ርዕሰ አንቀጽ

ግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ነው!

ዶናልድ ትረምፕ ያሸንፋሉ ብሎ ያሰበ የለም። ትረምፕ ከፓርቲአቸው ጋር ግብግብ በመግጠማቸው ከጅምሩ አጋር ከድቷቸዋል። ብሸነፍ ውጤቱን አልቀበልም ማለታቸው ሌላ ውዝግብና ሥጋት ፈጥሮ ነበር። ሂለሪ እንደሚያሸንፉ ግን በትረምፕ ፓርቲ ዘንድ ሳይቀር ጥርጥር አልነበረም፤ ጥያቄው ሂለሪ በምን ያህል ድምጽ ባላጋራቸውን ጉድ ይሠራሉ ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል? እንዳቀዱት አልሆነም። “ዕጣ በጕያ ይጣላል፤ መደብዋ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” [ምሳሌ 16፡33]

ምሑራን፣ ሊቃናት፣ የቁጥር ጠንቋዮችና ተንታኞች ሠልስት እንደ አዲስ እየተንጫንጩ ነው። ሂለሪ የተሸነፉበትና ትረምፕ ያሸነፉበት ምክንያት እንዴት እንዳልታያቸው ለመረዳት የኋሊት ምርመራ ይዘዋል። ለሚቀጥለው የፖለቲካ ፍትግያ ዝግጅት ይዘዋል። ነገ የሚሆነውን የሚያውቅ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር በአደባባይ የሠወረውን ሰው በርብሮ አያገኘውም። የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሠወር ነው [ምሳሌ 25:2]። ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ የሚወድደውንም እንዲሾምበት ያውቁ ዘንድ ይህ ሆነ [ዳንኤል 5፡21]። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?[1 ቆሮንቶስ 1፡19-20]። በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም። ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም … ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና [ዳንኤል 4፡35፣37]

ኦባማ ከስምንት ዓመት በፊት ሥልጣን ላይ ሲወጡ፣ ምድሪቱን አሳርፋለሁ፤ ጦርነት እሽራለሁ፤ ክፍፍሉን አቃናለሁ ብለው ቃል ገብተው ነበር። በአሳባቸው እንዲበረታቱ፣ ኖርዌይ የሰላም ኖቤል ሜዳልያና ለጒዞአቸው የሚሆን 1 ሚሊዮን 400 ሺህ ዶላር ስንቅ ሰነቀችላቸው። ክፍፍልና ጦርነት ግን ሊቀንስ ቀርቶ ተባባሰ። ኦባማ በሙሴ ተመሰሉ፤ ከግብጽ ማማ ላይ ያወጁት ዲስኲር ግን ማናችንንም “ከነዓን” አላገባም፤ ይልቅ ምድረበዳ ላይ በትነውን ሊወርዱ ነው። ሙሴ ከእግዚአብሔር ተቀብሎ “ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው … ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ያለውን፦ ወንድና ወንድ፣ ሴትና ሴት ቢጣበቅ፤ ሴት ወንድ፣ ወንድ ሴት ነኝ ቢል ችግር የለበትም የሚል የህግ ጽላት አስጽፈው ከኋይት ሃውስ ኮረብታ ወረዱ። ያገር መሠረት የሆነውን ቤተሰብ አዋረዱ። ኦባማ በመሲሕ ተመሰሉ፤ የነፍሱ ቀርቶ ከሥጋ ህመም ማናችንንም አላዳኑም። ያወጁት የጤና ኢንሹራንስ ከሥልጣን ሳይወርዱ መቀልበስ ጀምሯል።

ትረምፕስ የት ይሆን የሚወስዱን? ተቃዋሚዎቻቸው በሂትለር መስለዋቸዋል። እውነት የሂትለር አምሳያ ናቸው? ከሳሾች የአባታቸው ግንድ ጀርመናዊ መሆኑን ብቻ ያሰቡ ይመስላል ሴት ልጃቸው ከይሁዲ ተጋብታለች። አሜሪካ ሂትለር እንደ ነገሠባት ጀርመን የአንድ ዘር ምድር ስላልሆነች ክሱን ችላ ብለናል። ታዲያ ወዴት ይሆን የሚመሩን? በኛ ዘንድ የሚያውቅ የለም።

ተስፋ ያረግነው ተስፋችንን አጨልሞ አይተናል። ያጨልማል ያልነው ያበራልን እንደሆነስ ማን ያውቃል? እግዚአብሔር ባልታሰቡ ሰዎች የጽድቅ ሥራ ሠርቶ አሳይቷል። ለማንኛውም “በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል” [መዝሙር 118፡8]። ለሁሉም፣

እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ነው / እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ነው / እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ነው / ማነው የሚረታው?!

ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ ነው / ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ ነው / ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ ነው / ማነው የሚረታው?

አምላኬ በዙፋኑ ላይ ነው / አምላኬ በዙፋኑ ላይ ነው / አምላኬ በዙፋኑ ላይ ነው / ማነው የሚረታው?

ጌታዬ በዙፋኑ ላይ ነው / ጌታዬ በዙፋኑ ላይ ነው / ጌታዬ በዙፋኑ ላይ ነው / ማነው የሚረታው?

ህዳር 1/2009 ዓ.ም [11/10/16]