ርዕሰ አንቀጽ

በኢየሱስ ሕይወት የተገመደ አይበጠስም

ማርያምና ዮሴፍ ለመሲሑ የሕይወታቸውን መንገድ ባይለቁ ኖሮ የሚያስታውሳቸው ባልተገኘ።  በእስራኤል ምድር ብዙ መንደሮች ነበሩ፤ ኢየሱስ ስለ ተወለደባት ብቻ አናሳዋ ቤተ ልሔም ከበረች። መሲሑ ቀርቦ ሳለ ያላስተዋሉ ጠቢባንና ኃያላን በኢየሩሳሌም ነበሩ፤ ኢየሱስን በማየት ግን ከምሥራቅ የተጓዙ ቀደሙአቸው። ብዙ አገሮች ነበሩ፤ ከሄሮድስ ጭከና መሸሸጊያ የሆነች ግን ግብፅ ነበረች። የእስራኤል ጠባቂና እረኛ በመምጣቱ ተንቀው በጭለማ የኖሩ እረኞች ታሰቡ። ዕድሜና ኑሮ ያንገላታቸው በኢየሩሳሌም ብዙ ነበሩ፤ በጾም በጸሎት የተጉ ስምዖንና ሐና ግን የእስራኤልን ተስፋ አዩ።

ባላገሮችና አሳ አጥማጆች ነበሩ፤ ቤተሰብ መረብ ሳይሉ ከኢየሱስ ጋር ዕጣቸውን የጣሉ የነፍሳት ነዶ ተሸክመው በእግዚአብሔርና በሰው ታሪክ ውስጥ የክብር ሥፍራ ተቀዳጁ። ስመ ጥር መምህር ገማልያል ካሠለጠናቸው መካከል አንዱ ሳዖል ነበር፤ ሌሎቹ ወዴት ደረሱ? ከማቴዎስ ጋር ሌሎች ቀረጥ ሰብሳቢዎች አልነበሩም? ከሉቃስ ሌላ ሐኪሞች፣ ከልድያ ሌላ ሐብታም ነጋዴዎች አልነበሩም? እነዚህ ሁሉ መታሰቢያቸው ወዴት ደረሰ? በኢየሱስ ሕይወት ታሪካቸው የተገመደ ግን ዘመን አልፎም እንኳ በረቱ እንጂ አልተቆረጡም። ነቀፌታ ሳይበግራት በራሱ ላይ ውድ ሽቱ ላፈሰሰች ኢየሱስ መሰከረ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፣ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይሰበካል” [ማርቆስ 14፡9]። ለሚያምኑ ማረጋገጫ ሰጠ፦ “የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” [ዮሐንስ 11፡25-26]። ጸለየ፦ “አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ [ዮሐንስ 17፡21]።

ሞት ሌጣ ክር ነው፤ አለመገመድ ነው፤ መበጠስ ነው። በኢየሱስ ሕይወት መገመድ ግን ተስፋና ደስታ ደህንነትና ሰላም የዘላለም ሕይወት ነው። እንዲህ ዓይነቱን ተስፋ ያገኘ፣ “ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፣ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ” እያለ አይሰጋም [ኢሳ 38፡12]። ይልቁን፣ ከኢዮብ ጋር፦ እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል፣ ይላል [19፡25-27]። እንደ ጳውሎስ ይላል፦ “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን” [2ኛ ቆሮንቶስ 5፡1-5]። እንደ ማርያም ይላል፦ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል” [ሉቃስ 1፡46-55]። ከዮሐንስ ጋራ ፍጻሜውን ይቃኛል፦ “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም። እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ። አለኝም። ተፈጽሞአል። አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ። ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” [ራእይ 21፡1-7]።

በኢየሱስ ሕይወት የተገመደ አይበጠስም፤ ፍጻሜውም የተረጋገጠ ነው። ሕይወቴ በኢየሱስ ሕይወት ተገምዷል ወይስ ሌጣ ነው? የጌታ ልደት በአንድ መልኩ ይህን ጠያቂ ነው። “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች …ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት፣ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” [ዮሐንስ 1፡3፣4፣12]። 

የእግዚአብሔርን ስጦታ፣ ኢየሱስን ስለ ተቀበሉ ስማቸው በሕይወት መዝገብ የተጻፈ፣ ሰው የማያውቃቸው፣ እግዚአብሔር ያወቃቸውና እግዚአብሔርን ያወቁ ብዙዎች ደግሞ አሉ።

ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድራችን ለሰውም ሁሉ በጎ ፈቃድ።