ራእይ ሲደበዝዝ

በፀሐይ ዓለሙ

“የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋል … ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም። በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።” (ዕብራውያን 1036፣ 139)

ባለ ብዙ ተስፋ ባለ ብዙ ራእይ የነበሩ ሰዎች ዛሬም አሉ። አጀማመራቸው ያማረና የሚቀጥል የሚመስል፣ ወቅቶችና ሁኔታዎች መፈራረቅ ሲጀምሩ እንደ ማመንታት እያሉ ግራ በመጋባት ላይ ያሉ ጥቂት አይደሉም።

ለመጠራታቸው ማስረጃ የሚሆን የሕይወታቸው ምስክርነትና ጸጋቸው ይናገራል። ግን እየቆዩ ከዋናው ዓላማቸው ሸርተት ብለው ከማይመስለውና ከማይመቸው አኗኗር ጋር ተደባልቀውና ተመሳስለው ለመኖር የሚያደርጉት ጥረት ክብደት ነስቷቸው ተራ ሰውነት ይዘው ይገኛሉ።

ትልቁ ሰው እንደ ትንሽ፣ ትንሹም ሰው እንደ ትልቅ ያልሆነውን ለመሆን ሲጥር፣ ውሸቱም እንደ ልክ ተቆጥሮ የሕይወት መመሪያ ሆኖ ሲጠናከር፣ ውስልትናም እንደ ክብር ተጐናጽፈውት ሲሠለጥን፣ ራእዩ ገደል ገብቷል እንጂ የት አለ? ባለ ራእዩስ እንደ ሁኔታው ከተቀየረ ጽኑ ምስክርነቱ የት አለ? ገና ጨቅላዎቹስ ይህን የሳተ መንገድ ተከትለውት ለወደ ፊቱ እንዴት ያሉ ሆነው ያድጉ?!

ታዲያ እውነተኞች ሲጠፉ፣ ያሉትም ከማይመስል ጋር ሲመሳሰሉ ወደፊት የምድሯ ሁኔታ ምን ይመስል ይሆን?

ትዳር ዝብርቅርቁ ወጥቷል። ጥንቃቄና ማስተዋል የሚያስፈልገው ይኼ ዋና ነገር እንደ ቀላል ተቆጥሮ የስብከቱም ዓይነት ለዚሁ እንደሚያመች ሆኖ ቀርቧል። አግቢም ተጋቢም፣ መራጭ ተመራጭም በዓይነታቸው አልተገናኙም። ነገሩ እንደ መደብር ዕቃ የሚሸመት ሆኗል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የሚገርመው አገልጋዮች ተሳታፊ ሆነው መሰለፋቸው ነው።

ትዳር ለመጀመር ይሁን ሌላ “የእግዚአብሔር ፈቃድና ምሪት” የሚባለው በውሸት ትንቢት ተተክቶ የሩቅ ምሥራቅ ጠቢባንን የመራቸውን ልዩ ኮከብ ያህል ታምኖበታል። ውሎ አድሮ ግን ትዳሩም ትዳር ሳይሆን ቤቱም ጣራውም ተሸንቁሮ ዝናብ እንደሚያንጠባጥብ ያህል የማያቋርጥ አሳርና መከራ እያስከተለ፦ ክርስትና ይኼ ነው እንዴ? አሰኝቷል።

አንድ ባለ ታክሲ ተሳፋሪው ሲያስቸግረው፦ “ውረድልኝ … ባይበላ፣ ባይጠጣስ” እንዳለ ሁሉ፦ ባይገባስ? “የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፣ ጌታ ተናግሮናል” ባይባልስ? ይልቅ እንዲሁ ስለ ፈለግሁ በራሴ ወስኜ ገባሁበት ቢባል አይሻልም?

ውሸት የሆነ ነገር አይበጅም፤ አያዋጣም። ኋላ ነገሩ ዕርቃኑን መቅረቱ አይቀርም። ይታወቃል። ያኔ ቀና ብሎ መሄድ የለም፤ እፍረት ብቻ ነው።

ያ ባለ ራእይስ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው? ጌታው ሹመቱን ለሌላ ለታመነ ሰው ይሰጠዋል። ምን ጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር ጥቂቶች ይሁኑ እንጂ ፈቃዱን በታማኝነት የሚያገለግሉ አያጣም።

ላስተዋለው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክርስትና መልኩ ተለውጧል። አመጽ ከመብዛቱ የተነሳ ራእይ ሁሉ ደብዝዟል። እውነት በውሸት ኃይል ተሰልስላ ልትበጠስ የደረሰች ትመስላለች። ያልተመሳሰሉ ጥቂት እውነተኞች ቢኖሩም ድምጻቸውን አጥፍተው ግራ በመጋባት ጭጭ ብለዋል! እውነቱን ጮኽ ብሎ ለማሰማት የሚጥር የለም!!

ሌሎች አመጽን ለማጠናከር ሲሯሯጡና ሲያያዙ የብርሃን ልጆች ግን በርቀት ተበታትነው ቆመዋል። ይህን ሁሉ ውዥንብር ማን ያስቁም? ማንስ ይጠራ?

አንዲት በእግዚአብሔር ኃይል ወኔ የተዘጋጀች ወንጭፍና ጠጠር ድንጋይ ጠፋችን? ማንስ ይወርውራት? እውነትን የተረዳ የሚመስለው ሁሉ ልብ አጥቷል!! መጪው ዘመን የሚወልደው አንድ ኃያል ጀግና ብቅ ይል ይሆን?