ዓለምና ጥልቅ አሳቢቱ ዘሪቱ

ዘሪቱ ከበደ በ2009 ዓ.ም. በለቀቀችው “እዛ አልቀረሁም” ነጠላ ዘፈኗ እንዲህ ብላለች፦
የማትታመኚ መልክሽም የውሸት / ብዙ ማጭበርበሪያ የተሳሳለበት
አሁን ግን አየሁሽ ተጋልጠሽ በብርሃን / በቃ አትደልዪኝም ስለተነቃቃን
ውሸታም / ዓለም ውሸታም
ውሸታም / አታላይ ነሽ በጣም

ዓለም ስታታልል ማታለሏን ሳታስነቃ ነው። ደስታና ሰላም ስትሰጥ ከሥር ኃዘን ጎዝጕዛ ነው። ያለብርሃን አታላይነቷን ለይቶ ማወቅ ያዳግታል። ያ ብርሃን የኅሊና ብርሃን ብቻ ወይስ የወንጌልም ነው? ወንጌል “የዓለም ብርሃን” ኢየሱስ ነው ብሏል። ኢየሱስን ሳይይዝ የዓለምን ውሸት መለየትና ከወጥመዷ ማምለጥ አይቻልም።

የዘሪቱ የሕይወት ለውጥ በፌስቡክ መንደርተኞች መሓል ባለሦስት ረድፍ ጦርነት አስነስቷል። እዚህ አንደግመውም። የጦርነቱ መነሻ፣ ለአንዳንዶች ጥቅም ቀርቶባቸው፤ ለሌሎች ኢትዮጵያዊ ወኔ፣ ጭፍን ጥላቻና የወንጌልን አስተምህሮ አጥርቶ አለማወቅ ነው።

ዘሪቱ፣ ጥላ የመጣችው ዓለማዊነት የጌታን ደጅ ሲያጣብብ ማየቷ ጥያቄ ሳይፈጥርባት አልቀረም። ቢሆንም ተስፋ መቁረጥ የለባትም፤ ምክንያቱም ያመነችው ጌታ ባመኑት የጀመረውን የሕይወት ቍምነገር ከፍጻሜ ሳያደርስ የሚተው አይደለምና። ለእርስዋም ለራሳችንም እንጸልይ።

ዘሪቱ ስለ ቀመሰችው ሕይወት ኃላፊነት የለባትም ማለት አይደለም። ኢየሱስን የተጠጋ ኢየሱስን ከመከተል ውጭ በሰዎችና በሁኔታዎች ማመካኘት አይችልም። ማንም ወደ ኢየሱስ ቢጠጋ በቅድሚያ የሚታየው የራሱ እራቍትነት፣ ኃጢአተኛነት ነው። ጌታን፣ ይቅር በለኝ፣ ጽድቅህን አልብሰኝ ይለዋል። ጌታም ይህን ሰው ወዲያው ይቅር ይለዋል፤ ጸጋውን ያለብሰዋል። ያም ሰው፣ ለካንስ በጸጋው እንጂ ከራሱ ማንም ምንም የለውም ይላል። ይህን ርኅሩኅና መሓሪ ጌታ ይበልጡን ማወቅ ይሻል፤ ቃሉን ማወቅ፣ እርሱን ካመኑት ጋር ኅብረት ማድረግና እግዚአብሔርና ሕዝቡን ማገልገል ይሻል። “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” [ሮሜ 12:1-2]። ይህ ሰው ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አይጠመድም። “ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል። በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ስለዚህም ጌታ። ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ። እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል” [2ኛ ቆሮንቶስ 6:14-18]። በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል። ለመሞላቱ ምልክቶች በሕይወቱ ማየት ይጀምራል፦ አንደበቱ ተለውጦ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ ከቅዱሳን ጋር ሲነጋገር ራሱን ያገኛል። ለጌታ በልቡ ሲቀኝና ሲዘምር፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ ማመስገን ይጀምራል [ኤፌሶን 5:18-20]። ባጭሩ፣ የልቡ ዐይኖች የበሩለት ይሆናል። ክርስቶስን በጨለማ ዓለም ውስጥ መከተል እንግዲህ ይህን ይመስላል።

በዔደን ገነት የተጀመረ ፍልሚያ ዛሬም አልበረደም። ፍልሚያው በብርሃንና በጭለማ መሓል ነው። ዛሬ ፍልሚያው በግራጫው ወገን ለመገኘት ሆኗል። የእውነትና የውሸት፣ የልክና የስህተት ድንበር ደብዝዞ ሁለቱም በአክራሪነት ተፈርጀዋል። በግርግር መሓል የተረሳው፣ ግርጫ አዲሱ አክራሪነት መሆኑ ነው። ግራጫ [“ፍቅር” “መቻቻል” “አንድነት”] ብርሃን ይመስላል፤ ብርሃን ግን አይደለም። “ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን [የዚህ ዓለም ገዥ] ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና” ብሏል። [2ኛ ቆሮንቶስ 11:14] ብርሃን ስለ መሰለ ብቻ፣ ከኢየሱስ ነው ማለት አይደለም!

እዚህም እዚያም መሆን ቢቻል ምን ነበር? ከማንም ጋር ሳያነካካ ለራስ ብቻ ክርስቲያን መሆን ቢቻል? ሳያስቀይሙ ያፈቀዱትን ማድረግ ቢቻል ምን ነበረ? ከክርስትና፣ ከእስልምና፣ ከኢሬቻ፣ ከክህደት በጎ በጎውን መርጦ መውሰድ ቢቻል ምን ነበር? ይህ ዓይነቱ ምኞት ግን ምድራዊ ብልኃት እንጂ የክርስቶስን መስቀል ያማከለ ጥበብ አይደለም። ክርስትና አይደለም። ክርስትና ሰዎች በስምምነት የቀመሙት ሳይሆን ኢየሱስ የኖረውና ያስተማረው ሕይወት ነው፤ ኢየሱስ መንፈሱን በሰጣቸው ውስጥ በሚኖረው ሕይወት እንጂ በሥጋ ፈቃድ የሚሆን አይደለም።

ኢየሱስ አዳኝ ነው፤ ኢየሱስ ጌታም ነው [የሐዋሥራ 2፡36፤ ዮሐንስ 13፡13፤ ሉቃስ 2፡11፣ 6፡46]። ብዙዎቻችን የአዳኝነቱን በረከት ተቀብለን፣ ለጌትነቱ የሥፍራና የሁኔታ ድንበር አበጅተንለታል። አንዳንዶቻችንም ጌትነቱን ጥለን የቆሎ ጓደኛ አድርገነዋል። እምቢ ማለት የሚከብደው ዓይነት ጓደኛ፤ “ምንም አይደለም” የሚል ዓይነት ጓደኛ፤ ካባበሉትና ከካሱት “ደስ እስካሰኘሽ፣ ሰው እስካልጎዳ” የሚል ዓይነት ጓደኛ። አልፎ አልፎም “አስቀይምኩህ ይሆን? ይቅርታ” የሚል ዓይነት ጓደኛ። ጌታ ጌትነቱ ድንበር ከተበጀለት ቀድሞውንም ጌታ አይደለም። ጌትነቱ ለችግር ሰዓት ብቻ ከተፈለገ አልተረዳነውም። ጌታ ብለን የያዝነው የአእምሮአችንን ፈጠራ ከሆነ ደግሞ የራሱ መጠሪያ አለው፤ ጣዖት ይባላል። በቃሉ እውቀት ላይ ያልተመሠረተ አምላክና አምልኮ ጣዖት ከማምለክ አይለይም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚታዩ ፈታኝ ትርዒቶች መንስኤው የኢየሱስ አዳኝነት ከጌትነቱ መነጣጠሉ ነው። ሰዎች ራሳቸውን ጌቶች ባለቤቶች አድርገው ስለ ሾሙ። ገልጸው ጌቶች እኛው ነን አለማለታቸው [አገልጋዮች ነን ማለታቸው እንኳ] ይህን ሐቅ አይሸሽግም።

ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በታሪካችን ያለፈቃዳችን አስጨንቀው እንደ ገዙን ጌቶች እንዳይመስለን። ለጌታ ኢየሱስ መገዛት ወደ አሳር ሳይሆን፣ ወደማያልቅ ወደ በዛ ወደማይናወጥ ሰላምና ተስፋ መጥለቅ ነው። በነውጥ መሓከል ፈጽሞ መተማመን ነው። ዓለምና ትርፏን መናቅ ነው። ጌትነቱ በቅድስናው ነውና፣ ጌታ በሰው ፈቃድ አይሸነገልም። የኃይሉ ታላቅነት “ከሙታን ሲያስነሳው፣ ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ [ነው።] በሰማያዊ ሥፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛለት፣ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።” [ኤፌሶን 1:19-23፤ ፊልጵስዩስ 2:1-10]

በክርስቶስ ተከታዮች ዘንድ ወደ ፊት አለመገስገስ ወደ ኋላ መመለስ ነው። “ባለህበት ሂድ” ብሎ ነገር የለም። ጎራ አለመለየት፣ ጎራ መለየት ነው። እግዚአብሔርን መውደድ ዓለምን መጥላት ነው፤ ዓለምን መውደድ እግዚአብሔርን መጥላት ነው። በራሴ ትርጉም ክርስቲያን ነኝ፤ የግድ እንደ እናንተ አድርጌ ማመንና መሆን ግን አይጠበቅብኝም ማለት ፍሬነገሩን ከመሠረቱ መሳት ነው። መነሻው፣ መተላለፊያውና መድረሻው ኢየሱስ እንጂ የግለሰብ ፍላጎት አይደለም። ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ አይደለም። ኢየሱስ የኖረውና ያዘዘውን ማሻሻል እርሱን መናቅና ራስን መካከለኛ ማድረግ ነው። የሕይወትን ፈር መልቀቅ ነው። ፍቅር ይበልጣልና፣ ያመነችና ያላመነ እስከ ተዋደዱ ይጋቡ? ቤት ሆኖ መጸለይ ይቻላልና ቤተ ክርስቲያን መሄድ ይቅር? በዓለም ነንና እንደ ዓለም እንኑር? የሚገርመው እንዲህ የሚያስቡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መብዛታቸው ነው። ጥለው እንዳይሄዱና መዋጮ እንዳይጎድል መሪዎች “ማንም ፍጹም የለም” “ፍቅር ይበልጣል” “ማን ፈራጅ አረገኝ?” እያሉ ነው። ለእውነት እንደ መገዛት፣ ማፈንገጥና መደራደር ተመርጧል።

እምነቴ ለራሴ በልቤ ነው ማለት፤ በድርጊት እስካልታየ፣ የሞተ እምነት ነው። ከቤተ መቅደስ ትንሽ ከዓለም ትንሽ ለጊዜው ከችግር ያድን ይሆናል፤ ጌታን ያስደስታል ማለት ግን አይደለም። ክርስቶስን ያመኑ ከእውነት ሌላ የሚሹት ሊኖር አይገባም። የክርስቶስ ተከታዮች እውነትን ሲፈሩ፣ ችላ ሲሉና ሲሸቅጡ ከማየት የባሰ የሚያምም ነገር የለም። ጥያቄው ዛሬም እንደ ጥንቱ አንድ ነው፦ የብርሃን መንገድና የጨለማ መንገድ አለ፤ በየትኛው ላይ ነህ? ዘመኑ ወንድም ሴትም ነኝ፤ ወንድም ሴትም አይደለሁም እያለን ነው። ግራጫም ብርሃን ነው እያለን ነው። የሚስማማንን እውነት እንፍጠር እያለን ነው።

ስለ ብልጽግና ወይም ስለ ብልግና እስካልሆነ፤ አማኝ ስለ ዓባይ፣ ስለ ቢራቢሮ፣ ስለ ማሽላ፣ ስለ ከበሮ ቢዘፍን ምን ይጎዳል? አንዳንዱን መዝሙር “ክሮስኦቨር” እና “ኮንሠርት” ይሉታል። ወይም “ክርስቲያን ኮንሠርት” “ሮክ” = “ክርስቲያን ሮክ” “ጋንግስተር ራፕ” = “ክርስቲያን ራፕ”። አብዮተኛ መንፈስ ነው። የኢየሱስን ስም በአደባባይ የሚጠሩ ክርስቲያን ያይደሉ “ክርስቲያን” አርቲስቶች በዙ። “ክሮስኦቨር” ማንንም ላለማስቀየም፣ ሁሉን ለማስደሰት፤ ዳር የቆመውን ወደ መሓል ለመሳብ። ዓላማው ዞሮ ገንዘብ ነው። እንደ ገንዘብ የጌታን ሥልጣን የሚቀናቀን የለም። ዓለምን መኮነንና ኢየሱስን ማወደስ ውጤትና ግንዛቤው አንድ ነው ማለት አይደለም። ለዓለምና ለገንዘብ መዝፈን ምንም አይደለም ያሉ ፈረንጅ ክርስቲያን ወዳጆቻችን እነሆ በነፍሳቸውና በኑሮአቸው እየከፈሉ ይገኛሉ። ዓለምን መኮነን መልካም ነው፤ ዓለምን መኮነን ውዳሴ አምላክን ሊተካ ግን አይችልም። ኢየሱስን ያላማከለ ውዳሴ ከንቱ ውዳሴ ነው።

ሰሞኑን ፈረንሳዮች ኢማኑኤል ማክሮ[ን] የተባለ የ39 ዓመት ሰው ለአገር መሪነት መርጠዋል። የማክሮ[ን] ሚስት ዕድሜዋ 64፣ ባሏን በ25 ዓመት ትበልጠዋለች። እስከተፋቀሩ ታዲያ ምን ያስከፋል? ማንስ ያገባዋል? እንል ይሆናል። እርግጥ ነው ማንም አያገባውም። የ15 ዓመቱን ማክሮ[ን]ን አስተማሪው ሆና ንጽሕናውን መግሠሧ ምንም አይደለም? እርሱ 39፣ እርሷ የ15 ዓመት ተማሪው ሆና ክብረ ንጽሕናዋን ቢገሥሥ በቀላሉ ይታለፍ ነበር? ወንጀል በ“ፍቅር” ሲሳበብ እነሆ። ባልና ሦስት ልጆቿን ጥላ ማክሮ[ን]ን ማግባቷስ? ምንም አይደለም? ይህን ሁሉ የምናነሳው ዘመኑ ምን ያህል ከሰነበተ ስነምግባር እንደ ተዛነፈ ለመግለጽ ነው። ይባስ ብሎ ማክሮን የፈረንሳይን ሕዝብ “በፍቅር እመራችኋለሁ” እያላቸው ነው። በፍቅር መምራት ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ነገር ግልጽ ይሁን፦ ኃጢአት በሥልጣኔ ብዛት አይሻሻልም፤ ሁሉም ከዔደን ገነት ጀምሮ እንደ ነበረው ነው። ፈረንሳዮች ስላደረጉት፣ ኃጢአት ኃጢአት መሆኑ ይቀራል? ኢየሱስ የኖረውና ያስተማረውም አይሻሻልም፤ ፍጹም ሕይወት አይሻሻልም።

[ውሸታም/ ዓለም ውሸታም / ውሸታም / አታላይ ነሽ በጣም]

ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከምናየውና ከምንሰማው ይኸ በምን ይለያል? የወንጌል ብርሃን ሁሌም የሚያስታውቀን ልክና ልክ መሳዩን ለይተን እንድናውቅ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ አማንያን በላከው ደብዳቤ፣ የአባቱን ሚስት [እንጀራ እናቱን] ስላገባው ወጣት፣ “የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው” ይለናል [1ኛ ቆሮንቶስ 5:1]። ስላልተለመደ ያስደነግጣል፣ ያስቆጣል፣ ያሳፍራል። ሲደጋገም ይለመዳል። መለመዱ መደንዘዝን እንጂ ልክ መሆኑን አይገልጽም። በሌላ ሥፍራ ለወንድና ለሴት በሚሆን ጕዳይ ሐዋርያው፣ ይህንንማ “ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን?” ይላቸዋል [1ኛ ቆሮንቶስ 11:14-15]። በሌላ አነጋገር፣ ዛሬ የምናየው ያልነበረ እንዳይመስለን። የነበረው ነው ስም ቀይሮ የሚመላለስ። ለዚህ ዓይነት ማታለል፣ መንፈስ ቅዱስን ማዳመጥና መጸለይን፣ በቃሉ መሞላትና ጌታን ከሚያውቁ ጋር ኅብረት ማድረግን የመሰለ መከላከያ አይገኝለትም።

ZerituThinking“ሪቪል” መጽሔት ከሁለት ዓመት በፊት ከዘሪቱ ከበደ ጋር ያደረገውን ቃለመጠይቅ ከፊሉን ከታች አቅርበናል። በቃለምልልሱ ውስጥ የዘሪቱን ጥልቅ አሳቢነት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። ጥልቅ አሳቢዎች ያመኑበትን፣ ከሕይወት ገጽታዎች ጋር ካላገናዘቡ አይረኩም፤ ተነጥለው መቆም አይፈሩም። ይህ አቋማቸው አንዳንዴ ለትችትና ለአደጋ ያጋልጣቸዋል። ፍልሰታቸው ከዓለም ወደ ኢየሱስ እስከሆነ ድረስ ግን፣ የሚያዋጣው አብዝቶ ወደ ነጻ አውጪው ኢየሱስ መጠጋጋት ነው፤ በአንዳንዶች ትችትና አለመረዳት ጠላት መግቢያ እንዳያገኝ ቀዳዳውን መዘጋጋት ነው። ቅድም እንዳልነው፣ የሚያዋጣው በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ነው፤ ኢየሱስን በቃሉ ውስጥ በማወቅ ማደግና መጠጋት ነው፤ ኢየሱስን በማወቅ ከቀደሙ፣ የልብና የአእምሮ ስፋት ጸጋ ከተለገሳቸው ጋር መጎዳኘት ነው።

ቃለምልልሱን ያቀረበው ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ፣ መግቢያው ላይ በራሱ ሚዛን፣ “ዘሪቱ ዘፋኝ ጓደኞቿን ትታ (በሥራ) ዘማሪያኑን ብትቀላቀል የባሰ ስካር እንደሚጠብቃት አታጣውም” ይለናል። ይኸ የሚቆጠቍጥ ትዝብት ነው። አንድ ነገር ግልጽ ይሁንልን። ‘አንድ እግር እዚህ፣ አንድ እግር እዚያ’ ‘ግራ ጆሮ እዚህ፣ ቀኝ ጆሮ እዚያ’ እና የተከፈለ ልብ ሁላችንንም ይፈታተነናል። ሁለት መውደድ መጕደል ነው፣ ከሁለት ማጣት ነው። ማክረርና ሚዛን ማጣት መልካም አይደለም፤ በፍቅርና በሕይወት ጉዳይ ግን የሚበጀው ጎራ መለየቱ ነው። ጎራ አለመለየት፣ ባዶ መቅረትና መንከራተት ነው። ኢየሱስን ብቻ ያሉ፣ ሌላም ሁሉ ይጨመርላቸዋል። ኢየሱስን ይዤ፣ ዓለምንም ይዤ ያሉ ኢየሱስን አጡ። “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ብሏል [ማቴዎስ 6:24]። 

ኢትዮፕያንቸርች ዶት ኦርግ

ክፍል አንድ። ዘሪቱ ከበደን ወትሮም ከዘፋኝነት ከፍ አድርጌ ነው የማያት። በአንድ ቃለምልልስ ካገኘኋት በኋላ “ይህቺ ሴት አንድ ዘፋኝ ብቻ አይደለችም ነው” የሚል ስሜት ነው የፈጠረችብኝ። ገና ወደ እውቅናው ስትመጣም አንዲት የምታምር ድምጻዊት ብቻ ሆና አይደለም። ዘሪቱ የሚባለውን ስም በራስ መተማመኗ ከፍ ያደረገች ናት። ዘፈኑን ብትተወውም፣ ዘማሪ ብትሆንም፣ ዘፈንና መዝሙርን ቀላቅላ ብትሰራም ለእኔ ያው ናት። አሁን የሚዘመሩትም ከዘፈን ጋር ተዳቅለው ነው። እዚያም ሁከት በዝቷል። ዘሪቱ ግን ለሁከት እዚያ ድረስ ትደክማለች ብዬ አላምንም። የሰከረው ዓለም መች ቦታ ጠበበው? ለመንፃትም ሀይማኖት አትቀይርም። በሀይማኖት መንፃት የለም። ለእምነቷ የተሻለ ያለችው ስፍራ ላይ፣ እግዚአብሔርን በፍፁም ፈቃዷ ለማገልገል የተሻለ ያለችውን መምረጥ የእርሷ መብት ነው። ኦርቶዶክሶቹ የሚንጫጩትና ፕሮቴስታንቶቹ እንደ ድል የሚቆጥሩት ሁለቱም ጭንቃቸው የቁጥር መቀነስና መጨመር ስለሆነ ነው። ማናቸውም የዘሪቱ ሕይወት አይደለም። ትግሉ ሌላ ነው። ሀይማኖታዊ ፖለቲካ ነው። ሀይማኖታዊ ቁማር ነው።

ዘሪቱ ዘፋኝ ጓደኞቿን ትታ (በሥራ) ዘማሪያኑን ብትቀላቀል የባሰ ስካር እንደሚጠብቃት አታጣውም። ቦታ መቀየርም ትልቁ ጉዳይዋ እንደማይሆን አምናለሁ። ራሷን በማፍረስ እንጂ ቤት በመቀየር መለወጥ አለ ብላ የምታምን አይመስለኝም። እንደ ብዙዎች ካባዋን ሳይሆን እንደራስዋ ስጋዋን በመላጥና አዲስ ስጋ በማብቀል አዲሷን ዘሪቱ የመስራት አቅም ያላት ይመስለኛል። እግዚአብሔር ደግሞ እንደ ልቧ መሻት ያደርግላታል። የሚያደርግ አምላክ ነው። ለነገሩ አድርጎላታልም። ይህ የነቃ ሀሳብ ከባዶ የመጣ አይደለም። የመሰጠት ነው። ፎቶዋን ይዞ ለወጣው መጽሔት የሰጠችው ቃለምልልስም ሕይወት እንጂ የቦታ ጥበት እዚያ እንዳልወሰዳት ከቃሏ ያስነብበናል። ዘሪቱ ስትመጣም ስትሔድም (እርግጥ ሄድኩ አላለችም) አንዲት ዘፋኝ አልነበረችም። ዘማሪም ብትሆን አንድ ዘማሪ ብቻ አትሆንም። እንደ ዘማሪያኑም ዓለም ላይ ወድቃ እንደማትገኝ (አንዳንዶቹ ጭራሽ ከዓለምም የወደቁ ናቸው) ተስፋ አደርጋለሁ። አነጋጋሪው ቃለ ምልልሷን እንካችሁ።

ሪቪል፡- ከመንፈሳዊነት ጋር ተያይዞ መዝፈን አቁመሻል?
ዘሪቱ፡- መንፈሳዊነት ሁለገብና የሁለንተናችን ለውጥ ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ ከአለማዊነት ስንወጣ የማይነካ የህይወታችን ክፍል የለም። ሁሉም ነገር እኔ እንደምለውና ዓለም እንደምትሰብከው ሳይሆን እግዚአብሄር እንደሚለው የማድረግና የመሆን ሂደት ነው። በዚህ ውስጥ ታዲያ እንደ ሁሉ ነገሬ የጥበብ ሥራዬም ሳይፈተሸ አያልፍም። ስለዚህ ሙዚቃም ይሁን ፊልም፤ ብቻ ምንም ነገር ልስራ የማደርገው ነገር እግዚአብሄር የሚፈልገውን መልዕክት ያደርሳል ወይ? ሰዎችን ይጠቅማል ወይ? ደሞስ እንደሱ ፍቃድና ልክ ሰዎችን ያሳዝናል? ያስደስታል ወይ ብዬ በመጠየቅና ይልቁንም ከሱ ከራሱ መልዕክትን በመቀበል ወደ መስራት መንፈሳዊነት እያደኩ ነው። መዝፈን ይሁን መዘመር አላውቅም። የማውቀው እግዚአብሄር እንደሚከብርበት ነው።

ሪቪል፡- ብዙዎች ግን “ዘሪቱ ወይ ትዘምር ወይ ትዝፈን መቁረጥ አቅቷት እየወላወለች ነው” ይላሉ። በእርግጥ እየወላወልሽ ነው?
ዘሪቱ፡- እየሱስ ክርስቶስን ተከትያለሁ ብዬ በማምንባቸው ዓመታት ውስጥ በአካሄዴ ሁሉ እግዚአብሄርን ደስ አሰኝቻለሁ ብዪ አላስብም። ምንአልባትም በአንዳንድ የህይወቶቼ ክፍሎች እግዚአብሄርን አይፈሩም ተብለው ከሚታሰቡት ሰዎች እንኳን ብሼ አውቃለሁ። እንደ እግዚአብሄር ምህረትና እንደ አባትነቱ ፍቅር ባይሆን ኖር ዛሬ ያለሁበት ቦታ አልገኝም ነበር። አድርጌ የማላውቅ ግን መወላወል ነው። ፈርቼ አውቃለሁ፤ ግራ ገብቶኝም ያውቃል፤ ፈርሶ ሲሰራ እንደሰነበተ ሰው ደግሞ በሁሉም ነገር እርግጠኛ ሆኜ ሀሳቤን ሳለውጥ መጥቻለሁም ብዬ ለመናገርም አልደፍርም። ወላውዬ ግን አላውቅም። ዘሪቱ ሙዚቃ አቁማለች ብሎ ሚዲያ ጭምር ሲዘግብ፤ እኔን ጠይቆና አነጋግሮ አይደለም። መንፈሳዊ ከሆነች መቆሟ አይቀርም ብለው በራሳቸው በመደምደም ነው። እኔ ህይወቴን ስቀጥልና ከተነገሩት ዜናዎች በተቃራኒ የሙዚቃ ስራዎች ወደ አድማጭ ሲደርሱ የወላወልኩ የሚያስመስል መልክ ሊያሰጠኝ ችሏል።

ሪቪል፡- ግን ዝናና ገንዘብን መስዋትነት ማድረግ የሚከብድ አይደለም?
ዘሪቱ፡- እኔ ለመተው የሚከብድ የገንዘብ ክምችት የለኝም። ዝናንም በተመለከተ ዘማሪዎች ከዘፋኞች ባልተናነሰ ዝነኞች የሆኑበት ዘመን እንደሆነ ነው የማስበው። ከዝና ወደ ዝና ብሸጋገር አሁን ከምከፍለው ዋጋ የበለጠ እንደምከፍል አውቃለሁ።

ሪቪል፡- ቤት መኪናና ሌሎች አያስፈልጉም ብለሽ ነው የምታምኚው?
ዘሪቱ፤ እኔ የማምነው ከሆነ ቦታ ተነስተህ የሆነ ቦታ ለመድረስ ትራንስፖርት እንደሚያስፈልግ ነው። መኪናው ያንተ ከሆነ ጥሩ፤ ካልሆነም መኖርህን ለማታውቅበት ለዛሬ ባለቤትነትህ ያለው ፋይዳ ውስን ነው። የቤትም አስፈላጊነት መጠለያነቱ፤ ትርጉሙም አብረውህ በሚኖሩት ሰዎች እንጂ በባለቤትነት ካርታው አይደለም። የባለቤትነት ዋስትና ለእኔ ትርጉም የለሽ ነው። እግዚአብሄር ወዶ ለሚጨምርልኝ ለእያንዳንዱ ቀን የሚያስፈልገኝን ሁሉ እንደሚያዘጋጅልኝ አምናለሁ።

ሪቪል፡- እንደዚህ ያለ ህይወት ግን ላገባችና በተለይም ልጆች እናት ለሆነች ሴት አይከብድም?
ዘሪቱ፡- እንደዚህ ያለ ህይወት ለማንም ቀላል አይደለም። በተለይም እንዳልከው ቤተሰብ ላለን ሰዎች ደግሞ የማይታሰብ ነው። ነገር ግን ይህ በስጋዊ አቅማችን ስንሞክረው ነው። ሰው የመሆንን ትርጉም ለመረዳት በፈቀድን መጠን ግን ራሱ እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ይችለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ማለት፤ ሰው በሀጢያት ከመውደቁ በፊት ወደ ነበረው ማንነት የመመለስ ጉዞ ማለት ነው። ያ ማንነት ደግሞ ከእግዚአብሄር የመሆንና ማንነቱን የማንፀባረቅ ህይወት ነው። በመሬታዊ ገደብ እሱን ማንፀባረቅ አይቻልም። በመንፈስ ቅዱስ አሰልጣኝነት ከመሬታዊ ገደብ ወደ እሱ ማንነት የሚያሻግረን መመሪያ ሁሉ ደሞ በቅዱስ ቃሉ ወስጥ አለ። ኢየሱስ ለምን አይነት ክብር እንደጠራን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ከንግዳችን፣ ከቤተሰባችንና ከራሳችን ጭምር በላይ እሱን እንድናስቀድም ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ደቀመዛሙርቶቹ ልንሆን እንምንችል በግልፅ አስቀምጦልናል። ስለዚህ እሱን በመከተል ውስጥ ምንም አይነት አቋራጭ አልፈልግም።

ሪቪል፡- ባለቤትሽ በዚህ ደስተኛ ነው?
ዘሪቱ፡- በጣም ደስተኛ ነው እንጂ። የምትገዛ ሚስት አድርጎለታል። ከዚህ ህይወት ጋር በተዋወኩባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በእኔ ላይ ባስከተለው የማንነት መናጋት ተከትለው በመጡ ጥፋቶች ብዙ ዋጋ ከፍሏል። ሚስትህ ፈርሳ እስክትሰራ መታገስ ቀላል ነገር አይደለም። ከመጀመሪያዋ የተሻለች ሚስት እንዳለችው እሱ ምስክር ነው።

ክፍል ሁለት። ለዘጠኝ አመታት ያህል ሌላ ተጨማሪ የሙዚቃ አልበም ለምን እንዳልለቀቀች ተጠይቃ ስትመልስ፦...ለዚህ እንደምክንያት የምቆጥረው ያለፉት ዘጠኝና አስር አመታት በኔ ሕይወት እንደ ሰውም ይሁን እንደ አርቲስት የተለያዩ ለውጦች ያስተናገድኩባቸው በመሆናቸው በአንድ አቋም ተረጋግቶ አሁን ይሄ ነው የሚባል የሙዚቃ ስብስብ ለማበርከት የሚያስችል ሁኔታ ላይ አልነበርኩም።

ሪቪል፦ እነዚህ ለውጦች ምንድናቸው?
ዘሪቱ፦ ...ከሁሉም በላይ ግን በሙያዬ ካገኘሁት ተቀባይነት የተነሳ አደባባይ ሲቆም እንዲሁም በተከታታይ የስራ ግንኙነቶች ውስጥ ሳልፍ የገጠሙኝ ውጣ ውረዶች ቆም ብዬ ራሴን እንዳይና እንዲመረመር ስላረጉኝ፤ እግዚአብሔር መኖሩን እንደምታምን ሴት፤ በመኖሩ ማመኔ ን ዋጋ የሚሰጠውን በፈቃዴ እንደፈቃዱ ለመኖር ግድ ሆኖ ያገኘሁት የሚኖረው ሕይወት የመፈተሽና የተሻለውን ለመሆን ፈርሶ የመሰራት ሂደት ነው።

ሪቪል፦ ፈርሶ የመሰራት ሂደት በጣም የሚያስፈራ ጉዞ ይመስላል።
ዘሪቱ፦ በጣም ህመም ያለውም ጉዞ ነው። ነገር ግን የእውነትን መንገድ ለመፈለግ ለታደለ ሰው ሁሉ የግድ የሆነ ጉዞ ነው። ማንነትን የሚያህል ነገር እንኳን ይሁን ብሎ መልቀቅ ይጠይቃል።

ሪቪል፦ ...ከለቀቅሻቸው አንዳንድ ነጠላ ዜማዎች መንፈሳዊ ይዘት ጋር ተያይዞ ዘሪቱ እንደ ሌሎቸ አንዳንድ ድምጻውያን የኘሮቴስታንት እምነት ተከታይ ሆናለች ይባላል። ለዚህ ምላሽሽ ምንድነው?

ዘሪቱ፦ እኔ የኘሮቴስታንትም ሆነ ሌላ ሃይማኖት ተከታይ አይደለሁም። የየትኛውም ሃይማኖት ተቋም ወይም ድርጀት አባልነት ሆነ ተጠሪነት የለኝም። ካለፍኩበት ብዙ ውጣውረድ የተነሳ እረፍትና ፍትህን ፍለጋ ፊቴን ወደ እግዚአብሔር መልሻለሁ። በዚህም ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከዚህ አለም መንግሥት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ልጅነት ተሸጋግሬያለሁ። የእግዚአብሔር መጽሐፍ እንደሆነ ያመንኩትን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ ያዘጋጀውን እሱን ወደ መምሰል የሚያደርስ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጂ ሃይማኖታዊ ድርጅትን መከተልን አንድ ጊዜም አላስተማረኝም። ስለዚህ የሚከተለው የሚጠብቀውና የሚጸናበት ሃይማኖት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ሪቪል፦ ነገር ግን የእግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስ እኮ ስለ ቤተክርስቲያን የያወራል። ለዚህ ምላሽሽ ምንድነው?
ዘሪቱ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረኝ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቶስ አማኞችና ተከታዮች ስብስብ እንደሆነ ነው። እሱ መካከለኛና ራስ የሆነበት ተከታዩቹ ደግሞ እንደሚኖርባቸው ጸጋ በአካሉ ውስጥ የተለያየ ብልት ሆነው፤ በፍቅር እየተጉ እሱን ወደ መምሰል ሙላት አብረው የሚያድጉበትና እግዚአብሔርን የሚያከብሩበት ኀብረት ነው።እንደዚህ ያለው ህብረት ደግሞ ተቋማዊ መታወቂያ ካላቸውም ከሌላቸውም ወንድሞችና እህቶች ጋር በሚገባ አለኝ። ልዩነታችንን ታግሰን አንድ በሚያደርገን በክርስቶስ ዙሪያ መሰብሰብ እጅግ የሚያስደስት ነው። ስለዚህ ሕይወት እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።

ሪቪል፦ ብዙ ገንዘብ እያመለጠሽ ነው። ሀብታም መሆን አትፈልጊም?
ዘሪቱ፦ ለምድራዊና ለጊዜያዊ አለማ መሳካት እንኳን ዋጋ መክፈል ግድ ነው። ከትልቁ ከእግዚአብሔር ጋር በመንግስቱ ስራ ባልደረባ ወደ መሆን ክብር ከፍ ላረገኝ የልጁ ደቀመዝሙርነት ይልቅ ብዙ ዋጋ በመክፈል የሚኖር ነው። የሚያጓጓኝ አለምን የሚቀይረው የፍቅሩ ኃይል ብልጽግና ነው።

ሪቪል፦ ብር በደንብ ከሰበሰብሽ በኃላ ነው የጠፋሽው፤ አመለካከትሽንም የቀየርሽው?
ዘሪቱ፦ ይሄ እውነት አይደለም። ከመጀመሪያም እንደ ብርታትም ሆነ ድካም ገንዘብ የመሰብሰብ ልማድ የለኝም። በቀደመ ሕይወቴ፣ እንደ ጥበብ አፍቃሪነቴ ያገኘሁትን ሁሉ መልሼ ለጥበብ ሰጥቻለሁ። አሁን ደሞ የባሰ ፍቅር ላይ ነኝ፤ ይሄ ፍቅር ደሞ ኑሮሽ ይበቃሻል፣ የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለም ይለኛል። ጥቂት እንደሚበቃ ከመረዳቴ በፊት ገንዘብ ብዙ አጥፍቻለሁ፤ እኔን ብቻ ሳይሆን በአካባቢዬ ያሉትንም ብዙዎች ጎድቻለሁ። አሁን ግን ጥቂት በዝቶልኝ እኖራለሁ። አንዳዴም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች አልፋለሁ፤ ቢሆንም ከአላማዬ አያደናቅፈኝም። በገንዘብ በኩል ሲሰራም፣ ገንዘቡን የሚፈልገው ለራሴ በቅቼ የማካፍለው እንዲኖረኝ እንጂ የሚያስጎመጀኝ ምንም አይነት ቅምጥልና የለኝም።

ምንጭ፦ ክፍል አንድ፣ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ / ክፍል ሁለት፣ (#ዘጸአት) አሌክስ

ምትኩ አዲሱ
5/17/17 [9/9/2009 ዓ.ም]

እነዚህንም ይመልከቱ፦ ዘሪቱ / ቴዲ / ዳኒ / ክልክል? / ዮናስ