ሳናወሳስብ ቀላሉን መንገድ እንምረጥ

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አዲስ ፈተና ተጋርጦባታል። ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ያሳለፈችው ፈተና ሳያንስና ሳይፈታ፣ በአናቱ ሸክም ተጨምሮ እያንገደገዳት ነው። ከሁሉም ወገን የተነሳሳው ቊጣ ችግሩን በሰከነ አእምሮ ማመዛዘን እንዳይቻል ደንቃራ ሆኗል። ልበ ሰፊና አስተዋይ አመራር ከወዴት ይምጣ? ከዚች ታላቅ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለማሸማገል የሚበቃ ጠፍቶ ሕዝበ ምዕመን ሃያ ሰባት ዓመት ተቃቅሮና ተበታትኖ ኖረ። ቤተክርስቲያንም ከጥሪዋ ውጭ ባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች እጅ ወደቀች።

ቤተክርስቲያን የራሷ አስተዳደር ቢኖራትም፣ በምድር ላይ ነችና ከመንግሥት ጋር አብራ መሥራት ግድ ነው። የ1987ቱ ህገ መንግሥት (ም.2፣ አንቀጽ 11፤ ም.3 አንቀጽ 27) አንደኛቸው በሌላው ጣልቃ አይገባም ቢልም፣ መንግሥትን ጣልቃ ከማስገባት ውጭ አማራጭ አጥታለች። መንግሥትም ችግሩ በጊዜ ካልተገደበ ሕዝብ ያባላልና ዝም ብሎ ማየት አይሆንለትም።

መፍትሔ ለመፈለግ እንግዲህ የችግሩን መንስኤ አጥርቶ ማወቅ ያሻል። መፍትሔ ሲተለም የረጅም ዘመን ውጤት ታስቦ መሆን አለበት፤ ውጤቱ ጋ ለመድረስ ደግሞ የአጭር ጊዜ መስዋእት መክፈል ግድ ነው። “እኔ ያልኩት ካልሆነ” ማለት ማባባስ ነው፤ “ከጥንት የነበረ” ማለት የትውልዱን መረዳትና ጥያቄ መሳት ነው። መደማመጥ፣ ሌላኛው ወገን አናሳም ቢሆን አሳቡን እንዲያብራራ ዕድል መስጠት፣ በአሉባልታ አለመነዳት እይታዎችን ለማቀራረብ ይረዳል። በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ፍርሓት ይዞታል። አንዱ ለሌላው የፍርሓት ምንጭ ሆኖበታል።

“የኦሮሚያ ቤተክህነት ኣደራጅ ኮሚቴ” የተሰኘ፣ የኦሮምያ ቤተክህነት ጽ/ቤት ይቋቋም ነው የሚለው። የቊቤ ትውልድ እንኳንስ ግዕዝ፣ አማርኛ ሳያውቅ ስላደገ፣ ቋንቋውን የሚያውቁ በቂ ቀሳውስት ስለሌሉና ተሳላሚ ስለ ተመናመነ፣ ቤተክርስቲያን ባዶ ቀርታለች፤ ስለዚህ በቋንቋው ይሁንለት፤ “በአንዲት ቤተ ክርስቲያንና በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ እናምናለን፤ አንከፋፍልም፤ አንገነጥልም … በክልሉ እየተባባሰ የመጣው የምእመናን ፍልሰት እና የመናፍቃን ወረራ ያሳስበናል” ብሏል።

ጥያቄ የቀረበለት ክፍል፣ አገር የመገንጠል ሤራ ነው በሚል ምክንያት የኮሚቴውን አባላት ይቅርታ ጠይቁ ብሏቸዋል። የኮሚቴው አባላት በአጸፋው “ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ ከሆነ መጠየቅ ያለባቸው ላለፉት አመታት ስር የሰደደውን የቤተ ክርስቲያኗን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ቤተክርስቲያኗን የፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶቻቸው ሎሌ ያደረጉ ብፁሃን አባቶች በመሆናቸው ሕዝቡን ይቅርታ በይፋ ጠይቀው ህዝቡን እንዲክሱ በትህትና በዚህ አጋጣሚ እንጠይቃለን፤ በአጠቃላይ በእነዚህና አያሌ አሳማኝ ምክንያቶች ያለጥፋታችን ይቅርታ ጠይቁ የተባልነውን አስገዳጅ ኣካሄድ አልተቀበልንም” ሲሉ መልሰዋል።

ከዚህ በመነሳት ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ 1/ “የተጠቀሰው አደረጃጀት ሕጋዊ እውቅና የሌለው መሆኑን ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን አውቃችሁ የግለሰቦቹን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመቃወምና በቀደመው አንድነታችሁ ጸንታችሁ ቤተክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ጠብቁ” የሚል መልእክት አስተላልፏል፤ 2/ ጒዳዩ ያሳሰባቸው ሌሎች፣ ሀ/ “መንግሥት ይህንን ዓይነት ተግባራዊነት የሌለው የቃላት መግለጫውን በማለፍና ዝምታውን በመስበር በጽንፈኞችና በሕገ ወጦች ከወዲሁ ተግባራዊ እርምጃ ካልወሰደ በስተቀር በዚህ አያያዝ እነዚህ ጽንፈኞች እና ሕገ ወጦች አድገው እና የመንግሥትነት ኃይል ጨብጠው ፋሺስት ኢጣሊያ በቤተክርስቲያናችንና በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰውን እልቂት አይደግሙም ብሎ ማሰብ አይቻልም” ለ/ ኢትዮጵያን ለመታደግ የተዋህዶን እምነት አንድነት መደገፍ ያስፈልጋል። እምነት የግል ነው የሚለውን መርህ ብ(ን)ቀበልም፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታላቅ ተቋም ናት፤ የአገር መከታና መመኪያ ናት። ፊደል ያስቆጠረች(ን) ይህችው ቤተክርስቲያን ናት። የዚህችን ታሪካዊ ተቋም መከፋፈልና ማፈራረስ የፖለቲካ ጉዞና ሴራ ከኢትዮጵያ መፈራረስ ጋር አጣም(ረን) እናያቸዋለሁ ብለዋል፤ 3/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም በመላው አገሪቷ እንዲካሄድ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርታለች፤

አንዳንድ ጒዳዮችን ግልጽ እናድርግ። አሁን የተከሰተው የከረመ ጥንስስ እንጂ አዲስ አይደለም። ህወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ከመረከቡ አስቀድሞ ያሰበበትና ሥልጣን ሲይዝ ተግባራዊ ያደረገው አሠራር ነው። በሌላ አነጋገር፣ ባላት አደረጃጀት ቤተክርስቲያን የዘለቀ እርምት ለመውሰድ ያዳግታታል። መንስኤው የጎሳ ፖለቲካ ነው፤ የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አመራር መዳከም ነው፤ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ መሆኗን አለማስተዋል እና ምዕመን እምነቱን እንደሚገባ አለማወቁ ነው። መፍትሔውም እነዚህን ከማቃናት ይጀምራል።

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በሁኔታዎች፣ በቡድኖችና በግለሰቦች ላይ ከማላከክ ተቆጥባ ኃላፊነት መውሰድ ይኖርባታል። የአሠራር ድክመቶቿን ለይታ እስካላወቀች ግን የሚያመረቃ ውጤት ልታስገኝ አትችልም። የምትወስዳቸው ውሳኔዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ውጤቶችና የሥልጣኗን ገደብና ተመጣጣኝነት ማመዛዘን ይኖርባታል። "የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ...የግለሰቦቹን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመቃወም ... ቤተክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ጠብቁ" ብላ ያስተላለፈችው መመሪያ ወደ ግጭት እና እልቂት እንደማያመራ ምን መተማመኛ አለ? በተረፈ፣ ሁሉን በጅምላ ከመውቀስ፣ እንዳስፈላጊነቱ ከሌሎች የእምነት ክፍሎች ጋር ግንባር መፍጠር ይኖርባታል።

ለመሆኑ፣ ቤተክርስቲያን “ህገ ወጥ” ያለቻቸውን ግለሰቦች ማግለል ወይም መቅጣት ትችላለች? ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራችው እርምጃ መውሰድ ስላልተቻላት ነው? ኃላፊነትን ከጫንቃዋ ላይ ለማውረድ በማሰብ ነው? የቤተክርስቲያን ችግር የሚፈታው በሕዝባዊ ሰልፍ ነው? ሰልፈኛው ሰላም አንግቦ እንደሚነሳ ዋስትና መስጠት ይቻላል? (ከድረገጾችና ከቴሌቪዥን ላይ የሚታየውና የሚሰማው ግን በአብዛኛው ከክርስቲያን የማይጠበቅ ቊጣና የስድብ ናዳ ነው!) ሰላማዊ የተባለው ሰልፍ ወደ ረብሻ ቢለወጥ መሪዎች ተጠያቂነቱን ይወስዳሉ? ወይስ ያ ክፍል የመንግሥት ብቻ ጒዳይ ነው? “የኦሮሚያ ቤተክህነት ኣደራጅ ኮሚቴ” ነን ያሉት ሕዝቡን ሲያደራጁ የቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነው? የህወሓት/ኢሕአዴግ ክልላዊ አሠራር ያልከለከለውን፣ ቤተክርስቲያንም እርምጃ ያልወሰደችበትን፣ ዛሬ ተነሥቶ መቀልበስ እንዴት ይቻላል? እነዚህና ተጓዳኝ ጥያቄዎች አብረው ሊታሰቡ ይገባል።

ወደ መፍትሔ ለመቃረብ ከተፈለገ፣ ስሜትን መግዛት ያስፈልጋል። “የለዘበች መልስ ቍጣን ትመልሳለች፤ ሸካራ ቃል ግን ቍጣን ታስነሣለች” (መጽሐፈ ምሳሌ 15፡1)። መንግሥትን ተሳድቦ፣ ፕሮቶስታንቱንም ተሳድቦ (“መናፍቃን” "ተኲላ")፣ ኦሮሞውን በጅምላ (“ጽንፈኛ” “ወራሪ” "ፋሺስት") ኮንኖ ሁለት ወዶ አይሆንም! ከጒያዋ ሥር ያለውን ወጣት ጥያቄ እንደመመለስ በፀረማርያምነት ፈርጃ አባርራ፣ መልሳ በሌሎች ማሳበብ ሁለት ፊት ጒዳት ነው።

በፖለቲካውና በኃይማኖቱ ረድፍ ግራና ቀኝ የሚያዋክቡን ባብዛኛው በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦችና አጃቢዎቻቸው ናቸው፤ ብዙሓኑ ሕዝብ ሰላምተኛ ነው፤ ከምኑም የለበትም። ግልጽ እኮ ነው! ያልተጣራ ወሬ ይዘን አገር ፈረሰ አንበል! ይልቅ ደህንነታችንን ከሚያስጠብቅልን ጎን እንሠለፍ! አንድ ነገር አንዘንጋ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው ሞኝ አይደለም፤ አስተዋይ ነው። ለመሆኑ መሪዎቻችን አገር ይፈርሳል ብለው ያላስፈራሩበት ዘመን አለ? እነርሱ አንድባንድ ፈረሱ እንጂ አገርስ አለች!

የኤርትራን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አካሄድ እናስታውስ። በ1983 ዓ.ም. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል፣ በቅድሚያ ያደረገችው ከእስንድርያ ግብጽ ኦርቶዶክስ እውቅና ማግኘት ነበር፤ በወቅቱ የነበሩት አቡነ ሸኑዳ ሳልሣዊ ለጥያቄው ወዲያው ምላሽ ሰጥተዋል። ይኸ ዛሬ እንደማይደገም ምን ማስተማመኛ አለ? ግብጾች ውሃችንን እየቀዱ መልሰው ለማደፍረስ እንዳደቡ ነው። እንፍቀድላቸው ወይስ ነቅተን እንቋቋማቸው?

ወደ መፍትሔ ለመቃረብ፣ ነገሮችን ከማወሳሰብ እንቆጠብ። እንደ ቀድሞው ዘመን፣ በዘመነ ቴክኖሎጂ ነገር መሠዋወር እንደማይቻል አንርሳ። ማንም ያፈቀደውን ማመን ወይም አለማመን፣ ቤተክርስቲያን ለመሳለም ላለመሳለም፣ አፈቀደው ሄዶ ማምለክ መብቱ እንደሆነ አንርሳ። ቤተክርስቲያን ጥሪዋ በተቀዳሚነት የክርስቶስን ወንጌል መስበክ እንጂ የራሷን ድርጅት ወይም ታሪክ ማግነን አይደለም። ጥሪዋን የምትወጣው በፍቅርና በሰላም እንጂ በክርክር በዛቻና በጥላቻ አይደለም። እናበጃለን ያልነውን ይልቅ በእልኽ እንዳናባብስ እንጠንቀቅ! ቤተክርስቲያን ለሰው ሁሉ ፍቅር ሳታሳይ ወገን ለይታ በመቆራቆስ ክርስቶስን ማስደሰት አትችልም፤ እርሱን አለመታዘዝ ደግሞ ሌላ የራሱ መዘዝ አለው! ይኸ ለኦርቶዶክሱም ለጴንጤውም አንድ ነው። ፈተናው የሁላችን ነው። መፍትሔው ብዙ ጥንቃቄና ጸሎት ይጠይቃል፤ ይልቊን ብዙ ንስሃ። የቤቱ ጌታና አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያኑ ይድረስላት። በቤቱ ለሾማቸው ማስተዋልና ጥበብ ይስጥ።

መስከረም 2/2012 ዓ.ም.