ከ “ኵሽ” ወደ “ኵሽ” ?

ኦሮሞ ፕራይድ [Opride.com] በፈረንጆች አቆጣጠር ኦገስት 18/2017፣ “ከኵሽ” ወደ “ኢትዮጵያ” መልሶ ወደ “ኵሽ” በሚል ርዕስ መርጋ ዮናስ ከቄስ ዶክተር በንቲ ኡጁሉ ቴሶ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ አትሞ ነበር። ቃለምልልሱን ያነበቡ ብዙዎች ወገኖቻችን በመረጃ ከማሳመን ይልቅ በስድብ ናዳ በታጀበ ቁጣ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። ኢትዮፕያንቸርች ኦገስት 23/2017 ቀጥሎ የተመለከተውን ምላሽ ሰጥተን፣ በዚህ [ጉዳይ] ዕድሜ ልክ ጥናት ያደረጉ ስመ-ጥር ሊቃናትን ምክር መሻት [ይኖርብናል] የሚል አሳብ አቅርበን ነበር። ዲሴምበር 6/2017 የታሪክና የቋንቋዎች ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ "ኢትዮጵያ ወይስ ኩሽ" ብለው ያቀረቡት ጽሑፍ ለጥያቄአችን መልስ ሆኖ ስላገኘን ከምስጋና ጋር አትመናል። 

 

[የኢትዮፕያንቸርች መልስ]

ፓስተር ዶ/ር በንቲ ቴሶ የተሃድሶ መሪውን ጀርመናዊ ማርቲን ሉተርን ካባ ተረክቧል ማለት ትንሽ ከልኩ ያለፈ ይመስለኛል። ቄስ ዶ/ር ማርቲን ሉተር የዕብራይስጥና የግሪክ ቋንቋዎች ሊቅ ነበርና መጽሐፍ ቅዱስን በተራ ጀርመንኛ ተረጎመ፤ ሰው የሚድነው በጸጋ ብቻ፣ በእምነት ብቻ፣ በክርስቶስ በማመን ብቻ ብሎ አስተማረ [ሮሜ 1:17]። ያን በማድረጉ በዘመኑ ከነበረችዋ ሮማ ካቶሊካዊት ተጽዕኖና ትብታብ ሕዝቡን ገላገለ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ተራው ሕዝብ በሚገባው ቋንቋ መተርጎሙ ወደ ሌሎች አውሮጳ አገራት ተዛመተ። ወንጌልም፣ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወዳስተማሩበት ሁኔታ ተመለሰ።


ዶ/ር በንቲ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮሞኛ እንደ ተረጎመው እንደ ኦነሲሞስ ነሲብ እንኳ የቋንቋዎችና የነገረ መለኮት ሊቅ አይደለም። "ኢትዮጵያ" በ "ኩሽ" ይተካ ነው የሚለን። ይህን የሚለው ለኦሮሞ ሕዝብ በማሰብ፤የኦሮሞ ሕዝብ "ኢትዮጵያ" እንዳይባል በመፈለግ ነው። ኦሮምኛ ኩሺትክ ቋንቋ ነው [እንደ ሲዳምኛ፣ ሶማልኛ፣ ወዘተ]፤ አማርኛ ደግሞ ሴማዊ። ኦሮምኛም ሶማልኛም አማርኛም ትግርኛም በቤተሰብ "አፍሮ ኤዥያቲክ" ነው። ዶ/ር በንቲ ይህን ወይ አላወቀም ወይም ሊደብቀን ፈልጓል።
ይኸ የሚያነጋግረን ጉዳይ የጥንት ታሪክ በመሆኑና የአካባቢው ሕዝቦች፣ የድንበሮች መስፋትና መጥበብ፣ መቀያየጥ ብዙውን ስላድበሰበሰው ያለን ምርጫ በዚህ ረገድ ዕድሜ ልክ ጥናት ያደረጉ ስመ-ጥር ሊቃናትን ምክር መሻት ነው። ለምሳሌ፣ ኡለንዶርፍ "ኢትዮጵያ" መባሉን አይቃወምም። ጀርመናዊው ሉዶልፍም። ሌሎችም። ባጭሩ፣ "ኢትዮጵያ" መባል ኃጢአት አይደለም፤ አለመባል ጽድቅ አይደለም።

ፓስተር በንቲ፣ ዋቄፈና ከክርስትናና ከእስልምና ብዙ አይራራቅም ይለናል። ዋቄፈና፣ እስልምና ሌሎችም ኃይማኖቶች ከክርስቶስ ወንጌል ጨለማ ከብርሃን፣ ሞት ከሕይወት እንደሚራራቅ ይራራቃሉ!! ይህን ለምን እንደ ዘነጋው አልገባኝም። ብዙ ትምህርት ወደ እብደት ያዞራል ልበል?! ይባሱን ሚሲዮናውያን የኦሮሞን አምልኮ አዛብተዋል ይለናል። ሚሲዮናውያን በሁሉም ረገድ ተዋጥቶላቸዋል ባልልም፤ ቢያንስ ወንጌልን ህክምናን ትምህርትን በሄዱበት አገራት አዳርሰዋል። ፓስተር በንቲ የዚህ ተጠቃሚ ነው፤ ይልቅ ሳያስበው ኦነሲሞስ የከፈለውን ትልቅ መስዋእት ከንቱ ሊያደርግበት ነው። እርግጥ "ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና" [ዕብራውያን 1:1-] ራሱን ገልጧል፤ በዋቄፈታም እግዚአብሔር ራሱን ያለ ምስክር አልተወም። በዘመን መጨረሻ ራሱን በሙላት የገለጸው ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ይኸ ኢየሱስ የዓለም አዳኝ ነው፤ የኩሽ አዳኝ ነው፣ የሴም አዳኝ ነው። የበንቲ ቴሶ አዳኝ ነው። "በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ የፈጠረ" ነው [የሐዋሥ 17:26]፤ የጥል ግድግዳን ያፈረሰና "አንድን አዲስ ሰው" የፈጠረ ነው [ኤፌ 2፡15-16]። ያም ማለት እግዚአብሔር ኦሮሞነትን አማራነትን ሶማሌነትን ፈረንሳይነትን ይጠላል ማለት አይደለም። የቋንቋዎች ልዩ ልዩ መሆንና አለመግባባት እግዚአብሔርን ያለመታዘዝ ኃጢአት ውጤት ነው [ዘፍጥረት 11]። በጴንጤቆስጤ ቀን ከዓለም ቋንቋዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ነበሩ [የሐዋሥ 2]። ፓስተሩን ስሰብክ እንዳልገኝ እንጂ! የቀድሞውን መመኘትና ወደ ኋላ መመለስ ግን በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ በደል አይሆንም?

በሌላ በኩል፣ ዶ/ር በንቲ አዲስ ነገር አላመጣም። "ኢትዮጵያ" መባሉና "ኩሽ" አለመባሉ እንደ ስህተት መታሰቡ ራሱ ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ሰፊና ጥልቅ መጽሐፍ ነው። ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላም እንኳ ገና የማናውቀው ብዙ ነገር አለ። በክርስቶስ አምኖ ለመዳን ግን አንዴም አንሶ አያውቅም። በተኣማኒነቱ፣ በጥንታዊ አስረጅ ሰነዶቹና ማስረገጫዎቹ [የቤተክርስቲያንና የመንፈስ ቅዱስ ህልውና ምስክሮች] የሚተካከለው የለም። ጥቁሮች ወገኖቻችን "ጥቁር ኢየሱስ" ብለው መጽሐፍ ቅዱስ አትመዋል፤ ይህ የሆነው፣ አውሮጳውያን ኢየሱስን ነጭ ስላደረጉትና ጥቁሮች ለባርነት እንደ ተፈጠሩ ለማድረግ ማሰባቸው ነው። ኢየሱስ ግን ነጭም ጥቁርም አይደለም፤ አይሁድ ነው። ላቲን አሜሪካውያን ደግሞ ኢየሱስን ነጻ አውጪና አብዮተኛ አድርገውታል፤ ይህም ምዕራባውያን፣ መንግሥት ሰማያት መግባት እንጂ ስለ ምድር ማሰብ አያሻም እያሉ፣ ያደረሱባቸውን በደል ለማረም ነው። በሴትነታቸው የደረሰባቸውን በደል ለማቃናት "ጾታ አልባ" መጽሐፍ ቅዱስ አትመዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ለግል አጀንዳ ማዋል ወደማያልቅ ወደማይወጣበት ስህተት ውስጥ መግባት ነው። አውሮጳውያን ዛሬ ባብዛኛው ክርስትናውን ችላ ብለውታል፤ ያለፈው ታሪካቸው ኃፍረት ሆኖባቸዋል። ዶ/ር በንቲም ብዙ ርቆ ሳይሄድ መረጃ የሳሳበት የግል ግንዛቤው ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊና መንፈሳዊ ቀውስ [ኩሽና ኢትዮጵያ የተለያዩ ስለሆነ፣ እስካሁን ያለው ግንኙነታቸው በውሸት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ አብረው ማምለክ አይችሉም ነው?] ቢያስብበት ይሻላል።

ሳልረሳ፣ ዶ/ር በንቲ ዶክትሬቱን የሠራበትን ሰነድ የትና እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ቢነግረን የበለጠ ለመመካከር ይጠቅመናል።

 

+  +  +

ኢትዮጵያ ወይስ ኩሽ

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

 

አንድ ሰሞን “የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በሪቨረንድ በንቲ  ቴሶ  ኡጁሉ ተጽዕኖ የኢትዮጵያን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰርዛ በኩሽ ለውጣዋለች” የሚል ወሬ ተናፍሶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን አበሳጭቶ ነበር። ብዙ ተቃውሞም ተጽፏል። ይኼ ተጨማሪ ማብራሪያ ነው።

 

ከመጀመሪያው ለመነሣት፥ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ቅድመ ክርስቶስ፥ ሁለተኛው ድኅረ ክርስቶስ የተጻፉ ባለ ሁለት ክፍል ነው። የመጀመሪያው ክፍል ብሉይ ኪዳን ይባላል። ይህንን ክፍል በቋንቋቸው በዕብራይስጥ ጽፈው የሰጡን አይሁድ ናቸው። ሁለተኛው ክፍል ሐዲስ ኪዳን ይባላል። የተጻፈው በጽርእ (በግሪክ ቋንቋ) ነው። በግሪክኛ ጽፈው የሰጡን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ናቸው።

ብሉይ ኪዳን በመሠረቱ የአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ግን የክርስትና ሃይማኖት በብሉይ ኪዳን ላይ ስለተመሠረተ ፈላጊዎቹ እጅግ ብዙ ሆኑ። የአይሁድ ሃይማኖትም ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈላጊው ስለበዛ፥ የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳን የግብፁ ግሪካዊ ገዢ (በጥሊሞስ ፊላዴልፎስ (285-246 ቅድመ ክርስቶስ) ሰባ (ሁለት) ሊቃናት ሰብስቦ ወደዓለም አቀፉ ቋንቋ ወደግሪክኛ አስተረጐመው። (ሕፃኑን ኢየሱስን በቤተ መቅደስ ያቀፈው ሽማግሌው ስምዖን ከሰባ ሊቃናት አንዱ ነበር የሚል ተአምር በእኛ ዘንድ ይነገራል።) አሁን እንግዲህ፥ ሐዲሱም ብሉዩም በግሪክ ቋንቋ  ሊነበብ ቻለ። የግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ የተተረጐመው ከዚህ ከግሪኩ ቅጂ ነው። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፥ “ኢትዮጵያ ብሉይ ኪዳኗን የተረጐመችው በቀጥታ ከዕብራይስጡ ነው” ይላሉ። ማስረጃቸው አርኪ አይደለም።

 

እነዚህ ሰባ (ሁለት) ሊቃናት ሲተረጉሙ፥ ዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሀገርና የሕዝብ ስም ሲያጋጥማቸው አንዳንዱን ዕብራይስጡ ውስጥ እንዳለው ይወስዱታል። አንዳንዱን፥ ለምሳሌ እንደ “ኹሽ” እንደ “ፍልስጥኤም” ያሉ ስሞችን እንዳለ በመውሰድ ፈንታ፥ የግሪክ ተመሳሳይ ስም ይሰጡታል። (ፍልስጤምን “ኢሎፍሊ”፥ ኩሽን “ኤይቲኦፕ” አሏቸው።)  የዕብራይስጡ “ኩሽ” የሚያመለክተው ጥቁርን ሕዝብ ነው። ግሪኮች ደግሞ ጥቁሩን ሕዝብ የሚጠሩት “ኤይቲኦፕ” ብለው ስለሆነ፥ “ኩሽ” የሚለውን ስም “ኤይቲኦፕ” ቢሉት አይገርምም። ባጭሩ፥ ግሪኩ “ኤይቲኦፕ” የሚላቸው ዕብራይስጡ “ኩሽ” የሚላቸውን ሕዝቦች ነው። “ስልቻ” እና “ቀንቀሎ” እንደማለት ነው፤ ሁለቱ ቃላት በምን ይለያያሉ? እኛ ደግም፥ ከላይ እንደተናገርኩት፥ መጽሐፍ ቅዱሳችንን የተረጐምነው ከግሪኩ ስለሆነ፥ “ኤይቲኦፕ” የሚለውን “ኢትዮጵያ” አልነው። ከዕብራይስጡ ተርጕመነው ቢሆን ኖሮ ምናልባት “ኩሽ” (ኩሳ) እንለው ነበር።  “አለቀ ደቀቀ። ፓስቶሩ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የዛሬ ስድሳ ሁለት ዓመት ባሳተሙት በግዕዝ መዝገበ ቃላታቸው ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም እንዴት እንደተቹት ቢያይ ኢትዮጵያና ኩሽ ትርጕማቸው አንድ ሆኖ የሚያመለክቱት ኢትዮጵያንና ሱዳንን መሆኑን እንደምናስተምር ይረዳ ነበር።

ጥያቄው መሆን ያለበት “የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢትዮጵያ’፥  የዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ‘ኩሽ’ የሚሉት ስሞች  የሚያመለክቱት እነማንን ነው?” የሚል ነበር። መልሱ ቀላል ሆኖ ሳለ አስቸጋሪ እናደርገዋለን። አንደኛ፥ እነዚህ ስሞች የሚያመለክቱት ጥቁሩን ሕዝብ ነው ብለናል። ሁለተኛ፥ በዓለም ላይ ብዙ ጥቁር ሕዝቦች ቢኖሩም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራስያን የሚያውቋቸው ጥቁር ሕዝቦች በቅርባቸው ያሉትን ኖባን (ሱዳኖችን) እና ኢትዮጵያውያንን ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ አንድ ጥቁር ሰው ከተነገረ፥ ያ ሰው ወይ ኢትዮጵያዊ ወይም ኖባዊ (ሱዳናዊ) ነው። ባጭሩ፥ ለግሪክ ደራሲዎች “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም የሱዳኖችና የኢትዮጵያውያን መጠሪያ ነበር። ኢትዮጵያን ያላንዳች ማስረጃ ለኢትዮጵያ ብቻ ወይም ለሱዳን ብቻ መስጠት ስሕተት ነው። በዚያው አስተሳሰብ፥ ለዕብራይስጥ ደራሲዎች “ኩሽ” የሚለው ስም የሱዳኖችና የኢትዮጵያውያን መጠሪያ ነበር። ኩሽን ያላንዳች ማስረጃ ለኢትዮጵያ ብቻ ወይም ለሱዳን ብቻ መስጠት ስሕተት ነው።

“የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በሪቨረንድ በንቲ  ቴሶ  ኡጁሉ ተጽዕኖ የኢትዮጵያን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰርዛ በኩሽ ለውጣዋለች የሚለው ወሬ ውሸት ነው። ውሸቱ እንዲፈጠር ያደረገው  መርጋ ዮናስ ሪቨረንድ በንቲ  ቴሶ  ኡጁሉን አነጋግሮ ያወጣው ጽሑፍ ነው።  መርጋ ጽሑፉን ሲጀምር “An Oromo pastor has taken up the mantle by translating or changing biblical words deemed erroneous” (አንድ የኦሮሞ ፓስተር [በንቲ  ቴሶ  ኡጁሉ] የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን በመተርጐም ወይም ስሕተት የመሰሉትን በመለወጥ  [የማርቲን ሉተርን] አጽፍ አነሣ) ይለዋል። ነገሥት ለተከታያቸው አልጋ እንደሚያወርሱ ነቢያት ለተከታያቸው አጽፍ ያወርሳሉ--ኤልያስ አጽፉን ለኤልሳ እንዳወረሰው። መርጋ ሪቨረንድ በንቲን እንዲህ ሲሸነግለው ሪቨረንዱም አላስተባበለም። በመቀጠል፥ “Among the most notable changes or corrections in the new bible is the term Ethiopia, which was changed to Cush. Rev. Benti Ujulu Tesso is one of the scholars behind some of the latest changes.” (እመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዋናዎቹ ለውጦች ወይም እርማት መካከል ያስፈለገው ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ነበር፤ ወደ ኩሽ ተለውጧል። ሪቨረንድ ኡጁሉ ቴሶ ከለውጡ በስተጀርባ  ካሉት ምሁራን አንዱ ነው) ይላል። በለውጡ ብንስማማም ባንስማማም፥ አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር የጀርመንን ሊቃውንት አማከረ ሲባል ማንም ኢትዮጵያዊ ሊኮራ ይገባዋል። ግን የጀርመን ሊቃውንት ብሉዩን ከዕብራይስጥ፥ ሐዲሱን ከጽርዕ (ከግሪክ) ወደጀርመን ቋንቋ ሲተረጕሙ እንደ በንቲ ያለ አንድ ሰሞነኛ ካህን አማከራቸው ማለት የሚያስቅ ነው። ምክንያቱም፥ ከመርጋ ጽሑፍ እንዳገኘነው፥ በንቲ የአንድ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን በክህነት እያገለገለ ገና የዶክትሬቱን ድርሰት ይጽፍ የነበረ ሰው ነው። ለመመረቂያ የሚጽፈውም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ሳይሆን፥ ግሪክኛና ዕብራይስጥ ማወቅ በማያስፈልገው “ሰማይ አምላክ ነው” በሚለው በኦሮሞ ቅድመ ክርስትና ሃይማኖት ላይ ነበር። (“Oromo Indigenous Religion and Oromo Christianity: Contradiction and Compatible.”)

ጀርመኖች ማርቲን ሉተር መጽሐፍ ቅዱሱን ወደጀርመንኛ እስኪተረጕምላቸው ድረስ የሚጠቀሙት በላቲኑ ቅጂ ነበር። የተረጐመውም ሐዲሱን ከግሪክኛ ብሉዩን ከዕብራይስጥ ነበር። በንቲ ስለጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙም ስለማያውቅ ማርቲን ሉተር የተረጐመው ከላቲን ነው ይላል። የጀርመን ቤተ ክርስቲያን አሁን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሷን እንደገና ለ2017 ዓ. እ. እንዲደርስ አድርጋ ተርጕማለች። የትርጐማው ግብረ ኀይል ሊቀመንበር፥ ፕሮፌሰር ዶክተር ክሪስቶፍ ኬለር (Professor Dr. Christoph Kähler, Bishop Emeritus) በጽሑፍ እንደገለጠው፥ ጀርመኖቹ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ትርጐማ ሲከልሱ፥ ሪቨረንድ በንቲ እንኳን የማርቲን ሉተርን አጽፍ ተጐናጽፎ በትርጐማ ሊሳተፍ ቀርቶ፥ አጠገባቸውም እንኳን አልነበረም።

ሁለተኛውና ዋናው ውሸት “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም ፓስቶር በንቲ  በ “ኩሽ” አስለወጣቸው ማለቱ ነው። የጀርመን መጽሐፍ ቅዱስ  ዱሮውንም “ኢትዮጵያ” የሚል ስም አልነበረበትም። ያልነበረ አይለወጥም። የነበረውና አሁን ወደ “ኩሽ” የተቀየረው Mohrenland/Mohren  ነው። ታዲያ ሌሎቻችንስ ብንሆን የቀድሞው Mohrenland/Mohren  ሳያስቆጣን ወደ Cush/Cushite ቢለወጥ ምኑ ነው የሚስቆጣን? Mohrenland/Mohren እንዳለ ቢቆይ እንመርጥ ነበር ማለት ነው? እንዲያውስ እኛ እጀርመን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስከዛሬ ሳንገባ ዛሬ ምን አስገባን? ጀርመኖቹ Cush/Cushite ን የመረጡት Mohrenland/Mohren ስድብ ስለሆነ የጥንቱን ስም ብንይዝ ይሻላል ብለው ነው። ወይስ ምን ምክንያት ሰጥተን Mohrenland/Mohrenን ወደ Cush/Cushite መለወጣችሁን ትታችሁ ወደ ኢትዮጵያ ለውጡ እንበላቸው። መቈጣት ካስፈለገ፥ Cush/ Cushite ያለውን የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳን ነው።

“ፈረንጆች ስማችንን ለወጡብን፤ የአንድን አገር ስም መለወጥ የሚችል የሀገሬው ሕዝብ እንጂ ፈረንጅ አይደለም” የሚል ቁጣ ይሰማል። የሀገር ስም መለወጥና ለአንድ ስም አዲስ ትርጕም ማምጣት የተለያየ ነገር ነው። የሀገራችንን ስም ማንም አለወጠውም። ሁለት አንድ ነገር ቢሆኑ ኖሮ THE GIDEONS የሚባሉት ፕሮቴስታንቶች በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለውን ወደ Cush ከለወጡበት ጊዜ ጀምሮ ኩሽ እንባል ነበር። ግን አልተባልንም። አንድም ፈረንጅ “ይድረስ ለኩሽ መንግሥት  ፕሬዚዴንት...” ብሎ ሲጽፍም አላየንም። ቢልም ፖስተኛው አያደርስለትም።

ሆኖም አንድ ጥያቄ ማንሣት እንችላለን፤ ዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን “የካም ልጆች ኩሽ፥ ሚስራይም፥ ፉጥ፥ ክናዐን ናቸው” ይላል። ይኸንን ዐረፍተ ነገር አዲሱን የጀርመን ትርጕም አዘጋጆች ምን ብለው ተረጐሙት? ስሞቹን እንዳለ ገልብጠዋቸዋል ወይስ “ምስራይም” የሚለውን ስም Ägypten (Egypt ግብፅ) ብለውታል? “ምስራይም” የሚለውን ስም እንዳለ መገልበጣቸውን ትተው እንደ ግሪኩ Ägypten ብለውት ከሆነ (ባላየውም እንዳሉት አልጠራጠርም)፥ ለምንድን ነው “ኩሽ” የሚለውን ስም እንደግሪኩ Äthiopien (Ethiopia ኢትዮጵያ) ያላሉት?

 

መርጋ “ሌላ ምን ለውጥ ተደርጓል?” ብሎ ሪቨረንድ በንቲን ቢጠይቀው፥ “ሌላውን አሁን ልነግርህ አልችልም” አለው። እውነቱን ነው፤ የማያውቀውን፥ ያልዋለበትን እንዴት ሊነግረው ይችላል?

ሦስተኛ፥ “ኢትዮጵያ የሚለው ስም ስድብ ነው” ይላል ፓስቶሩ፥ ጋላ የሚለው ስም ስድብ ነው እንደተባለው ማለት ነው። “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ስድብ  ከሆነ፥ “ኩሽ” የሚለው ስም እንዴት ስድብ አይሆንም? እንደእውነቱ ከሆነ፥ “ኢትዮጵያ”ም ሆነ “ኩሽ” የኛ ስም ከሆነ ቅዱስ ስም ነው። አንዳንድ ሰዎች የሚሉትማ ሌላ ነው፤ ኩሽ የኖኅ እርግማን ስላረፈበት እርጉም ነው ይላሉ። ስድብ ማለት ይህ ነው። ኖኅ ሦስት ልጆች ነበሩት፤ ሴም፥ ካም፥ ያፌት። ጥፋተኛው ካም አራት ልጆች ወለደ፤ ኩሽ (ኩሳ)፣ ምስራይም (ግብፅ)፥ ፉጥ፥ ከነዓን። ቢጐዳም ባይጐዳም፥ የተረገመው ከነዓን ነው። ሌሎቹ አልተረገሙም።

አራተኛ፥ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ወደ ኩሽ ቢለወጥ ፥ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ያገለላቸውን “ኩሽ” የሚባሉትን ኦሮሞችን ሲዳሞችን፥ ... ያቅፋል ይላል።ይኸ አስተሳሰብ “አባቶቻቸው ከጣና ባሕር የመጡ ወንድማማቾች ናቸው” ከሚለው ተረት ይሻላል። ግን ሁሉም አለማወቅ ያመጣብን ስሕተት ነው። አገር ቤት ሄደን አንዱን የኦሮሞ ወይም የሲዳማ ገበሬ፥ “ደስ ይበልህ፤ ኢትዮጵያዊ መባልህ ቀርቶ ኩሳዊ ተብለሃል” ብንለው፥ እብዶች ያደርገናል እንጂ በደስታ ጮቤ አይመታም። ዕውቀቱ ካለው፥ “ኩሽ” መባል የሚወድ ሕዝብ “ኢትዮጵያ” ቢባል አይጠላም?

የቋንቋ ተመራማሪዎች “ሴማዊ፥ ኩሻዊ” የሚሏቸው ቋንቋዎች አሉ። ይህ አከፋፈል የተመሠረተው በቋንቁዎቹ ላይ እንጂ፥ በተናጋሪዎቹ ዘር ላይ አይደለም። የሁለቱም ዘራቸው አንድ ነው። በቋንቋ “ሴማዊ” እና፥ “ኩሻዊ”፥ በዘር “ኢትዮጵያ” እና “ኩሽ” የሚያመለክቱት ያንኑ አንዱን ሕዝብ ነው። “ኩሽ የሚለው ስም በይበልጥ ያቀራርበናል” ማለት ኢትዮጵያን አንቀበልም ለሚሉ ወገኖች የተፈጠረ ፖለቲካዊ አስተዋፅኦ ነው--የሃይማኖት አስተማሪን ሳይቀር የተተናኰለ በሽታ።

 

አምስተኛ፥ የሀገሪቱ ስም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ Abyssinia ነበር፤ ወደ ኢትዮጵያ የተለወጠው አሁን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነው ይላል ፓስቶሩ። አለማወቅ ካልቀረ እንደዚህ ነው። በየትኛው ዘመን ነው ኢትዮጵያ ራሷን በእንግሊዝኛ Abyssinia ትል የነበረው? የትኛው ንጉሥ ነው “እኔ እገሌ ንጉሠ ነገሥት ዘብሔረ Abyssinia” ያለ? ከ1307 እስከ 1336 ዓ.ም. በነገሠው በአፄ ዓምደ ጽዮን እንኳ ብንጀምር፥ ራሱን የሚጠራው “ንጉሠ ጽዮን፥ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” እያለ ነበር።  የውጭ አገር ጸሐፊዎች አገራችንን Abyssinia ይሏት ነበረ። በእኛ በኩል ግን አገራችን መንግሥት ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ያለው ሰነድ የሚያመለክተው ኢትዮጵያ መባሏን ነው። ሰነዶቹ ሜዳው ሁሉ ናቸው። አነጋግሯቸው አታኵርፏቸው።

ስድስተኛ፥ ሐበሻ ማለት ድብልቅ ማለት ነው ይላል። ከየትኛው መዝገበ ቃላት ነው እንዲህ  ያለ ትርጕም የሚገኘው?  ወይስ ዐዋቂ መስሎ የተራ ሰው አነጋገር ከሰው ፊት ማቅረቡ ነው? ሐበሻ የነገድ ስም ነበረ። የነገድ ስም ስድብ ሊሆን አይችልም። ሁለተኛም አንድ ሀገር በአንድ ነገድ ስም መጠራት በኢትዮጵያ አልተጀመረም። 

ለማጠቃለል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከመተዋወቃችን በፊት ጀምሮ ሀገራችንን የምንጠራው “ኢትዮጵያ” ብለን ነው። በሌላ ስም ትጠራ ማለት ተንኮል ነው። ስማችንንም፥ መጽሐፍ ቅዱሳችንን አናስነካም። ሆኖም፥  የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጐማ አይቆምም፤ ይቀጥላል። ወደፊትም ብዙ ዛሬ ያልታወቁ የግሪክና የዕብራይስጥ ቃላት በምርምር ብዛት ይታወቃሉ፤ አዲስ ትርጐማን ያስገድዳሉ። ተቀባዩ ቋንቋም ያረጃል፤ በዛሬው ሰዎች ቋንቋ የተተረጐመ መጽሐፍ ቅዱስ ለነገ ሰዎች እንግዳ ይሆንባቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የሚቋቋመው እነዚህ ምክንያቶች አዲስ ትርጐማ ሲያስገድዱ ተዘጋጅቶ ለመገኘት ነው። 

ምንጭ፦ ኢትዮፓኖራማ ዶት ኮም