ነቢይነት ሹመት ነው ጸጋ?

በዘላለም መንግሥቱ

ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤ ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ። 1ቆሮንቶስ 14፥37፥38

በጣም ጥንት የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ስሜ የሚባል የክፍላችን ተማሪ ነበረ። በመጀመሪያው የትምህርት ቀን የክፍል አስተማሪያችን ስማችንን ሲመዘግብ እኔ አጠገብ የተቀመጠው የስሜ ተራ ደረሰ። አስተማሪው፥ “ስምህ ማነው?”  አለው። “ስሜ ሲአሞ”  ብሎ መለሰ። “ሲአሞ ማን?” የአያቱን ስም ተናገረ። እስከ አያቱ ተጠይቆ መናገሩ ገርሞናል። ልጁ ስሙን ከነአባቱ ሲናገር አስተማሪው፥ “ስሜ ሲአሞ ነው” ያለው ነበር የመሰለው። ከዚያ በኋላ በደንብ እስኪያውቀው ድረስ ለብዙ ሳምንታት አስተማሪያችን ስሜን በአባቱ ስም ሲአሞ እያለ ይጠራው ነበር። አሁንም በልጅነቴ አንድ ሰው አባቴን የሚጠራው አጠራር ከነድምጹ ይታወሰኛል። ሲጠራው “ጋሼ ሻምበል”  ይለው ነበር። ሻምበል ስሙ መስሎታል፤ ወይም ከማዕረግ በፊት ሌላ የማዕረግ ፎቅ መደረቡ ነው።

በቅርብ ደግሞ አንድ ዲቪዲ ላይ ይሰብክ የነበረ ሰውን ሲመለከቱ አንድ ቤት ደረስኩና ማን መሆኑን ስለማላውቅ ጠየቅኩ። ስሙን፥ “ነቢዩ ይባላል፤ ነቢዩ እገሌ” አለችኝ አንድዋ እኅት። ሌላዋ ደግሞ፥ “የለም ስሙ እገሌ ነው እንጂ ነቢዩ አይደለም፤ ነቢዩ ሹመቱ ማዕረጉ ነው”  ብላ አብራራች። አስተማሪያችን ልጁን በአባቱ ስም ጠራ። እዚህ ደግሞ ማዕረጉና የሰውየው ስም ተምታቱ። የተምታቱ ነገሮች ዘመን ላይ ነን።

ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት ሐዋርያው እገሌ የሚባለውን ሹመት ተከትሎ አምናና ዘንድሮ ደግሞ ነቢዩ እገሌ የሚባሉ ሰዎች መታየት ጀምረዋል። “እውነት ሐዋርያት በዚህ ዘመን አሉ?” ተብሎ ለተነሣው ጥያቄ በሁለቱም አቅጣጫ ሰፋ ያሉ ነገሮች ተብለዋል። እኔ ከቃሉ እንደምረዳው ሐዋርያ የሚባል አገልግሎት አለ። አንዳንዶቹ ‘ቢሮ’ እንደሚሉት ግን ሹመት አይደለም። ሐዋርያ ማለት ወንጌልን ይዞ ቤተ ክርስቲያን ልካው ወንጌል ወዳልተነገረበት ጠፍ ምድር ወንጌልን ሊሰብክ የሄደ ቤተ ክርስቲያን ቆርቋሪ ወይም ተካይ ሰው ነው። የሄደ ሰው። በአማርኛ ቃሉ ራሱ የሄደ ማለት ነው። አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ቋንቋ ደግሞ የተላከ ማለት ነው።  ሐዋርያ ማለት ይኸው ነው። ይህንን የሚያደርጉ ሐዋርያ ቢባሉ ትክክል ነው። ይህ እንግዲህ በዚህ ዘመን ነው። ያኔም ሆነ አሁንም ሐዋርያነት የጸጋ ስጦታ ነው፤ ይህ ስጦታ የተሰጣቸው ሰዎች ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡበት ሁኔታም ነው። ሁለቱም ነው። በዘመናችን እንደሆነው ግን ሐዋርያነት የብዙ ዘመን አገልግሎት መለዮ ወይም ከፍተኛ የሹመት እርከን ወይም የክብር ማዕረግ አይደለም።

ያኔ ጌታ የሾማቸውና በቀጥታ የላካቸው ሐዋርያት በራሱ የተሾሙ ናቸውና መደባቸውም ሹመታቸውም የተለየ ነው። ጌታን ያወቅንባቸውን ቃሉን የጻፉልን ብቻ ሳይሆኑ በእጆቻቸው ድንቆችና ምልክቶች የተደረጉባቸው ሰዎችም ናቸው። ከአምናና ካቻምና ወዲህ የሚታዩት ሐዋርያት የሐዋርያነትን ሹመትና ማዕረግ ከሚያሳድዱ ይልቅ የሐዋርያን አገልግሎት ቢሹ ኖሮ ምንኛ ድንቅ ነበር። ዘንድሮ ስማቸውንም ሳይቀር እየቀየሩ ሐዋርያው ጳውሎስ እና ነቢዩ ዳንኤል ተብሎ መጠራት ወግ እየሆነ ነው። ዝም ከተባለ ይህኛው ሥልጣን ከዓመት ወይ ከሁለት ዓመት በኋላ ይነፍስበትና በሚቀጥለው ደግሞ ንጉሡ ዳዊት ሳይሆኑ ይቀራሉ?  አሁንም እንኳ ‘የንጉሥነት ቅባት’ የሚሉትን የጀመሩ የቃል-እምነት ሰባኪዎች ብቅ ብቅ ብለዋል። እኛስ ደህና፤ ብቻ ይህ ከምድራዊ መንግሥትም ጋር እንዳያጋጫቸው ያስፈራል።

አሁን ደግሞ ስለ ነቢያት እንይ። እነዚህ ሰዎች እውነት ነቢያት ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ከመጠየቃችን በፊት ነቢይ ምንድርነው? ምን ያደርጋል? ብለን መጠየቅ ለንጽጽር ይረዳናል። ነቢይ ማለት ትርጉሙ እግዚአብሔርን ወክሎ የሚናገር ወይም ለእግዚአብሔር የሚናገር ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን ቋንቋ ነቢይ የሚናገር (ናቢ)  ወይም የሚያይ (ሮዔ)  ይባላል። ሮዔ ባለ ራዕይ እንደሚባለው ማለት ነው። ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም ሲናገር ያ የሚናገረው ነገር የራሱ አይደለም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ነውና ሥልጣን አለው፤ ከተጻፈም ዘመናትን የማለፍ ኃይል አለው። ነቢዩ ሲያይ ወይም ሲሰማም በተራ ዓይንና ጆሮ ከሚቀበሉት ያለፈ ነገርን የተቀበለ ሰው ነው። እንደ እግዚአብሔር ወካይነቱ በተወከለለት ኃይል ለሁሉ የሚታዩ ግልጽ ዓላማቸውም የላከው ክብር፥ ግባቸውም የሕዝቡ ጥቅም የሚሆኑበትን ተአምራት ያደርጋል። የብሉይ ኪዳን ነቢያት ይህን የሆኑ፥ እነዚህንም ያደረጉ ናቸው።

በዘመናችን እየታዩ የመጡት ነቢያት ከአገልግሎት አንጻር ስለሆነ ከዚህ መነሻ ትርጉም ተንደረደርኩ እንጂ በብሉይ ኪዳን ነቢይ የሚለው ቃል ከዚህ ሌላ አሳብንም የያዘ ነው። ከላይ እንዳየነው ወክሎ ቃልን የመናገር ወይም አይቶ የማሳየት ነገር ያላደረጉ ሰዎችም ነቢይ ተብለው ተጠርተዋል። ምናልባት ተናግረው ይሆናል አልተጻፈም እንጂ የሚለውን አልተጻፈምና አናነሣውም። በዚህ ተርታ አብርሃም ነቢይ ተብሎአል፤ አሮንም ነቢይ ነበር [ዘፍጥረት 20፥7፤ ዘጸአት 7፥1]። ሌሎችም የአሮንን እኅት ማርያምን፥ ሰፋኒቱን ዲቦራን፥ ናታንን፥ ጋድን፥ የኢሳይያስን ሚስት ጨምሮ ነቢያት ናቸው። ነቢያት ሲታሰቡ በብሉይ ኪዳን ዘመንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ሐሰተኞች ነቢያትም መኖራቸውና እውነተኛ ነቢያት ከሐሰተኞቹ ተለይተው የሚታወቁባቸው የተዘረዘሩ መፈተሻዎች መኖራቸውም መረሳት የለበትም። ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ በአዲስ ኪዳን ነቢያት መኖራቸው እውን ነው። ነቢይ ሲባል በዘልማድ የሚመጣልን ትርጉም ወደፊት የሚሆነውን የሚናገር የሚል ነው። ይህ ነቢይ ከሚያደርጋቸው ነገሮች አንዱና ዋና ያልሆነው ነው። ይህ ዋናው የነቢይ ትርጉም አይደለም። ይህንን ለመረዳት የነቢያትን መጻሕፍት ማንበብ ብቻ በቂ ነው። የአብዛኞቹ ነቢያት አብላጫው ይዘታቸው የቀደመው ወይም በጊዜው የነበረው ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንጂ ወደፊት የሚሆነውን የሚናገር አይደለም። ስለወደፊት የሚናገረው የፍርድም ይሁን የበረከት ቃል በአንድ አንቀጽ ወይም በአንዲት ጥቅስ ብቻ ተጽፎም የሚገኝባቸው የትንቢት መጻሕፍት አሉ።

አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ቋንቋ ነቢይ ወይም ትንቢት ተናጋሪ ገልጦ የሚናገር፥ አውጥቶ፥ ወደፊት አምጥቶ የሚናገር ማለት ነው። ነቢይ ቤተ ክርስቲያንን ለራእይዋ፥ ለተልእኮዋ፥ ለጥሪዋ የሚያነሣሳ መልእክት የመናገር ስጦታ ያለው ወይም ከላይ እንደተገለጠው እውነትን ገልጦ በማሳየት መነሣሳትን የሚያመጣ አገልጋይ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ እንደምናየው ነቢያትም ነበሩ፤ የትንቢት ስጦታም ነበረ። ነቢይነት ግን ሹመት ሆኖ እነዚህ ሰዎች “ነቢዩ እገሌ” ሲባሉ አይታይም። በሐዋርያት ሥራ 13፥1 በአንጾኪያ ነቢያትና መምህራን እንደነበሩ ተጽፎ ስማቸውም ተዘርዝሮአል። ግን ነቢዩ በርናባስ፥ መምሬ ስምዖን፥ መጋቢ ሉክዮስ፥ ወዘተ እየተባለ አልተጻፈም። ጸጋው አላቸው ጸጋው ግን ሹመታቸው አልነበረም። በሐዋ. 15፥32 ይሁዳና ሲላስ ነቢያት ነበሩ። ግን ነቢዩ ይሁዳና ነቢዩ ሲላስ አልተባሉም። ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው በማጽናታቸው ጸጋቸው ከአገልግሎታቸው ጋር በጉልህ ተጽፎአል። በሐዋርያት ሥራ 21፥10 ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተብሎ ተጽፎአል። ነቢዩ አጋቦስ ግን አልተባለም። ምንድርነው ልዩነቱ ነቢዩ አጋቦስ እና አጋቦስ የሚሉት ነቢይ ቢባል ልዩነቱ ትኩረቱ ነው። ነቢይ እና ነቢዩ የተለያዩ ናቸው። ሐዋርያና ሐዋርያው የተለያዩ እንደሆኑ ማለት ነው። በነገራችን ላይ፥ ነቢዩ የሚባል ወይም የተሰኘ ነቢይ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የለም። ከኢየሱስ በቀር። አዲስ ኪዳን ነቢዩ የሚለውን ቃል ሲጠቅስ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ሲገልጥ ብቻ ነው።

በ1ቆሮንቶስ 12፥28-29 እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ነቢያትንም ማድረጉ ተጽፎ ነቢያት ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ተጽፎአል። በ14፥29 ደግሞ ነቢያት ሁለት ወይ ሦስት ሆነው በጉባኤ እንዲናገሩ ሌሎችም እንዲለዩአቸው ተጽፎአል። ነቢይ የሆነ ወይም የመሰለው ማንም ስጦታውንና ስፍራውን ለመረዳት ጠንቅቆ መረዳት ያለበት ምዕራፍ ይህ 1ቆሮንቶስ 14 ነው። ነቢይነት ሥልጣን ከቶም አይደለም። ለነገሩ የአዲስ ኪዳን ወይም የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን በሰው ትከሻ ላይ ተረማምዶ ወደ ቆጥ ወጥተው የሚሰቀሉበት ሳይሆን ትኅትናን እንደ ልብስ ተላብሰው እርስ በርስ እየተዋረዱ ዝቅ በማለት የሚያገለግሉበት ነው። አንዳንዶች ዛሬም ከቀደሙት ተርታ ብቻ ሳይሆን ከቀድሞዎቹ የበለጡ ሐዋርያትና ነቢያት በዘመናችን እንዳሉ ወደፊትም እንደሚነሡ ይናገራሉ። በምዕራቡ ዓለም ሐዋርያው ወይም ነቢዩ የሚባሉት እንዲያውም ከቀደሙት ነቢያትም አቻ ብቻ ሳይሆን የላቁ መሆናቸውን ለማሳየት ሐዋርያትና ነቢያት ብቻ ሳይሆን “Super Apostles and Prophets” እየተባሉ ነው የሚጠሩት። ከቃሉ እንደምንረዳው የቀደሙቱ ሐዋርያትና ነቢያት በምልክትና በድንቆች ማንነታቸው የተገለጡ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን እናጢን፤ ምልክቶችና ድንቆች ሁሉ የሐዋርያነት ምልክት ሊሆኑ ያለመቻላቸው ወይም በሰይጣንም ሊደረጉ የሚችሉ መሆናቸው አንዱ ነው። ሌላው ደግሞ፥ በዘመናችን ተደረጉ የሚባሉት ምልክቶች አንዳንዶቹ በቅርበት ሲጤኑ ያሉ የመሰሉ ግን ከቶም ያልኖሩ መሆናቸው ነው።

እነዚህን ነጥቦች ይዘን የዘመናችን ነቢያትና ሐዋርያት ከቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያትና ሐዋርያት ተርታ የማይሰለፉ መሆናቸውን ከሌላም አንጻር እናያለን። ይህን የአሁኖቹ በላጮች መሆናቸውን የሚያስተምሩ ሰዎች ትልቅ ስሕተት እዚህም ላይ ነው። የቀድሞዎቹ ነቢያትና ሐዋርያት የእምነታችን መሠረቶች ናቸው። በሐዋርያትና ነቢያት መሠረት ላይ ተመሥርተናል፤ የማዕዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ነው [ኤፌሶን 2፥20]። ከዚህ አንጻር የዛሬዎቹ ሐዋርያትና ነቢያት እነዚያን ሊሆኑ ከቶም እንደማይችሉ እናያለን። ሌላ አዲስ ነገር እየመሠረቱ ካልሆነ በቀር። መሠረቱ አንዴ ተመሥርቶአልና በየዘመናቱ እንደገና አይመሠረትም። ነቢያት ነን የሚሉ ሰዎችን ነቢይነታቸው ጸጋ ወይም ሥልጣን መሆኑን እንዲናገሩ ማድረግ ተገቢ ነው። ጸጋ ከሆነ ነቢዩ እገሌ መባል የለባቸውም። ከሆነ የመስጠት ጸጋ ያለው “ለጋሱ እገሌ” የፈውስ ስጦታ ያለውም “ፈዋሹ እገሌ”  እውቀትን መናገር የተሰጠው “አዋቂው እገሌ” በልሳን መናገር የተሰጠውም “ልሳናሙ ወይም ባለ ልሳኑ እገሌ” ሊባሉ ነው። እነዚያ ነቢዩ ከተባሉ እነዚህም እንዲህ የማይባሉበት ምክንያት የለም። እንዲህ ያሉ ሰዎችን በቃሉ መሠረት መርታት ካልቻልን መራቅ አለብን።

ሌላው በነዚህ ራሳቸውን በራሳቸው በሚሾሙ ሰዎች ዘንድ የሚታይ ከፍተኛ የሥልጣን ጥም አለ። ከገንዘብ ጋር ክፉኛ የመቆራኘትና ሰዎችን መጠቀሚያ ለማድረግ ሥጋዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ጠምዶ የማቆየት ሥርዓትም አለ። እንዲህ ከሆነ እነዚህ እውነተኞች ሳይሆኑ ሐሰተኞች ነቢያት ናቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ በመልእክቶቻቸው አጽንተው የገለጡልን ሐሰተኞች ነቢያትም እንደሚነሡ ነው፤ 2ጴጥሮስ 2፥1 እና 1ዮሐንስ 4፥1። እና ነቢዩ እገሌ ሲባል እናጢን፤ እንጠንቀቅ፤ እናስተውል፤ እንጠይቅ። ጌታ ከአርያም ይባርካችሁ።