ርዕሰ አንቀጽ

ባይን የገባ ዐይን አወጣ

ባለፈው ወር “ቢግ ብራዘር” የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ ነበር። ፕሮግራሙ ጨርሶ የማይተዋወቁ ወንዶችና ሴቶችን በብልጽግናና በታዋቂነት ተስፋ እያደፋፈረ በአንድ አካባቢ የሚያከርም ውድድር ነው። በዚህ ዓመት ከአገራችን የተመረጡት ቤቲና ባምላክ ናቸው። ለዚህ ጽሑፍ ቤቲ መነሻ ትሁን እንጂ ከቤቲና ከባምላክ ሌላ ሌሎችም ተወዳድረው እንዳልተሳካላቸው አንርሣ። ውድድሩ በአደባባይ ግብረ ስጋ መፈጸምን ይጨምራል። አሸናፊ 300 ሺህ ዶላር ሽልማትና በቪዲዮና በድረገጽ እውቅና ያገኛል። ቤቲ በገንዘቡ የቱሪስት አስጎብኚ ድርጅት እንደምታቋቁም ተናግራለች። የ26 ዓመቷ ወጣት በመምህር ደመወዝ ብቻ ከመኖር እንደ እነ ቤትልሔም ጥላሁን የራሷን ንግድ ማቋቋም አሳብ ነበራት። እንዳሰበችው አላሸነፈችም፤ አድራጎቷም ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶባታል። እናቷ እናት ናቸውና ልጄን አትንኩብኝ ብለዋል። ቤቲ ግን ለ”ማለፊያ” ራዲዮ በሰጠችው ቃለ ምልልስ አገራችንን ለማስተዋወቅ ያደረግሁት ብዙው ተረስቶ በ”ትንሿ ነገር” ላይ እንዲህ ማተኮር አግባብ አይደለም ብላለች።  ወጣት ባምላክ የተፈጠረውን ተቃውሞ በማጤን ይመስላል ሙሉ ተሳትፎ ሳያደርግ ተገልሏል።

ብዙ ሰው ከማዘንና ከማፈር አልፎ ቁጣውን እየገለጸ ነው። ጥቂቶች ግን ማንም አያገባውም፤ ኢየሱስ እንኳ በዝሙት ከሥሰው ያመጧትን “ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” ነው ያለው፤ ስለዚህ ኃጢአት የሌለብን ስለሌለን መውቀስ አንችልም ብለዋል። እነዚህ የዘነጉት የሴትየዋ ከሳሾች ዓላማቸው ኢየሱስን በተንኮል ማጥመድ መሆኑን ነው። ተወግራ ትሙት ቢል፣ “የኃጢአተኞች ወዳጅ” የሆነውን በሕዝብ ዘንድ ሊያስጠሉት፤ አይሁድ የሞት ቅጣት እንዲፈጽሙ ህግ ስለማይፈቅድላቸው ከሮም መንግሥት ጋር ሊያጣሉት። አትወገር ቢል የሙሴን ህግ አፈረሰ ሊሉ። “ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ” ማለቱ ርህራሄና ይቅርታ ብቻ ሳይሆን ማስጠንቀቂያም ጭምር መሆኑን እነዚሁ ይዘነጋሉ። “እኔም አልፈርድብሽም” ማለቱ ባድራጎትሽ እስማማለሁ ማለቱ ሳይሆን፣ ይልቅ የወደቁትን ማንሳትና ማጽናት እንደሚወድ ያሳያል። የኢየሱስ ቃል ለቤቲም ለያንዳንዳችንም አንድ ነው፤ በበደላችን ተጸጽተን ስንቀርበው ከወደቅንበት ያነሳናል፣ በጓዳ ይሁን በአደባባይ ከታወቀ በደላችን አንጽቶ አዲስ ሕይወት ያጎናጽፈናል። ምሕረቱ ከቁጣው ትቀድማለች፣ ፍጥረታችንን ስለሚያውቅ ይታገሠናል ማለት እንጂ እንዳፈቀደን እየኖርን አይፈርድም ማለት እንዳይደለ መገንዘብም ይበጃል። የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ እንደ ነበርን እንድንቀጥል ሳይሆን ከኃጢአት እስራት ነጻ እንድንወጣ ነው፤ ወደ ሰላሙና ወደ ጽድቅ መንገድ እንድንገባ ነው።

ለመሆኑ፣ ሽልማቱ 10 ዶላር ቢሆን ኖሮ ስንቶች ይወዳደሩ ነበር? ለገንዘብ ሲሉ ክብራቸውን የማይጥሉ ቃላቸውን የማያጥፉ ስንት ይገኙ ይሆኑ? ቤቲ የተማረችና የወጣቶች መምህርት መሆኗ ስለ አገራችን ትምህርትና ማህበራዊ ስነ ምግባር ምን ያስረዳናል? ሦስት መቶ ሺህ ዶላር ብታሸንፍ ኖሮስ ከሚከሷት ስንቶች ይሆኑ ቀዝቀዝ የሚሉ? ልታቋቁም ባሰበችው የንግድ ሥራ ውስጥ ተቀጥረው ለመሥራት የሚሰባበሩስ? የቤቲ ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው። የተገኘነው ከአንድ ማህበረሰብ ነውና በርሷ ውስጥ የምናየው ራሳችንን ነው። አድራጎቷን ማህበራዊ በደል የሚያደርገውም ይኸው ነው። ማህበረሰብ የስነ ምግባርና የሐፍረት ድንበር በማበጀት ህልውናውን ያስከብራል፤ የሚተላለፍ ማህበርተኛውን በማግለል ይቀጣል፤ እንዲህ በማድረጉም ከመበታተን ይድናል።  በአንጻሩ፣ በሌላው መብት አያገባንም የሚሉ የግል ወይም ማህበራዊ መብት ምን እንደ ሆነ ያላወቁ፣ መብት ግዴታንም እንደሚጨምር ያልተገነዘቡ ናቸው። “ሁሉም እንዳፈቀደ ይሁን” ስብዕናን፣ ቤተሰብንና አገርን የሚያፈርስ ነው። ገደብ የለሽ ነጻነት ብሎ የለም፤ ገደብ በሌለው ነጻነት የተመሠረተና የጸና አንድም ሕዝብ በታሪክ ውስጥ አይገኝም። የቤቲ አድራጎት ከ15 ዓመት በፊት አይደፈርም ነበር፤ ከ30 ዓመት በፊትማ ጨርሶ አይታሰብም። ቤቲ የገንዘብ ፍቅር አሳውሯት ተታልላለች እንበል።

ድርጊቷ ያስቆጣቸው ብዙሃን“ወግ አጥባቂ” የሚል ስም ወጥቶላቸዋል። ባዮቹም ከቃላቸው ብዛት “ነውር አጥባቂ” መስለዋል። ሌላ ስንት አንገብጋቢ ጉዳይ እያለ ለዚህ ጊዜ ማጥፋት አይገባም ብለው የሚያንኳስሱ አሉ። ሌሎች ደግሞ ተስፋ በቆረጠ ልብ፣ የወሲብና ስነ ምግባር መፋለስ በአገር ደረጃ ሥር የሰደደ ስለሆነ ላያስቆም መጯጯህ ምን ፋይዳ አለው? ይላሉ። ፋሲል የተባለ ጸሐፊ በዘሐበሻ መጽሔት ላይ [ጁን 13/2013] የጻፈው ምናልባት አብዛኛውን አስተያየት ስለሚወክል እንጠቅሰዋለን፦

ቤቲ አንዲት ኢትዮጵያዊ እህታችን በሃገራችን ያለውን ባህላዊ፣ ማህበረሰባዊ እና ስነልቦናዊ ጫናዎችን ተቋቁማ በዚህ መድረክ ላይ በመሳተፏ አድናቆት ይገባታል። በመዘናጋት ትንሽ መጠኑ ከፍ ያለና ባታደርገው ሁላችንም የምንመርጠው ነገር ግን ሁሌም እኛ ባሰብነው ብቻ  ሳይሆን ባላሰብነው መንገድ ነገሮች ተከስተው ቤቲ ይህንን ነገር ብታደርግም ምንም ማለት ያልሆነና  ቀጣይ ቆይታዋ የተሳካ  ሆኖላት ጥሩ ውጤት እንድታመጣ ሁላችንም ከጎኗ ልንሆንላት ይገባል። ወደድንም ጠላንም ቤቲ የኛው እህት፣ የኛው ልጃችን ናት። እንደስህተትም ከተቆጠረባት የሚሰራ ሰው ይሳሳታልና ስህተቷን አስተካክላ ነገ  የተሻለ ስብእና እንዲኖራት ሁላችንም ከጎኗ እንሁን። ስሜቷን ከሚጎዱ መንፈሷን ከሚረብሹ ድርጊቶች ተቆጥበን በሰላም ተቀብለን የቀድሞ ህይወቷን ምንም ባለመሳቀቅ እንድትቀጥል እንርዳት እላለሁ።”

በጥቁር ፈረንጅቱ ዘፋኝና ልቅ ተወዛዋዥ ብዮንሴ አስታክከን ይህን ጉዳይ እስቲ እንመዝን። እንደሚታወቀው በ99 ብዮንሴ ምድራችንን ጎብኝታ ነበር። ጉብኝቷ በያኔ ሃያ ዓመቷ ወጣት ቤቲና እኩዮቿ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን እንበል። ባይን የገባ ልብ ያሸፍታል እንበል። ጄምስ ብራውን [አፍሮ፣ ቤልቦተምና ፕላትፎርም ጫማ] ቀጥሎ ማይክል ጃክሰን [እንደ ፍየል ኩልኩልት ግንባር ላይ የምትንጠለጠል ጠጉርና ጥቁር ጃኬት] ከቀደመው ትውልድ ብዙ ተከታይ አፍርተው ነበር። የብዮንሴን ልዩ የሚያደርገው ሦስት ነገር ነው። አንዱ፣ ማህበራዊ ልቅነትና ቴክኖሎጂ ዓለምን ከዳር ዳር ባያያዘበት ሰዓት ላይ መገኘታችን። ሁለተኛ፣ የአርባ ዓመትና በታች ወጣት ቁጥር 85 በመቶ ያህል መድረሱና ዕድል የጠበበት መሆኑ። ሦስተኛ፣ የስነ ምግባር አእማድ ተቋማት [ቤተሰብ፣ ቤተ ክህነት፣ ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት አመራሩ] ለአድራጎቷ ያልታሰበ ድምቀትና ድጋፍ መጨመራቸው ነው።

ብዮንሴ ሀብታም፣ ታዋቂና ቆንጆ ትሁን እንጂ በስነ ምግባር ደረጃ ለኢትዮጵያ ወጣት አርኣያ ልትሆን ይቅርና ልትታሰብ አይገባም። ካሳተመችው ሲዲዎች አንዱ የክርስቶስን መስቀል የሚያቃልል ነው። የተቀረው በውዝዋዜ ሽፋን ፍትወትን የሚያገንን ነው። የቋንቋ ድብልቅልቅ፣ ዕጽ ተጠቃሚና ኤድስ ተበራክቶ ከውዝዋዜዋ ምን በጎ ፍሬ ይለቀማል? በሊቢያው ገዢ ጋዳፊ ቤተሰብ ግብዣ ላይ መዝፈኗ ተቃውሞ ሲያስነሳባት የተከፈላትን አንድ ሚሊዮን ዶላር ለሄይቲ ጉዳተኞች ማቋቋሚያ ይዋል ስትል ሸፋፍናለች። ባጭሩ፣ የሚፈልጓትን የምትፈልጋቸው ስለ ገንዘብና በታዋቂነት ተገን ተሰሚነትን ለማግኘት ነው። በጎ አድራጎት ተፈላጊነትን ማጠናከሪያ እንጂ መነሻ አሳብ አይደለም ማለት ነው።

የራሳችንን ባህል ጥለን ሳናጣራ የሌላውን ባህል መኮረጅ ስነ ልቡናዊና ማህበራዊ ቀውስ መፍጠሩ አይቀርም። ለብዮንሴ ለአገር መሪ የሚደረግ አቀባበል ተደርጎላታል። በቤተ መንግሥት ከአገራችን ፕሬዚደንት ጋር ውይይትና ፎቶ። ምሽቱን 5ሺህ ለሚያህል ወጣት ዕርቃን ቀረሽ ውዝዋዜ። ቀጥሎ ከቤተ ክህነት አባት ጋር በቅድስት ሥላሴ ፎቶና መስተንግዶ። ለርስዋ ክብር ቀሳውስትና ዲያቆናት ልብሰ ተክህኖ ተጎናጽፈው ቆመው ቅዱስ ዝማሬ አሰምተዋል። የቅድስት ሥላሴ ተማሪዎች ይህንን በመቃወም የረሐብ አድማ መትተዋል። ይህን የሚያይ ወጣት ሐፍረት መጣልም ባለ ጸጋ ያደርጋል፤ በእግዚአብሔር፣ በአገር መሪዎችና በመንፈሳዊ አባት ዘንድ ነውር የለበትም ቢል ምን ይደንቃል? ጳውሎስ ለሙዚቃና ለሙዚቀኞች የነበራቸውን ፍቅር አንዘንጋ። በ1997 አዲስ አበባ ላይ  በተዘጋጀው የቦብ ማርሊ ስድሳኛ ልደት በዓል ላይ ማርሊ “መንፈሳዊ ልጄ” ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የገንዘብ መዋጮ በማሰባሰብ፣ ሕዝብ በማስተባበርና ሐውልታቸውን በማስተከል የዘፋኙ የመሐሙድ አህመድ የቀድሞ ባለቤት ወ/ሮ እጅጋየሁ በዋነኛነት ትጠቀሳለች። የማርሊ ባለቤት ሪታ ማርሊ፣ እንደዚሁም ብዮንሴ ሌሎቹ ናቸው።

ገንዘብ ማግኛ መንገዱ ጠባብ ቢሆንም ጥቂቶች ከምንም ተነስተው በአቋራጭ የናጠጡ ከበርቴዎች ሆነዋል። ሁላቸውም ንጹህና ሕጋዊ መንገድ ተከትለዋል ማለት ግን አይደለም። ህግን ተገን አድርገው የዘረፉ አሉ። ዘርፈው ያልተቀጡ አሉ፤ የመንግሥት ቴሌቪዥንና ጋዜጦች እንዳስታወቁን ከነዚህ ዋነኞቹ የአገርና የቤተ ክህነት መሪዎች ናቸው። የመሪዎች አርኣያነት ይህን ከመሰለ ወጣቱ አባቶቹን፣ አስተማሪዎቹን፣ ወንጌል አስተማሪዎቹን፣ መሪዎቹን ቢመስል ምን ይደንቃል? ከፍተኛ የሥራ እጦት ባለበት፣ የትምህርት ጥራት ባነሰበትና ቤተሰብ የመመሥረት ዕድል በጠበበት እየተንሳፈፈ የሚገኘው ትውልድ በዕድፍ ጎርፍ ቢወሰድ ስብዕናውን በገንዘብ ቢቸበችብ ምን ይደንቃል?

በየአውራ ጎዳናው የተበራከተውን ሁኔታ እያየን ምድረ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ቅዱሳን እንደ ሆኑ አናስብም። መጸዳዳት የተፈጥሮ ሕግ ነው ብንልም በአደባባይ ቪዲዮ እየቀረጸ ካልተጸዳዳሁ ማለት ግን የጤና ነው ማለት አይደለም። ግማቱና የሚፈጥረው ተውሳክ አየሩን ውሃውንና ተጠቃሚውን መበከሉ አይቀርም። የአንድ ሰው መጸዳዳት ስለሆነ ብዙ አይጎዳም እንቻቻል ይባል? ሺህ ሰው ቢጸዳዳስ? ማንም በአደባባይ እንዳይጸዳዳ ሕግ ባይወጣስ? ለመሆኑ “ብዮንሴ” ለጸሎት ካልሆነ በተቀር ከቤተ ክህነት ምን ጉዳይ አላት? ከትምህርት ቤት ምን ጉዳይ አላት? ቤተ መንግሥት የሚያስደርስ ምን ጉዳይ አላት? እርዳታ እንድታደርግ ለማግባባት መልካም ስነ ምግባር ወደ ጎን መደረጉስ ተገቢ ነው? ከአገር መሪዎች ጋር መታየቷና የተለገሳት አክብሮት ሳይታሰብ ለምግባሯ ያልተገባ እውቅናን እንዳጎናጸፈ እናያለን።

የስነ ምግባር ልቅነት እየተስፋፋ ነው። ልኩን የሚያውቁ ከሰው የሚገኘውን ክብር ለማግኘት ሲሉ ዝምታን መርጠዋል። የተዘረጋው የትምህርት ፖሊሲ ግለኛነትን፣ ለጎሠኛ ክልል እውቅናን ከመስጠት አልፎ በማህበራዊ ግዴታና በአገራዊነት ላይ ስላላተኮረ ክፍተት ተፈጥሮአል። መሪዎቻችን ለእግዚአብሔር ፍርሃትና ለሰው አክብሮት እንዳላቸው ማረጋገጥ አልተቻለም። ለረጅም ዘመናት ያካበትነው የሞራል ቅርስ በነውር ጎርፍ እየተሸረሸረ መሠረቱ እየተናደ ነው። ትኩረቱ ባፋጣኝ ባቋራጭ ገንዘብ ማግኘት ላይ ሆኗል። ለዛሬ እንጂ ለነገ ማለት ተረስቷል። ወጣቱ ያለፈ ታሪኩ ተዘባርቆበታል፤ ነገ ስላላሰተማመነ አገሩን ጥሎ እየጎረፈ ይገኛል። “ኢትዮፕያን አይዶል” “ብዩቲ ኮንቴስት” “ሙስና” “ዲፕሎማ” ወዘተ ባቋራጭ የመክበሪያና የሎተሪ ሕይወት ምልክቶች ናቸው፤ ይህም ራስንና ስነ ምግባርን የሚያሸጥ ሕይወት ነው። የወንጌል ዘማርያን አንዴ “ሪሚክስ” ሲሉ አንዴ “ኮንሠርት” ሲሉ፣ በደላላ ሲመከሩ፣ በአለባበሳቸውና በቁመናቸው ጸጋ ሲያሻሽጡ ትኩረቱ ይኸው የገበያና የገንዘብ ፍቅር ስለሆነ ነው። ትርፍ ባይገኝበት ስንቶች በ“ፓስተር” እና በ“ዘማሪነት” ይቀጥሉ ይሆን? በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ እህቶቻችን በምድራቸው ምርጫ ከማጣት የተነሳ ለግርድናና ለአረቦች ስድነት ሲዳረጉ ሲደፈሩና እንዲሠልሙ ሲገደዱ የደከሙበትን አሥር ጊዜ ሲያጭበረብሯቸው፤ ለኢትዮጵያዊነት ስም መጉደፍ ሰበብ ሲሆኑ፣ እነርሱን መመልመልን ገንዘብ ማግኛ ያደረጉ ወገኖቻቸው ናቸው። ውጤቱ በመጪው ትውልድ ጤና፣ ስነ ልቡናና ቤተሰብ አመሠራረት ላይ የሚያስከትለው የታሰበበት አይመስልም፤ በሶሻሊስቱ አብዮት ዘመን ወጣቱን ከቤተሰብና ከቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ማፈናቀል በኤድስ ለመለከፉ አስተዋጽዖ እንዳደረገ ማለት ነው። ሴቶች ቤተሰብና ማህበረሰብን የማያያዝ ዋነኛ ድርሻ አላቸው። አገራችን በኢኮኖሚ ዕድገት ማሳየቷ መልካም ነው። የሞራል መሠረት በዜጎቿ አለመተማመን እየተደረመሠ እውነተኛና ዘላቂ ዕድገት ግን ሊመጣ አይችልም። በሌላ አነጋገር ጉቦና ባቋራጭ መክበር በተንሠራፋበት እውነተኛ ዕድገት ሊኖር አይችልም። የቤቲ ጉዳይ ከነዚህ ሁሉ ሂደቶች ተነጥሎ አይታይም። ያም ማለት አድራጎቷን በሌላ ታላክክ ማለት አይደለም። በምርጫዬ ማንም አያገባውም ማለት ትችላለች። ሌላው አማራጭ ደግሞ ከሰውና ከኅሊና ክስ አንጽቶ ይቅርታ፣ ሰላምና ተስፋ ወደሚያጎናጽፋት ወደ ኢየሱስ መሸሽ ነው፤ ብዙዎች ይህን መንገድ መርጠው ትርጉምና ዕረፍት ያለበትን አዲስ ሕይወት ተቀዳጅተዋል።

የእግዚአብሔር ፍርሃት ሲጠፋ ውጤቱ ከግለ ሰብ አልፎ አገርን ያጎድፋል። ማፈርያ እንደ ክብር ይሆናል። የእግዚአብሔር ፍርሃት በሌለበት እንኳን ለሌላው ለራስም እንኳ አክብሮት አይኖርም። ፈርሃ እግዚአብሔር [እና ከዚህ የተነሳ የሰውን ክቡርነት የሚያጸና የህግ የበላይነት] ሳይኖር አገርና ሕዝቦቿ አይለሙም አይባረኩም። “ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ። አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ … የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው …እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል [መዝሙር 491220፤ ምሳሌ 9101516]

ምን እናድርግ? አቤቱ፣ ማረን! እንበል። የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን ሁላችን ለእውነት ልንመሰክር ተጠርተናል፤ ልኩን እያወቅን ዝም ብንል ከተጠያቂነት አናመልጥም። አገር የሁሉ ነች፤ በአገር ጉዳይ አያገባኝም ብንል እንሳሳታለን። ስህተቱን ልክ የሚሉትን ሃይ እንበል። የስነ ምግባር አጥር ፈርሶ ሁላችንንም የአሳር ጎርፍ ሳያሠጥመን እንነሳ። እንጻፍ፣ እንናገር፣ እንነጋገር። ከባሕላችን ውስጥ በጎውን ለይተን እንያዝ። የምድር ጉዞአችን አጭር መሆኑን እያሰብን በእግዚአብሔር ፍርሃትና በአክብሮት እንተያይ።

ባንተ በኩል ስትቦረቡር    እንዴት እዚህ ላይ ደረስን