ር እ ሰ  አ ን ቀ ጽ

የ ስ ም ም ነ ት  ቸ ር ች

ziona1

እንጋቲአሩአ እና አሬሩአ በክ አይላንድ [ደሴ] የሚገኙ ሁለት ተጎራባች መንደሮች ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ በንድፉ ተስማምተው መሐንዲስ ቀጠሩ። ይኸ የሆነው የዛሬ 135 ዓመት ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱን ጽዮን እንበላት አሉ። ህንጻው ሲገባደድ፣ ውጭው ነጭ ቀለም ይቀባ አሉ፤ በውስጠኛው ቀለም ግን መስማማት አልቻሉም። አንዱ ወገን ቀይ ሐምራዊ ሲል፣ ሌላው አረንጓዴ ውሃ ሰማያዊ አለ። ተጨቃጨቁ፤ ጭቅጭቁ ከመሪዎች አልፎ ወደ መንደርተኞች ተዛመተ። መሰማማትና መስማማት አልቻሉም።

አስታራቂ መፍትሔ አገኙ፤ ቀይ ሐምራዊ ያሉ በአንድ ወገን፣ አረንጓዴ ሰማያዊ ያሉ በሌላ፣ መሓሉ ላይ ግድግዳ ገነቡ። ሁለት መግቢያ አበጁ። ችግሩ ግን ሊረግብ አልቻለም፤ አንደኛው ወደ አምልኮ ሲታደም፣ ሌላኛው ከውጭ ጩኸትና ግርግር የበዛበት ጨዋታ ይጫወታል። እሑድ ረብሻ ሆነ፤ የጎሪጥ መተያየት ሆነ።

ከዓመታት በኋላ፣ ይኸ ድርጊት የትም እንደማያደርስ የተረዳ አንድ መጋቢ ሁለቱን መንደርተኞች እየዞረ ማነጋገር ጀመረ። ሳይቆይ ወደ አንድ ስምምነት አመጣቸው። ግድግዳው ከመሓል ይፍረስ አሉ፤ ፈረሰ። ውስጠኛው ግድግዳ የማያጣላ ደብዛዛ ቀለም ከላይ ይደረብለት አሉ፤ ተደረበለት። በሮች እንዳለ ተተው። ዝማሬ በተራ ሆነ። አትሮንሱ ከመሓል ተተከለ። ሰባኪው አቋቋሙን አስተካክሎ ይሰብክ ጀመር።

ከዓመታት በኋላ ዘመናዊነት ተስፋፍቶ፣ ትውልድም አልፎ ተተክቶ፣ ከላይ የተደረበው ቀለም ለምን ተፍቆ አይነሳም መጣ፤ በጥንቃቄ ተፍቆ ተነሳ። የቀድሞው ባለሁለት ወገን ደማቅ ቀይ ሐምራዊ እና ደማቅ አረንጓዴ ውሃ ሰማያዊ ቀለም ተቀብሮ ከኖረበት ብቅ አለ። ታዳሚ በመረጠው በር ይግባ ተባለ፤ በተመቸው ቀለም ወገን ተቀምጦ ያምልክ ተባለ፤ እንደዚያው ሆነ።

ቤተ ክርስቲያኒቱን የተከሉበት ከተማ ሞውክ ተሰኘ፤ ትርጓሜውም ለሁለት የተከፈለ ማለት ነው። በሰላም ውቅያኖስ ተከብባ ሰላምን ያላወቀች ማህበር። በውቅያኖስ መሓል የደሴት ጠብታ።

+ + +

እሑድ ጧት ጽዮን አምልኮ ለመካፈል፣ ዓርብ እኩለ ሌሊት ቀጥታ በረራ መውሰድ ነው። ከአዲስ አበባ ወደ ሲድኒ አውስትራልያ አቅንቶ የኢንድያን እና የፓሲፊክ ውቅያኖሶችን ማቋረጥ ነው። በየትኛው በር መግባት ይሻል ይሆን? በሁለቱም በር ባንድ ጊዜ መግባት አይቻል። ማንንም ላለማስቀየም፣ በአንዱ ገብቶ በሌላው መውጣት ይሻል ይሆን?

© 11/26/2017

Picture credit: lonelyplanet.com