መሪ አገልጋይ - አገልጋይ መሪ

በጎዳና ጎግያጎ

ስለ መሪ ብዙ ተብሏል። ለመናገርም ሆነ ለመጻፍ የሚመች ርዕስ ነው። በዚያው ልክ በየጎራው የ’መሪ ያለህ’ጩኸት መበራከቱ መናገርም ሆነ መጻፍ ቢቀርስ ያስብላል። ወንድሞቼ እኔንም ከጩኸቱ ጎራ እንድቀላቀል ስለገፋፉኝ አንድ ብያለሁ። ያገልጋይ መሪ ያለህ!

ይሁን እንጅ ብዙ በተባለበት ጊዜ ላለማጥፋት፥ ለጅምር ያህል አንዲህ ልበልና እምብዛም ትኩረት ወዳልተሰጠባቸው ጉዳዮች ላምራ። ካነበብኩትና ከሰማሁት አንጻር ስለመሪዎቻችን ድካም አንስቶ ማላዘን የጩኸቱ እምብርት ሆኗል። ከቶ ራሱን ስንኳ በቅጡ ያልመራ ተነስቶ በህዝባቸው፣ ባምላካቸውና በሌሎችም ፊት ጥቂት በጎቻቸውን ለማገድ የሚፍጨረጨሩትን ሲሳለቅባቸው ተመልክተናል። መሪነት ሲባል መሪዎችና ተከታዮች ያሉበት የጨዋታ ሜዳ መሆኑን የዘነጋን ይመስላል። መልካም መሪ እንደሚፈለግ ሁሉ፥ ጥሩ ተከታይም ያሻናልና ቸል መባሉ አያዛልቀንም። መሪዎች ዘንድ ድካም የለም ለማለት አይደለም። የመሪነት ልምድና ፀጋ ያየንባቸው ሌሎች ሲያድጉ ከተገኙ ወዮላችሁ የተባሉ ይመስል አርጩሜ አይሉት ዘነዘና በታዳጊዎቻቸው ላይ ሲያነሱ ለነገ የማይሉ እንዳሉም አይተናልና። የርስ በርስ ሽኩቻ ማሳደድና መመከት የመሪ አገልጋዮቻችን የዕለት ተዕለት ቀዳሚ ሥራ ሆኖባቸው አቅም አሳጣን። ይህም ከሁሉ የባሰ አባዜ ነው። እኔና መሰል ተናጋሪና ፀሀፊዎችም መሪ ማለት የፍጹምነት ቁንጮ፣ የብቃት ጣሪያ፣ የጥበብ ምንጭ፣ የቅድስና ድምድማት አድርገን በማቅረብ ቢያንስ የዱላ አቀባይነትን ልዕልና ተጎናጽፈናል። ይህን በመመልከት መሪው እንደተባለው ሳይሆን ሲቀር የጎበዝ አለቃ እያደራጀ ልምራ ከማለት አልፎ መሪውን ለመውገር ወንጭፍ ያነሳ በግም አለና። በመካከል ህዝብ ተጎዳ፣ ራዕይ ተመሳቀለ። ከቤተሰብ ጀምሮ በቤተክርስቲያንም ሆነ በህዝብ አስተዳደር እስከ ከፍተኛው የስልጣን እርከን ድረስ የመሪ ክምችት ሳሳ።

እግዚአብሄር ይቅር ይበለን። ይህም አያዛልቀንምና። አንዲያውም በዚህ ወዳጅ ከጠላት ተለይቶ በማይታወቅበት የተሳከረ ዘመን ቤተክርስቲያን፣ ህዝብና ሀገር የመሪ ድርቅ እንዳያጋጥማት ልንሰጋ ይገባል። ያውም እስካሁን ሰላም ከሆነ። ለነገሩ ይህን ሃሳብ ያካፈልኩት አንድ ወዳጄ፣ የግርግሩ መንስዔ የመሪ ድርቅ ስለመታን ሳይሆን የመሪ መበራከት ስላጋጠመን ነው ሲል ከደቡብ ኢትዮጵያ የሰማውን አንድ የድሮ ዘመን ምሳሌ ነገረኝ። የትርምሱ አካል ነውና ላካፍል።

በቀድሞ ዘመን ብዙ ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ የወለዱ ሃብታም አባት የመሞቻ ቀናቸው ስለተቃረበ ልጆቻቸውን በመጥራት ክሞትኩ በኋላ በሃብት ክፍፍል እንዳትጣሉ ዛሬ በኔ ፊት ተካፈሉ አሏቸው። ልጆቹም እንዳገሩ ልማድ፣ ለሁሉ እንደ ዕድሜውና እንደተስማሙበት ሲካፈሉ፥ አባት በኩር ለሆነችውና አግብታ በቤትዋ ላለች ሴት ልጃቸው የተሰጠ ድርሻ እጅግ ስላነሰባቸው፥ ልጆቻቸውን ተቆጥተው እንዲጨምሩላት አዘዙ። በብዙ ውትወታ ጥቂት ቢቆነጥሩላትም አባት አልረኩም። ይሁን እንጂ ወንዶች ልጆቻቸውን ላለማሳዘን ከልመና ያለፈ ነገር አላደረጉም። በመጨረሻም ሴት ልጃቸውን፥ በይ ወንድሞችሽን የዕድሜ ታናሾችሽም ስለሆኑ ስላካፈሉሽ ድርሻ በልብሽ እንደተሰማሽ አመስግነሻቸው ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ ይሏታል። እርሷም ወንድሞችዋን ጠርታ፥ ወንድሞቼ ‘ከቤታችሁ የወይፈን መንጋ፣ ከጓሮና ደጃችሁም የለመለመ ሣር አይታጣ’ ብላ መርቃቸው፣ የያዘችውን ይዛ ሄደች። አባትም ምን ብላ እንደመረቀች ሊሰሙ ጓግተው ልጆቹን ሲጠይቁ በሰሙት ነገር ተደናግጠው ባስቸኳይ እንዲያስጠሯትና ምርቃቱን እስክታስተካክል ድረስ ተጨማሪ እንዲሰጧት የግድ ይሏቸዋል። ከመንገድ መልሰዋት፣ ብዙ ተጨማሪ ድርሻ ከሰጧት በኋላ ግን ‘ወንድሞቼ፣ የተገባኝን አግኝቻለሁ፥ እቤታችሁ አንድ ወይፈን ይገኝ፥ ጓሮና ደጃችሁም የሣር እጦት ያጋጥመው’ ብላ መርቃ ሄደች። ልጆቹም በሆነው ሁሉ እጅግ አዝነው፥ አባታቸውን ድርሻችንንም፣ መልካሙን ምርቃታችንንም አስወሰድክብን አሉት። አባትም፣ የ’ሣር መበራከት’ የከብቶች አለመኖር ውጤት፥ የ’ወይፈን መንጋጋትም’ የሥርዐት አልበኝነት፣ የልምድ ማጣት፣ የማን አለብኝነትና የተፈታ ቤት ምልክት እንደሆነ አስረዷቸው።

እንግዲህ ዘመናችን ወደየትኛው ምርቃት እያዘመመ ይሁን? ግርግሩ አንቱ የተባለ መሪ አጥተን ወይፈን ስለፈላብን ወይስ ከነአካቴው የመሪ ድርቅ? ትርምሱን የማረጋጋት ተልዕኮ ልሸከመው አልችልምና አንባቢ በዚህ ረገድ አይጠይቀኝ። ያላዋቂ ሳሚ መሆን ስለማልፈልግ። ‘እሸከመዋለሁ’ ባይ ግለሰብ ከተገኘም ‘ወራጅ አለ’ ከሚሉ ወገን ነኝ። በጋራና ከጌታ ጋር ግን፣ በፀሎትና እግዚአብሄርን በመፍራት ከዚህ የከፋውንም ምድረ በዳ እንሻገረዋለን። እንግዲህ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ መሪ አገልጋይ (ወይንም አገልጋይ መሪ) ለመሆን ፍላጎት ላላቸው መነሻ ሃሳብ ከመስጠት ያለፈ አይደለም። ለዚያውም ብዙ አዲስ ሃሳብ የለበትም። ትኩረት የተነፈጉ ጥቂት ነገሮች ያሉ ስለመሰለኝ እንጂ።

መሪነት ምንድነው?

መሪነትና ሥልጣን እጅግ የተቆራኙ ከመሆናቸው የተነሣ ለያይቶ ማየት አስቸጋሪ ነው። ሥልጣን ደግሞ አንድን ነገር የማግኘት፣ የማድረግና የማስፈፀም መብት ወይም ፈቃድ ስለሆነና፥ ባንዳንድ መልኩ ይህ ፈቃድ ሃይልንም ስለሚያካትት፥ መሪነትን የፈላጭ ቆራጭነት እርካብ አድርጎ መውሰድ ተለምዷል። ሥልጣን ግን አማላይ ጽዋ ናት። አያሌ ሰዎች የሚከጅሏት፤ ግን የተደባለቀች፥ ድፍርስ ጽዋ። እጅግ ጣፋጭ፣ እጅግም መራራ የተቀላቀለባት! አጥብቀው የሚሿትን ከባድ ዋጋ ታስከፍላለች። ይህን ያላወቀ ያልቀመሰ ብቻ ነው። ሁሉ ይራኮቱባታል፥ የቀመሰም፣ ያልቀመሰም። እንዲያውም በቀመሰው ባይብስ? ላገኟት፥ ሥልጣን ደመወዟ ከፍተኛ ነው። መሪነትም እንዲሁ። ዋጋ ታስከፍላለች፣ ታስከብራለችም። ሁለቱ ግን አንድ ተደርገው መወሰድ የለባቸውም። መሪነት በጣም የላቀ የህዝብ አገልጋይነት ደረጃ ሲሆን፥ ተገልጋዮች በረኩበት መጠን ቀኛቸውን የመስጠት፥ መሪው በበኩሉ ባገኘው ክብር፣ ሥልጣንና ፍቅር መጠን ይበልጥ ለማገልገል መሃላ የሚያደርግበት፥ እርስ በርስ፣ አንዱ ለሁሉ፣ ሁሉ ላንዱ የመገዛዛት ፉክክር ነው። የተሳካ መሪነት መሪውንም ሆነ ተመሪውን በጎ ለውጥ ያጎናጽፋል።

እውነተኛ መሪ በሰውም፣ በእግዚአብሄርም ፊት የተመሰገነና የተከበረ ነው። ሥልጣን ስላለው ብቻ ግን ለዚህ ዓይነት ክብር ላይታጭ ይችላል። የሥልጣን መኖር ብቻውን መሪነትን አያመለክትም። ለምሳሌ አንድ የሥራ ሂደት ሃላፊ አዲስ ሥራውን እንደተረከበ ያንን ሥራ በተመለከተ ሥልጣን አለው። የሥራው መሪ ለመሆን ግን በያዘው ሥልጣን በቀጣይነት የሚያደርጋቸው ነገሮች ወሳኝ ናቸው። መሪ ግን ያለሥልጣን አይሆንም። ሥልጣን መሪውን ትከተለዋለችና። የሥልጣን ጥመኞች መሪዎች ነን ወይም መሆን እንፈልጋለን ሲሉ ይደመጣል። ወደ ፖለቲካው አገር ሲጠጋማ፣ ሥልጣንን በዝርፊያና በስርቆሽ ያገኘው ሳይቀር ቢያንስ ለህዝብ ሲል፣ አሊያም ህዝብ ሰጥቶኝ ነውና መሪ ልባል ይገባኛል ይላል። በቤተክርስቲያንም ሆነ ባያሌ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች፣ በህዝብ ድርግቶችና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋሞችም ጭምር ይህ ስላለ ታዲያ መወቃቀስ ስንኳ አንችልም። መሪነትና ሥልጣን ተቀላቀሉብን። ፉክክሩ ባሳዛኝ ሁኔታ የሥልጣን እንጂ የመሪነት መሆኑ ቀረ። ስለዚህ መሪ እንበላቸው፤ አንፍረድባቸው። በሥልጣን ቦታ ላይ የተቀመጠ ሁሉ እንዲያ ይባላልና። መሪ ሆናችሁልን ወይ ብለን ደግሞ አንጠይቅ፤ አይፍረዱብን። ሥልጣን በመያዝ ብቻ መሪ መሆን አይቻልምና።

ባንጻሩ ሥልጣን የሌለው መሪ የለም። ሊኖርም አይገባም። ለዚህም ነው መሪውን፥ ባለስልጣን የምንለው። የለመድነው ተገላብጦሹን ሆኖ ጠላነው እንጂ፥ በዚህ አጠራር ልናፍርበት አይገባም። ችግሩ ያለው ሥልጣንና መሪነት ቅደም ተከተላቸው ሲዛነፍ፣ መስመራቸው ሲጣረስ፣ ዓላማቸው ሲመሳቀልና ሲብስም ለእኩይ ተግባር ሲደጋገፉ ነው። ዋናው ጥያቄ ታዲያ ‘የምንፈልገው ምንድነው?’ የሚለው ነው። ሥልጣን ወይስ መሪነት? ማስመሰል እንዳይሆንብን ልባችንን እንፈትሽ። መሪ ለመባል ከምንጓጓ ውስጥ መሪ ለመሆን የቆረጥን ስንቶች እንሁን? ድንገት የተዛባ ጉጉት የተጣባን እንደሁ መነሻው ከምንድን ነው?

በቅድሚያ፣ መሪነትን ለሚመኙ የምሥራች አለ። ጉጉቱ በራሱ ክፋት የለውም። መጽሃፍ ቅዱስ ስለ ቤተክርስቲያን መሪዎች ሲናገር፣ የህዝብ እረኝነትን ሃላፊነት ለመውሰድ የሚፈልጉ ሁሉ የከበረ ሥራ ላይ ዓይኖቻቸውን እንዳነጣጠሩ አውቀው፥ ለሥፍራው ብቁነት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ፥ የመሪ መሥፈርት፥ ዝርዝር መመሪያ ይሰጣል (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡ 1 – 12፣ ቲቶ 1፡ 5 – 9)። በማንኛውም አደባባይ የህዝብ መሪ ለመሆን የሚመኝ ሊበረታታ ይገባዋል። ይህ አባባል ግን ያለቦታው ሲነገር ያሳስታል። እንደ መጽሃፍ ቅዱስ፥ መሪ ለመሆን መመኘት ብቻውን ከንቱ ነው፤ መሪነት የከበረ ሥራ ስለሆነ የሚመኙዋት ተመጣጣኝ ዝግጅት ማድረግ ያሻቸዋል።

አገልጋይ መሪ

መሪነትን፣ በተለይም አገልጋይ መሪነትን ሁሉም ሰው አጥብቆ መሻት አለበት። መጽሃፍ ቅዱሳዊው መሪነት፣ የሁለንተናዊ ለውጥ (transformational) አገልጋይነት ነው። መሪ ለመባል ከመጓጓት መሪ ለመሆን መጣጣር የህይወታችን ተልዕኮ ሊሆን ይገባዋል። ስመጥር መሪ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተከታዮቹ መካከል ሁለት ወንድማማቾች የግራና ቀኙን መቀመጫዎች በቋመጡ ጊዜ ሹመት ለአገልግሎት እንደሆነ ከርሱ ምሳሌ እንዲማሩ በግልጥ ተናግሯል (ማቴዎስ 20: 24-28; ማርቆስ 10: 41- 45; ሉቃስ 22: 24-27)። መሪነት በጉልበት፣ በልመና ብዛት፣ በእናት አማላጅነት ወይም በሌላ አይገኝም። መሪ ለመሆን የምንፈልግ ሁሉ ይህን ደጋግመን ልናስተውል ይገባል። ከክርስቶስ ልደት በፊት አንድ ሺህ ዓመተ ዓለም ግድም የእሥራኤል መሪ ከነበረው ከንጉስ ዳዊት ህይወት በመነሳት፥ ሌሎችን ለማገልገል ራሱን ዝቅ የሚያደርግ አገልጋይ፥ የሚከተሉት ሶስት እምብዛም ትኩረት ያላገኙ የአገልጋይ መሪ መልክና መለያዎች እንዳሉት እናስተውላለን።

ሀ) ብቃት

አገልጋይ መሪ ለሥራው ብቁ ነው። ይህ እምብዛም የተሰወረ ሃሳብ አይደለም። አገልጋይ መሪ ሥራውን በሚገባ ያከናውናል። በያዘው ሥራ ታማኝ ያልሆነ መሪ ሌላ የከበረ ሥፍራ ከተሰጠው ጥፋቱ ለሃላፊነት ባጨው ላይ ነው። ባንድ ሥራ ብቃቱ ያልተመዘነ፥ ከፍ ወይም ሰፋ ያለ ሥፍራ ባይሰጠው ላገልጋዩም ለተገልጋዩም መልካም ነው። ብቃት ለመመዘን ዕድል ባይኖር በሥራ ላይ እያለ መገምገም ቸል ባይባል። መሪው ቦታውን የተቆናጠጠው በውድድር፣ በምርጫ፣ በሽንገላ፣ በጉልበት፣ በሹመት፣ ‘በታሪክ አጋጣሚ’ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ቢሆን፥ የያዘውን ሥራ ማከናወን ካልቻለ፥ ጊዜ እያለ በፍቅርና በጥበብ በዚያ ሥራ ረገድ “መሪ አትሆነንም” ካላልን ያቦካውን ሲጋግር የባሰ እንከፋለን። ባንፃሩ በሥራው ታማኝ ባለመሆኑ ‘በቃህ፣ የልቤ የሆነ ሌላ አግኝቻለሁ’ ተብሎ በአምላክ የተነገረው ሳዖል (1ኛ ሳሙዔል 13:13)ስንኳ ሥፍራውን ላለመልቀቅ ከጌታውና በእግዚአብሄር ከተቀባው ጋራ አተካራ መግጠሙን ስናይ ይህ ዓይነቱ ዜና ለመሪዎች መድረስ ያለበት በምን ያህል ፍቅርና ጥንቃቄ እንደሆነ እንገነዘባለን። ዛሬም በዓረብ ንቅናቄ ዘመን ያስተዋልነው ትርምስና ያስከተለው አፃፋ የመሪዎች የሥልጣን ሙጥኝታ ጊዜና ቦታ የማይወስነው እንደሆነ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። የዘመኔን ዓረባዊ ያገር መሪዎች የመልስ ምት ስኮንን ከርሜ በዲሞክራሲያዊቷ አሜሪካን አገር በቅርቡ በአንድ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ያጋጠመኝ ትርዕይት አስደምሞኛል። ወንድሜ ለሠላሣ ዓመት ከተቀመጡበት ሥፍራ እንዳገሩ የምርጫ ህግና ደንብ መሠረት ከተፎካካሪዎቻቸው ባንዱ ስለተበለጡ የመልቀቂያ ንግግር እንዲያደርጉና ከረጅም ልምዳቸው ለተተኪዎች እንዲያካፍሉ በተሰጣቸው ዕድል መድረክ ላይ ቆመው መራጮች ላይ ያዥጎደጎዱት የስድብ ውርጅብኝና ውረፋ የዓረብ መሪዎች ህዝባቸው ላይ ካርከፈከፉት የነፍጥ ትንታግ ጋር ሊነፃፀር ይከጅለው ነበር። ላብሰከሰከኝ የእልህ ወላፈን ማርከሻ እጄን ቃታ ላይ የማሳረፍ ዕድል ቢኖረኝ እታቀብ ይሆንን ብዬ ራሴን እንድጠይቅም አስገድዶኛል። የሥልጣን ጥማት ጊዜና ቦታ፣ ዕድሜና ችሎታ፣ ዘርና ፆታ አይወስነውምና።

ከላይ በጠቀስኩት ስብሰባ ስገኝ የመጀመሪያዬ ከመሆኑ ጋር ከተሸኚው ባለሥልጣን ንግግር በመነሳት መራጩንም የታዘብኩት አለ። ወንድሜ ለሠላሣ ዓመት ሥፍራውን የተቆናጠጡት በብቃት ምዘና አለመሆኑ ግልጽ ነበር። እንዴት ታጩ? እንዴትስ ተመረጡ? ዳዊት ለሹመት ከመታጨቱ በፊትም ሆነ በተሰጠው የተለያየ የመሪነት ሥፍራ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ እንደነበር መጽሃፍ ቅዱስ ይነግረናል። በ1ኛ ሳሙዔል 17፡ 30 እንደተገለጸው፥ በልጅነቱ ያባቱን በጎች ሲጠብቅ ከነጣቂ አንበሳና ድብ ተሟግቶ ይታደጋቸው ነበር። አባቱ በጦር ሜዳ ያሉ ወንድሞቹን ጠይቆ እንዲመለስ በላከው ጊዜ፥ በጎቹን ለጠባቂ በመተው (1ኛ ሳሙዔል 17:20)፤ የጦርነቱን አካሄድ ለመቃኘት ወደ ግንባር ከመዝለቁ በፊት ለወንድሞቹ የተላከውንና በጁ ያለውን ዕቃ ለጠባቂ በማስረከብ (1ኛ ሳሙዔል 17:22)፤ እናም መጀመሪያ ከሳዖል ፊት በኮበለለ ጊዜ በቤተሰቡ ላይ ክፉ እንዳይደርስባቸው አባትና እናቱን በሞዓብ ንጉሥ ዘንድ ማስቀመጡ(1ኛ ሳሙዔል 22:4) ዳዊት ከትልቅ እስከ ትንሽ ነገሮችን ሁሉ እንዴት በጥንቃቄ ያከናውን እንደነበር ያሳየናል።

ከፍ ያለ የአገልግሎት ዕድል ሲያጋጥመው ይህ ጥንቁቅነቱ ረድቶታል። በሳዖልና በቢንያም ነገድ ላይ ትዝብት ነው እንጂ፥ ጠጉር ስንኳ በማይስቱ ቢንያማውያን ወንጫፊዎች የተደራጀውና በቢንያማዊው ሳዖል የሚመራው የእሥራዔል ጦር ተብረክርኮ ሳለ፥ ከበጎች ጋር ሲውል ራሱን ለከበረ ዕድል ያዘጋጀውና ባምላኩ የታመነው ዳዊት የፍልስጥዔማዊውን ዛቻ የገጠመው በወንጭፍ መሆኑ ያስገርማል (መሳፍንት 20፡16)። በተመሰከረለት የውጊያ ልምድ የዳበረውን ይህን ፍልስጥዔማዊ የጦር መሪ በመዘረር ከእሥራዔል ስድብን አስወግዷል። ልምድና ብቃት ባምላኩ በታመነ ጥንቁቅ ለጋ ወጣት መረታታቸው ዛሬ ምን ያስተምረን ይሆን? የሚገርመው፣ ዳዊት ከዚህ የጦር ሜዳ ውሎ በኋላ በሳዖል ላይ ወይም ከጦር መሪዎች ባንዱ ላይ አፉን ሲያንቀሳቅስ አናየውም። የተሠጣቸውን ሥራ አዝረክርከው ሲያበቁ ባለቆቻቸው ላይ ምላሳቸውን ማስረዘም ሙያ ያደረጉትንስ ምን እንበላቸው? ባንጃ ግራንጃ፥ ‘ጤፍ የሚቆላ’ ምላሳቸው ተለክተው፥ ሥልጡን መስለው፥ መሪ ሊሆኑን?

ዳዊት በሳዖል ዘመነ መንግሥት በእሥራዔል ጦር አባልነት ሲያገለግል፥ ንጉሡ በላከው ሥፍራ ሁሉ አንጀት አርስነቱ ተመስክሮለታል። ለዚህ ተግባሩ በጦሩ ውስጥ የመሪነት ሥፍራ ሲሰጠው ሁሉም የጦር መሪዎች ደስ ተሰኝተዋል (1ኛ ሳሙዔል 18:5)። ዳዊት አንቱ የተባለ የጦር መሪ መሆኑን ካሳዩ አጋጣሚዎች አንዱ የስደት መንደሩ የሆነችው ጺቅላግ ተወርራ፣ ያላቸው ሁሉ ተማርኮ በተወሰደበት ጊዜ ከሃዘናቸው ብዛት አቅም እስኪያንሳቸው ያለቀሱና እርሱን - ራሱን - መሪያቸውን ለመውገር የተነሳሱትን ጎበዛዝት መክሮ፣ አሳምኖ፣ ወራሪዎችን አሳድዶ ምርኮውን ማስመለሱ (1ኛ ሳሙዔል 30፡1-16) እንደነበር እንገነዘባለን። በስደቱ ዘመን ከንጉሥ አኪሽ ‘በፊቴ እንደእግዚአብሄር መልአክ ነህ’ እስኪባል ሞገስን አግኝቷል (ምንም እንኳ ይህ የባዕድ ንጉሥ እሥራዔልን ወጋሁልህ እያለ ግሩም አድርጎ ያታለለው ቢሆንም) (1ኛ ሳሙዔል 29፡9)። ከሳዖል ሞት በኋላ አበኔር በገለዓድ ያነገሰውን የሳዖል ልጅ የተከተሉ ቢንያማውያን እንኳን ሳይቀሩ ‘እሥራዔልን በማስገባትና በማስወጣት የተፈተንክ ነህና እባክህን ንገስብን’ ብለው ዳግመኛ ቀቡት (2ኛ ሳሙዔል 5፡ 1 – 5)። የያዙትን ሥራ በብቃት ማከናወን ለመሪነት መነሻ መስፈርት ነው።

የዳዊት አመራር ብቃት በጦር ሜዳ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ጦሩን ብቻ ሳይሆን አስተዳደሩንና ቤተመቅደስንም ጭምር በሥርዓት አደራጅቷል። በቤተመቅደስ የአሮንን የክህነት አደረጃጀት እንደገና በማደስ (1ኛ ዜና 24፡19) ሌዋዊያንን የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጎአል። አራት ሺህ የሚያህሉትንም ለዜማና ዝማሬ ለያቸው። የዝማሬ ነገር ከተነሣ የዳዊት የዜማ፣ የዝማሬና ቅኔ ክህሎት ወደር የማይገኝለት እንደሆነ እስከዛሬ በየቤተእምነቶቻችን የሚዜሙ ቅኔዎቹን ማጤን በቂ ነው። በሙዚቃ ችሎታው የንጉሥ ሳዖልን ቁጣ ለማብረድ ለህይወቱ አስጊ በሆኑ አጋጣሚዎች እንኳ አገልገሏል (1ኛ ሳሙዔል 18)። ሙዚቃ፣ ዜማ፣ ዝማሬ፣ ቅኔ፣ ግጥምና መሰል የጥበብ ሥራዎች ደግሞ አንድን የጠለቀ ሃሳብ ለሌሎች በቀላል፣ ባጭሩና በማይረሳ መልኩ ለማካፈል ዓይነተኛ መንገዶች ናቸው። የአንድ መሪ የብቃት መለኪያዎች ከሆኑ ነገሮች አንዱ ሃሳቡን በግልጽና ለማስታወስ ቀላል በሆነ መንገድ ማካፈል መቻል ነው። መሪ የተከታዮቹን ቀልብ ለመሳብ ትናጋው እስኪሰነጠቅ መጮህ አያሻውም። እንዲሁም፥ መልካም ምክክርና ውይይት ተገቢ ሥፍራ ያላቸው ቢሆንም አቅል የሳተ የኮሚቴና ድርጅታዊ ስብሰባ ነገርን ከማንዛዛትና ሲያልፍም አፍራሽ ተጽዕኖ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የላቸውም። ዳዊት በዚህ ረገድ እጥፍ ፀጋ የተሰጠው፥ እጥፍ ድርብም ያሳደገ መሆኑን እንረዳለን።

የመሪ ዓይነተኛ የብቃት መለኪያ ግን ከዚህም ያለፈ ነው። የሁለንተናዊ ለውጥ አገልጋይ የሆነ መሪ ዋነኛና ምናልባትም የመጨረሻው ትልቅ ሃላፊነት ሌሎችን ማሳደግ ነው። ይህ የራስን እግር የሚተካ መሪ ማፍራት የሚያጠቃልል ቢሆንም በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከመሪ እጅ በታች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ብዙ ሰዎች ይገኛሉ። ያገልጋይ መሪ ትልቁና ከባዱ ሸክም የተከታዮቹን ተፈጥሮ፣ ፀጋ፣ ተሰጥኦ፣ ብቃት፣ ክህሎት፣ ህልም፣ ፍላጎት፣ ምኞት፣ ተነሳሽነትና ድካም ሳይቀር ጠንቅቆ በመረዳት አሰማምሮ፣ አስማምቶ፣ አሳድጎ፣ አደራጅቶና አንቀሳቅሶ ለውጤት እንዲበቁ ማድረግ ነው። አገልጋይ መሪ እንግዲህ ሌሎችን አሳድጎ ለውጤት የሚያበቃ ነው። ተከታዮቹ ለውጤት ሲበቁ በእጅጉ ይረካል። የተከታዮቹ ስኬት አያስፈራውም። ምክኒያቱም በሚያሳድጋቸው ወቅት ሳያሸማቅቃቸውና ማንነታቸውን ሳይነፍግ፥ እንዲያውም ፈጣሪ የቸራቸውን መልካካም ማንነት በውል ተገንዝበው እንዲያጎለብቱት እየረዳቸው፥ ራሱን በነሱ ውስጥ በሰፊው ዘርቷልና ነው።

ሌሎችን ማሳደግ የጅምላ ጉዳይ እንዳልሆነም መገንዘብ ያሻል። በዚህ ዘመን በተለይም በቤተክርስቲያን በሺህዎች የሚቆጠሩ አባላት ያሉዋቸው ቤተእምነቶች ትልቅ ተደርገው ከመወሰዳቸው ሌላ መሪዎቻቸውንም የከበሩ አድርገን እናያቸዋለን። በርግጥም ከምንም ተነስቶ በርካታ ተከታዮችን ማፍራት ቀላል ሥራ አይደለምና ባግባቡ ሊከበሩ ይገባል። ከተከታዮቻቸው መካከል ግን ስንቶች መሪዎች ናቸው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው “ዓለሙን ከራሱ ጋራ ያስታርቅ ነበር” ተብሎ እንደተጻፈ (2ኛ ቆሮንቶስ 5፡19) ከማናቸውም መሪዎች የላቀ ሃላፊነት የተረከበና “በርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ” ብሎ እንደመሰከረለት (ማቴዎስ 17፡5) አገልግሎቱን በተሳካ ሁኔታ ያጠናቀቀው ዓለሙን ሁሉ ያግበሰበሰ ቤተክርስቲያን በመመሥረቱ አልነበረም። ያ ቢሆን የዛሬ ተከታዮቹ አባል አይሆኑምና። ይልቁንም በጥቂቶች ህይወት ውስጥ ራሱን በተነ፤ በዓሣ አስጋሪዎች፣ በሃኪሞች፣ በመንግሥት ሰራተኞች፣ በፈላስፎች፣ በቤት እመቤቶች፣ በሌሎችም ውስጥ። እነዚህም እንደማንነታቸው ሁሉ ኢየሱስን አስፋፉት፤ ዓለም እስክትገለባበጥ፣ በማያባራ፥ ሰማይን በናፈቀ የለውጥ ማዕበል እስክትነዋወጥ ድረስ። ያስታራቂነቱም ሥራ እርሱ ራሱ ሲመለስ መቋጫ ያገኝ እንደሁ እንጂ ማንኛውም ሃይል አይበግረውም።

ሙሴም በበርካታ የጎሣ መሪዎችና ዳኞች እየተረዳ ቢያገለግልም አንድ መሪ - ኢያሱን - አሠለጠነ፤ አዘጋጀውም (ዘዳግም 34:9)። ከካሌብ ጋራ ራዕዩን እንደሚያሳኩለት አውቆ በእምነት አስረከበው (ዘዳግም 31:7)። ለልጄ፣ ላክስቴ ልጅ አላለም። መሪነት በደም የሚተላለፍ አድርገው የሚገምቱና እንዲህ እንድናምንላቸው የሚፈልጉት ተላሎች ልጃቸውንም ሆነ ሌላ በማዘጋጀቱ ላይ ቢያተኩሩ እንዴት በወደድንላቸው? የወላጆቻቸው ቅርሻት እያንገፈገፈ ሊያስታውኩባቸው የሚከጅሉ ልጆቻችውን በህዝብ ጫንቃ ላይ ለመጫን ልክ ያምላክ ገፀ በረከት እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ለዓረብ መሪዎችም እንዳልጠቀመ ዘመናችን በድጋሚ አፍረጥርጦታል። መሪነት፣ በተለይም ብዙ ህዝብ፣ ጥሪትና ግንኙነቶችን የመምራት ሃላፊነት፥ ከንቅልፍ እንደባነኑ እመር ብለው የሚቆናጠጡት አይደለም። ረጅም ዝግጅት ይጠይቃል። እንደሙሴና ዳዊት ተግዳሮት ባለበት፥ ተቀናቃኝ በበዛበት የፖለቲካ መሪነት ለማገልገል ራሳቸውን የሰጡ ምን ያህል ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸው አንባቢ ይገምት። ‘የነ ቶሎ ቶሎ ቤት’ እንደሚባለው ቢሆን፥ ‘ሲሮጡ የታጠቁት’ እንዳይሆን!

እንግዲህ ኤልያስም ኤልሳዕን (2ኛ ነገሥት 2)፥ ጳውሎስም ጢሞቴዎስንና (2ኛ ጢሞቴዎስ 3:10 – 4:18) ቲቶን (ቲቶ 1:5 – 3:11) ማሳደጋቸውን መጥቀስ ይቻላል። ወደ ዳዊት ስንመለስ ግን የጦር መሪ እንደመሆኑ ያሰለጠናቸው የጦር መሪዎች ብዛት በዘመኑ ሁሉ አንቱታን ሠጥተውታል። ወደ 600 የሚያህሉ፥ የተገፉና የተጎዱ ሰዎችን በማስከተል ‘ጫካ የገባው’ ዳዊት 37 ታላላቅ የእሥራዔል ጦር መሪዎችን አሠልጥኖአል። ከነዚህ ዝናቸው የገነነ መሪዎች ለዳዊት በጣም ቅርብ የሆኑት ሦስት እጅግ ታላቅ የተባሉ ነበሩ። የሚገርመው አጎቶቹ ኢዮአብ፣ አሳሄልና አቢሳ በተለያየ ወቅት የጦሩ አዛዦች የነበሩ ቢሆኑም መጽሃፍ ቅዱስ ወደ ዳዊት ሦስቱ ታላላቆች የቀረቡ እንዳልነበሩ ይመሰክራል (2ኛ ሳሙዔል 23)። ዳዊት በቤተልሄም ከተማ በር አጠገብ ካለችው ምንጭ ውሃ ለመጠጣት በተመኘ ጊዜ በከተማይቱ መግቢያና ዙሪያ የመሸገውን የፍልስጥዔም ጦር ሰንጥቀው በመግባት ለንጉሣቸው ከምንጩ ውሃ ያመጡ ሦስት ጀግኖች ከእነዚህ ታላላቆች መካከል መሆናቸውን እናስተውላለን (2ኛ ሳሙዔል 23:13)። እውነተኛ ተከታይ ያሳደገ መሪ የሚያሰጋው የለም። ዙፋኑም (ቢያንስ ከተከታዮቹ አንጻር) የተደላደለ ነው። ዳዊት ይህን በጀግኖች ላብና ደም የተቀዳ ውሃ አልጠጣውም። ምጡቅ ብቃት ያለው መሪ በተከታዮቹ መሥዋዕትነት የተገኘውን በረከት ለራሱ አይጋትም። ይህ ምሥጋናን ካለማጓደል ጋርም አይወዳደርም። የመሪያቸውን ጥልቅ መሻት ለማርካት አይከፍሉ ከፍለው ውጤት ያስገኙ ተከታዮች ሥራቸው ከሽልማትና ሹመት በላይ መሆኑ ሲመሠክርላቸው ነፍሳቸው ከመሪያቸው ነፍስ ጋር በፍቅር ትታሰራለች።

ለ) ፍቅር

ስለ ብቃት ይህን ያክል ካልን በቀሩት ሁለት ምዘናዎች ላይ ጥቂት ሃሳቦች እናንሳ። አገልጋይ መሪ ህዝቡን ይወዳል። ቤተሰቡን፣ ጎረቤቶቹን፣ ጓደኞቹን፣ ተከታዮችን፣ ህዝቡን በሙሉና የሚጠሉትንም ጭምር ይወዳል። መሪ፥ ወዳጆች እንዳሉት ሁሉ ጠላቶችንም ያፈራል። ጠላቶቹን ይወዳል ስንል ታዲያ ጥንቃቄ የተሞላበት ፍቅር ማለታችን ነው። በእሥራዔል ንጉሥ ሳኦል ዘመን ታላቅ የጦር አለቃ የነበረው የኔር ልጅ አበኔር ከሳዖል ሞት በኋላ ንጉሥ ዳዊትን ሊያናግረው በመጣበት ‘እንደሰነፍ ይሞታልን?’ ተብሎ የተለቀሰለት ጠላቶቹን ያለጥንቃቄ በማፍቀሩ ነው። የዳዊት ጦር አለቆች ኢዮአብና አቢሣ የታናሽ ወንድማቸውን የአሣሄልን ደም ለመበቀል ‘በንጉሥ ፊት ሞገስ አግኝተሃልና አይዞህ፤ ለጥቂት ጊዜ በቆይታ እናናግርህ’ ብለው አጃጃሉት (2ኛ ሳሙዔል 3:22–34)። ዳዊት ግን ወዳጆቹንም ጠላቶቹንም በፍጹምነት መውደዱ ተመስክሮለታል።

ከሳዖል ፊት በሸሸ ጊዜ ለቤተሰቡና ለዘመዶቹ ያደረገውን ጥንቃቄ አንስተናል (1ኛ ሳሙዔል 22:4)። ገና ከመንገሱ በፊት የእሥራዔል መንደሮች ሲጠቁ አያስችለውም። ይታደጋቸዋል። አሳልፈው ከመስጠት ወደኋላ የማይሉትን እነቅዒላን ጭምር (1ኛ ሳሙዔል 23:1-6)። ወገኖቹ ናቸውና በሌላ ሲጠቁ እጁን አጣጥፎ አይመለከትም። ህዝብን እየዘረፈ፥ እያገተ፥ እያፈነ ትግል አካሂዳለሁ የሚል የሥልጣን ጥማት እንጂ የመሪነት ራዕይ የለውም። ከጺቅላግ ወራሪዎች የዘረፉትን ምርኮ ተዋጊዎች ብቻቸውን ለመቀራመት ባሰቡ ጊዜ የተዋጉም፣ ደጀኑም፣ ሥንቅ አቀባዩም፣ ሌላው ቀርቶ ምናልባት እቤት ቁጭ ብለው የጸሎትና ሃሳብ ድጋፍ ብቻ ያደረጉትም ጭምር እንዲካፈሉ የጦር ሜዳ ደንብ በማድረግ ስስት ሁሉን በእኩል ዓይን ማየትን እንዳይተካ አድርጓል (1ኛ ሳሙዔል 30)።

ዳዊት ያሳድደው የነበረውን ሳዖልን ካንዴም ሁለቴ ‘እግዚአብሔር በጁ ጥሎለት’ ጠላቱን ከማጥፋት የሚገኘውን ደስታ ናቀ (1ኛ ሳሙዔል 24:10 እና 26:10)። ፍቅር ምህረትን ያደርጋልና። ከሳዖል ጋር ብርቱ የሞት ሽረት ትግል ላይ እያለ ምህረትን ማስበለጡ ዛሬ እንዴት ተበለጥኩ ብለው አንገትን ለሚቀሉ ወይም እንዳያዳግም ለሚጎሽሙ መሪዎች ትምህርት ይተው ይሆን? መሪዎች ዳዊት ‘እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሳም’ ማለቱን ብቻ የሚያነብቡ ስለመሰለኝ ነው። ዳዊትሳ አልተቀባምን? ፍቅር ከቅባትም በላይ መሆኑን ዳዊት አስረድቶናል። የስደት ኑሮ፥ በምድረበዳ መንከራተቱ ቢበቃና ቤተመንግሥት ቢገባ አይጠላም። የእሥራዔልን መሪ እንደሰነፍ አጋድሞ ግን አይሆንም። እሥራዔል የጌታ ህዝብ፥ እሥራዔል የዳዊትም ህዝብ እንዲህ ዓይነት ውርደት እንዲሸከም የተቀባው ዳዊት አይፈርድም። ሳዖል ግን እስከሞተበት ቀን ድረስ የዳዊትን ቅባት ተፈታተነ። መቼም ይህ ሳያበሳጨው አይቀርም። ሲያጋጥም ቢለውና ቢገላገልስ? ለነገሩማ ሳዖል ብቻ ሳይሆን ምናምንቴ ሰው ናባል ‘ከጌታው የኮበለለ አውደልዳይ’ ብሎት የለም? ንጉሥስ ያሳድደው፤ ጠጅ የጠገበ ሁላ ይሳደብ? ለእንደዚህ ዓይነቶችም ምህረት ማድረግ የመሪነት ቅባት በከንቱዎች ደም እንዳይረክስ ያደርጋል (1ኛ ሳሙዔል 24)።

ንጉሥ ከሆነም በኋላ እንኳ የጌራ ሰው ሣሚ ሲሳደብ ዳዊት አደብ መግዛቱ የፍቅርን ፍጹምነት ያመለክታል ። ምላስ እንደሰደድ እሳት የሰውን ህይወት እንደሚያቃጥል (ያዕቆብ 3:6) ዳዊትም ሣሚም ያውቃሉ። ስድቡ ረቂቅ ነበር። “መንግሥትህ ተወሰደችብህ፤ ደም አገኘችህ፤ ተንኮታኮትክ!” ክፉ ትንቢት ያዘለ ስድብ። የዳዊትን ህይወት የሚያጨልም፥ የሚያቃጥል ሰደድ እሳት። ዳዊት ግን እሳቱን በምህረት አዳፈነ። እግዚአብሄር እንዲምረኝ ማርኩት አለ (2ኛ ሳሙዔል 16:10)። ስድቡም አላገኘውም። ይልቁንም፤ ከዙፋኑ ሸሽቶ በምድረበዳ እንዲንከራተት ምክንያት የሆነውን፥ የመንግሥት ግልበጣ ዋነኛ ተዋናይ ልጁን አቤሴሎምንም ምህረት እንዲያደረግለት ጉልበት ሆነለት። በጠራራ ፀሃይ በመላው እሥራዔል ፊት ያሳፈረውን፥ ያዋረደውን፥ ቂመኛ፣ ቀማኛ፣ ክፉ ልጁን ማረው፤ ክፋቱ ባገኘው ጊዜ ስንኳ፥ ሞቱን በሞትኩለት ብሎ መሪር ሃዘን፥ ብርቱ ለቅሶ አደረገለት። መሪ በጠላቶቹ ላይ የሚደርሰው መቅሠፍት ያስደነግጠዋል፥ ይቆጨዋል እንጂ አያስካካውም። የመሪ ሆድ ሰፊ፥ ልቡም ርህሩህ ነው።

ጠላቶቹን ለመውደድ ጉልበት ያገኘ ደግሞ ሌላውን ያለአድልዎ ለመምራት እምብዛም አይቸገርም። ህዝብን መውደድ ማለት ደግሞ አለማዳላት ማለት ነው። ዳዊት ለእሥራዔል ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገ (1ኛ ሳሙዔል 8:15፤ 1ኛ ዜና 18፡14)። በየትኛውም ሥፍራና ጊዜ በዘመድ፣ በጓደኝነት፣ በጉርብትና፣ በጎሣ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ ባገር - ወንዝ ልጅነት፣ በእከከኝ ልከክህ፣ ወዘተ ተመሥርቶ የሚደረግ ማንኛውም አድልዎ የህዝብን አንጀት የሚያቆስል፥ እግዚአብሔርም የሚጸየፈው ድርጊት ነው። አድልዎ ያለበት አገልግሎትና መሪነት ጭንጫ የበዛበት ጉርሻ ነው፤ ማላመጥ ሲያስቸግር መተፋቱ አይቀርም። ብቃት የመሪነት እርካብ መቆናጠጫ ምስጢር፥ ወደከፍታዋ የመወጣጫ መሰላል ስትሆን፥ ፍቅር ደግሞ ህዝብን የማብዛት፣ የመሪነት ሜዳ ማስፋፊያና መደልደያ መሣሪያ ናት። ፍቅር፥ በተለይም መሥዋዕትነት ያዘለች ፍቅር አገር ታሰፋለች፤ የማትመነጥረው ጫካ፥ የማትነቅለው ጉቶ አይኖርም። መሪ ሆይ ህዝብህን ከልብህ ውደድ! ካስመሰልክ ለይስሙላ ይገዙልሃል። ችግር የለም፥ ያውቁታል፤ ቀናቸውንም ቆርጠዋል።

ሐ) ንስሃ

ለዚህኛው መሥፈርት የተሻለ ርዕስ ባገኘሁ። አንባቢ እጅግ መንፈሳዊ መስሎት እንዳይሸሸው። ንስሃ በሃጢአት ተፀፅቶ ከእግዚአብሔርና ከሰው ይቅርታ መጠየቅ፥ ያንንም ሃጢአት ዳግመኛ ላለመሥራት ውሳኔ ማድረግ፥ እንዲሁም በበደል ፈንታ መልካሙን ነገር በማድረግ መትጋት ሲሆን በዚህ ሥፍራ ግን ትንሽ የሰፋ ትርጉም እንሰጠዋለን - ሁልጊዜ ራስን መመዘን። የዘመኑ “ግምገማ” ንድፈ ሃሳብ ይህንን በቁንጽሉም ቢሆን ይነካል። ንድፈ ሃሳብና ተግባር ለየቅል እንደሆኑ ግን ሳንጠቅስ አናልፍም። አገልጋይ መሪ ራሱን ይመዝናል። ብቃት የዕድገት፣ ፍቅር የመስፋት መንገዶች እንደሆኑ ሁሉ በሰውና በእግዚአሔር ፊት ራስን እየመዘኑ መመላለስ የመሪነት ጥልቀትና ጥንካሬ መገለጫ ነው ማለት እንችላለን። ራሱን የማይመረምር አገልጋይ ደግሞ ከንቱ፥ ንብ የሌለው ቀፎ ብቻ ሣይሆን አደገኛም ነው። ያደረገው፣ የሠራው፣ የያዘው፣ የረዘዘው ሁሉ ትክክል ይመስለዋል። ሃይ የሚለው ካላገኘ። በዚህ ዘመን አገልግሎታችንና መሪነታችን መቅኖ ያጣው መሪዎች በትህትና መመላለስ ሲያቅተን ሃይ ባይ ስለማናገኝ ነው። ባጠገባችን ያሉ መሪዎች ቢሆኑም ህዝቡ እውነትን በፍቅር ስለማይገልጡልን ሜዳውም ፈረሱም የኛ ብቻ መሰለን። አጉረምራሚው እጀበና ሥር፣ ወይም በየመሸታ ቤቱ፥ ቤት ለቤት ነገርን በነገር ያባዛል። ለመግለጥም የደፈረው ጥበብ ወይም ድጋፍ ስለሚጎድለው የባሰ ጡጫ ይቀምሳል። ደግነቱ ለእውነተኛ መሪዎች በትክክለኛው መንገድ ሃይ የሚል አለ። ቢያንስ ዳዊትን አግኝቶታል። ዝሙቱን ከሰው መሸሸግ ሃያላኑን ከማስገደል ጋራ ሲያነፃፅረው ማለፊያ ውሣኔ የመሠለው ዳዊት፥ ከእጁ በታች ያደገውን፣ ለዳዊትና ለቤተሰቡ ደህንነት፥ ለእሥራዔልም ክብር ራሱን የሰጠ፣ ከዳዊት 37 ታላላቆች መካከል የተቆጠረ ጀግና፣ ሂታዊው ኦሪዮን በራሱ በዳዊት ቀጥተኛ ትዕዛዝ የጠላት ጦር ሰለባ አደረገው። ሚስቱን ያባለገበት ሳያንሰው፥ ያለጥፋቱ አስገደለው። አሳድጎት ቀጨው። ሚስቱንም ጠቀለለ። የንጉሥ ሃጢአት ተገልጦ አገር ከሚሸበር፥ ያንድ ጀግና ሞት፣ የዚህ ለጋ ቤተሰብ መፍረስ ሸጋ መስሎ ታየው።

የለም! ኦሪዮን የእሥራዔል ጀግና ደሙ የሃጥያት መሸፈኛ ሆኖ ሊቀር? አይደረግም። እግዚአብሔር ዳዊትን እዚህ ላይ በህይውት ዘመኑ ሁሉ የማይረሳ ትምህርት ማስተማር ነበረበት። በዝሙት የተወለደው ልጅ መቀሠፍ ነበረበት፤ በዳዊት በራሱ ቤት በልጆቹ መካከል፥ አገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ከዝሙት የከፋ አስገድዶ መድፈር በወንድምና በእህት መካከል መከሰት፤ የወንድማማቾች መገዳደል፤ የሚወደው ልጁ መሰደድ፤ ኋላም ጠላቱ በመሆን ከዙፋኑ እስኪያሳድደው ማመጽ፤ ያንድ የዳዊትን ዝሙት ለመሸፈን በተደረገው ጠንቅ፥ በመላ እሥራዔል ፊት የዳዊት ቁባቶች ሁሉ ላይ በልጁ የተፈፀመ ዝሙት! (2ኛ ሳሙዔል 11-19)። ሲያስፈራ፤ ሲዘገንን። መጽሃፍ ቅዱስ ይህን ታሪክ 9 ምዕራፍ ሙሉ ሰጥቶ ይተርከዋል። ካገልግሎት ከፍታና ስፋት ጥልቀቱ ይበልጣልና ዳዊት ይህን ጠንቅቆ መረዳት ይኖርበታል። “እንደ ልቤ የሆነልኝን፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ” (1ኛ ሳሙዔል 13:14፣ የሐዋሪያት ሥራ 13:22) አለ? ‘እንደ ልቤ ያደረግኩትን’ ማለቱ ይሆን?

እውነትም ወለላ አድርጎታል፥ ከዚያ በኋላ። የተረገጠ፣ የተቀጣ፣ የተማረ፣ ማንነቱን በሚገባ ያወቀ። ፈቀቅ ባለ ቁጥርም ሌላ ፈጣን ዱላ እየቀመሰ። ለምሳሌ ቢመከር እምቢ ብሎ ተቀማጭ የጦር ሃይል በመቁጠሩ በራሱና በእሥራዔል ላይ ተመሳሳይ ፈጣን ዱላ አስከትሏል (2ኛ ሳሙኤል 24)። ክብር ፍለጋ፥ ውርደት ሽሽት፥ ሃጢአትን በሃጢአት መደበቅ የባሰ አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ነው። እግዚአብሄር እርሱ ብቻ ታላቅ! ስለዚህ በፊቱ በጥንቃቄ፣ በፍርሃትና በትህትና ልንራመድ ያስፈልጋል። ዝማሬዎቹ የዳዊትን የተማረ ወለላ ልብ ስለሚገልጡ ጥቂቶቹን መጥቀስ አስፈላጊ ነው። በመዝሙር 6:6 ዳዊት ሃይል እስከሚያጣ ማልቀሱን፥ አልጋውም በእንባ ጎርፍ መራሱን፤ መዝሙር 69:3 ከልቅሶው ጩኸት ብዛት ጉሮሮው መሰንጠቁን፤ በመዝሙር 143:6 እጁን ወደላይ አንስቶ ሲጮህ እንደውሃ ጥም ያቃጠለው መሆኑን ዘምሮልናል። ነቢዩ ናታን ለንጉሥ ዳዊት በረቀቀ ጥበብ ወደቤርሣቤህ መግባቱና ባልዋን ዖርዮን ማስገደሉ ከፍተኛ በደል መሆኑን ካስረዳው በኋላ ዳዊት በተሰበረ ልብ ያዜመው መዝሙር 51 የህይወቱ መመሪያ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህ መዝሙር በመነሣት ራስን መመርመር ማለት ሦስት ዋና ዋና ነገሮች እንደሚያጠቃልል እንመለከትና በዚሁ ይህንንም ጽሁፍ እናጠቃልል።

በመጀመሪያ፥ ራሱን በትክክል የሚመረምር፥ ሰው ፍፁም ሆኖ እንዳልተወለደ ይገነዘባል (መዝሙር 51:5)። ሰው አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ ፍፁምነት ይጎድለዋል። መሪም ከጅምሩ ጎዶሎ፥ ሲሠራም ተሳሳች ነው። ያደረግኳት ሁሉ እንደወተት የነጣች፣ እንደፀሐይ ፍንትው ያለች ናት እያሉ ደርቆ ማዳረቅ ትርፉ ትዝብት ነው፤ ሲብስም ያስነቅፋል። ሰው ስህተትን ለማድረግ በውስጡ እምቅ ሃይል ያለው ፍጡር ነው ብንል ይህን ጭብጥ ጠንከር አድርጎ ለማስረዳት ያግዘናል። ዳዊት ራሱን ሲመዝን ከማህፀን ጀምሮ ሃጢአተኛ እንደነበር ተገነዘበ። በተጨማሪም፥ ልቡ ይህን እምቅ ሃይል ለመጠቀም ሁሌ እንደምትፈልግ አጋጣሚው ሲገኝ፥ ሲያስፈልግም ተወጥኖ ሲፈጠር ሰውና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ሃጥያት እንደሚሠራ አወቀ (መዝሙር 51:10)። ለዚህ ነው ‘ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ’ ሲል ያዜመው። በመጨረሻም፥ ይህን ሁሉ ለማድረግ ግን መንፈሱ ፈቃደኛ ልትሆን ይገባል (መዝሙር 51:12)። በጎ ያልሆነ አካሄድ ፍፁም ደስታን የሚሰጠው ሰው ያለ አይመስለኝም። ካለም የሰብዓዊነት ክብር የጎደለው መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ጠማማ ነገር ንቆ መተው መንፈሳቸው ትሁት ስብዕናቸው ምሉዕ የሆኑት ብቻ የሚያገኙት ፀጋ ነው። የእጅ ንፅህና፣ የልብ ቅድሥና፣ የመንፈስ ትህትና አገልጋይ መሪ ራሱን የሚያይባቸው ሚዛኖች ናቸው። ተከታዮችም በተመሣሣይ ሚዛን ያስቀምጡታልና። ቀሎ ከተገኘ፥ ጥልቀት የሌለው፣ ተንሳፋፊ አገልግሎት ይዞ ይኳትናል እንጂ ለመሪነት አይበቃም።

ማጠቃለያ:- ያልኩትን ከመድገም ጥያቄዎች ብቻ ጠይቄ ላብቃ። ጥቂት ነገር እንኳ አከናውነን ጎሽ ሳንባል ደርሶ መሪዎች ላይ አንዳች መለጠፍ ለምን ያምረናል? አንድን ሥፍራ መያዝ በብቃት ምዘና የማድረግ ባህል እንዲዳብር ምን ማድረግ ያሻል? አያድርስ እንጂ ብቃት፣ ፍቅርና መልካም ሥነምግባር የሌላቸው መሪዎች ቢፈነጩብን ምን ይበጀናል? የመሪዎች አካባቢ እንደተለበለብ ቁጥቋጦ ወጣቶች የጠፉበት፥ ገላጣ የሆነው ከምንድነው? ሌሎችን ማሳደግ የትና መቼ መጀመር ያስፈልጋል? መሪዎች ድካማቸውን ከገለፁ ሊደርስባቸው የሚችለውን መከራ እንዴት ይቋቋሙታል? ተመዝነው የቀለሉብንን መሪዎች እንዴት እናስተናግዳቸው? እግዚአብሄር ቢረዳንና በሁሉም መስክ ካሉት መሪዎች እነዚህና የመሣሠሉትን ጥያቄዎች አንስተው መማር በቻልን!   [© ጎዳና ጎግያጎ - ሐምሌ 2003; This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.]