ሁለት እግር አለኝ ብሎ

leopard climbing

ፈርጠም ያሉ እግሮች አሉኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ለመውጣት የሞከረን ጎረምሳ ታሪክ አንደግመውም። ሁለትና ሦስት ጉዳይ ባንዴ ማከናወን ዘመናዊነት፣ ጒብዝናና ቅልጥፍና ማስመስከሪያ ሆኗል። “መልቲ ታስኪንግ” ይሉታል። ሐቁ ግን የሰው አእምሮ በወረፋ ካልሆነ ድርብርብ ተግባራትን ማከናወን እንደማይችል ሳይንስ ደርሶበታል። መጽሐፍማ ቀድሞ፣ ስትወድ፣ ስትሠራ በአንድ ልብ አእምሮና ኃይል እንጂ በተከፈለ ልብ አእምሮና ኃይል አይሁን ሲል ደምድሞታል። [ማር 12፡30፣31። መክ 9፡10]

ዘመናዊ ይምሰል እንጂ ባህሉን የጀመሩት እናቶቻችን ናቸው። ልጅ አዝለው እንጀራ ይጋግራሉ ሽሮ ያፈላሉ። ልጅ እያጠ-ቡ ጥጥ ይፈትላሉ፣ ቡና እየጠጡ፣ ምስር ይለቅማሉ፣ ይጠያየቃሉ። የእናቶቻችንን ልዩ የሚያደርገው፣ እንደ ዘመናዊው በራስ ላይ አለማተኮራቸው ነው፤ ሌላውን ማስቀደማቸው፤ እርካታ የሚያጎድል ጥድፍያ ሳይኖርበት ሁሉን በቦታውና በጊዜው ማከናወናቸው ነው።

+ + + +

ዘመናዊነት ድንኳኑን ቤተክርስቲያን ደጅ ዘርግቶአል። አምልኮ፣ መዝናኛም ነው። ጽሞና፣ ትርዒት። ቃላት ማዥጎድጎድ፣ መንፈሳዊነት። ሁለቱንም አንድ ላይ ማድረግ ይቻላል ነው። ጸጥታ የሚባል ጠፍቷል። (ዝላይና ኡኡታ ጽሞና ሊሆን አይችልም!) የለየ አቋም መውሰድ መክሰር ነው። “አይ ኒድ ቱ ኪፕ ማይ ኦፕሽንስ ኦፕን” ይላል፤ ትርጓሜው፣ ሁለት ምላስ ማለት ነው፣ የተከፈለ ልብ፣ አለመሰጠት፣ አለመታመን ነው፤ የሰው ፊት ማየት፣ የሰው ሙገሳ መሻት ነው፤ ባዶ መቅረት ነው! “ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፣ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መስዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና። እግዚአብሔር በሰማይ፣ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፣ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኲል፤ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን …ለአፍህ አርነት አትስጥ” የሚለው ተዘንግቶአል። [መክ 5፡1-]

ሰው በአንድ ጊዜ ከአንድ ነገር በላይ ማከናወን አይቻለውም። ሰው አምላክ አይደለማ! እግዚአብሔር፣ በተከፈለ ልብ ለሚቀርበው፣ ራሴን፣ ሰውና እግዚአብሔርን አስደስታለሁ የሚለውን፣ ከአሳቤና ከአሳብህ መሓል አንዱን ምረጥ ይለዋል! [ኢያሱ 24:15]

በሁለት በሦስት አሳብ መሆን ማንከስ መዋተት ነው [1ኛ ነገሥት 18፡21]። እረፍት የለሽ የስጋት ኑሮ ነው። ባንዴ ሁለት ዛፍ ላይ ካልወጣሁ የሚል ጫፍ ሳይደርስ ወድቆ ይሰበራል። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ላስቀደመ ብቻ በጎ ሁሉ ይጨመራል።

Photograph by Richard De Gouveia