አዋቂ ተኮር አገልግሎት ቢቀየርስ?

ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፤ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።” - ምሳሌ 22:6

በተድላ ሲማ

ሐዋሳ በልጆች አገልግሎት ሸክም የነበረው አንድ ወንድም፣"አይ ቤተ ክርስቲያን፥ ለሙን መሬት ትታ በጭንጫ ላይ ዘር በመዝራት ትደክማለች" አለ። ይህ ሰው ይህን ያለው የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን መንፈሳዊ ፕሮግራም ሲካፈሉ፥ ልጆቹ ግን ውጪ ፀሐይ ላይ ሲንቃቁ በማየቱ፥ ለምን ትኩረት ተነፈጋቸው? ለማለት ነበር። በርግጥ አዋቂዎችን በ"ጭንጫ" መመሰሉ ጠንከር ያለ አባባል ሊመስል ይችላል። ለአዋቂዎች የሚሰጠው ትኩረት ተገቢ አይደለም ለማለትም አይደለም። ሆኖም የሚታቀዱት ፕሮግራሞች በአብዛኛው አዋቂ ተኮር መሆናቸውን ለማሳየትና ይህ አካሄድ እንዲስተካከል ለማስገንዘብ ነው። ከቤተ ክርስቲያን በጀት አብዛኛው አዋቂ ተኮር ለሆኑ ዕቅዶች እንጂ ልጆችን ያማከለ እንዳልሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ለመሆኑ የልጆች ኮንፍራንስ የሚል ሰምተን እናውቃለን? የአገልጋዮች ጊዜና ጉልበት በአብዛኛው የሚባክነው አዋቂዎችን በማገልገል ነው ወይስ ልጆችን? የልጆች ቁጥር በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ከአዋቂው የማይተናነስ መሆኑንም መዘንጋት የለበትም።

ቤተ ክርስቲያን ለልጆችና ለታዳጊ ወጣቶች የምትሰጠው ትኩረት በጣም ሊጨምር ይገባል፤ ይህ ካልሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተረካቢ ትውልድ ልታጣ ትችላለች። ልጆችና ታዳጊ ወጣቶች ላይ ብዙ ሊደከምባቸው ይገባል። የልጆች አገልግሎት ኃላፊነቱ ለተወሰኑ ሰዎች ተጥሎ ባወጣ ያውጣው ሊባል አይገባም። የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችና መሪዎች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። ስንት አብያተ ክርስቲያናት ናቸው ለልጆችና ለታዳጊ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የመደቡ? ይህ ጥያቄ ሲነሳ የበጀት ጉዳይ ሊነሳ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ግን ከልብ ካለቀሱ እንዲሉ የገንዘብ ችግር ብቻ ሳይሆን የእይታም ችግር ነው ያለብን። አንዱ ችግር በአሁኑ ወቅት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችና መሪዎች በአብዛኛው ስለ ልጆች አገልግሎት ተገቢ የሆነ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ ነው። የተለምዶ አሠራር ከመከተል ውጪ ታስቦበትና ተጨንቆ የልጆችን አገልግሎት ማካሄድ ከእይታቸው ውጪ መሆኑን ማየት አይቸግርም። ይህን ችግር ለመቅረፍ ለመሪዎችና ለሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ ወገኖች፣ አግባብነት ያለው ሥልጠና ሊሠጥ ይገባል። ያን ጊዜ ስለ ልጆች አገልግሎት የመሪዎች ዓይን ይከፈታል። በልጆች ውስጥ ትውልድን ማየት ይችላሉ። ሕጻናትን ሳይሆን ትውልድን አሻግረው ማየት ይችላሉ።

የልጅነት ጊዜ በሰው ሕይወት ውስጥ ዋና ዋና የሆኑ ነገሮች የሚቀረጹበት ወቅት በመሆኑ ወሳኝ ነው። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከመቶ ሰባ አምስቱ እጅ በልጅነታቸው በሰንበት ት/ቤት በእግዚአብሔር ቃል ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው። በልጅነት ጊዜ የሚዘራ መልካም ዘር ለኋለኛው የሕይወት ዘመን እጅግ ጠቃሚ መሠረት እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃልም ሆነ የስነ ልቦና አስተምሮ ይነግረናል። “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፤ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም (ምሳሌ 22:6)።” የስነ ልቦና ምሑራን የተናገሩትን ጠቅሶ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “አንድን ልጅ በተገቢ ሁኔታ የመጀመሪያውን 9 ዓመታት ካሳደግከው፥ ከ11 እስከ 20 ዓመት ያለውን የዕድሜ ዘመኑን ትታደጋለህ፤ ከ11-20 ያለውን የዕድሜ ዘመኑን በሚገባ ኮትኩተህ ከያዝከው ደግሞ ከ21-90 ዓመት ባለው የሕይወት ዘመኑ መልካም ሕይወት እንዲመራ ትረዳዋለህ” (ያውም 90 ዓመት ለመኖር ከታደለ ነው)።

መልካም ነገሮችን የመዝሪያው ዕድሜ የአዋቂነት የዕድሜ ክልል አይደለም፤አዋቂዎችን ለመለወጥ (አይቻልም ባይባልም) እጅግ ይቸግራል ። ልጆች ግን ምንም ነገር እንዳልተጻፈበት ነጭ ወረቀት የሆነ አእምሮ ስላላቸው በጎ ወይም በጎ ያልሆነውን በማስተማር ተጽዕኖ ልናመጣባቸው እንችላለን። ቤተ ክርስቲያን የልጅነት ዕድሜ መልካም ዘር ለመዝራት ተገቢው ወቅት መሆኑን አውቃ ለአዋቂዎች የምትሰጠውን ያህል ትኩረት ለልጆች በመስጠት ልጆችን በመልካም መሠረት ላይ ልታንጽ ይገባል። ትኩረት መስጠት ስንል በደፈናው አይደለም። የሚለካ ሊሆን ይገባል። ይህም ማለት ከበጀቷ ምን ያህሉ በልጆችና በልጆች ተዛምዶ ባለው ጉዳይ ላይ ዋለ? የልጆች የመነቃቂያ ጊዜ ወይም ኮንፍራንስ አቅዳለች? ለልጆች አገልግሎት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መድባለች? እንደዚህ ዓይነት ፕሮግራሞችን አቅዶ ለማሳካት ማሰብን፥ መነቃነቅን፥ አለመድከምን፥ ብርቱ ጥረትና የማያቋርጥ ክትትል ይጠይቃል። የልጆች አገልግሎት እገሌ ይስራው ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም። ለአዋቂዎች በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ እንደምንረባረብ ሁሉ ለልጆችም አገልግሎት እኩል ትኩረት ልንቸር ይገባል። ከዚህ አቅጣጫ የአመለካከት ለውጥ ልናመጣ ይገባል። አልበርት አይንስታን፣ “አንድን ነገር በተለመደው መንገድ እየሠራህ የተለየ ውጤት የምትጠብቅ ከሆነ አብደሃል ማለት ነው” ብሏል። በተመሳሳይና በተለመደው መንገድ የልጆችን አገልግሎት እየመራን ለውጥ እናመጣለን ማለት ዘበት ነው።

በልጆች አገልግሎት የተሳካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ካሉም ተመክሯቸውን መቅሰም ይገባል። የልምድ ልውውጥ ስብሰባ በማቀድ መማማር ይቻላል። በአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ አማካኝነት በተቀናጀ መርሐ ግብር በግል ት/ቤቶች መካከል እየተካሄዱ ያሉ የልምድ ልውውጦች ለየትምህርት ቤቶቹ ያስገኙት ፋይዳ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በዝግጅቶቹ ላይ የተሳተፉ የትምህርት ባለሙያዎች ያውቁታል። አብያተ ክርስቲያናትም የልጆችን አገልግሎት በተመለከተ የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር ቢያዘጋጁ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ይሆናል። በተጨማሪም ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ ወገኖች የምክክርና የውይይት ጊዜ ቢዘጋጅ ብዙ ትምህርት ሊቀሰምበት እንደሚችል እምነት አለኝ። በልጆች አገልግሎት አቅጣጫ በእኔ እይታ ፈር ቀዳጅና ስኬታማ ሥራ በኢትዮጵያ እየሠራ የሚገኘው በወንድም ኤፍሬም የሚመራው “ሻረን የልጆች አገልግሎት” ለ አብያተ ክርስቲያናት ግንዛቤ በማስጨበጥ ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችል እምነቴ ነው።

ለልጆች የተስተካከለ እድገት ኃላፊነቱ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው የሚል እሳቤ የለኝም። ወላጆች የበለጠውን ኃላፊነት አለባቸው። ሆኖም ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ኃላፊነቷን ለመወጣት ስትንቀሳቀስ ለአዋቂዎች የምትሰጠውን ያህል ትኩረት ለልጆችም አገልግሎት ልትነፍግ አይገባም። ለልጆች የምንሰጠው አገልግሎት ምን ይመስላል? ልንፈትሽ ይገባል። የዛሬ ልጆች የነገ ታዳጊ ወጣቶች ናቸው፤የዛሬ ታዳጊ ወጣቶች የነገ ወጣቶች ናቸው። የዛሬ ወጣቶች የነገ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው። በርግጥ ብስለት ያላቸው አንዳንድ ወጣቶች ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤የሆኑም አሉ። ጢሞቴዎስ ወጣት የቤተ ክርቲያን መሪ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርገን መጥቀስ እንችላለን። የልጆች አገልግሎትን ጠቀሜታ በተመለከተ ከ ministry-to-children.com ላይ በመውሰድ ወደ አማርኛ የመለስኩትን ጠቃሚ ነጥቦች ከዚህ በታች በማስነበብ እደመድማለሁ።

የልጆች አገልግሎት ለልጆች ያለው ጠቀሜታ። እግዚአብሔር ስለ ልጆች ይገደዋል፤እኛም ስለ እነርሱ ሊገደን ይገባል። ልጆችን በእግዚአብሔር ቃል እውነት ስናገለግላቸው ብዙ የሚያገኙት ነገር አለ። ስምንቱ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። 1/ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ለመቀበል ይረዳቸዋል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ከማንኛውም የዕድሜ ክልል ይልቅ የልጅነት ወቅት ክርስቶስን ለመቀበል የተከፈተ ልብ የሚገኝበት ወቅት ነው። በሌላ አነጋገር ልጆች ከአዋቂዎች ይልቅ ለጌታ ቅርብ ልብ አላቸው። ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ልባቸው እየጠነከረ ሊሄድ ይችላል። በመሆኑም በልጅነት ስለ ጌታ ኢየሱስ አዳኝነት መማራቸው ለመዳናቸው መንገድን ይከፍታል። 2/ የሕይወት ትርጉም እንዲገባቸው ያደርጋል። ግዑዙን ዓለም ማን እንደፈጠረው ማወቃቸው፥ የሰውን ውድቀትና እግዚአብሔር የማዳንን መንገድ ማዘጋጀቱን መገንዘባቸው ለሕይወታቸው ትርጉም ይሰጠዋል። ለምን እንደሚኖሩ ከታናሽነታቸው ጀምሮ ይገባቸዋል። ለምን እንደሚኖር የገባው ሰው ትርጉም ያለው ሕይወት ይመራል። 3/ ዘለቄታዊ ደስታን እንዲያጎለብቱ ይረዳቸዋል። እግዚአብሔርን በማምለክ የሚገኘውን እውነተኛ ደስታ እንዲለማመዱ ይረዳቸዋል። በጌታ ደስ መሰኘትን ይማራሉ። እግዚአብሔር የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ነውና። 4/ አላስፈላጊ ከሆኑ አንዳንድ የኃጢአት አስከፊ ውጤቶች እንዲጠበቁ ይረዳቸዋል። በርግጥ የእግዚአብሔር ፀጋ ብቻ ነው ልባችንን መቀየር የሚችለው። ሆኖም እግዚአብሔርን አለመታዘዝ የሚያስከትለውን አስከፊ ጣጣ በልጅነት ማወቃቸው ልጆችን ጠንቃቃ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ኢየሱስ ሊያድናቸው የከፈለውን ትልቅ ዋጋ ሲረዱ፥በጽድቅ መንገድ ለመጓዝ ልባቸውን ያቀናሉ። የእግዚአብሔርን ጽድቅና ፍቅር ስናሳያቸው፣ በፍቅሩ ልባቸው ሲማረክ፥ጽድቁንና ቅድስናውን ሲያውቁ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ልጆች ሆነው ያድጋሉ። በአክብሮትም ይገዙለታል። 5/ የዓለማዊነትን በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ ለመቋቋም ይረዳቸዋል። ሁላችንም በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን ክፉ ተፅዕኖ እናውቃለን። ይህን በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ መቋቋም እንዲችሉ በጎና አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚያመጣባቸው አካል ያስፈልጋቸዋል። ያም አካል የወላጆችና የቤተ ክርስቲያን ጥምር አስተዋጽዖ ነው። 6/ ሌሎችን መውደድን ይማራሉ። ሁለተኛው ታላቁ ትዕዛዝ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ነው። ይህን ደግሞ በልጆቻችን ላይ ልናሰርጽ የምንችለው ለተቸገሩት ስንጸልይና ስንረዳ ሲያዩ ነው። ርህራሄ ተሞልተው እንዲያድጉ የሚታይ የፍቅር ሥራ እንደ ወላጅም እንደ ቤተ ክርስቲያንም ልናሳያቸው ይገባል። 7/ ጥሩ ጓደኞችን የሚያገኙበት ሥፍራ ይሆናል። ልጆች ጥሩ ጓደኛ ከሚያገኙበት ሥፍራ አንዱ ቤተ ክርስቲያን ነው። 8/ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚተዋወቁበትና ዝማሬን የሚማሩበት ሥፍራ ይሆናል። የቃል ጥቅሶችን እንዲያጠኑ ሲደረግ በአእምሮአቸው ስለሚሰርጽ በጎ ተጽዕኖ ያመጣባቸዋል። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክንም እንዲማሩ ይረዳቸዋል። ዝማሬዎችንም በመስማትና በመዘመር እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል። ቤተ ክርስቲያን በዛሬው ተግባሯና በወደፊቱ ውጥኗ ለልጆችና ለታዳጊ ወጣቶች አገልግሎት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ወደ አዋቂዎች ያዘመመው አገልግሎቷ ሚዛናዊ ይሁን እላላሁ። አዋቂዎችን ችላ እንበል የሚል እንድምታ የለኝም። ሁለቱንም እኩል እናገልግል፤ ያን ጊዜ አገልግሎታችን ሙሉ ይሆናል። ጌታ ሁላችንንም ይባርክ!