መታመን ለልማት መሠረቱ ነው
ክፍል ሁለት

መተማመንን መፍጠር የመሪዎች ተቀዳሚ ተግባር ነው። መመሪያዎች ግልጽና ወቅቱን የሚጠብቁ ሆነው፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ውጤት ማካተት ይኖርባቸዋል። መተማመን በመሪና በተመሪ መካከል ብቻ ሳያበቃ፤ በመሪዎች መሓል እና በተመሪው መሓል መዝለቅ ይኖርበታል። በማባበል፣ በማስገደድና በማስፈራራት መታመን አይገኝም። በፈቃደኛነት፣ በግልጽነትና በፍትሓዊነት ላይ ሲመሠረት መተማመን ዘለቄታ ይኖረዋል። የብዙኃኑን ተሳትፎ ሲያግድና የጥቂቶችን ሲያገን ማኅበረሰብ ኅልውናው ለአደጋ ይጋልጣል። እያንዳንዱ ዜጋ መብቱን ሳይዘነጋና ፍርኃት ሳይገታው የአገሩን ጉዳይ የማወቅና የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት። አገር ሳይኖርና ሳይረጋጋ ለብዙኃኑ ዘለቄታ ያለው ሰላማዊ ሕይወት፣ እድገትና ነጻነት አይኖርም።

አገራችን በአምስት፣ አለመተማመንን በሚያባብሱ፣ ያልገነፈሉ ያልረጉ ቅራኔዎች ተይዛለች። የመጀመሪያው፣ የሕዝብ ንብረት በዘረፉ ባለሥልጣናት ላይ ከወሬ ባለፈ ሕጋዊ እርምጃ አለመወሰዱና ዘረፋው መቀጠሉ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሙስና በተንሠራፋበት ኢኮኖሚያዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ እድገት ይፋፋል ማለት ራስን መሸንገል ነው። ሙስና ማህበራዊ ምስጥ ነው፤ በሥልጣን ላይ ከሚሰየሙት ብቃት ጀምሮ ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ እምነቶችና የንግድ ማእከሎች በገንቢና ፍትሓዊ ስነ ምግባሮች [አለ]መተዳደራቸውን ይመለከታል። ሙስና በአገር ደህንነት ላይ ከሽብር ፈጣሪዎች ያላነሰ ዘላቂ ውድቀት ያስከትላል፤ በጊዜ ካልተገታ መደበኛ ባህል ይሆናል።

ሁለተኛው፣ ከሃያ ዓመታት በላይ እልባት ሳያገኝ የቆየው የመሬት ይዞታና ተከትሎ የመጣው የአዲስ አበባ ህጋዊ ምንነት ግልጽ አለመደረጉና ማስተር ፕላን የተባለው ጉዳይ ነው። መንግሥት አገር-አቀፍ የልማት ሥራዎችን ለማካሄድ ቅድሚያ ቢኖረውም ኗሪውን በማያካክስና ሥጋት ላይ በሚጥል መንገድ እርምጃ መውሰዱ ተገቢ አይደለም። ልማት ምንጊዜም በሕዝብ ለሕዝብ ነው፤ ልማት ሕዝቡን ሳያሳትፍ፣ ሳያቅፍና ፍላጎቱን ሳይመዝን የትም አይደርስም። በአሁኑ ወቅት የሕዝቡን ሥጋት ያበረታው ለኢንዱስትሪ ልማት የታሰበው የአዲስ አበባና አካባቢ ቆዳ ስፋት ከ1ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሆኖ ከሃያ በላይ የገጠር ቀበሌዎችን ማካተቱ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ኗሪዎች ይዞታቸውን ሊለቁ ማለት ነው። ሰው በምርጫው ቀዬውን ለቆ ወደ አዲስ ሠፈራ መጓጓዝን አይመርጥም።

“ኢንዱስትሪን” ያስቀደመ ፖሊሲ በሚቀጥሉት ሃያ አምስት ዓመታት ማሌሽያ ከደረሰችበት ላይ ያደርሰናል ተብሎ ይገመታል [በሁለት ትውልድ ማለት ነው። ገዥው ፓርቲ ሥልጣን ከያዘበት ጀምሮ በሃምሳ ዓመት ማለት ነው። እንደ አፄ ኃይለሥላሴና ደርግ ዘመን፣ ሌላ ፓርቲ ለሥልጣን እንደማይታሰብ እናስተውል፤ ትውልድ የራሱን ፈር መቅደድ ይሻል የሚለውን ማህበራዊ እውነታን እንደሚክድ እናስተውል]። በዚህ የረጅም ጊዜ እቅድ መሠረት፣ ሰማንያ አምስት በመቶ ሕዝብ በግብርና የሚተዳደርባት አገር፤ የትምህርትና የቋንቋ ፖሊሲ በተዘባረቀበት፣ ፍልሰት በገነነበት፣ የሕዝብ ንብረት ዘረፋ በበረታበትና ተሳትፎ በመነመነበት ይህን መሳይ የባሕልና የኢኮኖሚ ለውጥ ማምጣት ቀላል አይሆንም። ደርግ የሩስያና የቻይናን የእድገት ፈለግ ለመከተል፣ ቻይናና ሩሲያ ደግሞ ምዕራባዉያን የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ሲሉ ያወደሙት ቅርስ፣ የሠውት ሕዝበ ሚሊዮን እንዳይደገም ምን መተማመኛ አለ? በደርግ ዘመን ሰላም፣ እኩልነትና ብልጽግና የሠፈነባትን ኢትዮጵያን ለመፍጠር በግዴታ ውዴታ ብዙ መስዋእት ተከፍሏል። የተሠውት አንዳቸውም ያቺን ዓይነት ኢትዮጵያ ሳያዩና ሳይኖሩባት አለፉ። የተረፉት ያቺን ዓይነት ኢትዮጵያ ሳያዩና ሳይኖሩባት እስከ ዛሬ አሉ፤ ለተሳሳተ ፖሊሲ ሰለባና ባለዕዳ ሆኑ። አስተዋይና ርህሩህ መሪዎች የሚያስፈልጉት እንግዲህ ለዚህ ነው። በ1970 ዓም የወጣው የቻይና “በቤተሰብ አንድ ልጅ” ፖሊሲ፣ ለምሳሌ፣ አገሪቱን የጧሪ-አልባ አዛውንትና ቤተሰባዊ እይታ የራቀው ትውልድ በማድረጉ ቻይና ከፍተኛ የሞራል፣ የማህበራዊና የሴኩሪቲ ማጥ ውስጥ ተዘፍቃለች። በወቅቱ ፖሊሲውን የተቃወሙ፣ መንግሥት ተጻረሩ ተብለው እንደተወገዱ አንዘንጋ።

የክልል መስተዳደር ጠቃሚነት አለው። በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ምክንያት የተከሰተው ተቃውሞ ግን የክልል አደረጃጀት መራራ ፍሬም እንደቋጠረ እየተናገረ ነው፤ በጊዜ ሰሚ ያገኝ ይሆን? ዜጋ በተናጠል ስለ ክልሉ መብት ብቻ ሲሟገት፤ መንግሥት ኢንዱስትሪ ማስፋፋትን ከሕዝቡና ከአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ጋር ማስታረቅ ሲያቅተው እያየን ነው። መንግሥታዊ መመሪያዎች፣ የሕዝብ ፈቃድና ተሳትፎን ማማከላቸው ቁልፍ ነው ማለት ነው። በሕዝብ ስምና ለሕዝብ የቆመ መንግሥት ከሕዝቡ የተለየ፣ ሁሉን አወቅ፣ የማይጠየቅ አካል ሊሆን አይገባም። የሕዝብ ጥያቄ ማድመጥ አማራጭ የለውም። የማያስገርመው። ጥያቄዎች በአብዛኛው የሚነሱት ከቀድሞ ጠ/ሚ መለሰ ዜናዊ ትውልድ ጀምሮ በተማሪዎች ነው። መሬት ላራሹ። ዲሞክራሲ። ነጻ ፕሬስ። በረሓብ ላለቀው ሕዝብ ባለሥልጣናት በሕግ ይጠየቁ፣ ወዘተ።

ሦስተኛ፣ በዚህ ዓመት የተከሰተው ረሓብ ጉዳይ ነው [ረሓብ የሌለበት ዓመት እንደሌለ አንርሳ]። መጀመሪያ ረሓብ የለም፤ ከዚያ ረሓቡ አሳሳቢ አይደለም ተባለ። ቀጥሎ፦ ልንቆጣጠረው እንችላለን፤ ከዓለም ገበያ በቂ እህል ሸምተናል። ከዚያ፤ የ1977ቱ ረሓብ በኛ ዘመነ መንግሥት አይደገምም ተባለ። ከዚያ መጠነኛ እርዳታ ያስፈልገናል። ከዚያ፣ ረሓቡ በአገሪቷ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ፣ የ77ቱን የሚያስከነዳ ነው እየተባለ ነው [ሪፖርተር]። መንግሥት እንዴትና ለምን በጥቂት ወራት ውስጥ እንዲህ የተለያዩ አቋሞች ሊኖረው ቻለ? ለረሓብ የተጋለጠው ቁጥር መጀመሪያ 4 ሚሊዮን፣ ከዚያ 7 ሚሊዮን፤ ከዚያ 10 ሚሊዮን፤ አሁን 15 ሚሊዮን ደርሷል። በዚያ ሳያበቃ የችግሩ መንስኤ “ዔልኚኞ” ነው ተባለ። “ዔልኚኞ” በምድር ሠቅ አካባቢ ታኅሳስ ወር ሲገባ በየዓመቱ የሚከሰት የነፋስ እንቅስቃሴ ነው። የሚመለከታቸው አገራት ቀድሞ ዝግጅት ስለሚያደርጉ ጉዳቱ አይበረታባቸውም። በሌላ አነጋገር፣ “ዔል ኚኞ” የነበረን ችግር ያባብስ እንደሆነ እንጂ በራሱ ዋነኛ መንስዔ ሊሆን አይችልም። መንግሥት ‘ካሊፎርኒያና አውስትራልያም እንኳ ድርቅ እያጠቃቸው ነው’ ማለቱ ንፅፅሩ ንቀትና ኃላፊነት የጎደለው ሆኖ ለብዙዎች ታይቷል። በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ቲማቲምና ጤፍ እጥረት በሱዌዝ ካናል መዘጋት ይሳበብ እንደ ነበረ። በደርግ፣ እጥረትና ፍጥረት በኢምፔሪያሊዝምና በሠርጎ ገቦች ይሳበብ እንደነበር። ዛሬ ደግሞ በሽብርተኞችና “ዔልኚኞ”። ሦስቱም መንግሥታት አንዳቸውም ለተከሰተው ቀውስ ተጠያቂነትን አልተቀበሉም፤ ለጠፋው ሕይወትና ለደረሰው ሰቆቃ በሕግ አልተጠየቁም። አምላካዊ ምላሽ ግን ተሠውሯል ማለት አይደለም። ለመሆኑ ይህን የተወናበደ ዜና የሚሰማ ዜጋ ምን ግንዛቤ እንዲኖረው ይጠበቃል? የአገር መሪዎች አይታመኑም እንዲል? ወይስ መሪዎች በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄደውን አያውቁም? ወይስ መሪዎች ለራሳቸው እንጂ ለሕዝቡ ግድ የላቸውም? ወይስ መሪዎች እርስበርስ ስምምነትና መተማመን ስለሌላቸው በአንድ ድምጽ መናገር አቅቶአቸዋል?

አገራችን የተጋረጠባት አደጋ መጠኑ ምን ያክል ነው? ነገ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀዋል የሚል ዜና ይፋ ቢወጣ ተጠያቂ ማን ሊሆን ነው? ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ እውነቱን የሚያውቁ ሁሉ ለዓለም እንዲያሳውቁ ሰብዓዊነትና ፈርኃ እግዚአብሔር ሊያስገድዳቸው ይገባል። ጠ/ሚ መለስ ከሦስት ዓመት በፊት ለሁለት ወር የደረሱበት ባጠያየቀበት ሰዓት በመንግሥት ባለሥልጣናት ይሰጡ የነበሩት መግለጫዎች እርስበርስ የተጻረሩ እንደነበረ አንዘነጋ። አመራር በደቦ መሆኑ ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ማስከተሉ እውን ነው። ግልጽ አመራርና መመሪያ ሳይኖር ከዜጋና ከመሪ ተመጣጣኝ ግዳጅ መጠበቅ ደግሞ ራስን መሸንገል ነው።

አለመተማመንን ያባባሰ አራተኛው፤ የአገር ድንበር ጉዳይ ነው። ያካባቢው ኗሪ፣ ዜጋ ማኅበራትና የሱዳን ጋዜጦች ገሃድ እስካወጡበት ጊዜ ድረስ፣ የሱዳንና የአገራችን ድንበር ህልውና በድብቅ ተይዞ ነበር። ድንበርን ያክል ከብዙኃን ተሠውሮ መቆየቱ ሥጋትና የአለመተማመን ናዳ ፈጥሯል። ያሳሰባቸው ኢትዮጵያዉያን በአሁኑ ወቅት ፊርማ አሰባስበው ለተባበሩት መንግሥታትና ለሚመለከታቸው ተቋማት አቤቱታ በማቅረብ ዘመቻ ላይ ተሠማርተዋል።

በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ኡስማን ናፊ እ.አ.አ. ኖቬምበር 23/2015 ለአሳያ ዐረብኛ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሁለት [አንድ ውሸት፣ አንድ አስገራሚ] ነገሮችን ተናግረዋል። ውሸቱ፣ ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ስለተጨናነቀች ሥፍራ ጠቧታልና ድንበር መግፋት ጀምራለች ሲሆን። አስገራሚው፣ የድንበሩን ችግር ያባባሰው የክልሉ መንግሥት እንጂ የመሓሉ አይደለም፤ የመሓሉ መንግሥትማ ከካርቱም ማኅጸን የወጣ ነው ማለታቸው ነው። መንግሥት ይህን ዜና ተከትሎ የተለሳለሱ ማብራሪያዎችን ለቋል። ጠ/ሚ ኃይለማርያም ለምሳሌ፣ “ሕዝባችንን አስፈቅደን” የሚል ቃላት ማዘውተር ጀምረዋል። በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሳቢያ ለደረሰው ሞትና እስራት “ሕዝባችንን ማፈናቀል አንሻም፤ ፕላኑ ለጥቅሙ ታስቦ ነበር። ሕዝቡ ጥቅሙ እስኪገባው ድረስ ፕላኑ ተግባራዊ አይደረግም” ብለዋል። በሌላ አነጋገር፣ የሕዝብ ተሳትፎ ቅድሚያ ሳይሰጠው ስለተዘነጋ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ድንበሩን በተመለከተ እስካለፈው ወር ድረስ “ቀድሞ በነበረው ውል መሠረት ይከናወናል” ሲሉ እንዳልነበር፣ ታኅሣሥ 15/2008 ዓ.ም. ፓርላማ ፊት ቀርበው “ሕዝቡን ሳናማክር ምንም እርምጃ አንወስድም” ብለዋል። ለብዙዎች ጥያቄ የሆነው፣ ድርድሩ ይፋ ባይወጣና ተቃውሞ ባይሰማ ኖሮ በስውር ሊፈጸም፣ ኗሪው ተገድዶ ሊፈናቀል ነበር? የሚል ነው። ይህን ተከትሎ፣ ኧረ ለመሆኑ አገሪቱን የሚገዛው መንግሥት የቆመው የማንን ጥቅም ለማስከበር ነው? የሚሉ በዝተዋል። ከላይ እንደገለጽነው፤ ዋናው ችግር የአገሪቱ መሪዎች ጉዳዮችን በወቅቱ ለሕዝቡ ግልጽ ከማድረግ ይልቅ ማድበስበስና የተናገሩትን መቀልበሳቸው ጉዳዮች ነው። ለዚህ ምክንያቶቹ ለሕዝብ ከበሬታ ማጣት፣ የውስጥ ፍትጊያ እና አገራዊ ስሜትን የሚያዳክም መርሆ ማራመድ ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ሕዝብ ሳያውቃቸው በምሥጢር የሚካሄዱ ሌሎች ምን ምን ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን? መሪዎቻችን ለምን በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ቢያጡ ግድ አይሰጣቸውም? የሕዝብ አመኔታ ማጣት ለአመራራቸው ችግር፣ ለአገሪቱ ደኅንነት ሥጋት እንደሚፈጥር እንዴት ታጣቸው? መካሪ በማጣት ወይስ ችግር ሲከሰት በኃይል ለማስቆም ይቻላል ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው?

አለመተማመንን ያባበሰ አምስተኛው ነጥብ፣ የምሑራንና የመሪዎች አርቆ አለማሰብ፣ ዋሾነትና ግንጥል አመለካከት ነው። የአብዛኞቹ ምሑራንና መሪዎች የሞራል ጥንካሬ እውነትን በከፊሉ እንጂ መድፈር የማይበቃ ነው። እውነቱን እንደማስተማር ግራ ቀኙን የማያውቀውን ሕዝብ ተቀራምተውና ተገን አድርገው በሌለ በማይደረስበት ተስፋ ይደልላሉ፤ እየሳቱ ያስታሉ። የሕዝቡን ምሬት ያባብሳሉ፤ ያለፈ የተጋነነ ሰቆቃውን በመቀስቀስ በአንጃ ይከፋፍላሉ፤ የአጭር ጊዜ ዒላማቸውን ለማሳካት ምሬትና ጥላቻ ይዘራሉ። ከዚህ የተነሳ መንግሥትና ሕዝብ በሥጋትና ውጥረት ላይ ይገኛሉ፤ ተደጋጋሚ ጥያቄ ከሕዝብ ሲነሳ መንግሥት በተደጋጋሚ የወሰዳቸው ተመጣጣኝ ያልሆኑ እርምጃዎች ለዚህ ማስረጃ ናቸው። እርምጃዎቹ ችግሮችን እንደ መፍታት እያባባሱ የሕዝብ አመኔታ እያመነመኑ ነው። አገሪቱ በከፍተኛ እድገት ላይ ትገኛለች ሲባል፣ ተደጋጋሚ፣ መብራት ውኃ ስልክ እህል እጥረት፣ ተሠርቶ ያለቀ መንገድ ፈርሶ ሲቆፋፈር፣ ወዘተ፣ እነዚህ ተደማምረው ሕዝብ በመሪዎቹ እንዳይተማመን እያደረጉ ነው።

ማስተር ፕላኑን በተመለከተ ሁለት የሕግ ሊቆች ዶ/ር ደስታ አንዳርጌና ኡርጌሳ ቱራ ያስነበቡትን እስቲ እንመልከት [እዚህ እዚህ ይጠቁሙ]። የዶ/ር ደስታ ሥጋት ማስተር ፕላኑ ያስነሳቸው ጥያቄዎች የአገሪቱን ልማት ስለመተግበር ሳይሆን የኦሮሚያ ክልል ብቻ ጥያቄ መስሎ መታየቱ ነው። ስለሆነም፣ መንግሥት ብዙ የአመራር ስህተት ቢኖርበትም ካሳ ሰጥቶ ልማት ለማካሄድ ሕገ መንግሥቱ ይደግፈዋል የሚለውን አቋም አጉልተዋል። ኡርጌሳ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎች የሰጠውን መስተዳደራዊ መብት መንግሥት መጣስ አይችልም የሚለውን አስምረውበታል። የሁለቱም ምሑራን ሥጋት ተገቢና ከፊል እውነት ያዘለ ነው። ሆኖም፣ ሁለቱም ምሑራን ግለኛ አቋማቸውን ከማስቀደማቸው የተነሳ ከእውነቱ እንዳስቀሩ እንመለክታለን። ያልገለጹትና ከምሑራኑ ሊሠወር የማይችለው ሀቅ ግን ገዢው ፓርቲ ሆን ብሎ አዲስ አበባን፣ ራሷን የቻለች ክልል ትሁን ወይም የኦሮምያ ክልል ወይም የፌደራል ከተማ፤ ግልጽ ሳያደርግ በእንጥልጥል መተው ነው። ይህ ሁኔታ ያስከተለው ቅራኔ ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ሳያገኝ መሰንበቱና ለፖለቲካ ፍጆታ መዋሉ አሁን ለተከሰተው እልቂት ምክንያት ሆኗል። መንግሥት ተቃውሞ ሊነሳ እንደሚችል ሳይገምት ቀርቶ አይደለም፤ ከዚህም በፊት ተደጋግሟልና። ነገር ግን ተቃውሞ ቢነሳ በሽብርተኛነት ፈርጆ በጸጥታ ኃይል ማስቆም እንደሚችል ተማምኖ ነው። ተቃውሞው በርትቶ ይህን ያህል ይዛመታል ብሎ የጠበቀ ግን አይመስልም። ሰማንያ ስድስት ያህል ተገደሉ[*]፤ ከ2ሺህ የሚበልጡ እስር ቤት ገቡ። ይህ ሆኖ፣ የጉዳተኛውን ቁጥር እስከ ዛሬ ይፋ ለማድረግ መንግሥት አለመፍቀዱ ሌላ የአለመታመን እርከን ፈጥሯል። ተማሪዎቹን በዘዴ ማረጋጋትና ማስረዳት ሲገባ “ሽብርተኞች” ብሎ መፈረጅና ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ባልታጠቁ ዜጎች ላይ መጠቀም ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን አለመታመን ወደ ቁጣና ጥላቻ ያሻግረዋል።

መፍትሔውስ ምን ሊሆን ይችላል? አለመተማመንን ያባብሳሉ ካልናቸው አምስት ጉዳዮች አንጻር መተማመንን የሚያዳብሩ መስመሮችን መቀየስ ይቻላል። በመጀመሪያ፣ ከሁሉም ወገን ውሸትን መመሪያ አለማድረግ። ስላልተስማማ ብቻ አስተያየት መስጠት መከልከል የለበትም፤ የነጻ ፕሬስ መኖር አማራጭ የለውም። ሕዝብ እያወቀው መዋሸት፣ ንቀት ነው። ዋሽቶ ይቅርታ ሳይጠይቅና ሳያካክስ እዘልቃለሁ የሚል ደግሞ ቁጣንም ያስነሳል። ሁለተኛ፣ በድህነትና በፍትህ መጓደል ለሚማቅቀው ዜጋ በሰላማዊ መንገድ የድጋፍ ድምጽ ማሰማት፣ የእርዳታ እጅ መዘርጋት። ሦስተኛ፣ የሕዝብን አደራ ችላ ባሉባቸው ጉዳዮች ላይ መሪዎችን ከማሳሰብ አለመቆጠብ ሕግ የተላለፉትን ለፍርድ ማቅረብ። አራተኛ፣ በተገኘው ክፍተት ውዥንብር የሚነዙትን፣ ጨርሶ በጎ ነገር የለም የሚሉትን፣ ማጋነን የሚያበዙትን ለይቶ ማወቅ። አምስተኛ፣ ያላግባብ የታሠሩትን መፍታት። ስድስተኛ፣ የሕዝብ አደራ ተቀባይ ባለሥልጣናት “በሕያው እግዚአብሔር ስም” ቃለመሓላ እንዲፈጽሙ አማራጭ መስጠት። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በእግዚአብሔር የሚያምን እንደመሆኑ የብዙኃንን ፈቃድ ጣት ለማይሞሉ ውሳኔ መተው ወይም መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ ናቸው ብሎ ማሳበብ የማኅበረሰብን የሞራል መሠረት ቀስ በቀስ እንደ መናድ ነው [መንግሥት ከሕገ መንግሥቱ ውጭ ዘወትር በኃይማኖት ጣልቃ እንደሚገባ ምስክር መጥራት አያሻም]።

* * *

እውነቱን አውቆ ማሳወቅ፣ ለሚያወናብዱ ሰለባ ከመሆን ይጠብቃል። የአገርን ኅልውና የሚያናጋውን ለይቶ ማወቅ ለመቋቋም፤ በንጹሓን ላይ በሚደርሰው በደል ተባባሪ ከመሆን ያድናል፤ ትክክለኛ ጸሎት ለመጸለይ ይጠቅማል። እውነትና የመንፈስ አንድነት ሳይኖር ትክክለኛ ጸሎት ሊኖር አይችልም። የወንጌላዉያን አብያተክርስቲያናት ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል? በቅድሚያ የራስን ቤት ማጽዳት ነው። ከዚያ ሁሉን በሚገዛ አምላክ ፊት መውደቅ ነው። ከላይ ስለተዘረዘሩት ጉዳዮች ትክክለኛ መረጃ መሰብሰብና የሚሠራጩትን ሁሉ ቶሎ ከመቀበል አስቀድሞ ማመሳከር ነው። ልናውቅ ሲገባ እውነቱን ባናውቅ ለሚከተለው ጥፋት ከተጠያቂነት አናመልጥም። ሁሉን የፈጠረ አምላክ፣ በአምሳሌ ለፈጠርኩት ተሟገት ይላል። በእውነት ላይ አትደራደር ይላል። “አፍህን ስለ ዲዳው ክፈት፥ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ። አፍህን ክፍት፥ በእውነትም ፍረድ፤ ለድሀና ለምስኪን ፍረድ” ምሳሌ 31፡8-9። መጸለይ ቀዳሚ ነው፤ በሥጋም በሚያስፈልገው ሁሉ መርዳት ተገቢ ነው። እልቂት ከመበርታቱ በፊት መድረስ አስፈላጊ ነው። ነገ የዜና ማሠራጫዎች ይህን ያህል ሺህ ሕጻናት አልቀዋል ቢሉ ወንጌላዉያን ምን ምላሽ ሊሰጡ ተዘጋጅተዋል? የአገር መሪዎችስ?

ምንጮች [ሁሉም በእንግሊዝኛ]፦ የሱዳን አምባሳደር ቃለመጠይቅ፣ ሆርን አፌርስ ዶት ኮም። ሪፖርተር ጋዜጣ። ኢትዮጵያን ሄራልድ፤ ዋልታ ኢንፎርሜሽን። ቪኦኤ። ኢትዮፕያ ኦብዘርቨር። ኦል አፍሪካ ዶት ኮም።

[*] ቢቢሲ በሰኔ ወር ዘገባው የተገደሉትን ቁጥር 400 አድርሶታል፤ መንግሥት 170 ብቻ ነው ብሏል።

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave