ሕይወት ተሰጥቶናል፤ ሕይወት ይሻለናል!

ሙግቱን በአንድ እውነታ ላይ ብቻ የመሠረተ እንደ ክርስትና ያለ ሃይማኖት የለም። ጳውሎስ፣ “ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው፤ እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ደግሞም፦ ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል …እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።” በማለት ክርስቶስ ከሙታን መነሣቱን በእርግጠኝነት አውጇል [1ቆሮ.15፡13-19]። የክርስቶስን ትንሣኤ መቀበልና አለመቀበል ሁለቱም ዘላለማዊ ውጤት ያስከትላል። በጥንቃቄ መረጃዎቹን መመርመር  ከሞት ያድናል፤ ወደ ሕይወት ይመራል።

ትንሣኤ የማይመስል ነገር ነው የሚሉ፣ እንደ ዛሬው ያኔም ነበሩ። የሙታን ትንሣኤ አለ የሚሉ ዛሬም ቀድሞም ነበሩ። ትንሣኤ የለም የሚሉ፣ መረጃ ስለ ጠፋ ሳይሆን የምሥራቹን ስላልሰሙ፣ ወይም ሰምተው ለማመን ስላልፈቀዱ ነው። ጳውሎስ፣ “አንተ ሞኝ፣ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም” በማለት የሚጠራጠሩና የሚቃወሙትን እንዲያምኑ ያበረታታቸዋል። ትንሣኤ ለሰው የማይቻል ነው። ለእግዚአብሔር ግን ይቻላል! ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለም!

ለመሆኑ፣ ሰዎች ለምን የሙታን ትንሣኤ እንደሌለ ያስባሉ? ዋነኛው ምክንያት፣ ትንሣኤን ካመኑ የሕይወታቸውን አቅጣጫ ለመለወጥ ስለሚገደዱ ነው፤ እውነት ነው ብለው የያዙት ሊፋለስባቸው ነው። ስለኖሩት ሕይወት ሊጠየቁበት ነው። ትንሣኤ ማረጋገጫ ማኅተም ነው፦ ኢየሱስ የተናገረው እውነት ስለ መሆኑ [ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው ስለ መሆኑ፣ የመስቀል ሞት ሙቶ ከሙታን በሦስተኛ ቀን ስለ መነሣቱ]፣ ስለ እግዚአብሔር አብ [ቤዛ አድርጎ እንደ ላከው]፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ [የእውነት መንፈስ፣ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራ፣ በሚያምኑት ውስጥና ጋር ስለ መኖሩ]፣ ስለ ቤተክርስቲያን [በክርስቶስ ስለሚያምኑት አንድነት፣ አካሉ ስለ መሆናቸው፣ የሲዖል ደጅ እንደማይቋቋማት]፣ ስለ ሰው [ኃጢአተኛነቱ፣ ራሱን ማዳን እንደማይቻለው፣ ለኃጢአቱ ዋጋ ስለ መከፈሉ]፣ ስለ ጽድቅ [በክርስቶስ በኩል የኃጢአት ይቅርታ መታወጁ፣ ጽድቅ በርሱ በማመን ብቻ መሰጠቱ]፣ የራሱ የሆኑትን ሊሰበስብና በርሱ ባላመኑት ሊፈርድ ዳግመኛ ስለመምጣቱ፣ መንግሥተ ሰማያት [ምድራዊ ሕይወት እንደሚያበቃ፣ ይህ ዓለም መሸጋገርያ እንጂ ዋነኛና ዘላቂ እንዳይደለ]፣ ወዘተ።

ይኸ እኔን አይመለከተኝም፣ ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ ነው ማለት ይህን ታሪካዊ እውነት አንዳች አይለውጠውም። ሁለት መንገድ አለ፤ አንዱን መምረጥ የግድ ነው። የኢየሱስ መንገድ፣ የሰው መንገድ። የሕይወት መንገድ ወይም የጥፋት መንገድ። ሁለቱን ማስታረቅ ከንቱ ድካም ነው። ኢየሱስ እውነተኛው የሕይወት መንገድ “እኔ ነኝ” ብሏል። ሌላ መንገድ የለም።  መንገድ የጠፋበት ሰው እኮ ማንንም ይከተላል፤ ኢየሱስ ጋ ሲደርስ ታዲያ ምነው? ሰው የኃጢአት ይቅርታን በነጻ ለምን አይቀበልም? ዓለም የማያውቀውንና የማይሰጠውን ሰላም ለምን ይገፋል? የማይጨልም የማያሳፍር ተስፋ ተዘርግቶለት ለምን ይዘገያል? ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ ከደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፣ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” [ራእይ 3፡20]። ያለ ትንሣኤ፣ የኢየሱስ ሞት ተስፋ የማይሰጥ፣ የንጹሕን ሰው ደም ያፈሰሰ በደል ከመሆን አያልፍም። ትንሣኤ ያለ ቀራንዮ፣ ሰዎች ራሳቸውን ለማታለል የቀመሙት ተረት ብቻ ይሆናል። ዓርብና እሑድ ማለዳ፣ ቀራንዮና ትንሣኤ አይነጣጠሉም። በዚህ ዘመን ቀራንዮን የሳተ ወንጌል እየሰበክን ይሆን?

እስቲ ወደ መሠረቱ እንመለስ። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቀለ። ኢየሱስ ሞተ። ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ ተቀበረ። ኢየሱስ የተቀበረበት መቃብር ባዶ ሆኖ ተገኘ። ኢየሱስ ከሙታን ተነሣ፤ ከተነሣ በኋላ ወዳጆቹም ጠላቶቹም አዩት። ያዩትም መሰከሩ። ጳውሎስ የተሰኘው ሳዖል ጠላት የነበረ ምስክር ነው [“እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር” የሐዋርያት ሥራ 26፡9]። የጌታ ወንድም ያዕቆብ ሌላኛው ነው [“ወንድሞቹም ስንኳ አላመኑበትም ነበርና … ዘመዶቹም ሰምተው፤ አበደ ብለዋልና ሊይዙት መጡ። ዮሐንስ [7፡3-10፤ማርቆስ3፡21]። ከላይ የዘረዘርናቸውን ታሪካዊ መረጃዎች ከሐዲዎችና የአይሁድ እምነት ተከታዮች ሳይቀሩ የሚቀበሉት እውነት ነው። ኢየሱስን ሲናገር የሰሙት፣ ያዩትና የዳሰሱት፣ ያስተላለፉትን ቃል ዛሬም እንኳ ሰምተው ብዙዎች ያምናሉ። ማረጋገጫም ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላሉ። ካመኑቱ አንዳንዶቹ ዘመዶቻችን፣ ሌሎቹ የቅርብ ወዳጆቻችን፤ የሥራ ባልደረባዎቻችን፤ ከሕዝብና፣ ከነገድ፣ ከወገንም ከቋንቋም የተውጣጡ፣ የተማሩና ያልተማሩ፣ ጎበዛዝትና አዛውንት፣ ሴቶችና ወንዶች ናቸው። ልባቸው እውነቱን ለሚሻ እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤ ያለምስክር አይተዋቸውም ማለት ነው። የገለጠውን እውነተኛውን የሕይወት መንገድ፣ አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን ያምኑ ዘንድ ይታገሣቸዋል። ያቀርባቸዋል፣ ይቀርባቸዋል። ከዚህ የበለጠ ፍቅርና ርኅራኄ የለም።  ምሕረት ተዘርግቷል። ሕይወት ተሰጥቶአል። ምላሹ የያንዳንዱ ሰው ፈንታ ነው።

"... የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ።

ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ። ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ? ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ደግሞም። ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም። ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤ በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል። እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው? በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ። እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ።

ነገር ግን ሰው። ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው። ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው። የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና። የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። እንዲሁ ደግሞ። ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ። ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ [1ኛ ቆሮንቶስ 15]።"

ሕይወት ይሻለናል፣ ወዳጄ፣ ሕይወት ይሻለናል
ዓለምን ብናተርፍና ነፍሳችንን ብንጥል
ምን ይጠቅመናል ይልቅ ሕይወት ይሻለናል