እግዚአብሔር እንዲያረጋጋኝ ተንበርክኬ ጸለይኩ

mamo2ታሪክ ተመራማሪ፣ ተርጓሚና ፀሐፌ-ተውኔት ማሞ ውድነህ ባደረባቸው ህመም በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው በ 81 ዓመታቸው ዛሬ የአድዋ ጦርነት መታሰቢያ ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ማሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደ ጨረሱ ቀጥለው ለመማር እድሉ ስለ ጠበበባቸው በጋዜጠኛነት ተሠማሩ። ኋላም፣ የ ”ፖሊስና እርምጃው” ጋዜጣ መሥራችና ዋና አዘጋጅ፣ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚደንትና በሌሎችም ዘርፎች መሪና ተሳታፊ ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል። በጠቅላላ ከስድሳ በላይ መጻሕፍትን ያሳተሙና ገና ያልታተሙ ሥራዎችም እንዳሉዋቸው ይነገራል። ዲግሪ ያሳበደው፣ የስድስቱ ቀን ጦርነት፣ ካርቱም ሄዶ ቀረ፣ ጊለን የክፍለ ዘመኑ ሰላይ፣ ምጽኣተ እስራኤል፣ የኛ ሰው በደማስቆ፣ የበረሐው ተኩላ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ የካይሮው ጆሮ ጠቢ፣ ብዕር እንደዋዛ። የተሰኙትን መጻሕፍት ይዞ መታየት ምንኛ ክብር እንደነበረ ማን ይዘነጋል?

በ 1991 ዓ.ም. ፖል ዊሊያምስ ለተባለ የታሪክ ምሑር፣ ፋሺስት ጣልያን ወላጆቻቸውን በቦምብ ጣይ አይሮፕላን እንደ ገደለባቸው ማሞ ውድነህ ተናግረዋል። ይኸ ሲሆን የአምስት ዓመት ልጅ ነበርኩ ይላሉ። ከዓመታት ኋላ ለሥራ አሥመራ ሄደው፣ ከአንድ ጣልያን ሽማግሌ ጋር ስለ መካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሲያወጉ፣ የጣልያን አየር ኃይል አብራሪ እንደነበረና ከሙሶሊኒ ልጅ ጋር አብረው መዝመታቸውን በብዙ ኩራት ያጫውታቸው ጀመር። የዘመተበትንም አካባቢ ሲጠቃቅስ ቀዬአቸውን ከወላጆቻቸው ጭምር ያወደመ እርሱ ሆኖ ተገኘ። ማሞም ያለ ወላጅ ያስቀራቸውን እያዩ መታገሥ ቢሳናቸው ሳያስጨርሱት ሽጉጥ ለማምጣት ወደ አልቤርጎአቸው አመሩ። እንደደረስኩ፣ ተንበርክኬ እግዚአብሔር እንዲያረጋጋኝ ጸለይኩ ይላሉ። እግዚአብሔርም፦ አሁን ይህን ሰው ብታጠፋው ፋሺስት ያረገውን ከመድገም ወዲያ ወላጆችህን አትመልሳቸው፤ ያንተስ ቤተሰብ ምን ላይ ይወድቃል? እንዳላቸውና አሳባቸውን እንዳስቀየራቸው ገልጸዋል። በነጋታው አግኝቼው፦ “ትናንት የነገርኸኝ ታሪክ እኮ በጣም የሚገርም ነው፣ ለካንስ አንተ ኖረሃል መንደሬን አውድመህ ያለ እናት ያስቀረኸኝ” እንዳልኩ፣ ሽማግሌው ተደናግጦ ፊቱ ተለዋወጠ። በማስከተል፣ እኔ ግን ይቅር ብዬሃለሁ ስለው፣ ዕንባ ባቀረሩ ዓይኖቹ እያየ አቅፎ ሳመኝ ብለዋል።  

የጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ሞት የሁላችን ኅዘን ቢሆንም፣ ለትውልድ የሚተርፍ አርኣያነታቸውን በዚህ ወቅት ማስታወስ ይገባል። በመጀመሪያ ትጋት የሚያስገኘውን ውጤት እንመለከታለን። ራሱን በራሱ ታትሮ ያስተማረ፣ በሁኔታዎች አለመሟላት ያላመካኘና ያልተበገረ ሰው እነሆ። ሁለተኛ፣ ቂምና ቁርሾ በበረከተበት በዚህ ዘመን ስለ እግዚአብሔር ይቅር ማለትና ይቅርታ መጠየቅ የሚያስገኘውን ግላዊና ማኅበራዊ ነጻነት። ሦስተኛ፣ አስተሳሰብን ማስፋት፣ አብሮ ለመኖር፣ የራስ የሆነውን ለማክበር ብሎም ከመንደርተኛነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ ዓይነተኛ ተግባር እንደሆነ። በመጨረሻም፣ በዜጎችና በአገር መሪዎች ዘንድ ሕዝቡን በቅንነት ያገለገሉ ተረስተውና ተጥለው እንዳይገኙ ተገቢ አክብሮትና እንክብካቤ ማሳየት  እንደሚያሻ። እግዚአብሔር ያዘኑትን ሁሉ ያጽና፣ ያጽናና።      2/3/2012