ር እ ሰ  አ ን ቀ ጽ

ዝንብ እና ሽቶ አብረው አይሄዱም

zinbshito

እንግዶችን ተቀበሉ ብሎናል መጽሐፍ (ዕብ 13:1-2)። እኛ ግን በየቤተክርስቲያኑ አልቤርጎ ዘረጋን፣ ጸጋን በገንዘብ ቸበቸብን፤ የማስተናገድን ጸጋ አራቆትን። “ቴክኖሎጂ ለወንጌል!” አልን፣ ወንጌሉን ባስደንጋጭ ዩቱብ፣ ባጓጊ ውሸት ለባበጥን። በ “ላይክ” አርጉኝ ፌስቡክ መፈክር አጀብን። ማራኪ ውሸት “ሼር” አረግን። ፍራንክ ለቃቀምን። የእውነትን ወይን ጠጅ አቀጠንን።

አዋቂነታችንን ለማወጅ እንግሊዝኛ አሰባጠርን፣ “ዋው! ብርክ! ውድድድ” ተሞጋገስን። የማያውቁትን ብዙኃን በታላላቅ ቃላት አደነቆርን፣ ነጻ የሚያወጣውን፣ የጠራውን ወንጌል አደፈረስን። “ፍቅር፣ ፍቅር” አልን። ለኃጢአት ምክንያት ደረደርን። ኃፍረትን ጣልን። “የማይገባውን አያደርግም፥ … ከእውነት ጋር … እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም”ን ሻርን፣ ሸረሸርን። ስለ ጽድቅ ያነሳብንን ተቧድነን ኮነንን። ምሕረት በቲፎዞ አወጅን። እንደየፈቃዳችን ብልኃት አበጀን። ብልጠትን ጥበብ፤ የምድሩን፣ ሰማያዊ ጥበብ አሰኘን! ግብዝነትና ዓመጽን ክርስትና አስነስተን ታቀፍን። በሰፊ ጥርጊያ ተዋብን። “አትፍረድ” ብሏል እያልን፣ ለራሳችን ፈረድን!

ስለ ኃጢአት ምክንያት ደረደርን፣ ከሚያመኻኙ ጋር አበርን። በዚህም፣ የሞቱ ዝንቦች ሽቶውን አገሙት የሚል ቃል በራሳችን ላይ መሰከርን!