አ ገ ል ጋ ይ  መ ሪ ነ ት

ነቢዩ ኢሳይያስ

nebiyouPic1. የአገልጋይ መሪ ምንነት። አገልጋይ መሪነት የሚለው ንድፈ ሓሳብ በማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት የራሱ የሆነ ይዘት፣ሓሳብና ትንታኔ አለው። የሓሳቡ መነሻ የተወሰደው ከመጽሓፍ ቅዱስ ቢሆንም በሙያው ዘርፍ የተሰለፉ ሰዎች ግን ሓሳቡን ያስቀመጡት፣ ለራሳቸው በሚመቻቸው መንገድ ነው፤ ይሁን እንጂ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት በኩረ ቃል “ዲያቆን’’ ማለት ሲሆን፣ ይህም አገልጋይ የሚለውን ያሳያል። ከዚህ ውጭ ግን “ባሪያ” የሚለውን አያመለክትም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ አገልጋይነት ሲታሰብ፣ ያለው አመለካከት ግን ስለ “አገልጋይ መሪነት’’ ሳይሆን ስለ “ባርነት” ነው። የአገልጋይ መሪነት ትክክለኛው ትርጓሜ ግን በሕይወታችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ፣ ሌሎችን ለመርዳት የክርስቶስን መንፈስ ይዞ በትህትና ልብ ማገልገልና መርዳት የሚለውን ያሳያል። በሌላ መልኩ ደግሞ ዝናን፣ ሥልጣንን፣ ሐብትን፣ ክብርንና የተለየ ጥቅምን በመፈለግ ያለ ማገልገል ማለት ይሆናል። በየትኛውም ደረጃ ያለው ሓሳብ መሪነት ሥልጣን ሳይሆን አገልጋይነት መሆኑን በተጨባጭ ማሳየት ነው።

አንድ ሰው አገልጋይ መሪ ሲባል የመሪነት ሥልጣኑን ሌሎችን ለመጥቀምና ለማገልገል እንደ መሣሪያ አድርጎ መመልከት አለበት። ከዚህ ውጭ አገልጋይ መሪ ባለ ሥልጣንና ጌታ ሆኖ መታየት የለበትም። መሪ አገልጋይ ነው የሚለው አስተሳሰብ በአገራችን ካለው አመለካከትና  ባህል ጋር እጅጉን ይጋጫል። በአገራችን የመንግሥት መዋቅር ውስጥና በማህበረሰባችን መካከል አገልጋይ መሪነት በዋናነት ታሳቢ አድርጎ የሚነሳው መሪዎችን ተገልጋይና ገዥ በማድረግ ነው፤ ስለዚህ አንድ ሚኒስትር ከሕዝብ አገልጋይነቱ ይልቅ በሕዝብ ተገልጋይነቱና ገዥነቱ ጎልቶ ሲታይ ኖሯል። በቤተ ክርስቲያን ያለው አገልጋይነት ከዚህ አስተሳሰብና ባህላዊ አመለካከት የጸዳ ስለ መሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

ሰው መሪ ከመሆኑ በፊት ልቡ ከተገልጋይነትና ሥውር ጌትነት መንጻቱ አስቀድሞ መመርመር አለበት። ሥውር ጌትነትን ናፋቂ ልብ ያለው ሰው የታይታና የከበሬታ ወንበር ፈላጊ አገልጋይ እንጂ አገልጋይ መሪ ሊሆን አይችልም። በዚሁ መንፈስ ወደ አገልግሎት ከመጣ የመልከኛና ገባሪ የኑሮ ሥርዐትን ያስፋፋል። አንድ አገልጋይ ኑሮው ተፈትሾ ዝናን፣ ሥልጣንን፣ ሐብትን፣ ክብርንና የተለየ ጥቅምን ከመፈለግ ነጽቶ ካልተገኘ፣ እርሱ ሎሌ ወይም አገልጋይ መሪ ነው ለማለት ይከብዳል። እንዲህ ማለት ግን ወንጌልን በመስበከና በማስተማር ለሚያገለግል ወንጌል የሚፈቅድለት ደምወዝ አይገባውም ማለት አይደለም (1ጢሞ 5፡17-18)። የሚያበራየው በሬ አፉ እንደማይታሰር ለሠራተኛም ደምወዙ ይገባዋል (1ቆሮ 9፡13-16)። አገልጋይ መሪነት ዝቅ ማለትን የግድ ይላል። ዝቅ የሚል ማንነት የሌለው ሰው አገልጋይ መሪ ሊሆን አይችልም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ዝቅ ያለማለትና የከበሬታን ወንበር የመፈለግ ችግር ነበረባቸው፤ ስለዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ ወንጌል ሲናገር እንዲህ አለ፦ “ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ። እንዲህም አላቸው። የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ። ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ” (ሉቃ 22፡24-30)።

በማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ የታላቅነት ፈተና ችግር አለ። በአንድ ወቅት ኢየሱስ በራሱ አነሳሽነት ደቀ ዛሙርቱን ወደ ተራራ ላይ ይዟቸው ወጥቶ  ነበር። በዚያም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ኢየሱስም በፊታቸው ተለወጠ፣ ልብሱስም በምድር ላይ አጣቢ አጥቦ ሊያነፃው በማይችል ሁናቴ ነጭ ሆነ። ከጋረዳቸው ደመና ውስጥም ድምጽ መጣ። ጴጥሮስም በክስተቱ በመደነቅ ለእኛ በዚህ መሆን ይሻለናል ሲል፣ ማርቆስ ግን የሚናገረውን አያውቀውም ነበር ሲል በስሜታዊነት መስከሩን ይተርክልናል። የዚህ ክስተት ዋነኛ ዓላማ በመስቀል ላይ ተዋርዶ የሚሞተው ጌታ የራሱ የሆነ ክብር ያለው አምላክ መሆኑን ለእነርሱ ማስታወቅ ነበር። ከተራራው ከወረዱ በኋላ ግን፣ የደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ፈተና ውስጥ የወደቀው “ከመካከላችን ታላቅ ማነው?” በሚለው ጥያቄያቸው ነበር (ማር 6፡10)። ሰው ሁሉ ወደ አገልግሎት ሲመጣ ፈተናው ይኸ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፤ ነገር ግን እውነተኛ ታላቅነት ከሰው ውስጣዊ መንፈስና ልብ ጋር የተያያዘ ነው፤ በቅዱሳን መካከል ታላቅነት ዝቅ በማለት እንጂ ወደ ላይ በመንጠራራት የሚገኝ አይደለም። እንደ አዲስ ኪዳን ትምህርት መሠረት ታላቅነት ሥልጣንን፣ የመሪነትን ሥፍራ፣ ተደማጭነትንና ዝናን ማግኘት ወይም ታላቅ የሆነን ተግባር ማከናወን ማለት አይደለም። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ታላቅነት የሚመጣው በምናደርገው ነገር ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ፊት በትህትና መንፈስ በምንሆነው ነው። ሉቃስ 22፡ 25-27 ላይ እንዲህ ይላል፣ “የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን።” በተለይም ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩ (የሚያስተዳድሩ) አገልጋይ መሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል። እውነተኛ አገልጋይ መሪነት በየትኛውም ቦታ በእምነት፣ በትህትና፣ በመልካም ባህርይ፣ በጥበብ፣ ራስን በመግዛት፣ በትዕግሥትና በፍቅር ሆነን መገኘትን ጠያቂ ነው። እውነታው እንዲህ ከሆነ ታዲያ አገልጋይ መሪነት ምንድነው?፦

ሀ/ ገዥነት ሳይሆን፣ አገልጋይነት ሲሆን፣ ይኸውም የክርስቶስ ኢየሱስ ምሳሌነትና ትዕዛዝ ነው፣ መሪዎች በአገልግሎታቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌነት ሲተው ወዲያውኑ የሚሆኑት ለከበሬታ ወንበር የሚኖሩና ገዥዎች ነው፣ ለ/ በሕይወት ጉዞና በአኗኗር ሥርዐት የክርስቶስ ኢየሱስን ሞትና ትንሣኤ የመከተል ዘይቤ ነው፣ መ/ በአገልግሎት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጂ ራስን ማማከል አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ጨቅላነት በቡድነኝነት አራት ቦታ በተከፋፈለች ጊዜና ሰዎች በአገልጋዮች ዙሪያ በተሰባሰቡ ወቅት “ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ አገልጋዮችና እንደ እግዚአብሔር ምስጢር ባላደራዎች ይቁጠረን” በማለት ተናገረ (1ቆሮ 4፡1)። አገልጋይ መሪ በክርስቶስ ኢየሱስ ዙሪያ እንጂ፣ በራሱ ዙሪያ ሰዎችን አያሰባስብም፤ ራሱንም አያማክልም ወይም ራሱን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለማስተካከል አይዳዳም። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚያገለግላቸውን ሰዎች ምኞቱ ለክርስቶስ ለማጨትና ፍጹም አድርጎ ለማቅረብ ነበር፣ ሠ/ አገልጋይ መሪነት ከክርስቶስ ሙላት (ጸጋና እውነት) ተቀብሎ፣ በሕዝቡ መካከል በመሆን፣ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ በፍቅር መሥራት ማለት ነው። አገልጋይ መሪ ጸጋን ይቀበላል እውነትን ይታዘዛል፣ ረ/ የግዴታ ሳይሆን የምርጫ ሕይወት ነው። የአገልጋይነት መነሻ ሆነ ብሎ የአገልጋይነትንና የኃላፊነትን ሕይወት መምረጥ ማለት ነው፣ ሰ/ ገንቢነት እንጂ አፍራሽነት አይደለም። የዓለማችን ትልቁ ችግር በሥልጣን ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ፣ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ለራስ ጥቅም መሰለፍና በሥልጣን መባለግ ነው፣ ሸ/ ልበ ሠፊነት ነው። ልበ ሠፊነት ራዕይን ለማስፈጸም፣ ከግብ ለመድረስና ውጤታማ ለመሆን ወሳኝ ነገር ነው፤ ስለዚህ አገልጋይ መሪነት ልበ ሰፊ፣ ትዕግሥተኛ፣ የተደላደለና የማይዋዥቅ መሆንን ይጠይቃል፣ ቀ/ ጥሩ አድማጭነት ነው፤ ጥሩ አድማጭ ያልሆነ ነገር ያዛባል ወይም አገልጋይ መሪ ጥሩ አድማጭ ካልሆነ የሚያስተላልፈውን ሊያውቅ አይችልም።

2. አገልጋይ መሪነትና የትሕትና ሕይወት። አገልጋይ መሪነት የትህትናን ሕይወት የግድ ይላል። ለዚህ ምሳሌያችን ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል “ራሱን ባዶ አደረገ” (ፊል 2፡5-11)። ሐዋርያው ጳውሎስ “ራሱን ባዶ አደረገ’’ ሲል፣ መብቱን ሥልጣኑንና ክብሩን በገዛ ራሱ ፈቃድ ተወ ማለቱ ነው። በዚህ ኢየሱስ ራሱን ለደቂቃም ሆነ ለሰከንድ ባለማሰብ ፍጹም  ትህትናውን በማሳየትና የሰው ልጆች ምትክ በመሆን እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህም መንገድ በማገልገል በመጨረሻ አባቱን አከበረ። እርሱ በሰማይና በምድር በትንሳኤው ያለ ልክ የከበረ ጌታ ተደርጎ መሾሙ ወደር በማይገኝለት የትህትና ሕይወቱ ነው። ታዲያ አገልጋይ መሪነት ትህትናን የሚጠይቅ ከሆነ፣ ትህትና ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው ጥያቄ እዚህ ላይ ይነሳል። ትህትና፣ አዲስ ኪዳን መጀመሪያ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ “ኬኖሲስ’’ ማለት ሲሆን፣ ይኸውም የራስን አስፈላጊነት ለደቂቃና ለሰከንድ እንኳ ያለማሰብ (ራስን ፍጹም ባዶ ማድረግ) ማለት ነው። የምናደርገውን ነገር ሁሉ፣ የራሳችንን አስፈላጊነት እያሰብን የምናደርገው ከሆነ፣ ያ ትህትና የሌለበት የትዕቢት ሕይወት ይሆናል። ትህትና ፍጹም ራስን የመካድ ሕይወት ነው። ትህትና በሌላኛው ትርጉሙ ለሌሎች ሰዎች ጥቅም ሲባል የራስን መብት መተው ማለት ነው (ፊል 2፡3)። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አንድ ነገር አድርገን እንዲያከብሩን እንፈልጋለን፤ ሆኖም ያንን ነገር ማድረግ አንችልም እንበል። ስለዚህ ያንን ያጣነውን ነገር ለማግኘት ስንል ራሳችንን ዝቅ ብናደርግ ወይም ከሌላ ሰው አንሰን ለመታየት ብንሞክር፣ እርሱ ግብዝነትና ማስመሰል እንጂ የትህትና ሕይወት ማለት አይደለም። ትህትና ያጣነውን ነገር በተዘዋዋሪ መንገድ ለማግኘት ስንል ራሳችንን ዝቅ በማድረግና ትህትናችንን በአንደበታችን ብቻ እየገለጽን በሌሎች ዘንድ ትሁት በመምሰል የምንታይበት ሕይወት ዘዬ ሳይሆን፣ ሌሎችን ከእኛ እንደሚሻሉ የምንቆጥርበት ሕይወት ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በእኩል ደረጃ ያለ አምላክና ፈጣሪ ነው፤ ነገር ግን እርሱ ትህትናን ያሳየንና ያስተማረን ስለ ራሱ ማንነት እኔ አምላክ ነኝ ብሎ ባለ ማሰብና ራሱን ባዶ በማድረግ ነው። ለዚህ ነው ትህትና ማለት ስለ ራስ አስፈላጊነት ለደቂቃና ለሰከንድ እንኳ ያለማሰብ ሕይወት ነው በማለት የተረጎምነው። ከዚህ ውጭ ከልብ ጋር ያልተያያዘ ትህትና እውነተኛ ትህትና ሳይሆን፣ ምናልባትም ስውርና ድብቅ ኩራት ሊሆን ይችላል። እውነተኛ ትህትና ከላይ የተመለከትናቸውን ሁለቱ የትርጓሜ ሓሳቦች ይይዛል። ይህ ከሌለ ግን አገልግሎታችን ትክክለኛውን የኢየሱስ ክርስቶስን የአገልግሎት እሳቤ የተከተለ ነው ለማለት ያስቸግራል። 

3. አገልጋይ መሪነትና የአገልግሎት በጎ ተጽዕኖው። መሪ አገልጋይ ትውልድን ተጽዕኖ ውስጥ የሚጥል ኑሮና አገልግሎት ሊኖረው ይገባል። ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያቱ በአገልግሎታቸውና በአመራራቸው ትውልድን አሳርፈዋል። መሪ አገልጋይ እንደ መሪ በትውልድ መካከል ትውልድን የሚያሳርፍ መሪ አገልጋይ መሆን ይጠበቅበታል። የትውልዱን ልብ የማናሳርፍ አገልጋይ ትውልድን በወንጌል ተጽዕኖ ሥር አላደረገምና ባያገለግል ይሻለዋል። አገልጋይ በቤተ ክርስቲያን በምናገለግለው አገልግሎት ሕዝብ ሊታመንብን፣ሊያርፍብንና ሊያምነን የማይችልበት ከሆነ፣ አገልግሎት ምን ይሰራልናል? በጌታ ቤት እርስ በእርስ ለመቀባበል አስፈላጊው ነገር ለአገልግሎት የተሰጠን ጸጋ ሳይሆን፣ የባህርይ መቀረጽ ነው። ሰው የአገልግሎት ጸጋ ኖሮት፣ ባህሪዩ ያልተቀረጸና ያልተሞረደ ከሆነ ትውልዱን በተጽዕኖ ውስጥ ማድረግ አይችልም። የኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ትሁት አገልጋይ ነበረ፤ ይሁን እንጂ ይህንን ትህትና የመሠከረው ሐዋርያው ጳውሎስ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱም ስለነበረው የትህትና ሕይወት እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እናንተ ሸክም የከበደባችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፣ከእኔም ተማሩ፤እኔ በልቤ የዋህና ትሁት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬም ልዝብ ሽክሜም ቀላል ነውና” (ማቴ 11፡28-29)።

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በተመላለሰባቸው ጊዜያት ፍጹም ትሁትና ታዛዥ ነበር። የዕብራውያንም  ጸሓፊ ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን እንደተማረ ይገልጽልናል’’ (ዕብ 5፡ 11-12)። እርሱ ለሰው ልጆች የቀረበልን የእረፍት ግብዣ ወደ እዚህ የትህትና ሕይወት የሚያመጣ ነው፤ ሆኖም ወደ እዚህ የትህትናና የእረፍት ሕይወት መምጣት የሚቻለው ደግሞ ቀንበርን በመሸከምና ከኢየሱስ ክርስቶስ የትህትና ሕይወት በመማር ሲሆን፣ እውነተኛው የነፍስ እረፍት የሚገኘው በዚህ ውስጥ ነው። ብዙዎች ወደ ክርስቶስ መጥተው በባህርይ ቀረጻ የሕይወት ልምምድ ውስጥ ያላለፉ በመሆናቸው፣ ስለ አገልግሎታቸው እንጂ ስለ ባህሪያቸውም ግድ የሌላቸውና ኃላፊነት የማይሰማቸው ናቸው። እንዲያውም ያልተቀረጸና አስቸጋሪ ባህሪያቸውን መንፈሳዊነትና ስለ ጌታ ዋጋ የሚከፍሉበት ሕይወት በማድረግ ይወስዱታል። ከዚህም የተነሳ ክፉና አስቸጋሪ አመል እንጂ የትህትና ሕይወት አይታይባቸውም። እንዲያውም ከዓመት ዓመት ከዘመን ዘመን ባልተለወጠና ባልተቀረጸ ጠባይ መመላለሳቸው ያዳናቸውን ጌታ ባህርይና የተጠሩበትን ሕይወት ዓላማ በትክክል ማወቃቸውን በጥያቄ ውስጥ ያስገባል። ሰው በሥላሴ አምሳልና ምሳሌ ተፈጥሯል። ውድቀት ግን ይህንን የእግዚአብሔር አምሳል አደብዝዟታል። እግዚአብሔር ግን በክርስቶስ የመቤዥት ተግባር መልሶ በመስቀሉ ሥራ ቢታደገው እንዲሁም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ቢያድነው መልሶ የልጁን ባህርይ በእርሱ ውስጥ መመልከት ነው (ቲቶ 3፡5፤ ሮሜ 8፡29)። በክርስቶስ መስቀል በኩል የተከናወነው አጠቃላይ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ የጽድቅንና የትሕትናን ሕይወት የግድ ይላል። ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ የዳነው  የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ዕለት ዕለት ለሚለወጥ ሕይወትና ለሚቀረጽ ባህርይ ነው። በተሰጠን ጸጋ የማገልገል ችግር  የለንም። በዚህ ዘመን በእግዚአብሔር ቤት በምንመላለስ አማኞች ሕይወት ግን ብዙ የባህሪ ችግር አለ። ትዕቢት፣እኔነት፣ግብዝነት፣ክፋት፣ ሐሜት ወዘተ… የአማኞች ቀላል ልምምዶች ናቸው። ሰው ሁሉ ቀርበው ሲመለከቱት ክፋቱ፣ ግብዝነቱና ትዕቢቱ ይገለጣል። ማንም ሰው በዚህ የሚስማማ ይመስለኛል። ታዲያ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ይነሳል። ይኸውም ወደ እዚህ የባህርይ መቀረጽ እንዴት እንመጣለን? የሚለው ነው። በመንፈስ ቅዱስ በተገለጠው ጸጋ መለከትና በቅዱስ ቃሉ አማካይነት በአማኙ ሕይወት የሚሠራው ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ እኔ ግን በሁለት መንገድ ወደ ተቀረጽ ባህርይ መምጣት እንደሚቻል እመለከታለሁ። የመጀመሪያው ቀንበርን በመሸከም፣ የክርስቶስ የሕይወት ፈለግ በመከተል ወይም ከእርሱ በመማር ነው። በዚህ የራስን ነፍስ ማሰልጠን ይቻላል። ጌታ ባቀረበልን ጥሪ ውስጥ ያስተላለፈልን ትዕዛዝ “ቀንበሬን ተሸከሙ፣ከእኔም ተማሩ …” የሚለውን ነው።        ብዙዎቻችን ወደ ክርስቶስ ከመጣን በኋላ የምንዘነጋው ነገር፣ኢየሱስ ያዳነን ወይም ቀንበራችንን ከላያችን ላይ ያነሳልን ጌታ ሊሆንብን መሆኑን ነው። የክርስቶስ አዳኝነት ክርስቶስ በእኛ ላይ ጌታ መሆኑን ጠያቂ  ነው። ቀንበሩን መሸከም ስንማር ለክርስቶስ ጌትነት ራሳችንን እያስረከብንና ለነፍሳችን እረፍትን እያገኘን እንመጣለን። እውነተኛ ትህትና ቀንበርን በመሸከም፣ የራስን አስፈላጊነት ከነፍስ ውስጥ በመቀነስና ባዶ በማድረግ የሚመጣ ሕይወት ሲሆን፣ ወደ ትሁት ሕይወት መምጣት የሚቻለው በእንዲህ ዓይነቱ የሕይወት ልምምድ በማለፍ ነው። ይህ ደግሞ “እኔ’’ ለሚባለው ክፉ ባህርይ አይመችም። ይህ የመጀመሪያው እውነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ወደ እዚህ ሕይወት ለመግባት መወሰን ወይም ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ነው። ብዙዎች ባህሪያቸው የተቀረጸ እንዲሆን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ ኃላፊነት እንዳለ ይዘነጋሉ። እግዚአብሔር ወደ እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት እንዲያመጣን ወይም እንዲያግዘን ስንለምን፣ፈቃዳችንን አንቅተን እንጂ፣ በነገሩ ላይ ጉልት አዕምሮ ይዘን መሆን የለበትም። ሳንወስን ለውጠኝ ወይም ቅረጽኝ እያልን ብንለምን አእምሮአችን በነገሩ ላይ አልወሰነምና ጸሎታችን መልስ አያገኝም። በአእምሮ ወስነን ስንጸልይ ግን፣ እግዚአብሔር ውሳኔያችንን የሚያቆምና የሚያጸና ጸጋንና አቅምን በውስጣችን ይጭምራል።

ሕይወትና አገልግሎት ያለ ትህትና ወይም ያለ ባህርይ መቀረጽ ምንም ፍሬ የለውም። የተሰጠን የአገልግሎት ጸጋና የእኛ ባህሪይ አይገኛኝም፤ ጸጋ ጸባይ ታይቶ፣ ጾምና ጸሎት ተለክቶ አይሰጥም፤ ሆኖም ባህሪያችን ያልተቀረጸ ከሆነ ግን አገልግሎታንን ሊያበላሽብንና ፍሬ አልባዎች ሊያደርገን ይችላል። እግዚአብሔር ጸጋን ሲሰጠን ባህሪያችንን ተመልክቶ ሳይሆን በቸርነቱ ተማምኖ ነው። በተሰጠን ጸጋ ሌሎችን በትክክል ማገልገል (ለማነጽ) እንድንችል ግን ትህትና ወይም የባህሪይ መቀረጽ ያስፈልገናል። እንደ አገልጋይ መሪ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ በጎ ተፅዕኖ የምናመጣው በሕይወት ምሳሌነታችን እንጂ በንግግራችን ወይም ስብከትና ትምህርታችን አይደለም። በዚህ ዘመን ብዙ አንደበተ ርቱዕ ሰባኪና አስተማሪዎች አሉን። የነገረ መለኮት መረዳታችንም ከፍ ያለ ነው። ክርስቶሳዊ ሕይወትና ባህርይ ግን ጎድሎናል። በአንድ ፕሮጀክት ውስጥ ሠርቶ ማሳያ እንዳለ፣ የክርስትና ሕይወታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት እየኖሩ ማሳያ ነው (ፊል 2፡14-15)። በማያምነው ማህበረሰብ መካከል የቤተ ክርስቲያን ጥንካሬ፣ የክርስቶስ ባህርይ ወይም መልኩን በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ መገለጡ ነው፤ ስለዚህ አገልጋይ መሪዎች የክርስቶስን ባህሪይ (መልክ) የተላበሱ መሆን ይጠበቅባቸዋል። አገልጋዮች ወደ አገልግሎት ከመምጣታቸው በፊት፣ በተቀረጸ ባህርይ ልምምድ ውስጥ ያለፉና የሚያልፉ መሆናቸው ከምንም ነገር በላይ ግምት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። ቤተ ክርስቲያንን በቀዳሚ መሪነት የሚያገለግሉ አገልጋይ መሪዎች እንዲህ ዓይነቱ የሕይወት ልምምድ የሌላቸው ሰዎች ከሆኑ፣ ሠይጣን የእነርሱን ባህሪይ ያለ መለወጥ (መቀየር) ችግር በመጠቀም የክርስቶስን ምስል ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት ሊያጠፋ የሚችልበት ሁኔታ ይመቻችለታል፤ ምስክርነቷንም ያጎድፋል። በዚህም በማህበረሰቡ መካከል የተናቀችና የተጣለች እየሆነች ትመጣለች። የተለወጠ ሕይወት ከሌለ ዓለም አትፈልገንም፤ የተጣልንም እንሆናለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ትምህርቱ ላይ በማህበረሰቡ መካከል እንደ ብርሃንና ጨው ስለሚገለጥ የአማኞች ሕይወት ሲናገር “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም” (ማቴ 5፡13)። በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ አልጫ የሚባል አብረቅራቂ ነጭ ድንጋይ አለ። ይህ ድንጋይ በመልኩ ከጨው ጋር ይመስላል። እንዲህ ዓይነቱ ድንጋይ ከጨው ጋር የሚመሳሰል መልክ ስላለው በስህተት ምግብ ውስጥ ቢገባ፣ ስለማይሟሟና ጣዕም ስለማይሰጥ በመጨረሻ እንደ ድንጋይ ይጣላል። ቤተ ክርስቲያንም በማህበረሰቡ መካከል የክርስቶስ ባህርይ ከሌላት አትፈለገም። በአማኞች ሕይወት ውስጥ የክርስቶስ ባህርይ መገለጥ እግዚአብሔር ከፍተኛ ዋጋና ግምት የሚሰጠው ነገር ሲሆን፣ የእርሱም መለኮታዊ ውሳኔ የልጁን መልክ እንድንመስል ነው (ሮሜ 8፡ 29)። ለዚህ ደግሞ እግዚአብሔር የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል፤ ደግሞም ይሰጠናል (ሮሜ 8፡32፤ 2ጴጥ 1፡2-3)። ክርስቶስን መስለን ባንገኝ ችግሩ የእኛ ነው። ይህ ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት ከአገልጋይ መሪዎችና ከሚመራው  ሕዝብ ሕይወት እየተወገደ  ሲመጣ ክርስትና ሕይወት መሆኑ ቀርቶ የማይጠቅም፣ ተራና ርካሽ ኃይማኖት ይሆናል። ገብያተኛም አይኖረውም። የእግዚአብሔር ዓላማው የልጁን መልክ በእኛ ሕይወት ገልጦ በማሳየት በጨለማው ዓለም እንደ ከዋክብት እንድንታይ ማድረግ ነው። የከዋክብቶች ውበት በጨለማ ውስጥ እንደ ሆነ፣ የክርስቶስም ውበቱ በቤተ ክርስቲያን በኩል በሚገለጥ ባህሪው በዚህ ጨለማ ዓለም ላይ ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን ሕይወቷ የብርሃንና ጨው ነው። በዚህ ጨለማ በዋጠው፣ ክፉና ጠማማ ትውልድ መካከል ቤተ ክርስቲያን እንደ ብርሃን እንድትታይ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኗል (ፊል 2፡14-16) ይህም ብርሃን በአማኞች ሕይወት የሚገለጽ የክርስቶስ መልክ ወይም ባህሪይ እንደሆነ እናምናለን።

ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ወዳለ አገልግሎት መምጣት ያለባቸው፣ በባህሪይ ቀረፃ እርከን ውስጥ ካለፉ በኋላ መሆን አለበት። ይህንን ዘለው ወደ አገልግሎት የሚመጡ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ሕይወታቸው እንዲሠራ የሰጣቸውን መልካም እድል በመተው ከዚያ በኋላ ባለ የሕይወት ዘመናቸው በሕይወታቸው በሚንጸባረቀው ባህርይ ያልተሠሩና አስቸጋሪ ሰዎች ይሆናሉ። እንደ እነዚህ ዓይነት አገልጋይች ምናልባትም የሚያገለግሏቸውን ምዕመን ከማነጽና ወደ እውነት ከመምራት ይልቅ ያልተገራ ባህሪያቸውን የሚያስተላልፉባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። መሪ አገልጋይ ተብለው ከባህሪይ ችግር የተነሳ ሰዎችን በቦክስ ለመምታት እጃቸውን ቢዘረጉ፣ የሰዎችን ቢያጎሳቁሉና ስማቸውን ቢያጠለሹ ችግሩ የባህርይ ያለ መቀረጽ ችግር ከመሆን ውጭ ምንም ሊሆን አይችልም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር የማይከበርበት ባህሪይና ሕይወት ያላቸው አገልጋዮች፣ ሠይጣን የክርስቶስን መልክ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማጥፋት የሚጠቀምባቸው ዋና መሳሪያዎች ናቸው። ሰዎች የሰማዩን አባታችንን የሚያመሰግኑት መልካሙን ሥራችንን ተመልክተው እንጂ መሪዎች መሆናችንን ተመልክተው አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን ኤጴስቆጶስነትን በተመለከተ በሰጠው መመሪያ ውስጥ “አዲስ ክርስቲያን አይሁን” የሚለው መመዘኛ፣ አዳዲስና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያልበሰሉ አማኞች አስቀድመው ሳይታዩ ወደ አመራር ቢመጡ በዲያብሎስ ሊነዳ የሚችል ባህሪይ ሊኖረው ስለሚችል ነው። ሰዎች ባህሪያቸው መጽሓፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ባህርይ ዓይነት ካልሆነ፣ የእነርሱ ክፉ ባህሪይ የዲያብሎስ እግር ማቆሚያ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ ከኤፌሶን መልእክት መገንዘብ እንችላለን (ኤፌ 4፡25-31)። ዲያብሎስ በሰዎች ሕይወት እግሩን የሚያቆመው በሰዎች ብልሹ ባህርይ ላይ በመመስረት ነው። መንፈስ ቅዱስ በእኛም ሊያዝን የሚችለው በእንዲሁ ዓይነት ባህርይ ነው። ሰዎች በባህሪያቸው ንዴት፣ ጩኸት ስድብ ውሸት፣ ቁጡነት፣ ሌብነት፣ ጸጋ የጎደለውና የማያንጽ ንግግር፣ መራርነት፣ ስድብ፣ ንፉግነት፣ ክፋትና ይቅር ያለ ማለት ኃጢአት ሲኖር ሰይጣን በሕይወታቸው ሥራ ለመሥራት እድል ያገኛል። በተለይም ተበድሎ ሰዎችን ይቅር ያለ ማለት ከሕይወት ያርቃል። በ2ኛቆሮ 2፡11 ላይ ይቅር ስለ ማለት ሕይወት ሲናገር “በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን ሓሳብ አንስተውምና” ይላል። ጠላት በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በጣም ከሚሠራበት ባህርይ አንዱ ተበድሎ ይቅር ያለ ማለት ሕይወት ነው። ይቅር የማይል ባህሪይ ያላቸው ሰዎች ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን እጁን ዘርግቶ እንዲያተራምስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። የአገልጋይ ባህሪይ በክርስቶስ ባህርይ (መልክ) ካልተቀረጸ፣ ለአጋንንት ምቹ የመሸሸጊያሥፍራ ነው (ያዕ 3፡13-16)። ስለዚህ የክርስቶስ ምስል በአማኞችና በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ይገለጥና ክፉው እድል ፈንታ ያጣ ዘንድ አገልጋይ መሪዎች ባህሪያቸው የተቀረጸ ባህርይ ሊኖራቸው ይገባል። አገልጋይ መሪነትን ከባህሪይ መቀረጽ አንጻር ስንመለከት፣ ማወቅ ያለብን ስለ ትህትና ብቻ ሳይሆን ስለ ታማኝነትም ጭምር ነው። ስለታማኝነት ስናነሳ ታማኝነት ማለት ማንም ሰው በሌለበት በሁሉም ነገር ታማኝ ሆኖ መመላለስ ማለት ነው። የጥላቻንና የፍቅርን ሕይወት በአንድ ላይ አጣምሮ መሄድ ታማኝነት አይደለም። አገልጋዮች ግን በዚህ ዘመን ይህንን ማድረግ ችለንበታል። በአገልግሎታችን ውስጥ የሎሌነት ባህርይ የሚንጸባረቅበት አመራር ለመስጠት ትህትና ብቻ ሳይሆን፣ ታማኝነትም ያስፈልጋል። ታማኝነት ቦታና ጊዜ አይጠይቅም። ታማኝነትን፣ በጊዜ፣ በነገርና በቦታ ትክክለኛ ነገር ማድረግ ማለት ነው። ጌታ ሲመጣ ወደ ጌታው ደስታ የሚገባ ታማኝ አገልጋይ ብቻ ይሆናል።

4. በመሪነት አገልግሎት ውስጥ የአገልጋዮች ችግር። ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነው (ዘፍ 1፣26-27)። ሆኖም ይህ መልክ በውድቀት ምክንያት እንደ ደበዘዘ የተሐድሶ ነገረ መለኮት አራማጆች ይናገራሉ። በክርስቶስ የመስቀል ሞት የእግዚአብሔር የተሓድሶ ፕሮግራም፣ በሕያው ቃሉና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ይህንን መልክ የማደስና በቅዱሳን ሕይወት ክርስቶስን በመሳል (በመቅረጽ) የእግዚአብሔር መልክ ማደስ ነው። ሐዋርያቱም በወንጌሉ አገልግሎት ሲያደርጉ የነበረው አንዱ ተግባር ይኸ ነው። ከዚህ አኳያ የዘመናችን አገልጋዮች ችግር ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ከብዙ በጥቂቱ የራስ ምስልን በአማኞች ውስጥ መቅረጽ ሆኖ እናገኜዋለን። አገልጋዮች የወንጌል መልእክት አስተላላፊዎች ነን። ይህንን እውነት ለትውልድ በማስተላለፍና እንደ ቅርስ ለማስቀመጥ በሰዎች ሕይወት ውስጥ በወንጌሉ ቃል የክርስቶስን ምስል መሳል ይጠበቅብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት የገላትያ አማኞች ከወንጌል እውነት በወጡበት ጊዜ ክርስቶስ በእነርሱ ድጋሚ እስኪሳል ድረስ እንደገና  በምጥ ተይዞ ነበር (ገላ 4፡19)። የቆሮንቶስንም አማኞች ለክርስቶስ እንደ ንጽህት ድንግል ለማቅረብ ይደክም ነበር። በእርሱና በሌሎች አገልጋዬች ዙሪያም ምዕመናን ሲከማቹ አጵሎስም፣ ጳውሎስም ኬፋም ለእናንተ አልሞቱም፣ እናንተም በእነርሱ ስም አልተጠመቃችሁም እያለ ወደ ክርስቶስ ይማራቸውና ያሳያቸው ነበር (1ቆሮ 3፡1-16)። ደክሞ የወንጌሉን ቃል ቢያስተምርና በተማሩት እውነት የማይኖሩትን ቢገስጽ አንድን ፍጹም ሰው በክርስቶስ ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ነበር (ቆላ 1፡28)። የእውነተኛ አገልጋይ ባህርይ ይኸ ነው። በሰዎች ሕይወት ውስጥ ክርስቶስን የመሳያው መንገድ የጸጋው ወንጌል (የመስቀሉ ቃል) ነው። አገልጋዮች በወንጌሉ መልእክት ላይ ተታከን ክርስቶስን ሳይሆን ራሳችንን ለመሳል ወይም ለመቅረጽ የሚፈልግ ልብ ካለን ግን፣ ጸሎታችን፣ ስብከታችንንና ሌላውም ሌላውም አገልግሎታችን ሁሉ ራሳችንን በሰዎች ውስጥ በመሳል እንድንወደድና የራሳችን ተከታዮች ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊሆን ይችላል። በዚህ ዘመን ብዙዎቻችን የክርስቶስን ሳይሆን የራሳችንን ምስል በሌሎች ሕይወት ውስጥ የመቅረጽ ችግር ያለብን ይመስላል። ይህም በሕይወታችን የሚገለጸው ጉባኤው ወይም የምናገለግለው ሕዝብ እንዲከተለን በሚያስብ ልብ በዓላማ ሕዝቡን ከወንጌል እውነት እንዲወጣ እያደረግነው በመሆኑ ነው። በዚህ ዘመን አገልጋዮች ከሌሎች ጋር ብንጣላ፣ ጉባኤውን ብዙ ብናስጨበጭብና እግዚአብሔር ያልተናገረውን እንደ ተናገረ በማለት የመልካም ምኞት መግለጫችንን ብንገልጽና “አሜን!” ብናስብል፣ ይህ ሁሉ የራሳችንን ምስል በሕዝቡ ሕይወት ለመቅረጽ ካለ ችግር የመጣ ነው። በዚህ የክርስቶስን ሳይሆን የራሳችንን ምስል ቀርጸናል፤ የራስን ምስል ከሰው ውስጥ ለማውጣት ከተፈለገ ከሰዎች ብድራት ሳይፈልጉ ማገልገል ነው። ይኸ ሁሉ ችግር ከየት መጣ? እንደ እኔ ግምት ስለ ራሳችንንና ስለ አገልጋይ መሪነት ያለን ግምትና ትርጓሜ የተሳሳተ በመሆኑ ነው። ስለ ራስ ያለ ግምት ራሳችንን ልክ ነን እያልን የምናደንቅበት ነው። ይህ በሌላ አገላለጽ ራስን ማምለክ/አምልኮት ነው። የምስል ችግር እነዚህን ሁለቱን ችግሮች በውስጣችን ያመጣል ። ይህም ችግር የግብዝነት ሕይወት ችግር ውስጥ ይከተናል። ከዚህ ችግር ለመውጣት ነፍስን መስቀል እያሸከሙ ማሰልጠን ያስፈልጋል። ከዚህ ስንላቀቅ ትሁት እንሆናለን። 

5. በአገልጋይ መሪ ሕይወት ውስጥ ቁልፍ ነገሮች።

5.1 ማገልገል ማለት መስበክ ሳይሆን መሆን ነው። “ሰውነታችሁን ሕያውና ቅዱስ መስዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራሄ እለምናችኋለሁ። እንደሚል ራሳችንን እለት እለት ለጌታ ማቅረብ አለብን። 

5.2 የምንወስናቸው ውሳኔዎቻችንና ምርጫዎቻችን ከሕይወት መንገድ እንዳያወጣንና ጸጋውን  እንዳያስጥለን በምርጫችን መስቀሉን መሸከም።

5.3 አደራረጋችን ሁሉ እንደ ቃሉ ማድረግ፣ ለቃሉ ሥልጣን መገዛት።

5.4 ክርስቶስን ለማገልገል ከእርሱ ፍቅር ሌላ ሰበብ አለመፈለግ።

6. አገልጋይ መሪ ትክክለኛ ወይም የሰመረ ሕይወት እንዲኖረው የሚያስፈልጉት ነገሮች።

6.1 የልብ ሰው ወይም የሕይወት ምስጢራችንን የምንጫውተው ወዳጅ ያስፈልገናል። ይህንን ማድረግ ያለመቻላችን የግለኝነት ሕይወት እያዳበርን እንድንመጣ ያደርገናል። ይህ ደግሞ ችግራችንን አውጥተን እንዳንናገር የማድረግ ባህርይ ስለሚኖረው ወደ መደበት ሕይወት ሊያመጣን ይችላል። 

6.2 የሚያሰለጥኑን፣ መመሪያንና መርህን የሚያስይዙን ያስፈልገናል። 

6.3 ጸጋውንና ልምዱን የሚያካፍለን ሰው ያስፈልገናል። በአንድ ነገር ወይም አሠራር ላይ ጸጋቸውን፣ ችሎታቸውንና እውቀታቸውን የሚያካፍሉን ያስፈልጉናል። 

6.4 በማህበራዊ ኑሮ የሚረዱን፤ አብረን ለመብላት፣ ለመጠጣትና ለመጫዎት በአጠቃላይ ሐዘንና ደስታችንን የሚካፈሉን ማለት ነው።

7. አገልጋይ መሪ ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ ነገሮች።

7.1 የገንዘብ አጠቃቀም ላይ መጠንቀቅ አለበት። ያገኘውን ገንዘብ አጠቃቀሙ ማንነቱን ያሳያል። አገልጋይ መሪ ገንዘብ ያስፈልገዋል። በገንዘብም በአግባብ መጠቀም አለበት። ከዚህ ውጭ አፍቅሮተ ነዋይንና ስስታምነትን ማስወገድ ያስፈልገዋል፤ ወይም ደግሞ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ቀለል ያለ ኑሮ መለማመድ ያስፈልጋል።  

7.2 ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባለው ግንኙነት ጠንቃቃ መሆን አለበት። የዐይንና የሰውነት መዳራት ድንግልናን የሚያበላሽ ነገር ነው። ስለዚህ አገልጋይ መሪ ትዳሩን በንጽህና ለመጠበቅ የዐይንን ድንግልና መጠበቅ ያስፈልገዋል። 

7.3 ሥልጣን አጠቃቀምና አተገባበር ላይ መጠንቀቅ አለበት። ለምሳሌ አገልጋይ መሪ ሥልጣኑን ምዕመናንንና በሥሩ ያለ አገልጋዮችን ለማስመረርና ለማስለቀስ ሲጠቀምበት በሥልጣን ያለ አግባብ መጠቀም ነው።  

8. አገልጋይ መሪና ብድራቱ። በአመራር ውስጥ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር ብድራት አለ። ማገልገል ያለብን ከጌታ መልካም ብድራትን ለማግኘት ነው እንጂ ክፉ ብድራትን ለመቀበል አይደለም። በአገልጋይ መሪነት ውስጥ የእኔ የሕይወት ዓላማ ክርስቶስ ነው ብለን ስንነሳ፣ ሰዎች ለእኛ ሥፍራ ሲሰጡን አልፈልግም ማለትን ወይም ደግሞ ለራሳችንም ሥፍራ መንሳትን ይጠይቃል። ምክንያቱም ዛሬ ሆሳዕና ንገሥልን ያለን ነገ ስቀለው ሊለን ይችላል። የሰው ልጅ እንደ ባንዲራ ገመድ ራሱ ይሰቅላል ራሱ ያወርዳል። ሰዎች ክብርን ወደ እኛ እየወረወሩ ፈተና ውስጥ ሊከቱን ይችላሉ። ውስጣችን እምቢ ማለት ካልቻለና የራሳችንን ምስል ለመሳል ስንል የግብዝነት ሕይወት ብንመጣ ብድራት ወይም ዋጋ አይኖረንም።

ወንድም ነቢዩ ኢሳይያስ ቨርጂኒያ በምትገኘው አንጾክያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ናቸው።