ቋ ን ቋ ን  በ ቋ ን ቋ

~ ቋንቋህ ያስጠላል፤ ቋንቋዬ ይበልጣል ~

ስለ ቋንቋ የተለያዩ እይታዎች መኖራቸው አዲስ አይደለም። የሚገርመው ይልቅ፣ ብዙዎች እንደ ሹምና አቡን ትእዛዝ ሲሰጣጡ ማየት ነው። ትእዛዙን ማን፣ እንዴት ይፈጽም? እይታዎችን ማቀራረብና መተግበርስ ይቻላል? መቸ በምን ቅደም ተከተል? ወዘተ። ይህን ያሰቡበት ቢኖሩ ድምጻቸው አልተሰማም። የራስን አጉልቶ፣ የሌላኛውን ማድበስበስ የተለመደ በመሆኑ፣ የጽሑፌ ይዘት ለያንዳንዱ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ የተዘነጉ ጥቃቅን አሳቦችን ማነጋገር ይሆናል።

ቋንቋ ቢያንስ ሀ/ ድንበር ተሻጋሪ መሆን ይኖርበታል፤ አማርኛ ተናጋሪ፣ እርስ በርሱ ብቻ ከሆነ፣ ከኬላው ውጭ በምን ይግባባል? ለ/ ድንበር ተሻግረን እንግሊዝኛ፣ አማርኛ፣ ወዘተ፣ የቆነጠርን ቢያንስ አኗኗራችንን ለማሻሻል እንደ ሆነ አንርሳ ሐ/ ቋንቋ ተሻጋሪ እንዲሆን፣ ድልድይ የሚሆን ቋንቋ ይሻል። አማርኛ ድልድይ ነው። እርግጥ፣ ሁሉን ቋንቋ ማወቅ የተሻለ ነበር። ይህ ስላልተቻለ፣ ከቋንቋዎች መርጦ መጠቀም ግድ ሆነ። በአመራረጡ ላይ፣ የፖለቲካ ኃይላት ተጽዕኖ አላሳደሩም ማለት ግን አይደለም። [ቅኝ] ገዥዎች፣ ሥርዓተ ትምህርት፣ ሥርዓተ ኃይማኖት፣ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ጦርነት፣ ወዘተ፤ ኃይላቱ ተጽዕኖ እያሳደሩ፣ ራሳቸውም የሚለወጡ ናቸው።

በህዝቦች ታሪክና ባህል ውስጥ እንደ ነበረ የሚቀጥል የለም።

ሰዎች፣ ተደራጊም አድራጊም ነን። ገዢ መደብ ከህዝብና ከአገር ቀድሞ በአንድ ጀንበር አይወለድም። ነገሮች የየራሳቸው ሂደት አላቸው። አንዱ ባንዱ ላይ በኃይማኖት በንግድ ወይም በቋንቋ ወይም በጦር ኃይል መግዛት በአገራችን አልተጀመረም፤ አልተጀመረም ማለት በደል የለም ማለት አይደለም።

ከአማርኛ ውስጥ የኦሮምኛን ተጽዕኖ ለቃቅመን ብናወጣ፣ ጐንደር ትሸበራለች። የፈረንሳይኛ ተጽዕኖ ከእንግሊዝኛ ቢወገድ፣ ሎንዶን የእብዶች ከተማ ትሆናለች። ትኵረታችን በመግባባት ላይ እንጂ በተቃርኖ ፖለቲካ ላይ ብቻ መሆን የሌለበት ለዚህ ነው፤ ስንደማመጥ ነው መተማመን የምንጀምረው። ይህ ሁሉ ግን ድንቅ አይደለም፤ በኢትዮጵያ ብቻ አልተከሰተም። ቋንቋ ሁሉ እኩል ጠቀሜታ ይኖረዋል ማለት ደግሞ የሌለ ታሪክ መፍጠር ነው። የትም አገር እንዲሁ ነው። እንግሊዝኛ ከስልጤ ከአፋርኛ ከአማርኛ ይሻላል ማለት አይደለም።

“እኵል” ምን ማለት ነው? እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። አሥር ሰው የሚገለገልበትን ቋንቋ፣ ሺህ ሰው ከሚገለገልበት እኵል መመደብ አክሳሪና ፍትህ የጎደለው አመለካከት ነው። በአንጻሩ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ዳውሮ ቋንቋዎችን ጨፍልቆ በትእዛዝ አንድ (ትልቅ) ቋንቋ (ወጋጎዳ) መፍጠር አደገኛነቱን አይተናል። አማርኛም እንኳ ይህን ያህል ዘመን በሥራ ላይ ከርሞ፣ በመኃይምነት መንሠራፋት፣ ህዝቡን ባላሳተፈ ኃይማኖታዊ ሥርዓትና በብልሹ አስተዳደር ከመቶ፣ ሲሦውን ህዝብ ማዳረስ አልተቻለም። ኦሮምኛ በኃይለሥላሴና በደርግ ዘመን ሁለተኛ ብሔራዊ ቋንቋ መሆን ይችል ነበር፤ ግን አልሆነም። እዚህ ላይ፣ ለምን አልሆነም ብለን መከራከር ወይም በደልን በበቀል ማካካስ፣ የትም አያደርስም።

አማርኛ ብሔራዊ/ፌደራል ቋንቋ መሆኑ ሊደንቅ አይገባም። ምን ምርጫ ነበረን? ዐረብኛ? ፈረንሳይኛ? ጣልያንኛ? እንግሊዝኛ? አራቱም ተቃጥቶብን አልተሳካም። ቢሳካ ኖሮ፣ ይኸኔ በኃይማኖት፣ በአበላል፣ በአስተሳሰብና በትውልድ፣ ዐረቡን፣ ፈረንሳዩን፣ ጣልያኑን፣ እንግሊዙን በመሰልነ። እነዚህም በአካል እንኳ ባይሆን በስነልቡና በገዙን። ለማንኛውም አልሆነም፤ ወደ ኋላ መመልከቱን ትተን የደከምንበትን መልካሙን ሳናወድም፣ አጠናክረን ወደ ፊት እንዴት እንገስግስ የሚለውን እንመልከት።

ቋንቋ የልቡናን አሳብ ማስፈጸሚያ ነው። መለስ ዜናዊ የጠራ አማርኛና የጠራ እንግሊዝኛ ቢናገሩ፣ ፓርቲአቸውን ለማጽናትና የውጭ መንግሥታትን አሳምኖ ግባቸውን ለመምታት ነው፤ በዚህ ረገድ፣ በአመዛኙ እንደ ተሳካላቸው መካድ አይቻልም። ጸጋዬ ገብረመህን፣ ሰሎሞን ዴሬሳና ገብረክርስቶስ ደስታ፣ የተገኙበትን ባህል አዳቅሎ ለማበልጸጊያና የሦስት ትውልድ አስተሳሰብ ለመቅረጽ የተጠቀሙት አማርኛን ነው። የኪነጥበብ ሥራዎቻቸው የኃይማኖትና የቋንቋ ድንበር የማይገድባቸው የስብእናችን እና የባህላችን እምቅ ኃይል መገለጫ ናቸው። የጸጋዬ “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” በፊደል መጻፉ (በቁቤ አለመጻፉ) ጉዳቱ ምኑ ላይ ነው? በእንግሊዝኛስ ቢተረጎም? ቍምነገሩ በሁሉም መልኩ አስተሳሰብን ባህልን መጋራት፣ ማጋራት፣ ስብእናን ማስከበር፣ ህልውናን ማጽናት፣ ተጽእኖ መፍጠር ነው።

abagadaa

በቋንቋ አሳብና ልምድ እንዋዋሳለን። ኢትዮጵያውያን ምሑራን በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በየአገራቱ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያስተምሩ፣ የአገሬውን ትውልድ አስተሳሰብ እየቀረጹና እየተቀረጹ ጭምር ነው። ከዚህ የተነሳ እውቀት ይስፋፋል፣ ድንቁርና ይሸሻል። ባእዳን በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በዐረብኛ፣ ወዘተ፣ እኛን ይቀርጹናል። ቋንቋ እንደ ወራጅ ወንዝ፣ በመዋዋስ ይፋፋል፣ የቀደመውን ትርጕሙን ይስታል፤ ይሞታል ያንሠራራል። ስብእናችንም እንደዚሁ ይከበራል ይዋረዳል። ይኸም ድንቅ አይደለም፤ በኢትዮጵያ ብቻ አልተከሰተም።

መጽሐፍ ቅዱስ የአንድን ሕዝብ ቋንቋና የሞራል ሰውነት በማነጽ ከፍተኛ ድርሻ አለው። በእንግሊዞች ምድር (እና እንግሊዞች በደረሱበት ሁሉ)፤ በጀርመን ምድር፣ በሩስያ፣ በኢትዮጵያ፣ ወዘተ። አናሲሞስ ነሲብ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጕም፣ ፊደልን መምረጡ፣ የኦሮሞን ህዝብ መንፈሳዊ ማንነት፣ ስብእናና አብሮነት ለማነጽ ተስማሚ ሆኖ ስላገኘው ነው። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኦሮምኛ ለማስተማር ሥርዓተ ትምህርት ማሰናዳቱ ትክክለኛ ሂደት ነው። ውሳኔው፣ ለምሩቃኑ አብሮነትና የሥራ በር ከፋች ይሆናል ብለን እንለፈው። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን አርኣያነት አለመከተል፣ እውቀትን መገደብና ማህበራዊ ትስስርን ባለመገንባት የዩኒቨርሲቲን መሠረተ ዓላማ መሳት ይሆናል።

አማርኛ የጠላት ቋንቋ ስለሆነ መማር አይገባም የሚሉ ነበሩ፣ ተመናምነውም ቢሆን ዛሬም አሉ። ይኸ የድንቍርና አንድ ገጽታ ነው። መማር እንዲያውም የጠላትን ቋንቋ ነበር እንጂ። በመማማር ውስጥ ይወዳጃል፤ የሚጋራቸውን እሴቶች ለይቶ ያውቃል፤ በጭፍን ከተጓዘበት አካሄድ ይታረማል። ምሥጢር የሚያበዛ ድብቅ ሰው፣ ተረጋግቶና አረጋግቶ መኖር አይሆንለትም። አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ መሆኑን ከመጥላቱ ብዛት፣ አማርኛ በእንግሊዝኛ ይተካ የሚል ጥናት መሰል ጽሑፍ አንብቤአለሁ። ቋንቋ ቃላት መቀመር ብቻ ሳይሆን ባህልን፣ የኑሮን ፍልስፍና፣ ኃይማኖትን ጭኖ እንደሚመጣ አልተገነዘበም። ለማንኛውም፣ በራሳችን ያልተቻቻልነውን፣ ከባህር ማዶ መጥቶ ሊያስማማን አይችልም ብለን እንለፈው።

በቋንቋ ምክንያት ብዙ ኦሮሞ ወንድሞቻችን በአገራቸው ጉዳይ ሙሉ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ተደርጓል። ልድገመውና፣ ምክንያቱ የመሪዎች መታወር ነው። ከትምህርት ገበታ፣ ከሥራ፣ ከጤና፣ እድሉ አምልጧቸው የተፈናቀሉትን፣ ግለሰቦቹና እግዜር ብቻ ያውቃሉ። የነኦቦ ለማ መገርሳ አካሄድ ይልቅ ተስፋ ሰጭ ነው። አማርኛ የጠላት ቋንቋ ነው ያሉ፣ እንግሊዝኛ ወይም ፈረንሳይኛ የሥልጣኔ በር ከፋች እንደሆነ ነግረውናል። እነዚሁ፣ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አፋርኛ፣ ወዘተ ሥልጣኔ እንደሆነ ዘንግተዋል። ሥልጣኔ ግድ አውሮጳዊ መሆን አይጠይቅም። ከሰባት ቢሊዮን ተኵል የዓለም ህዝብ ላቲን የሚጠቀመው ሲሦ ያህሉ ብቻ እንደሆነ አንርሳ። ያለ ላቲንም ሥልጣኔ መጋራት ይቻላል ማለት ነው። እንዲያማ ባይሆን፣ ከዓለም ህዝብ የእጅ ብልጫ ያላቸው ዐረቦች፣ ቻይናዎች፣ ሩሲያዎች፣ ህንዶች፣ ኤዥያዎች (ቪዬትናም፣ በርማ፣ ላኦ፣ ቲቤት፣ ወዘተ) የራሳቸውን ቋንቋ መጣል ሊኖርባቸው ነው። ከጎረቤቱ ጋር ሳይግባባ እዚያ ማዶ ማለት የብብትን መጣል ነው። ውዥንብር ለሚነዙ ቀዳዳ መፍጠር ነው። በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመው በደል፣ ማንንም ያልማረ፣ ኢፍትኃዊ አስተዳደር እንጂ ቁቤን አለመጠቀም አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ ቁቤ ብቻውን ፍትኅ አያስገኝም፤ በደል አያርቅም። ኦሮሞ በኦሮሞ ላይ፣ አማራ በአማራ ላይ፣ ትግሬና ወላይታ በትግሬና በወላይታ ላይ የሚያደርሱትን በደል የዘነጋን ይመስላል!

ፊደል የቆጠሩ ወገኖቻችን፣ አፍ ከፈቱበት አማርኛ ወይም ኦሮምኛ ወይም ትግርኛ ይልቅ እንግሊዝኛ ማሰባጠር የሰነበተ ልማድ መሆኑ ለምን ይሆን? እንዲያውም፣ በስድሳዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን፣ ለመሪነት የሚታጩ፣ በከባድ ቃላት እንግሊዝኛ ዲስኵር ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር። የአገራችን መሪዎችና ልሂቃን ከእንግሊዝኛ ይልቅ አፋርኛ ወይም ሲዳምኛ የሚያሰባጥሩት መቸ ይሆን?

አማርኛ መናገርን ብቸኛ ቅዱስ ተግባር የሚያስመስሉ ነበሩ። አንዳንዶች፣ ሳድስና ሳልስ አልሆን ያለውን ሁሉና የጽሑፍ ባህል የሌለውን የሚያንኳስሱ ናቸው። አውሮጳውያን፣ የጽሑፍ ባህል የሌላቸው አፍሪካውያንን አናሳ እንደ ሆኑ ሲያስቡና ሲያሳስቡ ኖረዋል። እኛም መሓል ይኸ አመለካከት አይጠፋም። የጽሑፍ ባህል በመሠረቱ በአፍ ከመቀባበል የቀጠለ እንጂ በአፍ መቀባበልን የሻረ አይደለም። ዘረኛ አውሮጳውያን፣ እስከ ቅርብ ዘመናት፣ የማኅደረ ትውስታን ኃይል ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ ኖረዋል። እነዚሁ፣ በጽሑፍ ያልሠፈረ አይታመንም ብለውናል። ጽሑፍ፣ ትልቅ ታሪካዊ እመርታ መሆኑ አይካድም። ጽሑፍ አያስፈልግም ማለት አይሁንብንና፣ በ “ትረምፕ ትዊትና ፌስቡክ” ዘመን፣ መርሳትና መዘባረቅ በሽበሽ በሆነበት፣ በጽሑፍ የሠፈረ ይታመናል ማለት መሞኘት ነው! በአንጻሩ፣ ባለቅኔ ሰሎሞን ዴሬሳ የትውልድ ሐረጉን እስከ 40 መቍጠር ይችል እንደ ነበር በዜና እረፍቱ ላይ ተጠቅሶ አንብቤአለሁ። የኦሮሞን የአማራን ወይም የትግራይን ዜና መዋዕል ሽንጡን ገትሮ ከሚሞግተው አብዛኛው አንብቦ ወይም አመሳክሮ ሳይሆን ከአያቶቹ አፍ ሰምቶና እንደየሁናቴው ጨማምሮበት ነው፤ እግረ መንገዱን፣ ቴዎድሮስን ዮሐንስን ምኒልክን ኃይለሥላሴን እያነሳና እየጣለ፣ አፋቸው ውስጥ ምኞትና ሙግቱን ይጨምራል። አማርኛና/ትግርኛ አፍ መፍቻ ከሆናቸው “ባለፊደላት” ባመዛኙ፣ ማንበብና መጻፍ እንኳ የማይችሉ ናቸው። የቻሉ ጥቂቶች፣ ደርግ ዘመኑ አልፏልና ነው እንጂ “እድሜ ለደርግ!” ቢሉ ጭቦ አይሆንባቸውም!

በአገራችንና በመሰል አገሮች፣ ሁለትና ሦስት ቋንቋ መናገር ድንቅ አይደለም። ስለሆነም፣ የጎረቤትን ቋንቋ አለመማር በሰዎች መሓል ሊኖር የሚገባን ትሥሥር ማጨናገፍ ነው፤ ውጤቱም ሥጋትን ዘርቶ ፍርሓትን ማጨድ ነው። ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ከአማርኛና ከኦሮምኛ በተጨማሪ በትግርኛ እንደሚግባቡ እየተወራ ነው፤ ከመቶ እጅ ቢያንስ ሰማንያውን የአገራችንን ህዝብ መግባቢያ ያውቃሉ ማለት ነው። ይኸ ሌላው ቢቀር፣ ለአመራራቸው በጎ ተጽዕኖ አይፈጥርም ማለት የቋንቋን ማህበራዊ ሚና አለማጤን ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በረጅም ዘመን ታሪኩ፣ የሚበታትን ብዙ ሁኔታ ገጥሞታል፤ አብሮነቱ ግን ዛሬም እንኳ አልጠፋም። አብሮነቱ የደፈረሰ ሲመስል፣ ተመልሶ የመጥራት ኃይል በውስጡ ቋጥሯል። የደፈረሰ ደግሞ እንዲጠራ፣ አለማባባስና ትእግስት ይጠይቃል። በአገራችን የታየው፣ በሶማሌ ምድር የሌለ እውነታ ነው፤ በሱዳንም የለም፤ በሶርያ የለም፤ በዩጎዝላቭያ አልነበረም፤ ወዘተ። ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ በኋላ እንደ ዩጎዝላቭያ ብትንትኗ ይወጣል ተብሎ ነበር፤ ተበላላን እንጂ አገራችን አልተበታተነችም። ከሊቀመንበር መንግሥቱ በኋላማ ይባሱን መንግሥት ፈርሶ አልተበታተነችም። ከጠ/ሚ መለስ ሞት በኋላም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “ዋ! እንደ ሶርያ፣ ዋ! እንደ ሩዋንዳ፣ እንደ ኢራቅ” እየተባልን ነው፤ የሚገርመው፣ ይህን የሚሉን የአገር መሪዎች መሆናቸው ነው!

የአገራችን ኤኮኖሚ እያደገ መምጣቱ ከዚህ ቀደም ያልታየ ትልቅ የአመለካከት ለውጥ እያስከተለ ነው፤ ለኤኮኖሚ ተሳትፎ የኦሮምኛ አስፈላጊነት እየጨመረ መጥቷል። አማርኛ ለፖለቲካ ተሳትፎ ምን ያህል እንደጠቀመ ኦቦ ጃዋርና ኦቦ ሌንጮ በጠራ አማርኛቸው እያስመሰከሩ ነው። ኦቦ ሌንጮ በአንድ ብሔራዊ ስብሰባ ላይ በአስተርጓሚ እንጂ በአማርኛ አልናገርም ያሉት ናቸው። ዛሬ ደግሞ፣ ሰው ቃሌን ከሚያጣምምብኝ እኔው ላስረዳ ማለታቸው ትልቅ ማስተዋል ነው። መግባባት ምንጊዜም ካለመግባባት ይሻላላ! ውጭ አገር የፈሰሰው ዜጋ ዐረብኛውን ቻይንኛውን ስዋሂሊኛውን የሚያንበለብለው ኑሮውን አሸንፎ ለወገኖቹ ለመትረፍ ነው። ትግርኛ እንጂ ቢል ጦሙን ያድራታል!

ብዙ መግባባት ብዙ ያበለጽጋል። ሆላንዶች ከአውሮጳ በሕዝብ ቍጥርና በመሬት ቆዳ ስፋት አናሳ መሆናቸውን ስለተገነዘቡ፣ እንግሊዝኛን ሁለተኛ ቋንቋ አድርገው ድንበራቸውን ዓለም ዳርቻ አድርሰውታል። ቻይና፣ ከአገሯ ስፋትና ከህዝቦቿ ብዛት የተነሳ ማንደሪንን ዋነኛ መግባቢያ አድርጋለች። ለህንድ፣ ሂንዲና እንግሊዝኛ ዋነኛ ሲሆኑ፣ ሌሎች 14 ቋንቋዎች ለየአካባቢው መግባቢያ እውቅና ተሰጥቶአቸዋል። ህንድም ቻይናም የኢትዮጵያን ህዝብ 13 እጅ ያጥፋሉ። ደቡብ አፍሪካ፣ እንግሊዝኛ ዋነኛ ሆኖ ለ11 ቋንቋዎች እውቅና ሰጥታለች። ኃያሏ አሜሪካ እንግሊዝኛን ብቸኛ መግባቢያ ማድረጓ ከወጪ አንጻር ብቻ ሳይሆን፣ ህልውናዋ በማያቋርጥ ፍልሰት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ህዝቦቿን ለማዋሃድ ጭምር ነው። በሁሉም አገራት ቀዳሚ የተደረገው የኢኰኖሚና ማህበራዊ እሴቶችን አለማባከንና ሉዓላዊነትን ጠብቆ አብሮ ማደግ ነው። አገራችን እንደ የትኛው ታድርግ? ምናልባት ጥያቄዬን ማሻሻል ይኖርብኛል፤ ከውስጥ ለመጠናከርና ዘመን አመጣሽ ጫና ለመሞገት የሚመጥነው አሠራር የቱ ነው?

ቋንቋ በወዳጅ ያበለጽጋል። ከያይነቱ ወዳጅ እንዳይኖረው የሚሻ፣ አንድ ዐይና መሆን የማይገደው ብቻ ነው! እስቲ ዙሪያችንን እንቃኝ፤ የወዳጆቻችን ዓይነት ምን ይመስላል? የክልል ስሜት ስንቶቻችንን ከኖረ ወዳጅ አቆራርጦናል? መግባባት እንደሚያበለጽግ ከተጠራጠርን ቍልቢ ገብርኤል፣ ካምቦሎጆና መርካቶ እንውረድ። አማርኛ ተናጋሪ፣ ኦሮምኛ እየሰባበረ ቢናገር በሰሚው ላይ የሚያስከትለውን በጎ ስሜት እናስብ። ፈረንሳዮች እና አሜሪካኖች በቋንቋቸው ለመነጋገር የሚሞክረውን ምን ያህል ለመረዳትና ለመርዳት እንደሚፈቅዱ ብዙዎቻችን አስተውለናል። ጀርመኖች፣ ጃፓኖች፣ እንግሊዞች፣ ካናዶች፣ ሩሲያዎች ለምን እኛ የናቅነውን ቋንቋችንን እንቅልፍ አጥተው ይማሩታል? የሌላውን ቋንቋ መማር፣ ያለአስተርጓሚ በቀጥታ ለመግባባት፣ የህዝቦችን ስነ ልቡና ለመበርበር፣ ለመዋዋልና ልምድ ለመዋዋስ፣ ተጽዕኖ ለማሳደር ጭምር እንደሚያበቃ ስለ ገባቸው ነው። ዲሞክራሲ ምድራችን ላይ እንዲበቅል ብንታገል፣ የህዝብ ተወካይነት በጎሳ መሆኑ ያበቃና በብቃት ይሆናል፤ ተወካይ ለመመረጥ ሲል የአካባቢውን ቋንቋ ሳይወድ ይማራታል። ኦሮሞ የኦሮሞ ብቻ፣ አማራ የአማራ ብቻ ህዝብ ተወካይ መደረጉ አገራዊነትን ያላማከለ የፖለቲካ ስህተት ነው።

ጋዜጠኛና አታሚ አብርሃ በላይ ስለ ሐረር ጕዞ ገጠመኙ ያሠፈረውን፣ ቢፈቀድልኝ እዚህ ልጥቀስ፦

“‘ሹፌሩ አካባቢ ጨዋታው ደርቷል። ሹፌሩን ከበው የሚያወሩ መንገደኞች ዘና ብለው በኦሮምኛ ያወራሉ። ድንገት ደግሞ በሳቅ ኋ! ብለው ይፈነዳሉ። አንዴ እንደ እሳተ ጎመራ ሲፈነዱ፣ ከኔ ጋር ያለው ዘመዴ ሶማልኛ፣ ትግርኛ እና ኢንግሊዝኛ አሳምሮ የሚያውቅ፣ በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ በአማራነቱ ራሱን ፈጽሞ ገልጾ የማያውቅ አፋን ኦሮምኛን እንደእናቱ ቋንቋ የሚናገር ሰው ነው። በሰዎቹ ቀልድ ግራ የተጋባሁት ኦሮምኛ የማላውቀው እኔ ብቻ ነኝ። እና ... ‘ምን እንዳሉ አውቀሃል?’ አለኝ። በመገረም ፈገግ ብሎ! ‘ኧረ አልገባኝም! ምን ተገኝቶ ነው እንዲህ የሳቁት?’ አልኩት”

ተሳፋሪ በሳቅ ሲፈነዳ፣ አብርሃ ብቻውን መቅረቱ እንዳላስደሰተው ግልጽ ነው። ደግነቱ፣ ዘመዱ ደረሰለት። “‘ምን እንዳሉ አውቀሃል?’ ‘ኧረ አልገባኝም! ምን ተገኝቶ ነው እንዲህ የሳቁት?’ አልኩት …”

ከዚያች ቀን ወዲህ አብርሃ አንድ ሁለት ኦሮምኛ ቃል በመማር ቍጭቱን ተወጥቷል ብዬ እገምታለሁ!

* * *

አፄዎቻችን ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ምንሊክና ኃይለሥላሴ ከነበረባቸው ባዕድ ከበባ አገሪቱን ለመታደግ፣ የሚገዙትን ህዝብ ለማስተሳሰር የቋንቋን ተግባርና ኃይል ተገንዝበው ነበር። እንዲያውም፣ የዘመናዊ ትምህርት ዋነኛ ትኲረቱ የባእድ ቋንቋ መማር ነበር። ቴዎድሮስ በዐረብኛ ይነጋገሩ ነበር። ኃይለሥላሴ በፈረንሳይኛ። ፋሺስት ጣልያን አገራችንን በቋንቋና በጎሳ ለመከፋፈል የሞከረበት ምክንያቱ ግልጽ ስለሆነ አልደግመውም። ጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ ሥልጣን ሲረክቡ በንግግራቸው ውስጥ እንዳስረዱን፣ መያያዛችን ቅድሚያ ሳይሰጠው ከገባንበት ማጥ መውጣት አንችልም። በዚህ ረገድ ሚንስትሩ የተጠቀሙትን ተስፋ ሰጭ ቋንቋ መጥቀስ ያሻል። ለምሳሌ፣ “ተቃዋሚ” የሚለውን “ተፎካካሪ” ብለውታል። “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያዊ”ን 39 ጊዜ፤ “አገራችን”ን 27 ጊዜ ደጋግመውታል። ቃል ብቻ ምን ያደርጋል ብንል እንስታለን፤ ድርጊትና ባህርይን ለመለወጥ ቃል ወሳኝ ነውና። “ዲያስፖራ” “ሽብርተኛ” “ኦሮሞ” “ነፍጠኛ” “አንድ ለአምስት” “አማራ” “ወያኔ” “ስደተኛ” “ተቃዋሚ” “ጠባብ” “ትምክህተኛ” “ኪራይ ሰብሳቢ” ወዘተ፣ እየተባባልን የጋራችን በሆነች አገር እንደ ባእድ ስንተያይ ቆይተናል። ይህ መቆም አለበት።

ከደርግ በኋላ፣ ዘመኑ የመካለልና የመካረር ሆነና ኦሮምኛ ከፊደል ወደ ላቲን ተሻገረ። መነሻ አሳቡ፣ ማህበራዊነትን ያላገናዘበ፣ ፍትህ የሚሻ ፖለቲካዊ ብሶት ነበር፤ ከ “ቅኝ አገዛዝ” መላቀቅ ነበር። ከህዝብ ያልተሰጠውን ሥልጣን በግርግር ባቋራጭ መያዝ ነበር። አልተሳካም ብለን በትዝብት እንለፈው? ፖለቲካዊ ብቻ አመለካከት ስለ ነበረ፣ በአብዛኛው የወቅቱን የመከፋፈል ፖለቲካ አባባሰው፤ ድርጊቱ የኦሮሞ መሪዎች ብቻ ውሳኔ እንዳልነበረ አንርሳ።

ከስድሳ ስድስቱ አብዮት ዛሬም የተማርን አይመስልም። የ19ኝኛውን ክፍለ ዘመን መሓል-ጠርዝ፣ ጨቋኝ-ተጨቋኝ አመለካከትና የግለሰቦችን ምሬት በአገር ደረጃ ማጋነን ዛሬም አላቆምንም። አንርሳ፦ “ጨፍልቀው!” “ወይ ጠላት ወይ ወዳጅ” አስተሳሰብ ጀንበሩ ባትጠልቅም መሽቶበታል። ትውልዱ ወጣት ነው። ዘመኑ እምብርተ-ብዙ ሆኖ፣ “ቆመህ ጠብቀኝ” የማይባልበት፣ ፈጥኖ የሚፈራረቅ፣ ዓላማን ለይቶ ማወቅን እና የአመለካከት ስፋትና ፈጣን ውሳኔን የሚጠይቅ ነው። ይህን ያላስተዋሉ፣ የራሳቸውንና ወከልነው የሚሉትን ህዝብ ሕይወትና ቅርስ በማባከን የተሠማሩ ናቸው።

በሰማንያ ሦስትና ቀጥሎ፣ የታሪክና የቋንቋ ሳይንስ እውቀት ያለውም የሌለውም እኵል ማውራት ጀመረ። አብዝተው የጮኹ በረቱ። አንዳንዶች፣ ስለ ወጪውና ስለ አንድነታችን ስንል ወደ ፊደል እንመለስ አሉ። ሌሎች፣ በቁቤ እንጂ ወደ ፊደል ምን ተደርጎ አሉ። ሰዎች ስንባል፣ የሚያረጋጋ መሪና የሚያስተማምን አማራጭ ሳይገኝ የያዘነውን አንለቅም። ይኸ ለምን ይደንቃል?

ታዲያ ምን አማራጭ አለ? ቁቤን ሁለተኛ ብሔራዊ/ፌደራል ቋንቋ ማድረግ፣ “ወጋጎዳ” በትንሹ እንደ ጠቆመን ጥንቃቄ ይሻል፤ ማህበራዊ ትርምስ እንዳይፈጠር፣ በቅድሚያ ቅንና የኢትዮጵያን ደህንነት የሚያስቀድሙ መሪዎች ሊነሱ ይገባል። ኦሮምኛ ሁለተኛ ብሔራዊ/ፌደራል ቋንቋ መደረጉን በመሠረቱ እቀበላለሁ። የኔ ችግር አፈጻጸም ላይ ነው። ኦሮምኛ ብሔራዊ ቋንቋ ይደረግ ካልን፣ ቅድመ ዝግጅቱ ምን መልክ ይኑረው? ህዝቡን እንዴት ማግባባት ወይም ማስገደድ ይቻላል? ከ105 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወይም እንግሊዝኛ ማንበብና መጻፍ የሚችለው ምን ያህሉ ነው? አማርኛ ብቻ ተናጋሪ ኦሮሞዎች ቁጥራቸው ምን ያህል ነው? ኦሮምኛ ብቻ ተናጋሪ አማሮችስ? ኦሮምኛና አማርኛ ተናጋሪዎችስ? ማንበብ መጻፍ የማይችሉትን ለማስተማር የሰውና የገንዘብ ኃይል ከየት ይመጣል? ይኸስ በህዝቦች ስብጥር አሠፋፈር ላይ ምን በጎ ያልሆነ ውጤት ያስከትላል?

ማህበራዊ ክፍተቶችን ለመድፈን ከቍቤ በተጨማሪ ኦሮምኛ በፊደል ቢጻፍስ? ኦሮምኛን በፊደል ለመማርና ለመጻፍ ህግ እስኪወጣ መጠበቅ አያስፈልግም! አማርኛን በ(ላቲን) እንግሊዝኛ በየፌስቡኩና ዩቱቡ እየቸከቸክን አይደል?! በሁለተኛ ደረጃና በዩኒቨርሲቲ ኦሮምኛ ለመናገርና ለመጻፍ የሚያበቁ ኮርሶችን መውሰድ ግዴታ ቢደረግስ? የኦሮምያ ክልል ስኮላርሺፕ በመስጠት ወጣቱን ቢያበረታታስ? በነገራችን ላይ፣ ላቲን ከፊደል ይልቅ ኦሮምኛን ያነጋግራል የሚለው አባባል ባብዛኛው የሥልጣን ፖለቲካ እንጂ የቋንቋን ማህበራዊ ጠቀሜታ የተከተለ አይደለም።

ይህ ሁሉ በተግባር ሲተረጎም፣ እንደ ፈራነውና እንደ ጠበቅነው ይሆናል ማለት አይደለም። መሪዎች የግል ዓላማቸውን ወደ ጎን አድርገው፣ የህዝቡን የመረዳት አቅምና ጥያቄውን ማስቀደም ይኖርባቸዋል። የአሠራር ለውጥ ምንጊዜም ጅማሬ ላይ ግር ማለቱ አዲስ አይደለም፤ ተግቶ በማስፈጸም ይለመድና መደበኛ ይሆናል እንጂ። አገር በክልል ሲዋቀር፣ አገራችን መፈራረሷ ነው ያላልን ስንቶች ነን? አገራችን ግን አልፈረሰችም። ሚካኤል ጠብቋት ነው እንጂ ልትፈርስ ነበር ማለት ይልቅ ያምራል! “ክልል” ያልነበረን ነገር አላመጣም! እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ጊቤ፣ ሸዋ፣ ወላይታ፣ ጂማ፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ትግራይ፣ ወዘተ፣ እያልን በየክልላችን እንደ ኖርን አንርሳ። ዛሬ አለንበት ላይ መድረሳችን እንዲያውም ሊያኮራን ይገባል! በካርታ ላይ ከታየው ለውጥ ውጭ፣ የሕዝቦች አሠፋፈር ከቴዎድሮስ ጀምሮ ምን ጉልህ ለውጥ አሳይቷል? ችግራችን፣ በቂ መረጃ ከማጣት የመነጨ ፍርኃትና ሥጋት ነበር፣ ነው፤ ለሥልጣን ሲሉ ከውስጥና ከውጭ ይህን የሚያራግቡ መኖራቸው ነበር፣ ነው። መፍትሔው ደግሞ ዝግ ብሎ መመካከር ነው። ያለውን እውነታ መገንዘብ ነው። ቍቤ የአንድ ትውልድ መግባቢያ ከሆነ ሰነበተ። ወደ ኋላ መመለስ፣ ጊዜ ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ቅሬታን ማባባስ ነው። ለዚህም ነው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኦሮምኛን ለማስተማር የተተለመው፣ በሌሎች ክልሎችም አማርኛን በማስተማር ሊጎለብት የሚገባው።

ከምንሰማውና ከምናየው አብዛኛው፣ የጥቂቶችን እንጂ የብዙኃኑን ድምጽ አይወክልም። በአገራችን የምናየው ውጥንቅጥ በአብዛኛው በመሪዎችና በተቀናቃኞቻቸው መሓል እንጂ በሰፊው ህዝብ መሓል እንዳልሆነ አንርሳ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማርኛ/ኦሮምኛ ተናጋሪ ትውልደ ኦሮሞ/አማሮች እንዳሉ አንርሳ። ጥቂት ያይደሉ ኦሮሞ ወገኖቻችን የአናሲሞስን ትርጕም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጠቀሙ አንርሳ። ከኦሮሞና ከአማራ የተወለዱ ወገኖች ቍጥር የአደባባይ ምሥጢርና የመተሳሰራችን ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ አንርሳ። የጠራ ኦሮሞ፣ የጠራ አማራና ትግሬ፣ ወላይታ፣ ወዘተ ብሎ የለም። “ንጹህ” ኦሮሞ አማራ አኝዋ ጉራጌ ብሎ የለም፤ በኢትዮጵያ ቀርቶ በየትም አገር የለም። በኢትዮጵያ ቀርቶ በየትም አገር የለም። ቢኖር እውነቱን በማያውቁና ሌላ ዓላማ ባላቸው ሰዎች ልቡና ውስጥ ብቻ ነው። ከትግራይ እስከ ሞያሌ፣ ከጋምቤላ እስከ ጅግጅጋ የኦሮሞ ቋንቋና ባህል አሻራ ያልተወበት የአገራችን ክፍል የለም። ሕይወትና ታሪክ፣ ከሞላ ጎደል፣ በመዋዋስ፣ በመዳቀልና በመቀባበል ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ በዓለም ሁሉ ነው።

አገር በመከፋፈል፣ በወኔ ብቻና በምሬት አትገነባም። ዝግ ብሎ መመካከር የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። ለምሳሌ፣ አገራችን ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገርባት ምድር እንደ ሆነች ደጋግመን እንሰማለን። ይህንኑ፣ የአራት ቤተሰብ ቋንቋዎች ምድር ነች ብሎ መግለጽ ይቻል ነበር፤ ሴማዊ (አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጉራግኛ፣ ሐረሪ፣ ወዘተ)፤ ኩሻዊ (ኦሮምኛ፣ ሶማልኛ፣ ሲዳምኛ፣ አፋርኛ፣ ወዘተ)፤ ኦሞአዊ፤ እና ናይሎቲክ። ሴማዊ፣ ኩሻዊ፣ ኦሞአዊ አፍሮ-ኤዥያቲክ ናቸው። ሁለቱም አባባሎች እውነት ቢሆኑም፣ የመጀመሪያው ልዩነታችንን በማጉላት ለፖለቲካ ፍጆታ ውሏል። ሁለተኛው ደግሞ በቋንቋ ቤተሰብ አድርጎ ያስተሳስረናል። ሁለቱም አመለካከቶች የሚያሳድሩት ተጽእኖ ቀላል አይደለም። አመራር መስጠት የነበረበት መንግሥት የቋንቋን ነገር በእንጥልጥል የተወበት የራሱ ምክንያት ቢኖረውም፣ ውሳኔው አድሮ ካስከተለው አጥፊ ውጤት ራሱንና አገሪቱን ሊያድን አልቻለም። ስለ ሁሉ ነገር የመንግሥት እጅ ማየት ደግሞ አግባብ አይደለም። የትኛውም መሪ፣ ህዝብ እርስበርሱ እንዳያወራ የማድረግ አቅም የለውም። ሾፌሩን ከብበን እያወጋን ለመሳሳቅ እኛም ወግ ይድረሰን!

አዲሱ ትውልድ አብዝቶ የሚያውቀው የተገኘበት ዘመን ያቀበለውን ነው፤ በጎሪጥ አንየው። ዛሬ የቸገረ፣ በስፋት አለማየት፣ የምንሰማውን አለማጣራትና ነገሮችን የማክረር አባዜ ነው። የአንዳንዶቻችን ሙግት፣ የዛሬ መቶና ሁለት መቶ ዓመት የተያያዝነው ቂም ለምን ይረሳ የምንል መስሏል! የተጋቡ ቢኳረፉ ለምን ይደንቃል? እርግጥ ባይኳረፉ ይመረጣል። ኩርፊያ አብሮ የመኖር አንዱ መገለጫው ነው። አብሮ መኖር ደግሞ ለራስ ጭምር ነው። እንዲበጀን፣ በፍትኃዊ የኤኮኖሚ ትስስር ላይ እናተኩር። ሆዳችን ሞልቶ ብንኳረፍ ባይሆን ያምራል። ይኸው ሳናስበው የኢትዮጵያን ችግር ፈታን!

ሁለት አሳቦችን በአንድነት እንያዝ። መጀመሪያ፣ እንዴት ከውስጥ እንጠናከር? ከውስጥ ሳንጠናከር ወራሪ አሳቦችን መቋቋም አንችልማ። አጀማመሩ መልካም ቢሆንም፣ የክልል ፖለቲካ ሰለባ የሆነውን የትምህርት ዘርፍ፣ ለአገር በሚቆረቆሩ፣ ቅንነትና ሰፊ እውቀትና ልምድ ባላቸው ዜጎች ማጠናከር፣ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፤ ሀ/ ጥራት ከጎደላቸው ሠላሳ ዩኒቨርሲቲዎች ይልቅ፣ ሃያዎቹን ማጠናከር የዩኒቨርሲቲዎችን የማያያዝ ማህበራዊ ተልዕኮ ያሳካል፤ ቅርስን ለዘላቂ ተግባር ያውላል ለ/ በየክልሉና በግል የትምህርት ተቋማት ሲጠቀም የቆየውን፣ በተለይ የታሪክ መማሪያ መጽሐፎችን መመርመር ግድ ይላል። ሁለተኛ፣ የልጆቻችንን ተስፋ እህል በማይሆን እልህ እንዳናጨልም ምን እናድርግ? ቆሞ የማይጠብቅ ጊዜን በሚገባ አለመጠቀም በህጻናትና በአዛውንት ሕይወት መቀለድ ነው።

በዘመነ ቴክኖሎጂ፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ዙሪያ፣ ወጣቱ የቋንቋና ቀለም ድንበር የማይገታው ግንኙነት ፈጥሯል። ስደት ከተንሸዋረረ አመለካከትና ከመንደርተኛነት አላቅቆ ታታሪ አድርጎታል። አገሩን ከምንጊዜውም ይበልጥ አስወድዶታል። የእግር ኳስ ቡድናችን ደቡብ አፍሪካ እና ሯጮቻችን ኑዮርክና ለንደን ላይ ሲሳተፉ የአገሩን ባንዲራ እያውለበለበ “ጥሩ ጥሩ ደራርቱ ደራርቱ ሳላዲን መብራቱ” የሚለው ማን ሆነና ነው? መልከ ብዙና ያልረጋ ሂደት፣ መልከ ብዙ ዝግጅት፣ የልብ ስፋትና ተሳትፎ ይጠይቃል። ቋንቋ መግባቢያና መከባበርያ ነው።

ምትኩ አዲሱ

ግንቦት 15/2010 ዓ.ም.

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave