ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም

dawn2

ወንጌላውያን፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያጸናውን አንድነት እየሰበኩ አንድ አይደሉም፤ የፍቅር፣ የይቅርታና የሰላምን ወንጌል ተሸክመው ገና በጥል አሉ፤ ጎንበስ ብለው እንደ ማገልገል መገልገልን መርጠዋል፤ የከበሬታ ወንበር ላይ ተኮፍሰዋል። ለማሸማገል የሚበቃ በመሓላቸው አልተገኘም። ሰሞኑን ይህን ስንሰማ ነበር።

የሚያሰባስብ ከመሓላቸው በመታጣቱ፣ ሐሙስ፣ ሰኔ 13/2011 ዓ.ም.፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በጠሩት ስብሰባ ላይ 400 የሚያህሉ የወንጌላውያን መሪዎች በቤተ መንግሥት አዳራሽ ተገኝተው ውይይት አካሂደዋል። ወንጌላውያን ለተቀበሉት ተልእኮ ታማኝ መሆን እንዳልቻሉ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ምሳሌዎችን ጠቅሰው ተናግረዋል።

ስብሰባው፣ ድንግዝግዝ ባለ ሁኔታ ውስጥ ገና ብሩህ ተስፋ እንዳለም የታየበት ነው። የመጀመሪያው፣ ቄስ ግርማ ዘውዴ ያቀረቡት የወንጌል አማኞች የረጅም ዘመን አገራዊ ተሳትፎ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በአማርኛ መተርጎሙ (1833 ዓ.ም.)፣ ወንጌል ለማስፋፋት በ1942 ዓ.ም. የመንግሥት ፈቃድ ለማግኘት የነበረው ደጅ ጥናት እና የተከፈለው መስዋእት፣ የተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ማእከሎች፣ ለአገር የበቁ መሪዎች፣ ወዘተ። ቄስ ግርማ ወዳለፈው ታሪካችን ፊታችንን መመለሳቸው ተገቢ ብቻ ሳይሆን አሁን ለገባንበት የሞራል ውድቀትና የራእይ ጥበት የሚያሰባስብ ፍቱን መድኃኒት ነው። ታሪክን እንደ መርሳት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለም። በራስ ላይ እንደ ማተኮር፣ እግዚአብሔር በሌሎች ሕይወት የሠራውን ሥራ የሚያሳንስና የሚያስረሳ የለም!

ቀጥለው፣ ሁለት እህቶች (እህት ሕይወት ተስፋዬና ስማቸውን ያልጠቀሱ ሌላ እህት) ችግሩ “የእኔነት” ማየል እና የወንጌል ማህበራዊ ተልእኮ መዛባት ነው ብለዋል። በሌላ አነጋገር፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል የሚቀናቀን አለ ማለት ነው። በመጨረሻ፣ ስማቸውን ያልጠቀሱ ወንድም፣ ዛሬ በምድራችን የምናየው የብዙዎች ጸሎት ውጤት ነው ካሉ በኋላ፣ ከእንግዲህ ለሚሆነው ከዚህ ሳንወጣ እያንዳንዳችን በግልና በጋራ ድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንግባ ብለዋል። “በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።” (ሮሜ 5:5)

የነጋሶ መንገድ