መስከረም

ኢዮሃ አበባዬ / መስከረም ጠባዬ
ኢዮሃ አበባዬ / መስከረም ጠባዬ ...

meskeremመስከረም የወራት ሁሉ ቁንጮ። ግንቦት እሳት፣ ሰኔ ውሃ ነው። የኢትዮጵያ ምድር በእሳትና በውሃ ሳትጠመቅ እረፍት እና ልምላሜዋን አታጋራም። ከግንቦት መጨረሻ እስከ መስከረም መጀመሪያ ያለው የጊዜ ርቀት ሦስት ወር ብቻ ቢሆንም እስኪጠባ መጠበቁ ሦስት ዓመት ያስመስለዋል። የመከራ አንዱ ቀን እንደ ዘላለም ነው፤ እግሮቹም በብረት ሰንሰለት ከብደዋል። ደስታ ግን ክንፍ እንጂ እግር የለውም።

ግንቦት ድርቅና ብክነት ነው። መስከረም እረፍትና ልምላሜ ነው። ወራት መኳንንት ቢሆኑ መስከረም ንጉሥ ነው። መስከረም ደጅ ያስጠናል። እርሱ ካልፈቀደ ካላሳለፈ ጥቅምትን ማየት አይቻልም። አስራ አንዱን ወር እንደ ምንም ተንፏቆ የደረሰ አምስት እና ስድስት ቀን ጨምሮ ደጅ እንዲጠና ይገደዳል፤ ራሱንና ጓዳውን ማጽዳት ማዘጋጀት ይኖርበታል።

ይህን ያህል ርቀት ተጉዘው ለጥቂት ከደጅ የሚቀሩ አሉ። ሰኔ ላይ ጎርፍ ጠርጎ ይወስዳቸዋል የተባሉ ነፍስና ሥጋቸውን በጥርሳቸው አንጠልጥለው የሐምሌና የነሐሴን ሙላት ይሻገራሉ። ሁሉም በበኩሉ ዳርቻው ላይ ቆሞ እንደ አቅሙ ባሳለፋቸው ወራት የደረሱለትንና ያልደረሱለትን ምኞቶቹን ያስባል፣ ያሰላስላል። ሆያ ሆዬ ይላል። ሙልሙል ይገምጣል።

እንደ ሞት ብቅ ይላል፤ መስከረም ሳይታሰብ ብቅ ይላል። መስከረም እንዳላስጠበቀ ሁሉ ሌቱን ገስግሶ ከተፍ ይላል። ያለፈውን ዘመን አስረጅቶ ቀብሮ አዲስ ሕይወት አዲስ ተስፋ ይዞ ይቀበላል። ፍሬ ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም።

መስከረም እንቁጣጣሽ እንቁጣጣሽ ይላል፤ ጉዝጓዝ ሣር ይሸታል። እንኳን ደህና መጣሽ። ዓመት ዓመት ያምጣሽ፣ ይላል።

ኢዮሃ አበባዬ / መስከረም ጠባዬ
ኢዮሃ አበባዬ / መስከረም ጠባዬ
መስከረም ሲጠባ
ወደ አገሬ ልግባ ...

የግንቦት ሕጻናት ቢይ እና አፈር ያቦናሉ፣ ያፍሳሉ፤ ንፍሮና ቆሎ ጠግበው ቁቅ ይላሉ። የመስከረም ሕጻናት እሸት እሸት ይሸታሉ፤ ያስገሳሉ። አደይ አበባ ይለቅማሉ። ወረቀት ያቀልማሉ፤ አበባ ይስላሉ። ለክርስትና አባታቸው ለክርስትና እናታቸው ለሚወዱት አጎታቸው ለሚያቀብጣቸው አያታቸው ለአክስታቸው ለጎረቤታቸው ያበረክታሉ። ስሙኒ ይለቅማሉ። ሜንታ ከረሜላ ይሞጠሙጣሉ፤ በደስታ ከረሜላ ይደሰታሉ። ቼሬአሊያ ይኮረሽማሉ፤ ጮርናቄ ያላምጣሉ። ይሳሳቃሉ። እንደ ተርብ ይሯሯጣሉ። ግንባር ለግንባር ተላትመው ይላቀሳሉ። ይንከባለላሉ። ይንቦጫረቃሉ። ስሙኒአቸውን ደጋግመው ይቆጥራሉ። ከሸመቱበት በኋላ ፍራንኩ ለምን እንዳነሰ በጥርጣሬ ያሰላሉ፤ ኪሳቸው ውስጥ ደጋግመው ይቆጥራሉ።

ከሐምሌና ከነሐሴ ጎርፍ የተረፉ ይሰባሰባሉ። በየቤቱ በየቤተክርስቲያኑ ይሰባሰባሉ። በየአደባባዩ ይጨፍራሉ። የክረምት ቄኪ ያስላሉ። ይገባበዛሉ። ይጎራረሳሉ። በሞቅታ ይንገዳገዳሉ። ይደጋገፋሉ። ሰላምታ ይሰጣጣሉ። ተስፋ ይቀባበላሉ፤ እንደ ማይጉም ሽቶ ተስፋ ይርከፈከፋሉ። መስከረም ደስታ ነው፤ ልምላሜ ነው፤ ንጹሕ አየር ነው፤ ጤና ነው፤ ብሩህ ፀሐይ ነው፤ ሰማያዊ ሰማይ ነው፤ የተባዘተ ጥሩ ጥጥ ብሩህ ደመና ነው። የአድማሳት ቡልኮ የሚካበድ ደመና ነው። የሚያስቆዝም የሚራገፍ የሰላም ዝናብ የሲሳይና የነጎድጓድ የቆርቆሮ ጣሪያ ድምጽ ነው። መስከረም ዳዊት የሚያስደግም ወር ነው፣

ምድርን ጎበኘሃት፣ አጠጣሃትም
ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ
የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው
ምግባቸውን አዘጋጀህ፣ እንዲሁ ታሰናዳለህና
ትልምዋን ታረካለህ
ቦይዋንም ታስተካክላለህ
በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ
ቡቃያዋንም ትባርካለህ
በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ
ምድረ በዳውን ስብን ይጠግባል
የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ
ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ
ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ
ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ
በደስታ ይጮኻሉ፣ ይዘምራሉም። [ዳዊት 65፡9-13]

masqalደጁን አንኳኵተው ለከፈተላቸው መስከረም ግብዣው ብዙ ነው፤ ድግሱ የጦፈ ነው። በአስራ ሁለት የጉራጌ መስቀል፣ በአስራ ስድስት ደመራ፣ በአስራ ሰባት ለተቀረነው መስቀል። ጠፍቶ የከረመው የሚገኝበት እሳትና ዐመድ የተስማማበት ዕለት ነው። ግንቦት በፀሐይ እሳት ያቦነነውን፣ መስከረም በደመና እሳት አብርዶ ያሳርገዋል።

በአስራ ስምንት ተማሪ ልብሱን አጥቦ ተስፋ ፍለጋ እውቀት ፍለጋ ደብተሩን ይዞ ወደ ተማሪ ቤት ይሮጣል። ከጳጉሜ [ጳጉሜን፣ ቋቁሜ] እስከ መስከረም መጨረሻ የአገር ሰላምታ እንደ በረቅ እንደ ነጎድጓድ ከቅርብና ከርቀት ይንጎደጎዳል፣ እንደ ምንጭ ውሃ ይዥጎደጎዳል፦

እንኳን አደረሰህ ... እንኳን አደረሰሽ
እንኳን አደረሰሽ ... አሜን እንኳን አደረስዎ
እንኳን አደረሰዎ ... እንኳን አደረሰሽ
እንኳን አደረሳችሁ ... እንኳን አደረስዎ አባባ
ሃፒ ኒው ይር ... ሃፒ ኒው ይር
አደረሳችሁ ...
ይመስገነው
ክብሩ ይስፋ

መስከረም የወሮች ሁሉ ንጉሥ ነው። የኢትዮጵያ ክልሎች፣ ወረዳዎች፣ አደባባዮች፣ ቀዬዎች እና ጓዳዎች እጅ ይነሳሉ። የሰላም እሳት ያጋያሉ፣ ያደፈውን እና ያረጀውን ያቃጥላሉ። የተስፋ ችቦ ያበራሉ። በአንድነት ሆ ይላሉ። የደስታ ሆታቸውን በሸንተረር በሸለቆ በጋራና ፈፋ ያስተጋባሉ።
ኢዮሃ አበባዬ / መስከረም ጠባዬ
መስከረም ሲጠባ / አደይ ሲፈነዳ
እንኩዋን ሰው ዘመዱን / ይጠይቃል ባዳ

ለተቀረው ዓለም አዲስ ዓመት ጥር ነው። ለኛ አዲስ መስከረም ነው።

የእግዚአብሔር ሰላም በምድራችን ለወገኖቻችን ይሁን፤ ለሕዝብ የሚራሩ የሚያሳርፉ መሪዎች ይብዙ።

© ምትኩ አዲሱ፣ዘንድሮስ አልዋሽም” [2010 ], ገጽ 32-35 / photo credit: google.com