አታክርር፣ በማስተዋል ሚዛን ጠብ

“ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች” ብሎ አያቆምም፤ “እንዲሁ በምድር ትሁን” ይላል። በዓለም ናችሁ፣ ከዓለም ግን አይደላችሁም ብሏል … ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ … ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። [ቀጥሎ] ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው ይላል። … ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና … መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤ ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና [ማቴዎስ 28፡18። ሮሜ 13፡1-4]

ገዥዎች ክፉ ሲያደርጉ፣ ሕዝብ ሲያስፈራሩ፣ ለእግዚአብሔርም ለሰውም ተጠሪ እንዳልሆኑ ሲመስላቸው፤ የቤተክርስቲያን ምላሽ ምን ሊሆን ይገባል? ገዥዎች በሚገዙት ሕዝብ ላይ አላግባብ ሰይፍ ሲያነሱ፣ ክፉ አድራጊዎች ተመስግነው መልካም ያደረጉ ሲዋረዱ፣ ገዥዎች ራሳቸውን ከህግ በላይ ሲያደርጉ፤ በአምላክ አምሳል የተፈጠረውን ሲከፋፍሉ፣ ሲበድሉ ቤተክርስቲያን ያላት አማራጭ ዝምታ ብቻ ነው? ዝምታስ ከመተባበርና ከመስማማት በምን ይለያል?

scalesሚዛን አለመጠበቅ በብዛት ያታያል። ፖለቲካ ውስጥ አንግባ ከሚሉት አንዳንዶቹ የመንግሥትን በደል መቃወም እንጂ ማሞገስ ፖለቲካ የማይመስላቸው ናቸው። ለሚፈርስ ሥጋ ለሚያልፍ ዓለም መጨነቅ አያስፈልግም፤ እኛ ሰማያዊ ዜጎች ነን፤ የተጠራነው ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለማግባት ነው ይላሉ። የመንግሥት ውለታ አለብን ይላሉ። በጎ በጎውን ብቻ እናውራ፤ ለወቀሳ ጊዜ የለንም ይላሉ። አምስት መቶ ዜጋ ሞተ ከማለት፣ አምስት ሚሊዮን ሕጻናት ተከተቡ እንበል ይላሉ።

ስለ መንግሥት፣ ስለ ቤተ እምነት እና ስለ ማኅበራዊ ጉዳይ ምንነትና ግንኙነት በሁሉም ዘንድ የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል። “መንፈስ ብቻ” እና “ቁስ ብቻ” የተቃረነና የሳተ አመለካከት ነው፤ ስለ ጽድቅ፣ ስለ ቅድስና፤ በመንፈስና በአእምሮ ስለ ማደግ፣ ስለ ሰማያዊና ስለ ምድራዊ ያሉንን አመለካከቶች የሚያዛባ ነው። ወንጌል “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን” በማለቱ ለአንዴና ለመጨረሻ የተነጣጠለውን ማንነት በራሱ ቤዛነት አስታርቋል [ዮሐንስ 1:14፤ ኤፌሶን 2:15-17፤ ቆላስይስ 1:16-17] እርግጥ አማንያን ሁሉ ስለ ቤተክርስቲያንና ስለ መንግሥት ያላቸው መረዳት አንድ ወጥ ሊሆን አይችልም። ያም ሆኖ ከሞተላትና ከሙታን ከተነሳው፣ ሊሰበስባት ከሚመለሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ጌታ እንደሌላት ተጠሪነቷም ለርሱ ብቻ እንደሆነ የማታምን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በምድራችን የለችም። ያም ሆኖ መንግሥት ከሕዝብ የተለየ አለመሆኑን ብዙዎች አያስተውሉም። መንግሥት በውልደትና በአፈሙዝ ሲፈራረቅ መኖሩ ለዚህ ባህል መንስኤ ሆኗል። ከዚህ ለመላቀቅ፣ ጊዜና ትሑት አርቆ አሳቢ መሪን ይጠይቃል።

ብዙዎች ትምህርት ቤቶችን ክሊኒኮችን ማቋቋም ለመንግሥት ግዴታው እንደሆነ አያስቡም፤ ውለታ እንደተደረገላቸው ይቆጥራሉ። ጥርጊያ መንገዶች በሕዝብ ታክስ፣ በሕዝብ ጉልበትና በሕዝብ ስም በተገኘ ብድር እንደ ተገነቡ ብዙዎች አያስቡም። ባለሥልጣናት ሕዝብ ይህን መብቱን እንዲያውቅ አይሹም፤ ደጅ መጥናቱንና ማስጠናቱን ይፈልጉታል። ሕዝብ ከእውቀት ማነስ የተነሳ ደጅ መጥናት የኃይማኖቱ አንድ ገጽታ ይመስለዋል። መንግሥት የሕዝብ ከበሬታ የሚያገኘው የተቀበለውን አደራ በቅንነት ተግባራዊ ባደረገ መጠን ነው። ለመሆኑ በፍትሓዊ አመራሩና በቅንነቱ የሚታወስ ከበሬታ ያገኘ መሪና መንግሥት በታሪካችን አለ? አገር ቀን የጣለላቸው የባለሥልጣኖችና ባለሥልጣኖች የፈቀዱላቸው የጥቂቶች እንጂ የሁሉም እንደሆነች ብዙዎች አያስቡም። መንግሥት ኮንዶሚኒየም ሠርቶ በዕጣ እስኪያድል ይጠብቃል እንጂ የብድር አሠጣጥ ሥርዓቱ ለምን የመንግሥት እጅ ሳይገባበት እንዳልተመቻቸ፣ ለምን ለሁሉም ዜጋ እኩል እንደማይሠራ አይጠይቅም። ህገመንግሥቱን በሚገባ ስለማያውቅ መብትና ግዴታውን አልለየም። ምን ዋጋ አለው፣ ወረቀት ብቻ ነው በሚል ተስፋ በቆረጠ ዐይን ይቃኘዋል። የጋራ በሆነች ምድር እያንዳንዱ ድምጹን ቢያሰማና ቢሳተፍ ለውጥ እንደሚመጣ አይገምትም። የብዙኃን ተሳትፎ የሌለበት ማህበረሰብ ዕድገቱ እንደሚቀጭጭ ሳይታለም የተፈታ ነው። ዜጋ የመንግሥት እጅ ሳይገባበት በራሱ ጥረት እንዲያደርግ ቢመቻችለት ለመንግሥትም ሸክሙ ይቀልለት ነበር፤ መንግሥት መመሪያዎችን ከማውጣትና ከማስከበር ውጭ በየጥቃቅኑ ጣልቃ መግባቱ ለምናየው ዝርክርክነትና ምዝበራ ዋነኛ ምክንያት ነው። ጥቂቶች ከብዙኃን አፍ ነጥቀው ሲንደላቀቁ፣ ብዙኃኑ በገዛ አገሩ ድርሻውን ተነጥቆ ለድህነትና ለመከራ ሲዳረግ የመከራው ምንጭ ምን እንደሆነ ሳይጠየቅ ምግብና መጠለያ ማቅረብ ብቻውን ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። የሕዝብ ንብረት የመዘበሩ ወደ ፍርድ ፊት ሳይቀርቡ ፍትሕ ይኖራል ማለት ራስን መደለል ነው። እያንዳንዱ በገዛ አገሩ ጉዳይ ሳይቆጠብና ሳይፈራ ድምጹን ቢያሰማ አገር ትለማለች፤ ቢቆጠብ ግን ጉዳቱ ለሁሉም ነው። በዚህ ሁሉ የአማንያን ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል? የቤተክርስቲያንስ?

ዜጋና ቤተክርስቲያን በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለሚኖራቸው ድርሻ በኢትዮፕያንቸርች ድረ ገጽና በ [እንግሊዝኛ] ብሎግ መጻፍ ከጀመርን አስር ዓመት አልፎናል። ሌሎችን ለማሳተፍ ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም ብለን እንለፈው። ለዚህ ምክንያቶቹ የፖለቲካን ምንነት አለማወቅ ነው፣ ፍርኃት ነው፣ ምክንያት ማብዛት፣ ፈቃደኛ አለመሆን፣ ፖለቲካን ከሸርና ከትጥቅ ትግል ጋር ማያያዝ፣ ተቃዋሚ ላለመባል፣ የዜግነትን መብትና ግዴታ፣ ህገ መንግሥቱን አጥርቶ አለማወቅ፣ የቤተክርስቲያንን ተልዕኮ ቆንጽሎ ማየት፣ ስለ መንፈሳዊው ከለትለት ባላለፈ ጠባብ አመለካከት መኖር፤ አንዱ ከሌላው ጋር ትብብርና የጋራ አቋም አለመፍጠር፤ ያልተመረመረና ወንጌልን ያላገናዘበ አስተምህሮ፣ መንፈሳዊነትና ፍትሓዊ አስተዳደር እንደማይነጣጠሉና እንደሚጠባበቁ አለመገንዘብ ጥቂቶቹ ናቸው።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አለአግባብ መገደላቸውና በገዛ አገራቸው ታድነው “ህጋዊ እርምጃ” እንዲወሰድባቸው መደረጉ ያስከተለው ድንጋጤና ቊጣ አንዳንዶችን በብዙኃን መገናኛ ስሜታቸውን እንዲገልጹ አስገድዷቸዋል። አገር ቤት ያሉ መሪዎች ሌላ ለማለት ባይደፍሩም፣ መንግሥት ሕዝብ ተርቧል፣ በሁሉም እርከን አስተዳደሩ ተበላሽቷል፣ የሕዝብ ንብረት ዘረፋ ብሶበታል በሚልበት ሰዓት፤ “የለም፣ የሰላምና የበረከት ዓመት ነው” ብለው የሚተነብዩትን ወረፍ እያደረጉ ይገኛሉ። አንዳንዶች በቴሌኮንፈረንስ፣ በፌስቡክና ፓልቶክ ሹክሹክታ አሰምተዋል። ኢትዮፕያንቸርች በአውሮጳ ከ 2006 ጀምሮ በዚህ ርዕስ ላይ የለጠፍናቸውን እዚህ እና እዚህ ይመልከቱ። የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ነሐሴ 26/2008 ዓ.ም “ስለ ወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳይ” በሚል ርዕስ ባለ 3-ገጽ የአቋም መግለጫ አውጥታለች። ወንጌላዊ ያሬድ “ለክቡር ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ” ከአሜሪካ በላከው ደብዳቤ ላይ “ዛሬ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍሎት በልብ ጭንቀትና በብዙ ዕንባ ነው” ካለ በኋላ “ከሰሞኑ በእርሶ አንደበት የተነገረውንና የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ” የታዘዘው አግባብ እንዳልሆነና “በእግዚአብሔር፣ በሰውና በኅሊናዎ ዘንድ ከፍተኛ ተጠያቂነት” ያመጣብዎታል ሲል ኃዘኑን ገልጿል። ወንጌላዊ ያሬድ ጠ/ሚንስትር ኃ/ማርያም ክርስቲያን ነኝ ማለታቸው ምናልባት ለመፍትሔ ያቃርብ እንደሆነ ተስፋ እንዳደረገ ያስታውቃል። ቄስ ዶ/ር ቶለሳ ጉዲና ከአትላንታ አሜሪካ እሑድ መስከረም 22/2009 ዓ.ም ያሰሙትን ከታች ይመልከቱ። በቶሮንቶ ካናዳ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ዶ/ር ግርማ በቀለ መስከረም 30/2009 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያንና በወቅቱ የአገራችን የሰላም ሁኔታ ውስጥ “የክርስቲያኖች ኃላፊነትና ድርሻ ምንድነው?” በሚል ጥያቄ ዙሪያ የመጀመሪያውን ክፍል “ምጋቤያዊ ደብዳቤ” አስነብበዋል። ሃያ አምስት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በካናዳ እንደዚሁ ጥቅምት 1/2009 ዓ.ም “የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ” ለጥፏል። በመጨረሻ፣ ፓስተር ዘላለም መንግሥቱ “መንግሥት፣ ቤተ/ክ እና ደቀመዝሙር፤” በሚል ርዕስ ሁሉ ሊያነብበውና ሊወያይበት የተገባ ባለ-17 ገጽ ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጅተዋል [ጥቅምት 2009/ ዕዝራ ቁ. 37]። ጽሑፉን ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይጠይቁ።

ዋናው ጉዳይ አጣርቶ መነጋገሩና አጣርቶ መስማቱ ላይ ነው፤ ለአገሬ በጎ አሳብ አለኝ፤ አሳቤን ሳልቆጠብና ሳልፈራ መግለጽ አለብኝ። ያገባኛል፣ የኔ መሳተፍ ከሌሎች አሳብ ጋር ተደምሮ አንድ ውጤት ያስገኛል በሚል ተስፋ መሳተፍን ይጠይቃል። ከየትኛውም ወገን ውሸትና ጥላቻ የሚነዙትን ለይቶ ማወቅና እውነቱን አውቆ መግባባትን። ስለ ዜጋ እኩልነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ መብትና ግዴታ፣ ስለ ህግ የበላይነት፣ ስለ አገር አንድነት መነጋገር፣ በአንጻሩ ልዩነታችንን አጒልተው የሚከፋፍሉንን በተገኘ አጋጣሚ መቃወምና ተገቢ ምላሽ መስጠት፣ በሕዝብ ላይ በደል ያደረሱ ተገቢ ፍርድ እንዲሰጣቸው፣ አላግባብ የታሠሩ እንዲፈቱ ወዘተ ድምጽ ማሰማት ግድ ነው። ባጭሩ፣ ዝምታ ምን ያህል ቢሞገስ ከቸልተኛነትና ከክፉ ጋር ከመስማማት ተለይቶ አይታይም።

ቄስ ዶ/ር ቶለሳ ጉዲና በአትላንታ አሜሪካ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን እሑድ መስከረም 22/2009 የሰበኩት በፊደል ተለቅሞ እነሆ፦

“እጅ ከፍንጅ ስላልተያዝን፣ ማንም መስካሪ ስለሌለ ከወንጀል ከኃጢአት ነጻም ነን ማለት አይደለም። ጨለማ ለብሰን የዘራናቸውን የጥፋት እንክርዳዶች በጠራራ ፀሐይ በዓለም ዐይን ፊት ማጨድ እንዳለ እንዳትረሱ እንዳትረሱ [ጭብጨባ]። በአሁኑ ጊዜ በምድራችን እየሆነ ያለው የውስጥ ውጥረት አንድ ትክክል ያልሆነ በቤተ መንግሥት፣ በቤተ ክህነት፣ በቤተ ክርስቲያን በምድሪቷ ዜጎች ዘንድ ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ የሚያመለክት ነው - አንድ ትክክል ያልሆነ ነገር አለ … ማነው ትክክል የሆነውን ነገር የሚነግረን? … ለምህረትና ለምሪት ወደ እግዚአብሔር መመለስ የማስተዋል እንጂ የድካም ምልክቶች አይደሉም … ባልጠበቅነው መንገድ የምድሪቷ ጽዋ እየሞላ ስለሆነ ያለ እግዚአብሔር እርዳታ የሕዝቡን ብሶት ፀጥ የሚያሰኝ የለምና ለእርዳታ ወደ እግዚአብሔር መጮህ ምርጫ የለውም፤ ጽዋው ሞላ የሕዝቡ ብሶት እየተሰማ መጣ [ዩ ካንት ዱ ኤኒ ቲንግ አባውት ኢት]። ሰው ምንም ሊያደርግ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም መንግሥታት ቢሰበሰቡ ምንም ማድረግ አይችሉም። [ኢትስ ፊኒሽድ፣ ደን]። አሁን የሚያዋ የሚያዛልቀን የሚያዋጣን እግዚአብሔር ብቻ ነው እግዚአብሔር ይድረስልን በሉ፤ አዎ እግዚአብሔር ይድረስልን በሉ፣ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የብሔር ብሔረሰቦች የድብብቆሽ ዲፕሎማሲ ሳይሆን በልብ ግልጽነት በመደማመጥና በመቀራረብ በንስሃና በይቅርታ በመቀባበል በማያዳግም ሁኔታ ያለፈውን በመቅበር ለወደፊት በምህረትና በጽድቅ ላይ የተመሠረተ ሰላም - አዲስ ትውልድ ያስፈልገናል - ያለው ትውልድ ተበላሽቷል። ውስጡ ተበላሽቷል። ጤናማ አስተሳሰብ ያለው የለም፤ አዲስ ትውልድን እግዚአብሔር ይስጠን። ጥላቻና ዘረኝነት ያሰከረው ትውልድ ከብሔር ብሔሩ ጋር ጮቤ ካልረገጠ የዓለም መጨረሻ የሆነ ይመስለዋል። በቃ ሁሉ ነገር እዚሁ፤  ሁሉ ነገር ራሱ፤ ሁሉ ነገር ክልሉ ፤ አንድ ክልል ብሎ ወሰን፣ ቦታ ያ ክልል፤ ይኸ እብደት ነው። በዚያ ልንቀጥል አንችልም … በዚህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ግሎባላይዜሽን የዓለምን ዓለም አንድ ስንዝር ባደረገበት ወቅት ሰዎች ልዩነታቸውን አስወግደው ከኢኮኖሚ እድገት ድርሻቸውን ለመካፈልና ለልጆቻቸው የሥራ እድል ለመፍጠር ረጃጅም ድልድይ እየሠሩ ነው፤ ረጃጅም መንገድ እየተጓዙ ነው። እኛ እዚያው ልንጨራረስ ነው። እኛ እዚያው ልንጨራረስ ነው። ማንም ከምድሪቱ ሳይወጣ ያለፈለት? ማነው ያለፈለት? … እነ ኃይሌ ገብረሥላሴ … ከጎጃሞቹ ጋር ከወለጎቹ ጋር ከጉራጌዎቹ ጋር ቢወዳደሩ ኖሮ የት ይደርሱ ነበር? ትርፋቸው ምን ይሆን ነበር? ላብ ብቻ! [ሳቅ] እዚህ ግባ የማይባል ወረቀት ብቻ! ምን አደረጉ? ከዚያ ውልቅ ብለው ወጡና በዓለም ደረጃ በዓለም መድረክ ላይ መወዳደር ጀመሩና ካሉበት ድህነት ወጡ [የዘገየ ጭብጨባ] ዛሬ አእምሮ አለን? ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ነው፤ መውጣት አለብን። እዝችው እዝች ክልል ፈጥረን በክልሉ የምንገዳደልበት ምክንያት ምንድነው? ምን ለማትረፍ ነው ያን ከገደልክ? የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር ማስተዋል ይስጠን [አሜን!] … ከድንጋይ ትዝታ አልወጣንም … እግዚአብሔር የሰየመን መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠራን የዓለም ሕዝብ የሚያውቀን “ኢትዮጵያ” ብሎ ነው። ከዚያ ውጭ እኔ ሌላ ሰው አላውቅም [ደማቅ ጭብጨባ]። እነዚህ አማራ ትግሬ ኦሮሞ … የሚባሉ እነዚህ ጥቃቅን አምላኮች ም ማ እንዲያው ይኸ ጣዖቶች ተነስተው ሕዝብ የሚያፋጁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ቃል አልተጻፈላቸውም [መጽሐፍ ቅዱስ ከፍ አድርገው እያሳዩ] … እግዚአብሔር “ኢትዮጵያ” ብሎ ነው የሚጠራት … [ደማቅ ጭብጨባ፣ እልልታ… ታዳሚ ብድግ ብሎ ጭብጨባ] … ውጡ ከነዚህ ጥቃቅን ጣዖቶቻችሁ … ” [ነቢዩ ዳንኤል በመከራ ውስጥ ለነበረው ሕዝብ ያደረሰውን ጸሎት ጠቅሰው፣ ኖቬምበር 12/2016 እና እስከዚያ ድረስ ስለ ታቀደው የጾምና የጸሎት ፕሮግራም አስታውቀው ጨርሰዋል]።

የምድር ሁሉ ገዥ ሕያው እግዚአብሔር፣ የዳንኤል አምላክ፣ ሰላምን የሚወድዱ፣ ለሕዝብ የሚራሩ፣ ቅንና አስተዋይ መሪዎችን ያስነሳ!

ጥቅምት 29/2009 ዓ.ም [11/08/16]