በር ያስገባልበር ያስወጣልወዴት ያስገባልወዴት ያስወጣል

doors

በር መሸጋገሪያ ነው፤ ከአዲስ ወደ አሮጌ ሁኔታ መሻገሪያ፤ ከአሮጌ ወደ አዲስ መሻገሪያ። ከሞት ወደ ሕይወት። ከሠፈር ወደ ሌላ ሠፈር። ከዛሬ ወደ ነገ። ከሹመት ወደ ሽረት፤ ከሽረት ወደ ሹመት። ሽግግሩ አንዳንዴ በምርጫ ነው፣ አንዳንዴ ያለምርጫ። መወለድና ሞት በምርጫ ነው?

ተሻግሮ ከበር ወዲያ ምን እንደሚገጥም አይታወቅም። በግራ ወይስ በቀኝ በር መግባት ይሻላል? በመስታወቱ ወይስ በብረቱ? በድፍኑ ወይስ በሚያሳየው? ማመንታት አለ። ባወጣው ያውጣው ብሎ የሚገባበት አለ። ምርጫው ሐዘን ሊያስከትል ይችላል፤ ደስታና ሰላም ሊያመጣ ይችላል።

አፉን ከፍቶ የሚጠብቅ በር አለ። ተዘግቶ ከመቆየት ብዛት ሸረሪት ያደራበት አለ። የሚገባበት አጥቶ የሚያዛጋ፣ መታጠፊያው የዛገ፣ ሲከፈት ቅር ቀረረረርር የሚል አለ። ተዘግቶ የማይገጥም በር አለ። በግድ የሚዘጋ፣ ቂም እንደ ያዘ ሰው ነክሦ ተደብድቦ በግድ የሚከፈት አለ። ተዘግቶ የተከፈተ ያህል የላላ በር አለ። ሲዘጉት መልሶ መልሶ የሚከፈት፣ እንደ ችኮ ልጅ እልኽ አስጨራሽ በር አለ።

በተከፈተው ዘው ብሎ መግባት። ወይም የተዘጋውን ማንኳኳት፤ እስኪከፈት መጠበቅ። ወይም አለመጠበቅ፤ ጥሎ መሄድ። ተዘግቶ ከበስተኋላው ምን እንዳለ አያስታውቅም።

ያገኘውን በር ከፍቶ ለመግባት የሚደፍር ሰው አለ። ገብቶ በዚያው ቀረ፤ አልተመለሰም፤ በሩ በላው? መግባት የማይደፍር አለ። ስላልደፈረ፣ ምን ይጠብቀው እንደ ነበረ ስላላወቀ፣ እንደ ተፀፀተ ይኖራል። ምነው በገባሁ ኖሮ ይላል።

ለወዳጆቹ:- አንድ ጊዜ የተከፈተ በር አጋጥሞኝ፣ ልግባ? ልተው? ብዬ አመነታሁ። ከውስጥ የሚከፍትልኝ አይኖር ይሆን አልኩ። ኋላ ስሰማ በሩ ክፍቱን ነበር አሉኝ! የያዝኩት ቊልፍ ይከፍተው ነበር አሉኝ። እኔ ግን በሩን ከፍቼ አፋፍ ላይ ቢያወጣኝስ ብዬ ፈርቼ ተውኩት!

በተከፈተው በር አንገቴን አስገብቼ ምንም ስላላየሁ ወዲያው ተመለስኩ የሚል ደግሞ አለ፤ ለካንስ ከገባሁ በኋላ አንድ እርምጃ ወደ ቀኜ ብታጠፍ ኖሮ ወደ ትልቁ አዳራሽ የሚያስገባ ሌላ የውስጥ በር ነበር። ደርሼ ለጥቂት! ወየሁ! ምነው በገባሁ ኖሮ! ያሳለፍኩትን መከራ አላየው ነበር ይሆን?

አንዳንድ የተዘጋ በር:- ከውጭ ለቆመ “አትገባም”፤ ከውስጥ ለቆመ “አትወጣም፣ ለደህንነትህ ሲባል መዘጋቱ ይበጃል” ይለዋል።

በር ካለ፣ ከውስጥ ሰው አለ ማለት ነው? ከውስጥ ሰው ካለ፣ ከውጭ ለመግባት የሚጠብቅ ሰው መኖሩ እንዴት ይታወቃል? ከውጭ ይሁን ከውስጥ የቆመው ሰው አሳቡ በጎ ይሁን ክፉ በምን ይታወቃል? ለሚያንኳኳ ለመክፈት ወይም ላለመክፈት እንዴት መወሰን ይቻላል? የሰላም ማንኳኳት ያስታውቃል? የሰላም ማንኳኳት ከጣዕር ማንኳኳት በምን ይለያል? ማለዳ ማንኳኳት፣ እኲለ ሌት ከማንኳኳት በምን ይለያል?

ሲንኳኳ ሰምቼ ምነው በከፈትኩ ኖሮ ይላል። ለራሱና ለወዳጆቹ፦ አንድ ጊዜ ደጅ ተንኳኲቶ፣ ልክፈት? አልክፈት? ብዬ ሳመነታ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ። ጧት ስነቃ ማታ መንኳኳቱ ትዝም አላለኝ። ተንኳኲቶ እንደ ነበረ ያስታውስኩት ውሎ አድሮ በሁለተኛው ቀን፣ ፖሊስ በሩን ሰብሮ ገባ የሚል ዜና ስሰማ ነው።

ሲንኳኳ ሰምቼ ጆሮዬ ነው አልኩ፤ ሲደግመው ጆሮዬ ነው ወይስ በዚህ ሰዓት ማ ያንኳኳል አልኩ። ሲደግመው፣ ከደጅ ሰው ሳይኖር አይቀርም አልኩ። የምሩን ከሆነ ትንሽ ልጠብቅና ልይ አልኩ። ጠበቅሁ። ጠብቅሁ። ጠበቅሁ። ጥርሴ ባይኖር ልቤ ባፌ ሊወጣ ትንሽ ቀርቶታል። ሳንባዬ በአየር ተወጥሯል። እንደ ገና የተንኳኳ መሰለኝ፤ ጆሮዬ ነው ወይስ እውነት ተንኳኲቶ ነው አልኩ። አላስችል ሲለኝ ብድግ ብዬ ተነሳሁና ከፈትኩ። ስከፍት ከደጅ ማንም የለም። ጆሮዬ ነው ወይስ ስዘገይ ትቶ ሄዶ ነው አልኩ። እስከ ዛሬ መልስ አላገኘሁለትም።

አራት በር ፊቴ ተደቅኗል። በቢጫው ወይስ በቀዩ ወይስ በሰማያዊው ልግባ? አራተኛው በር ደጅ ይመስላል፤ ክፍት ነው ወይስ ዝግ? ልግባበት ወይስ ይቅር?

ምትኩ አዲሱ

ጥር 28/2012 ዓ.ም.

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave