ናርኪሦሥ እስከ ዙከርበርግ

narcissus

በዚያን ዘመን የናርኪሦሥ ውበት ያልማረካት ቆንጆ አልነበረችም። እርሱ ግን ናቃቸው እንጂ ለአንዳቸውም ምላሽ አልሰጠም። ንቀቱና ኵራቱ ከጎዳቸው አንዲቱ፣ ፍቅርን ንቆአልና ራሱን ይውደድ ብላ ጸለየች። አንድ ቀን ናርኪሦሥ ከኲሬ ውኃ ሊጠጣ ሲያጎነብስ የገዛ ፊቱን አይቶ በራሱ ፍቅር ተለከፈ፤ ዐይኑን ከዐይኑ ላይ ማንሳት አቃተው። እስከ መቸ እህል ሳይቀምስ? ቀስ በቀስ ከሳ መነመነ ተነነ፤ ሊፈልጉት የመጡ ከሥፍራው አጡት። ይለናል የግሪኮች አፈታሪክ።

ራስን መውደድ አዲስ ነገር አይደለም። ሰው ሁሉ ስለ ራሱ ትንሽ ያልሆነ ግምት አለው፤ ሰዎች ስለ እኔ ምን ያስቡ፣ ምን ይሉ ይሆን ይላል። በሰዎች ዐይን ለመወደድና ለመወደስ ምን ላርግ? ያደባል፤ ያመቻቻል፣ ያስመስላል። ችግሩ ሚዛኑን አለማወቅ ነው። በራሱ የሚተማመን፣ በሰዎች አስተያየት የማይነዳ ማን አለ? በአንጻሩ፣ ሰው ራሱን መውደድ ካላወቀ ሌላውንም መውደድ አይችልም:- "ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ" [ሌዋውያን 19:18፤ ያዕቆብ 2:8]። ሌላውን መውደድ መሠጠትን ይጠይቃል። መሥጠትና መቀበል በሚዛን ካልተያዘ ግን ጤናና ማህበራዊነትን ያቃውሳል። እኔ። የኔ። ለኔ። ልጆች፣ ወንዶች፣ ሴቶች፣ አዛውንት፣ የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ አማንያን፣ የአገር መሪዎች በቀን ስንቴ “እኔ፣ እኔ፣ እኛ፣ እኛ” እንላለን? ራሳቸውን የሚሰብኩ ሰባኪዎች? ቁመናቸውን አለባበሳቸውን ዝናቸውን የሚያዜሙ ዘማሪዎች? የገዛ ድምጻቸውን ማድመጥ የሚወዱ። ስንቶች በዐይንና በጣት፣ በአፍና በጆሮ ስንቴ በቀን የትዊት ቴክስት ሴል ደጅ ይሳለማሉ? አንድ ሰው በቀን ስንቴ ፊትና ቍመናውን በመስተዋት ያያል? ስንቴ ስለ ጠጕር፣ ጫማ፣ ስለ ልብስ፣ ስለ በላው፣ ስለ ማዕረጉ? መኪናው? ጢሙ፣ ጥፍሯ? ኧረ ሴልፎኑ፣ ስለ ሴልፊ [የነፍስ ሰልፊ] ያወራሉ? ሳይታወቀን ጤናችን ምን ያህል ተቃውሶ ይሆን? ወይስ እጅጉን ደህና ነን ...

ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ ብልኃተኛው ይሁዲ ዙከርበርግ፣ ፊት ቀላዋጭ “ፌስቡክ” የተሰኘ መስተዋት አንጠልጥሎ ገበያ ወጣ። ከናርኪሦሥ መጽሐፍ አንዷን ገጽ በጥሶ በዶላር ቢቸበችባት ዜግነቱን አስከዳችው። ኃይማኖቱን አስረሳችው [ከይሁዲ፣ ከሓዲ፣ ከቡዲስት፣ ዛሬ “በደፈናው ኃይማኖተኛ” ነኝ ብሏል]። መስታዪቱን ከሚኖርባት ዛኒጋባ አውጥቶ ወስዶ አደባባይ ላይ ተከላት። አላፊ አግዳሚው ተረባረበባት፤ ሰው ቆሞ ተጋድሞም ወሬውና ቀለቡ ፊቱን ድዱን መኝታውን ጓዳውን ቤተሰቡን ፀሐይ ላይ ማስጣት ሆነ።

ሁለት አመለካከት አለ። አንደኛው፣ ትክ ብሎ ራስን ማየት፤ ማስተያየት፣ ሁሉን ችላ ብሎ የባጥ የቆጡን መመኘት። ወይም፣ ራስን መርሳት፣ ለሌላው ሰው ቅድሚያ መስጠት። ሕይወታቸውን ለዓላማ፣ ለአገር፣ ለፍትኅ የሚሠው አሉ። ለራሴ፣ ለጎሳዬ ብቻ የሚሉ አሉ። መጠኑን ስላላወቁ ብዙዎች በራስ ወዳድነት ታነቁ፤ ሕይወትን ለይተው ላያጣጥሙ በዓለም መንፈስ ተለከፉ።

ወንጌል ግን ራስህን ካድ፣ ሌላውን አስቀድም ይለናል። “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል … እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ … መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም … በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።” [ማቴዎስ ወንጌል 22:35-40፣ 16:24፣ 10:38፤ ሉቃስ 9:23] ወንጌል፣ ራሱን ፈጽሞ ስለ ካደ፣ ለሰው ሁሉ ደህንነት በመስቀል ላይ ስለ ሞተ፣ ከዘላለም ጥፋትና እሥራት ነጻ ለማውጣት ሞቶ ከሙታን ስለ ተነሳ ኢየሱስ ስለ ተባለው ነግሮናል። ለብዙዎች ግን ራሳቸውን መውደድና ማዳን በልጦባቸዋል፤ ፊታቸውን ወደ ኢየሱስ ስላላዞሩ በራሳቸው ፍቅር ልክፍት ጠፍተዋል።  

አንተም አከረርክ፣ እንጂ “ፌስቡክ” ርቀትና ዘመን ከዘመድ እንዳያቆራርጥ፣ ጠፍቶ ከከረመ ወዳጅ ጋር እንዲያገናኝ መፍትሔ አመጣ የሚለኝ አይጠፋም። እኔም ይህን አልክድም። በባህላችን ውደዱኝ ማለት ስለሚያሳፍር በብልኃት “ላይክ” አድርጉኝ ያልነው ለዚህ ይሆን? “ሼር” ሺ “ፍሬንድ”? “ፎሎወር” ዙከርበርግ ከዘጠና ሚሊዮን በላይ “ተከታይ” አለኝ እያለን ነው። የግሪኮች ማህደር የቋጠረው ምሥጢር ዋዛ መስሎናል። እነሆ፣ ስንቱን ሰው በአንድ ጀምበር ተወዳጅ፣ ባለ ሺ ወዳጅ ጕራ አሳዳጅ አድርጎታል።

ይልቅ ስንከራከር፣ መስተዋት ፊትህ ላይ ደቅኖ፣ በእንቅልፍ ልብ ማር እንደላሰው ሰው ጣፍጦህ፣ ዐይን ዐይንህን ትክ ብለህ ስታይ፣ አንዱ መታወቂያህን ውሎና አዳርህን የቤተሰብህንና የወዳጅህን ዓይነት ጎልጉሎ ይዞብህ ሄዷል፤ ምን እንደሚያደርግበት የሚያውቅ እግዜር ብቻ ነው። ክርስቲያን ሆይ፣ “ፌስቡክ” ይልቅ የቀራንዮን መስቀል እንዳያስረሳህ። ይኸ ራስን የመውደድ ነገር በርትቶ ቀስ በቀስ እርቃን እንዳያስቀርህ ...

 10/30/2009 [7/10/17]

Painting credit: pinterest.com