቅጣት ከሆነ የከፍተኛ ውርደት ሞት ነው። የእርግማን ሞት ነው። በእንጨት የሚሰቀል የተረገመ ነው። በጌታ ዘመን ደግሞ የሮማውያን የመጨረሻው የከፋ ቅጣትና የውርደትና የእርግማን ሞት የመስቀል ሞት ነው። ጳውሎስ ያያያዘው የክርስቶስ እርግማን መሆን ይህ ስለ እኛ የሞተው ሞት ነው። ጳውሎስ በገላ. 3፥10-13 የጠቀሳቸው ሁለት የተረገሙ ክፍሎች ይገኛሉ፤ አንዱ ሕግን ጠብቀው መዳን ያልቻሉት፥ በሕግ መጽሐፍ በተጻፈው ጸንተው የማይኖሩትና የማያደርጉት ናቸው። ይህ ሰውን ሁሉ የሚሸፍን እርግማን ነው። ማንም ሕግን ፈጽሞ ተጠንቅቆ ጠብቆ የዳነ ፍጹም ሰው የለም። ስለዚህ ሕጉ እኛንም ጨምሮ ሁሉንም ከእርግማን በታች ያስቀምጠዋል። ሁለተኛው ክርስቶስ ነው። እርሱ ደግሞ ሕግን ሁሉ ስለ እኛ ፈጽሞ በፈንታችን የተሰቀለውና እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ወይም ኩነኔ ወይም ፍርድ የዋጀን ነው። ጌታ በመስቀል ላይ የተሸከመው የራሱ ኃጢአት አልነበረውም። የራሱ እርግማንም አልነበረውም። ነገር ግን የእኛን ኃጢአት በመውሰድ በፈንታችን፥ በምትካችን በመሞት በእንጨት የተሰቀለው እርግማን ሆነ። ይህን በማድረግም ዋጀን፤ ሙሉ ዋጋ ከፍሎ መልሶ ገዛን። ጌታ ስለ እኛ እርግማን የሆነው፥ በእንጨት ላይ የሚሰቀል የተረገመ እንደሆነ ሆኖልን የእኛን ኃጢአት በመስቀል ላይ በመሸከሙ ነው። ጴጥሮስም በ1ጴጥ. 2፥24 ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ ይለናል። ክርስቶስ ኃጢአታችንን በእንጨት (በመስቀል) ላይ መሸከሙ የኛን እርግማን የተሸከመ ሰው የሆነ አምላክ እንጂ ሰይጣን አያደርገውም። “ፖዝ” በግልጥ ያልተናገረውና ጋዜጠኛዋም በስሱ የጴጥሮስን አሳብ ምንነት ከመናገር ባለማለፍ እንዲገልጥ ያላደረገችው ነጥብ፥ 'በእርግጥ ጴጥሮስ ሰይጥኖ ነበር ወይ?' የሚለው ነው። እንደ ፖዝ ሰፊ ግን ግልጽ ያልሆነ ማብራሪያ ጴጥሮስ የሰየጠነ ሲሆን ኢየሱስ ጴጥሮስን ከሰየጠነበት ለማውጣት መሰይጠን ኖሮበታል ማለት ነው። በተድበሰበሰ ቋንቋ የተላለፈው አሳብ ይህ ነው።

“እኔ እስከ መሰይጠን ድረስ ወርጄ ከሆነ ክርስቶስ እኔን ለመቤዠት እስከ መሰይጠን ሊመጣ ይችላል። ወርጄ ከሆነ። ሲዖል ወርዷል አይደለም? የወረዱ ስላሉ እንጂ ስለተሸነፈ ነው? የሰው ልጆች ኃጢአት ስለከበደው ነው ሲዖል የወረደው? የወረዱ ስላሉ የወረዱትን ለማውጣት አይደለም? እዚያ ጥግ ድረስ ሲወርድ እኛ እስከ መሰይጠን ዘር ወርደን ከሆነ መውረድ ግዴታው ነው። . . . [መሰይጠንን] ለምን ይህንን ቃል በስድብ መንፈስ ተረዳሽው? ለምን የመውረዱን ጥልቀት አትረጂውም? ለምን እዚያጋ [እርግማንጋ] በቃሽ? እርግማን ላይ ስለደረስን ነው ክርስቶስ እርግማን የሆነልን፤ ኃጢአት ላይ ስለደረስን ነው ክርስቶስ ኃጢአት የሆነልን፤ በሽታ ላይ ስለደረስን ነው የተገረፈው፤ ድህነት ላይ ስለደረስን ነው ድኃ የሆነው፤ ድኅነት ብቻ ቢሆን ድንበራችን እዚያ ላይ ይቆም ነበር፤ መሰጠን ላይ ደርሰን ከሆነ ቢሰጥን ምን ችግር አለው? ደርሰን ከሆነ፤ ከሆነ ነው የምልሽ። . . . ይሄ ፊደል [ሰየጠነ የሚለው] አንቺጋ ረክሶአል፤ እኔጋ አልረከሰም። ጴጥሮስን እስከመሰይጠን ያወረደ ቃል ካለ ጴጥሮስን ለመቤዠት ጌታዬ ልክ እርግማን እንደሆነ እዚህ ድረስ ወረደ ብል ኢየሱስ ሰይጣን ነው እያልኩ አይደለም፤ ሊቤዠው ሰውየው እስከወረደበት ጥግ ወርዷል እያልኩ ነው። አይምሯችን ውስጥ ግን ፊደሉ ረክሷል፤ ስለረከሰ፥ 'እንዴት ለጌታዬ ይህን እላለሁ [ሴጠነ እላለሁ] ብለሽ ፊደሉ ላይ ሙግት ጣልሽ ማለት ነው። ፖይንቱ ክርስቶስ እርግማንም የሆነው፥ ኃጢአትም የሆነው፥ በሽታም የተሸከመው፥ ድኃም የሆነው፥ ሁሉንም የወረድነውን ጥግ ለመሸፈን ነው።”

ፖዝ ከላይ በተወሰደው ክፍል ከጋዜጠኛዋ ጋር በከረረ ክርክር መሃል ነው እነዚህን ነገሮች የተናገራቸው። በመጀመሪያ፥ በግልጽ ክርስቶስ ሰየጠነ አላልኩም እያለ፣ ያሉትን ሰዎች ትክክል ናቸው ካለ፣ ምንም ልዩነት የለውም። እርሱ ሊል የፈለገውንና በቀጥታ ሊል ወኔና ድፍረት ያጣበትን አሳብ ወክለው እነዚያ ካሉለትና ይህ አባባላቸው ከተስማማው ይህ የቃል ሳይሆን የአቋም ጉዳይ ነውና ተስማምቶበታል ማለት ነው። ሁለተኛ ደግሞ በጥያቄ እንጂ በአቋም ደረጃ ግልጽ አድርጎ ያልተናገረውና 'ሰው እስከ መሰይጠን ደርሶ ከሆነ' ብሎ ሳይገልጥ የዘለለው፥ ጋዜጠኛዋም በግልጽ ያልጠየቀችው አቋሙ፣ የጴጥሮስ ወይም የሰዎች መሰይጠን ክርስቶስ እነርሱ የወረዱበት ጥግ ወይም እስከ መሰይጠን ድረስ አድርሶታል የሚል ነው። ንግግሩ 'ምን ያስገርማል? በሚል ሻሽ ቢሸበብም ቃሉ አቋሙን ያሳያል። ኢየሱስ ሰይጣን ሆነ ወይም የሰይጣንን ባሕርይ ተላበሰ የሚለው ትምህርት በፖዝ የተጀመረ አይደለም፤ በእርሱም አይደመደምም። ፖዝ የሚነዛው የትምህርቱ ዋና አቀንቃኝ የሆነውን አሜሪካዊውም ዊልያም ኬንየንን መርዘኛ ትምህርት ነው። ከላይ ባየነው በተናገረው ክፍል ራሱ የጠቀሰው ኬንየን ይህንን የሐሰት ትምህርት ካናኙት ሰዎች አንዱ ነው። ከዘመናዊው ካሪዝማዊ እንቅስቃሴ በፊት በዊልያም ኬንየን በኋላም፥ በተለይም ከቃል-እምነት አስተማሪዎች መካከል ኬነት ሄግን፣ ኬነት ኮፕላንድ፣ ፍሬድሪክ ፕራይስ፣ ቤኒ ሂን እና ሌሎችም ይህንን ትምህርት አስተምረውታል። ቤኒ ሂን፥ ‘He [Jesus] who is righteous by choice said, “The only way I can stop sin is by Me becoming it. I can’t just stop it by letting it touch Me; I and it must become one.” Hear this! He who is the nature of God became the nature of Satan where He became sin! ብሎ ነበር። “ጻድቁ ኢየሱስ ነው ይህን እንዳለ ቤኒ ሂን የተናገረው፥ ኃጢአትን ማስቆም የምችልበት መንገድ አንድ ብቻ ነው፤ ያም እኔ እርሱን በመሆን ነው፤ ኃጢአት እንዲነካኝ በመፍቀድ ሳይሆን እራሱን በመሆን ነው፤ ይህን ስሙ፤ የእግዚአብሔር ባሕርይ የነበረው ኢየሱስ የሰይጣንን ባሕርይ በመውሰድ ኃጢአት ሆነ።” ይህ የቤኒ ሂን ትምህርት ነው። ኢየሱስ የሰይጣንን ባሕርይ መውሰዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም። የቃል-እምነት አስተማሪዎች፥ 'ኢየሱስ የሰይጣንን ባሕርይ ስለተጋራ ዳግም መወለድ አስፈልጎት ነበር፤ በሞቱና በትንሣኤው መካከል ነው ይህን ዳግም ልደት ያገኘው' ይሉናል። በአገላለጣቸውና ግልብ በሆነ ቋንቋቸው ይህንን የሦስት ቀን ቆይታውን፥ ኢየሱስ እንዴት በሰይጣን መረብ እንደተያዘ፥ እንዴት እየተጎተተ በፊቱ እንደቀረበ፥ እንዴት በባለ ሦስት ቀስት መውጊያዎቻቸው እየጎነተሉትና እየወጉት እንደተሳለቁበት፥ ሲገልጡት በስፍራው አብረውት የነበሩ የዓይን ምስክሮች ይመስላሉ።

ፖዝ እንደነዚህ ሰዎች ገላጭ ቋንቋ አልተጠቀመም፤ እንዲያውም በግልጽም 'ሆነ' አላለም። "ቢሆን ምን ያስገርማል?" ነው ያለው። ይህ ስልቻና ቀልቀሎ ማለት ነው። ኢየሱስ ሰይጣን ቢሆን ምን ያስገርማል? ሞርመኖች ኢየሱስ የሉሲፈር መንፈሳዊ ወንድም ነበር ይላሉ። እኛም ጭምር እንደዚያ መሆናችንን ይነግሩናል። ኢየሱስና ሰይጣን ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ናቸው ማለታቸው ነው። ኢየሱስ ሰው የሆነው የሰውን ሰውነት በሥጋና ደም ለመካፈል በሥጋው ኃጢአታችንን ለመሸከም፥ በደሙም የበደላችንን ስርየት ለመፈጸም ነውና ሰይጣንም የሆነው የወንድሞቹን የሰይጣናትን ኃጢአት ሊሸከም ከሆነ አጋንንትም ድነዋላ?! እናም አጋንንት በደኅንነት በኩል ወንድሞቻችን ናቸዋ?! ከኛ ጋር ተደባልቀው በቤተ ክርስቲያናችን እየተገኙ የድንቆችና ምልክቶች ርችት እየተኮሱ ቢያጅቡን ሊያስደንቅ የተገባው ነገር አይደለማ?! ኢየሱስ ሰይጣን ቢሆን እንዴት አያስገርምም?! ዛሬ ሐሰተኛ ድንቆችና ምልክቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሰይጣን እንደማይደረግ ምን እርግጠኛ ያደርገናል? ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል፤ 2ቆሮ. 11፥14። ፖዝ የሚያሰማን፥ 'ቢሆንስ ምን ያስገርማል?' ወደ ሰይጣን ጎራ የምታስገባ ታናሽ እርምጃ ናት።

ለመሆኑ፥ በእውን ጴጥሮስ ራሱ ሰይጥኖ ነበር ወይ? እስኪ በቅዱስ ቃሉ ውስጥ የተጻፈውን በጥሞና እንመልከት። በማቴ. 16፥ 23 ላይ፥ እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው ብሎታል። እዚያው ቁጥር 18 ላይ ደግሞ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም ብሎታል። እንግዲህ የዮና ልጅ ስምዖን ጴጥሮስ ወይም ዓለት ነው? ወይስ ሰይጣን? ወይስ እነዚህ ስሞች መግለጫዎች ናቸው? ጴጥሮስ 'ዓለት' የተባለው፥ 'አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ' በማለቱ እንጂ ድንጋይ ስለሆነ አይደለም። እንደዚሁ ሁሉ፥ 'ሰይጣን' የተባለውም፥ አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ስለጀመረ ነው እንጂ ጴጥሮስ በዚያች ቅጽበት ወደ ሰይጣንነት ተለውጦ ስለነበረ ወይም ስለሰየጠነ አይደለም። አይሁንብህ፥ ይህ አይደርስብህም ያለው ጌታ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበል እንደሚሞትና እንደሚነሣ ሲናገር ነው። ጌታ የመጣበትና ደጋግሞ ይናገር የነበረው ዋና ግቡ ይህ ነበር። ይህንን አውቆም ይሁን አዝኖለት በጥብቅ መቃወም የእግዚአብሔርን አሳብ መቃወም ነው። የእግዚአብሔርን አሳብ መቃወም ደግሞ የሰይጣንን አሳብ ማገልገል ነው። የሰይጣንን አሳብ ማገልገል ሰይጣንነት አይደለም፤ የእግዚአብሔርን አሳብ ማገልገል እግዚአብሔርነት እንዳልሆነ ሁሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በመሰለ ገላጭና ስዕላዊ ቋንቋ የተሞላ ነው። ለምሳሌ፥ 'እናንተ የእፉኝት ልጆች' (ማቴ. 12፥34፤ 23፥33)፤ ወይም፥ 'ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው' (ዮሐ. 6፥70)፤ ወይም፥ 'እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ' (ዮሐ. 8፥44)፤ ሲል ተመሳሳይ ቋንቋ መጠቀሙና የሰዎቹን ግብር ማመልከቱ እንጂ በቀጥታ እነዚያ ሰዎች እነዚያን ነገሮች ናቸው ማለት አይደለም። ጴጥሮስ ሰይጣን አልሆነም፤ ሰይጣንም አልገባበትም። ቢገባበትማ ያወጣለት ነበር እንጂ ሰይጣን የገባበትን ወይም ሰይጣን የሆነ ሰውን የመንጋው ሹም አያደርገውም ነበር።

ይቀጥላል